ሸንቁጥ አየለ

ሸዋ ውስጥ ደብር ዜና ማርቆስ የሚባል ገዳም አለ። በ1986 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል ፈተና ስጨርስ ወደ አንድ መነኩሴ አጎቴ ካንድ ጓደኛዬ ጋር ወደ እዚህ ገዳም ሄድን። ይሄን ጓደኛዬን ለማስመከር መሆኑ ነው። በወቅቱ ይሄ ጓደኛዬ ነገር ክርስቶስ ላይ ጥርጣሬ ቢያበዛ እስኪ ከኝህ አጎቴ ምክር ስማ ብዬ ነበር ይዤው የሄድኩት። እናም መነኩሴው አጎቴ ልንጠይቃቸው እንደመጣን ሲያውቁ ደስ አላቸው። ፈገግ ብለውም ተቀበሉን።

ሆኖም በቤታቸው ያለውንም የሚበላ ነገር አቀራርበውልን በትንሿ ቤታቸው ትተውን "በሉ ተጨዋቱ። እኔ ወደ ጸሎት መሄዴ ነው" ብለውን ሄዱ። ቢጠበቁ አልመጡም። እኛም ስለደከመን ቁጭ ባልንበት መደብ ላይ እንቅፍል ይዞን ሄዶ ኗሯል። እሳቸው ግን በጣም ከመሸ መጡ። ጥቂት አርፈው እንደገና ተነስተው ሌሊትም ለጸሎት ብለው ሄዱ። ጠዋት ቅዳሴ ቆይተው መጡ። አሁንም ያላቸውን ነገር አዘገጃጅተው አቀራርበውልን የተሰዓት ጸሎት ደርሷል ብለው ሊሄዱ ተነሱ።

ነገር ክርስቶስ ላይ ጥርጣሬ የገባው ጓደኛዬም የመነኩሴው ለጸሎት እያሉ ጥፍት ማለት ገርሞታል እና አንድ ጥያቄ ጠየቃቸው። "ለመሆኑ ጸሎት የሚበቃዎት መቼ ነው? የሚጸልዩትስ ምን እያሉ ነው?" ሲል ጠየቀ። እርሳቸውም ፈገግ እያሉ "የምድር ጸሎቱ ስሞት ነው የሚበቃኝ። ሆኖም በሰማይም ክርስቶስን ማወደሱ እና ማመስገኑ ይቀጥላል። የምጸልየውም "አምላኬ! ጌታዬ! ፈጣሪዬ! ንጉሤ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ምስጋና ይገባሃል እያልኩ ነው" ሲሉ መለሱለት።

ልቡ በክርስቶስ ነገር ላይ የሸፈተው ወጣትም "ክርስቶስ እኮ ፈጣሪ አይደለም። ለምንድን ነው ፈጣሪ የሚሉት?" ሲል ሳያፍር መነኩሴው አጎቴን ጠየቃቸው። እኔም አመዴ ቡን አለ። በፍርሃትም ተሸማቀቅሁ። እንዴት አንድን መነኩሴ እንዲህ በብልግና ይጠይቃል ብዬ መሆኑ ነው። እርሳቸውም ፈገግ አሉ። "ክርስቶስን ፈጣሪ አይደለም ብለህ ታስባለህ? ማለት ነው?" ሲሉ።

"አዎን!" አለ ምንም ቅር ሳይለው።

"እንዴት?" በድጋሚ ጠየቁ።

"ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያብራራው ..." ብሎ የሚያውቃትን ጥቂት ጥቅስ ጠቃቀሰ። ድንገትም የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አንድን መናገር ጀመረ። ድምጹን ከፍ አድርጎም እየተናገር የነበረው መነኩሴውን ክርስቶስ ኢየሱስ አምላክ አይደለም ብሎ ለማሳመን ነበር። ድንገት ግን ቀጥ ብሎ ቆመና መናገር አቆመ። "እንዴ ቆይ?" ብሎ መንጎራደድ ጀመረ። "እንዴ ... ቆይ ይሄ ምዕራፍ እኮ ስለክርስቶስ አምላክነት እና ፈጣሪነት የሚያስረዳ ነው። እንዴ? ..." እንደገና እራሱን አርሞ ምዕራፉን ደግሞ በቃሉ ለበለበው። እራሱ እየተናገረ እራሱ ደግሞ እያብራራ "እንዴ? እንዴ?! ..." ማለቱን ቀጠለ።

