ተሻለ መንግሥቱ

Rebels

በግዕዝ “ትንቢትሰ ይቀድሞ ለነገር” ይባላል። አንድ ነገር በእውን ከመፈጸሙ በፊት በትንቢት እንደሚጠቆም ለማስገንዘብ ነው እንዲያ መባሉ። እናም እውነት ነው የብዙ ነገሮች አፈጻጸም በትንቢት መልክም እንበለው በንግርት ወይም በዘመናዊ ቋንቋ በስድስተኛው የስሜት ህዋስ (the sixth sense, telepathy, by intuition, etc.) እንደምንለው አስቀድሞ እየተጠቆመ ሁሉም ማለት ባንችል የተወሰነው በተግባር ሲታይ እናስተውላለን። ስለዚህም እባካችሁ ኢትዮጵያን የምትወዱ ወይም ቢያንስ እንድትፈርስ የማትፈልጉ ወገኖች በሆነ ባልሆነው ከመሬት እየተነሳችሁ “እንዲህ ከሆነ/ካልሆነ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች!” እያላችሁ አታሟርቱባት። “ጥሩ ተመኝ ጥሩ እንድታገኝ” እንደሚባለው፣ ባይሆን ለዚህች ለበርካታ ዘመናት ለተጎሳቆለች አገር ደግ ደጉን ብትመኙላት ቢያንስ ኅሊናችሁ ይደሰታል። መገንባት ቀርቶ ማፍረስ ቀላል በሆነበት ዘመን እንዳመጣልን አናሟርት።

ሰዎች የተመኙትን የሚሆኑበት ወይም የሚያገኙበት አጋጣሚ ብዙ ነው። የዓለማችን ቅርጽ አሁን በምናየው ሁኔታ መገኘቱም የዚሁ የሰዎች ምኞትና ፍላጎት ነፀብራቅ ለመሆኑ ብዙ ነቃሽ መቁጠር አያስፈልግም። እንግዲህ የምናስበውን የምንሆንበት፣ በምናምነው የምንዳኝበት ሁኔታ በቀላሉ የሚፈጠር ከሆነ ደግ ነገር ለማድረግ ብናስብ እኛ ራሳችንም ተጠቃሚዎች እንሆናለን።

ከሁለት ዐሥርት ዓመታት በፊት የዚያድባሬ ሶማሊያ አሁን በምናያት ሁኔታ ትፈራርሳለች ብሎ ያሰበ ሰው አልነበረም። ግን የሆነው ሁሉ ሆኖ አንድ ቋንቋና አንድ ኃይማኖት ያለው አንድ ሕዝብ መቅኖ አጥቶ ተበጣጥሶ ቀረ። አንድ በሉ። ከሃያ ዓመታት በፊት የዚያኔዎቹ ሶቪየት ሕብረትና ዩጎዝላቪያ እንዲሁም ቼኮዝላቫኪያ በሉዓላዊነታቸው ከማንም በበለጠ የሚኮፈሱ አገራት ነበሩ። ግን የሆነው ሁሉ ሆኖ እነዚህ አገራት ተፈረካክሰው አሁን ባሉበት የተበታተነ ሁኔታ ላይ ሊገኙ ችለዋል። እንዲያውም ከዚህም አልፎ ከሶቭየት ከተገነጠለችው ዩክሬን፣ ክሬሚያ የምትባል ንዑስ ግዛት ተገንጥላ የራሷን መንግሥት እንደመሠረተች ይሁን ወደራሽያ ልግባ እንዳለች ይነገራል። ሁለት በሉ።

ከአሥራ አምስት ዓመታት በፊት የሣዳም ሁሤን ኢራቅ በአሜሪካን “የሐሰት ክስ” እንዲህ ፈራርሳ በሱኒና በሺዓይት ሰው-ሠራሽ የልዩነት ቁርቋሶ ሰበብ የአልቃኢዳና የአይሲስ መፈንጫ ትሆናለች ብሎ የጠበቀ ቅን አሳቢ አልነበረም። ግን የሆነው ሁሉ ሆኖ በጥንታዊ ሥልጣኔዋ የምትታወቀው ባቢሎናዊቷ ኢራቅ የደም ምድር ሆና ቀረች። ሦስት በሉ።

