ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ (በግራ) ዶ/ር መረራ ጉዲና (በቀኝ) / Prof. Beyene Petros (Left) & Dr. Merera Gudina (Right). (AP Photo/Mulugeta Ayene)ግርማ ሠይፉ ማሩ

በሀገራችን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማኅበራት እንዲሁም የሚዲያ ተሳትፎ እጅግ ወሳኝ እንደሆነ ሁሉም ይረዳዋል ማለት ባይቻልም፤ በተለይ የፖለቲካ ፓርቲ አባል አመራር የሆኑ ሰዎች ይጠፋቸዋል ብሎ የሚገምት ላይኖር ይችላል። እውነቱ ግን ከዚህ የተለየ ነው። በአሁኑ ጊዜ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ሰዎች የሚሳተፉት በዋነኝነት በሀገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን መዋጮ በማስላት ሳይሆን፤ ገዢውን ፓርቲ በማስወገድ ላይ ብቻ ያጠነጠነ ይመስላል። ይህንንም ማድረግ የሚፈልጉት ደግሞ በትርፍ ጊዜያቸው ከሥራ መልስ ወይም በጡረታ ጊዚያቸው ነው። ይህን ሲያደርጉ ደግሞ የብዙ ወጣቶች ጊዜና ጉልበት መስመር ባልያዘ አቅጣጫ እንደሚመሩ አይረዱም።

ለነገሩ የወጣቶችን ጊዜ በማባከን እና የወጣቶችን ፍሬያማ ጊዜ በከንቱ በማባከን ገዢውን ፓርቲ የሚወዳደር የለም። በሥራ እናገኛለን ተስፋ እና እራሳቸውን ከደህንነት ስጋት ለመጠበቅ ገዢውን ፓርቲ በምሽግነት ስለሚጠቀሙበት። ይህም ቢሆን ገዢው ፓርቲ ይህን ስለሚያደርግ ተቃዋሚዎች የወጣቶችን ጊዜ ያለአግባብ ማባከን አለብን የሚል ክርክር ሊገጥሙ አይገባም።

በእኔ እምነት የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሲኮን በተለይም አመራር ሲኮን፤ በቀጣይ የመንግሥትን ሥልጣን ለመያዝ መዘጋጀትን ይጠይቃል። በአሁኑ ወቅት በዚህ ልክ እራሳቸውን ያዘጋጁ የገዢው ፓርቲም ሆነ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ገዢው ፓርቲ ከሰበሰባቸው ሰባት ሚሊዮን አባላት ምርጥ ብሎ አውጥቶ አመራሩን መቀየር ባለመቻሉ ያሉትን የጡረታ ጊዜ እያራዘሙ 25 ዓመት ሞልቶታል። አሁንም ቢሆን በገዢው ፓርቲም ሰፈር ከፊት መጥተው ተስፋ የሚደረግባቸው አይታዩም።

በተቃዋሚ ጎራ ይህን ወሳኝ የፖለቲካ አመራር እና የመንግሥት ሥልጣን ቁርኝትን ባለመረዳት ፓርቲ የመሰረቱ እና ለመመስረት የሚራወጡ ሰዎች ግባቸው እንደ ከዚህ ቀደሙ የጡረታ ወይም ደግሞ ከሥራ መልስ ጊዜ ማሳለፊያ ከማድረግ የዘለለ ፋይዳ ያላቸው አይመስለኝም። ከዚህ በፊት ይህን ለማሳካት አንድነት ፓርቲ ያዘጋጀውን ስትራቴክ ሰነድ መሰረት አድርጎ የመድረክ አመራሮችን “ሻዶ ካቢኔ” እናቋቁም ብሎ ጥያቄ ሲያቀርብ በግልፅ ለፖለቲካ ሥልጣን የምናደርገውን ትግል በድብቅ ማድረግ የለብንም የሚለውን የአንድነትን ግልፅ አቋም በድብቅ በውስጣቸው ባለ ስውር የሥልጣን ጥም (ማን የካቢኔው መሪ ይሆናል?) ሳይቀበሉት እና ሳይሳካ ቀርቷል። በዚህም መነሻ አንድነት ያቀረበውን የስትራቴጂክ ፕላን ሰነድ ሳይቀበሉት ቀሩ፤ ቀጥሎም አንድነትን ገፍትረው አስወጡት። ለነገሩ አንድነትም በዚህ ትብትብ ውስጥ ድንክ ሆኖ አይቆይም ነበር።

አሁን ደግሞ በድጋሚ ማሳካት የሚፈልገው ዓላማ ምን እንደሆነ የማይታወቅ፤ ከአንድነት ፓርቲ ፍርስራሽ “ነፃነት” የሚባል ፓርቲ መመስረቱን ሰምተናል። ለምስረታው ከፍተኛውን ሚና ሲጫወት የነበረው አቶ ብሩ ቢርመጂ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይም የፓርቲው መሪ ሆኖ የተመረጠው ዶክተር ንጋት በእርግጥም የጃንሜዳ ልጅ ቢሆንም፤ በሰሜን ሸዋነቱ በቀጣይ መድረክ ውስጥ ለሚታየው የአማራ ፓርቲ ክፍተት ማሟያ እንደሚሆን ግልፅ ነው።

