ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም (ትርጉም በነጻነት ለአገሬ)

ቅዱሱ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፣ “የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው።” (ማቴ፣ ፭፣ ፱) ለሰው ልጆች የሰላም እና የዕርቅን መልክዕክት ለማድረስ ዓላማ አድርገው ለሚንቀሳቀሱ ሰዎች የተሰጠ መርሆ ነው። በግለሰቦች እና በአገሮች መካከል እውነተኛ ሰላም የሚገኘው በእርቀ ሰላም ሂደት የተሰበረውን ግንኙነት ቀድሞ ወደነበረበት መመለስ ሲቻል መሆኑን የሚያስተምረን መልዕክት ነው።

በአሁኑ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለግብጽ ሕዝቦች እንዲህ በማለት ነገረዋቸዋል፣ “ለግብጽ ሕዝቦች ለመናገር የምፈልገው ነገር እኛ ኢትዮጵያውያን የወንድማማችነት እና ጎረቤታማነትን የመንፈስ ዋጋ ውድነት እናውቃለን፤ እናም ፈሪሀ እግዚአብሔር/አምላክ ያደረብን ሕዝቦች ነን። ስለሆነም በምንም ዓይነት መልኩ የግብጽን ሕዝቦች አንጎዳም“ ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ቅዱሱ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፣ “ለክፉዎች ሰላም የላቸውም።“ በጠብመንጃ ኃይል ሰላምን ለማምጣት ለሚፈልጉ፣ ኃይልን ለሚጠቀሙ ወይም ደግሞ ሰላምም ጦርነትም የሌለበት ሁኔታን ለመፍጠር ለሚፈልጉ ሰላም የላቸውም።

ባለፈው ሳምንት እ.ኤ.አ በ2002 ዓ.ም በኤርትራ መንግሥት እና በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሬፐብሊክ መካከል የነበረውን የድንበር ማካለል ጉዳይ በማስመልከት የኤርትራ እና የኢትዮጵያ የድንበር ኮሚሽን የወሰነውን ውሳኔ ተቀብለው ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ባለፈው ሚያዝያ ወር በዓለ ሹመታቸውን ባከበሩበት ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቃል ገብተውበት የነበረውን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲህ በማለት ይፋ አደረጉ፡

“ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለበርካታ ዓመታት ጠፍቶ የቆየውን ስምምነት የመጨረሻ እልባት ለመስጠት ከልብ እንፈልጋለን። ከዚህም በተጨማሪ የእራሳችንን ኃላፊነት እንወጣለን። በሰከነ ውይይት አማካይነት ልዩነቶቻችንን ለመፍታት ዝግጁነታችንን ስንገልጽ የኤርትራ መንግሥትም ለጋራ ፍላጎቶቻችን ብቻ ሳይሆን በሁለቱ አገሮች መካከል ባለው የደም ትስስር ሲባል ተመሳሳይ አቋም በመያዝ ለስኬታማነቱ የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ“ ነበር ያሉት።

ለኤርትራ የሰላም የዘንባባ ዝንጣፊን ለማበርከት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግልጽ ባልሆነ ዴፕሎማሲያዊ ቋንቋ ወይም ደግሞ በፖለቲካዊ መንፈስ ትክክል በሆኑ ሆኖም ግን ከዋናው ጉዳይ ባፈነገጡ ቃላት አልተደበቁም። ሆኖም ግን እርሳቸው በአገር ውስጥ እና በውጭ ሰላም እና እርቅን ለማውረድ ከልብ የሚሰሩ እንደሆኑ ለዓለም ሕዝብ ግልጽ አድርገዋል።

“ልዩነቶችን በሰከነ ውይይት” ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ከልብ እንደሚሰሩ” የተናገሩት ልቤን ነክቶታል። ሁሉም ፖለቲከኞች በሁሉም የአፋቸው ጎን በመንታ ምላስ እንደሚናገሩ አውቃለሁ። እውነተኛ የሰላም ሰው ከልብ ትርታው እንቅስቃሴ አንጻር ይናገራል እንጅ በአእምሮው ውስጥ የጦርነት ከበሮን በመደለቅ የሸፍጥ ንግግር አይናገርም።

ለ27 ዓመታት ያህል የከፋፍለህ ግዛ እና በጦርነት፣ በኃይል እና በበቀል የመግዛት አባዜ የተጠናወተው የኢትዮጵያ የአገዛዝ ስርዓት ምስክር እንደመሆኔ መጠን በአገር ውስጥ ለሰላም እና ለእርቅ እንዲሁም ለጎረቤት አገር የፍቅር መርሆ መስዋዕትነትን ለመክፈል አጠናክሮ እየሰራ ያለ መሪ በኢትዮጵያ ውስጥ አያለሁ የሚል በጭራሽ ሐሳብም ኖሮኝ አያውቅም። ይገርማል! “ተስፋ በሰው ልጆች ልብ ውስጥ ዘላለማዊ ነው። ሰው ዘላለማዊ አይደለም። ሆኖም ግን ሁልጊዜ የተቀደሰ ነገር ይሆናል” የሚለውን አሌክሳንደር ፖፕ ንገግርን ያረጋግጥልናል።

በድንበር ኮሚሽኑ ብይን መሰረት ውሳኔውን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የመንግሥታቸውን ውሳኔ በመግለጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንዲህ ብለዋል፡

“ላለፉት 20 ዓመታት ከኤርትራ ጋር ከነበረን ጦርነትም ሰላምም ከሌለበት የከባቢ አየር ድባብ ሁኔታ ያተረፍነው ነገር ቢኖር ውጥረት ነው። ጦርነትም ሆነ ሰላም ከሌለበት ሁኔታ ኢትዮጵያም ሆነች ኤርትራ ምንም ዓይነት የተጠቀሙት ነገር የለም። ያሉንን ጥረቶች ሁሉ ለሰላም እና ለእርቅ በማድረግ ከጥቃቅን ግጭቶች እና ልዩነቶች እራሳችንን ነጻ በማድረግ ድህነትን በማስወገድ ላይ ትኩረት አድርገን እንስራ“ ነበር ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለአስርት ዓመታት ተንሰራፍቶ እና ዋና የችግር ምንጭ በመሆን በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የነበረውን ዴፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሽባ አድርጎት የቆየውን ሰይጣናዊ ድርጊት ከልብ በተሰነቁ ጥቂት ዓረፍተ ነገሮች በጣጠሱት። የጄ/ል ዶግላስ አርተርን አባባል በመዋስ በእንደዚህ ያለ ቀላል ድርጊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “የጠብመንጃን አውዳሚነት፣ የትናንሽ መሳሪያዎች ተኩስ ድምጽን፣ ልዩ እና አሳዛኝ የጦር ሜዳ ማጉረምረምን“ ጸጥ አድርገውታል።