ከአምስት ዓመታት በፊት የባሻር አላሳድ ሦርያ የአገሪቱን 11 በመቶ የሕዝብ ቁጥር በሚይዝ አላዊት ከሚባል ጎሣ በወጣ ዐይኑን በጨው ያጠበ አምባገነን ቡድን ሳቢያ እንዲህ ትፈራርሳለች ብሎ የገመተ ሰው አልነበረም። ግን የሆነው ሁሉ ሆኖ ራሱን ከሦርያ ባስቀደመ ጨቋኝ አገዛዝ ምክንያት ያቺ አገር ደብዛዋ ጠፋ፤ ከሞላ ጎደል ከምድረ ገፅም ተፋቀች። አራት በሉ። ዝርዝሩ አያልቅም። የመን፣ አፍጋኒስታን፣ ሊቢያ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ፣ ደቡብ ሱዳን፣ አይበልባትና የኛዋ ናት የምንላት ኢትዮጵያም በላያቸው ላይ የሚነፍሰው ቬርሙዳዊ ጥቁር ወጀብ አፍ አውጥቶ በግልጽ የሚናገር በመሆኑ የ“ማነህ ባለሣምንት ያስጠምድህ ባሥራ ስምንት” ዲያብሎሣዊ የጽዋ ማኅበር ወር ተረኞች ላለመሆናቸው ደፍሮ የሚወራረድ የለም። ስለዚህ አናሟርት። እንኳስ አሟርተን እንዲሁም አልቻልንም።

አፄ ኃ/ሥላሤ “እኔ ከሌለሁ ኢትዮጵያ አትረጋም፤ ትፈራርሳለች” ይሉ ነበር አሉ። ትንቢታቸው ሠመረና ካሁን በፊት ያየነውንና አሁንም በባሰ ሁኔታ እያየነው ያለነውን ትንግርት ሁሉ ለማየት በቃን። የደርጉ ሊቀመንበር ጓድ መንግሥቱ ኃ/ማርያም “እኔ ሥልጣን ከለቀቅሁ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ፍርስርሷ ይወጣል” ይሉ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ንግርታቸው ይዞላቸው አሁን በትንቢታቸው ሥምረት “እየተዝናኑ እንደሆነ” መገመት ይቻላል። የህወሓቱ ቁንጮ መለስ ዜናዊ “ኢሕአዴግ ከሌለ የኢትዮጵያ ሕዝቦች እርስ በርስ ይባላሉ፤ አገሪቱም ትበታተናለች” ሲሉ ነበር። እሳቸውም ቃላቸው ሠምሮላቸው ይሄውና ኢትዮጵያ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ በሚንቦለቦል የእሳት ነበልባል ልትቃጠል የቀራት ጊዜ በጣም ጥቂት ነው - እንጸልይ። ባጭሩ ለዚህች አገር ክፉ ያልተመኘና በተግባርም ያልታዬ ሟርት የለም። ይህችን አገር ያልረገመና ወደእውንነት በተለወጠ እርግማንም ያልተሰቃየንበት ዘመን የለም። የተለየች አገር ከተለየ ሕዝብ ጋር። ለዚህ ሁሉ የመከራ አዙሪት የተዳረግንበትን ምክንያት ባውቅ ደስ ባለኝ።

