የጠ/ሚ ኃይለማርያም የዘመቻ ትዕዛዝና የአምባገነኖች መመሳሰል
አክሊሉ ወንድአፈራው

የዛሬ አራት ዓመት የህወሓትና የኢህአዴግ የበላይ አዛዥና ናዛዥ አቶ መለስ ዜናዊ ሲያርፉ በቦታቸው የተተኩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ በትጥቅ ትግል ከተሳተፉት የህወሓት/ኢህአዴግ መሪዎች የተለየ ተመክሮ ያላቸው በመሆናቸው፤ ምናልባት የሀገሪቱን የፖቲካ አቅጣጫ ቀስበቀስ ከፍጹም ፈላጭ ቆራጭነትና ያአፍሪካ ቀንደኛ አፋኝ መንግሥታት ተራ አውጥተው ወደ የህዝብን መብት የማክበር አቅጣጫ ሊያመሩ ይችላሉ የሚል አስተሳሰብ በሰፊው ይሰማ ነበር። “ኢየሱስ ክርስቶስን የተቀበልኩ ክርስቲያን ነኝ” ብለው መናገራቸው ደግሞ፣ ከኃይማኖተቢሱ መለስ ዜናዊ የተሻለ ሰብዓዊ ርህራሄና ፈሪሃ እግዚአብሔር ያሳዩናል ብሎ የጠበቀው ብዙ ሰው ነበር።
የአራት ዓመት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሬከርዳቸው ግን ከአቶ መለስ ጥላ ስር ሊወጡ አለመቻላቻውን ብቻ ሳይሆን፤ እንዲያውም እየቆየ ተመሳሳይ ባህሪ እያንጸባረቁ መምጣታቸውን እያረጋገጡ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሚያና በአማራ የተለያዩ ክፍሎች የተነሳውን ህዝባዊ እመቢተኛነት ተከትሎ የሚያሳዩት ጭካኔ የተሞላበት አመራር ደግሞ ፈሪሃ እግዚአብሔር እንዳደረበት ሰው ሳይሆን፤ በሩቅም በቅርብም ከምናውቃቸውን አምባገነን መሪዎች እንደማይለዩ አሳይተውናል። ለግንዛቤ ያክል አንዳንድ ምሳሌዎችን ላንሳ።
የህዝብን ተቃውሞ የውጭ ጠላት ተቀጽላ አድርጎ የማየት አባዜ
ግብጽን ለ40 ዓመታት በፈላጭ ቆራጭነት የገዙት ሁስኒ ሙባረክም፣ በህዝቡ የነጻነት ፍላጎት የቀሰቀሰውን ተቃውሞ የውጭ ኃይል ፍላጎትን ለማሟላት የተደረገ ሙከራ አድርገው ነበር ያቀረቡት። የቱንዚያው አምባነነን መሪ ቤን አሊም ከሥልጣን ከመወገዳቸው ጥቂት ወራት በፊት ህዝብ በነቂስ አደባባይ ወጥቶ ያወግዛቸው በነበረ ጊዜ ባሰሙት ንግግር፤ የህዝቡን ተቃውሞ “በተባበሩት መንግሥታትና ሌሎችም ገለልተኛ መንግሥታት የተረጋገጠውን እድገታችንን ያበሳጫቸው ጥቂት ግለሰቦች፣ ለሀገራችን ክፉ የሚያስቡ ክፍሎች ያነሳሱት ኹከት” ብለው ነበር የገለጹት። (የቤን አሊን ንግግር ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)
