ለእነአባኪያ «የትራፊክ ደንብ» የተሰጠ ምላሽ (ከዳኛቸው ቢያድግልኝ)
«በኤርትራ በቀር ወደ ኢትዮጵያ ነፃነት የሚወስድ መንገድ የለም» ለሚለው የእነአባኪያ «የትራፊክ ደንብ» የተሰጠ ምላሽ
ከዳኛቸው ቢያድግልኝ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)
የጀመርነው ሃሳብን በነፃነት መግለጽ መቻል፣ መከባበር፣ እውቀትን ከፍ ከፍ ማድረግ ሊበረታታ ይገባል። አንዳችን የሌላኛችንን ሃሳብ ማክበር ስንችል እኛነታችንን ሳይሆን ሃሳባችንን እያብጠለጠልነውና እያብላላነው መሄድ ስንችል በአስመራ መንገድ ይሁን በቸርችል ጎዳና ብቻ ቤተመንግሥት ከች ማለታችን አይቀርም። ሁላችንም የምንተጋው ነፃነታችንን እንድናገኝ ነው። ባርነትን ለመምረጥ እሰጥ አገባው ባላስፈለገንም ነበር።
ይህንን ነፃነት ስንለማመድ ከአንደበታችን ስህተት ሊወጣ ይችላል። ትክክል የመሰለንና የሞገትንበት ነገር በሂደት ሊለወጥ ይችላል። የጎዳን የሃሳብ ሞኖፖሊ ነበር፣ አሁን ብዙ ቁምነገሮች በየድረ ገጾች ላይ እየናኙ ነው። እነአባኪያ ደግሞ ለነፃነት መንገዳችን የትራፊክ ቆብ አጥልቃችሁ ”የነፃነት መንገዳችን መነሻው በአስመራ መንገድ ብቻ ነው” እያላችሁን ነው። ያወጣችሁትን ሕግ ለመጣስ ሳይሆን የመንገዱን አደገኛነት ለማሳሰብ፣ መንገደኞችም በየጉድባው፣ በየሰርጣ ሰርጡ አልቀው ካሰቡበት መድረስ ላይችሉ ይገደዱ ይሆናል በማለት ፍርሃቴን አደባባይ ለማውጣት ነው። የአስመራዎቹ መሾፈር ስለሚወዱ የተሳካ እንደሁ እንኳ የኛ ተሳፋሪዎች ዕጣ ፈንታ ወያላነት እንዳይሆን ሰጋሁ። ይህንኑ ተረጋግተን እንድንወያይበት በመፍቀዳችሁ በዚህ መንደርደርያ ወደ ፍሬ ሃሳቤ ልግባ። በቅድሚያ ግን እንደ ትዕዛዛችሁ ሁሉ አምላኬ ሆይ መረጋጋትን ስጠኝ እላለሁ። («በኤርትራ በቀር ወደ ኢትዮጵያ ነፃነት የሚወስድ መንገድ የለም» በሚል ርዕስ አባኪያ እና ጓደኞቹ የጻፉትን ጽሑፍ አስነብበኝ)
የኔን ግምት እውነት ባደረገውና አባኪያና ጓደኞቹ ለመወያያ ብለው የዘየዱት የውይይት መንደርደርያ በሆነልኝ እያልኩ ነበር ያነበብኩት። አለበለዚያ እንደ ፈጣሪ ከኔ በቀር የገነት መግቢያ በር የለም አይነት አስደንጋጭ፣ አስፈሪና የመንገድ ምርጫ እንኳ የማይፈቅድ በኤርትራ በቀር ወደ ኢትዮጵያ ነፃነት የሚወስድ መንገድ የለም የሚል ”የመንገድ ትዕዛዝ” የመሰለ ርዕስ ባልመረጡ ነበር። የእነአባኪያ አካሄድ ደግሞ ለሻዕቢያ የውክልና ጦርነት (proxy war) አልያም ማስፈራርያነት ያግዝ እንደሆን እንጂ የፈለገውን ያህል ብንጃጃል ወይም እሳት የላስን የስትራቴጂ አዋቂዎች፣ የታክቲክ ጥበበኞች እንኳ ብንሆን በትክክል እንዳስቀመጣችሁት ሻዕቢያ ጠንካራ ኢትዮጵያን የሚያይበት የተጃጃለ ዓይን አይኖረውም። ይኖረዋል ብሎ ማሰብ አፈጣጠሩንና ፈጣሪዎቹን ካለማወቅ፣ ወይም ’የጠላቴ ጠላት’ በሚል ወያኔ ሻዕቢያ መልሶ ሊጠቀምበት የሚችል ”መርዝ” መሆኑን ልብ ባለማለት የመጣ ነው ብዬ አምናለሁ። በነርሱ ድጋፍ ከሄድን ደግሞ በስተመጨረሻ በማን ላይ ቆመሽ ሻዕቢያን ታሚያለሽ እንዳይሉን ምን የመውጫ መንገድ ይኖረናል ብዬም እሰጋለሁ?