የዛሬ 25 ዓመት ግድም የያኔው ጎልማሳ የአሁኑ አዛውንት ክቡር ሌንጮ ለታ “ኦሮሞነቴን የማታውቅልኝ ኢትዮጵያ አንድ ሺህ ቦታ ትበጣጠስ!” ብለው ነበር። ይህች አገር አበሳዋ! “አንተ ልጄ ኦሮሞ ነህ፣ አንተኛው ልጄ ደግሞ አማራ ነህ፣ አንቺኛዋ እዚያ ታች ያለሽው ሀመርባኮ ነሽ ...” እያለች “ማወቅና መቀበል” ነበረባት ማለት ነው እንደ እሳቸው አስተሳሰብ። የማይተማመን ጓደኛ በየወንዙ ይማማላል ይባላል። ለመሆኑ ማነው ማንን በምንነት አምኖ መቀበል ያለበት? ኢትዮጵያ ማን ናት? የማንስ ናት? ይቺ አገር አማራን በአማራነቱ ወይም ኦሮሞን በኦሮሞነቱ የምትቀበለው በምን አገባብ ነው? አንዲት ሴት ዲቃላ የወለደችለትን/በትን ሰው ነው “ይህን ልጄን ከርሱ ነውና የወለድኩት አባትነቱን አምኖ ይቀበለኝ ወይም በሰውና በሕክምና ላስመስክርና ላስፈርድበት” ብላ በፍርድ ቤት የምትጠይቀው። ከሰማንያ በላይ ዘውግ ያላት አገር ማንን ነው ከማን ለይታ የምትቀበለው? ምን ዓይነት አነጋገር እንደነበር እስካሁን ሳይገባኝ አለ። ኦቦ ሌንጮስ የያኔው ጥያቄያቸው አሁንስ ገብቷቸው ይሆን? አዎ፣ ስሜት ይሰክናል። ስሜት ሲሰክን ደግሞ ማስተዋል ይከተላል። ዕድሜ፣ ተሞክሮ፣ ትምህርት ... ሰውን ይለውጣል። ይህን እያየን ነው። ተመስገን።

በቅርቡ በለንደን አንድ የጎሣ ስብሰባ ላይ አንድ ልዩ ተልዕኮ አንግቦ የገባ ተሣታፊ “ኢትዮጵያን አፈራርሰን ስናበቃ ፍርስራሹ ላይ ኦሮሚያን እንገነባለን!” አለ አሉ - እንደ አካሄድ ይህ አነጋገር ጠብ ጫሪና ከጅምላ ጨራሽ የጦር መሣሪያዎች (WMD) ተለይቶ ስለማይታይ በተናጋሪው ግምባር ላይ (እንደሳልማን ሩሽዲ) ጥቂት ሚሊዮን ብሮች ሊለጠፉ በቻሉ ነበር፤ ባጭሩ ነውር ብቻ ሣይሆን ሕይወትን ሊያሳጣ የሚችል ከባድ ወንጀል ነው - በበኩሌ ማይምነትና የገንዘብ ፍቅር ለከት የሌላቸው መሆናቸውን የተረዳሁበት ሁኔታ ነበር በዚያ ስብሰባ ላይ የተከሰተው። እንዲያው ግን ይሄ ማፍረስ የሚሉት መተተኛ ነገር እንዲህ ቀላል ኖሯል ለካንስ ወንድሞቼ! ለመሆኑ እንዲህ መሰሉ ድፍረት ከምን ይገኝ ይሆን? ከሀሽሽ ወይንስ ከጉሽ ጠላ? ከዐረቦች ፔትሮ ዶላር ወይንስ ከኅቡዓን ድርጅቶች ሥውር ደባ? የምን ጥጋብ እንበለው? የዱባ ወይንስ የይሁዳዊ 30 ዲናር? እነጃዋርን መጠየቅ አለብን። “ኦሮሞው” ጃዋርም መልስ ሊሰጠን ይገባል። ለማንኛውም ግን ምሥጢሩን ጠልቀን እንመርምር! እንዲህ ዓይነት ድፍረት ምናልባትም ዕብደት እንዲሁ በትዝብት ብቻ ሊታለፍ አይገባም።

በቅርብ በተካሄደ አንድ የቪዥን ኢትዮጵያ ጉባኤ አራት የፖለቲካ ቡድኖችን ያቀፈ አንድ አገራዊ ድርጅት መመሥረቱ ይታወቃል። ያን አገራዊ ድርጅት በተመለከተ ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ እንዲህ አሉ፡- “ይህ የጋራ ሕብረት ፈረሰ ማለት ኢትዮጵያ ፈረሰች ማለት ነው”። አሁንም ገረመኝ። ሰዎች በመፍረስና በመበታተን ጽንሰ ሃሳብ ተሞልተናል ማለት ነው ብዬ ተገረምኩ። የዘመኑ ፋሽን ሆኖ ይሆን? መሆን አለበት። እዚህም እዚያም ማፍረስ እንጂ መገንባት ብዙም የለም። ማፍረስ ከመገንባት በመቅለሉ ሳይሆን አይቀርም ሰዎች ወደሚቀለው የሚያዘነብሉት። እንዲያው ትዝ ብሎኝ ነው።