ጠብመንጃዎች ጸጥ ብለዋል። በአሁኑ ጊዜ ሲሰቃዩ የቆዩት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሕዝቦች ይናገራሉ፣ ከዚህ በኋላ ሁለቱ አገሮች ድምጾቻቸውን ከፍ በማድረግ እንዲህ በማለት ይናገራሉ፣ “ጎራዴዎቻቸው ወደ ማረሻነት ይቀየራሉ፣ ጦሮቻቸው ወደ አበባ መቁረጫነት ይቀየራሉ። አገር በአገር ላይ ጎራዴ አይመዝም፣ ስለጦርነት ምንም ነገር አያስቡም።“ ጎራዴዎች ወደ ማረሻነት ሲቀየሩ የማየት ምስክርነቴ ለእኔ የደስታ ምንጭ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በይፋ ስልጣን ከተረከቡ ጀምሮ በወሰዷቸው ድፍረት እና ጥንካሬ የተቀላቀሏቸው እርምጃዎች እያንዳንዱን ሰው አስደንቀዋል። በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና እንደዚህ ያሉ ፈጣን ለውጦችን እያሳዩ በመሆናቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦልት (የአጭር ርቀት ፈጣን ሩጫ የዓለም ሪከርድን ያስመዘገበውን ኡሳይን ቦልትን በማስታወስ) እያሉ ይጠሯቸዋል።

በእያንዳንዱ ቀን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እውነተኛ የሽግግግር ስርዓት መሪ መሆናቸውን ለዓለም እያስመሰከሩ ነው። እርሳቸው አስተዳደራዊ ተቋማትን እና ሂደቶችን ብቻ አያደለም እያሸጋገሩ ያሉት። ሆኖም ግን እርሳቸው እያሸጋገሩ ያሉት በአገር ውስጥ ያሉትን ኢትዮጵያውያን እና በውጭ አገር ያሉትን ዲያስፖራዎች ልቦች እና አእምሮዎች ጭምር ነው። በየቀኑ የምሰማው ነገር ቢኖር “ዓብይን ያሳደጉት አነሱ ናቸው። የነሱ አገልጋይ ነው። መታመን የለበትም” የሚሉት ሰዎች በየቀኑ የዓብይ ደጋፊዎችህና ተከራካሪዎች እየሆኑ ነው።

እንግዲህ ይኸ ሊቋቋሙት የማይቻል የዐቢይ አሕመድ ታዕምራዊ ድርጊት ነው። ከአስር ሳምንታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሌላው ቀርቶ ድንጋይ ልብ የሆኑትን፣ የአረብ ብረት አእምሮ ያላቸውን ሰዎች ልቦች እና አእምሮዎች በቅንነት፣ በስልጡንነት፣ በሩህሩህነት፣ በጓዳዊነት፣ በፍቅር፣ በሞያዊነት እና በፍትሀዊነት አሸንፈዋል።

ለእኔ እርሳቸው በበለጠ እንዲወደዱ ያደረጋቸው ለእያንዳንዱ ሰው ሊታይ በሚችል መልኩ የኢትዮጵያዊነትን መለያ ምልክት በእጃቸው ክሳድ ላይ የማሰራቸው ሁኔታ ነው። ልክ እንደ እኔ ሁሉ ማለት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በይፋ ስልጣን በተረከቡ ጊዜ የቀድሞው የአፍሪካ የዩናይትድ ስቴትስ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄርማን ኮኾን እንዲህ ብለው ነበር፡

“መልዕክት ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፡ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሻሻል ድፍረት የተሞላባቸውን እርምጃዎች ከመውሰድ እንዳያቅማሙ። የህወሀት የፖለቲካ -ኢኮኖሚ ጠቅላዮች አጭበርባሪዎች መሆናቸው ተጋልጧል። እናም እርስዎን ሊያዳክሙ አይችሉም። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከእርስዎ ጎን ነው“ ነበር ያሉት።

እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም አምባሳደር ኮኾን እንዲህ ብለዋል፣ “ህወሀት እንደ አናሳ ቡድን አገሪቱን መግዛቱ እየተወገዘ ነው። ይህም ጉዳይ ለአገሪቱ መረጋጋት አደገኛ ሁኔታ ነው።“ እ.ኤ.አ ታህሳስ 2015 ዓ.ም ኖርማን ኮኾን በህወሀት አገዛዝ ከሕግ አግባብ ወጭ የተፈጸመውን ግድያ እና የዘፈቀደ እስራት አውግዘዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት የፖለቲካ መሪዎች እነርሱን በመቃዎም በመንገዶች ላይ ሰላማዊ ሰልፍ የሚያደርጉትን ተቃዋሚዎች የመግደል መመሪያ አላቸው። እ.ኤ.አ ታህሳስ 2017 ዓ.ም ኖርማን ኮኾን በህወሀት ላይ እንዲህ የሚል ትንበያ አድርገዋል፣ “በዋናነት የኢኮኖሚ እና የስልጣን ማጋራት የሚባል ነገር የለም። እናም እንደዚህ ያለ አናሳ ቡድን ነው የነበረው። ይኸ በጣም ጤናማ ያልሆነ ነገር ነው፤ እናም ይኸ ጉዳይ ብዙ የሚቆይ ነገር አይደለም። አሁን እያየሁት ባለው መረጃ መሰረት ብዙ ሊቆይ የሚችል አይደለም፣ ብዙ አይቆይም“ ነበር ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአገር ውስጥ ለሚያካሂዱት የሽግግር ለውጥ እና የዴሞክራሲያዊ ጥረቶች እና የአፍሪካን ቀንድ ቀጣና ከማረጋጋት አኳያ ከኢትዮጵያ ሕዝብ እና ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጠንካራ ድጋፍ እንዳላቸው ብዙም የሚያጠራጥር አይደለም። በእርግጥ የእርሳቸው የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ተግባራዊ ማድረግ ሊለካ ከሚችለው ባላይ ቀጣናውን ሊያረጋጋው ይችላል።

የተሳሳተ ሐሳብ ይዘው ለሚጮሁት እውነትን መናገር፡ ለድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ውጤት መለስ ዜናዊን አውግዙ እንጅ ዐቢይን አሕመድን አትንኩ፣