ወንድሞቼ እነአባኪያ ይህ ሃሳባችሁ እንደ ወንዝ ድንጋይ እርስ በርሱ የሚጋጭ አይመስላችሁም? ”... ለራሳቸው ለኤርትራዊያን መለስን ለመጣል፤ ጥለውም ለኤርትራዊያን እንደልባቸው የሚዋዋሏት ኢትዮጵያ፤ ለኛም እንደ ሃሳባችን ኢትዮጵያን መልሰን ለመገንባት የተሻለው መንገድ ከኤርትራ ጋር መሥራት ነው ብዬ እጽፋለሁ። ...” ይህን ሃሳብ እንኳ ሰፋ አድርገን ብንመለከተው ወያኔ ሲሸነፍ በሻዕቢያ አዝማችነት ወደ ሥልጣን የሚመጣው ጨቅላ መንግሥት ”እንደልባቸው ከሚዋዋሏት ኢትዮጵያ” ምን ይጠብቃሉ ብለን መጠየቅ አስፈላጊ ይመስለኛል። ያሻቸውን ለማድረግ ምን ያግዳቸዋል? ለኤርትራ ውለታ የምንገባው ቃል ምንድን ሊሆን ይችላል? ያኔ በዚያች ቅጽበት እንኳ በኢትዮጵያ ላይ የሰሩትን ግፍ፣ ከወያኔ ጋር እስከተጋጩበት ድረስ የነበረው የሚዘነጋ ነው? ይህ ቀደም ሲል ”... ንጉሱ ይውረዱ እንጂ ከዚያ በኋላ ...” ብሎ የታገለው ወገን ባለማወቁ ወደ እልቂት መጉዋዙን አያስታውሰንም? ”... ደርግ ይውረድ እንጂ ..” ያልንም የወያኔ መጫወቻ ነው የሆንነው። ”እንደ ሃሳባችን ኢትዮጵያን መልሰን ለመገንባት” እንደማን ሃሳብ? እነማን ናቸው ለድል የሚበቁት? የጎጥ ድርጅቶች? የአንድነት ኃይሎች? ምን ዓላማን ያነገቡ ያንድነት ኃይሎች? የአንድነት ኃይሎች ደግሞ በኤርትራ መሬት ሊኖሩም ያስቸግራቸዋል፤ ምክንያቱም አንድነት ብሎ የኤርትራን ቢያንስ ”የዳር ድንበርን፣ የሉዓላዊነትን ጉዳይ” አጀንዳው ውስጥ ያለማካተት ይቸግረዋልና። ያንን ያካተተ ድርጅት ደግሞ በኤርትራ ሞግዚትነት ሥልጣን ላይ ሊወጣ አይቻለውም። ስለ ትጥቅ ትግል ምንም እውቀት የለኝም፤ ግን ከወያኔና ሻዕቢያ ገድል አንጻር ሳየው በሂደት ”ኢትዮጵያ” የሚሉትን ”የነፃነት አርበኞች” በአሉባልታ፣ በክስ፣ በተዘዋዋሪ በቅጥፈት፣ በቀጥታ ጥቃትም እየጨረሱ የራሳቸው አሻንጉሊቶችን አራት ኪሎ ያደርሱ ይሆናል ባይ ነኝ።
ይህ ደግሞ የተካኑት ነገር ነው። እንዋጋ አልን እንጂ የምናምነው ጠንካራ ድርጅት እንኳ የታለ? ወያኔን ልጥል ተነስቻለሁ ካለ ሁሉ ጋር ነው የምንወግነው? ስለዚህ እነአባኪያ ለጋ ሰራሽ የፖለቲካ ቀመር የያዛችሁ ይመስለኛል።
ወያኔ ክፉኛ ስላስመረረን ብዙዎቻችን ”... በምንም መልኩ ይሁን ወያኔ ይውረድ እንጂ ...” የምንል አለን። እንደ እኔ እምነት ከዚህ የስህተት አዙሪት ነው መውጣት ያለብን። መድረሻውን እንደማያውቅ መንገደኛ የደከምንበት ስንሰፍር ዘመናት አስቆጥረናል የኋልዮሽ እያስገመገምን። በመድረሻችን ላይ በቂ ሃሳብ ከሰነቅን በኋላ፣ ማለትም ዓላማና ግባችንን ካወቅን በኋላ ሁላችንም ልንረዳው የምንችለው፣ ልንሸከመ የምንችለው የእውቀት ስንቅ መያዝ መቻል አለብን። በያዝነው የእውቀት ስንቅ ሳቢያ ተመሳሳይ ዓላማና የመንገድ ምርጫ ያለን በአንድ ድርጅት ጥላ ስር ልንከትም እንችላለን። ራዕያችን ወያኔን መጣል ሳይሆን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት ሊሆን ይገባዋል። ይህንን ሁሉም ስለሚለው ሰፊ ፕሮግራምና ጥሩ ትንተና ያካተተ ሰነድ ያስፈልግ ይመስለኛል፤ ተያይዞ ለመጓዝ። ወያኔን መጣል ወደዚያ ከሚያደርሱን መርኀ ግብሮች (Activities) አንደኛው እንጂ በራሱ ግባችን ሊሆን አይገባም። ስለዚህ ጥርት ባለ ቋንቋ ዓላማና ግባችን መታወቅ አለበት። ያኔ ካሰብንበት የሚያደርሰንን ድርጅት መለየት፣ መምረጥ አይገደንም። መሪም አናመልክም ምክንያቱም በቀየስነው መንገድ ይዞን ሊሄድ ይገባዋልና። ካልቻለም በሌሎች መሪዎች የሚተካ ይሆናል፤ በሕግና ደንቡ መሰረት። እናም ካሰብነው ሳንደርስ ደከመን፣ ታከተን፣ ሰለቸን አንልም።
