Clinton and Trumpየአሜሪካ ምርጫ - ዶናልድ ትራምፕ ወይስ ሂለሪ ክሊንተን - ምርጫው በተስቦና በኮሌራ መሃከል እንደመምረጥ ያህል ዐይነት ነው!!

ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)

መግቢያ
የዛሬ ስምንት ዓመት ባራካ ኦባማ ለፕሬዚደንትነት ምርጫ ለውድድር ሲቀርቡ፣ ከፕሪመሪው ጀምሮ የነበረውን የምርጫው ሂደት እዚህ አውሮፓ ሆነን በየሰዓቱ ሁኔታውን በጥብቅ እንከታተል ነበር። በማያጠራጥር መልኩ የብዙዎቻችን ፍላጎትና አድልዎ ለባራክ ኦባማ ቢሆንም፤ ባራክ ኦባማ ያንን አስቸጋሪ የፕሪመሪ ውድድር አልፈውና ተፎካካሪዎቻቸውን አሸንፈው የዲሞክራቲክ ፓርቲውን በመወከል ለፕሬዚደትነት ምርጫ ይቀርባሉ ብሎ የገመተ አልነበረም።

የመጨረሻ መጨረሻ ወይዘሮ ሂለሪ ክሊንተን በአሸናፊነት በመውጣት ፓርቲያቸውን በመወከል የሪፐብሊካን ፓርቲን ከሚወክለው ጋር ለውድድር ይቀርባሉ የሚል ግምት ነበረን። አሁንም ቢሆን የኢንስቲቱሽናል ሬሲዝምነትና አጠቃላይ ሬሲዝምነት በነገሠበት በአሜሪካን ሕብረተሰብ ውስጥ አንድ ጥቁር አሜሪካዊ ለፕሬዚደንትነት ምርጫ በመወዳደር በአሸናፊነት ይወጣል ብሎ መገመት በጊዜው የሚታሰብ ጉዳይ አልነበረም።

ቀደም ብሎ ምርጫው ከመካሄዱ በፊት ባራክ ኦባማ በአንዳንድ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ተጋብዘው በመቅረብ አሜሪካን በተለይም ቀደም ብሎ የነበራትን የኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ የበላይነት ስለማጣቷና፣ ገበያውም ከቻይና በሚመጡ ምርቶች ስለመጥለቅለቁ ይሰጡት የነበረው አስተያየት በጣም የሚያረካ ነበር። በእሳቸውም አባባል፣ ርካሽ የሰው ጉልበትን ለመጠቀም ሲባል ብዙ ኢንዱስትሪዎች እየተነቀሉ ወደ ቻይናና እንደ ሜክሲኮ የመሳሰሉ አገሮች በመወሰዳቸው ከውስጥ የኢንዱስትሪ መስኩ መዳከሙ ብቻ ሳይሆን፣ የውጭ ንግዱም እንደተጎዳና፣ አሜሪካም ከአበዳሪነት ወደ ተበዳሪነት በመሸጋገር አስቻጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደወደቀች የሚሰጡትን ትንተና ላዳመጠ በእርግጥም እኚህ ሰው ለፕሬዚደንትነት ተወዳድረው ካሸነፉ የኢንዱስትሪ መስኩን ማስተካከል ብቻ ሳይሆን በጊዜው በከፍተኛ ደረጃ አሽቆልቁሎ የነበረውን የስራ አጥ ቁጥር ሊቀንሱ ይችላሉ የሚል እምነት ነበረን። በዚህም ምክንያት የሰራተኛው ገቢ በማደግ በጊዜው የነበረውን ማኅበራዊና ባህላዊ ቀውስ እስከተወሰነ ደረጃም ሊቆጣጠረው ይችላል የሚል የተሰፋ ብልጭታ ይታያል የሚል ግምት ነበረን። በተለይም አንድ ጥቁር ሰው የነጭ የበላይነት በሰፈነበት አገር ፕሬዚደንት ሆኖ ሲመረጥ የጥቁሩ ሕዝብም ኑሮ የተሻለ እምርታን በማግኘት ጥቁሩ በራሱ ላይ የበለጠ እምነት ሊያገኝ ይችላል ብለን ያሰብን ጥቂት አልነበረም።

