ነፃነት ዘለቀ

Prof. Haile Larebo

በስንቱ አፍረን እንደምንዘልቀው አሁንስ ግራ ገባኝ። ይሄኮ ከነፍስ ግድያ አይተናነስም።

ዐረቦች እንዲህ ይቀልዱብናል አሉ - ከተጨባጩ እውነት ስንነሳም በጣም ልክ ናቸው። እየጎመዘዘንና እየመረረንም ቢሆን ልንቀበለው ይገባል። የብዙዎቻችን ወቅታዊ ምግባር ገሃድ እያወጣብን የሚገኝን መጥፎ አድራጎት በማይበልጥ የታሪክ ድርሣንና በከንቱ ውዳሤ ልናድበሰብሰው ብንሞክር “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” እንደሚባለው ከመሆን አይዘልም።

ፈጣሪ ሀበሻን መንገድ ላይ ያገኘዋል። “አንተ ሀበሻ፣ ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ? የፈለግኸውን ጠይቀኝ አደርግልሃለሁ። ነገር ግን ያን የማደርግልህን ነገር ለጓደኛህ ዕጥፍ አደርግለታለሁ።” ይለዋል። ሀበሻውም “ላስብበትና ልንገርህ ጌታ ሆይ!” በማለት ለማሰቢያ የሚሆን ፋታ እንዲሰጠው በትህትና ይጠይቀዋል። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሀበሻው አስቦ አስቦ ሲጨርስ እፈጣሪ ዘንድ ይቀርብና “ጌታየ አንድ ዐይኔን አጥፋልኝ!” ብሎ ይጠይቃል - የጓደኛው ሁለት ዐይን እንዲጠፋ - እርሱ ግን በአንድ ዐይኑ እንዲኖር። ይህን ወደ እውነት የቀረበ ተረት በበሬ አስመስለው የሚያወጉትም አሉ፤ አንዱን በሬውን እንዲገድልለት ይጠይቅና የጓደኛውን ሁለት በሬዎች እንዲገድልለት።

ሀበሾች ስንትና ስንት ደጋግ ማኅበራዊ ዕሤቶች እንዳልነበሩን አሁን አሁን ለይቶልን የምቀኝነት መፍለቂያ ዋሻ መሆናችን በጣም የሚያሣዝን ነው። ምን እንደሚሻለን እግዜር ይወቅልን። ከፈጣሪው ጋር የታረቀ እውነተኛ የሃይማኖት አባት ቢኖረን ኖሮ ብሔራዊ የምህላና የእግዚኦታ ዐዋጅ የሚያሳውጅ አደገኛ የቅስፈት ዘመን እንደመጣብን ተረድቶ ሕጻናትና ጥጆች ሳይጠቡ ወደ ላይ እንድንጮህ ያደርግ ነበር።

ይህን ብሶት የምናገረው በሰሞነኛ ጉዳዮች እጅግ ስለተደናገጥኩ ነውና ጥቂት ንጹሓንና መልካም ሰዎችን ይቅርታ ልጠይቅ ይገባኛል። በነገራችን ላይ ያ ሙግድ አፍ አቦይ ስብሃት የሚሉት ሰድቦናል አሉ። ሲያንሰን ነው። ይህ አሳዳጊ የበደለውና ጥላቻንና ቂም በቀልን ሲጋት ያደገ ሰውዬ ምን ብሎ እንደሰደበን በቅጡ አልሰማሁትም። ነገር ግን ምንም ቢለን ምን ከርሱ ዘንድ ጥፋት የለበትም ባይ ነኝ። የርሱ አንዱን መልክ የያዘ ነው። ከመነሻው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን አይወድም ብቻ ሣይሆን ከአጥፊዎቿ ጋር አብሮና ተባብሮ ይህችን ቅድስት ምድር ከነታሪኳ ከምድረ ገጽ ሊያጠፋት ተነስቷል። ስለዚህ የርሱን መሳደብ ከቁም ነገር ጥፎ መናደድም ሆነ ጊዜ ማባከን ምን ላይ ተቀምጦ ምንትስ ገማኝ እንደማለት ነው። ይልቁንስ የኛን ጉድ እንፈትሸው። ከርሱ የበለጥን ተሳዳቢዎችና “ነፍሰ ገዳዮች” በየአገራቱ ተደብቀን የምንረጨው መርዝ አገርን እያባላ ነው። ይህ ቀን ሲያልፍ ብዙዎቻችን እምን እንደምንገባ ሳስበው ከአሁኑ ይጨንቀኛል። ክፉ ነገር እስኪያልፍ ማልፋቱ ከፋ እንጂ ይህ የባለጌዎች ቀን ያልፋል። ሲያልፍ ግን ዝም ብሎ አያልፍም፤ ብዙ አቧራ አስነስቶና የጭቃ ደለልን ጠራርጎ ነው። ያኔ የአሁኑ “እዩኝ እዩኝ” ባዩ “ደብቁኝ ደብቁኝ” ይላል። ያኔ ብዙ ላለማልቀስ የአሁን ሣቅን መቀነስ ይገባል። ፍርድ አትቀርም። ፍርድ ደግሞ ለራስ ነው - የምትሠራት ሁሉ ነፍስ ዘርታ ትጠብቅሃለች - የማምለጫ በርም የለህም። ተረቱም “ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ…” ይላል።