መድረሻችንን ካወቅን የመንገድ ምርጫችን (አስጠቂውን ወይም አጥፊውን ካልመረጥን በቀር) የጊዜ ርዝመትና እጥረት እንጂ የግብ መደናገር አይፈጥርብንም። ግባችን ወያኔን መጣል ከሆነ ግን ወያኔ ከመውደቁ በፊት እርስ በእርስ ተጠላልፈን እንወድቃለን። ስንወድቅስ አልነበረም እንዴ - ትናንት ከትናንት ወዲያ? ታሪክ ጠቅሰው፣ ወኔ ጭረው፣ ”አረ ጎራው!” ብለው የተነሱ ድርጅቶች የንጹኀን ዜጎችን ደም ከገበሩ በኋላ ወደየጥሻው ተሸሽገው የለም? ስለዚህ ነው እውቀት ከሥልጣን መቅደም ያለበት፣ አዲሲቱን ኢትዮጵያ እንገነባለን እያልን የአዳዲስ አምባገነኖች ”ኢንኩቤተር” ወይም መፈልፈያ ልንሆን አይገባም። ባሩድ የሸተተው ደግሞ ከብዕር ይልቅ ሽጉጡን ያምናል። ስለዚህ ወያኔን ጥለን ማጣፊያው እንዳያጥረን መጠንቀቅ ያሻል።
ግንቦት 7 ወደ ትጥቅ ትግል እንገባለን ማለቱን ልብ አልልም። የተረዳሁላቸው ወያኔ ሕግ የሚለውን ባለመቀበል በእነመለስ ፍርደ ገምድል አስተያየት ሕገወጥ የሚሉትንም ትግል አማራጭ እንወስዳለን ያሉ መሰለኝ። በህቡዕ መታገልን፣ ወያኔ ካሰመረው መስመር ውጪ መታገልን ነው በአጽንዖት ሲናገሩ የሰማሁ። ከመንገድ ምርጫ በፊት ጠንካራና አስተማማኝ ድርጅት ይቀድማል። በጅምር ያሉትን አጣድፈን ወደ እሳት መጨመርና ሲደነቃቀፉ ለመዝለፍና ለማጣጣል መንደርደር የለብንም።
አንዱ በሌላኛው ቦታ ሆኖ የመመርመርን መርኅ ሊያሳይ በሚችል ኢትዮጵያዊው እንደ ኤርትራዊ ሆኖ ቢመለከት በሚል መልኩ ”... ኢትዮጵያዊያን ከኤርትራ ጋር መሥራት አይቻልም ብለው የሚያምኑት ሰዎች ይሄን ሃሳባቸውን የሚሰነዝሩት፣ እንደኤርትራዊ ሳይሆን እንደኢትዮጵያዊ እያሰቡ ነውና ...” ብላችሁ ያስቀመጣችሁትን እንመልከት።
እንደጠቀሳችሁትም የኔ ብጤ ኢትዮጵያዊ የኢሳያስ አፈወርቂ የ”ጡት አባትነት” የነፃነት ተስፋውን አያስመለክተውም። ምክንያቱም በአዕምሮው የሚመላለሱ ብዙ ጥያቄዎች አሉና። ሻዕቢያን ከወያኔ የሚለየው ምንድን ነው? የትኛውን ልዩነታቸውን ነው በዘላቂነት በአስተማማኝ መንገድ መጠቀም ይቻላል የምትሉት? ምን ያህል የሻዕቢያ አባላት ናቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ተመልሰው እየሠሩ ያሉ? ምን ያህሉ ናቸው የአስታራቂና የስትራቴጂ ጉዳዮች ውስጥ የሚሠሩት? እኒህ የማፊያ ድርጅቶች የፖለቲካ መርኅ የላቸውምና በፈለገው ጊዜ ግንባር ሊፈጥሩ አይችሉም የሚል ምን መተማመኛ ይዘናል? የሚሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ይጠይቃል። የሻዕቢያ አቀንቃኞች እንደምኞታቸው ነገሮች ባለመሄዳቸው ቁጭት አለባቸውና የወያኔ አባላትን ማስፈራራት አለባቸው። በእናንተ በኩል በዚህ ጉዳይ የዚህ አይነት እምነት ስላላቸው ከወያኔ በዚህ በዚህ ምክንያት ስለሚለያዩ ይህ ለኛ ይጠቅመናል የሚል ትንተና አልሰጣችሁም። ወገናቸውን አስገድለው የፖለቲካ ማይሌጅ ሲያስቆጥሩ ለኖሩ ግፈኞች ደም ተቃብተዋልና ላይታረቁ ተጣልተዋል ብለን እንድንደመድም እንዴት ይቻለናል?
