ሁለቱ አርበኞች ሳይጋጩ እንዲኖሩ
ገለታው ዘለቀ
በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሕይወት ውስጥ ሁለት ዓይነት የአርበኝነት ስሜቶች ገዝፈው ወጥተዋል። በርግጥ በአንድ አገር ውስጥ የተለያዩ የአርበኝነት ስሜቶች መፈጠራቸው በራሱ የሚያመጣው ችግር የለም። በአንድ ማኅበረሰብ ወይም አገር ውስጥ የአርበኝነት ስሜቶች በተለያየ መንገድ መገለፃቸው የሚያመጣው ችግር የለም ብቻ ሳይሆን ዜጎች የአርበኝነት ስሜት ሲይዛቸው ይህንን ስሜት በነፃነት የሚገልፁበትን መስመር መዘርጋት ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ነው። በዚህ በዛሬው ፅሁፍ ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ ጎልተው ስለሚታዩት ሁለት የአርበኝነት ስሜቶች እንወያይ። እነዚህ አርበኞች አንደኛ ብሔራዊ አርበኞች ሲሆኑ ሁለተኛ የብሔር አርበኞች ናቸው። ታዲያ እነዚህ አርበኞች ሲጋጩ ይታያል። ለምን ይጋጫሉ? ስለምን ይራራቃሉ? መቼም በአንድ አገር ውስጥ አርበኞች ከተጋጩ በዚያች አገር ውስጥ ሰላምንና ልማትን ማሰብ ወደፊት መራመድን ማሰብ እጅግ ከባድ ነው። አርበኞች እርስ በርስ ከተጠላለፉ መረጋጋት አይኖርም።
እስቲ የዚህን የአርበኝነት ስሜት ጉዳይ ከትርጉሙ ጀምረን በውስጡ የሚገዛቸውን የሰው ልጅ ስሜቶች ጥቂት እንመርምር። ሃሳባችንን ለማፋፋት መጀመሪያ አርበኝነት ምንድን ነው? ምን ምን ስሜቶችን ይቆጣጠራል? ካልን የሚከተሉት ስሜቶች ድምር ውጤት ነው። እነዚህ ስሜቶች፤
ታማኝነት (Loyalty)
መውደድ (Love)
ቅንዓት (Zeal)
መሰጠት (Devotion)
መጣበቅ (Attachment)
ድጋፍና ተከላካይነት (Support and safeguard) ናቸው።
ስለ አርበኝነት ስናጠና ስሜቱ ከነዚህ ከፍ ሲል ከተዘረዘሩት ጉዳዮች የተገነባ እንደሆነ እንረዳለን። እንግዲህ አርበኛ ስንል ከነዚህ ስሜቶች የተገነባ ተክለ ሰውነት ነው ማለት ነው። በመሆኑም አርበኝነት ስንል ዜጎች ለኃይማኖታቸው ወይ ለብሔራቸው ወይ ለአገራቸው ይህን ስሜት ያንፀባርቃሉ ማለት ነው - ማለት ነው። እንግዲህ ታዲያ አንድ ዜጋ ለራሱ ብሔር አርበኛ ሆኖ ብቅ ቢል የአርበኝነት ስሜቱን በተገቢው መስመር እስከገለፀ ድረስ ጤናማ አርበኝነት ነው። በማኅበረሰብ ውስጥ ስለሚፈጠር የአርበኝነት ስሜት ስናነሳ ስሜቱ የሚገለፀው በጎሣ በኃይማኖት ወይም በአገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን የሙያ አርበኞችም ይነሳሉ። እነዚህ የሙያ አርበኞች ከተራ ስሜት የዘለላ ተቆርቋሪ ይሆኑና ለሙያቸው ማኅበር