መነኩሴው አጎቴ በዚህ ሁሉ የጓደኛዬ ንግግር መሃከል ጣልቃ አልገቡም። እራሱ ክርስቶስ ፈጣሪ አይደለም ብሎ ጥቅስ ማብራራት ጀምሮ፤ እራሱ ደግሞ መዞ ባመጣው ጥቅስ ክርስቶስ ፈጣሪ ነው ብሎ እራሱን ማስረዳት ጀመረ። መነኩሴው አጎቴም በመጨረሻ ጓደኛዬን እያስተዋሉ እንዲህ አሉ። "አንተ ጎበዝ ልጅ ነህ። መካሪ ልብ ያለህ። ተመካሪ ልብም ያለህ። አሳስተው ያስተማሩህን ነገር በየዋህነት ሰምተህ በልብህ ብታስቀምጠውም፤ ልቦናህ ግን እውነትን የማድመጥ ጸጋን የተሰጠህ ሰው ነህና እውነት እና ሐሰትን አብላልተህ በራስህ መለየት ቻልክ።"

መነኩሴው አጎቴ ይሄችን ብቻ ከተናገሩ ብኋላ "በሉ እርስ በርሳችሁ ተማማሩ" ብለውን ጥለውን ወደ ጸሎታቸው ሄዱ። የልጁ ክህደትም ሆነ እራሱን አርሞ ወደ ትክክለኛ ሃሳብ መምጣቱ ድንቅም አላላቸው። ሲጀምር እኝህ መነኩሴ ምንም ነገር የሚደንቃቸው ነገር ያለ አልመሰለኝም። ከመመንኮሳቸው በፊት አላቃቸውም። እንዲህ ምንም ነገር የማይደንቀው ያደረጋቸው ምንኩስናው ይሁን ወይም አይሁን ግን አላቅም።

በሦስተኛው ቀን ከትንሿ ቤታቸው ተሰናብተን እየሄድን ሳለ፤ ድንገት አንድ ሃሳብ መጣልኝ። ለዘለዓለም ስንቅ የሚሆን ምክር ከኝህ ሰው ማግኘት። እናም ዞር ብዬ እያስተዋልኳቸው "አባ! በሕይወታችን ሙሉ የምንመራበት ምክር ቢለግሱንስ?" ስል ጠየቅኋቸው። እንደለመዱት ፈገግ አሉ። ከሰው ልጅ ባህሪ ውስጥ ፈገግ ማለት ጥልቅ የሰውነት ህሳቤ ሚስጥር ይመስለኛል። ገና ህጻን ሆኜ። እናም እኝህ አባት ውስጥ ይሄን ጥልቅ የሰውነት ሚስጢረ ሃሳብ ያነበብኩት መሰለኝ። እናም የሚናገሩትን ለማድመጥ በጥንቃቄ አቆበቆብን። ሌላው ቀርቶ በነገር ክርስቶስ ላይ ልቡ ሲዋዥቅ የነበረው ጓደኛዬም በሦስት ቀን ውስጥ የሆነ የማይታመን የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥቶ አባ የሚናገሩትን በአክብሮት እያደመጠ ነው።

አባ ምክር ስጠይቃቸው ፈገግ ብለው ሲያበቁ እንዳልሰማ ሆነው ግን "በሉ ሰላም ግቡ። ቆላማውን አገር እስክትወጡ ቀስ እያላችሁ።" ብለውን እንድንሄድ ገፋፉን። እኔም "ምክሩን እኮ አልነገሩንም!" ስል በድጋሜ ጠየቅሁ። አባ እንደገና ፈገግ አሉ። እናም "እውነተኛው ምክር እያንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ አለ። ሰው የልቡን እውነተኛ ምክር ለመስማት ከፈቀደ ከልቡ ውጭ መካሪ አያስፈልገውም። ለዚህ አባባሌም ምስክር የሚሆነው ይሄ ወጣት ነው" ብለው ወደ ጓደኛዬ በአገጫቸው አመለከቱ። "ተመካሪ ሰው ካለ መካሪ ልቦናንስ እግዚአብሔር በየሰዉ ውስጥ አኑሯል። ሰው ከልቦናው ውጭ መካሪ አያስፈልገውም" በማለት አባ አብራሩ። አጭር ግን ቆፍጠን ያለ ማብራሪያ ነበር።

እናም ሰሞኑን የመነኩሴው አጎቴ ጥልቅ ምክር ታስቦኝ እንደ እርሳቸው ብቻዬን ፈገግ አልኩ። በኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች መሃከል እየተከናወነ ያለውን የእርስ በርስ መጠፋፋት ጉዳይ ሊያስቀር የሚችል አንድ ግሩም ምክር አዘል ጽሑፍ ማዘጋጀት አለብኝ ብዬ ሰሞኑን አስቤ ተነስቼ ነበር። የኢትዮጵያ ነገር ለልቤ ጭንቅ፣ ለመንፈሴ ሕመም፣ ለህሳቤዬ እሩቅ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ፖለቲከኞች መሃከል እኮ አብሮነት ቢፈጠር "አንዲት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን" በፍጥነት እውን ማድረግ ይቻል ነበር ብዬ እንደ ሞኝ እፈላሰፋለሁ።

