ፕ/ር ኃይሌ ላሬቦ እና "የቁቤው ትውልድ" ፖለቲካ
ክንፉ አሰፋ
ለሰሞኑ ግርግር መንስኤ የሆኑት ፕ/ር ኃይሌ የተጠቀሟቸው ሁለት ቃላት ናቸው ተብሏል። "ጋላ" እና "እረኛ" የሚሉ ቃላት። በኢትዮጵያ የታሪክ መዛግብት ውስጥ እነዚህ ቃላት "ሰፍረዋል" ወይንስ "አልሰፈሩም" የሚለውን ጉዳይ ለግዜው እንተወው። ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ በቃለ-መጠይቁ እነዚህን ቃላት መጠቀማቸው "ስህተት ነው" ወይንም "ስህተት አይደለም" ወደሚለው ትንታኔም አልገባም። እነዚህን ጥያቄዎች ለታሪክ ለተመራማሪዎቹ ልተውላቸው።
ፕሮፌሰሩ ከወንድማገኝ ጎሹ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ እነዚያን ቃላት ባይጠቀሙስ፣ ከስድብ እና ከአድማው ይድኑ ይሆን? የሚለው ጥያቄ ግን ትንሽ ወደ ኋላ እንድዞር አድርጎኛል።
"ዳግማዊ ምኒልክና ታሪካዊ ክንውኖቻቸው" በሚል ርዕስ አንጋፋው ጋዜጠኛ ተክሌ የኋላ ከሁለት ዓመት በፊት ሦስት እንግዶችን በጀርመን ድምጽ ሬዲዮ ጋብዞ አወያይቷቸው ነበር። እንግዶቹ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፣ ዶ/ር ኃይሌ ላሬቦ፣ እና ዶ/ር ሹመት ሲሻኝ ነበሩ። በውይይቱ ሁለቱ የታሪክ ተመራማሪዎች የአቶ ቡልቻ ደመቅሳን በአፈ-ታሪክ የተቋጨ ሃሳብ በማስራጃ ውድቅ ስላደረጉት ...፤ በጃዋር መሐመድ የሚመራው ቡድን ለጀርመን ድምጽ ራዲዮ የቦርድ ዳይሬክተር አቤቱታ (petition) አስገባ። አቤቱታው ቀጭን ትዕዛዝ ይዞ ነበር። "ተክሌ የኋላ ባስቸኳይ ከሥራው ይባረር!" የሚል ትዕዛዝ። ግፊቱ በብዙ ተሞከረ። ግን አልተሳካም። ይልቁንም የጋዜጠኛ ተክሌ የኋላ ቃለ-መጠይቅ "መነጋገርያ የሆነ ምርጥ ሥራ" በሚል በቦርዱ ሙገሳን ነበር የተቸረው። በከሳሾቹ ግን እጅግ አዝኖ "እኛ አንስተነው እኛው ላይ ተነሳ" ብሎ የነገረኝ ትዝ ይለኛል።
በዚያው ሰሞን፣ ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ "ጥቁር ሰው" የሚል አልበም ለቅቆ፤ የአጼ ምኒልክን የፀረ-ቅኝ ግዛት ተጋድሎ አወድሶ ነበር። የ”ኦሮሞ ፈርስት” አቀንቃኞች ያዙኝ-ልቀቁኝ ሲሉ አዋራ አስነሱ። የሄነከን (በደሌ) ቢራ ኮንሰርቱን ስፖንሰር እንዳያደርገው ይኸው ቡድን ዘመቻ ከፍቶ 18 ሺ ፊርማ አሰባስቧል። በወቅቱ እነ አባዱላ ገመዳ የሚመሩት - ኦሕዴድ ከ20ሺ በላይ የኦሮሞ ተወላጆች እስር ቤቱን አጨናንቀውት እንደነበር የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዘገባ ያሳያል። ይህ በደል ለ"ኦሮሞ ፈርስቶች" ከቶውንም የትኩረት አቅጣጫ አልነበረም።