ሰሞኑን ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦን ከሥራ እንዲታገድ ለማድረግ “ኢትዮጵያውያን” በልበ ሙሉነት ማለቴ በልበ ድፍንነት ተንቀሳቅሰዋል አሉ። ምን ዓይነት ጉዶች ነን? በሰው አገር ሊያውም የመናገርና ሃሳብን በማንኛውም መንገድ መግለጽ በተግባርም በዐዋጅም በተረጋገጠበት አገር የሰው ፍርፋሪ እየበሉ ወገን ላይ እንዲህ መጨከን ምን ይባላል? የስብሃት ስድብ ታዲያ ከዚህ ጋር እንዴት ይወዳደራል? አሁንም እደግመዋለሁ ሲያሰን ነው። እስኪ የኅሊና ጓዳችሁን ክፈቱና አስቡት - አካላዊ ዐይኖቻችሁን ጨፍኑና በአርምሞ ሆናች ነገረ ሥራችንን መርምሩ - ወዴት እያመራን እንደሆነ ተገንዘቡ። ይህን ብልግና እኔ ስም አጣሁለት። አንድን ሰው የፈለግኸውን ያህል ብትጠላው በእንጀራው አትመጣበትም፤ በባህልም፣ በሃይማኖትም፣ በፍጡርነትም ነውርና ትልቅ ወንጀልም ነው።

ከወያኔ በስተቀር እንዲህ ያለ ፍጡር አለ ብዬ አላምንም ነበር። ወያኔዎች ግን ሲፈጠሩ ጀምሮ ታህተ-ሰብዕ (subhuman) እንደሆኑ ከተግባራቸው ስለተረዳሁ እነሱ ምንም ቢያደርጉ አይገርመኝም። ዜጎች አማራ በመሆናቸው ብቻ ባልንም ሚስትንም በብጫቂ ወረቀት ከየሚሠሩበት መሥሪያ ቤት በአንድ ጀምበር ያባረሩና እጅግ በርካታ ቤተሰቦችን በርሀብ አለንጋ የገረፉ አሁን ደግሞ ከዚያም በባሰ በአማራ አካባቢዎች በግልጽና በሥውር ብዙኃንን የሚገድሉ መሆናቸውን ለሚገነዘብ ሰው ወያኔን እንኳን ጦም በማሳደር በኦሽትዊዛዊ የጋዝ ቼምበር ታላቅ ዕልቂትን ከመፈጸም ያፈገፍጋል ብሎ ቅንጣት አይጠረጥረውም - “The Evil that Men Do” የሚል ቆየት ያለ ፊልም አለ - ይህን ፊልም እዩና የወያኔን ዕኩይ ተፈጥሮ ተረዱ። ከነዚህ “ሰዎች” ብሶ መገኘት ነገን እንድንፈራ ቢያደርገን ታዲያ አይፈረድብንም - ግን መጪውን ጊዜ አንፈራውም፤ ስለምናውቀው። ሰው ዕድሜ ልኩን አያለቅስማ! ደግማችሁ አስቡት - “እገሌን ከሥራ አስወጡልን!”፤ “ሥራ ስጡልኝ” ይባላል እንጂ እንዴት “ከሥራ አስወጡልን” ይባላል? ለሰሚም እኮ ግራ ነው።

