Ethiopian National Movement meetingይገረም አለሙ

የተቀዋሚዎች ብዛት የርስ በርስ ሽኩቻና የጎንዮሽ ትግል ለወያኔ ዕድሜ መርዘም ዋናው ምክንያት መሆኑ አሌ የማይባል ነው። የድርጅቶቹ ዓላማ ሳይሆን የመሪዎቹ ፍላጎት አይታረቄነት ተባብሮ ለመሥራት የማያስችል ሆኖ ውሾቹም ይጮኻሉ፣ ግመሉም ይሄዳል እየተባለ ሃያ አምስት ዓመት ዘልቀናል።

በተግባር እንዳየነው ለፓርቲዎቹ መብዛትም ሆነ ለመተባበር አለመቻል ዋናው ችግር የአደረጃጀትና የትግል ስልት ወይም የዓላማና ግብ ልዩነት ሳይሆን፤ የትግል ጽናትና ቁርጠኝነት አለመኖርና ከሚነገረው በስተጀርባ የተደበቀ የመሪዎች ፍላጎት መኖር ነው።

አገራዊ ንቅናቄን የመሰረቱት አራት ድርጅቶች ዘግይተውም ቢሆን ከዚህ በኋላ የወያኔ አገዛዝ እንዲቀጥል መፍቀድ የለብንም በማለታቸው ለመተባበር አደረጃጀታቸውም ሆነ የትግል ስልት ምርጫቸው መለያየት እንቅፋት አልሆነባቸውም። ከአንጀት ካለቀሱ እንባ አይገድም እንደሚባለው ከምር ለነጻነት ለመታገል ከተሰለፉና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በእነርሱ መስዋዕትነት እውን እንድትሆን ከወሰኑ ለመተባበር የሚገድ አንዳችም ምክንያት አይኖርም።

ስለሆነም ከደረሰባችሁም ሆነ ካደረሳችሁት ተምራችሁ በተለይ ህዝቡ ከእናንተ ቀድሞ ሞትን ተጋፍጦ ነጻነቴን በማለት የከፈለው መስዋዕትነት አነሳስቶአችሁ፤ ልዩነቶቻችሁን በማስወገድም ሆነ በማቻቻል እዚህ ደረጃ በመድረሳችሁ እንደ አንድ ነጻነት ናፋቂ ዜጋ ምስጋናየ ይድረሳችሁ እላለሁ።

የፊርማ ሥነ-ሥርዓቱን ለመከታተል በአዳራሽ የተገኘው ነጻነት የናፈቀው ዴሞክራሲ በሀገሩ አብቦ ማየት የሚሻው (ለሱም ባይደርስ ለልጆቹ) ኢትዮጵያዊ የየድርጅቶቹ መሪዎች ለመናገር ከመቀመጫችሁ ስትነሱና ወደ ወንበራችሁ ስትመለሱ እንዲሁም ስምምነቱን ስትፈርሙ ቆሞ አጨብጭቦላችኋል። ያጨበጨበው ለእናንተ ሳይሆን ላነገባችሁት ክቡር ዓላማ ነው፤ ለደረሳችሁበት የመተባበር ስምምነት ነው፤ ቃላችሁን ተግባራዊ አድርጋችሁ ትግላችሁን አስተባብራችሁ ከወያኔ አገዛዝ ኢትዮጵያን ታላቅቋት ዘንድ መልዕክት ነው። እናም ጭብጨባው የአድናቆት መግለጫ ከመሆኑ በላይ አደራ ነው፤ ትልቅ ሸክም ።

በመሆኑም አዛውንት ወጣት፣ ወንድ፣ ሴት ሳይል አዳራሽ የሞላው ታዳሚ በየደቂቃው ከመቀመጫው እየተነሳ ያጨበጨበበት ትዕይንት እንዴትነትና ምንነት ሁሌም የሚታወሳችሁ፣ በእያንዳንዱ ርምጃችሁ የገባነውን ቃል ምን ያህል እየተወጣን ነው እያላችሁ ራሳችሁን እንድትጠይቁ የሚያነሳሳችሁ፣ ሸብረክ ስትሉ ወኔ የሚለግሳችሁ፣ ደከም ባላችሁ ግዜም እንቅልፍ የሚነሳችሁ ትልቅ አደራና መልዕክት ነው።

ጥያቄው ከወያኔ አገዛዝ የመላቀቅ የነጻነት ጥያቄ ነውና፣ ነጻነት ደግሞ አለ ትግል አይሆንምና፣ ትግልም ያለ ድርጅት ለውጤት አይበቃምና ይህ ነጻነት ናፋቂ ወገን ተደራጀን ላሉት፣ ተባበርን ላሉት ሁሉ ብዙ ግዜ አጨብጭቧል፤ ገንዘቡን ለግሷል፤ በሚችለው ሁሉ ረድቷል። ነገር ግን ብዙዎቹ ቃል አባይና አደራ በል ሆነው አሳዝነውታል፣ አሳፍረውታል።

ነገር ግን በአገር ጉዳይ ተስፋ አይቆረጥምና፤ ይሄው ዛሬም ተባበርን ስላላችሁት በአዳራሽ ተገኝቶ ደስታውንም አደራውንም በጭብጨባ ገለጸ። ጅምራችሁ መልካም ነው፣ ታሪክ ለክብር አጭቷችኋል፣ ሕዝቡም አደራውን ጥሎባችኋል፣ ቃላችሁን የምትተገብሩ የተሰጣችሁን አደራ የምትወጡ ሕዝቡን ለነጻነት ሀገሪቱንም ለዴሞክራሲዊ ሥርዓት የምታበቁ ያድርጋችሁ።

