ገለታው ዘለቀ

TPLF

ለወትሮው ከገዢው ፓርቲ አካባቢ የተለመደው የተሃድሶ ትርጉም ለየት ያለ ነበር። “ኢህአዴግ” ስብሰባዎችን ያደርግና ሲጨርስ “የተሃድሶ ሰዓት!” ይባልና በዚያን ጊዜ የማእድ አገልግሎትና የተለያዩ መጠጦች የኪነት ትርኢት የሚቀርብበት ሰዓት ተሃድሶ ይባላል። ለአንድ የገዠው ፓርቲ አባል ተሃድሶ ሲባል ቶሎ ወደ ህሊናው የሚመጣው ነገር ድግስ ይመስላል። ከስብሰባ በኋላ ዘና ማለት። ይሁን እንጂ በቅርቡ ጠቅላይ ሚንስትሩ በጥልቀት በመታደስ ላይ ነን ሲሉ የገለፁ ሲሆን፣ ይህ ተሃድሶ በአዕምሮ መታደስን-መለወጥን የሚያሳይ እንደሆነ ተገልፃልናል። ይሁን ይሏል።

መቼስ የተሃድሶ ትርጉም ከድግስ አልፎ እውነተኛ ትርጉሙን ከያዘና በአዕምሮ መታደስን ከጨመረ አንዳንድ ለውጥ የናፈቀው ቢጓጓ አይፈረድም ይሆናል። በመሆኑም ተሃድሶ ከተለመደው ትርጉም አልፎ በአዕምሮ መለወጥን መታደስን ሪፎርሜሽንን ካመጣ ግሩም ነበር። እንግዲህ ጠቅላይ ሚንስትሩ በጥልቅ ተሃድሶ ላይ ሰነበትን ካሉ ለውጥ ያለ ልክ የናፈቀው ሰው በጥልቀት በመታደስ ላይ ከከረመ ፓርቲ የሚጠብቀው ጥልቀት ያለው ጉዳይ አለ። አንድ ድርጅት በጥልቀት ልታደስ ካለ ጥልቅ ችግሮች ገጥመውታል ማለት ነው። የችግሩን ጥልቀት ተገንዝቧል ማለት ነው። ይህ ፓርቲ የገጠመውን ጥልቅ ችግር ተረድቶ ለመውጣት ቆርጧል ማለት ነው። እናም ለውጥ ናፋቂው ሕዝብ የሚጠብቀው ጉዳይ መውጣት (exodus) ነው። ገዢው ፓርቲ እንደ ፓርቲም እንደ ግለሰብም በምን በምን ጉዳዮች ላይ መውጣት exodus ሊያውጅ ይገባል? በሚለው ላይ ትንሽ እንወያይ።

1. የፖለቲካ ኮሚትመንት ለማምጣት መውጣት

በጥልቅ መታደስ ማለት በጥልቀት ራስን ከውጭ ወደ ውስጥ ከውስጥ ወደ ውጭ አይቶ በደካማው ጎን ላይ ለመፀፀት ብቻ አይደለም። ጥልቅ ተሃድሶ መውጣት ማለት ነው። ዘ ፀዓት ማለት ነው። ሕዝብ ካልወደዳቸው የፖለቲካ አስተሳሰቦች፣ ከያዙን የብሔር ፖለቲካዊ አርበኝነት ስሜትና አደረጃጀት፣ ከፍርሃት፣ ብዙ አመት ተጉዘንባቸው ከሕዝብ ካጋጩን አስተሳሰቦች በጀግንነት መውጣት ማለት ነው ጥልቅ ተሃድሶ ማለት። በጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ ከረምኩ ያለ ፓርቲ ከግምገማው ማግስት ካጠፋቸው ጥፋቶች ሙሉ በሙሉ መመለስ ይጠይቃል። ከመፀፀት ያለፈ እርምጃ ይሻል።

