Half a million Ethiopians protest for regime changeኤፍሬም ማዴቦ

እንደኔ አንዴ ሲቆጥቡት አንዴ ሲደብቁት በድንገት ዕድሜያቸው ወደ ሃምሳዎቹ የገባ ሰዎች አንድ የምንጋራው እምነት አለ፤ እሱም የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች አንድ ነገር መጀመር እንጂ መጨረስ አያውቁበትም የሚል እምነት ነው። በፍጹም ሊፈረድብን አይገባም። ከልጅነት ወደ አዋቂነት የደረስነው ጥንስስ ሲጠነሰስ እንጂ እንጄራውን ሳናይ ነው። ፓርቲ ሲፈጠር እንጂ ውጤቱን ሳናይ ነው። የፖለቲካ ሕብረቶች ተፈጥረው ፈረሱ ሲባል ነው እንጂ፤ እንዲህ አደረጉ ሲባል ሰምተንም አይተንም አናውቅም። ባጠቃላይ የፖለቲካ ትግል ሲባል ነው እንጂ፤ ድል ሲባል ሰምተን አናውቅም።

ድል የረዥም ግዜ ትግል ውጤት እንደሆነ ይገባናል፣ ሆኖም ግን ዛሬ የሚረግጡን ሰዎች በረሃ ገብተው አዲስ አበባን እሲኪቆጣጠሩ ድረስ የወሰደባቸውን ግዜ ሁላችንም የምናስታውሰው ይመስለኛል። እኔ ይህንን ሁሉ ጉድ በዓይኑ እያየ ያደገ ትውልድ አካል ነኝ። ግን ይህንን ዕድሜ ልኬን ሲደጋገም ያየሁትን የአገሬን በሽታ መድኃኒት እፈልግለታለሁ እንጂ፤ “ከመሳሳት እራሴን ላድናት” እኔን ምን አገባኝ የ”እነሱ” ጉዳይ ነው ብዬ እጆቼን አጣጥፌ አልቀመጥም። ጉዳዩ የኔ ነው ... ጉዳዩ የኛ ነው። “እነሱም” “እኛም” አንድ ላይ “እኛ” ነን። ሰው የመሆኔ ትልቁ ምስጢር የሚነግረኝ በአካባቢዬ ካሉ ሰዎች ውጭ መኖር የማልችል ማኅበራዊ ፍጡር መሆኔን ነው። አንዳንዶቻችን መሳሳትን እንደ ጦር እንፈራለን፣ መሳሳትን ፈርተን እጃችንን አጣጥፈን ከምንቀመጥ እየተሳሳትንና ከስህተታችን እየተማርን የምንሠራው ሥራ ነው አገራችንን ነጻ የሚያወጣት። ስለዚህ በእኔ እምነት ምንም ይሁን ምን ከኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የሚጠበቅ ምንም ነገር የለም ብለን እጅና እግራችንን አጣጥፈን መቀመጡ የበሽታ ምልክት ነው እንጂ የጤንነት አይመስለኝም።

እኔ ይህ የኔ ትውልድ የኢትዮጵያን ችግር መፍታት ያለበት የአደራ ትውልድ ነው ብዬ የማምን ሰው ነኝ። ግን እንዴት ነው እኛ የኢትዮጵያ ልጆች በዘር፣ በቋንቋና በኃይማኖት ሳንከፋፈል አንድ ላይ ቆመን ኢትዮጵያን አንድነቷ የተጠበቀ የፍትህ፣ የነጻነት፣ የእኩልነትና የዲሞክራሲ አገር የምናደርጋት? እንዴትና መቼ ነው ሁሉንም ያቀፈ ስብስብ ፈጥረንና በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠን የአገራችንን ችግሮች በውይይት የምንፈታው? መቼ ነው ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ማዶ ለማዶ ለያይቶ ካስጮኸንና ካጨቃጨቀን ማለቂያ የሌለው የባዶ ቃላት ጫጫታ ተላቅቀን ሞት አፋፍ ላይ የደረሰችውን አገራችንን ከሞት የምንታደጋት? መቼ ነው ማንም ከማንም በላይ ኢትዮጵያዊነት ሳይሰማው በኢትዮጵያን ጉዳይ ከሚመለከታቸውና ከሚያገባቸው ወገኖች ሁሉ ጋር ተቀምጠን ስለአገራችን ችግሮች የምንወያየውና መፍትሔ የምንፈልገው? መቼ ነው በቋንቋ ብንለያይም፣ በኃይማኖት ብንለያይም፣ በሃሳብና በፖለቲካ አመለካከት ብንለያይም የጋራ የሆነው የአገራችን ጉዳይ አገናኝቶን በሠለጠነ ቋንቋ ተነጋግረን አዲስቷን ኢትዮጵያ አምጠን የምንወልዳት?