ለማቋቋም ይጥራሉ ሙያቸው እንዲከበር እንዲዳብር ብዙ ይደክማሉ። እነዚህ አርበኞች የነፃ ፕሬስ አርበኞች፣ የዳኝነት አርበኞች፣ የሰብአዊ መብት አርበኞች ወዘተ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህን ስሜቶች መንከባከብ በአግባቡ እንዲደራጁ ማድረግ የዴሞክራሲ እምነት ነው። ዋናው ጉዳይ ማንኛውም የአርበኝነት ስሜት በአብሮ መኖር በአክብሮትና ትእግስት የሚስተናገድ ከሆነ ዜጎች የተነኩበትን የአርበኝነት ስሜት መግለፅ ይችላሉ። ዴሞክራሲም ዜጎች በትክክለኛው መስመር ለብሔራቸው አርበኞች ሆነው ቢኖሩ ያተርፋል እንጂ አይከስርም። ታላቁ መሪ ዊንስተን ቸርችል እንዲህ ብለዋል። “ፍቅረ ባህል ወይም ልማድ ብሔራዊነትን አያደክምም።”
የአርበኝነት ስሜት ችግር የሚያመጣውና ብሔራዊነትን የሚያዳክመው በአንድ አገር ውስጥ የአርበኝነት ስሜቱ ፈሩን ለቆ ሲሄድና ሁሉን ለመጠቅለል ሲነሳ የብሔር ፖለቲካ ፍቅር ሲይዘው ነው። ያን ጊዜ መንግሥት ያንን የአርበኝነት ስሜት መመርመር አለበት። የብሔር አርበኛ በፍቅረ የብሔር ፖለቲካና ፍቅረ ነዋይ ከተነደፈ ያ ብሔራዊነትን ያደክማል።
ከፍ ሲል እንደተገለፀው በአገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ በሌሎች አገሮች ባልታየ መልኩ ሁለት የአርበኝነት ስሜቶች ጎልተው የወጡ ሲሆን እነዚህ ብሔራዊ አርበኞች እና የብሔረሰብ አርበኞች ባላንጣዎች ሆነዋል። የብሔረሰብ አርበኛው ቁጥር በቅርብ ጊዚያት ከፍ ያለ ይመስላል። እነዚህ አርበኞች ከብሔራዊ አርበኞች ጋር ከሚያጋጫቸው ምክንያት አንዱ የብሔረሰብ አርበኞች አርበኝነታቸውን ሊገልፁ የፈለጉበት መንገድ ነው። የማንነት ፖለቲካን ሲመኙ ነው ከብሔራዊ አርበኞች ጋር የሚጋጩት። በአሁኑ ሰዓት በአንዳንዶች ዘንድ አብቦ የሚታየው የብሔር አርበኝነት ለብዙዎች የሚያስፈራው ይህን የአርበኝነት ስሜት የያዙ ወገኖች ወደ ፖለቲካ ሥልጣን ሲመጡ ይህ በብሔር አርበኝነት ስሜት ላይ የተገነባ ተክለ ሰውነት ብሔራዊ የሆኑ ጉዳዮችን አይሸከምም በውስጡ ያለውን ፍቅር ቅንዓት ታማኝነት መጣበቅ ከለላ መሆን የመሳሰሉትን ወሳኝ ስሜቶች ብሔሩ ስለወሰደበት ፍትህን በአገር ደረጃ ለማስፈን የአርበኝነት ስሜቱ ተከፍሏል ወይም አልቋል ብለን እንድናምን ስለሚያደርግ ነው። ህወሓት ላይ ብዙ ኢትዮጵያውያን እምነት የሚያጡት የመሪዎቹ የአርበኝነት ስሜት ቡድናዊነቱ ያይላል ብለው ስለሚያምኑ ነው። ህወሓት ንግድ ውስጥ ሲገባ ይጠረጠራል፣ በአገር ዳርድንበር ጉዳይ ላይ ይጠረጠራል፣ በአገር ፍቅር ላይ ይጠረጠራል። ይታማል። ለምን ሲባል ህወሓት ብሔራዊ አርበኛ ሳይሆን የቡድን አርበኞች