አመልካች ነፃነት ዘለቀ

Oromo protesters (Photo: Reuters)

የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት በቅርብ እንደሚመሠረት እገምታለሁ። አሁን ይህን የሥራ ፈላጊ ማመልከቻ የማስገባው ማንም ሳይቀድመኝ ከአሁኑ የአንድ ዕጩ ቦታ ለመያዝና ተወዳድሬ ካለፍኩ ቀጥዬ የምጠቁመው የሥራ ቦታ ላይ ተመድቤ ለመሥራት ነው። የማመለክትበት የሥራ ቦታ በኢትዮጵያ የታራሚዎች አስተዳደር ዋና የኃላፊነት ቦታ ነው። ለምን እንደመረጥኩት አስረዳለሁ። በቅድሚያ ግን ...

እንኳንስ ለአሜሪካው ምርጫ በሰላም አደረሰን፤ ትራምፓውያንም እንኳን ደስ አላችሁ። ለክሊንተናውያን የተሰማኝን አዘኔታ ደግሞ በዚሁ አጋጣሚ ልግለጽ። ዓለም እንዲህ ናት። ምርጫን በመሰለ አንድ ነገር ሁለት ወገኖችን ማስደሰት አይቻልም። አንዱ ማዘኑ ሌላው መደሰቱ ያለ ነው። “እንዲህ ቢሆን ኖሮ፣ እንዲያ ባይሆን ኖሮ” እያሉ መቆላጨቱ ነገር ካለፈ በኋላ አይሠራም። ደግሞም “ሺም ታለበ መቶ ያው በገሌ ነው” ብላለች አሉ አንዲት ጊደር። ለነገሩ አሜሪካ ውስጥ ማንም ይመረጥ ማን ለአሜሪካ ጥቅምና ፍላጎት እንጂ፤ ለሌላ ደንታም የለውም - ወሳኞቹ ደግሞ በአብዛኛው ኮንግረሱና ሴኔቱ ናቸው። ወያኔ በእንቅልፉም ፓርላማ ተብየው የደናቁርት ስብስብ ላይ እንደሚያደርገው ማንም በማንም ላይ የግል ምኞቱን ለመጫን አይደፍርም። ዴሞክራሲ የሚሏት ካርድም የሚጠቅሙትን ለመጥቀምና የሚጎዱትን ለመጉዳት ካልሆነ እስከዚህ ከቁም ነገር የሚጥፉት ጉዳይ አይደለም። የዴሞክራሲ ቃል ፍጹም በማይጠራበት ሳዑዲ ዐረቢያ፤ አሜሪካ ዋና ሼሪክ ናት፤ ዴሞክራሲ እንደውዳሴ ማርያም ቀን ተሌት በሚደገምባት የወያኔ ኢትዮጵያ በዴሞክራሲ ስም የሚፈጸመውን ወንጀልና የዘር መድሎ እያወቁ እዚህም አሜሪካዎች የማፊያው ቡድን ሼሪኮች ናቸው፤ ዕንቆቅልሽ ፍጡራን መሆናቸውን ማንም ያውቃልና ኢ-ዴሞክራሲያዊ አስመሳይ ተፈጥሯቸውን የማይገነዘብ የለም።

የአሜሪካ ምርጫ በሌላው ዓለም ላይ ተፅዕኖ ስላለው ሁሉም ተንጫጭቷል፤ በምርጫው ውጤት የተከፋም የተደሰተም ሞልቷል። በአሜሪካን አገር ብዙም ባልተመለደ ሁኔታ በምርጫው ማግሥት የምርጫውን ውጤት ተቃውመው የወጡ ዜጎች ነበሩ። የፈሰሰ አይታፈስ ሆኖ ተጯጩኸው ወደየመጡበት ሄዱ እንጂ። ዋናው አትቀደም ነው። ወርቅ የተጫነች አህያ ደግሞ ደረማምሳ የማታልፈው ምሽግ የለም፤ ዶናልድ ትራምፕ ቢሊዮኔር መሆኑ አይዘነጋም።