አቶ ኃይለማርያምና ድርጅታቸውም እርሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ ወዲህም በተመሳሳይ መልከ ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል “ኢትዮጵያ የራሷ የተፈጥሮ ሀብት እንዳትጠቀም የሚሹ፣ እድገታችንን ለማደናቀፍ የፈለጉ ኃይሎች፣ የትምክተኞች፣ የጠባቦችና” የኤርትራ እጅ እንዳለበት አስመስለው ነው የሚነግሩን። በሺህዎች የሚቆጠር ህዝብ ተሰልፎ፤ የሻዕቢያ ቅጥረኛ የእርስዎ ድርጅት እንጂ የኛ እንቅስቃሴ አይደለም እያለ በይፋ ሲናገር እንኳ፤ ከዚህ ጭፍን አመለካከታቸው አቶ ኃይለማርያምም ሆኑ ህወሓት/ኢህአዴግም ሊወጡ አልቻሉም። ይህ ተግባር አቶ ኃይለማርያምንና ድርጅታቸውን ከሌሎች የታወቁ አምባገነኖች ጋር አንድ ያደርጋቸዋል። እዚህ ላይ ሻዕቢያ ችግር ከመፍጠር ወደ ኋላ ይላል ወይም ደግሞ ኢትዮጵያ የራሷን የተፈጥሮ ሀብት እንዳትጠቀም የሚሹ ሀገሮች የሉም ለማለት ሳይሆን፤ ያሁኑ የህዝብ ብሶት ህወሓት/ኢህአዴጎች እንደሚሉት የሻዕቢያ ተልዕኮ ውጤት ሳይሆን፤ የ25 ዓመታት የሥርዓቱ አሰቃቂ ግፍ የወለደው መሆኑን ለመቀበል ያለመቻልን አባዜ ነው የሚያሳየው። አቶ ኃይለማርያምና ራሳቸው ባንድ በኩል ሥርዓቱ “በስብሷል፣ የሕግ የበላይነት ጠፍቷል፤ መልካም አስተዳደር የሚባል ነገር በሀገሪቱ ውስጥ የለም” እያሉ እየተናገሩ፤ በሌላ በኩል የህዝብ ብሶት ምክንያቶች ሌሎችን አድርጎ ለማሳየት መሞከራቸው፤ እርሳቸውም ሆነ የሚወክሉት ሥርዓት የሚጓዝበትን የተምታታ መስመር የሚያመለክት ሲሆን፤ ሥርዓቱ ለህዝብ ጥያቄዎች አመርቂ መልስ ለመስጠት ብቃት እንደሌለውና ትልቁ ትኩረቱ የሥልጣን ጊዜን ማራዘም እንደሆነ ያሳያል።
የህዝብን መሰረታዊ ተቃውሞ ለማፈን ሰፊ ጭፍጨፋ ውስጥ መግባት
የህዝብ ተቃውሞ የተወሰነ ደረጃን ካለፈ በኋላ ወደነበረበት ለመመመለስ ለአምባገነኖች እጅግ ያዳግታል። ይህን ለማድረግ የሚጠቀሙት ባብዛኛው ከፍተኛ የኃይል እርምጃን ነው።
ሳዳም ሁሴን በ1980ዎቹ ከኩርድ እና ከሻአ ማኅበረሰቦች ከፍተኛ ተቃውሞና የህዝብ መነሳሳት ደርሶባቸው ነበር። በተለይም በኩርዲስታን ክፍለ ግዛት የተነሳው ተቃውሞ አይሎ የሀላብጃ (Hallabja) ከተማን ሲቆጣጠር፤ ሳዳምና መንግሥታቸው ቀደም ሲሉ ይጠቀሙበት የነበረው የትግል ማኮላሻ ታክቲክ ሁሉ እንደማይሰራ ተረዱ። ይህን ተቃውሞ ለማጥፋት የሀገሪቱን ሠራዊት ሁሉንም ኃይል ተጠቅሞ አካባቢውን ከተቃዋሚዎች እንዲያጸዳ በሰጡት ትዕዛዝ በማርች 16፣ 1988 በሮኬት፣ በታንክና በአይሮፕላን ተደግፎ ባካሄዱት ዘመቻ፤ በታሪክ ባስከፊነቱ ሲታሰብ የሚኖር ጭፍጨፋ ፈጽመዋል። በዚህ ዘመቻ በሀላብጃ (Hallabja) ነዋሪዎች ላይ የኬሚካል ቦንብ ጥለው ከ3ሺህ እስከ 5 ሺህ የሚገመቱ ኩርዶችን ወዲያውኑ ሲገድሉ፤ ከ7 እስከ 10 ሺህ የሚቆጠሩ ደግሞ አቁስለዋል። በቀጣዮቹ ዓመታትም ከዚሁ ጥቃት ጋር በተያያዘም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ሞተዋል። ያካባቢውን የህዝብ አመጽ ለጊዜውም ቢሆን ማፈን የቻሉት የዚህ አይነት መጠነ ሰፊ ግፍ ፈጽመው እንጂ፤ የህዝብን ብሶት አዳምጦ ፖለቲካዊ መፍትሔ በመፈለግ አልነበረም።
