አንዱዓለም ተፈራ

Irrecha protest, 2nd Oct 2016

የሃሳብ ልዩነት፤ ያለ ነገር ብቻ ሳይሆን፤ አስፈላጊም ነው። የተለያዩ ሃሳቦች መከሰት፤ አማራጮችን በመድረክ ላይ በማቅረብ፤ ልዩነቶችን እንድንመረምርና፤ በብዙኀኑ ዓይን የተሻለ የተባለውን እንድንመርጥ ዕድል ይፈጥርልናል። ከነዚህ የተለያዩ ሃሳቦች ተነስቶ ርስ በርስ መወነጃጀሉ፤ አንድም እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን ባይነት ብሎም ራስን የማግዘፍ ጥንውት ነው። ሌላም ትግሉ መልክ ይዞ ወደፊት እንዳይሄድ እንቅፋት ለመሆን የተጠነሰሰ ሴራ ነው።

አክራሪዎች መኖራቸውንና የትግላችን አንዱ ገፅታ መሆኑን መቀበል አለብን። ይህ በቀኝ ይሁን በግራ፣ በፊት ይሁን በኋላ፣ ፈለግነውም ጠላነውም፤ ያለ ሐቅ ነው። ይህ የትግል አቅጣጫችን ሊቀይር ቀርቶ፤ ትኩረታችንን ሊስብ አይገባውም። የሀገራችን የፖለቲካ እውነታ፤ ያደግንበትም ሆነ አሁን ያለው ተጨባጭ ሐቅ፤ መፈናፈኛ በማሳጣቱ፤ አክራሪዎች መፈጠራቸው፤ ሁኔታው የወለደው ክስተት ነው። እናም አክራሪ የምንላቸውን ለማጥቃት ወይንም ለማጥፋት ዓይኖቻችንን ከዋናው ግባችን መንቀል፤ ለራሳችን ጥቃት በሩን ለጠላት በርግደን መክፈታችን ነው። ትኩረታችን መሆን ያለበት ሰፊው ህዝብ የሥልጣኑ ባለቤት የሚሆንበትን በመፈለግና ያን በመቀበል ላይ ነው። ብዙኀኑ የተቀበሉት ለስኬት እንዲበቃ፤ ጥረታችንን በሙሉ በዚያ ላይ ማረባረብ አለብን። በግራና በቀኝ ተፋሰሶች እያበጀን፤ ጉልበታችንን እኛው ራሳችን አናዳክም።

“አስቀድሞ መግደል አሾክሿኪውን ነው!” ብለው ቀደምቶቻችን ሲያስተምሩን፤ አሾክሿኪው የጠላት አንድ አካል መሆኑን፤ እነሱም ሆኑ ራሱ አሾክሿኪው ስለሚያምኑበትና ስለሚቀበሉት ነው። በተጨማሪም፤ እጅ ከፍንጅ መረጃው ስለተያዘ ነው። እኛ የያዝነው ግን፤ “እኔ የምለውን ያልተቀበለ፤ ‘ወያኔ’ ነው!” የሚል ጠባብ፣ ራስ ተኮር፣ እኔ ብቻ ነኝ አዋቂ ባይነትና ከሀገር በላይ ግለሰብን ወይንም የራስ ድርጅትን የሚያስቀምጥ አባዜ ነው።

ባሁኗ ሰዓት፤ በፖለቲካ ትግሉ መስክ፤ ባንድ በኩል የሀገር አንድነትን ፈላጊዎች፤ “ሀገር አቀፍ ትግል እንጂ ሌላ ምን ሲባል!” የሚል ምሽግ ሠርተናል። በሌላ በኩል ደግሞ በሀገር ውስጥ ባለው የፖለቲካ እውነታ በመመርኮዝ፤ “የለም፤ የአማራ ወጣቶችና የኦሮሞ ወጣቶች የትግሉን የበላይነት ጨብጠውታል። እናም ያን ሐቅ ተቀብለን፤ እኒህ ክፍሎች የሚቀራረቡበትንና የሚተባበሩበትን በመፈለግ፤ የወደፊቷን ኢትዮጵያ እንመሠርታታለን!” ባዮች አንድ ምሽግ ሠርተናል። ለኒህ ሁለቱ የትግል መስመሮች ጠላታችንም ግባችንም አንድ ነው። መንገዳችን ግን የተለያየ ነው። በርግጥ የትኛው የተሻለ ይሆናል የሚለውን፤ ሁለቱ ክፍሎች ቀርበን ለመነጋገር፤ አሁን ትልቅ ችግር ላይ ነን። የዜሮ ድምር ፖለቲከኞች፤ “ሌላው መታሰብ እንኳን የሌለበት ነው!” የሚል አቋም ያራምዳሉ። እንዲያውም ሁለቱም ክፍሎች በየጎራችን ጎድበን፤ አንዳችን ሌላችንን፤ ከወራሪው ፀረ-ኢትዮጵያ የትግሬዎች ቡድን የበለጠ ጠላት አድርገን በመፈረጅ፤ ለመጠፋፋት ተነስተናል።