ይህን ምርጫ በቀጥታ ስከታተል አረፈድኩ፤ ዋልኩም። “ምነው ለአንዲት ሰዓት አሜሪካዊ ሆኜ በሞትኩ!” ብዬም ለማይረባ ምኞት ራሴን ትንሽ አስጨነቅሁ። ዴሞክራሲ ፍጹምነት ባይኖረውም “ወደው የዋጡት ቅልጥም ከብርንዶ ይጥም” እንዲሉ ነውና፤ አሜሪካውያን በዚያ ዓይነት ሰላማዊ የምርጫ ሂደት የፈለጉትን ሰው ለሥልጣን ሲያበቁ ሳይ በኔው ሸፋፋ ዕድል ተበሳጨሁ። “ቀጥ ያለ ሲጠፋ ይመለመላል ጎባጣ” ያሉም ነበሩ። ይህ ምርጫ ከመነሻው ጀምሮ ብዙ አነጋግሯል።

የኛዎቹ ማፈሪያ ማፊያዎች በቅጡ ማጭበርበር እንኳን ተስኖአቸው ታች አምና 100 በ100 አሸነፍን አሉን፤ በወራት ውስጥ ግን የዚያን ግልባጭ እንደቋቁቻ እዚያና እዚህ በሚፈነዳዱ ሕዝባዊ እምቢተኝነቶቹ አማካይነት በግልጽ ተመለከትን። “እነዚህ አሳፋሪ ወያኔዎች ስለ አሳማኝ ማጭበርበርና ማምታታት የሆነ ትምህርት ቤት ገብተው ቢማሩ ምን ነበረበት” አልኩ። ማጭበርበር እኮ አርት ነው፤ ሁሉም ሰው አይችለውም። የወያኔዎች ደግሞ የተለዬ ነው። እንኳንስ እግዜርን ሰይጣንንም የማያሳምን የሌባ ዓይነ ደረቅ የቁጩ ሥራ ነው የሠሩት።

ድራማ ከሕይወት ምንጭና ባህር የሚቀዳ የእውነተኛው ዓለም ነጸብራቅ ነው። አንድ ድራማ በቁሙ ማለትም እንዳለ እውነት ሊሆን ይችላል ተብሎ አይጠበቅም - መነሻው ግን እውነት፣ ሕይወትና ውበት ነው። ጥሩ ድራማ ማለት እንግዲህ በተዓማኒነቱ ለእውነት እጅግ የቀረበና ሰውን ማዕከል ያደረገ መሆን ሲኖርበት ነው። ከዚያ ውጪ ያለው ግን ፍሬ ፈርስኪ ነው። የወያኔም የምርጫ ድራማ እንደዚሁ ነው። በኛ የቀለዱ መስሏቸው የራሳቸውን ግብዝነትና ማይምነት ነው ለዓለም የገለጡት። “51 ለ49 አሸነፍን” ቢሉና 49ኙም የነሱ እንዲሆኑ በለመዱት የሸፍጥ አሠራር ለማስመሰል ቢሞክሩ ድራማውን በተወሰነ ደረጃ ወደ ጥሩ ልቦለድነት ሊያስጠጉት በቻሉ ነበር። ቢያንስ አሳዳሪዎቻቸው በተዓማኒ ተውኔት ደራሲነታቸው ይደነቁላቸው ነበር፤ ለዚያ እንኳን ያልታደሉ የለዬላቸው ድፍን ቅሎችና የማይም ዕብሪተኞች ናቸው። ይህ የ100 ፐርሰንት ጣጣ ግን ያው ትግሬ ወያኔዎች በተፈጥሯቸው ባልጩት ድንጋይና ምንም ነገር የማይሰማቸው መሆናቸው በጃቸው እንጂ ታዛቢና ፈራጅ ቢኖር ኖሮ ጉድ ሆነው ነበር።