300 የኦሮሞ ተወላጆች በኦሮሞነታቸው ብቻ ከዩኒቨርሲቲ ሲበረሩ፣ የቁቤው ትውልድ አቀንቃኞች ምን እንዳደረጉም አይተናል። ጁነዲን ሳዶ የተማሪዎቹን መባረር የሚደግፍ መግለጫ ሰጠ። ይህ በደል ከሜንጫዎቹ ተቃውሞም ሆነ የፔትሽን ሃሳብ አልነበረውም። ይልቁንም እንደ አገዳ ተመጥጦ የተጣለው ጁነዲን ሳዶ ዛሬ ጀግና ሆኖ ታሪካችንን ሊነግረን በዲያስፖራ ብቅ ብሏል።
ፕ/ር ኃይሌ ባለሳምንት ናቸው። ነገ ሌላም ምሁር ይቀጥላል። የአጼ ምኒልክን ስም የሚያነሳ ምሁር በሙሉ እንዲሸማቀቅ እና ዝም እንዲል የሚደረግ ሙከራ ነው። በመገናኛ ብዙሃን ቀርቦ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚናገር ምሁር ወይንም፣ ታሪኩን እነሱ በሚፈልጉበት መንገድ ቀይሮ ካልተናገረ ላለመሰደቡ ዋስትና የለም። የፖለቲካውን ጡዘት የሚያወላግደው ከቶውንም እንደሰበዝ መዝዘው ባወጧቸው ቃላት አይደለም። ጸቡ ያለው ከዳግማዊ ምኒልክ እና እሳቸውን ከማወደስ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ከተመክሮዎቹ በግልጽ እናያለን።
አንድ ነገር ግልጽ ይሁን። በኦሮሞ ሕዝብ መሃል ኖረናል። ባህሉን፣ ሥነ-ልቦናውን እና ቋንቋውንም ጭምር እናውቃለን። የምናውቀው ኦሮሞ ፍጹም ጨዋ እና ትዕግስተኛ ሕዝብ መሆኑን ነው። የኦሮሞ አባቶች ለትውልድ አውርሰው ያለፏቸው እሴቶች ብዙ ናቸው። እነዚያ እሴቶች፣ በባህላዊ የገዳ ሥርዓት፤ ችግርን በንግግር መፍታት፣ ፍትሃዊ አስተዳደርን፣ ጨዋነትን እና አርቆ አሳቢነትን እንጂ ነውርን፣ ስድብን እና ዋልጌነትን አልነበረም።
የፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ ቃለ-ምልልስ በኢሳት እንደተለቀቀ የፓንዶራው ሳጥን የተከፈተ ያህል በርካታ ስድቦችን በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ተመልክተናል። ጉዳዩ በስድብ እና በተቃውሞ ብቻ አላበቃም። ከኢሳት ቦርድ በጉዳዩ መግለጫ እንዲያወጣም ተደርጓል። መግለጫውም ነገሩን አላስቆመውም። የይቅርታ ነገርም ተነስቷል።
ኃይሌ ላሬቦ ከሚያስተምሩበት ቦታ እንዲባረሩ በኢንተርኔት አቤቱታ እየተሰባሰበ ነው። ርምጃው ሁሉ ብዙ የሚያስኬድ ባይሆንም፤ ነገሩ እንዲሁ እየተንከባለለ መቀጠሉ ግን አይቀርም። ምክንያቱም ለተነሳው ጉዳይ ምላሽ መፍትሄው መጮህ፣ መሳደብ እና አድማ መጥራት አይደለም። መፍትሄው መጋፈጥ እና ማስረዳት፣ ጉዳዩን ጠረጴዛ ላይ አፍረጥርጦ መበታተን።