እንግዲህ ሐቁ እንዲህ ነው። አስታራቂ ሽማግሌ ከየትም አይመጣም። እውነት የህዝቡን ድል ፈላጊዎች ከሆንን፤ ከባህላዊ ዘፈናችን አንድ ስንኝ ልዋስና፤ “አስታራቂም የለን፤ እኛው እንታረቅ”። የርስ በርሳችን መወነጃጀልና ጉልበታችን ለዚሁ ማጥፋት ማንን እንደሚረዳ፤ እኔ ለናንተ አልነግርም። አስቸጋሪ የሆነው ደግሞ፤ ይህ የታጋዮች በሁለት ጎራ መመሸግ፤ እየተከሰተ ያለው በቀጥታ ሳይሆን፤ በተዘዋዋሪና ትግሉን በቀጥታ በሚጎዳ መልክ ነው። መድረካችን በሳል የትግል ነጥቦችን በርጋታ የምንነጋገርበት ህዝባዊ ስብስብ ሳይሆን፤ ፓልቶክና ፌስቡክ፣ ትዊተርና የየግል የሬዲዮ ስርጭት መስመሮች ሆኗል። በመጀመሪያ ደረጃ፤ የፖለቲካ ልዩነት መግለጫና መነታረኪያ ባህላችን፤ ስድብ ማሽጎድጎድ ሆኗል። ብዙ በመሳደብ፤ የአቸናፊነት ሽልማት ለመቀበል መስገብገብ ይታያል። “ወያኔ!” ብሎ አንዱ ሌላውን አስቀድሞ ስለወነጀለ፤ ወንጃዩ የህዝብ ወገን፤ ታርጋው የተለጠፈበት ደግሞ የጠላት ወገን የሆነ ይመስለዋል። አጉል ቅዠት ነው። ስድብ ስለቆሸሸው የሰዳቢ አፍ ይናገራል እንጂ፤ የተሰዳቢውን ማንነት አይገልጽም። ይህ መጥፎ ባህል ነው። ይቅርብን።

አንዱ የመነጋገርያ ነጥብ የአማራውን መደራጀት የሚመለከት ነው። አማራው መደራጀት አለበት ብለው ያመኑና በዚሁ እምነታቸው የገፉ አሉ። ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታትና አሁንም በአማራው ላይ እየደረሰበት ያለውን የዘር ማጽዳት ወንጀል በመንተራስና፤ የትግሬዎችን ቡድን የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያ መረጃ በመያዝ፤ አማራው በሕልውና እንዲኖር፤ ተደራጅቶ መታገል አለበት! የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። በሌላ በኩል ደግሞ አማራው መደራጀት የለበትም በማለት፤ “ትግሉ መካሄድ ያለበት በኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው!” የሚለውን ሃሳብ ሙጥኝ ብለው የተጣበቁ አሉ። በጄ! ይህን በተለያየ መልኩ ማየት ይቻላል። ነገር ግን፤ አንዱ ወገን የሌላውን ወገን ከመስማት ይልቅ፤ በራስ ጭንቅላት የፈጠሩትን ደጋፊ ወይንም ነቃፊ ነጥብ በማብጠልጠል፤ ከራስ ጋር ሙግት የተያዘበት ሐቅ ነግሷል። የሌላውን ነጥብ ማዳመጡ ቦታ አልተሰጠውም።

