ያዬ አበበ

የሦስተኛው ምጥ አዋላጅ ኢህአዴግ ይሳካለት ይሆን?

ኢትዮጵያ ምጥ ላይ ነች። ከዚህ በፊትም ሁለቴ አርግዛ አዋላጆቿ የሚያደርጉትን ስላላወቁ፤ እናት ብዙ ደም ፈሷት ከሞት አፋፍ ድናለች። የሦስተኛው ምጥ አዋላጅ ኢህአዴግ ይሳካለት ይሆን?

እንዴት እዚህ ደረስን?

በዘመናዊ ትምህርትና በምዕራባዊያንና ምስራቃዊያን ፍልስፍናና ርዕዮተ ዓለም የተቀረፀው የ1960ቹ ትውልድ፤ ኢትዮጵያን እንደሌሎቹ ሀገሮች የዳበረችና የበለፀገች ሀገር ለማድረግ ምኞቱና እምነቱ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ፤ የንጉሡም ዕድሜ 80ዎቹ ውስጥ ስለነበረ፣ ዓለምአቀፋዊ ኢኮኖሚያዊ ሂደቶች/የነዳጅ ዋጋ ስለናረና፣ ዓለምአቀፋዊ ሁለት ግዙፍ የፖለቲካ ጎራዎች ገዝፈው ከመውጣታቸው ጋር ተደምሮ፤ ኢትዮጵያን ከባህላዊ አስተዳደር ወደ ህዝባዊ አስተዳደር ተስፈንጥራ እንድትገባ የሚታገል አብዮታዊ ትግል ተጧጧፈ። አብዮትም ፈነዳ።

የተማሪው ንቅናቄ ያስተናገደውና ወደ ውስጡ ያሰረፀው የምስራቃውያን ርዕዮት ኢትዮጵያን ከኋላቀርነትና ድህነት ወደ ሥልጣኔና ብልፅግና ለማሸጋገር አቻ የሌለው አማራጭ ተደርጎ በወታደሩ፣ በተማሪውና በፖለቲካ ድርጅቶች ልሂቃን ውስጥ ቅቡልነት አገኘ። "ኢህአዴግ ዛሬ ለምን ከአገልግሎት አሰጣጥ ተሃድሶ ይልቅ ወደ ፖለቲካዊ ሥርዓት ተሃድሶ አይገባም?" ለሚለውም ጥያቄ ዋናው ምክንያቱ ርዕዮታለማዊ መሰረቱ ነው።

ኢህአዴግ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የሚሠራ ድርጅት ነው። በዚህ ሌኒናዊ አወቃቀር ውስጥ ውሳኔ ከማዕከላዊ ኮሚቴ ወደ ህዝብ ይፈሳል። ከህዝብ ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔም ተፅዕኖም አይፈስም። ኢህአዴግ ይሄንን ለምን መረጠ? በተማሪው ንቅናቄ ወቅት ለኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ 'የሚመጥን' ታሪካዊ፣ ማኅበረሰባዊና፣ ፖለቲካዊ ሂደት የተገኘው ከምስራቃዊያን ርዕዮተዓለም ስለነበረ ነው።

ዛሬ በኢህአዴግና በህዝብ መካከል ያለው ቅራኔ፤ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ከሚያይበትና ከበየነበት መንገድ የተነሳ ነው። ኢህአዴግ ኢትዮጵያ ከኋላቀርነትና ድህነት መውጣት ምትችለው በአንድ አውራ ፓርቲ አመራር ብቻ ነው ብሎ ያምናል። ይሄ እምነቱ በግልፅ የተሰመረበት ጉዳይ ነው። የሀገራችን ቅራኔ እምብርቱ ይሄ መሆኑን መገንዘቡ ኢህአዴግ የኃይል እርምጃን መንገድ ብቻ ለመምረጡ ዋናው ማብራሪያ ነው።

የተማሪው ንቅናቄ አመራር አባል የሆነ አንድ ሰው፤ 'በሚልየኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን መስዋዕት አድርገን ሀገራችንን ለመለወጥ ዝግጁ ነን' የሚል ነገር እንደነገራቸው አንድ አውሮፓዊ ፀሐፊ ጠቁመዋል። ያንን ያላቸው ሰው በ1960ዎቹ ነው። ዛሬም ኢህአዴግ ውስጥ ያንን አይነት ስሌት እንዳለ ከኢህአዴግ ተግባር ማየት ይቻላል። "ህዝብ ጎርፍ ነው፣ ወደ ቀየስክለት ይፈሳል" የሚል እምነት ያላቸው ሰዎች የሚመሩት ኢህአዴግ፣ ሀገሪቱን ወደ እርስበርስ ግጭት ይዟት እየነጎደ ነው።

ወዴት እየሄድን ነው?