ከዳር ሆናችሁ ለምትመለከቱ፣

ድርጅቶቹን የማቀራረብና እዚህ ደረጃ ለማድረስ ብዙ የጣሩትና በከፊልም ቢሆን የተሳካላቸው (ብዙ ድርጅቶች ባለመካተታችሁ) ተመስጋኝ ዜጎች ሲናገሩ እንደሰማነው፤ ለአብሮ መሥራት የቀረበው መስፈርት የኢትዮጵያን ሉአላዊ አገርነት፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ማድረግና ሥልጣን የሚያዘው በሕዝብ ፈቃድ ብቻ መሆኑን መቀበል ነው። ይህን መስፈርት ኢትዮጵያዊ አይደለንም ወይንም ኢትዮጵያዊ ለመሆን እንደራደራለን ከሚሉትና መገንጠልን ዓላማ አድርገው ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ውጪ ማንም አይመቸኝም ልቀበለው ይቸግረኛል ሊለው አይችልም። ካለም ራሱን ትልቅ ጥያቄ ውስጥ ይጥላል።

ታዲያ ምን ሆናችሁ፣ ምን አስቸግሮአችሁ፣ ምንስ ልታልፉት የማትችሉት ደንቃራ ገጥሞአችሁ ነው አራት ድርጅቶች ለወራት ሲወያዩና ሲደራደሩና ከስምምነት ሲደርሱ የዳር ተመልካች መሆን የመረጣችሁት። የሃያ ዓመት ልምዳችን እንደሚነግረን ችግሩ የግለሰቦች ነውና፤ የየድርጅቶቹ አባላትና ደጋፊዎች መሪዎቻችሁ ለምን ከሌሎች ጋር እንደማይተባበሩ ጠይቁ፣ ውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ትግል አድርጉ፣ እናም የመሪዎቻችሁን ጠባብ ፍላጎት አሸንፉና ድርጅቶቻችሁን ከዳር ተመልካችነት ወደ ትብብሩ አካልነት አሸጋግሩ። ለዚህም ነገ ሳይሆን ዛሬ ሥራ ጀምሩ።

ተቃውሞ ለምታሰሙ፤

በአገር ጉዳይ ጋባዥና ተጋባዥ ሊኖር አይገባምና፤ ድርድሩ/ውይይቱ ሲከናወን አድፍጦ ቆይቶ አይሆንም ያሉት ሲሳካ አልተወከልንም፣ አልተጋበዝንም የሚል ተቃውሞ ማሰማቱ ተገቢ አይደለምና፤ አባላትና ደጋፊዎች ጣታችሁን መቀሰር ያለባችሁ ትብብር ወደ ፈጠሩት ድርጅቶችና ወደ አመቻቹት ሰዎች ሳይሆን ወደ መሪዎቻችሁ ነው። ለምን የአገራዊ ንቃናቄው አካል አልሆናችሁም ብላችሁ ጠይቁ፣ የትብብሩ አካል መሆን አለባችሁ ብላችሁ ሞግቱ፣ አባል ለመሆን የማያበቃ ችግር በየድርጅቶቻችሁ ካለ ቤታችሁን አጽዱ፣ አመራራችሁን አስተካክሉ። አባልነት ተከታይነት ሳይሆን ባለቤትነት ነው። ደጋፊዎችም የሚነገራችሁን ብቻ እየተቀበላችሁ የምታስተጋቡ ሳይሆን፤ ለምን እንዴት ወዘተ እያላችሁ የምትጠይቁ መሆን አለባችሁ። እናም ጥያቄአችሁን ወደ ቤታችሁ መልሱና ምከሩ፣ መፍትሔ ፈልጉና እምቢተኛውንም አስገድዱና ድርጅቶቻችሁ የአገራዊ ንቅናቄው አካል እንዲሆኑ አብቁ።

ትብብር የሚመሰረተው ትግሉን ወደ ድል ለማምራት እንጂ፤ በድርጅቶች ልዩነት ለመጠመድ ባለመሆኑ በአንድ ብሔር ስም አራት አምስት ሆናችሁ የተደራጃችሁና ስምምነት አጥታችሁ ርስ በርስ የምትናቆሩ ሁላችሁም ሆናችሁ ከመካከል አንዱ የንቅናቄው አባል ቢሆን ጤና አይሰጥም።

መጀመሪያ ነገር የተደራጃችሁት በርግጥ እንወክለዋለን ለምትሉት የሕብረተሰብ ክፍል ነጻነት ከሆነ እንዲህ በዝቶ መደራጀቱ አስፈላጊ አልነበረም፤ ከሆነም በልዩነታችሁ በዝታችሁ በሚያስማማችሁ አንድ መሆን የሚገድ አልነበረም፤ ስለሆነም በቅድሚያ በየቤታችሁ በሽታችሁን እወቁ፣ በቂ ሕክምና አድርጉ፤ ከዛ ጋርዮሽ ፈጥራችሁ ካልሆነም ከመካከላችሁ ከበሸታው የተፈወሰ አንዱ አባል ሊሆን ይችላል። ይህን ሳታደርጉ ሌላውን መውቀስ ግን እንደምን ይቻላል። ነገም ሌላ ቀን ነው።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!