በጣም በቅርብ ደግሞ ሙሉነህ ኢዮኤል እንዲህ አለ አሉና አግራሞቴን ጨመሩብኝ። “ወያኔ የተከለውን የፌዴራል ሥርዓት መንካት ኢትዮጵያን እንደማፍረስ ነው”። እውነት ብሎ ይሆን? መልስ ባገኝ ደስ ባለኝ። “ብሎ ከሆነ፣ አልብሎ ከሆነ” በሚል የታሳቢ ትንታኔ ውስጥ አልገባም። እንደ አጠቃላይ ግን ከዚህ ከማፍረስና ከመበተን አስተሳሰብ የምንወጣበትን መንገድ ብንፈልግ ጥሩ መሆኑን እያሳሰብኩ ትዝብቴን እዚህ ላቁም።

ሳቆም ግን አንድ ከተነሳሁበት ማዕከላዊ ሃሳብ ገንጠል የሚል አስተያየት በመሰንዘር ነው።

ሰሞኑን የነፃነት ታጋዮች የጦፈ ትግል ላይ እንደሆኑ በነፃ ሚዲያዎች እየተከታተልን ነው። በዚህ ትግል ውስጥ እዚያና እዚህ የሚወረወሩ የጠላት የሚመስሉ ወቅትን ያልጠበቁ የነገር ውርጅብኞች አሉ፤ እነዚህን መሰል አፍራሽ ውርክቦች ለከፍተኛ ትዝብት ይዳርጋሉ። በአንድ ጎራ ውስጥ ናቸው በሚባሉ ኃይሎች መካከል የሚስተዋሉት የነገር ዱላዎች ታዛቢን ሳይቀር ግራ እያጋቡና ሕዝብን ተስፋ እያስቆረጡ ናቸው - የግጭቶቹ ዓላማም ሕዝብን ሆን ብሎ ተስፋ ለማስቆረጥ ይመስላል - እንዲያ ባይሆን ኖሮ በዚህ በትንቅንቅ ወቅት ትግስትን መላበስ በተገባ ነበር - ችግር እንኳን ቢኖር ማለቴ ነው። ከሥልጣን ሽሚያ አኳያ እንዳይባሉ “ወጡ ሳይወጠወጥ” ዓይነት ነው የሚሆን። አበው “ከብቱ ሳይገዛ ሌባው በረት ሞላ” የሚሉት አባባልም አላቸው። ወያኔ ኢትዮጵያን ቀርቶ ዓለምንና ከባቢዋን እግር ከወርች አሥሮ የሁሉም አዛዥ ናዛዥ በሆነበት ሁኔታ ገና ለገና ህወሓት ወድቆ የሥልጣን ፍርፋሪ አገኛለሁ ከሚል ከሆነ ይህ ሁሉ መሰዳደብና መደነቃቀፍ የተፈጠረው በጣም ያሳዝናል፤ ይህ ነገር በርግጥም የኛን የኢትዮጵያውንን ሥነ ተፈጥሮ ዳግም እንድንመረምር ያስገድደናል። ይህን አስተያየት የምታነቡ ወገኖች ራሳችሁን ፈትሹ። ስሞችን ያላነሳሁት ሆን ብዬ ነው። ስም ሳይጠቀስ መማማር፣ መመካከርና መግባባትም ይቻላልና።