አማራው ያለበት የዘር ማጽዳት እውነታ ለመቀየር፤ ማንኛውንም በማድረግ ሕልውናውን መጠበቅ እንዳለበት መረዳት ያስፈልጋል። ይህን እረዳለሁ ብሎ የተነሳን ደግሞ፤ ማንም ቢሆን ማን ሊያቆመው፣ ሊከለክለው ወይንም ሊቃወመው አይገባም። መቃወም ማለት በአማራው ላይ መዝመት ማለት ነው። ለዚህ ክፍል፤ ኢትዮጵያን ከማሰብ በፊት፤ አማራው መዳን አለበት። ይህ አከራካሪ የመሆኑን አጥር ዘሏል። ስለዚህ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ መሄዱ አስፈላጊ አይደለም። ይልቁንስ ለመረዳት መጣሩ ተገቢ ነው። ኢትዮጵያ እንዴት ትድናለች የሚለው ጥያቄ ያንገበገባቸው ሰዎች፤ ታጋዮችንና በሀገሪቱ ያለውን ሐቅ፤ የምርምራቸው መነሻ ማድረግ ይገባቸዋል።

ሁለተኛው መነጋገሪያ ነጥብ፤ ኢሳትን የተመለከተ ነው። ኢሳት የራሱ ግብ ያለው የግል ተቋም ነው። ባለቤት አለው። ኢሳት የኢትዮጵያ ህዝብ ንብረት አይደለም። ውሎ አድሮ ለንግድ የተዘጋጀ ተቋም ነው። ስለዚህ ባለቤቱ የሚያዝበት እንጂ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያዝበት ተቋም አይደለም። ይህን ማለት፤ ኢሳት መጥፎ ነው ማለት አይደለም። ነገር ግን፤ ማንም ተነስቶ ይሄን ካላደረገ ወይንም ያንን ካላደረገ የሚልበት አለመሆኑን ለማስጨበጥ ነው። ማንም ግለሰብ ይህን የግል ተቋም፤ በግሉ ሊረዳ ይችላል። ማንም ግለሰብ ደግሞ፤ በግሉ ይሄን የግል ተቋም ላይረዳ ይችላል። ነገር ግን ማንም ግለሰብ፤ ከባለቤቱ በስተቀር፤ ሊያዝበት አይችልም። ይህ መታወቅ አለበት። እናም ይሄን ይዘን፤ የግሉን ተቋም ለምን ይሄን አላደረገም ብሎ መወንጀል፤ ተገቢ አይደለም። ይህ በታጋዮች መካከል ለመጣላት ምክንያት ሊሆን አይገባውም። የኢትዮጵያዊያን ንብረት ቢሆን ኖሮ፤ ለምን እንዲህ ወይንም ለምን እንዲያ አላደረገም ብለን መናገር መብታችን ይሆን ነበር። አሁን ግን መብታችን አይደለም። ከወደድን እንደግፈው፤ ካልወደድንም ደግሞ እንተወው። በቃ።