በሀገራችን ውስጥም አሁን ለተቀጣጠለው የህዝብ ተቃውሞና እምቢተኛነት፤ የሠለጠነ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በጉልበት ለማንበርከክ አቶ ኃይለማርያም በነሐሴ 24፣ 2008 መግለጫቸው እንዳሉት “ሁሉንም የጸጥታ ኃይሎች ሕግ እንዲያስከብሩ አዘዋል”። ይህ ማለት ታንከኛውንም፣ መድፈኛውንም፣ አየር ኃይሉንም ጨምሮ ማለት ነው። ይህንንም “ትዕዛዝ” ተከትሎ እጅግ ብዙ ሠራዊት፣ ታንክና ከባድ መሳሪያ ወደ ጎንደርና ጎጃም የተንቀሳቀሰ ሲሆን፣ በመላ ጎንደርና ጎጃም የብዙዎች ደም በመጉረፍ ላይ ነው።
ምርጫ 97ትን ተከትሎ አቶ መለስ በሰጡት ትዕዛዝ የተገደሉት ወገኖቻችን ወደ ሦስት መቶ እንደሚደርሱ ይገመታል። ዛሬ በ2008 ደግሞ በአቶ ኃይለማርያም ይፋ ትዕዛዝ ማግስት በጎንደር፣ በጎጃምና በሐረርጌ የተገደሉ ወገኖቻችን ቁጥር እጅግ ብዙ ነው፤ ትላንት ከትላንት ወዲያ በሶማሌና በጋምቤላ ወገኖቻችን ላይ እንደሆነው ሁሉ የዛሬው ጭፍጨፋ ሰለባዎች አሰቃቂ እውነታን በቪዲዮና በድምጽ ተቀርጾ ሁላችንም እንድናየው እየተደረገ ነው። ይህ ሁሉ ቀደም ሲል በኦሮሚያ ከተገደሉት ወደ አንድ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በተጨማሪ ነው።
አቶ ኃይለማርያምና ድርጅታቸው ኢህአዴግ/ህወሓት ይህን በዘር ላይ ያነጣጠረ የግድያ ትዕዛዛቸውን ሲያስተላልፉ ምን ያክል ሰው ለመግደል እንደተዘጋጁ፤ ከዚያም መቸ በቃ እንደሚሉ ባናውቅም፤ እስካሁን ባደረጉት ተግባር ግን እርሳቸውና ድርጅታቸው ሳዳም ሳዳምን እንደሚሸቱ ጎጃም ጎንደርና ኦሮምያንም ሀላብጃን እንዲመስሉ ለማድረግ መወሰናቸውን እየተመለከትን ነው።
ይህ ሁሉ የሥርዓቱን የችግር አፈታት ክህሎት ማነስ ብቻ ሳይሆን፤ በሥልጣን ላይ ለመቆየት ምን ያክል ግፍ ለመፈጸም እንደተዘጋጀና ሕጋዊም ሆነ የሞራል ብቃት እንደሌለው ያመለክታል።
ህዝብ ይወደኛል የሚል ቅዠት
የአምባገነን መሪዎች አንዱ ትልቅ ስህተታቸው በፍራቻና በትግስት አንገቱን ደፍቶ የሚኖርን ህዝብ ይወደኛል የሚል ትርጉም ሰጥተው፤ ራሳቸውንና ደጋፊዎቻቸውን ማታለላቸው ነው። ይህ ያምባገነኖች ባህሪ በተለያዩ ቦታዎች ተስተውሏል።
በአቶ ኃይለማርያም የሚመራው ህወሓት/ኢህአዴግ ለብቻው ተወዳድሮ 99.6% አሸነፍኩ ብሎ የፈጠረውን የራሱን ፖሮፓጋንዳ፤ እንደ እውነት ተቀብሎ እራሱንም ተከታዮችንም ሲያጭበረብር ቆይቷል። የሥርዓቱ ቁንጮዎች ባንድ በኩል ህዝቡ እጅግ ዘግናኝ በሆነ ሙስና የመብት ረገጣ፣ የሕግ ጥሰት ወዘተ እንደተሰቃየ እያመኑ ዘወር ብለው ደግሞ ህወሓት/ኢህአዴግ አሁንም ህዝብ “ያቀፈው መንግሥት” እንደሆነ ራሱን ያታልላል። በየቦታው የህዝቡን ልጆች የሚገድለው፣ ባደባባይ የሚረሽነው፣ ወዘተ ለራሱ ለህዝብ ነው በሚል ቅዠት ራሱን ያጭበረብራል። ንብረት የምነጥቀው፣ ከመኖሪያ የማፈናቅለውም ለራሱ ለህዝቡ ስል ነው ይላል።