በሌላ በኩል ደግሞ ሆ ብሎ ነቅሎ የወጣና ሻዕቢያን ያርበደብደ እኮ ኢትዮጵያዊው ነው። የደርግ እያልን የፈረጅነው የተበተነው ሠራዊት እኮ ነው ሥራውን የሠራው። ስለዚህ ደም ተቃቡ የምንለው ከማን ነው? ማንንስ ነው አምርረው ሊጠሉ የሚገባቸው? ወያኔን ወይስ ”ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ” የሚለውን ኢትዮጵያዊ? ስትራቴጂና ታክቲክ እንደ አራዳ መገለባበጥ ከመሰለን ከኢሳይያስና ከመለስ የሚበልጥ ማንም ያለ አይመስለኝም። ስለዚህ እኔ እንደ ኢትዮጵያዊ ሳስብ ከኤርትራ ጋር ሠርቼ (የኤርትራን ሞግዚትነት አግኝቼ) ለኢትዮጵያ ነፃነትን ላመጣ አልችልም። እንደ ኤርትራዊ ሳስብ ደግሞ አጃጅዬና ጠፍንጌ ይዤ ለማስፈራርያ የሚሆን ጦር ሳዋ ላይ አስቀምጬ፣ መሀል ሀገር ላይ ሐበሾችን እንደ ፈረስ እጋልባቸዋለሁ፣ ከእጄ መዳፍ አይወጧትም ነው የምለው። ድንገት እነኝህ ”አድጊዎች” ቢለግሙ ደግሞ ሳዋ ላይ ካስቀመጥኩትና ከተራረፉ የወያኔ ምርኮኛ ወታደሮች ጋር ሰንጌ እይዛቸዋለሁ ነው የምለው። ከበሮዬን እየመታሁ ይህንን ዕድል በምንም ተዓምር አላስመልጥም ነው የምለው። እነአባኪያን ደግሞ ”አጆሀ!” ነውና የምትሉኝ ብድራችሁን እግዜር ይክፈላችሁ እላችኋለሁ - ትከሻችሁን ቸብ ቸብ እያደረግሁ።
ደካማ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሆዳም ኢትዮጵያውያንን ለማግኘት ብዙ መሰሪነትም አያስፈልግም በአይነት በአይነት ተትረፍርፎአልና። እናንተ ደግሞ ከታች እንደ ተጠቀሰው ትኩረታችሁ ዓላማ ላይ ሳይሆን ተግባራቸው ላይ ነው። የወያኔ ዓላማው ሳይሆን ያንገበገበን ሥልጣን ከያዘ በኋላ ያደረገው ነው ያላችሁትን እስቲ እንመልከት። እነአባኪያ እስቲ ይህን ሃሳብ መልሳችሁ አንብቡትና ምን ፅንሰ ሃሳብ ነው እዚህ ውስጥ የሰፈረው? ብላችሁ መርምሩት
”... ወያኔ/ኢህአዴግን ዓላማውን ከግብ ለማድረስ በጫካ ከተከተለው መንገድ ይልቅ አጠንክረን ያወገዝነው፡ የጠላነውም ሥልጣን ከያዘ በኋላ ባደረገውና በፈጸመው ግፍ ነው። የወያኔ አካሄድ ከጭቅጭቅና ከውዝግብ ያልጸዳ ቢሆንም፤ የበለጠ ያቃጠለን፣ በየትም ብሎ በየት ሥልጣኑን ከያዘ በኋላ የሠራው ነው። ወያኔ ከፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር ሁሉም ቢሆን ተባብሮ ደርግን መጣሉ ሳይሆን፣ ደርግን ጥሎ ላለፉት አስራ ሰባት ዓመታት የሚሠራው ፀረ-ኢትዮጵያ ሥራ ነው እንድንጠላው እንድንዋጋውም ያደረገን። ወያኔ እንደ አንድ ቡድን ደርግን አሸንፎ፣ ሥልጣን ከያዘ በኋላ በከፈትነው አዲስ የሕይወት ምዕራፍ የሠራው እየሠራም ያለው ግፍ ነው ያቃጠለን፣ የሚያንገበግበንም እንጂ፣ አስቀድሞ የሠራው የተከተለው ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎችን ሁሉ የመጠቀም ስልቱ አይደለም። ...”