በአሁኑ ጊዜ ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ ውሳኒያቸውን በገለጹት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንግግር ላይ የሚያጉረመርሙ ሰዎች አሉ። ውሳኔውን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ በመወሰናቸው “የአገር ክህደት” ፈጽመዋል፣ “ታሪካዊ ስህተት” እና “አሳፋሪ ድርጊት” ሰርተዋል በማለት በንዴት ይደነፋሉ። የኢትዮጵያ ኤርትራን ወሰን እና የባድመን ከተማ ለመጠበቅ ሲባል በተካሄደው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሞተዋል፤ እንዲሁም በርካታ በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ አገር ጥለው ተሰደዋል ይላሉ። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አምባገነናዊ መንግሥት ምንም ዓይነት ሕዝባዊ ውይይት ሳይደረግበት፣ ግብአት ሳይቀርብ፣ ክርክር እና ሞያዊ ምክክሮች ሳይደረጉ የእራሱን ውሳኔ ሰጥቷል ይላሉ። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ውሳኔ ያለመደሰታቸውን እና ተቃውሟቸውን ለማሳየት ታላላቅ ስብሰባዎችን በማድረግ እና ሰላማዊ ሰልፎችን በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።

እንደ አጋጣሚ ሆኖ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ላይ ቅሬታቸውን ለማሰማት የሚፈልጉ ሰዎች የተሳሳተ ሐሳብ ያያዙ ናቸው።

እነዚህ ሰዎች መረጃ የላቸውም፣ የተሳሳተ መረጃ ይዘዋል፣ በተሳሳተ መንገድ ተመርተዋል፣ እናም ከዚህ በታች ከተራ ቁጥር 1 – 5 ከቀረቡት ጉዳዮች ጋር አይተዋወቁም ማለት ነው፡

1ኛ) ከአልጀርሱ የስምምነት ሰነድ፣

2ኛ) ከድንበር ኮሚሽኑ ዝርዝር ተግባራት፣

3ኛ) ከተጭበረበሩ ስምምነቶች እና ከሌሎች ሳንክ ካለባቸው ዘገባዎች እና ኮሚሽኑ ከድንበር ማካለል ውሳኔው ላይ ለመድረስ የገመገማቸውን ማስረጃዎች፣

4ኛ) ለኮሚሽኑ ከቀረቡ ተገቢ ያልሆኑ የሕግ ክርክሮች እና ትንተናዎች፣ እና

5ኛ) ግትር ከሆኑ የስነ ስርዓት ሕጎች እና የአስታራቂነት ሂደት።

ከዚህ ቀጥሎ በሚቀርበው ትንተና አሳዛኝ በሆኑት የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ እውነታዎች ላይ ማስገንዘቢያ በማቅረብ እና ትንታኔ በመስጠት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ውሳኔ በአሉታዊ መልኩ የሚመለከቱትን እና በስሜት እና በደም ፍላት የተነሳሱትን ወገኖች ረግብ ያደርጋል የሚል ተስፋ አለኝ።

አስፈላጊዎቹ እውነታዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡

እ.ኤ.አ ታህሳስ 8 ቀን 2000 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የሰላም ስምምነት አዋጅ ቁጥር 225/2000ን አጸደቀ።

እ.ኤ.አ ታህሳስ 12 ቀን 2000 ዓ.ም አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ የአልጀርሱን ስምምነት በተለይም የኤርትራ እና የኢትዮጵያ የድንበር ኮሚሽን ገለልተኛ የሆኑ 5 አባላት የቅኝ ግዛት ስምምነት ውሎችን (እ.ኤ.አ የ1900፣ 1902 እና 1908 ዓ.ምን) መሰረት ያደረገ በዓለም ዓቀፍ ሕግ በአንቀጽ 4 (2) መሰረት የድንበር ማካለል ተግባራትን እንዲሰሩ በግሉ በመስማማት ፈረመ።

የተመድ የካርታ ስራ ባለሞያ (ካርቶግራፈር) የድንበር ማካለል መለያ መስመሮችን እና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮችን ለመስራት ቴክኒካዊ የሆኑ ሞያዎችን ያቀርባል። (አንቀጽ 4(7)

ውዝግብ ያለባቸውን የድንበር ክፍሎች እንዲሁም ሌሎች ተጨማሪ ማስረጃ በቀጥታ በጽሁፍ እና በቃል ለኮሚሽኑ ዘገባ ያቀርባል። አንቀጽ 4(10)

የድንበር ማካለሉን በተመለከተ የድንበር ኮሚሽኑ የመጨረሻ ውሳኔ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አአድ) እና ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ቀርቦ በአስቸኳይ የማካለል ስራው ይሰራል። አንቀጽ 4 (13)

በተለይ የኮሚሽኑ የድንበር ማካለል ምልክት የማድረግ ስራ የመጨረሻ እና ቀያጅ በመሆን ተቀባይነት አለው። (አንቀጽ 4 (15)

ከግጭቱ ጋር በተያያዘ መልኩ ለደረሰው ጥፋት፣ ጉዳት ሁሉም ለሚያቀርቡት የይገባኛል ጥያቄ ኮሚሽኑ በቀያጁ ሕግ የመወሰን ስልጣን አለው። አንቀጽ 5 (1)

በድንበር ኮሚሽኑ ፊት በመቅረብ ኢትዮጵያን የወከሉት ስዩም መስፍን፣ ፍስኃ ይመር እና ሰይፈ ስላሴ ለማ ሲሆኑ ጡረታ በወጡ በአንድ የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ዓለም አቀፍ የሕግ ፕሮፌሰር እና በሁለት አሜሪካውያን እና ሁለት ፈረንሳያውያን የሕግ ቡድን አባላት ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።

የድንበር ኮሚሽኑ በሄግ የሰላም ቤተመንግሥት (Peace Palace) እ.ኤ.አ ከታህሳስ 10 – 21 ቀን 2001 ዓ.ም ጉዳዩን ተሰምቷል። የሁለቱም አገሮች ተወካዮች የሕግ የክርክር ጭብጦቻቸውን እና የትንተና ማስረጃዎቻቸውን ለኮሚሽኑ አቅርበዋል።

ከአራት ወራት በኋላ ማለትም እ.ኤ.አ ሚያዝያ 3 ቀን 2002 ዓ.ም የድንበር ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ እና በኤርረትራ መካከል የድንበር ማካለሉን ስራ በመሬት በመስመር እና በካርታ አስደግፎ በአንድ ድምጽ የወሰነ መሆኑን የታተመ ሰነድ አወጣ። (ውሳኔውን ከገጽ 173 – 179 ያለውን ይመልከቱ)