ከብዙ ዓመታት በፊት አንድ ጲላጦስ የሚባል ዳኛ ነበር። ይህ ዳኛ ተሰሚነት የነበረው አንቱ የተባለ ዳኛ ነበር። ታዲያ አንድ ቀን አንድ ለሙያው ያለውን አርበኝነት የሚፈትን ሰዓት መጣበት። አንድ ንፁህ ሰው በሃሰት ተከሶ ወደዚህ ዳኛ መጣ። በዚህ ንፁህ ሰው ላይ ሕዝብን የሚያወናብድ ስራ ተሰርቶ አገር ተሸብሯል። ጲላጦስ ግን ሁሉን ያውቅ ነበርና በዚህ ሰው ላይ ለመፍረድ አንጀቱ አልቻለም። ይሁን እንጂ የቆረጠና የወጣ ዳኛ አልነበረም። ከዚያም ከዚህም ሳይጠየቅ ይህን ፈተና ለመወጣት የጣረ ብልጣብልጥ ዳኛ ነበር። እናም ለካህናቱና ለተከታዮቻቸው እኔ ከዚህ ሰው ምንም ጥፋት አላየሁም ነገር ግን እናንተ ካላችሁ የፈለጋችሁትን አድርጉ አላቸው። ይህ ብቻ ሳይሆን ለበኣል አንድ ወንጀለኛ ይለቀቅ ዘንድ አሳብ አቀረበና በርባን የተባለውን ወንበዴ ለቀቀ። በርግጥ ኢየሱስን የሰቀለው የእስራኤል ሕዝብ ወይም አይሁዳውያን ሁሉ አይደሉም። የተወሰኑ ካህናት ያወናበዷቸው ሰዎች ነበሩ። ጲላጦስ ይህን ያውቃል። ነገር ግን ሙያውን ህሊናውን ሰብሮ ከስራው መቆየትን መረጠ። ነገር ግን ከዚያ ሰው እዳ ነፃ ነኝ ብሎ እጁን መታጠቡ ከተጠያቂነት ነፃ አያወጣውም። ይህ ዳኛ አልወጣም። እጁን ታጠበ እንጂ ከህሊና ክስ ነፃ አይሆንም። ህሊናው አይታጠብለትም። እጁን ቢታጠብም ከፍርሃት የተነሳ ወንጀለኛ ለቆ ንፁህን ሰው አሳልፎ ሰጥቷልና በአዕምሮ አይታደስም። ይህ ዳኛ መውጣት ነበረበት። መውጣት እንደ ብርቱካን ሚዴቅሳ ነው። መውጣት ደረጃው ከፍ ያለ ነው። በጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ ከገቡ ካድሬዎች መሃል ድርጅቱ ከሕዝብ ጋር መራመድ ያልቻለ መሆኑን የተረዱ ነገር ግን በፍርሃት ውስጥ ሆነው ያሉ አባላት ሁሉ ምን አልባት በዚህ ጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ እጃቸውን መታጠብ አይበቃም። እምቢኝ ያሉ የወጡ ካድሬዎች ሲኖሩ ነው ለውጥ የሚመጣው። እነ ዶክተር መረራን፣ እነ እስክንድርን የመሳሰሉ ንፁህ ሰዎች ጉዳይ በጥልቀት ለመታደስ ለወሰነ ፓርቲ በርግጥ ለመታደስ ከልብ ፈቃደኛ ይሁን አይሁን ማሳያ ነው። ካድሬዎች በነዚህና በሌሎች ንፁሃን እስራት ላይ እጅ ከመታጠብ አልፈው ሊወጡ ይገባል። በመሆኑም ከጥልቅ ተሃድሶ ባሻገር የሚጠበቀው ነገር ከፍ ያለ እርምጃና ውሳኔ ነው። እንደ ጲላጦስ ያሉ ካድሬዎች የራሳቸውን ሥራ ከማቆየት ያለፈ ጥቅም አያመጡም። ሕዝብ የሚሻው የፖለቲካ ኮሚትመንት ነው። በመሆኑም ከዚህ ጥልቅ ተሃድሶ ሕዝብ የሚጠብቀው እጅ መታጠብን ሳይሆን እንደ ብርቱካን ሚዴቅሳ የውሳኔ ሰው እንድትሆኑ ነው። ያን ጊዜ ነው የጥልቅ ተሃድሶ ትርጉም የሚኖረው። ጲላጦስን አለመሆን ነው። በነገራችን ላይ ዳኛ ጲላጦስ በመጨረሻ ራሱን እንዳጠፋ ተመራማሪዎች ፅፈዋል።

2. ለብሔራዊ መግባባት ሁኔታዎችን ለማመቻቸት መውጣት

ሌላው ጉዳይ ገዢው ፓርቲ እንደ ፓርቲ ከጥልቅ ተሃድሶ ማግስት የሚጠበቅበት ነገር የብሔራዊ መግባባት ጥሪ ነው። አገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ በከፍተኛ ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ ናት። ማኅበራዊ ካፒታላችን እጅግ ወርዷል። ይህ ደግሞ አደገኛ ነገር ነው። የኢኮኖሚው እድገት ብዙ የመረጃ ችግር እንዳለበት ተገልጿል። ሙስና አገሪቱን ሊያፈርስብን ነው። የሰው ልጅ ይራባል። እጅግ ብዙ ህፃናት ጎዳና ወጥተውብናል። ሕዝቡ በኑሮ ውድነት እያነባ ነው። ወጣቱ ተሰደደ። ብዙ ወጣት ምድረ በዳ ቀረብን። ሴቶች በአንዳንድ አረብ አገራት ተሰቃዩ። ፖለቲካችን ውጥረት ውስጥ ነው። ሁኔታዎች በዚህ ሊቀጥሉ አይችሉም። በዚህ ወቅት አንድ ገዢ ፓርቲ ጥልቅ ተሃድሶ አደረኩ ካለ የምንጠብቀው ነገር ሃቅኛ ዲያሎግ ለማድረግ ቆርጦ መውጣትን ነበር። ከአንዳንድ ፓርቲዎች ጋር መራርጦ ንግግር አደረኩ ለማለት ያህል ሳይሆን መንግሥት ከማይወዳቸው ጋርም ለመነጋገር መውጣትን ይጠይቃል ጥልቅ ተሃድሶ። ለአገራችን መፃኢ እድል ትልቅ ተስፋ ያለው ከምክክር የሚመጣ መፍትሄ ነው። ብዙ ተቃዋሚን አግልሎ ጥቂት ፓርቲዎችን ሰብስቦ ብሔራዊ ምክክር እያደረግን ነው ማለት አይቻልም። ሁሉን አቀፍ ባልሆነ መድረክ ላይ የሚጋበዙ ፓርቲዎችም በሃቀኝነት እኛ ብቻ ሳንሆን ስለአገራችን የምናስበው ሌሎች ሃይሎችም ስላሉ እነሱም መጋበዝ አለባቸው አለበለዚያ ለማስመሰል የሚደረግ ውይይት ተገቢ አይሆንም ማለት አለባቸው። ለውጥ ፈላጊ ነን ለሕዝብ ነው የቆምነው የሚሉ ፓርቲዎች ሁሉ ይህን ጉዳይ ማንሳት አለባቸው። የገዢው ፓርቲ አባላትም መንግሥት ሁሉን አቀፍ ውይይት ያደርግ ዘንድ ፓርቲውን ወጥረው መያዝ አለባቸው። እውነት በጥልቀት ከታደሱ።

