አስፋ ጫቦ

Prof. Merera Gudina in jail

“እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር!” የሚል አባባል አለ። ወዳጄን ዶክተር መረራ ጉዲናን ሳስታውስ ያ አባባል ይመጣብኛል። ከዚያ የተሻለ ሊገልጸው የሚችል አባባል ሊኖር ይችላል። አልመጣልኝም! አሁን ታሰረ! በዚያ ምክንያት ነው ይህንን የምጽፈው።

መረራ ሲጽፍ፤ ሲናገር እውነቱን፤ መረራ የሚያውቀውን እውነት፣ ይጽፋል፣ ይናገራልም። ለማስቀየም ወይም ለማስደሰት፤ ወይም ፖለቲካዊ ጥቅማ ጥቅም ለማግኘት ብሎ ሲናገር የሰማሁበት ጊዜ የለም። ያ በንግግሩ፤ በጽሑፍ ያነሳቸው ሌሎቹን አላስቀየመም፤ አላበሳጨም አላጋለጠም ማለት አይደለም። ያ የመረራ ግቡ አይመስለኝም። ያ የተነገረው እውነት፤ የጻፈው እውነት ውጤት ነው። ከዚህ የተነሳ ምሁርነቱ፤ የፖለቲካ ተዋናኝ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ መረራ ለኔ “የሰፈር አስታራቂ ሽማግሌ!” መስሎ ይታየኛል። ባለአንጣዎቹ የሽማግሌውን ምክር ሰምተው ላይታረቁ ይችላሉ። ይህ የሽማግሌው፤ የመረራ ጥፋት አይመስለኝም። “እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ!” ብለው ፍንክች የማይሉ ተፋላሚዎቹ ጉዳይ ይመስለኛል።

መረራ ጊዲና ከ1992 በፊት አላውቀውም። በስም ግን አውቀዋለሁ። እኔ ማዕከላዊ ታስሬ የነበረ ጊዜ መረራ ከርቸሌ እስረኛ ነበር። በመኢሶንነት ነበር የታሰረው። ታዲያ በማዕከላዊና በከርቸሌ መካከል ላይና ታች እስረኛ ስለሚመላለስ ከርቸሌ ወጣ ብለው ስለሚታዩት ግለሰቦችና ቡድኖች በቂ መረጃ ነበረን። እኔ ነበረኝ!!

ማዕከላዊ በተለያዩ ምክንያቶች አንድ ወጥ የሆነ የሚያስቀና ትብብር ነበረን። ከርቸሌ ግን እንደዚያ ሳይሆን ውጭ ይባላ የነበረው የፖለቲካ ቡድን ያንኑ ስፍራው በሚፈቅደው መጠን ቀጥሎበት ነበር። በዚህ የተነሳ፤ መረራ መኢሶን በመሆኑ እዚያ ጫና የፈጠረው ቡድን “ገባር” ሊያደርገው ፈልጎ አልገብርም ብሎ አንገቱን ቀና አድርጎ የተፈታ መሆኑን የሚያቁት ይነግሩኝ ነበር። ካልገበር የማግለልና የመገለል ሁኔታ (oetricized) ይፈጥርበታል። ከምግብ ከሌላውም የማግለለል ሁኔታ ይፈጠራል። መረራ ይህ ተፈጥሮበት ከአቋሙ ዝንፍ ሳይል ተፈታ ይሉኛል።

መረራን መጀመሪያ ያገኘሁት በ1993-94 ይመስለኛል። ዋሽንግቶን ዲ.ሲ. አሁን በሕይወት የሌላውን፤ እንግዳ ተቀባይና አስተና ጋጁ ሙሉጌታ ኃይሉ ቤት ነበር። እኔ ከካሊፎርኒያ መረራ ከአዲስ አበባ መጥቶ እዚያ አርፈን ከረምንም መሰለኝ። አንድ በወቅቱ የነበረ ኢድሐቅ የሚባል ድርጀት ባዘጋጀው ስብሰባ ለመገኘት ነበር የመጣው። ምርጫ በየጊዜው እየተደረገ ዶክተር በየነ ጴጥሮስ ነበር የሚመረጠው። በዚህኛው ዙር መረራ ጉዲና ተመረጠ። በየነ ጴጥሮስ አኮረፈው። መነጋገር አቆሙ!

