ህወሓት የማይወድቅባቸው የትግል ሥልቶች
ነፃነት ዘለቀ
ባሳለፍነው እሁድ በደብረ ዘይት የኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ በአጋዚ የወያኔ ቅልብ ጦር ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖቻችንን ነፍስ እግዚአብሔር ይማርልን! ከዚህች ዘግናኝ ቀን በፊትም ሆነ በኋላ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በዚሁ የወያኔ ጦር ያለቁና ወደፊትም የሚያልቁ ወንድም እህቶቻችንንና ልጆቻችንን መንግሥተ ሰማይን ያውርስልን። ፈጣሪ የነሱን መስዋዕትነት እንደአቤል ንጹሕ ደም ቆጥሮልን የነፃነታችንን ቀን ያፋጥንልን። የቤተሰባቸውንም ሆነ የሁላችንን የተሰበረ ልብ ይጠግን። አሁንስ እጅግ በጣም እየተጎዳን ነው።
ወያኔ የማይወድቅባቸው አስር የትግል ሥልቶች
ወያኔ በምን እንደማይወድቅ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይ ቁልጭ ብሎ እየታየ ነው።
1. በምንም ዓይነት መንገድ ወያኔ በጩኸት አይወድቅም። እርግጥ ነው ሰሚ ከተገኘ ጩኸት ብሶትንና ግፍን ለመግለጽ ይጠቅማል። በኛ የእስካሁኑ ሁኔታ ግን ሰሚ የለንምና ጩኸታችን አልጠቀመንም። ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተሰማራው ኃይል ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው በመሆኑ “ዐውቆ የተደበቀ ቢጠሩት አይሰማም” እንዲሉ ሆኖ ለማንም ብንጮኽ ሰሚ አናገኝምና ትርፉ ድካምና ጩኸትን በከንቱ ማባከን ነው። የኛ ደም ውኃ ይመስል በየቀኑ እንደጎርፍ እየፈሰሰ በዋና ዋና የሚዲያ አካላት በስፋትና በጥልቀት የማይዘገብበት ምክንያት ሌላ ሣይሆን ጥፋትና ውድመታችን የታዘዘው ዓለምን ከተቆጣጠረው ዋናው የአጋንንት ኃይል በመሆኑ ነው። እንጂ አንድ የስዊድን ወይም የእንግሊዝ ዜጋ የወያኔ ወንድሞች ማለትም አይሲሶች ቢገድሉት ኖሮ የሣምንታት የዜና መክፈቻቸው በሆነ ነበር። እነዚህ ጉደኞች ከአምስት መቶ ህዝብ በላይ በጠራራ ፀሐይ የታጨደበትን አሳዛኝ ዕልቂት በመኪና ተገጭቶ የሞተ አንድ የአውሮፓ ውሻ ያህል እንኳን አልቆጠሩትም። ለይስሙላ ግን “In God we trust.” እያሉ በፈጣሪ ኅልውና ሲያላግጡ አያፍሩም፤ የሥራቸውን ይስጣቸው እንጂ ምን ይባላል። ለነገሩ ከሞላ ጎደል ሁሉም የዘሩትን እያጨዱ ነው፤ ወደፊትም ይህ የፈጣሪ ፍርድ በነሱም ላይ አይቀርም። ማንም የሥራውን ያገኛል።