አብረነው ከቆምን፣ ከተባበርነው፣ ከረዳነውና ግዜና ሃሳብ ከሰጠነው እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ የሚችል አካል ጥንስስ ባለፈው ወር አሜሪካ መዲና ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ መጀመሩን ብዙዎቻችን ኢሳት በለቀቀው ሰበር ዜና የሰማን ይመስለኛል። አገር ውስጥ የሚደረገው ትግል ማዕከላዊ አመራር በሚፈልግበት በዚህ አሳሳቢ ወቅት ኢትዮጵያዊያንን ማሰባሰብ የሚችል ድርጅት መፈጠሩ ሁላችንንም ሊያስደስት የሚገባ መልካም ዜና ነው። እኔም ይህንን መልካም ዜና እንደሰማሁ ቁርሴን በላሁና ፌስቡኩ፣ ድረገጹና ቲውተሩ የሚሉትን ለመስማት Internet ፍለጋ ወጣሁ። Internet ቤት ደርሼ አይፎኔን ገና ስክፍተው ዜናው ሁሉ የሚያወራው አዲስ ስለተፈጠረው አገር አድን ንቅናቄ ነበር። ለምን እንደሆነ አላውቅም እኔን ያጋጠመኝ ዜና ግን አዲሱን አገር አድን ንቅናቄ ገና ከመወለዱ “አትደግ” እያለ የሚራገም ዜና ነበር። በፍጹም አልገረመኝም! ምክንያቱም እንዲህ አይነት ከፈረሱ ጋሪው የቀደመ ትችት እየሰማሁ ነዋ ያደኩት። ስለዚህ በትዕግስት ማንበቤን ቀጠልኩ። ቆየት ብዬ ነገሮችን በስፋት እያዩና በጥልቀት እያሰቡ የሚጽፉ ሰዎችን ሃሳብ ሳነብ አንድ ነገር ተረዳሁ። በአገር አድን ንቅናቄው ስብሰባ ላይ የተነገረው ንግግር በሙሉ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ነበር፤ ከእያንዳንዱ ድርጅት ተወካይ አፍ ይወጣ የነበረው ቃል የወደፊቷ ኢትዮጵያ የጋራ ቤታችን መሆን አለባት የሚል ተስፋ የሞላበት ቃል ነበር፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ የስብሰባው መንፈስና የአገር አድን ንቅናቄው የተፈጠረበት ዋነኛ አላማ ኢትዮጵያን ከተደቀነባት አደጋ እናድናት የሚል ነበር።

እነዚያ ከሃሳባቸው ብዕራቸው የቀደመ ወገኖቼ የተመለከቱት ግን የጋራ ንቅናቄውን ይዘትና ይዟቸው የተነሳውን ግቦች ሳይሆን፤ ላይ ላዩን የሚታየውን የአገር አድን ንቅናቄውን ቅርጽ ብቻ ነበር። በተለይ አብዛኛው ሰው የተቸው ሦስቱ ድርጅቶች በብሔር የተደራጁ ድርጅቶች የመሆናቸውን ጉዳይ ነበር። እርግጠኛ ነኝ አሁንም ይህ ስለዚህ ጥንስስ የሚያወራው ጽሁፌ ብዙ ጩኸት ይዞብኝ እንደሚመጣ አውቃለሁ። የሚያወሩ ሰዎች ያውሩ የሚሉም ሰዎች የሚሉትን ሁሉ ይበሉ፤ እኔ ግን አንድ የማረጋግጥላቸው ነገር አለ። እሱም ድምጽ ፈርቼ ኢትዮጵያን ከአደጋ የሚያድን ሃሳብ ከማፍለቅና ከመናገር በጭራሽ ወደ ኋላ ከማይሉ ኢትዮጵያዊያን ውስጥ አንዱ መሆኔን ነው። “ለተቀማጭ ሰማይ ቅርብ ነው” የሚል አባባል እየሰማሁ ነው ያደኩት። ዛሬ ይህንን አባባል ሙሉ ለሙሉ አልቀበለውም። ያገኘውን አጋጣሚ አይጠቀምበትም እንጂ ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ብቻ ሳይሆን እጁ ላይ ነው ያለው።