ባራክ ኦባማ የመጨረሻ መጨረሻ ውድድሩን አሸንፈው ለፕሬዚደትነት ሲቀርቡና ከሪፓብሊካኑ ከሜኬን ጋር ተወዳደረው በከፍተኛ የሕዝብ ቁጥርና በኤሌክቶራል ድምጽ ሲያሸንፉ፣ ውጤቱ በአሜሪካን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ የሆነ አዎንታዊ ተፅዕኖም እንደሚኖረው መገመቱ ቀላል አልነበረም። እንደሚታወቀው ባራክ ኦባማ ቀደም ብለው በፕሬዚደንት ቡሽ የሚመራው አስተዳደር በኢራክ ላይ ያወጀውን ጦርነትና ወታደርም የመላኩን ጉዳይ አጥብቀው የተቃወሙ ነበሩ። ስለሆነም የሳቸው መመረጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምን የሚያስቀደም ፖለቲካና፣ በተለይም ደግሞ የሶስተኛው ዓለም ተብለው ለሚጠሩ አገሮች ወደ ውስጥ ለዕድገት የሚያግዛቸው የሚያፈናፍን ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል የሚል አስተሳሰብ በጭንቅላታችን ውስጥ ይብሰለሰል ነበር። እነዚህና ሌሎችንም የሰውየውን አቀራረብ ለተመለከተ የአሜሪካን ፖለቲካ ከአግሬሲብ ባህርይው በመላቀቅ በአገሮች መሀከል ”በእኩልነትና በመከባበር“ ላይ የተመሰረተ ግኑኝነት እንደሚፈጠር ለማመን ተቃርበን ነበር።

የፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ የስምንት ዓመቱ የፖሊሲ ውጤት!

ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ከተመረጡና በጥር ወር 2009 ዓ.ም ሥልጣናቸውን በመሃላ ከተረከቡ በኋላ የጠበቃቸው የቤት ስራ እጅግ ከባድ ነበር። በመጀመሪያ ደረጃ የግል ባንኮችና የእንሹራንስ ኩባንያዎች ለቤት መስሪያ ወይም መግዢያ ለተወሰነው ሕዝብ በማበደር የአሜሪካንን ኢኮኖሚ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የከተቱበት ሁኔታ ነበር። በዚህም ላይ አብዛኛው የአሜሪካን ኢኮኖሚ ከ1980ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ከኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ ይልቅ በአገልግሎት ላይ እየተመካ በመምጣቱ ይህ መስክ የስራ እድል ለመክፈት የነበረው ኃይል በጣም ውስን ነበር። በዚህም የተነሳ አሜሪካ ወደ ውጭ ከምትልከው ይልቅ ወደ ውስጥ የምታስገባው ከፍ እያለ በመምጣቱ የንግድ ሚዛኗ የተናጋበት ወቅት ነበር። ስለሆነም የአሜሪካን መንግሥት፣ የመንግሥት ቦንድን በማደል ከውጭው ዓለም ብድር በመቃረም በዕዳ የተተበተበበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። በዚህ ላይ ደግሞ የቡሽ መንግሥት ወደ ኢራክና አፍጋኒስታን ወታደሮችን በመላክ ለጦርነት ወደ አንድ ትሪሊዮን የሚቆጠር ያህል ገንዘብ በማውጣቱ ወደ ውስጥ የስራ መስክ ለመክፈት በሚያስችሉ ፕሮጀክቶችና ኢኮኖሚውን ሊያንቀሳቅሱ በሚችሉ የኢንዱስትሪ መስኮች ላይ የመዋዕለ-ነዋይ እጠረት በመከሰቱ ጠቅላላው ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ተናግቶ ነበር። በዚህም ምክንያት የተነሳ አገሪቱ በከፍተኛ የማኅበራዊ፣ የሕብረተሰብና የባህል ቀውስ ውስጥ በመውደቅ ከዚህ ሁኔታ ለማንሰራራት አዲሱ የባራከ ኦባማ አስተዳደር በቀላሉ ሊፈናፈን የሚችልበት ሁኔታ አልነበረውም።

