በአንድ ሰሞን ጩኸት፣ አይገኝ ነጻነት
ይገረም አለሙ
![የሕዝብ ተቃውሞ በገዥው ፓርቲ ላይ። [ፎቶ፣ Reuters] Protests accusing the Ethiopian government](/amharic/images/doc/images/articles/2017/170525-protests-accusing-ethiopian-government.jpg)
እንደ መነሻ፣ ምክንያት እየፈለገ የወያኔን ኮቴ እየተከተለ የሚጮኸው ሁሉ በእኩል ደረጃና እምነት የወያኔ ተቀዋሚ መሆን አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ ነጻነት ፈላጊ መሆኑ ራሱ አጠራጣሪ ነው። ይህ ባይሆን ኖሮ ከምር ሁሉም ነጻነት ፈላጊ ቢሆን ኖሮ የጎሣ አጥር፣ የኃይማኖት ድንበር ወዘተ እየሰራ በየግል ሕልሙ ታጥሮ ለውጥ ሊያመጣ ቀርቶ ሰሚ ሊያገኝ እንኳን ያልቻለ ጩኸት በየመንደሩ በማሰማት ላይ ተወስኖ ሃያ ስድስት ዓመታትን ባላስቆጠረ ነበር።
ባለትልቅ ራዕይ በትናንሽ ጉዳይ አይለያይም፣
ዓላማው ነጻነት፣ ግቡ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማየት የሆነ ዜጋም ሆነ ቡድን ከዚህ በመለስ ባሉ ጉዳዮች ልዩነት እየፈጠረ አይወራከብም፣ የየራሱን ነጻ መሬት መስርቶ አይታኮስም (በቃላት)፣ ከሚታገለው ወይንም ከሚቃወመው ኃይል አንድ ርምጃ ቀድሞ ያስባል፣ ያቅዳል፣ ይዘጋጃል፣ ይተግብራል እንጂ፤ በትናንት ታሪክ አያላዝንም፣ ወያኔን መዝለፍና ማውገዝን የትግሉ መነሻም መድረሻም አያደርግም።
“ወያኔ የደደቢቱን እኛ የዕለት የዕለቱን” በሚል ርዕስ ከዓመት በፊት ይመስለኛል በዚሁ መድረክ ባቀረብኩት ጽሁፍ፤
ወያኔ የደደቢቱን ዓላማውን በተለያየ መንገድና ዘዴ ተግባራዊ ሲያደርግ እኛ አንድ ዓላማ ኖሮን፣ ዓላማችንን ተግባራዊ ለማድረግ ወደሚያስችለን ግባችን ለመጓዝ የሚያስችለንን ስትራቴጂ ነድፈን፣ በቂ ዝግጅት አድርገንና ጥንካሬ ፈጥረን ከመንቀሳቀስ ይልቅ፤ ተራርቀን የወያኔን እግር እየተከተልን ከምናደርገው ተቃውሞ አልወጣንም። ይህም ሕዝብን ለመስዋዕትነት ወያኔንም ለበለጠ እብሪትና አንባገነንነት ያበቃው በመሆኑ፤ ኢትዮጵያ ዛሬም የግፍና የጅምላ ግድያ እያስተናገደች ነው። ፖለቲከኞች ይህ አስቆጥቶአቸውና ቁጭት አሳድሮባቸው ከዚህ በኋላ ሌላ እልቂት ማየት የለብንም፤ “በቃ!” በማለት ተጠራርተው ሸንጎ ተቀምጠው መላ ሊመቱ፣ እቅድ ሊያወጡና ስንዴና እንክርዳዱ ተለይቶ በአጭር ግዜ ከተከታይነት ወደ ቀዳሚነት መሸጋገር የሚያስችል ስትራቴጂ መንደፍ በጀመሩ ነበር።
… የምትል ሀሳብ አስፍሬ ነበር። ከዛ በኋላ ወያኔ ብዙ ነገሮችን ከወነ፣ ተቀዋሚውም የትናንቱን እየረሳ ለዛሬው እየጮኸ፣ ከለመደው መጎነታተል ሳይላቀቅ፣ ከእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ልክፍቱ ፈውስ ሳያገኝ ለመተባበር ቀርቶ ለመከባበር የሚያበቃ ህሊናዊ እድገት መፍጠር ተስኖት እንዳለ አለ። እያንዳንድ ድርጊት ለዋናው ግብ ትንሽም ቢሆን አዎንታዊ ድርሻ የሚያበረክት መሆን አለበት፤ የጠራ በግልጽ የታወቀና የታመነበት ግብ ከሌለ ግን በብዙዎቹ ዘንድ እንደሚታየው በዕለት ዕለት ጉዳዮች ብቻ መጠመድ ይሆናል።