እ.ኤ.አ ሚያዝያ 14 ቀን 2002 ዓ.ም ስዩም መስፍን እንዲህ በማለት አውጇል፣ “ኢትዮጵያ ሕጉን ታከብራለች። ኢትዮጵያ በውሳኔው እረክታለች። በወታደራዊ ኃይል ወሰኑን በኃይል ለመውሰድ የሚሞክረውን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የዘጋ ውሳኔ እንደሆነ እናምናለን፡፡“ ስዩም እንዲህ በማለት ጨመረ፣ “ሰላም በጠብ አጫሪነት እና በኃይለኝነት ላይ ድልን የተቀዳጀበት ነው። ሕግ በጫካ አገዛዝ ላይ ድልን ተቀዳጅቷል“ ብሏል። ስዩም በይፋ የባድሜ ከተማ ለኢትዮጵያ ተሰጥታለች። የኢትዮጵያውያን ሉዓላዊ ግዛት ዋና መሰረት የሆነችው የባድሜ መንደር ለኤርትራ መንግሥት ተሰጥታለች በማለት የኤርትራ መንግሥት የማደናገር ሙከራ በማድረግ ላይ ነው በማለት ከሷል።

እ.ኤ.አ ሚያዝያ 16 ቀን 2002 ዓ.ም መለስ ዜናዊ የኮሚሽኑን ውሳኔ በመቀበል እንዲህ በማለት ድልን አውጇል፣ “የድንበር ኮሚሽኑ ከመጀመሪያ ጀምሮ ስናራምደው የቆየነውን የእኛን አቋም ደግፏል። በእኔ አስተያያት የእኛ ትልቁ ድል ይኸው ነው“ ነበር ያለው።

ከጥሬ ሀቁ ጋር እንፋጠጥ!

ከድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ውጤት ጋር በተያያዘ መልኩ ማንም ሰው ቢሆን ቅሬታ ለማቅረብ የሚፈለግ ከሆነ ከመለስ ዜናዊ፣ ከስዩም መስፍን፣ ከፍስኃ ይመር እና ከሰይፈ ስላሴ ለማ ውጭ በማንም ላይ ማማተር የለበትም።

ቀያጅ የእርቅ ስምምነት ለማድረግ የተደረገው የመፈጸም ተነሳሽነት ሊለካ የማይችል ግዙፍ የኪሳራ መጠን ነው። መለስ አንድ ጊዜ የአልጀርሱን ስምምነት ከፈረመ በኋላ በሰሜን ወሰን የሚገኙት የባድመ ዕጣ ፈንታ እና የሌሎች ግዛቶች ጉዳዮች በዚያው ተዘጋ። በአልጀርሱ ስምምነት መለስ ኢትዮጵያን በቦክስ በመምታት ልትወጣው ከማትችልበት ችግር ውስጥ እንድትገባ አድርጓል። ቀያጅ የእርቅ ስምምነት ለኢትዮጵያ የዕጣ ፈንታ ጉዳይ ነው። ማንኛውም የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ በሕግ የመጨረሻ እና ሊቀለበስ የማይችል ቀያጅ ነው። ለቀያጅ የእርቅ ስምምነቶች ሌሎች አማራጮች ነበሩ።

መለስ ዜናዊ በቀያጅ የእርቅ ስምምነት ላይ ስምምነት ማድረግ አልነበረበትም። ይህም ማለት በግል የተመረጡ ትንሽ የቡድን ባለሞያዎች እንደ ዳኞች (ኮሚሽን) የሚሰሩ እና ለኢትዮጵያ እጅግ በጣም ጠቃሚ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ይወስናሉ። ማንም ቢሆን የአልጀርሱን ስምምነት እንዲፈርም የሚያስገድድ ጠብመንጃ በጭንቅላቱ ላይ አልደገነም ነበር። “ቀያጅ የእርቅ ስምምነት” ማለት ኢትዮጵያ ወደደችም ጠላችም ያለምንም ጥያቄ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ መቀበል አለባት፣ እናም የባድመ ከተማ ዕጣ ፈንታ በከፍተኛ አደጋ ውስጥ ነበር።

መለስ ቀያጁን ስምምነት በተለይም ኤርትራ የጦር ጠብ አጫሪነት ለመጀመር የመጀመሪያ ሆና ሳለ እና በተደጋጋሚም ከወረረችው ግዛት በኢትዮጵያ ወታደራዊ ኃይሎች ተገፍትራ እየወጣች በነበረችበት ሁኔታ ለመቀበል ግዴታ አልነበረበትም። ከኢትዮጵያ ወታደሮች ድል መቀዳጀት በኋላ መለስ በጠብ አጫሪው አገዛዝ ላይ የተወሰኑ ሁኔታዎችን በቅድመ ሁኔታ በማቅረብ የአሰብን ወደብ መጠየቅን ጨምሮ ከፍተኛ የመራደሪያ አቋም ማቅረብ ይችል ነበር። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቹን ህይወት መስዋዕት ካደረገ በኋላ እና በጦር ሜዳ ውሎ ድል የተቀዳጀ አገር መሪ እንደዚህ ያለውን ታሪካዊ ዕድል በማምከን በቀያጅ የእርቅ ስምምነት ማድረግ ምን ያህል አእምሮን የሚበጠብጥ ነገር ነው!

ከዚህም በላይ መለስ እ.ኤ.አ ሀምሌ 10 ቀን 1900 ዓ.ም በኢጣሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል በነበረው ስምምነት (እ.ኤ.አ ግንቦት 15 ቀን 1902 ዓ.ም በእንግሊዝ፣ በጣሊያን እና በኢትዮጵያ መካከል የተተካው ስምምነት) እና እ.ኤ.አ ግንቦት 16 ቀን 1908 ዓ.ም በኢጣሎ-ኢትዮጵያ መካከል በነበረው ስምምነት መሰረት ለመጨረሻው የድንበር ማካለል እና ምልክት ማደረግ ጉዳይ ለቀያጅ የእርቅ ስምምነት ግዴታ የሚያስገባ ግዳጅ አልነበረበትም።