የውጭ ፖለቲካውን ስንመለከት፣ ከ1989 ዓ.ም. በኋላ የተፈጠረው አዲስ ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ ሁኔታ አሜሪካን እንደፈለገው የሚፈነጭ ስለመሰለው በተለይም አልታዘዙኝም ያላቸውን አገሮች ሁሉ በመተናኮል ወደ ጦርነት ውስጥ የገባበት ጊዜ ነበር። አክራሪ ”ወግ አጥባቂዎች“ (Conservative-Neo-Cons) በፕሬዚደንት ቡሽ የመንግሥት አስተዳደር ውስጥ የተካተቱና በፖሊሲ ደረጃም ተደማጭነት ስለነበራቸው፣ ከእንግዲህ ወዲያ ዘመኑ የአሜሪካን ዘመን ነው በማለት ያለ የሌለ ኃይላቸውን በሙሉ በጦርነትና አገሮችን በማተረማመስ ላይ በማዋል የዓለምን ሕዝብ የመኖርና ያለመኖር ዕድል ወሳኝ የሆኑበት ጊዜ ነበር። በዚህም ምክንያት የተነሳ ዩኒላተራል ፖለቲካን በመከተል ዓለም አቀፋዊ ውዝግቡ እንዲጦፍና፣ የአሜሪካን ትላልቅ የጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያዎችና የዘይት አውጭ ድርጅቶች አገሮችን በማመስና በመዝረፍ የትርፍ ትርፍ ለማካበት የሚያስችላቸው አመቺ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው ነበር። ከዚህም ባሻገር የኒዎኮንስ ስትራቴጂ ከመበታተን የተረፈችውን ራሺያን በመክበብና እንደገና የተቀረውን በመበታተን ኦይራሺያን የሚባለውን በጥሬ-ሀብት ክምችት የሚታወቀውን የራሺያን ግዛቶች በቁጥጥር ስር ማዋል አንደኛውና ዋናው ስትራቴጂያቸው ስለነበር አትክሮአቸው በሙሉ አሜሪካን በሁሉም አገር በሚለው መርሆቻቸው የዓለምን ማኅበረሰብ በማወካብ ላይ ነበሩ። በብዙ አገሮችም ይህን የበላይነትን ፖሊሲያቸውን ተግባራዊ የሚያደርግና ከውስጥ ሆኖ ደግሞ አገሩን የሚያምስ አዳዲስ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና እንዲሁም የሚሊተሪ ኤሊት በመኮትኮትና በመንግሥት መኪና ላይ በማስቀመጥ የበላይነታቸውን ለረዥም ጊዜ ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ዝግጅት ለማድረግ በቅተው ነበር። ከዚህም በመነሳት ብቸኛውና አማራጭ የሌለው ዓለምን እንደፈለገው የሚያሽከረክር ኃያል መንግሥት ሆኖ ለመውጣት የስለላና የሚሊታሪ ኢንዱስትሪ ውስብስብነቱን ያጠናከረበት ጊዜ ነበር፤ ነውም። ይህ ዐይነቱ የውጭ ፖለቲካ ግን ወደ ውስጥ የአሜሪካንን ሕብረተሰብ በሁሉም አቅጣጫ እያዳከመው እንደመጣና፣ የወንጀለኛውም ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ እንዳደረገው መገንዘብ ይችላል።