3. ይቅርታ ለመጠየቅ መውጣት

በአዕምሮ መታደስ ለማምጣት እልህ ወይም ደግሞ ትንሽ ለውጥ ፈልጎ እንደ ጲላጦስ እጅ መታጠብ ጥሩ አይደለም። መሪዎች እንደ ድርጅት ድርጅታቸው በሰራው ስህተት በብዙዎች ህይወት ላይ ተፅእኖ ፈጥሯልና መንግሥት ይቅርታ ለመጠየቅ መውጣት አለበት። ይቅርታ እድሜን ይጨምራል። ኮሙኒኬሽንን ያስተካክላል ያድሳል። ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰፈር የጠፋው ይሄ ነው። ይህ ሁሉ ችግር እየተፈጠረ መንግሥት ሃላፊነት የማይወስድ ከሆነ ከሕዝብ ጋር ይቆራረጣል። ባለሁበት የዓለም ክፍል መንግሥት ወይም መሪዎች ላጠፉት ጥፋት ይቅርታ ሲጠይቁ ማየት የተለመደ ነው። ይህ ዓይነት ልብ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ መሪዎች ሰፈር መገኘት አለበት። ይቅርታ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን የእርምት ርምጃ መውሰድን የሚጠይቅ ነው ይቅርታ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ልቦናው ቅን ነው። ይቅርታ ሲባል ርህራሄንና ክብርን በአፀፋው የሚዘረጋ ሕዝብ ነው። በመሆኑም በጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ ከረምኩ የሚለው ገዢ ፓርቲ የሚጠበቅበት አንዱ ነገር ይቅርታ መጠየቅ ነው። አንዳንዴ የሚገርም ነገር ይሰማል። መንግሥት ጥሩ ስራ ሥሠራ ጥሩ ሰራህ አልባልም መጥፎውን ብቻ ነው የሚያዩት ይላል። እንግዲህ ፖለቲካዊ መሪ መሆንን የመረጠ ሰው ይህንን መረዳት አለት። ጤና ኬላ በሰራ ቁጥር አጨብጭቡልኝ ማለት አይገባም። ሕዝብ ያውቃል። ምስጋናው ተገቢ ከሆነ ይሰጣል። ብዙ ጊዜ ዜጎች ህንፃ ተሰራልን ብለው መንግሥትን ለማመስገን ሰልፍ አይወጡም። ነገር ግን የመንግሥትን ድክመቶች እያወጡ መናገር የበለጠ ህብረተሰቡ ለህይወቱ ይጠቅመዋል። መንግሥት ድክመቶቹን ቶሎ እንዲያስተካክል ከመሻት ፈጣን ለውጥን ከመፈለግ ነው። በመሆኑም የፖለቲካ ፓርቲ ይቅርታ ቢጠይቅ ክብር ይጨምራል።