ማኅበር ነው ብሎ ብዙ ኢትዮጵያዊ ስለሚያምን ነው። የመንግሥት ተቃዋሚዎች ሆነውም በብሔር ፖለቲካ በጣም የከነፉትን ወገኖች ሁሉ ህዝቡ እንደ አገር የፖለቲካ መሪ አድርጎ አይቶ ተስፋ ሊጥልባቸው አይችልም። በአማራ አካባቢ ይሁን ወይም በሌሎች ብሔሮች አካባቢ ብሔርተኝነት እያበበ መሆኑ ሲሰማን ብዙ ሰው ምቾት የማይሰጠው ይሄ የብሔር የፖለቲካ አርበኝነት ለወደፊቷ አገራችን እጣ ፈንታ ጠቃሚ ባለመሆኑ ነው። በአሁኑ ሰኣት ብሔርተኝነታቸውን በብሔር ፖለቲካ መግለፅ የሚሹ ወገኖች ይህ ነቀፌታ ከሰፊው ህዝብ እንዳለባቸው የሚያውቁ ቢሆንም የቡድን አርበኝነታቸውን መልቀቅ አይሹም። ይልቁን ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለየብሔሩ አርበኛ እንዲሆን ያበረታታሉ። ይህ የአርበኝነት ስሜት አቅጣጫውን ስቷል በሌላው ዓለም ወንጀል ነው ሲባሉ ደግሞ ዓለም ሁሉ የሚደግፈውን ዴሞክራሲ የተባለውን ቅዱስ ስም ከጎናቸው ለጠፍ ያደርጉታል። እናም ዴሞክራቲክ የብሔር አርበኝነት ይሉታል። ዴሞክራቲክ ብሔርተኞች ነን ይላሉ። ይህ ስያሜ የብሔር ፖለቲካን ለመቀደስ የተደረገ ካልሆነ በስተቀር ዴሞክራሲና የብሔር ፖለቲካ ፀብ ናቸው። የብሔር ፖለቲካ በሁለት መንገድ ብቻ ሊፈጠር ይችላል። አንድም አገሪቱ በኮንፌደሬሽን የምትተዳደር ከሆነ ሁለትም ለመገነጣጠልና የራስን መንግሥት መስርቶ ለመለያየት ካማረን፣ ከቆረጥን ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ በፌደራል ሥርዓትም ሆነ በአሃዳዊ ሥርዓት የብሔር የፖለቲካ አርበኝነት ሊኖር አይችልም። አይገባም። በብዙ ዓለም ወንጀል የሆነውም ለዚህ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ የብሔራዊ አርበኞች ስሜት መበረታታት አለበት። በርግጥ ይህ ስሜት በፌደራል ስርዓት ጊዜ ወይ በአሃዳዊ ሥርዓት ወይም በአንድ አገር የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ በጣም አስፈላጊ ስሜት ነው። እንዲህ ዓይነት አርበኞች መብዛት አለባቸው። የተባበረችውን አሜሪካ፣ እስራኤልን፣ ታላቋን ብሪታኒያን፣ የመሳሰሉትን ኀያላን አገራት ስናይ ለኀያልነታቸው ትልቁ መሰረት ወታደሮቻቸው ብሔራዊ አርበኞች ስለሆኑ፣ ሳይንቲስቶቻቸው፣ የፖለቲካ መሪዎቻቸው በአገር ፍቅር የተመሰጡ ታማኝ የሆኑ ስለሆኑ ነው። ይህን ፅሁፍ ሳዘጋጅ የኢትዮ እስራኤላውያንን ወታደሮች እያሰብኩ ነበር። በርግጥ ለአገራቸው ያላቸው ታማኝነት፣ለሙያቸውና ለባንዲራቸው ያላቸው ፍቅር ለእስራኤል ያላቸው ጥልቅ ፍቅር ያስደምማል። አንዲት ወጣት ጀግና የእስራኤል መከላከያ ኦፊሰር “ህልሜ እውን ሆኗል” ብላ ለሙያዋ ያላትን መሰጠትና ፍቅር ስትገልፅ አየሁ። ይህ ቃል ትልቅ ነው። በውስጡ የአርበኝነት ስሜቶችን ሁሉ ጠቅልሎ ይዟል። ይህ ነው የሙያ ፍቅር። ይህ ነው አርበኝነት ማለት። ይህ ነው ወታደራዊ ሴንትመንት የሚባለው።
