20210302 adwa

የሰሜን አሜሪካ ስፖርት እና ባህል ፌስቲቫል (ESFNA) አመራሮች

የሰሜን አሜሪካ ስፖርት እና ባህል ፌስቲቫል (ESFNA) አመራሮች

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

አንድን ሰው ወይም ድርጅት መፈረጅ ቀላል ነው። ፍረጃ ደግሞ እንደተመልካቹ ነው። አሁን በአጭሩ የምናገረው የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ስደተኞች የስፖርት ፌዴሬሽን ስለሚባለው የቦሌ ሞልቃቆች - የፈረንሣይ ልዕልቶች ስብስብ ነው። የካሣ ዳምጤ ልጅ (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ) መሸፋፈን አያውቅም። ከአንጀቴ የወጣ ብሶቴን በጥሞና አድምጡ። ለዚያውስ ይህን ጽሑፍ የሚያወጣልኝ ድረገጽ ሳገኝ አይደል? ዓለም የምትንሰፈሰፈው ላለው ነው፤ ድሃን የምትጸየፍ ዓለም የኔን ብሶት ለማድመጥ ጊዜም የላት። የሚያስተናግደኝ አንድ እንኳን ባገኝ ዕድለኛ ነኝ። በውነት በጣም ተናድጃለሁ።

የወያኔነት ማዕረግ በትውልድ ሐረግ ወይም በጎጥ አይሰጥም። በምግባርና በጠባይ እንጂ። ለአብነት “እገሌ ትሮትስኪ ነው” ስንል - ዱሮ - ያ ሰው ራሽያዊውን ማንትስ ትሮትስኪን ሆኖ አይደለም - በሚያሣየው የአመለካከት ለውጥና አኳኋን ተመሥርተን እንጂ። እናም ይሄ ኢስፋና የሚሉት የዮዲት ጉዲት ውላጅ በውነትም ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የቆመ መስሎኝ በጉጉት ስጠብቀው ለካንስ ሕወሓትን የሚደግፍ የአገር ጠላት ኖሯል። አገርንም ሕዝብንም የሚንቅ የነሰው ጤፉ ዋሻ መሆኑን በሰሞኑ ውሳኔው አሳውቋል። ደግሞም “የዐይጥ ምሥክር ድምቢጥ” እንዲሉ ለሕዝብ መቆርቆር የነበረበት ጋዜጠኛ - ካሣሁን ይልማ - የነዚህን ጉዶች ውሳኔ ደግፎ “ውሳኔቸውን እናክብርላቸው” ሲለን ገረመኝ - አዝናለሁ። ሰውን ምን ነካው ግን? ራሱ ከተመቸው፣ ተደላድሎ ከተኛ፣ ከበላና ከጠጣና ከርሱ ከሞላ፣ የሞቀ ቤት ውስጥ ከኖረ … ስለሌላው ምሥኪን ግድ የለውም ማለት ነው? ምን ዓይነት የድንቅቁርና ዘመን ላይ ደረስን በሉ! መጥኔ ለኢትዮጵያ!

በኢትዮጵያ ላይ በጠላትነት ያልተነሣ የለም። የነዚህ ሰዎች ውሳኔ ግን ከሁሉም የተለዬ ነው። ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ የተሰባበረውን ድልድይ ልጠግን ብሎ ሲነሳ “የለም! በተሰባበረው ድልድይማ አትምጣብን! በርሱ አይደለም እንዴ የስደት ኑሯችን ያማረበትና ተንደላቅቀን የምንኖረው?” ብለውን እርፍ። ጤናማ ሰው የዚህን ብላቴና ጥረት በሙሉ አቅሙ ይደግፋል። ጤናማ የሆነ ሰው የዜጎች በስደት መንከራተት፣ ከፎቅ መወርወር፣ ተርዋዶ ከሰው በታች መሆን፣ በበረሃ በውኃ ጥምና በርሀብ፣ በዐውሬና በሰውነት አካል በላቾች ማለቅ፣ … ልቡ ይነካል፤ ከአንገት ሳይሆን ከምር ያዝናል።፡ ጤና ሰው በዜጎች መከፋፈል፣ በዜጎች መበተን፣ በዜጎች መደህየት … ይሳቀቃል፤ ያለቅሳል። እነዚህ ደነዞች ግን ሁሉ ነገር ለነሱ ከተመቻቸ ለድሃውና ለአገር ደንታ ቢስ ናቸው ማለት ነው። “እኔውም ዕብድ ነኝ ከወፍ የገበየሁ፤ መቀመጧን እንጂ መብረሯን የት አየሁ” ብሎ የተረተው ሰው እንደኔው አንጀቱ በንዴት ቢጨስ ነውና ልጅ ይውጣለት። ለካንስ በሰው ቁስል እንጨት መስደድና ጨው መነስነስ እንዲህ ቀላል ነው! ዐቢይ የነሱን ደጅ ያንኳኳው “ልጃችሁን ለልጃችን” በሚል ለሠፈር ሽምግልና መስሏቸው ይሆን እንዴ? ማይምነትንና ባህላዊ አስተሳሰብን የሚቀርፍ መድሃኒት አሜሪካ ውስጥ የለም ይሆን? ሰው ሲችል ወደፊት ይሄዳል፤ ያ ቢሳነው ያለውን ይዞ ይቆያል። እንዴት ቁልቁል ይነጉዳል? ኧረ አታሰድቡን እባካችሁን! በስንቱ ነው የምንሰደበው? ዐቢይ ከበረ - እነሱ ተዋረዱ።