ይህንን መጣጥፍ የሚያነብ አብዛኛው ሰው ተወልዶ ያደገው ኢትዮጵያ ውስጥ ነውና፤ ሁሉም ኢትዮጵያን እንዳቅሙ ያውቃል የሚል እምነት አለኝ። አገራችን ኢትዮጵያ የረዥም ግዜ ታሪክ ያላት አገር ናት። ታሪካችን እንደማንኛውም አገር ታሪክ መራራና ጣፋጭ ምዕራፎች አሉት። ግን ወደድንም ጠላን መራራውም ታሪክ ጣፋጩም ታሪክ የኛ ታሪክ ነው። ሁለቱንም የታሪክ ምዕራፎቻችንን እንደ ታሪክ መቀበል ብቻ ሳይሆን ለልጆቻችን ማስተማር አለብን። ኢትዮጵያ ለአውሮፓ ኢምፔሪያሊዝም እጄን አልሰጥም ብላ የራሷ ብቻ ሳይሆን የዓለም ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ምልክት ሆና የቆየች አገር ናት። ይህ ከምንወደውና በኩራት ከምንናገረው ታሪካችን ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ሕዝብ የበደለው ወይም ያገለለው ሕዝብ አለ ብዬ በፍጹም አላምንም። የተለያዩ የኢትዮጵያ ገዢ መደቦች ግን አንዱን ከፍ ሌላውን ዝቅ አድርገው ሕዝብን ከሕዝብ መለያየታቸውንና በሕዝብ ላይ ይህ ነው ተብሎ ሊነገር የማይችል እጅግ በጣም ከፍተኛ በደልና ሰቆቃ መፈጸማቸውን ለአንድም ደቂቃ ቢሆን መርሳት የለብንም። ይህ ደግሞ የመራራው ታሪካችን አንዱ ክፍል ነው። ይህም ታሪካችን በፍጹም ልንክደው የማንችለው የረዥሙ ግዜ ታሪካችን አካል ነውና አንገታችንን ቀና አድርገን በግልጽ ልንናገረው የሚገባ ታሪክ ነው። ከፋም ለማ ልንማርበት የሚገባ ታሪክ እንጂ የምናፍርበትና ከሌላው ዓለም ሕዝብ የተለየ ታሪክ የለንም። እንደ አንድ አገር ሕዝብ ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈን ወደፊት መጓዝ የምንችለው ባለፈው ታሪካችን ላይ ተመስርተን በዳይና ተበዳይ እየተባባልን ስንካሰስ ሳይሆን የበደለም የተበደለም እንዳለ ተማምነን ይህንን መራራ የሆነውን የታሪክ ምዕራፍ ላለመድገም ስንማማል ብቻ ነው። በታሪክ ነግዶ ብቻውን ያተረፈ ማንም የለም፣ ብቻውን የከሰረም የለም። የታሪክ ንግድ ትርፉ ያለፈውን ስህተት መድገም ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ማኅበረሰባዊ ኪሳራ ነው። ዛሬ የሁላችንም ዓይን አተኩሮ መመልከት የሚገባው የትናንቱን በደልና ጭቆና ሳይሆን የነገውን ብሩህ ዘመን ነው። እኛ ማድረግ የምንችለው የትናንቱን ስህተት ማረም ሳይሆን ከትናንቱ ስህተት ተምረን ነገን አስተካክሎ መቅረጽ ነው። ብዙ ሰው ለአገሩ ለኢትዮጵያ ስለሚሳሳ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ጉዳይ በጣም ያስጨንቀዋል። እኔ ተጨንቄም አላውቅ! ተፋቅረን፣ ተስማምተንና ተግባብተን አንድ ላይ ከሠራን የነገዋ ኢትዮጵያ ጉዳይ እኛ እጅ ላይ እንደሆነ በሚገባ አውቃለሁ። ታዲያ እጄ ላይ ላለ ነገር ለምን እጨነቃለሁ?