2. በምንም መንገድ በሰላማዊ ሰልፍ ወያኔ አይወድቅም። ሰላማዊ ሰልፍ ጊዜ ማባከኛ ነው። 25 ዓመት ተሰልፈን ያመጣነው ለውጥ የለም። “ደግሞ ጀመራቸው!” ከማስባልና እንደክፉ ዐመል የተተከለን ጠባይ ከማሳየት ውጪ ምንም አልፈየደም። ሰልፍ የሚሠራበት ሀገር አለ፤ ለኛ ግን አይሠራም።
3. በምንም መንገድ ህወሓት በድርድር አይወድቅም። ወያኔ ዘንድ ሰጥቶ መቀበል ብሎ ነገር የለም። የወያኔ ጠባይ ጨርሶ ማጣት ወይም ጠቅልሎ መውሰድ እንጂ የቁጥ ቁጥ ነገር አይዋጥላቸውም። አንድም የህዝብ ጥያቄ በአወንታ መልሰው የማያውቁት ጥያቄን በአግባብ መመለስን እንደመሸነፍ ስለሚቆጥሩት ነው። ለምሣሌ ሁለትና ሁለት ሲደመር ስንት እንደሚሆን ወያኔዎችን ብትጠይቋቸው ሦስት ወይም አምስት ይሉ ይሆናል እንጂ፤ እቅጩን “አራት ነው” አይሉም። ምክንያቱም በትክክል መመለስ ጠያቂን እንደሚያስደስት ስለሚያምኑና ያንንም ለነሱ እንደሽንፈት ስለሚቆጥሩት ነገረ ሥራቸው ሁሉ ጠማማ ነው። ይህ ጠባያቸው የሚያሳየን አዕምሯቸው ያልሠለጠነና በዕድገቱ ከእንስሳትም በታች መሆኑን ነው። ስለሆነም ከወያኔ ጋር ተደራድሬ ሀገሬን ነፃ አወጣለሁ የሚል አካል ቢኖር ራሱም ያበደ ነው። ወይም ወያኔ ጊዜ ገዝቶ ከጭንቀቱ እስኪገላገልና አንዳች ዘዴ ፈልጎ እስኪያጠፋው በመሣሪያነት ሊያገለግል የወደደ ጊዜያዊ የሥልጣን ፍርፋሪ የሚፈልግ መሆን አለበት። እርግጥ ነው ወያኔ በጣም ሲጨነቅ ከነልደቱ አያሌውና ከነፕሮፌሠር በየነ ጴጥሮስ ጋር ሊደራደር ይችል ይሆናል። እነዚህ ወገኖች በሥልጣን አራራ የሚታሙና የሚወቀሱም በመሆናቸው ለወያኔ የተወሰነ እፎይታ ለመስጠት በመናጆነት ሊያገለግሉ ቢሞክሩ አይገርምም - ጊዜና ዕድል ከገጠማቸው ሊያውም።
4. በምንም መንገድ ወያኔ በምርጫ አይወድቅም። ይህ ሳይታለም የተፈታ ነው። ምርጫን በግልጽና በማንአለብኝነት በማጭበርበርና ኮረጆን በመገልበጥ የሚታወቁትን ወያኔዎችን በምርጫ አሸንፌ ሥልጣን እረከባለሁ ማለት ከጅብ መንጋጋ ሥጋ ለመቀማት እንደመሞከር ያለ ቂልነት ነው። በፍጹም አይታሰብም።
5. በምንም መንገድ በምዕራባውያን ተፅዕኖ አይወድቅም። ሞልቃቃ ልጃቸው ስለሆነ በጠራራ ፀሐይ ሚሊዮኖችን ቢጨፈጭፍና የዘር ማጥፋት ወንጀል ቢፈጽምም፤ በሞራል ከማበረታታትና የገንዘብ ድጋፍ ከመለገስ በስተቀር ፊቱን የሚያዞርበት አንድም ምዕራባዊ ሀገር የለም። ምክንያቱም ከፍ ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው የኢትዮጵያ ጥፋትና ውድመት የተቀነባበረው በነዚህ ልዝብ ሰይጣናት የምዕራቡ ዓለም የደኅንነት ተቋማትና በዐረቦችም ጭምር የወልና የተናጠል ድጋፍ ነውና።