እንደ ሞኝ ያልኩት ያለምክንያት አይደለም። በጥልቅ ምክንያት ነው። እንኳን የማይተዋወቁ፣ በነገድ የሚለያዩ፣ በፖለቲካ ህሳቤ እና ርዕዮት ዓለም የተነጣጠሉ ኃይሎች አንድ ሊሆኑ ይቅር እና፤ በእውቀት ኮትኩተን እና አጀግነን ለጋራ ትግል ይሆናሉ ብለን የምናዘጋጃቸው ሰዎች በጣም በፍጥነት ሲገለባበጡ እና ሲከረባበቱ ብሎም ወደ ሌላ ጎራ ሲሰለፉ በተደጋጋሚ ላስተዋለ ሰው፤ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ለምን አንድ አልሆኑም ብሎ ማሰቡ በራሱ ሞኝነት ነው። አንድ ባይሆኑ ግን ለምን ተከባብረው አይታገሉም? ብሎ መጠየቅ ግን ጤናማ ጥያቄ ይመስላል። ግን ይሄም የኢትዮጵያን ፖለቲካ ቀርቦ በደንብ ለሚያጠናው ሰው የሞኝ ጥያቄ ነው።

እናም ማዘጋጀት የጀመርኩትን የምክር ጽሑፍ አጥፍቼ ስለ መነኩሴው አጎቴ ምክር ማንሰላሰል ጀመርኩ። "ተመካሪ ሰው ካለ መካሪ ልቦናንስ እግዚአብሔር በየሰዉ ውስጥ አኑሯል። ሰው ከልቦናው ውጭ መካሪ አያስፈልገውም" የሚገርም እና የተራቀቀ አባባል ነው። ኢትዮጵያውያን ይሄን ያህል ጥልቅ ሕዝብ ሆነው ሳለ፤ ለምን ጥልቅ መሰረት ላይ የቆመች አገር መመስረት አቃታቸው?

"መካሪ ልቦናስ አለ! ተመካሪ ፖለቲከኛ ግን ከወዴት አለ?" የሚል ጥያቄ ሲቀርብም ይሰማኛል። እናም በክፉ መንፈስ የተጠለፈውን፣ ዘረኛ እና አንባገነን ሥርዓት ለማስወገድ በተጋድሎ ላይ ያለው ሕዝባችን የተባበረ እርዳታ የሚፈልግበት ወቅት አሁን ነበር። ፖለቲከኞች ግን በመርዛማ የመጠላላት እና የመጠላለፍ ሃሳብ ውስጥ ወድቀዋል። ይሄ ዛሬ አልተጀመረም። ቅንጅት የተበታተነው የተንኮል ፖለቲካ ማጥ ውስጥ ተቀርቅሮ ጭምር ነው። ከቅንጅት በፊት የነበሩትን አብዮታዊ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ወደ መርዛማ አዘቅት ውስጥ የጣላቸውም ይሄው በሸፍጥ እና በአሉታዊ እንቅስቃሴ የተሞላው የፖለቲካ ህሳቤ ነው። የፖለቲከኞቻችን ልቦና እውነትን ሳይሆን ሸፍጥን ለማፍልቅ ፈጣን ነው።

እናም ምክር ፖለቲካን አቅጣጫ አያሲዘውም። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ አይነት ፖለቲካዊ ምኅዳር ውስጥ የሚተራመስ የፖለቲከኛ ህዝነ ልቦናም እራሱን ለመምከር የሚያስችለውን እውነተኛ ምክር ለማፍለቅ ልቦናውን ጸጥ የሚያደርግበት ሁኔታ ውስጥ አይደለም። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት ፖለቲከኛነት በልብ ውስጥ ትርምስ እና በውጭም ትርምስ የሰፈነበት ከባቢ ሕይወት ውስጥ መመላለስ ይመስላላል።

እናም "እውነተኛውን እና ትክክለኛውን ሁኔታ ለመለዬት እና ለማወቅ የሚያስችል መካሪ ልቦና በያንዳንዱ ውስጥ አለ። ተመካሪ ፖለቲከኛ ግን ከወዴት አለ?" ብሎ ዝም ማለት የቀለለው መፍትሔ ባይሆንም አንዱ አማራጭ ግን ይመስላል። "መካሪ ልቦናስ አለ! ተመካሪ ሰው ግን ከወዴት አለ?"

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