ወደማመልከቻየ ልምጣ - አይ አንድ ሌላ ነገር ላስቀድም መሰለኝ።

ሰሞኑን ወደገጠር ወጣ ብዬ ነበር። አማራው አምርሯል። በብዙ ቦታዎች ከነዚህ ደናቁርት ወያኔዎች ራሱን ነጻ አውጥቷል። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ነጻነታችን የተቃረበ ይመስለኛል። የእስካሁን ችግራችን ወደ ታሪክ መዝገብነት ሊቀየር የቀረን ትንሽ ጊዜ ነው። ብዙ መናገር አልፈልግም። የታዘብኩትን ነገር በሆድ ይፍጀው አልፈዋለሁ። ቢሆንም እንጸልይ!! እንጂ ...

የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ሆይ!

ኢትዮጵያችን ከወያኔ ትግሬዎች ዘረኛ የአፓርታይድ አገዛዝ ነጻ በምትወጣበት ወቅት ለዳግም ግንባታው ብዙ ዜጎች እንደሚያስፈልጓት አውቃለሁ። በየፈርጁ ለሚደረገው የመልሶ ግንባታና የተሃድሶ ሥራ አገራችን ብዙ ሰው ትሻለች። ያኔ አዲስ የሚወለድ ሰው ሣይሆን በየዓለሙ ተበትነው በጥንቃቄና በትጋት እየኖሩ የአገራቸውን ነፃነት በጉጉት የሚጠብቁ ደህነኛ ዜጎች በመብራት እየተፈለጉ ቦታ እንደሚሰጣቸው እረዳለሁ። አሁን ያለው በሙስናና በንቅዘት፣ በዘረኝነትና በድንቁርና የበሰበሰና የገማ የገለማ ቢሮክራሲ ሲጸዳ፤ ኢትዮጵያ ያለ ሰው ባዶ ትቀራለች ወይም ከነገማው ግሳንግሷ ተመሳሳይ ታሪክ እየተሠራ አሮጌው ወይን በአዲሱ አቅማዳ ተገልብጦ አገር በአዳዲስ ተሹዋሚ ደም መጣጮችና ሙሰኞች እየተሰቃየች በሌላ ዙር ንዳድ እንደተቃጠለች ትቀጥላለች። ከዚህ አኳያ መጪው የሽግግርም ሆነ ቋሚ መንግሥት ብዙ ኃላፊነት እንደሚጠብቀው መታወቅ አለበት፤ ነጻነት በራሱና ብቻውን ምንም ማለት እንዳልሆነም መረዳት ተገቢ ነው። ብዙ የተበለሻሹ ነገሮች አሉና ከአሁኑ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረጉ አይከፋም።

እኔ “እንድቀጠርበት” የማመለክትበት የማረሚያ ቤቶች አስተዳደርነት ቦታ ደግሞ ከሁሉ የበለጠ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ነው። ሁልጊዜ የሚያስጨንቀኝ ስለሆነም ነው በዚህ ዘርፍ “መቀጠር”ን የወደድኩት። (ከወያኔ እስር ቤቶች የወጡ ኅያው ምሥክሮችን ዘግናኝ የወያኔ እስረኛ አያያዝ ተከታተሉና ለምን ይህን ቦታ እንደመረጥኩ ተረዱልኝ።)

በመሠረቱ በአገራችን አንድ እስረኛ ቀርቶ ማንም ተራ ዜጋ እንደሰው አይቆጠርም። ይህ ደግሞ እኔ ባየኋቸው በሁሉም ሥርዓቶች ውስጥ የነበረና፤ አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ ተባብሶ የቀጠለ ነው። ያደለው ቀሪዎቹን እንስሳትም እንስሳዊ መብታቸውን ያከብራል፤ እኛ ግን እስረኛን እንደሰው የማይቆጥር መንግሥት እየገጠመን ክፉኛ ተቸግረናል። አሳዛኝ ነው።