በንጉሡም፣ በወታደራዊው መንግሥትም ውስጥ የሀገሪቱ አቅጣጫ ያሳሰባቸው ሰዎች፤ ሀገሪቱን ከአደጋ ለመታደግ ሞክረዋል። ከነ ገርማሜ ነዋይ አንስቶ እስከነ ጄኔራል ፋንታ በላይ ድረስ ለሀገሪቱ የተሻለ አማራጭ እንዳለ የተረዱ ሰዎች፤ ራሳቸውን ለድሃው ህዝብ ጥቅም ሲሉ አደጋ ውስጥ ጨምረዋል፣ ተሰውተዋል።

ዛሬም ሀገሪቱ ያለችበት አደጋ ሚታያቸው ሰዎች በኢህአዴግ ውስጥ አሉ ብሎ መገመት ይቻላል። ሀገሪቱን ከፅንፈኛ የግራ ርዕዮት ቁማራዊ ስሌት መታደግ ከሚችሉት ውስጥ አንዱ እነዚህ ሰዎች ናቸው። መሞከርም አለባቸው። ከውስጥ የሚነሳ ለውጥ ከሌለና የኃይል እርምጃው ከቀጠለ ግን ለየት ያሉ ሰዎች ተደማጭነታቸው በህዝቡ ውስጥ እየጨመረ ይመጣል። በተለይም የመንግሥትን የኃይል እርምጃ ለመቋቋምም ሆነ ለመግታትና ለማሸነፍ ተመጣጣኝ ብቻ ሳይሆን የጭካኔ ስልት መምረጥ የግድ ነው የሚለውን መስመር የሚከተሉ ታጋዮች በሀገሪቱ በሰፊው ይራባሉ።

በተለይም ተጠቃሚ ናቸው ተብለው በተመደቡ ብሔሮች ላይ ብሔር ተኮር ጭካኔ እየጨመረና የትግል ስኬት መለኪያና መስፈሪያም እየሆነ ይመጣል። በክልሎች ብቻ ሳይሆን በመዲናዋም ጭምር በሰፊው ግጭቱ ብሔር ተኮር ቅብ ይዞ ይስፋፋል። ይሄንን ክፍተት የሚያገኙ በሶማሌያና በኬንያ የሚገኙ አክራሪ ቡድኖች የራሳቸውን አጀንዳ ለማራመድ መንቀሳቀሳቸውም አይቀሬ ነው። አይ.ኤስ.ኤስም ጎራ ይል ይሆናል። በዚህ አጋጣሚም ሌሎች የጎረቤትና አካባቢያዊ ሀገራትም ፖለቲካዊ ስሌታቸውን ከጥቅማቸው አንፃር ያሰላሉ፣ ተፅዕኖ ማድረጋቸውንም በጣልቃገብነት በሰፊው ይያያዙታል።

እስከዛሬ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተነዛው አሉታዊ የብሔር ፕሮፓጋንዳ ፍሬ ሚያፈራውም በዚህ ወቅት ይሆናል። በተለይም በብሔር ላይ ያተኮረው 'የብሶት' ቁጣ ዱላም የሚያርፍበትን ሚያገኘውም በዚህ አጋጣሚ ነው። የኢህአዴግ አባላትና በተለይም የሥርዓቱ አራማጅ የሆኑ ግለሰቦችና ድርጅቶችን ማጥቃት የግጭቱ የሞራል ግዴታ ተደርጎ ይወሰዳል። ይሄንን አይነት 'ጀብድ' ሚፈፅሙትም 'ጀግኖች' ይሆናሉ።