ይልቁንስ ነፃነት በጠማው ሕዝብና ወያኔያዊ መዥገርና ትኋን በወረሳት ኢትዮጵያ እንዳትረገሙ ጊዜያዊ ያለመግባባት ችግር እንኳን ቢኖር የሆዳችሁን በሆዳችሁ ችላችሁ ለአንድ ዓላማ ቁሙ፤ በንግግርና በውይይት ችግር ማስወገድን ልመዱ። ለሁሉም ነገር ስድብና በትር የሚመልሰው ወያኔ ነው። ከወያኔ እሻላለሁ የሚልና ወያኔን በመጥፎነቱ የሚቃወም ኃይል የጉልበትንና የዕብሪትን መንገድ በምንም ዓይነት ሁኔታ መከተል የለበትም፤ ከእልህ እንውጣ፤ ከበቀለኝነት ስሜት እንታቀብ፤ ከቂም በቀል እንቆጠብ፤ ከአላስፈላጊ ፉክክርና ከምቀኝነት አባዜ እንላቀቅ። አሁን አንዳንዶቻችሁ እያሳያችሁት ያለው ምግባር ጥሩ አልመሰለኝም። ድሉን ማንም ያምጣው፤ ዋናው የድሉ መገኘት ነው። አትቀናኑ። የሚያስቀና ነገር በአሁኑ ሰዓት የለም። መሞት ደግሞ አያስቀናም። በረሃ ገብቶ በድንጋይ ትራስ፣ በጠጠር ፍራሽ መተኛት አያስቀናም። ከታች በሚርከፈከፍ ጥይት ከላይ በሚዘንብ ቦምብ እየተቆሉ ለነፃነት መዋደቅ አውሮፓና አሜሪካን አገር የመንፈላሰስን ያህል ሊያስቀና አይችልም። እርግጥ ለክቡር ዓላማ መሞት መሸታ ቤት ውስጥ በሴት ምክንያት ከመሞት የበለጠ ታሪካዊ የክብር አክሊል ስለሚያቀዳጅ ማንም እንደፈለገው የሚያገኘው ርካሽ ዕቃ አይደለምና በትግል የሚወድቁ ልጆቻችን በመንፈስ ያስቀናሉ። ነገ ሁሉም ነገር ሲጠራ ሰዎች በሠሩት ታሪክ ከመቃብር በላይ ውለው የትውልድ መኩሪያ ይሆናሉ። ሞት ለማንም አይቀርም። በእንቅፋትም በትንታም ሰው ይሞታል። በኤድስም በነቀርሣም በሽውታም ሰው ይሞታል። ሰው መሞቱ ካልቀረ ደግሞ ለተከበረ አገራዊ ነፃነት መሞቱ እልል የሚያሰኝና የሚያኮራ እንጂ የሚያስለቅስና በኀዘን የሚያኮራምት እንዳልሆነ እንኳንስ ጤነኛ ወገን ወያኔም ሣይቀር እየመረረው የሚቀበለው ነባራዊ እውነት ነው። ...