እንደእውነቱ ማረሚያ ቤት ብሎ ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ የለም። ያለው ሲዖል ነው፤ ከሲዖልም ሳይበልጥ አይቀርም። እኔ ታስሬ ባላውቅም ታስረው ከወጡ ሰዎች እንደምሰማውና የታሰሩ ሰዎችን የስቃይ ታሪክ በተለይ የፖለቲካ እስረኞች ላይ የሚደርሰውን ስቃይና መከራ ስሰማ እኔ ራሴ መፈጠሬን እረግማለሁ። ሰው በሰው ላይ ለምን ይህን ያህል እንደሚጨክንም ይደንቀኛል። አንድ “መርማሪ” በማያውቀው ሰው ላይ - የግል ጠብም በሌላው “ንጹሕ ዜጋ” ላይ እንዴት ድብደባ ይፈጽማል? እንዴትስ ፀያፍ ቃላትን በመጠቀም በአምሣሉ የተፈጠረ ሰውን ያዋርዳል? የአገራችንን የእስረኛ አያያዝ ከአውሮፓና መሰል የሠለጠኑ አገሮች የእስረኛ አያያዝ ጋር ሳወዳድር፤ በኔ አገር አሳሪዎች ከሰው በታች የሆነ ዐውሬያዊ ተፈጥሮ አዝናለሁ። ምን ነካን?

የአሁኑ የወያኔዎች የእስረኛ አያያዝ ደግሞ ከየትኛውም ዓለም የተለዬ ነው፤ ሁላችሁም ስለምታውቁት ዝርዝሩን መናገሩ ጊዜ ማባከን ነው። (አሳሪዎቻችንን ሳይጠጡ እያሰከሩ እንዲህ የሚሠሩትን ያሳጣቸውና በጭካኔ ያሳበዳቸው ዘረኝነቱ ይመስለኛል።)

ስለዚህ እኔ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደርነት ሥራ ቢሰጠኝ፤ የተፈረደበትም ሆነ ያልተፈረደበት በሕግ ጥላ ሥር የሚገኝ ዜጋ ተጨማሪ ጥፋት እንዳያጠፋና ኅብረተሰቡን እንዳያውክ ከእንቅስቃሴ ከማገድ ውጪ ሰብዓዊና የዜግነት መብቱን ገፍፎ በጠባብ ክፍል ስፍር ቁጥር የሌለው እስረኛ በማጨቅ በግርፋትና በወፌላላ ማሰቃየትን አስቀራለሁ። ዘመናዊ ትምህርት የተማሩ የወንጀል ምርመራ ባለሙያዎችን እጠቀማለሁ እንጂ፤ ዱላና አለንጋ ጠረጴዛቸው ላይ አስቀምጠው በጉልበት “የሚመረምሩ” ማይማን ገራፊዎችን ሥራ ላይ አላውልም። ሣይንሣዊ የወንጀል ምርመራ ዘዴን ተግባራዊ ባለማድረግ በኃይልና በጉልበት በሚገኝ መረጃ ሰዎች ለቅጣትና ለሞት እንዳይዳረጉ አደርጋለሁ። በሙስናና በተዛባ ፍርድ ዜጎች መድሎ እንዳይደረግባቸው አጥብቄ እሠራለሁ። ኢትዮጵያ የእስረኞችም እንደሆነች በተግባር አሳያለሁ። ወንጀለኝነት ሰብዓዊ እንጂ የአንድ ሰው ወይም የአንድ ጎሣ ልዩ መታወቂያም እንዳልሆነ አስተምራለሁ። በጥላቻና በቂም በቀል የሚከናወን የፍርድ ሂደት ዜጎችን ባለውና በሌለው፣ በ“ትልቅ” እና በ”ትንሽ”፣ በተማረና ባልተማረ፣ በኃይማኖትና በፆታ፣ በጎሣና በዘር ወዘተ ... ስለሚከፋፍል ትክክለኛ ፍትሕ እንዲበየን የበኩሌን ጥረት አደርጋለሁ። ...

ስለዚህ በዚህ ቦታ ላይ ተመድቤ አገሬን እንዳገለግል ይፈቀድልኝ ዘንድ ከአሁኑ አመለክታለሁ።

አመልካች ነፃነት ዘለቀ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