እነዚህ ስምምነቶች እየተባሉ የሚጠሩት እና እ.ኤ.አ በ1896 ዓ.ም የኢጣሊያን ወራሪ ቅኝ ገዥዎች በወሳኝ መልኩ ድል በመቷቸው የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት በነበሩት በዳግማዊ ምኒሊክ ላይ በግዳጅ ይጫኑ የነበሩት ስምምነቶች መሰረታዊ ችግሮች የነበሩባቸው ስለሆኑ የድንበር ማካለሉ ስራ የስምምነት መሰረት ሊሆኑ አይችሉም።

ለምሳሌም ያህል እ.ኤ.አ በ1908 ዓ.ም የተደረገው ስምምነት የድንበር ወሰኑ ወደ ደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ በመሄድ እና በትይዩ ከድንበሩ ወደ መሀል አገር እስከ 60 ኪ/ሜ ድረስ ገባ እያለ የፈረንሳይ ይዞታ የሆነችውን ሶማሊያ እስከሚገናኝ ድረስ ይዘልቃል። ሁለቱ መንግሥታት ከላይ የተጠቀሰውን ወሰን ለመካለል በጋራ ስምምነት በተቻለ መጠን በአስቸኳይ እንዲካለል እና ምልክት እንዲደረግበት ቃል ገብተዋል። የተካለሉ የድንበር መስመሮችን ሊያመላክቱ የሚችሉ የተመዘገቡ ማስረጃዎች የትም ቦታ አይገኙም። ግን እስከ አሁንም ድረስ የ1908ቱ ስምምነት እንደ ሕጋዊ ሆኖ ለቀያጅ ስምምነት እንዲያገለግል መለስ ተስማማበት።

የእርቅ ስምምነቱ በሚሰማበት ጊዜ የ1908ቱ ስምምነት በስራ ላይ መዋል ስለመቻሉ በመጀመሪያ የተነሳው ጥያቄ ስለድንበሩ ትርጉም ነበር። ኢትዮጵያ ስለድንበሩ ጉዳይ ደሴቶችን ጨምሮ ትታዋለች፣ እናም በተከታታይ አህጉሩን እራሱን በመከተል እንደ ድንበር ከመውሰድ በቀር የደሴቶች ድንበር እንኳ እንደ ድንበር አልተወሰደም ነበር። (የውሳኔውን ገጽ 89 ይመለከቷል።)

ስዩም መስፍን የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ወደ ጎን በመጣል በቸልታ እና አገሪቱን በወንጀል በመጉዳት የድንበር ማካለል እርቅ ሂደቱን ሲመራ ነበር። ድምጽን ከፍ አድርጎ በመጮህ በአምላክ አረንጓዴ ምድር እንደዚህ ያለ ብቃትየለሽ፣ ደንቆሮ እና አቅመቢስ ድሁር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን እንዴት የአገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ሊያስጠብቅ ይችላል!?

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ እንዲህ የሚለውን የጎቴን ምክር የመጨረሻ ዋጋ በመክፈል ላይ ትገኛለች፣ “በተግባር ከድንቁርና በላይ የሚያስፈራ ነገር የለም።“

ስዩም መስፍን እራሱ ኢትዮጵያን በድንበር ኮሚሽኑ ፊት የሚወክሉ የህግ ባለሞያዎችን መወከሉ እና መቅጠሩ ድርብ ጥፋት ማጥፋት ነው። ስዩም መስፍን እራሱ የሕጉን ስልት ይመራል፣ እናም ከመለስ ዜናዊ ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ከኮሚሽኑ ፊት በመቆም በሁሉም የግዛት ጉዳዮች የኢትዮጵያን የሕግ አቋሞች ይወስናሉ።

በቁስል ላይ እንጨት እንዲሉ የኮሚሽኑን ውሳኔ ለመቀበል ስዩም መስፍን እንዲህ ብሏል፣ “ኢትዮጵያ ሕግን ትቀበላለች። ኢትዮጵያ ረክታለች“ ነበር ያለው።

እንባ አውጥቼ አለቅስ እንደሆነ ወይም ደግሞ ጸጉሬን እነጭ እንደሆነ አላውቅም!

ፍስኃ ይመር እና ሰይፈ ስላሴ ለማ በኮሚሽኑ ፊት በሕግ ጉዳዮች ላይ ወሳኝ በሆነ መልኩ በቀጥታ የድጋፍ ሚና በመጫወት ተሳትፈዋል። እነዚህ ሁለት ግለሰቦች ስለተጫወቱት ሚና የሚጠየቁ እንዲህ በማለት እራሳቸውን የሚከላከሉ እንደሚሆን እተነብያለሁ፣ “አማክረናል፣ ከዚያ በተረፈ በመጨረሻው እንድናደርግ የተነገረንን ነው ያደረግን“ ነው የሚሉት።

በመጨረሻም የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔውን ሲያሳልፍ መለስ “ድልን” አወጀ። እሱ ድል ያቀዳጀውን ውሳኔ ለምንድን ነው ተግባራዊ ለማድረግ ያልፈለገው?

ምክንያቱም መለስ በባድሜ የፖለቲካ እግር ኳስ ለመጫወት ፈልጓል። መለስ አስቦበት በባድሜ እና በድንበር ውዝግቡ መካከል የእግር ኳስ በመጫወት ኢትዮጵያውያንን በሽብልቅ ለመከፋፈል እና በመሬት ግዛት ላይ የአርበኝነት ስሜትን ለማጥፋት እና እራሱን በስልጣን ላይ ለማቆየት የህዝብ ስሜትን ለማስቀየስ በመሳሪነት ለመጠቀም ነው።

መለስ የኮሚሽኑን ውሳኔ ለመቀበል ሙሉ ለሙሉ መስማማት በእሳት ላይ ነደጅ መጨመር እና መላ ኢትዮጵያውያን የበለጠ እንዲቆጡ ማድረግ እንደሆነ ተገንዝቧል። ድንበራቸውን ለመጠበቅ ሲሉ በርካታ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ያለቁበትን የእርቅ ስምምነት መሬት በአግባቡ ሳይደራደር ቀርቶ በሌላ አገር ቢወሰድ ከፍተኛ የሆነ ቅሬታ እንደሚቀርብበት ያውቃል። በኢትዮጵያ ሕዝቦች የመጨረሻ የአገር መክዳት እንደሆነ እንደሚታሰብ እና ግንዛቤ እንደሚወሰድበት ፈርቷል። መሬት ለመስጠት የማይደፈር መስሎ በመታየት እና ስምምነቱን ለመቀበል በመቃወም በኢትዮጵያ ሕዝብ ደካማ ጎን ላይ ለመዘፍዘፍ አስቧል። ጦርነትን እንደማስፈራሪያ በማቅረብ እና የሕዝቡን ስሜት በማስቀየስ ጉዳዩ ሰላም የሌለበት እና ጦርነት የሌለበት ሁኔታ ሆኖ እንዲቀጥል አስቧል።