ባራክ ኦባማ ሥልጣንን ሲረከቡ እነዚህን ሁሉ ማስተካከልና መጠገን ነበረባቸው። በመጀመሪያ ደረጃ እጅግ የተዳከመውን የባንክ መስክና የመኪና አምራች ኢንዱስትሪ እንደገና እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ ወደ $ 800 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚጠጋ ወደ ኢኮኖሚው ውስጥ አፍሰዋል። በዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲም ቢያንስ የመኪና ኢንዱስትሪው እንዲያንሰራራ አመቺ ሁኔታ ፈጥረዋል። ይሁንና ግን የካቢኔት ስዎቻቸውን ስንመለከት አብዛኛዎቹ ከዎል ስትሪት ጋር በጥብቅ የተሳሰሩና የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክ ፖሊሲን በማራመድ የሚታወቁ ኢኮኖሚስቶች ስለነበሩ፣ በከፍተኛ ደረጃ የስራ መስክ ሊከፍቱ የሚችሉ ማዕከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችን የሚደጉም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ሊያደርጉ አልቻሉም። በዚህም ምክንያት የተነሳ አብዛኛው ገንዘብ የፈሰሰው ወደ አክስዮን ገበያ (Stock market) ላይ ሲሆን፣ ተጠቃሚዎችም ቀደም ብለው አየር በአየር ንግድ የካበቱ ሀብታሞች ናቸው። ባራክ ኦባማ ሥልጣን ከያዙ ጀምሮ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ የስራ መስክ እድል ቢከፈትም፣ ፖሊሲው ግን በሀብታምና በዝቅተኛው የሕብረተሰብ ክፍል መሀከል የነበረውን የገቢና የሀብት ልዩነት ዝቅ ከማድረግ ይልቅ በከፍተኛ ደረጃ ልዩነቱ እንዲሰፋ ነው ያደረገው። ከዚህም በላይ የማዕከላዊ ባንኩ የሚከተለው የዜሮ ወለድ (Zero Interest) የገንዘብ ፖሊሲ የበለጠ የጠቀመው የአየር በአየር ንግድ ላይ የተሰማሩትን ኩባንያዎችና ግለሰቦችን ስለሆነ በዝቅተኛ ደሞዝ የሚተዳደረውን የሕብረተሰብ ክፍል ከከተማ ውስጥ ተገፍትሮ እንዲወጣ ለማድረግ በቅቷል። በዚህ ዓይነቱ የኢኮኖሚና የሞነቴሪ ፖሊሲ እንደ ኒዎርክ በመሳሰሉት ትላልቅ ከተማዎች ውስጥ 19 ካሬ ሜትር አፓርትሜንት ኪራዩ ከ900 $ ዶላር በላይ ነው። ከዚህም ባሻገር ይህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክ ፖሊሲ በአጠቃላይ ሲታይ የኑሮ ውድነት እንዲናር ያደረገና፣ አብዛኛው የአሜሪካን ሕዝብም በክሬዲት ካርድ ላይ የባሰውኑ ጥገኛ እንዲሆን ነው ያደረገው። ባራክ አቦማ ከብዙ ጊዜ ትግል በኋላ ተሳካላቸው የሚባለው ኦባማ-ኬር (Obama care) የሚባለውን ለ12 ሚሊዮን ሕዝብ የጤንነት ኢንሹራንስ ተግባራዊ ማድረጋቸው ነው። ይሁንና ይህ ጥሩ የሆነውን ያህል በቀረጥ የተደጎመ ባለመሆኑና፣ በጣምም ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረድ የበዛበት በመሆኑ እስከዚህም ድረስ አብዮታዊ እንዳልሆነ ብዙ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የባራክ ኦባማን የውጭ ፖለቲካ ስንመለከት፣ ከቡሽ የአግሬሲብ ፖለቲካ የተላቀቁ ቢያመስላቸውና የተወሰነ የወታደር ኃይል ከኢራክ ቢያስወጡምና የመጨረሻ መጨረሻም ከኢራን መንግሥት ጋር የአቶም ስምምነት ቢያደርጉም፣ እጅግ በረቀቀ መንገድ አፍጋኒስታን፣ ሊቢያና ሶሪያ ውስጥ የተቀጣጠለውን ጦርነት እንዲፋፋም በማድረግ የመንግሥት ለውጥ (Regime Change) እንዲመጣ ከሚያደርገው የአሜሪካን ስትራቴጂ በፍጹም ለመላቀቅ እንዳልቻሉ እንገነዘባለን። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የኢስላሚክ መንግሥት (IS) የሚባለውን የገዳይ ድርጅት በመሳሪያ፣ በምክርና በገንዘብ በመደገፍ ለብዙ መቶ ሺህ ሕዝብ ማለቅ ምክንያት ሊሆኑ ችለዋል። ይህም ፖሊሲያቸው ከሌሎች የአውሮፓ መንግሥታት፣ በተለይም ከፈረንሳይና ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር በማበር በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሶሪያውያን አገራቸውን ለቀው ወደ አውሮፓ እንዲጓዙ ለማድረግ በቅቷል። ራሺያን ለማዳከምና ብሎም ለመበታተን ሲባል በዩክራይን ላይ የተከተሉት የመንግሥት ግልበጣ ፖሊሲና የባልቲክ መንግሥታትን (Baltic States) አስታጥቆና ወታደር ልኮ ራሺያን መክበብና፣ የሶስተኛው ዓለም ጦርነት እንዲነሳ መቀስቀስ ባራክ ኦባማ የዴሞክራቲክ ፓርቲን ወክለው ሥልጣን ላይ ቢወጡም ፖሊሲያቸው በሙሉ በምንም ዐይነት ዲሞክራሲያዊ ነው የሚያስብለው አንዳችም ነገር የለም። ፓርቲያቸውም ሆነ እሳቸው የአሜሪካን የፖለቲካ ኤሊት አካል በመሆናቸው የአሜሪካንን የበላይነት ከማስቀደምና አገሮችን አዳክመው ከመበታተን እንደማይመለሱ ከሊቢያና ከሶሪያ መማርና ማየት ይቻላል። ስለሆነም የስምንት ዓመቱ አገዛዛቸው በዓለም ታሪክ ውስጥ ስላምን፣ መረጋጋትን፣ በአገሮች መሀከል መከባበርንና ለዕድገት አመቺ ሁኔታን ፈጥሮ ያለፈ ሳይሆን፣ የበለጠ አለመረጋጋትንና፣ መንግሥታት የበለጠ አሸባሪዎችን መዋጋት አለባቸው በሚለው ፈሊጥ ላይ አትኩራቸውን እንዲቀይሩ ያደረገና፣ ወደ ወስጥ በማኅበራዊና በኢኮኖሚ ግንባታ ላይ እንዳይሰማሩ ያደረገ እጅግ አደገኛ ፖሊሲ ነው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። በባራክ አቦማ የአገዛዘ ዘመን የዓለም ሕዝብ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ያመራ ሳይሆን የበለጠ ወደ ጨቋኝና ወደ መዝባሪ ሥርዓት ያመራ ነው ብሎ መናገር ይቻላል።