በኦሮሚያ ለ10 ተከታታይ ወራት ሰፊ ተቃውሞ እየታየ፣ አቶ ኃይለማርያም የሚመራው ህወሓት/ኢህአዴግ ሰላም አስፍነናል ይላል። በመላው ጎንደርና ጎጃም የህዝብ እምቢተኛነት ተቀጣጥሎ፤ በጎንደር ብቻ 100 ሺህ ሰው የተቃዎሞ ሰልፍ ሲያካሂድ “ጥቂት” ትምክተኞች ብሎ ይነግረናል። ህወሓት/ኢህአዴግ ካንድ ሣምንት በፊት በአቶ ኃይለማርያም ሰብሳቢነት ባካሄደው ጉባዔ መጨረሻ ባወጣው መግለጫ ሳይቀር፤ አሁንም ህዝብ እንደሚደግፈው ይናገራል።
የሊቢያው መሐመድ ጋዳፊ፣ የግብጹ ሙባረክና ሌሎችም አምባገነኖች በሥልጣናቸው መጨረሻ ሰሞን ተመሳሳይ “ህዝቤ ይወደኛል” የሚል ቅዠት የተቀላቀለበት ንግግር ያሰሙ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ዛሬ ከህወሓት/ኢህአዴግ መሪዎች የምንሰማውም ተመሳሳይ የጣር ጩኸት ነው።
ይህ ሁሉ ሥርዓቱ የመግዛት አቅሙ እንደዛለ ብቻ ሳይሆን፤ በመሬት ላይ የሚገኘውን እውነታ ማገናዘብ የማይችልበት ሁኔታ ላይ እንደደረሰና ከዚህ በሁዋላ በሥልጣን ላይ መቆየቱም ለሀገር ደህንነት ታላቅ አደጋ እንደሆነ ያመላክታል።
የራሱን ጥላ የማያምነው ህወሓት/ኢህአዴግና ለእርድ የተዘጋጁት ባለሥልጣኖች
በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የሚመራው ህወሓት/ኢህአዴግ፣ ህዝቡንና ተቃዋሚውን ብቻ ሳይሆን በዙሪያው ያሉትን “አጋሮቹን” ሳይቀር በጥርጣሬ ማየትን ከጀመረና አላምናቸውም ካለ ውሎ አድሯል። ቀደም ሲል የኦህዴድን አሁን ደግሞ የብአዴንን መሪዎችና አባላት በየቀኑ በአሳፋሪ ክስ በአደባባይ ሲወነጅላቸው፣ (ኪራይ ሰብሳቢ፣ ጠባብ፣ ትምክተኛ ወዘተ ሲሏቸው)፤ “ራሳችሁን አጋልጡ” እያለ ሲያስፈራራቸው፣ ሲያዋርዳቸው ወዘተ በሰፊው ይታያል።
የሰሜን ኮርያ አምባገነኖች እና ሟቹ ሳዳም ሁሴን በተደጋጋሚ እንዳሳዩት ህወሓት/ኢህአዴግም በተደጋጋሚ እንዳደረገው ሁሉ፤ አሁንም በአዲስ መልክ አጋሮቹን ተራ በተራ አኝኮ ለመትፋት ተዘጋጅቷል። እንደ ተራ እቃ ተጠቅሞባቸው ሊወረውራቸው እንደሚፈልግ በግልጥ እየተናገረ ነው። ይህንን እያወቁ ለእርድ ወደቄራ እንደሚሄድ በሬ ዓይናቸውን አፍጥጠው ይጠብቃሉዓ ወይንስ አማራጫቸውን በጊዜ ይፈትሻሉ የሚለው የሚታይ ይሆናል። ነገሩ ልብ ያለው ልብ ይበል እንደሚባለው ነው።
ማጠቃለያ