ጀርመናውያን የበርሊንን ግንብ አፍርሰው ወደ ውህደት ሲመጡ አንድ ሃበርማስ የተባለ ምሁር አንድ ድንቅ አሳብ ይዞ መጣ። ይህ ሳይንቲስት በርግጥ አርበኛ ነበር። ሃበርማስ ያመጣው አሳብ ሁለቱ ጀርመኖች ወደ ውህደት በሚመጡበት ዋዜማ የማንነት ጥያቄ ተነስቶ የነበረ ሲሆን ለዚህ ጥያቄ ይዞት የመጣው መልስ ለጀርመናውያን ሁሉ ህገ መንግሥታዊ አርበኛ (constitutional patriots) እንሁን የሚል የብሔራዊ አርበኝነት አሳብ ነበር። ይህ አሳብ በርግጥ ሁሉን አሳምኖ ጀርመኖችን ሁሉ በአንድ የፖለቲካ ጠገግ ሥር አርበኞች ያደረገ አሳብ ነበር። ሃበርማስ እንዳለው የዜጎች አርበኝነት ስሜት አንድ ማእከል ሲኖረውና በዚያ ላይ የጋራ ማንነት ሲሰራ ያኔ ነው አንድነት የሚመጣው።
ከፍ ሲል እንደተገለፀው ከራሳቸው በላይ ማሰብ በሚችሉ ብሔራዊ አርበኞች ነው ይህቺ አለም የቆመችው። በየትኛውም አገር በየትኛውም መስክ የነዚህ ብሔራዊ አርበኞች በረከት ዛሬ ለዓለም ተርፏል። በሳይንሱ በሚሊተሪው በሲቪሉ በኩል የአለም ጥበብ ያደገው በአርበኝነት ስሜት ነው። አንድ ሰው ከግል ህይወቱ እርካታ በላይ እንዲሰራ ዋጋ እንዲከፍል የሚያደርገው ሃይል የአርበኝነት ስሜት ነው። ታላቁ መሪ ጆን ኤፍ ኬነዲ አገሬ ለእኔ ምን አደረገችልኝ ሳይሆን እኔ ለአገሬ ምን አደረኩ ብለው ዜጌች እንዲጠይቁ መክረዋል። እኝህ መሪ ብዙ ብሔራዊ አርበኞች ከተፈጠሩ አገር እንደሚለውጥ በርቀት ስላዩ ነው። ይህ ስሜት የአርበኝነት ስሜት መሰረት ነው። አርበኞች ለአገሬ ምን ሰራሁ? የሚለውን ያስቀድማሉ። በእንዲህ ዓይነት የአርበኝነት ስሜት የተነኩ ዜጎች ወደ ፖለቲካው አለም ሲመጡ ብሔራዊ አርበኝነታቸውን የሚገልፅ የፖለቲካ ድርጅት ይመሰርታሉ። ኢትዮጵያውያን መረዳት ያለብን ይህንን ነው። ብሔራዊ አርበኝነትን ማበረታታት ያስፈልጋል። መኮትኮት ያስፈልጋል። ይህ አርበኝነት በርግጥ የቡድኖችን ማንነት ያከበረ ብዝሃነትን የአርበኝነቱ መሰረት ያደረገ መሆን ይኖርበታል። ለዚህ ነው ብሔራዊ አርበኞችም ስሜታቸውን መመርመር አለባቸው የሚያሰኘን። የብሔር ፖለቲካ አርበኝነትን እየኮተኮትን አሳድገን ሰማኒያ ሁሉት የብሔር ፖለቲካ አርበኞች ክንፍ መስርተን እንለወጣለን፣ እንበራለን ማለት አልመከር ያለ አርቆ ማሰብ የተሳነው አሳብ ነው። በመጀመሪያ የብሔር አርበኛ እንሁንና ይህ መንግሥት ሲወድቅ አዲስ አበባ ላይ ስለአገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ እንመካከራለን ማለት በጣም ማስተዋል የጎደለው ያልተመረመረ አሳብ ነው። ከፍ ሲል እንደተገለፀው የቡድን አርበኝነት ስሜት ብሔራዊ ማንነትን ሳይጋፋ ሲመጣ ደግሞ ዜጎች ሊያጨበጭቡለት ሊደግፉት ይገባል። ይሄ ነው ብዝሃነት ማለት። በዘመናችን ንፁህ የብሔር ማንነት አርበኝነትን ይዞ ከተነሳ ዜጋ መካከል የኮንሶው ንጉስ ይጠቀሳል። ይህ ንጉስ የፖለቲካ ሥልጣን አላማረውም። በአገሩ ይኮራል። ነገር ግን የኮንሶ ባህል ተጠብቆ ይኖር ዘንድ ይሻልና ለዚህ ማንነት ይታገላል። ነፃ የሆነ የባህል አስተዳደር ይሻል። ይህ ጤናማ የብሔር አርበኝነት ይባላል። በርግጥም የኮንሶ ባህል የኢትዮጵያ ባህል ነውና ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይደግፉታል። በመሆኑም ኢትዮጵያውያን የአርበኝነት ስሜቶቻችንን መፈተሽ ግድ ይላል። ወደ ተሻለ ሥርዓት አገራችን ትገባ ዘንድ በአገራችን የተነሱ አርበኞች መጋጨት የለባቸውም። በቅርቡ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምርና ፓሊሲ ተቋም የተጠናው ጥናት ይህን አሳብ ይደግፋል። በዚህ ጥናት ውስጥ የተገለፀው የብሔራዊ ማንነትና የብሔር ማንነት መገለጫ መርሆዎች በርግጥ ለአገራችን ፖለቲካ መሰረታዊ ለውጥን የሚያመጣ ነው። በመሆኑም በተለይ የብሔር ፖለቲካ አርበኞች ይህን የአርበኝነት ስሜት የዴሞክራሲ ጠበል የተረጨ አስመስለው ይህን አርማ ይዘው ከመነሳት ተቆጥበው ለአገራችን ለውጥ ብሔራዊ አርበኞች ሊሆኑ ይገባል። በአንፃሩ ብሔራዊ አርበኞች ብሔራዊነትን ከአንድ ቋንቋና ባህል ጋር ሳያያይዙ ለዴሞክራሲ ለእኩልነት መታገል ይገባል። እንዲህ ሲሆን ነው ወደፊት መራመድ የምንችለው። አርበኞች እርስ በርስ የሚጋጩበት አገር የትም አይደርስም። በአጠቃላይ በተለያየ ማንነት ላይ ተቆርቋሪ ሆነው የሚነሱ አርበኞች ይህን ስሜታቸውን በፖለቲካ ማንነት ለመግለፅ አይሞክሩ። በሴቶች መብት ዙሪያ ልቧ የተነካ እህታችን በዚህ ማንነት ላይ ሆና የሴቶች የፖለቲካ ድርጅት አታቋቁም፣ ለኃይማኖቱ የቀና ሰው ይህን አርበኝነቱን ለመግለፅ የኃይማኖት የፖለቲካ ድርጅት አያቋቁም፣ በብሔሩ ማንነት በፍቅር የተነደፈ የብሔር አርበኛ በዚህ ማንነት ላይ የፖለቲካ ድርጅት አያቋቁም፣ ነገር ግን ይህን የአርበኝነት ስሜት በነፃ ማኅበራት መግለፅ ዴሞክራሲያዊ ነው።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
ገለታው ዘለቀ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.