ከላይ የተጠቀሰውን ነጣጥለን እንመርምረው። ይህ ፅንሰ ሃሳባችሁ ነው ዋንኛው ”... ወያኔ/ኢህአዴግን ዓላማውን ከግብ ለማድረስ በጫካ ከተከተለው መንገድ ይልቅ አጠንክረን ያወገዝነው፣ የጠላነውም ሥልጣን ከያዘ በኋላ ባደረገውና በፈጸመው ግፍ ነው። ...” [ይህ እኮ ግዙፍ ስህተት ነው ዓላማና ግቡን ለማስፈጸም በጫካ እያለና በትረ መንግሥትን ከያዘ በኋላ ሊያደርግ የሚችለው መለያየቱ እርግጥ ነው። ስለዚህ አንዱን አለሳልሶ አንዱን አርክሶ ማየት እንዴት ይቻላል? ወያኔ የኢትዮጵያ ነፃ አውጭ ነኝ አላለም። ወያኔ ወያኔ ነው። በደንብ ካሰባችሁት ደግሞም እኮ ጫካ እያለ የተከተለው መርኅ አሁን ከሚያደርገው ይብሳል፣ አሁን ተደላድለው ስለያዙት ቶሎ ለማውደምም አልፈለጉም ዘረፋ እስኪጠግቡ በትንሽ በትንሹ ነው እየገደሉን ያሉት]
”... የትናንቱ የወያኔ አካሄድ ከጭቅጭቅና ከውዝግብ ያልጸዳ ቢሆንም፤ የበለጠ ያቃጠለን፣ በየትም ብሎ በየት ሥልጣኑን ከያዘ በኋላ የሠራው ነው። ወያኔ ከፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር ሁሉም ቢሆን ተባብሮ ደርግን መጣሉ ሳይሆን፣ ...” [ደርግ ከማለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የመከላከያ ኃይል ማለት ነገሩን በሚገባ ይገልጠዋል። ደርግ እኮ የጥቂት አምባገነኖች ስብስብ ነው። ደርግ ነው እንዴ ሠራዊት መልምሎ ጦር ያቋቋመው? የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል በደርግ ስም ሲመታ እኮ ነው ኢትዮጵያ መሞት የጀመረችው። የነበረውን ጦርነት የደርግ ባናደርገው ሠራዊታችንን የደርግ ባንል ኖሮ ወያኔም ቅማሉን ባላራገፈብን ነበር? ጀግኖቻችንን ለማኝ አድርገን ሜዳ ሲበተኑ ስቀን ነው ዛሬ የጀግና ያለህ የምንለው። መካከላችን ጥቂት ጥቂት መሣሪያቸውን እንደያዙ ተቀይጠው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ወያኔ አይኖርም ነበር። የጠላት አፈራረጅ ባለማወቃችን የዘራነውን አጭደናል]
ቀጥላችሁም እንዲህ አላችሁን ”... ደርግን ጥሎ ላለፉት አስራ ሰባት ዓመታት የሚሠራው ፀረ-ኢትዮጵያ ሥራ ነው እንድንጠላው እንድንዋጋውም ያደረገን። ወያኔ እንደ አንድ ቡድን ደርግን አሸንፎ ሥልጣን ከያዘ በኋላ በከፈትነው አዲስ የሕይወት ምዕራፍ የሠራው እየሠራም ያለው ግፍ ነው ያቃጠለን፣ የሚያንገበግበንም እንጂ፣ አስቀድሞ የሠራው የተከተለው ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎችን ሁሉ የመጠቀም ስልቱ አይደለም። .....» እንዴ ጠላት የምትሉትን ወያኔ የምትፈርጁበትን መንገድ ከአፈጣጠሩ ለይታችሁ የምታቀርቡ ከሆነ በዚህ መልኩ ሻዕቢያን እንዴት ነው የምታዩ ማለት ነው? ከምትሉት በመነሳት እናንተን ያንገበገባችሁ የያዙት ዓላማ ሳይሆን በሥልጣን ዘመናቸው የተገበሩት ነው (The source of your pain and bitterness is the effect not the cause)። ይህ ደግሞ የእናንተንም ስሜታዊነት፣ ለወያኔ መሸነፍ የመጓጓት ግብዝነትን እንጂ የስትራተጂ ብልህነትን አያስመለክትም። በዚህም ምክንያት ነው ወያኔና ሻዕቢያ ላይታረቁ የተጣሉ የመሰላችሁ።