6. በምንም መንገድ እዚያና እዚህ በሚደረግ ያልተቀናጀ ህዝባዊ እምቢተኝነት ወያኔ አይወድቅም። በዘርና በጎሣ እንዲሁም በኃይማኖት በተከፋፈለ ህዝባዊ አመጽ ወይም የእምቢተኝነት ንቅናቄ ወያኔ ይወድቃል ማለት ዘበት ነው። ይህ ዓይነቱ ነገር ለወያኔ ሥራ ያበዛበት እንደሆነ እንጂ፤ የመቆያ ሥልቶችን እንዲያሰላስል ዕድል ይሰጠው እንደሆነ እንጂ፤ ትንሽ እንዲጨነቅ ያስገድደው እንደሆነ እንጂ ከአራት ኪሎ አያስወጣውም። እንዲህ ዓይነቱ የተነጣጠለ ትግል ለአደጋና ዕልቂት የሚጋብዝ እንጂ ውጤት የለውም።
7. በምንም መንገድ በጋዜጣዊ መግለጫና በፉከራ አይወድቅም። ወያኔዎች ምሥጥ ናቸው። ዕድሜ ለተላላኪዎቻቸው፤ የትም ሆነህ ብትቃወማቸው ክንዳቸው ረጂም ነው፤ ባለኽበት ይመጡልሃል። አንተን የመሰለ ሰው አስርገው ይልኩብሃል። እናም እንኳንስ በጋዜጣዊ መግለጫና በፖለቲካዊ ጫጫታ ይቅርና በተደራጀ ጦርም እነሱን ማሸነፍ አስቸጋሪ ነው፤ ጨርሶ አይቻልም እያልኩ ግን አይደለም። ገንዘባቸው፣ ስለላቸው፣ በአባቶቻቸው የሚደረግላቸው የመረጃና የበጀት ድጋፍ፣ በጥቅም በዘርና በቋንቋ ሰውን መከፋፈላቸው፣ እኛን የሚመስለው የሰውነትና የቋንቋ እንዲሁም ሌላው ቅርጻቸው የኛን ትግል እጅግ ከባድና ውስብስብ ያደርገዋል። በዚያ ላይ ብዙ ተቃዋሚዎቻቸው ወያኔዎችን ይንቃሉ። እንደውነቱ ከሆነ በዋናነት ወያኔን የጠቀመው የነሱ ሸረኝነትና የኛ እነሱን መናቅ ነው። እነሱ እያደቡ ዕቅዳችንን ሁሉ ሲያከሽፉ እኛ ደግሞ ስንፎክርና በመግለጫ “ድባቅ ስንመታቸው”፤ ይሄውና ሩብ ምዕተ ዓመት ዘለቅን - ሁነኛ የማስወገጃ ሥልቱን በቶሎ ካልነቃንበት ደግሞ ምዕተ ዓመቱን ይደፍናሉ። አሁን አሁን ግን ህዝቡ ቀደመና መቆሚያ መቀመጫ እያሳጣቸው ይገኛል። የነሱ ተንኮል ማርከሻ ይህ ዓይነቱ መነሻው እንጂ መድረሻው በውል የማይታወቅ ህዝባዊ ቁጣ ነው። ብልህ ሰው ታዲያ ያስፈልገናል። ይህን ህዝባዊ እምቢተኝነት ወያኔዎች ብቻ ሣይሆኑ አለቆቻቸውም ይፈሩታል። ለምን ቢባል የህዝብ አመጽ የት ጀምሮ የት እንደሚያልቅ አይታወቅም። የወያኔ ጌቶች ወያኔንና መሰል አሸባሪ ድርጅቶችን ጠፍጥፈው ሲሠሩ በርቀት መቆጣጠሪያ ሳይቀር እየተከታተሉ የሚያሸክሟቸውን ተልዕኮ ተፈጻሚነት ያረጋግጣሉ። ህዝባዊ እምቢተኝነት ግን ከነሱ ዓላማና ፍላጎት ሊወጣ የሚችልበት አጋጣሚ ብዙ ስለሆነ ይፈሩታል፤ ፊት ለፊት ሊጋፈጡትም ብዙውን ጊዜ አይደፍሩም። ስለዚህ ይህን የትል ዓይነት ገፋ አድርጎ መቀጠል ተገቢ ነው።
8. በምንም መንገድ በስደተኞች ብዛትና ሀገርን ለወያኔ ለቅቆ በመሄድ ወያኔ አይወድቅም። ይህ ዓይነቱ ነገር ሳይዋጉ እጅን እንደመስጠት ነውና በሀገር ውስጥ ሆኖ መታገል አማራጭ የለውም።