ይልቅ እኔን የሚያስጨንቀኝና እንቅልፍ የሚነሳኝ አለመተባበራችንና የምንፈለገውን ነገር ለማግኘት አንድ ላይ አለመሥራታችን ብቻ ነው።

ብዙዎቻችን እኛ ከምናያትና ከምናስባት ኢትዮጵያ ውጭ ሌሎች የሚያዩዋትንና የሚያስቧትን ኢትዮጵያን ማየትም ማሰብም አንፈልግም። ይህንን ፍላጎታችንን በሌሎች ላይ እስካልጫንነው ድረስ እንደዚህ አይነት አስተያየት መያዙ በራሱ ብዙም ጉዳት የለውም። አደጋውና ጉዳቱ የሚታየኝ፤ እነሱ እራሳቸው እጅም ዶማም የሌላቸው ሰዎች ኢትዮጵያ ላይ የተደቀነው አደጋ የታያቸው ወገኖች አደጋውን ከወዲሁ ለማቆም ሲወጡና ሲወርዱ፤ “ከእጅ አይሻል ዶማ” እያሉ አላዋቂ ሳሚ ሲሆኑባቸው ነው። አደራ ... አትተቹ እያልኩ አይደለም። “መተቸት” ልንለምደው የሚገባን “መተቸትም” ሳንወድ በግድ መቀበል ያለብን ከሌሎች ጋር የሚያኖረን እሴት መሆኑን ከልቤ አምናለሁ። ሌላም በጽኑ የማምንበት እሴት አለ፤ እሱም አንድን ሃሳብ ከመተቸታችን በፊት ሃሳቡን አላምጠን መዋጥ ያለብን መሆኑን ነው። አለዚያ ከምንተቸው ሃሳብ በፊት ብዕራችን እየቀደመ የምንተቸው ትችት እሱ ትችት ሳይሆን የደፈጣ ውጊያ ነው። ውጊያ ደግሞ ተቺውንም ተተቺውንም ይገድላል እንጂ አያስተምርም። ሌላው ነገር ደግሞ ተቺዎችን መተቸት እንደሚቻልም መታወቅ አለበት።

እራሳቸውን በብሔር ተደራጅተው ማየት የሚጸየፉ ብዙ ኢትዮጵያውያን አሉ። መብታቸው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አሁን ያለው ሰው በላ አገዛዝና ተከታታይ የኢትዮጵያ መንግሥታት በሕዝብ ላይ በፈጸሙት በደል የተነሳ አንዳንድ ወገኖች ይበጀናል ብለው እራሳቸውን ያደራጁት በብሔር ወይም በዘር ነው። እነዚህም መብታቸው ነው። ሁለቱም ወገኖች እኩል ኢትዮጵያውያን ናቸው። አንዱን ወገን ከሌላው የሚያስበልጥም ሆነ የሚያሳንስ ምንም አይነት መመዘኛ የለም። ኢትዮጵያን ከዘረኛው የህወሓት አገዛዝ ነጻ ለማውጣት፣ አገራዊ አጀንዳ ለመቅረጽና አሁን ያለውን አገዛዝ የሚተካ የሽግግር መንግሥት ለመፍጠር በሚደረጉ ውይይቶች ሁሉ ላይና ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ጉዳይ በሚነሳባቸው መድረኮች ላይ የኢትዮጵያ ባለጉዳይ (Stakeholders) ሆነው መቅረብ የሚችሉት እነዚሁ እራሳቸውን በብሔር ያደራጁ፣ ጭራሽ በድርጅት ያልታቀፉና በሕብረ ብሔር ድርጅቶች የታቀፉ ኃይሎች ናቸው። የወደፊቷ ኢትዮጵያ የሁላችንም ኢትዮጵያ ሆና መቀጠል የምትችለው እነዚህ ሁሉ ኃይሎች አብረው በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው የምትበጃቸውን ኢትዮጵያ መፍጠር ከቻሉ ብቻ ነው። አለዚያ ሥራችንና ድካማችን ሁሉ የትናንቱን ስህተት እያወቅን መድገም ይሆናል።

እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ሕዝብ የሚያገናኙን ብዙ የጋራ እሴቶች አሉንና እንመሳሰላለን፤ በማያመሳስሉን ነገሮች ደግሞ እንለያያለን። ለምሳሌ በፖለቲካና በኤኮኖሚ አመለካከታችን እንለያያለን፣ አንዳንዶቻችን ወግ አጥባቂዎች ነን፣ አንዳዶቻችን ደግሞ ለዘብተኞች ነን። አንዳዶቻችን በብሔር መደራጀት እንፈልጋለን አንዳንዶቻችን ጭራሽ ነገራችን ሁሉ በተናጠል መሄድ ነው፣ አንዳንዶቻችን ደግሞ ከሕብረ ብሔር ድርጅቶች ውጭ መደራጀት አያምረንም። አንዳንዶቻችን መብት ሲባል የሚታየን የቡድን መብት ብቻ ነው፣ አንዳንዶችችን ደግሞ የግለሰብ መብት ከምንም ነገር ይበልጥብናል። ለኢትዮጵያ የሚያዋጣት አሃዳዊ መንግሥት ብቻ ነው ብለው የሚያምኑ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ፤ የለም ኢትዮጵያ ያለፈው ታሪኳን መድገም ካልፈለገች በቀር የሚያዋጣት ፌዴራላዊ መንግሥት ብቻ ነው ብለው የሚያምኑ ሰዎችም አሉ። ኢትዮጵያን እነዚህን የተለያየ አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎች የምታስተናግድ አገር ማድረግ እንችላለን፣ በዚህች የጋራ አገራችን ውስጥ እነዚህን እንደ ሁለቱ ዋልታዎች የተራራቁ አስተሳሰቦች ተግባራዊ ማድረግ ግን በፍጹም አንችልም። ስለዚህ አንድ ማድረግ ያለብን የተቀደሰ ነገር ቢኖር እነዚህን የተለያየ አቋም፣ አስተሳሰብና አደረጃጀት ያላቸውን ሰዎች ማሰባሰብና ተወያይተው ወደ አንድ የጋራ ወደ ሆነ ማዕከላዊ ሃሳብ እንዲደርሱ ማድረግ ነው እንጂ፤ በዘር መደራጀት የወያኔን ስህተት መድገም ነውና በዘር ከተደራጁ ድርጅቶች ጋር አብሮ መሥራት ወያኔን መሆን ነው እያልን፤ ግማሹን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኢትዮጵያዊነት መድረክ ላይ ጥፋ ማለት አንችልም። ደግሞስ እኛ ማነንና ነው አንዱን ጋብዘን አንዱን ጥፋ የምንለው? እንዲህ አይነት ልዩ መብት የሰጠንስ ማነው?

ዛሬ የብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ስጋት አገራችን ኢትዮጵያ ላይ የተደቀነው የመበታተን አደጋ ነው። ይህ ስጋት ደግሞ ለወያኔ ግዜ በሰጠነው ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ የሚሄድ ስጋት ነው። የሚገርመው ይህ ስጋት የወያኔን ዕድሜ ባሳጠርነው ቁጥርም እየጨመረ የሚሄድ ስጋት ነው። ህወሓት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻውን የያዘው ሥልጣን ከእጁ የሚወጣበት ቀን በተቃረበ ቁጥር ኢትዮጵያን ይበጁኛል ብሎ ለሚያስባቸው ኃይሎች እንካችሁ ብሎ በታትኗት ከመሄድ የሚመለስ ኃይል አይደለም። ምንም ነገር ሳንደባበቅ እንነጋገር ከተባለ የኢትዮጵያ የመበታተን ምንጭ ህወሓት ብቻ አይደለም። ለኢትዮጵያ አንድነት ሽንጡን ገትሮ የሚታገለው የግራና የቀኝ አክራሪውም እንደ ህወሓት ዓላማዬ ብሎ ባይሆንም በሚያደርጋቸውና በማያደርጋቸው ነገሮች የኢትዮጵያን መበታተን ያፋጥናል። ለምሳሌ መገንጠል አለብን ብለው ብረት ካነሱ ኃይሎች ጋር (በብሔር ከተደራጁ ኃይሎች ጋር) መነጋገር የለብንም ብሎ የውይይትና የድርድር በር የሚዘጋ ኃይል ሁሉ የሚሠራው ሥራ ቢኖር ሕዝብን ከሕዝብ ማራራቅና የመገነጣጠልን በር መክፈት ብቻ ነው። ወደድንም ጠላን አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ የመገንጠል ጥያቄ ያነሱ ኃይሎች አሉ። ኢትዮጵያ በፍጹም መገነጣጠል የለባትም የሚሉ ኃይሎችም አሉ። ኢትዮጵያ እንድትገነጠልም እንዳትገነጠልም የማድረጉ ቁልፍ ያለው ሁለቱም ኃይሎች እጅ ላይ ነው።