በአንድ የትግል መስመር ውስጥ ነን ብላችሁ የምታስቡ ወገኖች በአስቸኳይ ራሳችሁን መርምሩ። ጊዜው ጥሏችሁ ሳይነጉድ ተስተካከሉ። ጊዜ ወሳኝ ነው - ባናውቀው ነው እንጅ የራሱን ሰዎች እያንጓለለ ይመርጣል፤ ዜጎችን ሲፈልገው በቅሌት መዝገብ ሲሻው ደግሞ በክብር የወርቅ መዝገብ ይጽፋል - ምርጫው የኛው ነው። እናንተ የጊዜው ከሆናቸሁ ጊዜውም ይቀበላችኋል። በተሰነካከለ ዓላማ ተመርዛችሁ ከወቅቱ የተቀደሰ አገራዊ የነፃነት ትግል ጋር የማትጓዙ ከሆናችሁ ግን በሂደት ዘመኑ ይተፋችሁና ልፋት ድካማችሁ ከንቱ ሆኖ ይቀራል። ሁላችንም ቢያድለን ከግል ዓላማና ፍላጎት ባለፈ ለአገር መሥራት የሚጠበቅብን ወቅት ላይ እንገኛለን። የተደበቀ ይወጣል፤ የታመቀ ይፈነዳል፤ የተሸመቀ ይገለጣል። በተንኮልና በምቀኝነት እየተጓዝን የጋራ ትግልን የምናጓትት ከሆነ ታሪክና ጊዜ ይፈርዱብናል። ከሁሉም ደግሞ እንቻቻል፤ በረባ ባልረባው እየተቋሰልን ለጠላት ምቹ አንሁን። በኛ መናቆርና አለመስማማት ጠላት እፎይታ እያገኘ ሕዝብና አገርን መበታተኑን አስፋፍቶ ይቀጥላል - ስለዚህ ብልኅ እንጂ ደንቆቶ የጠላት መሣሪያ ከመሆን እንቆጠብ - የሚያልፍ ጊዜ የማያልፍ ሰቆቃ በወገናችን ላይ እንዳያሳርፍ እንጠንቀቅ። መነቃቀፍ ካለብንና ሲኖርብን ደግሞ በሚዲያ ሣይሆን በግል አድራሻዎቻችን ይሁን፤ “ጥንካሬያችንን ለሌሎች ደካማ ጎናችንን ለኛ” የሚለው የንግድ ቤት ማስታወቂያ በናንተም ዘንድ ይሥራ። በግል ተወቃቀሱ፤ ተተቻቹ፤ ተራረሙ፤ ተማማሩ፤ ይህን ማድረግ የትልቅ ሰውነት ምልክት ነው፤ ይህን ማድረግ ሰይጣናዊ ትዕቢትንና ትምክህትን ሰባብሮ መጣል ማለት ነው። ይህንን ታዲያ ስታደር አትናናቁ። በምድር ላይ ማንም ከማንም አይበልጥም። በላጭም ተበላጭም የለም። አንዱ ሌላውን የሚበልጥበት ነገር እንዳለው ሁሉ ሌላው ከሌላው የሚሻልበትም ነገር አለው - ነገሩ ሰጥቶ የመቀበል ጉዳይ ነው። ሁሌ ሰጪ ሁሌም ተቀባይ ሊኖር አይገባም። ስለሆነም ከሚያናንቁን ነገሮች ይልቅ የሚያከባብሩን ነገሮች ይበዛሉና ለነዚያ ቅድሚያ እንስጥ። በአደባባይ መነቃቀፍን ደግሞ የኅቡዕ የነፃነት ትግል መርኅ አይደግፈውም። በነፃነት ትግል ጊዜ ይሄ የዴሞክራሲ ነገር ብዘም ሊሠራ አይገባም፤ እዬዬም ሲዳላ ነው። ዴሞክራሲ አገር ሲኖርና ሥርዓት ሲዘረጋ እንጂ በበረሃ ከእባብና ከጊንጥ ጋር እየታገልክ ልታስበውም አይገባም። ምክርን መቀበል የብልኆች ጠባይ ነው። ምክርን መናቅ የደናቁርት ዕብሪተኞች መገለጫ ነው።
በመጨረሻም መልካም ልመኝና ልሰናበት። ዕርቅንና ስምምነትን በመሀላችን ያንግሥልን። አገራችንንና ሕዝባችንን እንድናስብ ያድርገን። የግል የሥጋ ፍላጎታችንን አብርዶ በዕውቀትና በጥበብ፣ በአስተውሎትና በፍቅር የምንጓዝበትን መንገድ ያመቻችልን። ኢትዮጵያውያን በተለይ በዚህ ዘመን ከምንታወቅበት ተባብሮ ያለመሥራት አባዜ አላቅቆ ሠምና ፈትል ያድርገን። ይህ ዓይነቱ የፍቅርና የመተሳሰብ ዘመን በጣም ናፍቆኛልና እኔን ሽማግሌ አባታችሁንም አቆይቶ ለዚያ ዘመን እንዲያበቃኝ ጠልዩልኝ - አሜን በሉ እንጂ ታዲያ፤ “ለራስ ሲቆርሱ” ይባል የለም? በያለንበት ሰላሙን ያብዛልን። ከጨለማው ዘመን አውጥቶ ወደ ብርሃኑ ዘመን ያስገባን። ቅኔ አልተቀኘሁም።

ተሻለ መንግሥቱ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