9. በምንም መንገድ በማዕቀብ እና ዕቃና አገልግሎት ከህወሓት ባለመግዛት ወያኔ አይወድቅም። ምክንያቱም በቂ የሀብት ክምችት አላቸው፤ ሁሉ በጃቸው ሁሉ በደጃቸው - ምን ሲጎድልባቸው። ህወሓት ሀገሪቱን ላለፉት 25 ዓመታትና ከዚያም በላይ ለሚቆጠር ጊዜ በብቸኝነት ሲበዘብዝ በመክረሙ የገንዘብም ሆነ የማቴሪያል ችግር ሳይኖርበት ብዙ ዓመታትን መዋጋት የሚያስችለው አቅም አጎልብቷል። ስለዚህ ከነሱ ዕቃ ባለመግዛት የምንጎዳቸው ነገር የለም።
10. በምንም መንገድ በፈቃዱ አይለቅም። ብሔራዊ ስሜት ቀርቶ የሰውነት ደረጃም የሌላቸው፣ የለየላቸው ዕብዶችና ሰካራሞች በመሆናቸው፤ የሀገሪቱና የህዝቧ ችግር ገብቷቸው ሥልጣናቸውን ለሽግግርም ይሁን ለቋሚ የህዝብ ተመራጭ መንግሥት ሊያስረክቡ አይችሉም። ትግራይንና የትግራይን ህዝብ በሆነ ኮሮጆ ውስጥ ይዘህ፤ “ይህን ኮሮጆ እሳት ውስጥ ከምጨምረውና ሥልጣናችሁን ከምትለቁ የትኛውን ትመርጣላችሁ?” ብለህ ብትጠይቃቸው ወያኔዎች ሥልጣናቸውን እንደሚያስቀድሙ ግልጽ ነው። ትግራይንና ተጋሩን ይቅርና በሚስትና በልጆቻቸው ሳይቀር ቁማር የሚጫወቱ የብዔል ዘቡል ደቀ መዛሙርት ናቸው። የሚገርም ተፈጥሮ እኮ ነው ያላቸው!
መፍትሔው
ስለዚህ መፍትሔው ምንድን ነው ቢባል መልሱ በበኩሌ እንዲህ ይመስለኛል።
ሁሉም ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎች በአንድ ወቅት ተባብረው በመነሣት በየአካባቢያቸው የሚመጣውን የወያኔ ጦር ቢቻል መማረክና ማስተማር፣ ያ ባይቻል አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ በቁጥጥር ሥር ማዋልና ለፍርድ ማቅረብ። ዕቃና ንብረት እየዘረፉ የሚያሸሹባቸውን መንገዶች ሁሉ መዝጋት፤ የጎበዝ አለቃ እየመረጡ ትግሉን በአንድ ጊዜ በሁሉም ሥፍራ ማጧጧፍ። የወያኔ ወታደራዊ ክንድ ከተመታ፣ በተለይም ኣጋዚ የሚባለው የሰይጣን መንጋ ከተበተነ ህወሓት ምንም አቅም አይኖረውምና በፍጥነት ይፍረከረካል። ያኔ ከያካባቢው የህዝብ ተወካዮች ተመርጠው ትልቅ ሀገራዊ ስብሰባ በማካሄድ ከታዋቂ ጤናማ ፖለቲከኞችና ታዋቂ ግለሰቦች፤ እንዲሁም የህዝብ እምነት ከሚጣልባቸው ተቃዋሚዎች የሚውጣጡ የአደራ መንግሥት ማቋቋም። ያ የአደራ መንግሥት ለሁለት ዓመታት ያህል ሀገሪቱን ካረጋጋ በኋላ በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አዲስና ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል የሚያለግል ዴሞክራሲያዊ መንግሥት መመሥረት። ስንታገል ደግሞ በአንድነት እንጂ ዘርና ጎሣ፣ ኃይማኖትና ክልል ለይተን መሆን የለበትም። እንደዚያ ካደረግን የወያኔን ፈለግ እንደመከተል ያለ ከንቱነት ነው። አሮጌው ወይን በአዲስ አቁማዳ ከተገለበጠ ጥፋትን በጥፋት መተካት ነውና ካለፈ ጠመዝማዛ ሕይወታችን መማር አለብን። ስለዚህ ትግሬን ከአማራ፣ ኦሮሞን ከሶማሌ፣ ከምባታን ከአፋር … አንዱ ከሌላው ሳይለያይ የአንዲት ሉዓላዊት ሀገር ህዝብ ባንድ ልብና ባንድ መንፈስ መታገል ይኖርበታል።