ዛሬ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረኮች ላይ የሚታየው ትልቅ ስህተት፤ አንዱ ወገን አገር አዳኝ፣ ሌላው ወገን አገር በታኝ ተደርጎ መታየቱ ነው። አሁንም ደግሜ ደጋግሜ መናገር የምፈልገው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያን ከመገነጣጠል አደጋ የሚያድናት የመገንጠል ጥያቄ ያነሳው ወገንና ኢትዮጵያ በአንድነቷ መቀጠል አለባት የሚለው ኃይል አንድ ላይ ሆነው የመፍትሔ ሃሳብ መፍጠር ሲችሉ ብቻ ነው። የተናጠል ሩጫው የሚያደርሰን ወደምንፈራው ቦታ ብቻ ነው። ደግሞም አንድን ችግር የምንፈታው ችግሩ ለምንና እንዴት እንደተፈጠረ አውቀን እራሳችንን ችግሩ ከተፈጠረበት ሁኔታ በላይ አድርገን ስንመለከት ብቻ ነው። ኢትዮጵያ ትልቅና ሁላችንንም በእኩልነት ማስተናገድ የምትችል አገር ናት። ይህንን የምናምን ኃይሎች ለኢትዮጵያ አንድነት ስንል የምንሠራው ሥራ ሁሉ ከአጉል ፈሪሳዊነት የራቀ መሆን አለበት። ደግሞም የኢትዮጵያ መገነጣጠል ሁላችንንም የሚጎዳ ነገር ነው ብለን እንገንጠል ለሚሉ ኃይሎች የአብረን እንኑር ጥያቄ ማቅረብ ያለብን እኛ እራሳችንን የ”አንድነት ኃይሎች” ብለን የምንጠራ ወገኖች ነን። ይህ ኃይል ሆደ ሰፊ ሆኖ የተለያየ አስተሳሰብና የተለያየ አደረጃጀት ካላቸው ኢትዮጵያዊያን ጋር ተገናኝቶ የኢትዮጵያን ችግሮች በጋራ ለመፍታት ፈቃደኛ ባልሆነ ቁጥር ኢትዮጵያ ህመሟ እየባሰበት ይሄዳል እንጂ ፈውስ አታገኝም። ይህ የ”አንድነት ኃይል” ነኝ ባይ ቡድን እሱ ብቻ ለኢትዮጵያ ተቆርቋሪና እሱ ብቻ የኢትዮጵያ ጠባቂ ነኝ ማለቱን ትቶ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር አብሮ መሥራት አለበት። ይህንን ማድረግ ከተቻለ ብቻ ነው ኢትዮጵያችን ነጻነቷም አንድነቷም ተከብሮ መኖር የምትችለው።