ክሊንተን ወይም ትራምፕ - ተስቦ ወይስ ኮሌራ!

በምርጫው የውድድር ሂደት ውስጥ እዚህ ጀርመን አገር የሚወራው ወሬ በወይዘሮ ሂለሪ ክሊንተንና በዶናልድ ትራምፕ መሀከል ያለውን ልዩነት የነቃው ምሁር ይገልጽ የነበረው በተስቦና በኮሌራ በሽታ መከሀከል እንደመምረጥ ያህል ነው እያለ ነበር። ሁለቱም የወረርሽኝ በሽታዎች የመጨረሻ መጨረሻ ሰውን አሰቃይተው የሚገድሉ ስለሆነ ሁለቱም ለምርጫ የሚቀርቡ አይደሉም እንደማለት ነው። ይሁንና በሚዲያ ዘንድና በፖለቲኮኞች መሀከል የነበረው አድልዎ ለወይዘሮ ክሊንተን ነበር። ዶንላድ ትራምፕ በሚሰነዝሩት ያልተገራ አውራርና፣ በተለይም ደግሞ ዝቅተኛውን የህበረተሰብ ክፍልና አካለ ስንኩሉ ላይ ወይም ሌላ የሴክሹዋል ኦሬየንቴሽን ባላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ ይሰነዝሩ የነበረው አላስፈላጊ ቃላቶች የመመረጥ እድላቸውን በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ እንደሚያደርገው መገመቱ ይህንን ያህልም ከባድ አልነበረም። በተጨማሪም ደግሞ በነፃ ንግድና (TTIP) በሰሜን አትላንቲክ የጦር ስምምነት ላይ ያላቸው አመለካከትና፣ አሜሪካ መጀመሪያ (America First) የሚለው አባባለቸው የጦርነቱ ስምምነት አባል አገሮችን ከፍተኛ የመንፈስ አለመረጋጋት ውስጥ እንደከተታቸው ለመከታተል ችለናል። በዚህም ላይ ፕሬዚደንት ፑቲንን ማድነቃቸውና፣ አማካሪያቸውም ከፕሬዚደንት ፑቲን ጋር የጠበቀ ግኑኝነት ነበረው ብሎ ስለሚታማ የውጭ ፖሊሲያቸው የበለጠ የአውሮፓ መንግሥታትን ሚና የሚያዳክም የሚያስመስለው ነበር። በዚህ ዐይነቱ አባባላቸው ወደ ፊት ይቀጥሉ አይቀጥሉ ከአሁኑ መገመቱ አስቸጋሪ ነው።