ሦስተኛው መነጋገሪያ ነጥብ ደግሞ፤ ትግሬዎችን የተመለከተ ነው። ባሁኑ ሰዓት፤ በሀገራችን ላለው የግፍና የስቃይ ውርጅብኝ፤ ተጠያቂው ወራሪው የትግሬዎች ቡድን ነው። ይህ ወራሪ ቡድን፤ በምንም መንገድ ይሁን በምንም፤ ትግሬዎችን ወክያለሁ ብሎ፤ በኢትዮጵያዊያን ላይ ግራና ቀኝ ጥፋት፤ በተለይም ደግሞ በአማራው ላይ የዘር ማጽዳት ወንጀል እየፈጸመ ነው። ይህን የሚፈጽመው፤ በአብዛኛው ትግሬዎችን በመሣሪያነት ይዞ ነው። በርግጥ ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የሆኑ አንዳንድ ሆድ አደሮች፤ በግለሰብ ደረጃ፤ በባንዳነት እየረዱት ናቸው። እኒህ ሆድ አደሮች ይሄንን በሚያደርጉበት ሰዓት፤ ሕልውናቸውን ሸጠው፤ የዚሁ የወራሪው የትግሬዎች ቡድን አካልና አምሳል ሆነው ነው። እናም እነሱ ትግሬዎችም ባይሆኑ፤ የዚህ የወራሪው የትግሬዎች ቡድን አካል ናቸው። ስለዚህ ይህን ቡድን በምንም መልኩ ብናየው የትግሬዎች ቡድን ነው። አማራውን ለማጥፋት የተነሳው ይህ የወራሪው የትግሬዎች ስብስብ ነው። ኦሮሞዎችን እየገደለ ያለው ይህ የወራሪው የትግሬዎች ቡድን ነው። አኝዋኮቹን የጨፈጨፈው ይህ የወራሪው የትግሬዎች ቡድን ነው። ኦጋዴኖቹን የበደለው ይህ የወራሪው የትግሬዎች ቡድን ነው። እና ገና ለገና ትግሬዎች ይበደሉ ይሆናል በማለት፤ በውጪ ሀገር ያሉ “ታጋይ ነን!” ባይ ትግሬዎች፤ ጥብቅና ከትግሬው ቡድን ጋር አብረው ተሰልፈዋል። አልሸሹም ዞር አሉ ነው። ጠላት የማብዛትና የማሳነስ ስልት አይደለም። አሁንም፤ ዛሬ የዘር ማጽዳት ወንጀል እየተፈጸመበት ላለው አማራና ዛሬ ለሚያልቀው የኦሮሞ ወጣት ከመቆም ይልቅ፤ ገና ለገና በትግሬዎች ንብረት ላይ ጉዳት ይደርስ ይሆናል ብሎ የሚጮኽ፤ በምንም መለኪያ ቢታይ፤ የወራሪው የትግሬዎች አጥፊ ቡድን አካል እንጂ፤ የህዝብ ወገን አይደለም። ጠላቱንና የትግል መስመሩን ለይቶ ያልተነሳ ታጋይ፤ የያዘውን ትግል አያውቀውም፤ ድሉም ምን እንደሆነ ስለማያወቅ፤ ለድል አይበቃም።

የያዝነው የምኞትና የፍላጎት ትግል አይደለም። በቦታው ያለውን ሐቅ ተቀብሎ፤ ያን ለማስተካከል የሚደረግ ትግል ነው። ወራሪው የትግሬዎች ፀረ-ኢትዮጵያዊያን ቡድን የሚታረቅ፤ የሚሻሻል፤ የሚታረም አይደለም። መሠረታዊ እምነቱ ኢትዮጵያዊነት አይደለምና! ከዚህ ቡድን ጋር እርቅ ለማድረግ የሚፈልጉና “ብዙ ሰው እንዳያልቅ!” እያሉ የሚያላዝኑ ሰዎች፤ ጎራቸው ከዚሁ ወራሪ ቡድን ጋር ይቀራረባል። ይህ ወራሪ ቡድን፤ ከትግራይ ውጪ ለሚያልቀው ወገን ደንታ የለውም። እየገፋበትም ነው። ይህን ቡድን በምንም መልኩ ለማዳን መሞከር፤ የዚሁ ቡድን ደጋፊነት ነው። አጥሩ ግልጽ ነው። ይልቅስ በታጋዩ ወገን ያለውን እናስተካክል። ለወራሪው ቡድን አሳቢዎች ብዙ አሉ። እኛ ለሱ መጨነቁን እንተወው። በአንድነት መታገሉን እስከወደድን ድረስ፤ ወደ አንድነት የሚወስደውን መንገድ እንከተል። በታጋዩ ጎራ ያለን ሁሉ፤ ወደ አንድ ለመምጣት ያለው በር አንድ ነው። ተቀራርቦ መነጋገር። እንዴት ወይንም መቼ ወይንም የት የሚለው፤ በሁለተኛ ደረጃ የሚከተል ነው። መጀመሪያ የአንድነቱን አስፈላጊነት መቀበል ነው። ይሄን ደግሞ ያልለፈለፈለት የለም። ታዲያ ቀጥሎ መገናኘት ነው። ለዚህ ጠሪው ብዙ አድማጩ ዜሮ ለሆነበት ትንግርት፤ እግሬን አስቀድሜ አነሳለሁ። እናም ውይይቱ ትናንት መሆን ቢኖርበትም፤ ትግሉ እየተካሄደም፤ ዛሬ ይቀጥል።

አንዱዓለም ተፈራ - የእስከመቼ አዘጋጅ
ሰኞ፤ መስከረም ፳፫ ቀን ፳፻፱ ዓመተ ምህረት

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