የፕሮፌሰሩን የታሪክ ትንታኔ ቃል በቃል የመሞገት ጉልበት ያላቸው የኦሮሞ ተወላጅ ምሁራን ጠፍተው ነው ለማለት ይከብዳል። ከአክቲቪስቶቹ መካከል ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል ገቢሣም አሉ። የታሪክ ምሁር ናቸው። ይህንን ጉዳይ ከሳቸው እይታ ይተነትኑታል ብሎ ያልገመተ አልነበረም። ቃለ-ምልልሱ ውስጥ ይቀርቡ የነበሩት መረጃዎችም ሆኑ ማስረጃዎች ውስጥ ስህተት አለ ብለው ካመኑ፣ በዚሁ መገናኛ ብዙሃን ቀርቦ መሞገት ምሁራዊ ተግባር ነው። ጉዳዩን በማስረጃ የማፍረስ ክህሎት ካላቸው፣ አደባባይ ወጣ ብለው ችግሩን ይፈቱት ነበር። እሳቸው ግን ከምሁራዊ ማዕዘን ጉዳዩን ከማስረዳት ይልቅ ጥላቻ መስበክን መምረጣቸው ያሳዝናል። እርግጥ ነው። በታሪክ ተመራማሪነታቸው ከሠሩት ሥራዎች ውስጥ ሲፈለግ የሚገኘው ስለ ሐረር ጫት እድገት የጻፉት ብቻ ነው። (Khat & Agricultural Transformation in Harerge, Ethiopia, 1875–1991) ሌላ ነገር የለም። ከእኝህ ምሁር ብዙ ጠብቀን ያገኘነው ግን ምሁራዊ ትንታኔ አልነበረም።
ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል ገቢሣ የነበረውን ታሪክ ማምከን እንኳ ባይደፍሩ፣ ቢያንስ ዶናልድ ትራምፕ እንደሚለው አማራጭ እውነታዎችን (alternative facts) ያሳዩናል ስንል፣ ጭራሹን ሌላ ቋንቋን መናገር እንደ ድንቁርና የሚወስደው ሃሳባቸውን ነገሩን። እንዲህ እያሉ በአመክንዮ ሳይሆን በስሜት ብቻ የሚመራውን ቡድን፣ ፍሬን በሌለው መሽከርክሪት ቁልቁል ይነዱታል። ይህ ደግሞ ማንን እየጠቀመ፣ ማንን እየጎዳ እንደሆነ ከወዲሁ እያየነው ነው።
ከምሁራን አክቲቪስቶቹ ይልቅ ያልጠበቅነው በእውቀቱ ሥዩም ፕሮፈሰር ኃይሌን በመሞገት ማብራርያ ይሰጣል፣
"ኦሮሞ የሚለው ቃል ፕሮፌሰር ላሬቦ እንደሚለው አሁን የመጣ ሳይሆን፣ከጥንት ጀምሮ የሕዝቡ ስም ነው። ስያሜው በብዙ ቀደምት ያውሮፓ መንገደኞች መጻሕፍት ውስጥ ተመዝግቦ መገኘቱ ለዚህ ማስረጃ ይሆናል። ለምሳሌ እንጦኒዮስ ዳባዲ የተባለ መንገደኛ በ1888 ላሳተመው ጥናት የሰጠው ርዕስ 'ጋላ በሚል ስም ለስለሚጠሩት ኦሮሞች - ያፍሪካ ታላቅ ሕዝብ' የሚል ነበር። ወንድሙ ሚካኤልም፤ ደጃዝማች ጎሹ ስላደረጉት ዘመቻ ሲጽፍ፣ 'ጋላ በሚባሉት ኦሮሞዎች ላይ የተካሄደ ዘመቻ፤ (campagne contre les ilmormas dits gallas)' ይላል"
"ቱቸር የተባለ የጀርመን ሊቅ ሁለት የኦሮሞ ተወላጆችን በ1844 ሙኒክ ላይ አግኝቶ ከነሱ እያጠያየቀ መዝገበ ቃላት አሰናዳ። በመዝገበ ቃላቱ Oromo የሚለውን ቃል ሲፈታ 'The name by which the Gallas call themselves in comparison with other nations' ይላል።