“ወገናችን”ን ከሥራ ለማሳገድ ቆርጦ መነሣት ማለት የሚቀምሰውን እህል ውኃ ማሳጣት ማለት ነው - በዚያውም መግደል፤ ግድያ ደግሞ መሣሪያን አይመርጥም - በጥይት መግደልም በርሀብ መግደልም ያው ነው። እንዲያውም በጥይት መግደል በርሀብ ከመግደል የበለጠ “ሰብኣዊ” ነው ማት ይቻላል፤ ጣር የለውም ቢኖረውም የርሀቡን ያህል አይጠናምና። “በጊዜ የጮኸ ጅብ አያሳድረኝም” ይላል የአገሬ ባላገር። እንደነዚህ ያሉ ማፈሪያ ዜጎች ወደሚቃዡበት የአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ቢገቡ ፊታቸውን የሚያዞሩበትን ሰው በቆንጨራና በሜንጫ አንገቱን እንደማይቆርጡት ምንም ማስተማመኛ የለንም። የገባንበት አረንቋ የተለዬ ነው። እነዚያ ተቻችለውና ተስማምተው ይኖሩ የነበሩ ብልኅና አስተዋይ የጥንት ኢትዮጵያውያን ወዴት ሄዱ ግን? እነምኖች ነን በነሱ ቦታ የተተካነው? እግዚኦ እንበል! ሱባኤም እንግባ። በቁማችን ተበለሻሽተናል ጎበዝ።

ይህ ዓይነቱ አሣፋሪ ዘመቻ ደግሞ በአንድ ሰው ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም። አንድ ኢትዮጵያዊ እውነትም ይናገር ሀሰት ሃሳቡን በሃሳብ መሞገት ሲያቅት ወደዚህ ጫፍ የምንሄድበት አጋጣሚ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተበራከተ ነው። በአገር ውስጥ በሕወሓት የተጀመረው ይህ ዓይነቱ ወያኔያዊ ደዌ እየተስፋፋ መጥቶ መላው ዓለምን እያዳረሰ ነው። ምናልባትም በተቃውሞው ጎራም ይህ ነገር ሳይለመድ አልቀረም። የራስን ጉድፍ ሳያጠሩ የሰውን ጉድፍ መናገርና ማውገዝ ደግሞ አሣፋሪ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “በራስህ ዐይን ውስጥ ያለን ዕርፍ እሚያህል ጉድፍ ሳታወጣ በሰው ዐይን ውስጥ ያለን ስንጣሪ ጉድፍ ለማውጣት አትሞክር” ይላል። ችግሩ በስሜት የሚነዳ እንጂ በአስተውሎት የሚራመድ ትውልድ እያጠጠን (እያጠረን) መምጣታችን ነው። ራስን መመርመር ቀረ፤ ራስን መመዘን ፋሽኑ አለፈበት፤ ራስን ብፁዕ ሌላውን ኃጥዕ ማድረግ የዘመኑ ፈሊጥ ሆነ። ምን ይሻለናል?

እኛስ ለምደነዋል። በተለይ ፈረንጆቹ ይህን ነገር ሲሰሙ በተፈጥሯችን ምን ያህል ይገረሙ?

ለሰላም ማስጠበቅ ሥራ - ወይ ቀልድ - በአገሩ ሰላም ያለ ይመስል - የወያኔው መንግሥት ጦር ወደ ላይቤሪያ ሄደ አሉ - ቀደም ሲል ነው። ከሌሎች የአፍሪካ አገራትም እንዲሁ ጦር ተልኮ ነበርና በአንድ ካምፕ ውስጥ ሁሉም ይኖሩ ነበር። የየአገሩ የጦር አባላት ካለፈቃድ ከካምፕ እየወጡና ነገር እያበላሹ ስለመጡ ወታደራዊ አዛዦች ተቸገሩ። ያኔ ከየአገሩ ጦር አንዳንድ ካቦ ተመርጦ ወገን ወገኑን እንዲቆጣጠር ተወሰነ። ኢትዮጵያውያን ሊመርጡ ሲሉ ጠባያችንን ጠንቅቆ የሚያውቅ የአፍሪካ ጦር አስተባባሪ ኮሚቴ አንድ አባል “ግዴላችሁም ኢትዮጵያውያኑን አታስመርጧቸው፤ ምክንያቱም ለነሱ ‹አትውጡ› ማለት ብቻ በቂ ነው። እርስ በርስ ስለሚመቀኛኙ አንዱ ሲወጣ ሌላው ይጠቁማልና በነሱ ችግር አይግባችሁ።”