ሀገርን በዘር፣ በጎሣ የሚነጣጥል ድርጅት፣ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ተግቶ የሠራ ድርጅት፣ ”ኢንፍራስትራክቸር” ያወደመን ድርጅት ደርግን እስከጣለ ድረስ ያደረገው አልጎረበጣችሁም። ምክንያቱም የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊትን ያ ሁሉ ምስኪንና ጀግና ኢትዮጵያዊን ከጥቂት የደርግ አምባገነኖች ጋር ፈርጃችሁ እንደ ዋና ጠላትም አድርጋችሁ ስለቆጠራችሁ ሊሆን ይችላል። ይህ ደግሞ አሁን ወያኔን የምታዩበት ዓይን ነው። ወያኔዎች ደርግ እስኪወድቅ ድረስ የተጠቀሙበት ታክቲክና ስትራተጂ አሁን ሀገሪቱ ከአለችበት የታሪክ አጋጣሚ ጋር የማይገናኝበት ምን ምክንያት አለው? እስቲ ለምንድን ነው ከወያኔ የተሻለ ነገር የጠበቃችሁትና በድርጊታቸውም ያዘናችሁት? ለወያኔ ምን አቀብላችሁታል ብድር የሚከፍላችሁ? ወያኔ ነፃነትና ዲሞክራሲ የሚያንበሸብሻችሁ ምን ስለሆናችሁ ነው? ወያኔ ሰተት ብሎ ለመግባት ዕድሉን ያላገኘ ቢሆን ሰሜን ሸዋ እስከደረሰበት ጊዜ ድረስ ፕሮግራሙ ምን ነበር? ምን ሰማያዊ ተስፋ ነው ሽፍቶች የከፈቱት አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ፍትህን የሚያዘንበው? ወያኔ እንደ እባብ ቆዳውን ለወጦ ኢህአዲግ አለ እንጂ ምኑ ተቀይሮ ነው? በእንጭጩ ሊጠፋ ይገባ የነበረው ነው ዛሬ ድፍን ኢትዮጵያን በዘር ያመሰው። የእነርሱና የሻዕቢያ የክህደት መንገድም ጭምር እኮ ነው ከሶማሌ ጦርነት ጋር ተደምሮ የሶሻሊዝም አረንቋ ውስጥ የከተተን። ከድጡ ወደማጡ እንዲሉ ከወታደራዊ አምባገነን ወደ ጎጠኛ ሽፍታ ስንሸጋገር አዲስ የተስፋ ጭላንጭል ያሳየን አዕምሮ እንዴት ቢያስብ ኖሯል?
የዐረፍተ ነገር አጨራረሳችሁማ የሚደንቅ ነው። ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎችን ሁሉ የመጠቀም ስልቱና ያስከተለው ጠባሳ ካልቆጫችሁ ምኑ ነው የሚያንገበግባችሁ? የሀገሪቱን ችግር የምትመለከቱበት የዘመን ስሌት (ካላንደር) ከየት ነው የሚጀምረው? ከቀድሞው የተማሪዎች ”የለውጥ ትግል” ጀምሮ አሁን እስካለንበት ድረስ ከጥፋት ወደ ጥፋት ያሸጋገሩን፣ ሀገራችን ያላትን ስትራቴጂያዊ የመልክዓ ምድር አቀማመጥና ታላቅነት ያሳጡን፣ በውሀ ሀብታችን ላይ እንኳ ጠንከር ያለ ዐረፍተ ነገር እንዳይወጣን አቅማችንን ያሳነሱበትን ሁሉ አቅልለን ልናይ እንዴት ይቻለናል? በዚሁ እናንተ ባጣጣላችሁት ቀመር እኮ ነው የግብፁ ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ የኤርትራን የመገንጠል ማሕተም ያለማቅማማት ያኖረው። ባለ ሁለት ጠጉር ነን የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች እኮ ከአጋም ቢጠጉ ነው ሲያለቅሱ የሚኖሩት። ወያኔና ሻዕቢያ ይዘው የተነሱት ሃሳብ እኮ ነው ሀገር እያፈረሰ ያለው ወገኖቼ!! ሥልጣን ከያዙ በኋላ ያደረጉትማ ትንሽ ነው (ተደላድለው እንደሚዘርፉ ባያውቁ ኖሮ ኢትዮጵያ ገና ድሮ ታሪክ ሆና ነበር።) እንደተጫኑት ክፋት ገና የሚያደርጉትን ነው መፍራት። በዚህ የነገሮችን ስረ መሰረት ባለመመርመር ምክንያት ሊሆን ይችላል እንቁላሎቻችንን ሁሉ የኤርትራ ቅርጫት ውስጥ ማኖር የመረጣችሁት፣ ከሚፈለፈለው የሚገማውን ልብ ባለማለታችሁ።