"ጣልያናዊው ፕሮፌሰር ቪትርቦ በ1887፣ ያሳተሙት የሰዋሰው መጽሐፍ ርዕስ 'Grammmatica Della lingua Oromonica' የሚል ነው።"
ሲል በእውቀቱ ሥዩም ታሪክ እየጠቀሰ ለማብራራት ሞክሯል። ወንድም በእውቀቱ ሥዩም ጥሩ አብራርቶታል። ጉዳዩን ግን ጠለቅ ብለን በመስመሮች መካከል የምናነበው ነገር አይደለም። በእውቀቱ ሥዩም ያልገባው፣ ወይንም ገብቶት ያላስገባው አንድ ነገር እንዳለ አንዘንጋ።
አንድ ሕዝብ "በዚህ ስም መጠራት አልፈልግም!" ካለ ይህ መብቱ መከበር አለበት። በዚህ የሚደራደር አይኖርም። ህወሓት ሥልጣን ከያዘ በኋላም በርካታ የጎሣ ስሞች ተቀይረዋል። ሲዳሞ ወደ ሲዳማ፣ ጃንጀሮ ይባል የነበረ አሁን የም እንዲባል፣ አዋሳ የነበረው ሃዋሳ እንዲባል ... ወዘተ። አፍሪካ-ሜሪካኖች ኔግሮ በሚለው ስም መጠራት አንፈልግም በማለታቸው ይህንን መብታቸውን አስከብረዋል። በጥቁሮች ላይ መጥፎ ስሜት (bad connotation) የሚያሳድረው "ኔግሮ" የሚለው ስም በግልጽ ይቁም እንጂ ከታሪክ መዛግብት ግን አልጠፋም። ሞኝና ወረቀት የያዘውን አይለቅም እንዲሉ ታሪክ ነውና ሊጠፋ አይችልም። በድጋሚ ነገሩ ያለው የቃለ-ምልልሱ ይዘት ላይ አይደለም። አንድን ምሁር ነጻ ሆኖ የምርምሩን ውጤት በመናገሩ ብቻ በማይገባው ክብር የሚነካ አጸያፊ ስድብ ማውረድ፣ ማዋረድ መሞከር፣ ከሥራው እንዲሰናበት አቤቱታ ማሰባሰብ ላይ ነው ጉዳዩ።
ፕ/ር ኃይሌ ላሬቦ የታሪክ ምሁር ናቸው። ዕድሜያቸውን በሙሉ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ሲመራመሩ ቆይተዋል። በቃለ-ምልልሳቸው የፖለቲካ ትንታኔ አልነበረም ይሰጡ የነበረው። በኢትዮጵያ ታሪክ ሲመራመሩ ያገኙትን እንደወረደ አስቀመጡ። የታሪክ ሰዎች የፖለቲካ ትክክለኝነት (political correctness) አይገዳቸም።
አዎ እንደወረደ። በቃለ ምልልሳቸው "አማራ የሚባል ጎሣ ወይንም ብሔር የለም" ብለዋል። ጎጃሜ፣ ጎንደሬ፣ ይፋቴ፣ መንዜ፣ ወሎዬ፣ ... ወዘተ እንጂ አማራ ነኝ የሚል ጎሣ ወይንም የሸዋ፣ የጎጃም፣ የአገው፣ የወሎ እንጂ የአማራ መንግሥት የሚል ነገር፤ በታሪክ መዝገብ ላይ የሌለ መሆኑን ለማስረዳት ሞክረዋል። ይህ ገለጻቸው ስለ ኦሮሞ ከተናገሩዋቸው ቃላቶች እጅግ የከፋ ነው። ግና የአማራው ሕዝብም ሆነ በአማራ የተደራጁ ወገኖች ሲሳደቡ፣ ሲያወግዙ ወይንም አቤቱታ ሲያሰባስቡባቸው አላየንም። በአንጻሩ "ኦሮሞ የሚባል ብሔር ወይንም ጎሣ የለም። ጉጂ፣ ሰላሌ፣ ወለጋ፣ ... እንጂ" ቢሉ ኖሮ እንደ ሳልማን ሩሽዲ በተገኙበት ይገደሉ የሚል ፍርድ እንደሚጠብቃቸው መገመት አያዳግትም።