ወደ ወይዘሮ ክሊንተን ስንመጣ ከፈተኛ የፖለቲካ ልምድ እንዳለቸው የሚነገርና፣ የአሜሪካን የፖለቲካ ኤሊት አካል (Establishment) እንደመሆናቸው መጠን በተለይም ወደ ውጭ የበለጠ አግሬሲብ ፖሊሲ ለመከተል እንደሚችሉ ግልጽ ነበር። ባላቸው ፕሬዚደንት ቢል ክሊንተን ሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ቢል ክሊንትን ይጎዝላቢያ እንድትበታተን በቦንብ ሊደበድቡ ሲቃጡ አንደኛውና በግልጽ የማይታየው አማካሪያቸው ሚስታቸው ወይዘሮ ክሊንተን እንደነበሩ መገመቱ ይህንን ያህልም ከባድ አልነበረም። የውጭ ጉዳይ ምኒስተርም ከሆኑ በኋላ ከፕሬዚደንት ኦባማ ጋር የነበራቸው ልዩነት ይህ ዐይነቱ አግሬሲብና የጦርነት ፖሊሲያቸው እንደሆነ አንዳንድ ተንታኞች ይናገራሉ። በተለይም ፕሬዚደንት ጋዳፊ እንዲገደሉና ሊቢያም እንድትበታተን ከፍተኛውን ሚና የተጫወቱት እኚህ ሴት እንደነበሩ በግልጽ ይታወቃል። ሶሪያንንም በቀጥታ ለመደብደብ ፕሬዚደንት ኦባማን ቢገፋፉም፣ ፕሬዚደንት ኦባማ የተከተሉት ፖሊሲ ግን የበለጠ ”ሲስተማቲክ“ በሆነ መልክ አሸባሪዎችን በመደገፍ የፕሬዚደንት አሳድን መንግሥት አዳክሞ እሳቸውና የአውሮፓ መንግሥታት ”ለዘብተኛ“ የሚሏቸውን ”ተቃዋሚ ኃይሎችን“ ሥልጣን ላይ ማውጣት ነበር። በመሰረቱ በሁለቱ መሀከል የነበረው ልዩነት የአመለካከት ሳይሆን የአካሄድ ወይም የስትራቴጂ ብቻ ነው።