እስከመቼ እንዲህ እየተቀለደብን እንኑር? መቼስ ነው የምናድገው? የፈረንጆች፣ የአፍሪካውያንና የእስያውያን መሣቂያና መሣለቂያ እንደሆንን ለመኖር የመረጥነው ምን ዓይነት ብዔልዘቡላዊ ንፋስ በመካከላችን ቢነፍስ ነው? ይህ ባሕርያችን እኮ ነው የሚያስንቀንና ለጠላቶቻችን እንደትልቅ የማጥቂያ ሥልት ሆኖ የሚያገለግለው - ትልቅ ሽብልቅ አቀበልናቸውና በዚያ ምሣር አለ አንዳች ርህራሄ ይሰነጣጥቁን ገቡ። ብዙ ሳይለፉ በቀላሉ የሚያሸንፉን በውስጣችን በተሰገሰገው የምቀኝነት መንፈስ ምክንያት ነው። በዚህ አስቀያሚ ጉዞ ከቀጠልን መቼም ቢሆን አገርና መንግሥት አይኖረንም። ይህን የምለው ምርጫችን ይህ ሆኖ ከቀረ ለማለት ፈልጌ እንጂ ጉድፋችንን መጥረግ ብንጀምር ፈጣሪ የሚታደገን መሆኑን አጥቼው አይደለም። “እሹ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ ይከፈትላችኋል” አይደለም እንዴ እርሱ ራሱስ የሚለን? ምን ከማን ለማግኘትና እንዴት ማግኘትም እንደምንችል ካላወቅን ከግብጽ ከነዓን ለመግባት ለ40 ዓመታት በበረሃ እንደተንከራተቱት የጥንት እስራኤላውያን መሆናችን ነው - የሣምንቱን መንገድ። ስለዚህ የምትፈልገውን አለማወቅም ከባድ ችግር ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንኳን ይህ ከሥራ አባርሩልን የሚሉት ፈሊጥ በስንት ወገኖቻችን ላይ እንደተሞከረ በጸጸት የምናስታውሰው ነው። እባክህን አንድኛህ አንባቢ ይህን ነገር ከየመዛግብቱ ልቀምና በማን ላይ ማን ወይም እነማን እንደዘመቱበት ጉዳችንን አስነብበን። ሀፍረትና ይሉኝታ እንደሆኑ ከአገራችን ለይቶላቸው ከኮበለሉ 40 ዓመት አለፋቸው። “ዘይገርም ሻሸመኔ ትብስ ኮፈሌ” አሉ? ይህ እኮ መቅሰፍት እንጂ ሌላ እንዳይመስላችሁ - ሰዎች እንዴት ቢያስቡ ነው - ምን ዓይነትስ አንጎል ቢኖራቸው ነው - ወደዚህን መሰል ቅሌት የሚወርዱት? “እገሌን ከሥራ አስወጡልን!” ብሎ ደጅ ጥናትና አቤቱታ? በሌሎች አገሮች ይህን ዓይነት ብልግና የሚታወቅ አይመስለኝም። ከሰውነት ደረጃ እኮ ተሸቀንጥሮ ወደ አዘቅት መውረድ ነው።

ምቀኝነት እንዲህ ፈሩን ለቅቆ በሰው አገር በሚታይ ማፈሪያ ድርጊት ሣይቀር ኢትዮጵያውያንን አንገታችንን እያስደፋን ነው። ከዚህ በላይ አሣፋሪ ነገር የለም። ለራሱ በጥገኝነት እየኖረ ከአደጋ የተጠለለ ወገኑን ጉሮሮውን አንቃችሁ ግደሉልን ከማለት የበለጠ ፋሽዝምና ናዚዝም ወይም ወያኔነት የለም። ይሄ አካሄድ በቀላሉ ፀረ-ዴሞክራሲ ነው ተብሎ ብቻ የሚታለፍ አይደለም፤ በሰው አገር እንዲህ ያደረገ ሰው ነገ ሥልጣን ቢይዝ ከፍ ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የፀሐይ ብርሃንንና አየርን ሣይቀር ለየነገድና ጎሣው በራሽን መልክ እንደሚያድል ጥርጥር የለውም - ለዚያውም የኔ ነው ለሚለው ጎሣ የአንበሣ ድርሻውን እየሰጠ። ከዚህ አኳያ ወያኔን የሚመርጥ ሰው ቢኖር በበኩሌ አልፈርድበትም። ሰው እንዲህ እየደደበ የሚሄድበት ምክንያት ደግሞ በጭራሽ አይገባኝም። በስማም …

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