አንዳንዶች ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን ከጀርባ ሆነው የሚያሽከረክሯቸው የህወሓት ሰዎች ናቸው፣ ስለዚህ እርሳቸው ምን ያድርጉ? የሚል መሟገቻ ያቀርባሉ። በርግጥ አቶ ኃይለማርያም የተቀላቀሉት ቡድን እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ባንድ ወቅተ “እኔ ምንአባቴ ላድርግ ብላችሁ ነው” ሲሉ መደመጣቸው ይታወሳል። ሆኖም ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዕድሜም በትምህርትም የገፉና ብዙ ዓለም አቀፍ መሪዎችንም አግኝተው የተመካከሩ፣ እጅግ ብዙ ግንኙነት ያላቸው ግለሰብ ናቸው። ስለሆነም በማያምኑበት ተግባር ላይ (ያውም በጭካኔ ተግባር) ሊሳተፉ የሚያስገድዳቸው ምንም ጉዳይ የለም። ሥልጣኑ አጓጉቷቸው ካልሆነ በስተቀር፤ የማይመስላቸውን ያውም ህዝብ ላይ ሠራዊት ማዝመትና ጭፍጨፋ መፈጸምን የመሰለ ታላቅ ጭካኔ የተሞላበት ውሳኔ ተቀብለው ማስተጋባትና ተግባራዊ ማድረግ በምንም ሰበብ ቢሆን ተቀባይነት የለውም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ሌሎች ባለሥልጣኖች እምቢ ስለማለት ደግሞ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ከዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ሊማሩ ይገባል። አቶ መለስ የአምባገነን ባህሪያቸው እጅግ እያየለ ሲሄድ ነበር ዶክተር ነጋሶ፤ “ምነው ደርግ ደርግ ሸተቱኝ” ብለው በትክክል የሚሰማቸውን የነገሯቸው። በርግጥ ዶክተር ነጋሶ ያንን ተከትሎ ከሥልጣናቸው ተባረዋል፤ ከሀገር ፕሬዝዳንትነት ተነስተው ተራ ሰው ሆነዋል። ሆኖም ግን ንጹህ አዕምሮ፣ መልካም ሰብዕናና ጽኑ መንፈስ እንዳላቸው ህዝብም መስክሮላቸዋል። በርግጥ ከቤተመንግሥት ተወግደዋል። በህዝብ ልብ ውስጥ ግን ታላቅ ቦታን ይዘዋል። ዶክተር ነጋሶና ቤተሰቦቻቸው ዛሬ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል አንገታቸውን ቀና አድርገው፣ እርስዎ ተብለው እንደተከበሩ መንቀሳቀስ ይችላሉ። በሚሄዱበት ቦታ ሁሉ ጥላቸውን አይፈሩም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምም፣ የተቀመጡበት ወንበርና፣ ከሥልጣን ጋር የሚመጣው ኃላፊነት ምን ያክል ከባድ እንደሆነ በመገንዘብ ለሀገር፣ ለህዝብና ለራሳቸው ታሪክ የሚሆነውን በጊዜ ሊያደርጉ እንደሚገባ መናገር ድፍረት አይሆንብኝም። አሁን በይፋ የሚታየው ድርጊታቸው ግን ለራሳቸው አዕምሮም ሆነ ለታሪካቸው፣ ለሀገርም ሆነ ለህዝብ በፍጹም አይበጅም። በይፋ የሚታየው ተግባራቸው የሚያመለክተው ለውጥ አጋችነትን እንጂ ለውጥ ፈላጊነትን አይደለም። የሀገሬ ሰው ሲከፋው እንደሚለው፣ ወይ ውረድ ውይ ፍረድ።
አክሊሉ ወንድአፈራው
ነሀሴ 30፣ 2008 (ሴፕተምበር 5፣ 2016)