አንድነትን ገፍትሮ ያስወጣው የፕሮፌሠር በየነ እና የዶክተር መረራ መድረክ አሁን ለነፃነት ፓርቲ ምስረታ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል። ይህ የሚያሳየን ኢትዮጵያ የፓርቲዎች እጥረት ስለአለባት የዜጎችን የመደራጀት ዴሞክራሲያዊ መብት ለመደገፍ ካላቸው ቀና አመለካካት ሳይሆን፤ መድረክ የኢህአዴግ “ፎርጅድ ኮፒነቱን” ለማሳካት የጎደለውን የአማራ ፓርቲ ለመሙላት ብቻ ነው። መድረክ በትግራይ ዓረና ለህወሓት፣ በኦሮሚያ ኦፌኮ ለኦህዴ፣ በደቡብ የፕሮፌሠር በየነ ፓርቲዎች እና የሲዳማው ድርጅት ለደህዴን የተዘጋጁ ሲሆን፤ ለብአዴን ግን የአቻ ፓርቲ ችግር ነበረበት። ከዚህ በፊት አንድነትን በውስጠ ታዋቂነትም ሲከፋም በይፋ የአማራ ፓርቲ አድርገው ይፈርጁ ስለነበር፤ ከአንድነት መውጣት በኋላ ይህ ክፍተት “ፎርጅድ ኮፒ” ለመሆን እንኳን አላስቻላቸውም። አሁን ግን የነፃነት ፓርቲ መምጣት ከመኢህአድም ሆነ ከሰማያዊ ጋር ያላቸውን ስር የሰደደ ጥላቻ አስወግደው ከመሻረክ፤ ይህን የአንድነት ፍራሽ በማስገባት ድሮ አንድነት ሊውጠን ነው ከሚለው ስጋታቸው ወጥተው እኩያቸው የሆነ ፓርቲ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። ነፃነት ቢሮ የሌለው ማሕተምና ፋይል በሰዎች መኖሪያ ቤት የሚገኝ፣ ይህ ነው የሚባል ድርጅታዊ ጥንካሬ የሌለው ፓርቲ ስለሆነ፤ ለመድረክ አባል ድርጅቶች የእኩዮች ጥምረት ይሆናል። “የፎርጅድ ኮፒ” ፕሮጀክት ክፍተትም ይሞላል። እንደሚታወቀው የፓርቲዎች ውህደት እኩል ሳይሆኑ በእኩልነት መንፈስ ይባላል።

ለማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ እውነተኛ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲኖር ይፈልጋል። ይህ ደግሞ የሚሆነው እውነትኛ የድርጅት አቅም ያላቸው አማራጭ የሚሆኑ፤ ህዝቡ ቢመርጣቸው የመንግሥት ኃላፊነት ተረክበው ሊያስተዳድሩት የሚችሉ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይፈልጋል። በግሌ አንድ ፓርቲ መንግሥት ቢሆን የካቢኔ አባሎቼ እነ እገሌ ናቸው ብሎ ብቃት ያላቸው 30 ሰዎች የሚያሳየኝ ካለ፤ አባል ለመሆን ዝግጁ ነኝ። አንድነት ውስጥ ይህን ማድረግ ስለሚቻል ነበር ለፖለቲካ ሥልጣን የምንሠራው፣ ይህ በገዢው ፓርቲ አልተወደደም። በገዢው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን፤ ተቃዋሚ ነን በሚሉት ጭምር (ሰማያዊና መድረክን ጨምሮ) በተለይ ሰማያዊ በአንድነት ፍራሽ የሚጠነክር መስሎት ስለነበር። ነገሩ ግን የተገላቢጦሸ ነው የሆነው።

አሁንም በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲኖር ካስፈለገ፤ የሚፈጠረው ፓርቲ እንደ ኢህአዴግ አመራር የማይወጣው 7 ሚሊዮን አባል በመሰብሰብ የመልካም አስተዳደር ችግር የሚፈጥሩ አባላትን በማብዛት ሳይሆን ምርጦች የሚሰበሰቡበት፣ ለጥቅም ሳይሆን “ለአቅመ መስጠት” የደረሱ፤ በእውቀታቸው እና ከራሳቸውና ከቤተሰባቸው አልፈው ለዜጎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ የሚጨነቁ ብቻ ሳይሆን አማራጭ መፍትሔ የሚያቀርቡ፣ በየደረጃው ለፖለቲካ አመራር የሚሰባሰቡበት መሆን ይኖርበታል። ስለዚህ መስጠት የማይችሉ ለአቅመ መስጠት እስኪበቁ በደጋፊነት መቆየት ይኖርባቸዋል። መረዳት ያለባቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አባልም ሳይሆኑ በዴሞክራሲ ሥርዓት ተጠቃሚ ይሆናሉ። በዚህ የሚጠቀሙት የኢህአዴግ አባለት ጭምር ስለሚሆኑ።

በተመሳሳይ ጠንካራ ሚዲያ እና ሲቪል ተቋማት መኖር አለባቸው። እርዳታ ለማሰጠት እና ለራሳቸው የእራ ዕድል ለመፍጠር የተደራጁ ሲቪል ማኅበራት፣ በሕትመት ለመቆየት ለዘብተኛ የሆኑ ሚዲያዎች ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ፋይዳ የላቸውም። ይፍረሱ!!!!!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