ተመሳሳይ ጠላት ያላቸው ጓደኛሞች ይሆናሉ
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አብርሀም ሊንከን የተናገሩት ይህ ቃል እውነት ቢሆንም ለእኛ አገር ፖለቲከኞች ለብዙዎቹ ግን አይሰራም። ሁሉም ወያኔን ሲያወግዙ ሲኮንኑ ብሎም ጠላታችን ሲሉ ይሰማሉ፣ በተግባር ግን ጠላታችን ከሚሉት ወያኔ በላይ በመካከላቸው ያለው ጠላትነት ያይላል። ይህም በመሆኑ እርስ በእርሳቸውም አይሸናነፉ ወያኔንም አያሸንፉ፡ ብቻ ሲያላዝኑና ብሶት ሲያወሩ መኖር።
ሰሞኑን አብሮ ለመስራት ትብብር ከፈጠሩት ድርጅቶች የአንዱ የኦጋዴ ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር ሊቀመንበር ነጻ እናወጣዋለን የምንለው ሕዝብ እኮ እያለቀ ነው በማለት፤ መገንጠል ወቅታዊ ጉዳይ አለመሆኑን ገልጸው፤ በኢትዮጵያ አገራዊ አንድነትና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በመመስረት ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል በማመን ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ጋር አብረው ለመስራት መስማማታቸውን የገለጹበት አነጋገር፤ ወቅታዊውን ችግር የተገነዘበ፣ መፍትሄውንም የተረዳ፤ በተግባር እንያችሁ ከማለት ውጪ እሰየው የሚያሰኝ ነው።
ነጻ እናወጣዋለን የምንለው ሕዝብ እኮ እያለቀ ነው፤ መገንጠል ወቅታዊ ጉዳይ አይደለም፤ … በኢትዮጵያ አገራዊ አንድነትና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በመመስረት ችግሮችን መፍታት ይቻላልየኦጋዴ ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር ሊቀመንበር
ከዚህ ቀድሞ የተመሰረተው አገራዊ ንቅናቄም በምስረታው ሰሞን አቶ ሌንጮ ለታ፤ “25 ዓመት ሙሉ ወያኔን በየኤምባሲው እየዞርን አማን፤ ውጤት አላመጣንም። አሁን የትግሉ መንገድ መለወጥ አለበት (ቃል በቃል አልገለጽኩ ይሆናል)፤ እንዳሉት ተበታትኖ ከማማትና እንዲህ ሆንን፣ እንዲህ ተፈጸመብን እያሉ ከማላዘን፤ ነጻነት በትግል እንጂ በጩኸት እንደማይገኝ ተገንዝቦ፤ ትብብር መስርቶ፣ አቅምን አቀናጅቶ፣ ለለውጥ መታገሉ ነውና የሚበጀው፤ ይህንኑ መንገድ መያዛቸው ተገቢና ወቅታዊ ርምጃ ነው። ታዲያ በዚህ አድራጎታቸው አራቱን ድርጅቶች ስናደንቃቸው፤ ከአንዱ በስተቀር የተግባር እንቅስቃሴ አላየንም፣ አልሰማንምና “ቃል የእምነት እዳ እንጂ የእናት አባት እኮ አይደለም” የሚለውን የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህንን አባባል በማስታወስ ቃላችሁን ተግብሩት ማለት ይኖርብን ይመስለኛል።