የአብሮ መሥራት መከራከርያ መሰረታችሁ የሻዕቢያ ቁጭት ነው። ቁጭት የራዕይ መሰረት ሊሆን አይችልም። ቁጭት ከስሜት (emotion) ይወለዳል፤ እውቀት ግን ከአመክኖ (Reason)። ሁለቱም ወደ ተግባር ሊነዱን ይችላሉ። ወደ ግብ የሚያደርሰን ግን አንደኛው ብቻ ነው። አኩራፊነትና ቱግ ባይነት ቶሎ መተንፈስም የአሥመራ ልጆች መለያ ጠባይ ነው። እናንተም ይህንኑ ለአብሮነት እንደ ማሳመኛ እንዲህ አቀረባችሁት ”... ኤርትራ መንግሥት ዛሬ የወያኔ ስርዓት የያዘው ሥልጣን የሱ እንደነበር በማሰብ የቁጭት ዕድሜ እየገፋ እንደሆነ መመልከት ይቻላል። ዛሬ ኢህአዴግ የሚንደላቀቅበት ሁሉ የነሱ ነበር። ...” በዚህ ዓይነት ቁጭት የሚናጥ እብሪተኛ፣ ኢትዮጵያውያንን አምርሮ የሚጠላ፣ የተፈጥሮ ሀብቷን በመቁለጭለጭ እየተመለከተ ያለን መሰሪ ይወግነኛል ማለት ሚዛን የማያነሳ የመከራከሪያ ነጥብ ይመስለኛል። ይህን ጥላቻና ክፋታቸውን ቀደም ብለው አውሮፓና አሜሪካ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ልብ አይሉትም ብዬ አላስብም። ኢትዮጵያ ውስጥ ወይም ከኤርትራ ተባርረው የወጡትን ያለመጠይቁ ይሻላል። በዘረፋ ክፍፍል ምክንያት እርስ በእርስ ለመጫረስ ወደኋላ ካላሉ ቡድኖች ከኢህአዲግና ከሻዕቢያ ብሎ መምረጥ ’ጅብ ይብላኝ አንበሳ’ ከማለት የራቀ አይመስለኝም። ለአብሮነት ሊሆን የሚችል ሚዛን የሚደፋ ቀመር ካለ ያንን ብትነግሩን ደስ ይለኛል።
ኤርትራ ኢትዮጵያን ሳታሰነካክል፣ የኢትዮጵያ የሉዓላዊነት ጥያቄ ትን ሳይላት ተቀብላ እንደ ጥሩ ጎረቤት ልትኖር ትችላለች ማለት አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም እንዴትም አድርጋ እንደ ሀገር ራስዋን ችላ መኖር አይቻላትም ”ቁጭትዋን” ሳትወጣ። ለዚያ መልካም ፈቃድ ካለን ወይንም እንደለመድነው ስንደርስ የምናደርገውን እናውቃለን የምንል ከሆነ አጨብጭበን ቁጭ ይመጣል። ”እንደለመድነው ትዕግስት ፍርሀት አይደለም እያልን በተራ በተራ እስክንጨፈጨፍ መጠበቅ ነው።” የለም አንተው ያልገባህ ነገር አለ ካላችሁ እውቀት አስጨብጡኝ የምማረው እጅግ ብዙ ነገር እንዳለ አምናለሁ። ”.. ዋናው ወያኔ ነው ከዚያ በኋላ ...” የሚለው መደናቆር ከታሪካችን ለመማር ያለመቻል ይሆናል ባይ ነኝ። ከጅቡም ከአንበሳውም መንጋጋ የሚያተርፈንን መንገድ ነው ልንመክርበት የሚገባ። ለዚህ አቅም ከሌለን እንደተሸነፈ ጄነራል ስለጦርነት ያለማውራቱ ይበጀናል።
”... በኢህአዴግ ስር ከምንኖር ደግሞ የተሻለውን ክፉ መምረጥ ይሻላል። ...” ብላችኋል። የሰይጣን ጆሮ አይስማውና ይህንን ያላችሁት አስባችሁ መስሎአችሁ ከሆነ ያላችሁትን ትንሽ ተረጋጉና መጀመሪያ በግል ከዚያ በደቦ ምከሩበት። የተሻለ ክፉ ለመምረጥ እንዴት ከሻዕቢያ ተቧድነን እንሙት? ሻዕቢያ ከወያኔ ይሻላል የምንለው በምን ሚዛን ሰፍረናቸው ነው? የደርግ ሥልጣን የዘመመ ሰሞን ወዳጆቼ ”... እንዲያው የፈለገው ቢሆን ከደርግ የከፋ መንግሥት ሊመጣ አይችልም ...” ይሉ ነበር። ከወያኔ ዘንድ ፍትህን ሊመፀወቱ። እናንተም የወያኔ የእምነት መሰረት ሳይሆን ያስመረራችሁ መርኀ ግብሩ ነው። ተግባር ከእውቀት ይወለዳል። የወያኔና የሻዕቢያ እውቀት ደግሞ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገርን ማጥፋት ነው። ይህን እውቀታቸውን ነው በአግባቡ እየተጠቀሙ ያሉት። ኢትዮጵያ ማለት ደግሞ እኔና እናንተ ነን። እኔና እናንተ ደግሞ ከበሬ የምንለየው ማሰብ ስለምንችል ነው። ስለዚህ አራጆቻችን ጓሮ ያለው ግጦሽ አያጉዋጓኝም። በዚህች ትንሽ የቁጭት ተስፋ ልቤ አይማልልም። ልጁን ለመጣልም ከአባቱ ጋር መወገንን ብልጠት አልለውም።
