ዮፍታሔ

“ሪፖርተር” ከሰሞኑ ካወጣቸው ዘገባዎች አንዱ "ከወጣቶች አሥር ቢሊዮን ብር በጀት ተጠቃሚ ለመሆን ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሥራ አጦች ተመዘገቡ" ይላል። ሲጀመር ሕወሓት ይህንን እቅድ ድንገተኛ ደራሽ በሆነ መንገድ በፓርላማ እንዲጸድቅ ያደረገችው የተፈጠረው ሕዝባዊ አመጽ አንዱ መነሻ ምክንያት የወጣቶች ሥራ አጥነት ስለሆነ ሥራ አጥነቱን በመቀነስ ሕዝባዊ አመጹን ማብረድ እችላለሁ ከሚል ስሌት ነው።

የሥራ አጥነት ችግር ለሕዝባዊ ነውጡ ከሚሊዮን ምክንያቶች አንዱ ብቻ ቢሆንም ሕወሓት እንዳሰበችው ዋና ምክንያት ነው ብለን እንያዝና ይህ 10 ቢሊዮን ብር በእርግጥ የሥራ አጥነት ችግርን ያቃልላል ወይ? መልሱ በአጭሩ አያቃልልም የሚል ነው። ለምን? አጠር አድርገን 4 ምክንያቶችን ብቻ እንይ፦

1. ከዚህ ቀደም ለወጣቱ የተደረጉ ተመሳሳይ የገንዘብ ድጎማዎችና ብድሮች ውጤት አላስገኙም። ይህን ለመረዳት ሩቅ መሄድ አያስፈልግም። የ”ጥቃቅንና አነስተኛ” ፕሮጀክቶች ስኬት ምን ይመስላል የሚለውን ማየት ብቻ ይበቃል።

የ”ሪፖርተር” ዘገባ የፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተርን በመጥቀስ እንዲህ ይላል፦

“በመጀመሪያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መጠናቀቂያ ላይ ከ700 ሺሕ በላይ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የነበሩ ሲሆን፣ ከእነዚህ በ2008 ዓ.ም. ወደ ታዳጊና መካከለኛ ደረጃ መሸጋገር የቻሉት 1,586” ናቸው።

ይህ ማለት ከተጀመሩት የ”ጥቃቅንና መለስተኛ ኢንተርፕራይዞች” ውስጥ 99.8% የሆኑት ከስረዋል፣ ከጀመሩበት ፈቅ ማለት አልቻሉም፣ ከስመዋል ማለት ነው።

ይህን በማጠናከር የአ.አ. ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር የራስወርቅ አድማሴ ደግሞ “ጥቃቅንና አነስተኛ” ብድር “ትርጉም ያለው የሥራ ዕድል ለወጣቱ በመፍጠር፣ ወጣቱን የሙያ ባለቤት በማድረግ፣ አቅም በመፍጠር፣ ለአገር ዕድገትና ልማት በማበርከት፣ እንዲሁም የፖለቲካ ድጋፍ በማስገኘት ረገድ ጭምር ይህ ነው የሚባል ነገር አለመፈየዱን” ተናግረዋል ይለናል። በሪፖርተር የወጣውን “ጥቃቅንና አነስተኛ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ወይስ ወጣቱን መሸንገያ?” የሚል ሀተታ መመልከት ይጠቅማል።

2. አሥር ቢሊዮን የሚለው የገንዘብ መጠን ሥራ አጥ ከሆኑት ወጣቶች ቁጥር ጋር ተገናዝቦ ውጤት ሊያስገኝ በሚችል መንገድ በጥናት ላይ ተመሥርቶ የተደረሰበት አይደለም። በጥናት ቢሆን ኖሮ ከገንዘቡ ቀድሞ በመጀመሪያ በፍላጎት (በገበያ) ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥናቶችና በዚህ ውጤት መሠረት የተዘጋጁ ፕሮጀክቶች በቅድሚያ ይታዩ ነበር። ይህን በሚመለከት የተደረጉ ጥናቶች፣ የጥናት ውጤቶችም ሆነ ፕሮጀክቶች አልታዩም፣ አልተመዘገቡም። እውነተኛ ጥናት ተደርጎ የተዘጋጁ ፕሮጀክቶች ቢኖሩ ኖሮ በሥራ ላይ ከዋሉ በኋላ ደግሞ ክትትልና ድጋፍ ስለሚያስፈልጋቸው በየጊዜው ውጤታቸው መገምገምና በግምገማው ውጤት መሠረት ቴክኒካዊ፣ አስተዳደራዊና የምርትና የገበያ ማስተካከያዎችን ማድረግ ስለሚያስፈልጋቸው ያንን ዝግጅት በዘገባዎችና በመግለጫዎች እንዲሁም በድርጊት እናይ ነበር። የዚያ ፍንጭ አንድም ቦታ አይታይም።