ድርጊቱ በራስ መተማመንን፣ ታሪክን እና ማንነትን ጠንቅቆ ማወቅን ይጠይቃል። ኢትዮጵያ የሁሉም አገር ናት። ማንም ሰው የበላይ ሊሆን አይችልም። ያለራሱ ሙሉ ፈቃድ ደግሞ ማንም ሰው ከሌላው የበታች አይሆንም። ፍጹም ጥላቻ እየነዳቸው ሌላውን ወገን "ውጡልን፣ እንገንጠል ..." እያሉ ራስን ማሳነስ ከበታችነት ስሜት የሚመነጭ ሕመም ነው። ለሕዝቡ አዝነው ሳይሆን ለራሳቸው የሥልጣን ጥማት መወጫ ሲሉ ብቻ፣ ትላቁን ሕዝብ ትንሽ በሚያደርጉ ተግባራት ላይ ተወጥረዋል።
የኦሮሚያ ፈርስት ሌላው አቀንቃኝ ዶ/ር ጸጋዬ አራርሳ ናቸው። የግርግሩን ነፋስ ለማጽዳት እሳቸውም አንድ ነገር ያደርጋሉ ብለን ነበር። ግን ከምሁራዊ ትንታኔ ከመስጠት ይልቅ፣ በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ OMN የቀረቡትን የአቶ አዴኦ ቦሩ ንግግር በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ለጥፈውታል። ጽሁፉ እንደሚከተለው ይነበባል።
"ወያኔን በቀኝ እጅ እየተዋጋን በግራ እጅ ያለፈው የፋሺስት የነፍጠኛ ሥርዓት እንዳያንሰራራ መዋጋት ያስፈልጋል። ከነፍጠኛጋር ያልተገባ ጋብቻ መፍጠር አስፈላጊ አይደለም። ሊገሉ፣ ሊወሩ፣ ሊዘርፉ የተዘጋጁትን የአበሻ የቀድሞ የፋሺስት ድርጅቶች ጋር ፈፅሞ፣ ከነሱ ጋር ሕብረት መፍጠር ፈፅሞ አያስፈልግም። ፈፅሞ! በኦሮሞ ሕዝብ ከነዚህ ጋር እየሠራ ያለድርጅት በኦሮሞ ሕዝብ የፖለቲካ ሽርሙጥና እየሠራ ነው። ከነዚህ ጋር ምንም ሕብረት የለንም። የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ድል እንደሚያመጣ ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ። ኦሮሞ ነፃ ከወጣ በኋላ፣ መሬቱን ካስመለሰ በኋላ፣ ባህሉን ካስጠበቀ በኋላ፤ ከፈለገ አብሮ ይኖራል፣ ካልፈለገ ለብቻው ይኖራል፣ ከፈለገ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ሌላ አገር ፈጥሮ ይኖራል።"
ዶ/ር ጸጋዬ አራርሳም ሆኑ የአቶ አዴኦ ቦሩ የፖለቲካ ስትራቴጂ ድንቅ ነው። ሁለት እግር ስላለን ሁለት ዛፍ በአንዴ እንወጣለን ነው የሚሉት። ሁለት እጅ ስላለን ሁለት ጠላት በአንዴ እንመታለን ነው የሚሉት። ግና ጣታቸውን የቀሰሩበት ሁለተኛው ጠላታቸውን ነፍጠኛው ከማለት ውጭ በግልጽ አላስቀመጡትም። አማራውን ማለታቸው ይሆን ወይንስ ፕ/ር ኃይሌ ላሬቦን፣ ራስ ጎበናን ማለታቸው ነው ወይንስ ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴን፣ ራስ ጢኖን ማለታቸው ይሆን ወይንስ ባልቻ አባ ነብሶን ...?