ያም ሆን ይህ ወይዘሮ ክሊንተንን ይህን ያህልም ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ የሚያሰኛቸው አንዳችም ነገር የለም። በብዙ ሺህ ድሮች ከዎል-ስትሪት (Wall Street) ጋር የተሳሰሩና ለአንድ የማይረባና የአንድ ሰዓት የውሸት ንግግር እስከ 600 ሺህ ዶላር የሚከፈላቸው ነበሩ። ወደ ውጭ ደግሞ ከሳውዲ አረቢያዊ የሞናኪ አገዛዝና የዋሀቢትን የእስልምና ሃይማኖት ከሚያስፋፋው ጋር የጠበቀ ግኑኝነት የነበራቸውና፣ አማካሪያቸውም አንድ የሳውዲ አረቢያ ሴት እንደነበረች በግልጽ ይታወቃል። ወይዘሮ ክሊንተንም ከሳውዲ አረቢያ የሞናርኪ መንግሥት ለፕሬዚደንት ምርጫ ካምፔይናቸው 900 ሚሊዮን ዶላር እንደተቀበሉ ይነገራል። ጎልድ ማን ሳክስ የሚባለው፣ ገንዘብ ከሀብታሞች እየሰበሰበ ቁማር የሚጫወትና፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ በጥሬ-ሀብት ዘረፋ ውስጥ ከሚቀራመተው ጋር ያላቸው ግኑኝነት በጣም የጠበቀ ከመሆኑ የተነሳ፣ ተጋብዘው ባደረጉት ንግግር ላይ በአሜሪካን አገር በ2007/2008 ዓ.ም ለደረሰው የዕዳና የቤት ስራ ቀውስ (Subprime crisis) ዋናው ተጠያቂ የሰራተኛው መደብ ነው በማለት የውሸት ንግግር አድርገው ወደ 600 ሺህ ዶላር ተቀብለዋል። ይህንና ሌሎች ፀረ-ዲሞክራቲክ ባህሪያቸውን ለተመለከተና፣ ክሊነተን ፋውንዴሽን በመባል በሚታወቀው በተለይም በሃይቲ የመሬት መንቀጥቀጥ የተነሳ ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ 1,76 % ብቻ መሄዱን ስንሰማ እሳቸው ቢመረጡ የአሜሪካን ሕዝብ አዲስ የበራ ዕድል ሊገጥመው እንደማይችል መገመት ይቻላል። ያም ሆነ ይህ እንደቋመጡትና፣ ሚዲያውና ሊበራል የሚባለው ሁሉ ለሳቸው ያላደላውን ያህል 09.11.2016 ዓ.ም የምርጫው ውጤት ሲነገር እሳቸውም ሆነ እኛ ራሳችን ማመን ነው የተሳነን። ዶናልድ ትራምፕ በመራጩ የድምጽ ቁጥር ሳይሆን በኤሌክቶራል ድምጽ (Electoral Vote) ማሸነፍ እንደቻሉ ሊነገርና ሊበስር ችሏል። ዶናልድ ትራምፕን የምደግፍ ባልሆንም በወይዘሮ ክሊንተን 45ኛው ፕሬዚደንት ሆኖ አለመመረጥ ከፍተኛ ደስታ ነው የተሰማኝ። በተለይም የዲሞክራቲክ ፓርቲን ስም አንግቦ ውሸት የሚያወራና፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጦርነትን የሚያስፋፋ ግለሰብም ሆነ ድርጅት ከማራምደው የሰብአዊነትና የዴሞክራቲክ፣ እንዲሁም የእኩልነት መርሆች ፕሪንሲፕልስ ጋር የሚጣጣሙ ስላይደለ ባለመመረጣቸው ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል። በሳቸውም አለመመረጥ የክሊንተን ዲናስቲ ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ወደ መቃበር ዓለም እንዲጣል ተደርጓል።

የዶላንድ ትራምፕ ፕሬዚደንት ሆኖ መመረጥ ያስፈራቸውም ያስደሰታቸውም አሉ። በአውሮፓ የፖለቲካ መስክ ውስጥ ፖፑሊስቶችና የቀኝ ፖለቲካ አራማጆች ደስ ሲላቸው፣ ወይዘሮ ክሊንተን እንዳይመረጡ የማይናቅ ሚና የተጫወቱት የራሺያ መንግሥት ተወካዮች በጣም ነው ደስ ያላቸው። ከግብጹ ፕሬዚደንት አሲስ ቀጥሎ የደስታ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዚደንት ፑቲን ናቸው። ምናልባትም ከፕሬዚደንት ፑቲን ጋር የቅርብ ግኑኝነት አላቸው የሚባሉና በራሺያ የውጭ ቴሊቪዢን ላይ ቀርበው የሚጠየቁት ቀደም ብለው የመከላከያ ጦር አባል የነበሩት ግለሰብ የዶናልድ ትራምፕ የካቢኔት አባል ከሆኑ ከራሺያ ጋር የሚኖራቸው ግኑኝነት ጦርነትን በማራገብ ሳይሆን፣ በዲፕሎማሲ ችግርችን መፍታት ይሆን ይሆናል የሚል ግምት አለ። ያም ሆነ ይህ የአውሮፓ መንግሥታት፣ በተለይም የኔቶ (NATO) ዋና ጸሀፊና የጀርመን መከላከያ ምኒስተር ከፍተኛ መደናገጥ እንደሚታይባቸው እንመለከታለን። በተለይም ራሺያ የጦር መሳሪያዎችዋን በጣም ውስብስብ ካደረገች ወዲህና፣ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ታንክ ካመረተችና እንደ S-400 የሚባለውን ተንቀሳቃሽ የሆነ ከሁሉም አየር ጋር የሚስማማ የረጅም ርቀት የሚጓዝ በመሬትና በአየር ላይ የሚንቀሳቀሱ ተዋጊ ጀቶችን የሚያሳድደውና፣ በተለይም ደግሞ የሚተኮሱ ፈንጂዎችን የሚያከሽፍ መሳሪያ ሰርታ ከተከለች ወዲህ የአውሮፓ መንግሥታትም ሆነ አሜሪካ በፍርሃት ውስጥ ይገኛሉ። ራሺያን በቀላሉ ሊቋቋሙ እንደማይችሉ ለመገንዘብ ችለዋል። አሁን ደግም መጪው ፕሬዚደንት የተናገሩትን የውጪ ፖሊሲያቸውን ተግባራዊ ካደረጉ የኔቶ አላስፈላጊነት የበለጠ ግልጽ እየሆነ ሊመጣ ይችላል። ይህ ጉዳይ ግን ወደፊት የሚታይ ነው። የአሜሪካን የውስጥ ኢንስቲቱሽኖች፣ ፔንታጎን፣ ሲአይኤና ሌሎችም ወደ አስራስምንት የሚጠጉ የስለላ ድርጅቶና፣ እንዲሁም ኮንግረሱን በተመራጩ ብዛት የሚመሩት የሪፓብሊካን ፓርቲ አባላትና የአሜሪካን ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በቀላሉ መፈናፈኛ ላይሰጧቸው ይችላሉ።