ደግሞ ዴሞክራሲ ይባልልኛል። የት የሚያውቁትን? ዴሞክራሲ ማለት ከመነሻው ምን ማለት ነው? አገሩስ የት ነው? ትንሹ ጆርጅ ቡሽ በዴሞክራሲ አልነበር ወደ ሥልጣን የመጣው? ዴቪድ ትራምፕ በዴሞክራሲ አይደል ወደ ዋ(ኋ?)ይት ሀውስ የገባው? እምዬ ምኒልክ በዴሞክራሲ መጡ? ዐቢይ አሕመድ ራሱ በዴሞክራሲ መጣ? ለምን ይቀለዳል? በምድር ዴሞክራሲ የሚባል ነገር የለም - ቁጩ ነው፤ ‹ፌክ›። (ገንዘብና ብልጠት ያላቸው) ጥቂት መሠሪዎች የሚፈልጉት ነገር በዴሞክራሲ ስም ጎጋው መንጋ እየተጭበረበረ እውን የሚደረግበት የማስመሰያ ጭምብልና ሕገ-ወጥነትን ሕጋዊ ልባስ መስጫ አፍዝ አደንግዝ ነው - ዴሞክራሲ፤ ቃሉ ሲጠራ ግን ደስ ይላል። ስለዚህ የፌዴሬሽኑ ውሳኔ በፈረደበት ዲሞክራሲ ስም የጥቂት ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-ሕዝብ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ፍላጎት ነው የተንጸባረቀበት፤ በግልጽ ይታወቃል። በዚህ ንቃትና ዕውቀት እንደልብ በሚሠፈርበት ዘመን ማንም አፈ ጮሌ - ይመስለዋል እንጂ - ሊያታልለን አይችልም። የኛ የጭቁኖች ፍላጎት እውን መሆን የእንጀራ ገመዱን የሚበጥስበት አካል በፌዴሬሽኑ ስም ሥራውን ሠራ፤ ልጅ አይውጣለት፤ ጥቁር ውሻም ይውለድ። ምላሴ ጥቁር ነው ደግሞ።

ኢትዮጵያ ሰላም እንዳትሆን የሚፈልጉ ወገኖች በየጎራው አሉ። በድጋሚ እራገማለሁ - እግዜር ይይላቸው። የሥራቸውንም ይስጣቸው።ይህን የሰይጣን ሥራ የሠሩ ወገኖች ምንም አይጠቀሙም።

በተለይ በዲያስፓራው ዘንድ የብዙዎች ፍላጎት የሚታወቅ አይመስለኝም። አንዳንዶቹ እንዲያውም መምሸት መንጋቱንም ሳይቀር በቅጡ የማያውቁና ከናካቴው ፍላጎትም ያላቸው የማይመስሉ ዞምቤዎች ናቸው። እንጂ ይህ ጠ/ሚኒስትር የተበታተነውን ሕዝብ ላስማማ ባለ በምን ሂሳብ እንዳይገኝ ይከለከላል? በፈረስ የፈለጉት በእግር ሲገኝ “እልል በቅምጤ!” ይባል ነበር እንጂ ከነሰው ብሶ መከልከልን ምን አመጣው? ዐቢይ ምን ይጎዳል? የርሱን ነጥብ አሳድጎ የነዚህን የአስተሳሰብ ድኩማን ሰዎች ነጥብ አስጣለ እንጂ ያጣው ነገር የለም - ይበልጥ ከበረበት፤ ይበልጥ ነገሠበት። ከዚህ በላይ ወያኔነት ደግሞ የትም የለም - ሕወሓትም ከዚህ አይከፋም። ለሕወሓት የሽፋን ተኩስ ከመስጠት የከፋ ወንጀል የለም። ኢትዮጵያውያንን ላስታርቅ የሚልን ሰው እያባረሩ ስለኢትዮጵያ ሕዝብ አስባለሁ ማለት ደግሞ ፍች አልባ ዕንቆቅልሽ ነው። ሆ! በጣም ነው የገረመኝ። ስንት ሰው አለ እባካችሁ! ደግነቱ ይሄ ልብስ የሚባል ነገር መኖሩ። ሁሉም ተሸፍኖ ሲሄድ ሰው ይመስላልና።