በነገራችን ላይ ዶ/ር ጸጋዬ አራርሳ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት - ኦሕዴድ አባል ሆነው በሲቪል ሰርቪስ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አንጋፋ ምሁራን ሲያፈሩ የነበሩ የህወሓትን አገልጋይ ነበሩ። በምናባቸው የተፈጠረ ታሪክ እና በዘር ጥላቻ ተለክፈው ዕድሜያቸውን እኩሌታ ከሚሰቃዩ ምሁራን አንዱ ናቸው። ከሺዎች ማይል ርቀት ላይ ሆነው ኢትዮጵያ የምትባለውን አብስትራክት ነገር የማፍረስ ህልም ያልማሉ። መቼም ሕልም አይከለከልም። አወዛጋቢዎቹ የአትላንታ እና የለንደን ኮንፈረንሶች፣ የ"ኦሮሚያ የነጻነት ቻርተር" ወዘተ ሁሉ ይኸው ጥላቻ አርግዞ የወለዳቸው የቂም ልጆች ናቸው።
የህሊና ዓይናቸው ካልታወረ በስተቀር፤ ከፕ/ር ኃይሌ ላሬቦ ንግግር ይልቅ የአዲሱ የማስታወቂያ ሚኒስትር የዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ንግግር ነበር የኦሮሞን ሕዝብ የሚያደማው። ነገሪ ሌንጮ ሰሞኑን ከፋይናንሻል ታይምስ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ የኦሮሞን አመጽ በማፈን እና በመስበር ድል እንደተቀዳጁ ነግረውናል። ሺዎች የተገደሉበት፣ በመቶ ሺዎች የታሰሩበት፣ የሰው ልጅ መብቶች በሙሉ የተገፈፈበትን እርምጃ ዶ/ር ነገሪ "ስኬታማ ድርጊት" ብለውታል። የ"ቁቤ ትውልድ" ነኝ ለሚለው ቡድን ግን ከዚህ በአፍንጫው ስር እንደቅጠል ከሚረግፈው ወገኑ በበለጠ የሚያሳምመው፣ የማያውቀው የምኒልክ የጀግንነት ታሪክ ነው። የቁቤ ፖለቲካ፤ ከቁቤው ላቲን ፊደል ትምህርት በተጓዳኝ ከህወሓት የትምህርት ቢሮ እንደ ክትባት የሚሰጥ መርዝ ነው። መርዙ አንድ ትውልድ ላይ የከፋ ጥላቻ እና ያለመተማመንን ፈጥሯል። ትውልዱ ዛሬን ሳይሆን ትላንትን ብቻ እያመነዠከ እንዲቆይ፤ ለገዥው ፓርቲ እና ለተቀጽላው ኦህዴድ መሰንበቻ የታሰበ የፖለቲካ ንድፍ ... ከሳጥን ውስጥ ያልወጣ አስተሳሰብ (out of the box thinking) ይዘው እንዲያድጉ የተደረገ ጥናት።
የትናንት ቁስል የሌለው ሕዝብ የለም። አሜሪካም፣ ጣልያንም፣ ጀርመንም ሁሉም የቆየ ሕመም አላቸው። ልዩነቱ ቁስሉ በእነሱ ላይ ጋንግሪን ሆኖ ያለመቆየቱ ነው። የትላንት ችግር ሊከተላቸው ቢሞክርም እንኳን፣ አትኩረው የሚመለከቱት ዛሬን እና ነገን ነው። ዶ/ር መረራ ጉዲና ከመታሰራቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ አምስተርዳም ላይ ባደረጉት ምክር አዘል ንግግር፣ "የታሪክ ሂሳብ አታወራርዱ።" ብለዋቸው ነበር። ዶ/ር መረራ ይህንን ያለምክንያት አልተናገሩም። በታሪክ ከሚወራረደው ሂሳብ እዳ በአብላጫው ማን ዘንድ እንዳለ ያውቁታል። የጥንት ታሪካችንን እያነሳን ወደ 16ኛው ክፍለ ዘመን ከተጓዝን ብዙ የሚጎረብጡ ነገሮችን ልናነሳ ነው።
ያም ሆኖ አሁን "የቁቤ ትውልድ ነኝ" በሚል በተነሳው በኦሮሞ "አክቲቪስት" ስም የሚደረገው ነገር የኦሮሞ መልካም ሕዝብን ስም ያጎድፋል። የታሪክ ተመራማሪው ከተናገሩት ውስጥ አንዲት ቃል መዝዞ በማውጣት በአጸያፊ ቃላት መሳደብና ጨዋነትን አያመለክትም። የፕ/ር ኃይሌን ዘር እየጠቀሱ ማንቋሸሽ የኦሮሞ ህዝብ ባሕል አይደለም።
ጃዋር መሐመድ በአንድ ወቅት ሲፎክር በአካባቢው ቀና የሚል ክርስትያን ካለ አንገቱን በሜንጫ እንደሚቆርጥ ነግሮናል። ይህንን ወንጀል በአንደበቱ የተናገረበት ማስረጃ አሁንም በግልጽ ተቀምጧል። እስካሁን አላስተባበለም። ይቅርታም አልጠየቀም። ይህንን የወንጀል ሸክም ከራሱ ላይ ሳያወርድ ዛሬ እሱ የሚመራው የኦሮሞ አክቲቪስት "ኢሳት ይቅርታ ይጠይቅ"፣ "ፕ/ር ኃይሌ ላሬቦ ለተናገሩት ይቅርታ ይጠይቁ!" ሲለን መብቃቱ እንዴት አድርጎ ቢንቀን ይሆን? በእርግጥ ይቅርታ መጠየቅ ትልቅነት ነው። እያወራን ያለነው ግን ስለ ባልና ሚስት ጸብ አይደለም። ጉዳዩ የፖለቲካ ነው። የፖለቲካ ይቅርታ ደግሞ ከኋላው እየተጎተቱ የሚመጡ በርካታ ነገሮች አሉበት። ይህ ባይሆን የአውስትራሊያ መንግሥት አቦርጅኖችን ይቅርታ ጠይቆ በተገላገለ ነበር።
ኢሳትም ሆነ ፕ/ር ኃይሌ ላሬቦ በዚህ ጉዳይ ይቅርታ ማድረግ ካለባቸው በቅድሚያ ዘመናዊው የኢትዮጵያን ታሪክ ለመሻር መወሰናቸውን ሲያሳውቁ ብቻ መሆን አለበት። መገናኛ ብዙሃንም ተጨባጭ ነገር ማቅረብ እንጂ ሁሉንም ወገን ለማስደሰት ብሎ መሥራት የለበትም።
ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦን ለመደገፍ የተዘጋጅው አቤቱታ ድረ-ገጽ ላይ በመፈረም፣ የኚህን ምሁር ሞራል እንጠብቅ። ይህንን ለማድረግ የሚከተለውን ሊንክ ይጫኑ። https://www.ipetitions.com/petition/petition-supporting-professor-haile-larebo
ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ ከወንድማገኝ ጎሹ ጋር ያደረጉዋቸውን ቃለ-ምልልሶች ለመመልከት የሚከተሉትን ሊንኮች ተጠቀሙ፣