ወደ ውስጥ ፖለቲካቸው ስንመጣ በተለይም ካለፈቃድ የሚኖረው ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ፍርሃት እንደለቀቁ ይታወቃል። ሰሞኑን እንደሰማነው ወንጀለኛ ተብለው የሚታወቁ እስከ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ የውጭ አገር ስዎችን፣ በተለይም ከሜክሲኮና ከተቀሩት የማዕከለኛውና የላቲን አሜሪካን አገሮች የመጡ ሰዎችን እንደሚያባርሩ ተናግረዋል። በተረፈ የኢኮኖሚ ፖሊሲያቸውን ለተመለከተ የዕገዳ ፖሊሲ (Protectionist Policy) እንደሚከተሉና የኢንፍራስትራክቸር ፖሊሲ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ይህንን ፕሮጀክታቸውን እንዴት አድርገው ፋይናንስ እንደሚያደርጉ ግን ግልጽ አይደለም። የቀረጡን መጠን ክ35% በመቶ ወደ 15% ዝቅ የሚያደርጉ ከሆነ መንግሥት በቀረጥ አማካይነት የሚያገኘው ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ ይላል ማለት ነው። በሌላ ወግን ግን አጠቃላዩ የኢኮኖሚ ፖሊሲያቸው የኔዎ-ሊበራል ወይም ሌላ ይሁን የሚታወቅ ነገር የለም።

ያም ሆነ የፕሬዚደንቱን የወደፊት ፖሊሲ ከአሁኑ አፍን ሞልቶ እንደዚህ ይሆናል ብሎ መናገር በፍጽም አይቻልም። አንድ ማለት የሚቻለው ነገር በአሜሪካን ምድር የበለጠ ዲሞክራሲና ሰላም አይሰፍንም። ያለው ሥርዓትም የበለጠ ይጠናከራል እንጂ በመላላት በመንግሥት መኪናና በተለያዩ ኢንስቲቱሽኖች ዘንድ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ሊንሸራሸር በፍጹም አይችልም። የአሜሪካኑ የኮርፖሬት ዴሞክራሲ የበለጠ ግፊት በማድረግ ሁኔታው ለሱ እንዲያመች ያደርጋል። ሥርዓቱ ስር የሰደደና ዲሞክራሲንና ስላምን በማይፈልጉ ኃይሎች የተከበበና የተወጠረ በመሆኑ የአሜሪካን ሕዝብ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚወድቅ መገመቱ ከባድ አይሆንም። በሌላ አነጋገር ምርጫ ተካሄደ አልተካሄደ በሰፊው ሕዝብ ህይወት ላይ የሚያመጣው ለውጥ ይህን ያህልም አይደለም። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ኢምፔሪያሊዝም ሆኖ ይቆያል ማለት ነው። ጦርነትን ከማካሄድና አገሮችን ከማዳከም ባህርይው ሊላቀቅ በፍጹም አይችልም።

ፈቃዱ በቀለ
ታህሳስ 14፣ 2016 እ.ኤ.አ.
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