በአገራዊ ንቅናቄው ምስረታ ማግስት “መልዕክት፤ ለኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ መስራቾች” በሚል ርዕስ በጻፍኳት መልዕክት፤ “የፊርማ ሥነ-ሥርዓቱን ለመከታተል በአዳራሽ የተገኘው ነጻነት የናፈቀው፣ ዴሞክራሲ በአገሩ አብቦ ማየት የሚሻው፣ (ለሱም ባይደርስ ለልጆቹ) ኢትዮጵያዊ የየድርጅቶቹ መሪዎች ለመናገር ከመቀመጫችሁ ስትነሱና ወደ ወንበራችሁ ስትመለሱ እንዲሁም ስምምነቱን ስትፈርሙ ቆሞ አጨብጭቦላችኋል። ያጨበጨበው ለእናንተ ሳይሆን፤ ላነገባችሁት ክቡር ዓላማ ነው፤ ለደረሳችሁበት የመተባበር ስምምነት ነው፤ ቃላችሁን ተግባራዊ አድርጋችሁ ትግላችሁን አስተባብራችሁ ከወያኔ አገዛዝ ኢትዮጵያን ታላቅቋት ዘንድ መልዕክት ነው። እናም ጭብጨባው የአድናቆት መግለጫ ከመሆኑ በላይ አደራ ነው፤ ትልቅ ሸክም።” ነበር ያልኩት።
በተግባር የሌሉ ለወሬና ለአሉባልታ እኩያ የሌላቸው የሕዝቡ እንቅስቃሴ ትንሽ ጎላ ባለ ግዜ አሸጋግረው ምኒልክ ቤተመንግሥትን በማየት አንገታቸውን የሚታመሙ ሰዎች ከሚያስነሱት አቧራ ራሳችሁን አርቃችሁ ወይኔን በሀሜትና በውግዘት ሳይሆን፤ ዓላማችሁ በድርጊት መታገሉን፣ ግባችሁ ደግሞ ራሳችሁን ለሥልጣን ለማብቃት ሳይሆን የሕዝብን የሥልጣን ባለቤትነት ማረጋገጥ መሆኑን በተግባር አሳዩ። ይህን የምለው ራሳችሁ የነገራችሁን ቃላችሁ በመሆኑ እንጂ “ውረድ በለው ግፋ በለው” ለማለት ድፍረቱ ኖሮኝ አይደለም። ከሚስቶቻቸው ጉያ ሳይወጡ ለምን አትዋጉም? ለምን ነጻ መሬት ይዛችሁ አታሳዩንም? ለምን ግዳይ ጥላችሁ አታቅራሩም? ወዘተ እንደሚሉት ሰዎች ለመሆን አይቃጣኝም።
ወያኔን እየተከተሉ ማላዘን!
ከምር ለነጻነት ከሚታገለው በምን ተቃውሞ ላሰማ፣ በምንስ ልጩኽ፣ እንዴትስ ራሴን የአደባባይ ሰው ላድርግ ወዘተ የሚለው በመብዛቱ እንጂ፤ የእሬቻው እልቂት፣ የባህር ዳርና ጎንደሩ ጭፍጨፋ፣ በአስር ሺዎች የተፈጸመው የገፍና የግፍ እስራት ወዘተ ተረስቶ፤ የሁለቱ ቴዎድሮሶች ጉዳይ መነጋገሪያም መነታሪኪያም ባልሆነ ነበር። ምዕራብ ወለጋ ልጇን ገለው አስክሬኑ ላይ አስቀምጠው የተመጻደቁባትና የተሳለቁባት እናት እንዴት ትረሳለች። አሩሲ ላይ የሁለት ጎልማሳ ልጆቻቸውን አስክሬን ጎን ለጎን አጋድመው የጠሩዋቸው እናትና አባት እንዴት ይረሳሉ?! በየእስር ቤቱ በእሳት የጋዩት ወገኖች እንዴት ይረሳሉ። ሌላም ሌላም፣ እኛ ግን ራዕይ የለሽ፣ ግብ የለሽ ሆንና ይህን ሁሉ ረስተን በዕለት በዕለቱ ጉዳይ እንጮሀለን። የወያኔ የሃያ ስድስት ዓመታት ድርጊት እያነሳን እናላዝናለን።
ወያኔዎች ገደሉ፣ አሰሩ፣ ደበደቡ፣ የአገር ሀብት ዘረፉ ወዘተ እያሉ ሃያ ስድስት ዓመታት ያላባራ ጩኸት ማሰማት የእነርሱን እኩይ ድርጊት ፈጻሚነት ሳይሆን፤ የእኛን ከንቱነት ነው የሚያሳየው። ለዚህ ደግሞ ሁለት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። አንደኛው ወያኔዎች ለምንና ለማን እንደታገሉ ዛሬ ድረስ መረዳት አለመቻላችንና ከእባብ እንቁላል ርግብ መጠበቅ የሚሉት አይነት መሆናችን ሲሆን፤ ሁለተኛው የምንጮህበት ድርጊት ሁሉ ሲፈጸም እኛ ምን አደረግን በማለት ራሳችንን ለመጠየቅ አለመድፈራችን ነው። ሌላው ቀርቶ ወያኔን ታግለን አሸንፈን ሥልጣን እንይዛለን የሚሉ ሰዎች፤ ወያኔ እየከፋፈለን ነው በማለት በአደባባይ ሲናገሩ ትንሽ እንኳን አለማፈራቸው ያሳዝናል። እንዲያጠናክራቸው ይሹ ነበር ማለት ነው?