4. የባህርይ ለውጥ ለማምጣት መውጣት

አልፎ አልፎ ስለ ገዢው ፓርቲ አመራሮች አስባለሁ። የውነት ለመናገር ባለ ሥልጣን ለምን ያጠፋል አልልም። እንደማንኛውም ዜጋ ማለቴ ነው። የሚገርመኝ ግን የማይማር መሪ ነው። በገዢው ፓርቲ አካባቢ ግምገማ የሚባለው አውጫጭኝ አይነት ነገር የተለመደ ነው። የግል ህይወት ሳይቀር በከፍተኛ ሁኔታ እየተዘረዘረ እርስ በርስ ይገማገማሉ። ግምገማችን ሳሙናችን ሲሉም እሰማለሁ። የሚገርመኝ ታዲያ የአንዳንድ መሪዎችን ሁኔታ አይና አሁን ይሄ መሪ ሰላሳ ኣመት ተገምግሟል? አሁን ይሄ ሰው አርባ ኣመት ተገምግሟል? እላለሁ። በዚያ ድርጅት ውስጥ አርባ ዓመት ቆይተው እንዴት ወደ ኋላ ይሄዳሉ እንደምን እውቀትና እንደምን ትህትና አልጨመሩም ያሰኛል። ምን አልባት ይህ ግምገማ ለድርጅቱ ጠቅሞ ይሆናል ። ፈሪ የሆኑ አባላትን ለማፍራት ጠያቂ ካድሬዎችን ለመምታት ጠቅሞ ድርጅቱን ደግፎ ይሆናል እንጀ ገዢው ፓርቲ ከዚህ የግምገማ ባህል ጥሩ ያገር መሪ ሲያፈራልን አናይም። እንዴውም ይህ ግምገማ አንዳንዱን ጥሩ አድርጎ አደንዝዞታል አንዳንዱን ደግሞ የጦፈ ጮሌ አድርጎብናል። የግምገማ መስመሮችን እያጠና ነገር ግን ረቂቅ ሙሰኛ ራእይ የለሽ ብዙ ሰው አፍርተናልና። ገዢው ፓርቲ ይህን ማጥናት ይገባው ነበር። በጥልቅ መታደስ የተባለው ይህን ዘዴ ተጠቅሞ ከሆነ ያ ተሃድሶ የሚባል ነገር ገዢው ፓርቲ መጀመሪያ ከሰጠው የተሃድሶ ትርጉም የዘለለ አይሆንም። ከድግስ ያለፈ ትርጉም አይኖረውም ። ገዢው ፓርቲ ያለበት አንድ ትልቅ ችግር በግምገማ ወቅት ብዙ ጊዜ የሚያየው ተዋንያኑን ነው። የሕዝብ ጥያቄ ደግሞ የሲስተም የፓሲሲ ጥያቄ ነው። ከገዢው ፓርቲ ግምገማ የምናተርፈው ፓርቲው አይዲዮሎጂውንና ፓሊዎችን በጥልቀት ገምግሞ ሲወጣ ነው እንጂ የካቢኔ ሹም ሽር አይጠቅምም። የባህሪ ለውጥ ሲባል አንዳንድ መዘንጋት የሌለባቸው ጉዳዮች አሉ። ከፍ ሲል እንዳልነው “የኢህአዴግ” ግምገማ ከባህርይ ለውጥ አንፃር ምን ላይ ከረምክ? ሲባል በሙስና ዙሪያ የአዕምሮ መታደስ ለማምጣት ሕዝባዊ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሥሰራ ነበር ቢለን ቀልድ ነው የሚሆነው። እኛ የባህርይ ለውጥ የምንለው አብሮ ለመስራት፣ ለመቻቻል ፖለቲካ፣ ለእርቅ፣ ለአቅም ግንባታ፣ ለአመራር ብቃት፣ ለአርበኝነት ስሜት መዳበር እንጂ ለሙስና የምን የሕዝባዊ ግንዛቤ ስራ ነው ደሞ። ስርቆት ወንጀል እንደሆነ ግንዛቤው አለ። ይህ ነገር የሚጠፋው በጠንካራ ህጎች፣ በዘዴ እንዲሁም በተሻለ ሲስተም ነው። ሙሰኛ በሆነ ሲስተም ውስጥ ያሉ አባላትን እንዳትሰርቁ በማለት አይቆምም። ሙስናን ለመምታት ሲስተሙ መለወጥ፣ የፖለቲካውና ሙሰኛ የሆነው የኢኮኖሚ ሥርዓት መለወጥ አለበት። ችግሩ መንግሥት ሙስናን ከላይ ልምታ ቢል ሥርዓቱ ድርምስ ይላል። የሥርዓቱ ተራዳ ሙስና ስለሆነ። በመሆኑም ጥልቅ ተሃድሶ በመንግሥት አካባቢ ትርጉሙ ከባድ ነው። የሥርዓት ለውጥ ነው ጥልቅ ተሃድሶ ማለት።