ወያኔዎች በተለይ ትግሬን ከሌላው ለመለየትና በሌሎች እንዲጎዳ በማድረግ ከነሱ ጋር ለመለጠፍ የሚያካሂዱትን የቀቢፀ ተስፋ ሸርና ተንኮል ነቅተን መጠበቅ አለብን። የወያኔን ሤራ በንቃት መከታተልና የእሳት ቃጠሏቸውን ሁሉ ሳይቀር እየተከታተልን ማጋለጥ አለብን፤ ሆን ብለው የሚጭሯቸውን ግጭቶች እየተከታተልን እውነቱን በወቅቱና አደጋ ሳያስከትሉ ይፋ ማድረግ አለብን። ሟች ይዞ ይሞታልና እነሱ ሥልጣናቸውንና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የማያደርጉት ነገር አይኖርም። እኛን ለመለያየትም የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። መለያየትን ደግሞ እስኪያንገሸግሸን አየነው፤ ክፉኛ ጎዳን እንጂ አልጠቀመንም። መኖር ከፈልግን እንግዲህ ማድረግ ያለብን እንደዚህ ነው። ሁሌ መሞኘት የለብንም። በመሠረቱ ብልጥ ከአንዴ በላይ መብለጥ አልነበረበትም። እኛ ግን የሆንነውን ሳናውቀው ዕድሜ ልካችንን በነዚህ ሰይጣኖች ስንታለልና ስንበለጥ ኖርን።
እንጂ እንዳሁኑ አካሄዳችን ከሆነ ሶማሊያና ሦርያ በስንት ጣማቸው የሚያስብል አስቀያሚ ሁኔታ እንደሚፈጠር በጣም ግልጽ ነው፤ የሚደርስልን ደግሞ እንደሌለ መረዳት ይገባል። ወያኔዎች አያያዛቸው “የምፅዓት ቀን ለምን ዘገዬ?” እያሉ ለአባታቸው ለዲያቢሎስ ከፍተኛ ተማፅኖ በማቅረብ ላይ የሚገኙ ይመስሉኛል። የታወከን ሀገር በብልሃትና በዘዴ እንደማረጋጋት ቦሃ ላይ ቆረቆር እንዲሉ በሰላም በዓልን በሚያከብር በሚሊኖች የሚቆጠር ህዝብ ላይ ከመሬትና ከሰማይ ጥይት ማዝነብ በየትኛውም ሥሌት ትርጉም የለውም። እነዚህ ድፍን ቅሎች የጥጋብ ሞራ ሁለመናቸውን ስለጋረደው የሚያደርጉት ነገር ምን ሊያስከትል እንደሚችል ማሰብ አልቻሉም፤ ተፈጥሯቸው ሁሌም በተቃርኖ የተሞላ ነው - “እንብላ” ሲሏቸው “እንተኛ” ዓይነት። ገና ለገና የላኳቸው የጥፋት ኃይሎች በሁሉም ረገድ አይዟችሁ ስላሏቸው ብቻ ምድራችን አይታውም ሆነ ሰምታው የማታውቀውን የክፋት ሥራ በኢትዮጵያውያን ላይ ይፈጽማሉ። በመጨረሻው የሚያስደስተው ነገር ግና የሠሯትን ሁሉ አንድ ባንድና በዕጥፍ ድርብ ያወራርዷታል፤ ያም ቀን ደርሷል።
እንደማሣረጊያ - ያገሬ ባላገር ምን አለ?
የማን ቤት ፈርሶ የማን ሊበጅ፤
ያውሬ መፈንጫ ይሆናል እንጂ።
እባክሽ እናቴ ውለጅ መንታ መንታ፤
ቀኝ እጄ ሲመክት ግራ’ጄ ተመታ።
እዚያ ማዶ ሆኖ አንድ ሰው ተጣራ፤
እዚህ ማዶ ሆኖ አንድ ሰው ወይ አለው፤
ጎበዝ ተጠራጠር ይህ ነገር ለኛ ነው።