ወያኔ ማድረግ ያለበትን ነው ያደረገው፣ እያደረገም ያለው፣ ወደ ፊትም የሚያደርገው። ይህን ደግሞ በጩኸትም ሆነ በማላዘን፣ በውግዘትም ሆነ በመኮነን ማስቆም እንደማይቻል ለመረዳት ሃያ ስድስት ዓመት ሊገባን አለመቻሉ ሌላው እንቆቅልሻችን ነው። ከዚህ በኋላ በዚሁ መንገድ በጩኸትና ዋይታ መቀጠል ደግሞ ተቀዋሚ እየተባሉ መኖርን ከመፈለግ ውጪ ሌላ ሊሆን አይችልም። እንደውም ቀን ቀን ወያኔ ይውደም እያሉ በአደባባይ ተቀዋሚ መስለው እየታዩ፤ ማታ ማታ በቤታቸው ለወያኔ ዕድሜ የሚለምኑ ሳይኖሩ እንደማይቀሩ የአንዳንድ ሰዎች ድርጊቶች ጥርጣሬ ያጭራሉ። ይህ አይነት ነገር የለም ከተባለ በሁሉም ተዋሚዎች ዘንድ ግለሰብ ድርጅት ሳይባል የወያኔን እግር እየተከተሉ መጮሁ ይብቃ፤ ወያኔ ግዜ እየጠበቀ ወደ ተቀዋሚው ጎራ በሚወረውረው ኳስ መጫወቱም ይብቃ። ቀድሞ ማሰብ፣ ቀድሞ ማቀድ፣ ቀድሞ መዘጋጀት፣ ቀድሞ መተግበር መቻል ነው በወያኔ ላይ የበላይነት ለመያዝና ወደ ድል ጎዳና ለማምራት የሚያስችለው። ሲሞቅ ማጋጋል፤ ሲቀዘቅዝ ድራሽን ማጥፋት በፍጹም ታጋይ ሊያሰኝ አይችልም።
የሚመከረው ነገር በዝግታና በጥልቅ ታስቦ በለዘብታ ክርክር ተጣርቶ በትዕግስት እየተመላለሰ ተመክሮ የተቆረጠ ነገር እንዲሆን ነው።ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጥቅምት 23/1935 ለፓርላማ አባላት ካሰሙት ንግግር
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጥቅምት 23/1935 ለፓርላማ አባላት ካሰሙት ንግግር የተወሰደው ይህ አባባል መካሪ ሊሆን ከቻለና የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ ካላሰኘኝ እነሆ! “የሚመከረው ነገር በዝግታና በጥልቅ ታስቦ በለዘብታ ክርክር ተጣርቶ በትዕግስት እየተመላለሰ ተመክሮ የተቆረጠ ነገር እንዲሆን ነው።” አዎ ወያኔን መታገል በዕለት ዕለት ጎዳዮች በግብታዊነት ጩኸት ሳይሆን በዕቅድ፣ በዝግጅት፣ በድርጊት ይሁን።