5. የሕዝብ ግንኙነትና የፕሮፓጋንዳ ለውጥ ዘ-ፀዓት

በርግጥ መንግሥት በጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ ከቆየ ከቅራኔ ፖለቲካ መውጣት አለበት። ተቃዋሚውን እንደ ባላንጣ እንደ ጠላት ያየዋል። ይሄ አደገኛ ባህል ነው። ተቃዋሚውን እንደ ባላንጣ ከማየት የተነሳ በቅርብ ያለውን በእስራት ይመታዋል ግማሹን ያጠፋዋል። ትንሽ ራቅ ያለውን ጥገኝነት ጠይቆ የሚኖረውን ደግሞ በረቀቁ ዘዴዎች ለማጃጃል መሞከር አይገባም። ቢያንስ የሌላውን አገር የዴሞክራሲ ባህል ማክበር ይገባል። በየአገሩ የተዘለሉ ጥገኞች እንዳይናገሩ እንዲሸማቀቁ በማድረግ ተቃዋሚን ዝም ለማድረግ መሞከር ከሁሉ የከፋ ድፍረትና ወንጀል ነው። ዓለም የሚዋጋው ነገር ነው ይሄ። መቆም አለበት። ድሆች የሚበሉት ባጡባት አገር ብዙ ገንዘብ እያፈሰሱ ጉቦ እየሰጡ ውጭ ያለውን ተቃዋሚ ማጥቃት ድርጅቶች እንዳይንቀሳቀሱ ማድረግና ከተቀናቃኝ ነፃ የመሆን ዝንባሌ አደገኛ አደገኛ ነው። በመሆኑም በርግጥ ጥልቅ ተሃድሶ ከተደረገ መንግሥት ተቃዋሚውን ማጥቃቱን ማቆም አለበት። እንደ ባላንጣ ማየቱን ለማቆም መውጣት ይጠይቃል ጥልቅ ተሃድሶ። ሃቀኛ የፓርቲ አባላት ይህንን ተቃውመው መውጣት ከቻሉ ነው በጥልቅ ታደስን የሚባለው። በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝብ መስማት ያንገሸገሸውን የመንግሥት ፕሮፓጋንዳ መለወጥ ይጠይቃል ጥልቅ ተሃድሶ። አገራችን በፈጣን እድገት መመዘኛ ከአፍሪካ አንደኛ ወጣች የሚለውን ዜና ሲሰሙ አንዳንዶች ደማቸው ይፈላል። አንዳንዶቹ ደግሞ መቀለጃ ያደርጉታል። እውን እነዚህ ወገኖች የአገራቸውን የራሳቸውን እድገት ማየት ጠልተው ነውን? አይደለም። መንግሥት በስልጣን ለመቆየት የሚረዳኝ ፕሮፓጋንዳ ነው ብሎ እንደሚያምን ስለገባቸውና በተግባር የሕዝቡን ህይወት ኑሮውን ስለሚያውቁት ነው። መንግሥት እድሜ ይቀጥልልኛል ብሎ የሚያደርገው ፕሮፓጋንዳ ከሕዝብ እያቆራረጠው ነው። በውነት በአዕምሮ መታደስ ካለ ፕሮፓጋንዳውን በተቃዋሚ ላይ ያለውን ዘመቻ መለወጥ ይጠይቃል። ይህን የፕሮፓጋንዳ ባህል መለወጥ ያስፈልጋል።

6. መተማመንን ለመገንባት መውጣት

ከፍ ሲል አንድ ሁለት እያልኩ ያነሳኋቸው ጉዳዮች በጣም የተለያዩ አይደሉም። ግንኙነት አላቸው። ነገር ግን ትኩረት የሚሹ ስለመሰለኝ ነው። በመንግሥትና በሕዝብ መሃል መተማመንን የሚያመጡ መስመሮች በኢትዮጵያ ውስጥ ተቆርጠዋል። ገዢው ፓርቲ በግምጃ ቤቱ መሳሪያ ስለሞላ አላሳሰበውም እንጂ ቀጥታ መተማመን ትንኗል ወይም ( vertical trust evaporated in Ethiopia ) ይሄ ጉዳይ ራእይ ላለው ድርጅት የሚያሰጋ ነው። በተከታታይ ዓመት የሚወጡ የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ጥናቶችን ብናይ ቀጥታ መታመን ከሚገባው በላይ ወርዷል። አንድ ጊዜ ባየሁት ጥናት ላይ ሕዝቡ ከፌደራል መንግሥት ይልቅ የምርጫ ሂደትን የበለጠ አያምንም። ይህ ማለት ከራሱ ከኢህአዴግም በላይ ምርጫ ቦርድ አይታመንም ማለት ነው። ጥልቅ ተሃድሶ ማለት ተራውን ካድሬ እንትና ቤት ገብተህ ነበር፣ ከተቃዋሚ መሪ ከአቶ እከሌ ጋር ያለህ ግንኙነት ምንድን ነው? አውጣ...... ከማለት ይልቅ ተቋማቱ ሕዝባዊ አመኔታ ጨርሶ የላቸውም እንዴት አድርገን ፈጠርናቸው? እንዴት አድርገን ነፃ እናውጣቸው? ብሎ መወሰን ነው ጥልቅ ተሃድሶ ማለት። መውጣት ማለት የፍርድ ቤቱን ልጓም እንልቀቀው፣ የመጣው ይምጣ ብሎ መወሰን ነው። ጥልቅ ተሃድሶ ይህንን ያመጣል። ከዚህ ውጭ ጥልቅ ተሃድሶ ጥልቅ ለውጦችን ካላመጣ ተሃድሶ የሚባለው ነገር ቀድሞ የተሰጠውን ስም ይይዛል።