የሰይጣን ዛፍ ከፍሬው ይታወቃል። ዕርቅና ሰላም የማይወዱ፣ በኢትዮጵያ መበታተን እንጀራቸውን የሚጋግሩ፣ የሕዝብ ስደትና እንግልት የደስታቸውና የክብረታቸው ምንጭ የሆነ፣ በመዋጮና በዲያስፖራዎች ድካም ዝናና ሀብትን ለማካበት የሚተጉ፣ ወያኔ በመንበሩ እንደተጎለተ ዕድሜ ልኩን እንዲቆይ የሚጸልዩ፣ … የወያኔ ተባባሪ ሰዎች አሁን ታወቁ። “ያውጡብሽ እምቢ፣ ያግቡብሽ እምቢ” ይላል ያገሬ ባላገር እንዲህ ያለ ግራ አጋቢ ነገር ሲገጥመው። በነሱ ቤት መሠልጠናቸው ነው። በነሱ ቤት መራቀቃቸው ነው። ሠልጥነውና ተራቀው ሞተው!

እነዚህ ሰዎች እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት እንደምንኖር አያውቁም - የቦሌ ሞልቃቆች ያልኳቸውም ለዚህ ነው፤ ስቃይና መከራ ምን እንደሆኑም የሚረዱም አይመስሉኝም። እኛ በምን ዓይነት ፍዳና መከራ ውስጥ እንደምንኖር ቢያውቁ ኖሮ ያን የመሰለ የዘበናይና የቅንጡ ሰዎችን ውሳኔ አይወስኑም ነበር። አንዳንድ አጋጣሚዎችን እየጠበቁ በዚህ በፈረደበት “Shame on you” መፈክር እያላገጡ መኖርን ሳይወዱት የቀሩ አይመስለኝም። እነዚህ ሰዎች የኛ ሰቃይ አይገባቸውም። ምናልባት ቀደም ብለው የወጡ ናቸው። ምናልባት በገንዘብ ደርጅተዋል‹። ምናልባት የአገር ፍቅርና ናፍቆትም ሆነ ትዝታ የላቸውም - ከጊዜ ብዛት አንጻር በንኖ ጠፍቶባቸውም ይሆናል። በዚያም ሳቢያ ምናልባት በሚኖሩት ኑሮ ደስተኞች ናቸው። ምናልባት ስለኢትዮጵያ ያላቸው ዕውቀት ወደ ዜሮ ተጠግቷል። በአንድ ወይ በሌላ ምክንያት ግን እነዚህ ሰዎች ስለኛ ስለብዙኃኑ መበደልና መገፋት አይሞቃቸውም፣ አይበርዳቸውም። የስሜት ህዋሶቻቸው ሞተውባቸውም ይሆናል። ስለዚህ ዐቢይን መከልከል ብቻም ሣይሆን ኢትዮጵያ ትሸጥ ትለውጥም ቢባል ከመፈረም አይመለሱም። ከወገንና ከአገር ስቃይና መከራ ይልቅ ጥቅም ያሳወራቸው ይመስላሉ። እንግዲያውስ ለነሱም እንዘን።

መጠንቀቅ ያለብን የችግሩ ሰለባዎች ነን። በተለይ በአገር ቤት ያለነው ዜጎች ከነዚህ ዓይነቶቹ ሥውር የወያኔን አጀንዳ አራማጆች አገራችንንና ራሳችንን መጠበቅ ይኖርብናል። በውጭ ያሉን ዘመዶች የሚያስቡልን እየመሰለን ብዙ ተታለናል ማለት ነው። የሚያስቡልን መኖራቸው እውነት ቢሆንም ይህ በዐቢይ ጥያቄ ላይ የተከለሰው ቀዝቃዛ ውኃ ግን በቀላሉ ሊታይ የሚገባው አይደለም። ወደፊት በስፋት ልንነጋገርበት ይገባል። ጉዳዩ ብዙ መልእክት አለው። የተሰጠው ምክንያትም ውኃ አያነሳም። ገና ድፍን አንድ ወር ለቀረው ጊዜ የፀጥታና የቦታ ጥበት ማንሳት የአያ ጅቦን ሳታመካኝ ብላኝ ተረት የሚያስታውስ የድንቃይ ቧልታይ ድርሰት ነው። ለማንኛውም ሌላ ጊዜ በስፋት እመለስበታለሁ። ለአሁኑ ግን ሰላም ለአገራችን፤ ትክክለኛው የፈጣሪ ፍርድ በየጎራው ላሉ ለጠላቶቻችን። (ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብቴን የምትነፍጉ ሁሉ … ልብ ይስጣችሁ።)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!