በአሁኑ ዙር አሜሪካ የመጣ ጊዜ በስልክ አንድ ሁለት ሦስቴ አግንቸው ነበር። በጫወታችን መካካለ የበየነ ጴጥሮስን ነገር አነሳሁበትና ሌላም የሠራውንና የሚሠራውን አነሳነው። ”አሰፋ እሱን እባክህ እርሳው! ጉዳት የለውም!” አለኝ። መረራ ነገር ፍቆ አልፎ መሔድ የሚችል መሆኑን አስተዋልኩ።

ከሚጻፋቸው ነገር አንዱ ትዝ የሚለኝ የኦነግ መሥራችና መሪ ስለነበረው ስለባሮ ቱምሳ በጦቢያ መጽሔት የጻፈው ነው። ባሮ የነጻ አውጭ ጦር ግንባር ለመክፈት ሐረርጌ ወርዶ እዚያ ነው የሞተው። “እገሌ ... እነእገሌ አስገደሉት!” የሚል ወሬ በወቅቱ ሥራዬ ተብሎ ጭምር ይናፈስ ነበር። መረራ ማስረጃና ስም ጠቅሶ “ባሮ የተገደለው አብሮት በዘመተ፣ ብዙ የሌለ ተስፋ ሰጥቶ ከወሰዳቸው፣ ተስፋ ከቆረጡት ልጆች በአንዱ፤ ከአምቦ ነው መሰለኝ በሔደ ወጣት ክላንሽኒኮቭ ነው” ብሎ ጻፈ። የኦነግ ነን በሚሉ ብቻ ሳይሆን በሌላው ኦሮሞ ዘንድ ሁሉ “እውነትስ ቢሆን እንዴት ታጋልጣለህ!” በሚል ክስና ውቅስ የሚያመጣ ነው። የመረራ ሥራ ግን እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር ነው።

የአሁኑ የመሸበት ማደር ግን ማደሪያውን ወህኒ ቤት አደረገው። የወያኔ አድሮ ውሎም የለየለት እውር መሆኑ ይደንቀኛል! አውቀዋለሁ ሆኖም ይደንቀኛል! ዶክተር መረራ ጉዲና እንዴት ይታሰራል? መታሰራ የሚገባቸው እዚያ ውስጣቸው እንደ አሽን ፍልተው ማለቴ ነው። ድንገት የሚታሰር ሰው እጥረት ቢፈጠር እንኳን መረራ ጉዲና መታሰር የለበትም። ከኢትዮጵያ ወይም ከመረራ አንጻር ሳይሆን ከወያኔ አንጻር አይቸው ነው። መረራ ጉዲና አውሮጳ ይሁን አሜሪካ ፤አውሮጳ ፓርላማ ይሁን ካፌ ውስጥ የሚናገረው ከላይ ያልኩትን እውነት ነው። እዚያው አዲስ አበባ ወያኔ ፊት ለፊት የሚናገረውን ነበር ለአውሮጳ ፓርላማ የተናገረው። እኔ እንደታዘብኩት መረራ ጊዲና ነገር መቀባባት፤ ሞቅ ሞቅ ማድረግ አያውቅበትም። እንደወረደ ነው። ታዲያ ከዚህ የተነሳ፣ መረራ ከሁሉም በላይ ለወያኔ ጠቃሚ ሀብት ነበር። ”ይኸው እንደልቡ የሚናገር ተቃዋሚ አለንኮ!” ለማለትይጠቅማላ!

ወያኔዎች እባካችሁ “እፍረት!” የሚባል ቃል ፈልጋችህ እፈሩ!

እና ዶክተር መረራ ጉዲናን ፍቱልን!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