ኢትዮጵያና ችጋር (ከፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም)
መንግሥት ባለበት ህዝብ በችጋር አይሞትም
መስፍን ወልደማርያም (ፕ/ር)
በ1930ዎቹ የኢጣልያ አገዛዝ ሊያበቃ ሲል፣ ክፉ ረሃብ በአዲስ አበባ ውስጥ እንደነበረ አስታውሳለሁ፤ ምናልባትም በገጠር የከፋና ወደ ችጋር የሚጠጋ ሳይሆን አልቀረም የሚል ግምት አለኝ፤ በአፄ ኃይለሥላሴ አገዛዝ ችጋርን በዓይኔ ያየሁበትና ቀምሼው ምንነቱን ያወቅሁበት ነበር። በዚህም ምክንያት ብዙ ተናግሬአለሁ፣ ብዙም ጽፌአለሁ።
በዚያን ጊዜ የደረስሁበት መደምደሚያ የኢትዮጵያ ገበሬ ነፃ ካልወጣና የራሱና የኑሮው ባለቤት ካልሆነ፣ በሀገሩ ላይ የሥልጣን ባለቤት ካልሆነ ችጋርና ኢትዮጵያ አይለያዩም የሚል ነበር። ይህንን በጥናት የተደገፈ ሃሳብ ለአለፉት ለሁለቱ አገዛዞችና ለዛሬውም አስታውቄአለሁ፤ ነገር ግን ሥልጣንና ዕውቀት የተጣሉበትና የማይነጋገሩበት ሀገር በመሆኑ ምንም ውጤት አላስገኘም።
ስለዚህም ዛሬ እንደተለመደው በውጭ የዜና ማሠራጫዎች ስለኢትዮጵያ ችጋር በምስል የተደገፈ ሐተታ እንሰማለን፤ የእኛ የህዝብ የዜና ማሠራጫዎች የሚያወሩት ስለጥጋብ ነው። በ1966 በአጼ ኃይለሥላሴ የመጨረሻ ዘመን የተቋቋመው መርማሪ ኮሚስዮን (ብዙ ሰዎች አውቀውም ይሁን ሳያውቁ፣ ዐዋጁን እንኳ ሳያነቡ ደርግ ገና ሳይፈጠር የተቋቋመውን ድርጅት፣ የደርግ መርማሪ ኮሚስዮን ይሉታል፤ ምናልባትም የአፄው ዘመን የመጨረሻው ዐዋጅ ወይም ከመጨረሻዎቹ አንዱ ይሆናል፤) ለ1965 ችጋር በኃላፊነት ምርመራ ከአካሄደባቸው መሥሪያ ቤቶች አንዱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ነበር። እንደሚመስለኝ የመርማሪ ኮሚስዮን ሠነዶችና ፊልሞች ሁሉ በዚያው መሥሪያ ቤት ናቸው። ለብሔራዊ የመጻሕፍትና የመዝገብ ቤት ተሰጥተው እንደሆነ አላውቅም። ፍሬ ነገሩ ምርመራው ለዚያ መሥሪያ ቤት ወደፊት የችጋር መረጃን በትክክል ባለማስታወቅ ተጠያቂ ሊሆን ነው መማር ተስኖት።
ነኀሴ 17 በአንድ የውጭ ቴሌቪዥን እንደሰማሁት፣ ቤንጋል በሚባል የሕንድ የምሥራቅ ክፍል፣ የታታ ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ከገበሬዎቹ እያስገደዱ (ማስገደጃው ዘዴ ብዙ ነው) በገዙት መሬት ላይ በዓለም በጣም ርካሽ (25,000 ብር ግድም) የተባለ መኪና ለመሥራት ያቀደውን ህዝቡ ተቃውሞ አስቆመው፤ የህዝብ የሥልጣን ባለቤት የሆነ ህዝብ ለማስቆም ይችላል። በአፄው ዘመን የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሲቋቋም በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ያስከተለውን ችግር ጽፌ ያነበበውም ባለሥልጣን የነበረ አይመስለኝም፤ ህዝቡም የሥልጣን ባለቤት አይደለምና በችግሩ ላይ ችግርን እየከመረ እስከዛሬ ይቀጥላል።