ለመሆኑ እኛ እራሳችንን የ“አንድነት ኃይሎች” ብለን የምንጠራ ወገኖች “አንድነት” ስንል አንድነት ከማን ጋር ነው? የብቻ አንድነት አለ እንዴ? ወይስ እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች መርጦ ሕዝቤ እንዳላቸው እኛም እየመረጥን ኢትዮጵያዊ የምናደርገውና የማናደርገው ሕዝብ አለ? ደግሞስ ይህንን ለማድረግ እኛ ማነን? ማነው የዚህ ዘመን ቄሳር ያደረገን? ትዝ ይለኛል ኮሎኔል መንግሥቱ ኢትዮጵያ ከእጁ እየወጣች ስትሄድ፤ ኢትዮጵያ ልትሞት ነው ... ኡኡ፣ አብዮታዊት ኢትዮጵያ ወይም ሞት ... ኡኡ፣ ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር ... ኡኡ እያለ ጆሯችንን ያደነቁር ነበር። ዛሬም አማራው ሊያልቅ ነው ... ኡኡ፣ ኦሮሞ ተጨፈጨፈ ... ኡኡ፣ ኢትዮጵያ አለቀላት ... ኡኡ የሚለው ጩኸት በየቦታው እየተስተጋባ ነው። የመንግሥቱ “ኡኡ” መንግሥቱን ወደ ዚምባቡዌ ከመፈርጠጥ እንዳላዳነው ሁሉ የዛሬውም የኛ “ኡኡ” አማራን ከዕልቂት ወይም ኦሮሞን ከጭፍጨፋ አያድነውም። አማራውንም ኦሮሞውንም ባጠቃላይ ኢትዮጵያን ከጥፋት የሚያድናት ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ኦሮሞ “አማራው ወገኔ ነው” አማራውም “ኦሮሞ ወንድሜ ነው” እያለ የሚጮኸውን ድምጽ በጥንቃቄ ስንሰማና ለዚህ ድምጽ ድርጅታዊ ምላሽ ስንሰጥ ብቻ ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ በየትኛውም መልኩ የተደራጀውን ኢትዮጵያዊ ማቀፍ እንጂ ማግለል የለብንም። ከዚህ በተረፈ አማራው ለፍትሕ፣ ለነጻነትና ለእኩልነት የሚያደርገውን ግዙፍ ትግል “ለአማራነት” ብቻ የሚደረግ ትግል ማስመሰልና፤ ከአንድ ዓመት በላይ የፈጀውንና የአያሌ ኢትዮጵያዊያንን ቀልብ ሰቅዞ የያዘውን የኦሮሞ ሕዝብ ተጋድሎ የኦሮሞ ብቻ ለማድረግ የሚደረገው ሩጫ አማራውንም፣ ኦሮሞውንም ባጠቃላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ተራ በተራ ያስጨፈጭፋል እንጂ ሌላ ምንም ፋይዳ የለውም። ከሁሉም በላይ ደግሞ አገር ቤት ውስጥ ያሉት የኦሮሞና የአማራ ወገኖቻችን እየተናገሩ ያሉት አንድነታቸውን ነው እንጂ ለየብቻ መሆናቸውን አይደለም። የኛ ተግባር ይህንን የአንድነት ድምጽ መደገፍ ነው እንጂ፤ በምንም አይነት የራሳችን አጀንዳ ሊኖረን አይችልም ... አይገባምም! የአገራችን የኢትዮጵያ አንድነት ፈተና ላይ መውደቁን ሁላችንም እያየን ነው። ይህንን አደጋ ላይ የወደቀ አንድነት ሙሉ ለሙሉ ጠግነን የኢትዮጵያን አንድነት የምናረጋግጠው “አንድነታችንን” አደጋ ላይ ጥለውታል ብለን ከምናስባቸው ኃይሎች ጋር በመደራደር ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ እራሳችንን የአንድነት ኃይሎች እያልን የምንጠራ ወገኖች ነን በዘር የተደራጁ ወገኖቻችን ያሉበት ቦታ ድረስ ሄደን እንደራደር ብለን የመጀመሪያውን እርምጃ መውሰድ ያለበን። ባለፈው ወር ዋሺንግተን ዲሲ ውስጥ ያየነው ይህንኑ መልካም ጅምር ነውና፤ ይህንን ጅምር እደግ ተመንደግ ልንለው ይገባል።

እቺ እናታችን ብለን የምንጠራት ኢትዮጵያ የሁላችንም እናት ናት። ኢትዮጵያ የእስልምና እምነት ተከታዮች ደሴት የመሆኗን ያክል የክርስትናና የዋቄፈቻ እምነት ተከታዮችም ደሴት ናት። ኢትዮጵያ የኦሮሞዎች አገር በሆነችው ልክ የአማራዎች፣ የሱማሌዎች፣ የትግሬዎችና የሌሎችም ብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት። እኛ እራሳችንን የ”አንድነት ኃይሎች” ብለን የምንጠራ ወገኖች ኢትዮጵያ ላይ አለን የምንለው ባለቤትነት እራሳቸውን በብሔር ያደራጁ ወገኖቻችን ካላቸው ባለቤትነት ቤሳ ቤስቲን አይበልጥም አያንስምም። ሁላችንም እኩል ኢትዮጵያዊያን ነን። ስለዚህ የወደፊቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት በሚደረጉ ጥረቶች ላይ ሁሉ ማንም ሰው ወይም ቡድን ከላይ ሆኖ ጋባዥና ከልካይ መሆን የለበትም፤ ሊሆንም አይችልም! ኢትዮጵያዊ የሚያደርገን የተደራጀንበት መንገድ፣ የምንናገረው ቋንቋ ወይም የምንከተለው ኃይማኖት አይደለም። ኢትዮጵያዊ የሚያደርገን ብዙ ዝርዝር ውስጥ ሳንገባ ኢትዮጵያ በምትባል አገር ውስጥ ተወልደን ማደጋችን ብቻ ነው።

