የትነበርክ ታደለ

 ECOWAS vs IGAD

ተሸናፊው የጋምቢያ ፕሬዚዳንት ያህያ ጃሜይ ከክብር ራሳቸውን አዋርደው አሁን አገር ጥለው ተሰደዋል። ገና የምርጫው ውጤት እንደተገለጸ የገቡትን ቃል አክብረው ውጤቱን በጸጋ እንደተቀበሉ ቢቀጥሉ ኖሮ ለአገራቸውም ለራሳቸውም ክብር ከመሆኑም ባሻገር ለመላው አፍሪካም አንድ የዴሞክራሲ መሰረት ጥለው ባለፉ ነበር።

ምን ያደርጋል ታዲያ ማን ጠላት እንዳሳሳታቸው ሳይታወቅ ቃላቸውን መልሰው በልተው ለራሳቸውም ውርደት ተከናንበው በጉልበት ከለምለሚቱ አገራቸው ሸሹ።

ይሁን እንጂ ሥልጣኔን በሰላም አላስረክብም ባሉባቸው አምስት ሳምንታት ውስጥ ብቻ የአገሪቱን የምርጫ ስርአት አናግተው፣ ጦሩ ፊቱን ወደ ህዝብና ወደ ተቃዋሚዎች እንዲያዞር አድርገው አገሪቱን ውጥረት ውስጥ ከተቱ። ይህም ብቻ አይደለም ፓርላማውን በሁለት እጅ አንቀው ይዘው ለሶስት ወራት ሥልጣናቸውን እንዲያራዝም ካደረጉ በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀው ሥልጣናቸውን ለማደላደል ይሰሩ ገቡ። በዚህም ተመራጩን ፕሬዚዳንት አዳማ ባሮን ጨምሮ 1.8 ሚሊየን ከሚሆነው ህዝብ 50 ሺህ በፍርሀት አገር ጥሎ እንዲወጣ አደረጉ።

በስተመጨረሻም በአካባቢው በይነ መንግሥታት ኢኮዋስ (ECOWAS) በደረሰባቸው ወታደራዊና ፖለቲካዊ ጫና ሳቢያ ራሳቸው ከአገር ሊወጡ ግድ ሆነ።

በዚህ ጊዜ ውስጥ ኢኮዋስ፦

* የጋምቢያን ጉዳይ ከየትኛውም አለማቀፍ ተቋማት በበለጠ በቅርበት ይከታተል ነበር፣
* ፕሬዚዳንቱ ሥልጣናቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲያስረክቡ ሲያግባባ ቆይቷል፣
* የሰውየውን እምቢታ ተከትሎም ጦሩን ወደ ጋምቢያ አንቀሳቅሷል፣
* ተመራጩ ፕሬዚዳንት ወደ ጎረቤት ሴኔጋል እንዲሄዱና በዚያም ከፍተኛ ጥበቃ እንዲደረግላቸው አድርጓል፣
* በተለይም ተመራጩ ወደ አገራቸው በዚህ ሁኔታ እንዳይመለሱ አድርጎ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መሰረት በስደት እንዳሉ ቃለ መሀላ እንዲፈጽሙ አመቻችቷል።

በጠቅላላው በጋምቢያ ውስጥ ሊመጣ የነበረውን ክፉ ሁኔታ ለማስቀረት ኢኮዋስ ትልቅ ስራ የሰራ ከመሆኑም በላይ በክልሉ አገራት ለሚያደርጉት ምርጫና ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ዋስትና መሆኑን አስመስክሯል።

ለመሆኑ የኛው የምስራቅ አፍሪካ ክልላዊ የልማት በይነ መንግሥታት የሚባለው ኢጋድ IGAD በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ አገራት ምን ሲያደርግ ነበር? ምርጫ በሚካሄድባቸው አገራት ውስጥ በሚከሰት አለመግባባት ኢጋድ ሁሌም ከማን ወገን ተሰላፊ ነው? ሥልጣን ላይ ካለው ወገን ወይስ ከተቃዋሚው? በኢትዮጵያ፣ በኬኒያ፣ በኡጋንዳ በታዩ የምርጫ ውጥንቅጦች ወቅት ኢጋድ የነበረው ድርሻ ምን ያህል ነው? እውን ኢጋድ የኢኮዋስን ያህል ተጽእኖ መፍጠርስ ይችላል? ሁኔታውን በቅርበት የታዘባችሁ ምላሹን ወዲህ በሉን።

ሰላም!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