3. ይህ 10 ቢሊዮን ብር ለሁሉም ወጣቶች እኩል “ተደራሽ” መሆኑ የተዘገበ መሆኑ ደግሞ ሌላው ጉዳይ ነው። ይህ ገንዘብ እኩል ተደራሽ የሚሆን ከሆነ ሪፖርተር በዚህ ሰሞን ባወጣው ዘገባ የተጠቀሱት 3.3 ሚሊዮን ወጣቶች ብቻ ናቸው በኢትዮጵያ ሥራ አጥ የሆኑት የሚለው ቅጥፈት ነው። ምክንያቱም ራሱ ሪፖርተር ቀደም ሲል ያወጣውን ዘገባ እንቀበልና በኢትዮጵያ ከ18 - 34 ዕድሜ ያሉ ወጣቶች ቁጥር 30 ሚሊዮን የሚጠጋ ነው። 3.3 ሚሊዮን ብቻ የሥራ አጦች ተመዝግበዋል ብሎ ማለት በሪፖርተር ከተጠቀሰው 30 ሚሊዮን ወጣት ውስጥ 10% ብቻ ሥራ አጥ ናቸው ማለት ነው። ይህ ደግሞ እስካሁን በግልጽና በተደጋጋሚ የተጠቀሰውን ትክክለኛ ስታትስቲክስ በጠቅላላ የሚቃረን ነው። በኢትዮጵያ ከጠቅላላው ወጣት ከ30 - 50% ሥራ አጥ እንደሆኑ የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ። እንዲህም ሆኖ 30 ቢሊዮን ብር ለተጠቀሱት 3.3 ሚሊዮን ወጣቶች ከሙስና ፍጹም በጸዳ መንገድ ይከፋፈል ቢባል እንኳን ለእያንዳንዱ ወጣት የሚደርሰው ብር 2900 ብቻ ነው። ብር 2900 ለአንድ ወጣት ለአንድ ወር ቀለብ ሊሆን ይችላል። አንድን ወጣት በዘላቂነት ራሱን ያስችላል ማለት ግን ከቀልድም ቀልድ ነው።

4. ሪፖርተር ቀደም ሲል ባወጣው ዘገባ ደግሞ ይህን 10 ቢሊዮን ብር “የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደሆነ፣ ነገር ግን የፈንዱ ተጠቃሚዎች አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ብድሩን የማቅረብ ሥራ እንዲሠሩ፣ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት በሌሉበት ደግሞ የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ብድሩን እንዲያቀርቡ ተደንግጓል።” ይለናል። ከዚያ ቀጠል አድርጎ ደግሞ የኦዲተር መስሪያ ቤቱ “ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመመካከር በፈንዱ ለሚሸፈኑ ፕሮጀክቶች የሚሰጥ የብድር ጣሪያ፣ የወለድ መጠን፣ የእፎይታ ጊዜና ተከፍሎ የሚያልቅበትን ጊዜ የተመለከቱ መመርያዎችን የማውጣትና የመወሰን ኃላፊነት ተሰጥቶታል።” ይለናል። ይህ እንግዲህ እስካሁን ከታየው ሥር የሰደደ ዘራፊነትና ሙሰኝነት (“ጥቃቅንና አነስተኛ” እና ሌሎችም የ”ልማት” ብድሮች ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ) ጋር ተደምሮ በዚህ ገንዘብ ላይ ስንት የተለያዩ እጆች እንደሚያርፉበት በግልጽ ያሳያል።

ስለዚህ ገንዘቡ የተመረጡ ግለሰቦች የሚከብሩበት እንጂ ለወጣቱ ምንም ዓይነት ፋይዳ እንደማይኖረው ተጨማሪ ምስክር ነው።

ይልቅ ወንድሜ እውነተኛ ለውጥ የሚያመጣውን ትግልህን አፋፍም!
ሕዝብ ያሸንፋል!
ወያኔም ይወድቃል!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