ያቀረባችሁት ኤርትራ እንደ አማራጭ ሊሆን ይችላል የሚል መላ ምት እንኳ ቢሆን ኖሮ መልካም ነበር። ምክንያቱም መላ ምት የሚፈተሽ በሙከራ በምርምር ወደ መልስ የሚያመጣ ያልተረጋገጠ ግን ሊሆን የሚችል ግምት ነውና። የእናንተ ግብ ወያኔን ማጥፋት ላይ ያነጣጠረ እንጂ ድኅረ ወያኔ ምን አይነት ኢትዮጵያ የሚል አለመሆኑ አዲስ ችግር እንጂ ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣ መንገድ አይመስለኝም። ለዚህም ነው በእኔ እምነት ካስማና ማገሩን ችሎ የማይቆም የመደርመስ ዕድሉ ከፍ ያለ የዘመመ የሃሳብ ዋልታ ይዛችኋል። እንዲያም ሆኖ ይህን ሃሳባችሁን እጋራለሁ ”... ኤርትራን እንደ አጋር ለማየት ከመወሰናችን ወይንም ከኤርትራ ጋር የመሥራት ሃሳብ ላይ ከመምከራችን በፊት ስለህወሓት/ኢህአዴግ ያለን እምነት ተቀራራቢ ካልሆነ፣ ቀድሞውንም በኤርትራ ጉዳይ ላይ መምከር የለብንም። ...” በዚህ መሰረት ወያኔን ከሻዕቢያ የሚለየውን የባህርይ፣ የስሪትና የራዕይ ልዩነትና አንድነት ለውይይት ማቅረብ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ኤርትራን እንደ የደህንነት መንገድ የሚመለከቱ ለዚህ ውይይት መረጃቸውን ቢያቀርቡ የኔ ቢጤው ዕይታውን ሊለውጥ ይችል ይሆናል። በወያኔ ላይ ያለ ተቀራራቢ ሃሳብም እንኳ ኤርትራን እንደ አጋር ለማየት መንደርደርያ አይሆንም። ይልቁንም መመዘንና ማወቅ የሚያሻው የሻዕቢያን ጉዳይ ነው።
ለእናንተ የሻዕቢያ ጉዳይ ያለቀለት ጥርጊያ መንገድ ይመስላል። የእናንተን መነጽር ተውሼ እስካይበት ድረስ ለእኔ ሻዕቢያና ወያኔ ከዳቦዬን ቀማኝ በላይ ጠብ የላቸውም። ሻዕቢያ ወያኔን ቁልቁል የሚያይበት የእብሪት ዓይኑን ከታከመ እኛን ገብረው በእኛ ደም ታጥበው ይታረቃሉ ባይ ነኝ። አቤት እንዴት ነው የማላምናቸው? «There is no permanent enemy in politics» የሚባለው ፈሊጥ እንኳ ፈታ አያደርገኝም። አንሰው ያሳነሱን፣ ተዋርደው ያዋረዱን ነው ጎልቶ የሚታየኝ። እውነቴን ነው የምላችሁ አሁን ባለኝ እውቀት የአሥመራ መንገድ የነፃነት ጎዳና ላይ አያወጣም ባይ ነኝ።
በጽሑፋችሁ መጨረሻ አካባቢ ከፈረሱ ጋሪውን አስቀድማችሁ ”ቼ!” ማለታችሁን አመላካች ዐረፍተ ነገሮች አክላችኋል። ስለዚህ በመጀመሪያ ለጠንካራ ድርጅት መመስረት ካለም ለመጠናከሩ ትጉ። በዚያ ውስጥ መሠራት ያለበት ሲጠናቀቅ ነው ያለን አቅም፣ የድርጅት ብቃት፣ የፓርቲው ፕሮግራም ዓላማና ግቡ ላይ የሰፈረውን ሃሳብ መዝነን ለመንገድ ምርጫ የምንደራደረው። የትንቢተ ኢሳያስን የቤት ሥራ ምልክቱን አላየንም የምንል ያለን አይመስለኝም፣ የሻዕቢያ ዘፍጥረትና የብጽአት የውይይት መንደርደርያችሁ እንዲሁ እንደ ጭውውት እንጂ ደም የሚያስከፍል ጉዳይ የሚመዘንበት አልመሰለኝም፤ ወይም አቅሜ አይፈቅድምና ልተወው። ለኢሳይያስ ዕድሜ መጸለያችሁ የኤርትራውያንን ጣር አብዛባቸው ማለት ነው። እግዜር ደግሞ ግማሽ ክርስትና አይገባውምና ለእኛ ደህንነት የሌሎቹን ጣር አብዛላቸው ብንል ደግ አይደለም። የሚሰማችሁ ከሆነማ ወያኔን አትንንልን አትሉም ነበር? መለስ መስለል ሲጀምር ባይ እኔም የጧፍ መዋጮ አቀርብ ነበር።
«... አምላኬ ሆይ ስለሰጠኸኝ መረጋጋት አመሰግናለሁ! የአባኪያና የጓደኞቹን ልብ ደግሞ አራራልኝ ለነርሱም መረጋጋትን አብዝተህ ስጥልኝ። ቸር ነህና ለስትራቴጂና ታክቲክ ይሆን ዘንድ የሩቁን አቅርቦ ማሳያ መነጽርም ስጥልኝ፣ ያዩትንም ያጋሩኝ ዘንድ አንደበታቸውን ክፈት። የጻፍኩትን አሽቀንጥረው እንዳይጥሉ ትዕግሥትን ስጥልኝ! »
ከዳኛቸው ቢያድግልኝ - This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