ሥልጣንን የጭቆና መሣሪያ የሚያደርግ አገዛዝና በጭቆና ተደቁሶ ጸጥ-ለጥ ብሎ የሚገዛ ህዝብ፣ ችጋርን በየዓመቱ እያስተናገዱ ማለትም በቋሚ መሥሪያ ቤት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ቀጥረው የሙት-ዓመት ድግስ እያዘጋጁ፣ የዓለምን ሀብታም ሀገሮች ለምፅዋት ይማጸናሉ። ይህ ኁነት በሦስት የተለያዩ የአገዛዝ ሥርዓቶች ሳይለወጥ እየቀጠለ ነው፤ የጅምላ ሞትን፣ ዓጽማቸው ብቻ የቀረ ሕጻናትን መደበቅ የማይቻል ሆኖ ነው እንጂ ሸምጥጦ በመካድ ችጋርን በጥጋብ ምስል ለመጋረድ ሳይሞከር አልቀረም። በ1965 መጋረጃውን አንስቶ ችጋሩን ያጋለጠው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የመምህራንና የተማሪዎች ትብብር ነበር፤ ዛሬ ሁሉም የሉም።
ችጋር የከፋ ሞት ነው። ማኅበረሰቡ እያንዳንዱን ሰው ከድቶት ቀባሪ እስቲያጣ ድረስ ለየብቻው የሚያስቀርበት አስከፊ ሁኔታ ነው። የኃይማኖት መሪዎች ሁሉ የሚሰብኩት ባዶ የቅንጦት ወሬ ሆኖ የሚጋለጥበት ነው፤ ሰብዓዊነት ቀርቶ ዝምድናና ወዳጅነት ትርጉም የሚያጡበት ሁኔታ ነው። ህዝብ ለጭቆናና ለብዝበዛ የተከማቸ መሣሪያ እንጂ ባለቤት ያልሆነበት ሁኔታ ነው። ህዝብ አለኝታውና ተስፋው ተሟጥጦ ሞትን የሚጠብቅበት ሁኔታ ነው። ህዝብ አቅመ-ቢስ ተደርጎና ለነገ ለራሱ እንዳያስብ ተሰንጎ በመደረጉ፣ ከጉንዳን ያነሰ መስሎ የሚታይበት ሁኔታ ነው። ሕፃን ልጅ ጡቷ የደረቀበትን የእናቱን ጡቷን ሲያኝከው በመቀሌ አይቻለሁ። ማንም ያንን ዓይነት ሁኔታ በየትም እንዲያይ አልመኝም፤ ከውስጥ የማይጠፋና የሚያንገበግብ ፍም ነው።
ችጋር የከፋ ሞት ነው። የአንዳንድ ሰው የግል የከፋ ሞት ብቻ አይደለም፤ የከፋ የህዝብ ሞት ነው። የከፋ የሀገር ሞት ነው። በችጋር የተጠቁ ከአምስት ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸው ሕፃናት አዕምሮአቸው ጎደሎ እንደሚሆን በጥናት የተረጋገጠ ነው። ስለዚህም ተከታታይ ችጋሮች የአዕምሮ ጉድለት ያለባቸውን ሰዎች እያበረከተ እንደሚሄድ መገንዘብ ያስፈልገናል። ጉዳቱ በሚሞቱት ሰዎች ቁጥር ብቻ የሚከሰት ሳይሆን፤ በተረፉትም ላይ ክፉ ማኅበረሰባዊ ጠባሳን የሚያስቀር ነው። የችጋር ጠባሳው አቅመ-ቢስ እያደረገ ለአገዛዝ ጭቆና የተመቸ ህዝብን፣ ከቆየም ለሀገር የመቆም አቅሙን ያጣ ህዝብን ይፈጥራል። ችጋር ተጠቂዎቹን ብቻ ሳይሆን ጨቋኞቹንም ሰው ከመሆን ደረጃ ያወጣቸዋል። አንዱን በአቅመ-ቢስነት፣ አንዱን በግድ የለሽነት።
የችጋር ጻዕር በሚሠማበት ሀገር፣ የችጋር ጻዕር አካሉን ጨርሶ ነፍሱን ሠንጎ በያዘበት ህዝብ ላይ ሥልጣን ምን ማለት ነው? እየፈሩ መግዛት፣ እየበሉ መክሳት ፋይዳ-ቢስ ከመሆናቸው ሌላ፣ የተለያየ ሕክምናን የሚጋብዙ ናቸው። እያፈሩ መግዛት ያከብር እንደሆነ እንጂ አያስከብርም። እጅ ያስነሣ ወይ አሽቃጣሪዎችን ያበረክት ይሆናል እንጂ አያስወድድም። ወተት የምትሠጠውን ላም አርዶ የሚበላ ገበሬ ለራሱም ሆነ ለቤተሰቡ እያሰበ አይደለም ግን የነገውን ችጋር እያረጋገጠ ነው።