7. የታሰሩ ፖለቲከኞችን ጋዜጠኞችን ለመልቀቅ መውጣት የሲቪክ ማኅበራትን መልሶ ማቋቋም

አንዱ ከጥልቅ ተሃድሶ የሚጠበቀው ነገር እያደር እየኮሰሰ የመጣውን የሲቪክ ማኅበራት ጉዳይ ማንሳት ነው። የምር ጥልቅ ተሃድሶ ከመጣ የተዘጉ የሲቪክ ማኅበራት እንደገና ስራ ይጀምሩ ዘንድ ማድረግ የሃቀኛ ተሃድሶ ውጤት ነው። የተዘጉ ጋዜጦች ይጀምሩ ዘንድ ጥሪ ማድረግ፣ ሌላው ቀርቶ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከብዙ ዓመታት በፊት የተባረሩ ምሁራንን እንዲመለሱ መጋበዝ በርግጥ ጥልቀት ያለው ተሃድሶን ያሳያል። ተዘልለው ለሚኖሩ ጋዜጠኞች ዋስትና መስጠትና ወደ አገራቸው ገብተው እንዲሰሩ ማድረግ የሃቀኛ የጥልቅ ተሃድሶ ውጤት ነው። የፌደራል ፓሊስ የሰባበረውን የድሆች ሳተላይት ዲሽ መካስ ነው ጥልቅ ተሃድሶ። የተዘጉ የሲቪክ ማኅበራት እንዲጀምሩ ማድረግ የተሃድሶ መገለጫ ነው። በአጠቃላይ ጥልቅ ተሃድሶ ለሽግግር ለለውጥ ብቁ ሆኖ መውጣትን የሚያሳይ ነው። በቅርቡ የተነሳውን ሕዝባዊ ጥያቄ ለመፍታት መቁረጥ ነው ጥልቅ ተሃድሶ።

ማጠቃለያና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በሚመለከት

ይህን ፅሁፍ ሳዝጋጅ ወደ 22 ፓርቲዎች ከመንግሥት ጋር ድርድር ሊያደርጉ እንደሆነ ዜና ይሰማል። ነገር ግን ሃቀኛና ችግር ፈቺ የሚሆን ውይይት ይመጣ ዘንድ ሁሉን አቀፍ ውይይት ለማድረግ መንግሥት መቁረጥ መውጣት አለበት። በአንፃሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የሕዝቡን እውነተኛ ፍላጎት በሃቀኝነት ማንፀባረቅ አለባቸው። ከሕዝብ ፍላጎት የወጣ ድርድር ማድረግ አይገባም። ሕዝቡ የሥርዓት ለውጥ ይመጣ ዘንድ በሃይል መፈለጉ በነዚህ ተቃዋሚዎች አማካኝነት በመድረክ ሊገለፅለት ይገባል። በሕዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች ዙሪያ ማመቻመች ትዝብት ላይ ይጥላል ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ ስህተትም ይፈጠራል። በድፍረትና በሃቀኝነት አገሪቱ ወደ ምርጫ እንድትገባ፣ ብሔራዊ እርቅ ኮሚሽን እንዲቋቋም መታገል ይጠበቅባቸዋል። አገሪቱን ከጥፋት የሚያድናትና መረጋጋትን የሚያመጣው የሽግግር ጊዜ ከተመቻቸ ነው። ብሔራዊ እርቅ ከመጣ ነው። መንግሥትን በርግጥ ጥልቅ ተሃድሶ አድርገህ ከሆነ የጥልቅ ተሃድሶ ውጤት መውጣት ነውና ውጣ! ማለት ይጠበቅባቸዋል ፓርቲዎች። መንግሥት ይህን ድርድር በአገሪቱ የተነሳውን ተቃውሞ ለማቀዝቀዝ ወይም የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የብሔራዊ መግባባት ግፊት ለማስቀየስ ሊጠቀምበት አይገባም። የኢትዮጵያ ሕዝብም የሚፈልገው ለውጥ እስኪመጣ ድረስ ስልቶችን እየቀያየረ መታገል አለበት።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