እስኪ እግዜር ያሳያችሁ እኛ የአንድነት ኃይሎች የምንባል ሰዎች እንዴት አድርገን ነው እኛ ከተደራጀንበት መንገድ ውጭ የተደራጀውን ኢትዮጵያዊ አግልለን የኢትዮጵያን አንድነት ከመፍረስ የምናድነው? የኢትዮጵያ አንድነት አደጋ ላይ ወደቀ ማለት አንዳንድ ወገኖች ከኢትዮጵያ የመገንጠል ጥያቄ አነሱ ማለት አይደለም እንዴ? ታዲያ ከእነዚህ ወገኖች ጋር ተቀራርበንና ሕመማቸውን ተጋርተን ለሁላችንም የምትስማማ ኢትዮጵያን ለመፍጠር የምናደርገው ጥረት ለምንድነው እንደ ኃጢያት የሚታየው? ጥረት የሚያደርጉት ወገኖችስ ለምድነው እንደ ማርያም ጠላት የሚታዩት? በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ጥያቄ ካነሱ ወገኖች ጋር ካልተቀራረብንና ካልተወያየን ከነማን ጋር ነው የምንወያየው? ከእነዚህ ወገኖች ጋር ሳንገናኝ እንዴት አድርገን ነው የኢትዮጵያን አንድነት የምናረጋግጠው? ... በኃይል? ... በስድብ? ... በዛቻ? እሱንማ ስንት ዓመት ሞክረን ውጤቱ ምን እንደሆነ አየነውኮ! ምነው ጃል ካለፈው ስህተታችን አንማርም እንዴ?

ህወሓትንና ድህነትን የመሳሰሉ ሁለት ግዙፍ ጠላቶች ፊት ለፊታችን ላይ ተገትረው የኛ እርስ በርስ መባላት ውጤቱ ሌላ ሦስተኛ ጠላት መፍጠር ብቻ ነው። ስለዚህ ዛሬና በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ከእኛ ከኢትዮጵያዊያን የሚጠበቀው ትልቁ ሥራ የትኛውን ስትራቴጂ፣ የትኛውን ስልትና የትኛውን ሃሳብ ብንከተል ነው የታሪክ ስብራታችንን ጠግነን፣ መከፋፈላችንን አስወግደንና አንድነታችንን አጠናክረን የወደፊቷን ፍትሕ፣ ዲሞክራሲና እኩልነት የተረጋገጠባትን ኢትዮጵያን መገንባት የምንችለው የሚለውን ቁልፍ የዘመናችን ጥያቄ መመለስ ነው። ይህንን ጥያቄ ለመመለስ እነ እገሌ ከዬት ነው የመጡት፣ እነ እገሌ እንዴት ነው የተደራጁት ወይም እነ እገሌ ኃይማኖታቸው ምንድነው እያልን ከሆነ የምንሰባሰበው እራሳችንን ከመሰረታዊ የሰው ልጆች ማንነት በታች አስመዝግበንና የማይሽር የታሪክ ጠባሳ ለልጅ ልጆቻችን ትተን ወደዚህ ዓለም “መጥተው ሄዱ” ተብሎ ይነገርልናል እንጂ፤ የአገራችንን ችግር አንፈታም። የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት ከችግሮቿ በላይ መሆን አለብን። ይህ ደግሞ መደማመጥን፣ መከባበርን፣ መተማመንን፣ ሰጥቶ መቀበልን፣ የሌላውን ቁስል መረዳትን፣ መናበብንና አንዱ ለሌላው ማሰብን ይጠይቃል። ይህንን ማድረግ ከቻልን አገራችን ኢትዮጵያን ትልቋ የጥቁር ሕዝብ ደሴት ማድረግ እንችላለን። ይህንን ማድረግ እንድንችል ቸሩ እግዚአብሔር ይርዳን። አሜን!!!! ቸር ይግጠመን።

ኤፍሬም ነኝ ከአርበኞች መንደር
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