ይሄ ሁሉ ግን ከኢህአዴግ የርዕዮት ወንፊት/filter የተነሳ ነው። ኢህአዴግ ከራሱ ሌላ ለሀገሪቱ የሚበጅ ሃሳብ የለም ብሎ ስለሚያምንና፣ ይሄንንም እምነቱን እስከ መጨረሻው ይዞ ለመግፋት ዝግጁ ስለሆነ ነው። ሀገሪቱ ከብሔር ጦርነትና ከባዕዳን ጣልቃገብነት በኋላ ምን አይነት ዕጣ ፈንታ እንደሚኖራት ለመገመት ሀገራዊ ተሞክሮ ስለሌለን ቢያዳግትም፤ ህዝባዊ አገዛዝ እንፈጥራለን ብሎ ማሰብ ግን የዋህነት ነው። ከድጡ ወደ ማጡ እንወርዳለን።

ኢህአዴግ እንዴት ጥሩ አዋላጅ ይሁን?

ኢህአዴግ ብቁ አዋላጅ ለመሆን ወደ ሽግግራዊ ድርድር (negotiated transition) ከማምራት ውጪ ሌላ አማራጭ የለውም። ሽግግራዊ ድርድር ማለት የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ማለት አይደለም። ሽግግራዊ ድርድር አሁን ካለንበት የአንድ ፓርቲ የበላይነት ወደ መድብለ ፓርቲ ሥርዓት ለመሸጋገር የሚያስፈልጉትን ቅድመ ሁኔታዎች የሚያመቻች ሂደት ነው። ሽግግራዊ ድርድሩ አዲስ የመንግሥት ሥርዓት ለመመስረት ሳይሆን፤ ያለውን ሕገመንግሥታዊ አወቃቀርና ፖለቲካዊ ሥርዓት ለማስተሳሰርና ወደ ሕገመንግሥታዊነት ሂደት ለመግባት ነው።

ሽግግራዊ ድርድር ለማድረግ ኢህአዴግ ቢያንስ የሚከተሉትን ማድረግ ይጠበቅበታል፦

1. ኢህአዴግ ራሱን ከአውራነት ወደ መደበኛ ፓርቲነት ደረጃ ለማውረድ መወሰን አለበት።

2. ኢህአዴግ በፓርቲና መንግሥት መካከል ልዩነት መኖር የለበትም የሚለውን አቋሙን መተው አለበት።

3. ሕጋዊ ፓርቲዎች በሀገር ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ የሚያቀጭጩና የሚያግዱ ሕጎቹን መሻር አለበት።

4. ለሽግግራዊ ድርድር ሕገመንግሥታዊ መሻሻል ለማድረግ የሚያስፈልጉ ነጥቦች ላይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር ፈቃደኛ መሆን አለበት።

5. ለሽግግራዊ ድርድር የሚያስፈልገውን የእርቅ ሂደት ለመጀመር በመንግሥታዊ የኃይል እርምጃዎች ላይ ያተኮረ የአደባባይ የምርመራ ጉባዔ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆን አለበት።

6. ለሽግግራዊ ድርድር በቅድሚያ በሀገር ውስጥ ካሉ ሕገመንግሥቱን ከሚቀበሉ ሕጋዊ ፓርቲዎች ጋር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ድርድር መጀመር አለበት።

7. ለሽግግራዊ ድርድር ሕጋዊ ተቃዋሚዎችን እንዲያገለግሉ የህዝብ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥንና ጋዜጦች በቋሚነት የአገልግሎት ጊዜ መደልደል አለበት።

8. ለሽግግራዊ ድርድር በኃይል እርምጃ ውሳኔና ትዕዛዝ ላይ ከተሳተፉ ከፍተኛ አመሮች ውስጥ ከትጥቅ ትግሉ ጊዜ ጀምሮ በኢህአዴግ ውስጥ ሲሳተፉ የነበሩ ግለሰቦች በሙሉ ከድርጅቱ በጡረታ ማሰናበት አለበት።

9. ከሽግግራዊ ድርድሮች በኋላ በአንድ ዓመት ውስጥ ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ለማደረግ ፈቃደኛ መሆን አለበት።

ሆኖም ዛሬ ኢህአዴግ ይሄን አይነት መንገድ ይከተላል ብሎ ማመን ግን አይቻልም።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