መለስ በየጊዜው የጦርነት ሹክሹክታን በማስወራት እና ከኤርትራ ጋራ ጦርነት እንደሚያደርግ በማስፈራራት የድንበር ኮሚሽኑን ዉሳኔ የስምምነት ጉዳይ ላለመቀበል በኮሚሽኑ ላይ ችግር በመፍጠር ተፈጻሚነት እንዳይኖረው ሲከላከል መቆየትን አስቧል። እ.ኤ.አ ሰኔ 2016 ዓ.ም የቅድመ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አገዛዝ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የመሬት ጠርነት እንደሚካሄድ ሹክሹክታ በማሰማት የጦርነት ነጋሪት መጎሰም ጀመረ። ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ላይ የመለስ የአገር መክዳት እና ማጭበርበር ሁኔታ በአልጀርስ ስምምነት አልተጀመረም ወይም ከፍጻሜ አይደርስም። ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ በኢትዮጵያ ግዛት ላይ ቁማር ሲጫወት ነው የቆየው። የአሰብን ወደብ በመስጠት ኢትዮጵያን ወደብ አልባ አገር እንድትሆን አድርጓል። ከቀያጁ የእርቅ ስምምመነት አኳያ አሰብን መደራደሪያ ለማድረግ ዕድሉን ሲያገኝ ሳይጠቀምበት የተገኘውን ዕድል አምክኗል። መለስ በሚስጥር የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት ኢንቨስተሮች እየተባሉ ለሚጠሩ ለሱዳን በቁራጭ ሳንቲም ሸጧል።

ባድመም ለመለስ ከዚህ የተለየች አይደለችም። እንደሌላው የኢትዮጵያ ግዛት ሁሉ እንደፈለገ መስጠት የሚችልባት ሌላ መሬት ናት። ያም ሆነ ይህ ለመለስ ኢትዮጵያ የሚባል ነገር የለም። ያለው ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች ነው። ኢትይጵያ ምትባል አገር ካለችም መቶ ዓመት አይሞላትም ነበር የሚሉት።

ጅብ ከሄደ ዉሻ ጮኽ እንደሚባለው ምንድን ማድረግ እንዳለብን፣ ምን ማድረግ እንደምንችል እና ምን ማድረግ እንደሚኖርብን ማወቅ ያስፈልጋል። ሆኖም ግን የባድመ ፈረስ ከታሰረበት በረት በመውጣት አምልጦ ሄዷል። ባድመ ከድልድይ ስር ያለ ውኃ ናት። እርሷን በሕግ ጥላ ስር ለማስመለስ ወይም ለመሟገት የሚያስችለን ምንም ዓይነት መሰረት የለንም። ኢትዮጵያ እንደገና ወደ 2000 ዓ.ም በመመለስ የአልጀርሱን ስምምነት ለመቀልበስ አትችልም። አንድ ጊዜ መለስ በአልጀርሱ የድንበር ማካለል ስምምነት ላይ ከፈረመ በኋላ ሁሉም ነገር አልቋል። የባድመ ዕጣ ፈንታ ተዘግቷል። የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ያለምንም ጣጣ ተግባራዊ ይሆናል።

ለአንዳንድ ሰዎች ነገሩን ለመዋጥ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ልንወጣው የማንችለው የአራት ወሮበሎች፡ መለስ ዜናዊ፣ ስዩም መስፍን፣ ፍስኃ ይመር እና ስይፈ ስላሴ ለማ የማታለል የስራ ውጤት ነው። የእነዚህ ሰዎች የስራ ውጤት ነው። የእነርሱ ጣቶች ፊርማዎች በሁሉም ውሳኔ ላይ አሉ። መለስ ዜናዊ፣ ስዩም መስፍን፣ ፍስኃ ይመር እና ሰይፈ ስላሴ ለማ እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 225/2000 ላይ ድምጻቸውን የሰጡት የፓርላማ አባላት ለባድመ መታጣት እና ለማንኛውም ለሌላ የድንበር መካለል ጉዳይ ብቸኛ ተጠያቂ እንደሆኑ ታሪክ መዝግቦ ይይዘዋል።

ስለሆነም እንዲህ የሚለውን የማይታለፍ ጥያቄ መጋፈጥ አለብን፡ በመለስ “ድል” የተባለውን እና በስዩም ደግሞ “አርኪ“ በማለት ተቀባይነት ያገኘውን ውሳኔ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተግባራዊ መደረጉ ችግሩ ምንድን ነው?

የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ ወስነው እየተንቀሳቀሱ ባሉት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ላይ ወቀሳ የሚያቀርቡ ሰዎች ከዓለም አቀፍ ሕግ መማር ይኖርባቸዋል። ለዓለም አቀፍ ቀያጅ የሕግ ስምምነት ሂደት የፈረመ አገር የስምምነቱን ውጤት ሲወድደው ብቻ አይደለም መቀበል ያለበት። ለእራሳችን ካልወሰኑልን በሚል ዓለም አቀፍ ዳኞችን በመጥራት ለማስፈራራት እና ለማሸማቀቅ፣ ለመግደል እና ለማሰር መሞከር አይቻልም። ቀያጅ የሆነ ስምምነት ውሳኔን አልቀበልም ማለት አይቻልም፤ ምክንያቱም ውጤቱን አልቀበልም ካልን በፈላ የፖለቲካ ውኃ ውስጥ ገባን ማለት ነው።

ስዩም መስፍን ሰላም “በጠብ አጫሪነት እና በእብሪት ላይ ድልን ተቀዳጀ” በማለት የመግለጹ ጉዳይ አስገራሚ ነገር ነው። “ሕግ በጫካው አገዛዝ ላይ ድልን ተቀዳጀ” ብሏል። ይኸ እድሜ ልኩን በጫካ ሕግ ውስጥ ከኖረ ሰው የመጣ ልዩ የሆነ መግለጫ ነው።

በመጨረሻም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ላይ የሚጮሁት እንዲህ በማለት እራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው፣ “መለስ በእነርሱ ላይ ዋሽቶባቸዋልን? መለስ ነው ወይስ የመለስ ውሸቶች? ስዩም በእነርሱ ላይ ዋሽቶባቸዋልን? TPLF በሚለው ቃል በስተመጨረሻ ያሉት ሁለት ፊደሎች ማለትም ‘LF’ “Lie Factory”/የውሸት ፋብሪካ ለሚለው ሀረግ የቆሙ ናቸውን?“

የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን
የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን አከላለል ካርታ

በአዞ እንባ አንቢው አርበኛ ስዩም መስፍን ላይ ተጨማሪ ታሪክ፣

ባለፈው ሳምንት በባድመ ላይ የአገር ክህደት ወንጀል የፈጸመው ያው አንድ ዓይነቱ ሰው ስዩም መስፍን እራሱን ከፍ ከፍ እያደረገ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንዴት መንግሥትን እያቆሸሹ እንዳለ እና በትግራይ ሕዝብ ላይ የስነ ልቦና ጦርነት እያደረጉ እንደሆነ በማለት የውስጡን ተንፍሷል። ስዩም መስፍን እንዲህ ብሏል፡

“ከመከላከያ ኃይሉ 14% የሚሆነው ከትግራይ ነው። ይህም ማለት በትግራይ የተወለዱት ብዛት እና በመከላከያ ኃይሉ ውስጥ ያሉት ናቸው። ከመቶው 14% ብቻ። ምክንያቱም ሳሞራ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም በመሆኑ ብቻ የህወሀት ወታደር ወይም የወያኔ ወታደር እየተባለ ይጠራል። እውነታው ይህ ነውን? የኢትዮጵያ ሕዝብ እምነት ይህ ነውን? በፍጹም አይደለም።

የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች አግዓዚ ጦር እየተባለ በሚጠራው ኃይል ይወከላሉን? ይኸ ከብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች የወጣ ወታደር፣ ተቋም ነው። እያንዳንዱ ሰው እራሱን በመስታወት ማየት እንደሚችለው የእራሱ ምስል ማለት ነው። የብዝሀነት ባህሪ ከሚታይበት ሕዝብ መካከል እራሱን የሚያንጸባርቅ ብቸኛ ተቋም ነው። ያንን ተቋም ነው እያቆሸሹት ያሉት። የደህንነቱን ተቋም እያቆሸሹ ያሉት ለምንድን ነው? እነርሱን ዒላማ ያደረጉት ለምንድን ነው? እነዚህ ተቋሞች የሚወድሙ ከሆነ መንግሥቱም ይወድማል። እነዚህ ተቋማት የሚወድሙ ከሆነ ሕገ መንግሥቱም ይወድማል። እንደሚመኙት ሁሉ እነዚህ ተቋማት ቢወድሙ በፍርስራሻቸው ላይ በመቆም ይደንሳሉ። ዓላማቸው ያ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን በማወቅ አጥብቀው መታገል አለባቸው። የትግራይ ሕዝብ እየተደረገ ያለውን የስነ ልቦና ጦርነት ለመመከት በመጀመሪያው ረድፍ ላይ በመቆም ላይ ነው። በትግሉ ውስጥ በመጀመሪያው ረደፍ ላይ መሆናቸውን ማወቅ አለባቸው። ያለኝ ሐሳብ ይኸው ነው“ (አጽንኦ ተጨምሯል።)

ይኸው ስዩም መስፍን በአሁኑ ጊዜ የፈጠራ የስነ ልቦና ጦርነት ተከፍቶብሀል በማለት የትግራይ ሕዝብ ጦርነቱን እንዲከላከል ጥሪ በማቅረብ ላይ ሲሆን በየካቲት ወር ደግሞ የፈጠራ የዘር ማጥፋት ፍጅት እንደሚፈጸምባቸው እና ይህንን መከላከል እንዲችል ለትግራይ ሕዝብ ጥሪ በማቅረብ 27 ዓመታት በስልጣን ኮርቻ ላይ ተቀምጦ ከቆየ በኋላ ከፍ ያለ የሀዘን ድምጹን በማሰማት ላይ ይገኛል። (የትግራይን ሕዝብ ለማስታጠቅ ከስዩም መስፍን ለቀረበ ጥሪ ምላሽ የሚለውን ይመልከቱ)

ለእኔ ግልጽ የሆነው እውነታ ስዩም መስፍን እራሱ መንግሥቱን እና ሕገ መንግሥቱን እያቆሸሸ በማለት የእራሱን የስነ ልቦና ጦርነት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ላይ ጥላሸት የመቀባት ስራ እየሰራ መሆኑ ነው። ስዩም መስፍን የእርስ በእርስ ጦርነት በማካሄድ በትግራይ ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ይፈጸማል በማለት በማስፈራራት፣ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ይደረጋል (መንግሥት ይገለበጣል እናም ስዩም እና የእርሱ ወሮበላ ጓደኞች ከዚህ አደጋ ይጠብቃሉ) እናም የትግራይ ሬፐብሊክ በማለት ትገነጠላለች እያለ የስነ ልቦና ጦርነት በማካሄድ ላይ ያለው እራሱ ነው።

ደህና ስዩም ሞክር፣ ሆኖም ግን የአንተን ፍርሀት እና ስም የማጠልሸት ስልት ማንም ከቁብ የሚቆጥረው የለም።

ስዩም መስፍን የስነ ልቦና ጦርነት እያለ የሚያምነው በአገር ውስጥ የኢትዮጵያውያንን እና በውጭ የዲያስፖራውን ልብ እና አእምሮ ለመማረክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እያደረጉት ያለውን ተጋድሎ መሆኑን ማስተዋል ተገቢ ነው። ስዩም ሁኔታውን በግልጽ ማውጣት አልቻለም ወይም ደግሞ በቅንት መረጃውን ለመስጠት አልፈለገም። ሆኖም ግን እኔ በእራሴ ምልከታ መዶሻ የያዘ ሁሉም ነገር ምስማር መስሎ ይታየዋል የሚለውን የዱሮ አባባል በመውሰድ መምደም እችላለሁ።

ጦርነትን ብቻ ለሚያውቀው ለስዩም ልብን እና አእምሮን ለመማረክ የሚደረግ ጦርነት ለእርሱ በእርግጠኝነት የስነ ልቦና ጦርነት መስሎ ይታየዋል።

ስዩም የእራሱን የስነ ልቦና ጦርነት ጨዋታዎች መጫወት መብቱ ነው። ሆኖም ግን ለበርካታ ጊዜ ደጋግሜ እንደተናገርኩት ለስዩም እና ለወሮበላ ጓደኞቹ ከዚህ በኋላ ጨዋታው ተጠናቋል!

ለድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ስምምነት አማራጩ ምንድን ነው?

የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ስምምነት ላለመተግበር ብቸኛው አማራጭ ጦርነት እና የበለጠ ጦርነት ማካሄድ ነው። እ.ኤ.አ ከ1998 እስከ 2000 ዓም ደረስ በተካሄደው የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ግጭት ከ70,000 እስከ 120,000 የሚገመቱ ወታደሮች እና ሲቪል ሕዝቦች ሞተዋል። ያ በቂ ሞት እና ውድመት ነው። ከዚህ በኋላ ሞት አይኖርም። ከዚህ በኋላ ጦርነት አይኖርም። ጦርነት ተሞክሮ ወድቋል።

እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም መለስ ዜናዊ የኤርትራን ሕዝቦች ህይወት ለማሳለጥ እና አምባገነኑን አገዛዝ ለማስወገድ እንዲህ በማለት አስፈራርቷል፡

“በቅርቡ አልሻባብን እና አገር በቀል የሆኑ አውዳሚ ኃይሎችን በማሰልጠን እና ለግዳጅ በማሰማራት አገራችንን ለማሸበር ኤርትራ በትጋት በመስራት ላይ ትገኛለች። ሆኖም ግን ግብጽ ከእነዚህ የጥፋት ኃይሎች ከሚደግፉት በግንባር ቀደምትነት ትገኛለች። እስከ አሁን ድረስ የእኛ ስልት ልማታችንን በማፋጠን ሉዓላዊነታችንን መከላከል ነበር። አሁን ግን በዚህ ዓይነት ጠንካራ ባልሆነ የመከላከል ስልት የትም አንደርስምእንደዚህ ያለ ደካማ የመከላክል ስልት እንደ ብቸኛ አማራጭ ሊወሰድ አይችልም። ስለሆነም የኤርትራን ሕዝብ አምባገነናዊ እገዛዝ ለማስወገድ የሚደረገውን ሂደት ማፋጠን አለብን። በአገራቸው ውስጥ ዘለን የመግባት ዓላማ የለንም። ሆኖም ግን እዚያ የሚደረገውን ተጽዕኖ ከፍ ማድረግ አለብን። የኤርትራ መንግሥት እኛን ለማጥቃት የሚሞክር ከሆነ እኛም ተመጣጣኝ ምላሽ እንሰጣለን“ (አጽንኦ ተጨምሯል።)

መለስ በኤርትራ የመንግሥት ለውጥ አንዲደረግ አቅዶ ነበር። ሆኖም ግን የዕጣ ፈንታ ኃይል የተለየ ሌላ ውጤትን አስከተለ።

እ.ኤ.አ ከ2006 ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ የመለስ ዜናዊ የሶማሊያ ወረራ በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ሶማሊያውያን ህልፈት እና ለበርካታዎቹ መፈናቀል ምክንያት ሆነ::

በመለስ የሶማሌ ጦርነት ስንት ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ሞቱ?

እ.ኤ.አ በ2009 ዓ.ም መለስ ዜናዊ በፓርላማው ፊት ቀርቦ በሶማሌ ስንት ወታደሮች እንደሞቱ ማወቁ አስፈላጊ አይደለም ብሏል።

በድንበር ጦርነቱ ተሳትፈው ስንት ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ወደ አገራቸው ተመለሱ? በኢትዮጵያ የኤርትራ የጦር እስረኞች ሁሉም ተለቀው ወደ አገራቸው ሄደዋል። ሆኖም ግን ስንት የኢትዮጵያ የጦር እስረኞች ተፈትተው ወደ አገራቸው ገቡ?

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ጦርነት ጊዜው አይደለም። አሁን ጊዜው ሁለቱም አገሮች ጎራዴዎቻቸውን ወደ ማረሻነት እንዲሁም ጦሮቻቸውን ወደ አበባ መቁረጫነት የሚለውጡበት ጊዜ ነው። አንዱ አገር በሌላው ላይ ጎራዴ አይመዝም። ከዚህ በኋላ ማናቸውም ጦርነትን አያካሂዱም።

አጥብቆ በመዘለፍ የሚተቹት የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔቪል ቻምበርሊን በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፣ “በጦርነት የትኛውም ወገን ቢሆን እራሱን አሸናፊ ነኝ ሊል ይችላል። በሁሉም በኩል አሸናፊዎች የሉም። ሆኖም ግን ሁሉም ተሸናፊዎች ናቸው።“

በሌላ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ማን ነው ተሸናፊ የሚሆነው?

የቀድሞው የአፍሪካ አርታኢ፣ የቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ጋዜጠኛ የሆነው ማርቲን ፕላውት በእንግዳ አምድ ድረ ገጼ እ.ኤ.አ መስከረም 2017 ዓ.ም “ትርጉም በሌለው የድንበር ጦርነት በርካቶች በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸውን አጥተዋል” በማለት ጽፏል። ተስፋ በመቁረጥ ፕላውት እንዲህ በማለት ተመልክቷል፡

“ ግዛቶች ይፈረካከሳሉ፣ ገዥዎች ይወድቃሉ፣ ነገስታት ወደ አፈር ትቢያነት ይቀየራሉ። እናም በእኔ አመለካከት የኢትዮጵያን እና የኤርትራን ሕዝቦች የሚለይ ነገር በጣም ትንሽ ነገር ነው። በእርግጥ ብዙ አንድ የሚያድርጓቸው ነገሮች አሉ። ጥልቅ መግባባት አላቸው። አስደናቂ የጋራ የሆነ ቅርስ እና ባህል አላቸው። እንደዚሁም ሁሉ እድገትን የሚያጓትቱ እና ስኬትን የሚያጨልሙ አሉታዊ ባህሪያት ማለትም፡ ግትር አቋም፣ ያለመለሳለስ እና ሚስጥራዊነት ባህሪያት አሏቸው“ ብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሮጌውን የግትር አቋም፣ ያለመለሳለስ፣ ሚስጥራዊነት፣ ፍርሀት እና ጥላቻ ባህል በመስበር በአዲስ ዘመን አስተሳሰብ እና በግልጽ ዴፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለሰላም፣ ለእርቅ እና ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ ሕዝቦች የጋራ ጥቅም መከበር እውነተኛ አቋም በማራመድ አንድነትን እየገነቡ ነው።

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በግትር አቋም፣ ባለመለሳለስ፣ በሚስጥራዊነት እና ዋስትና በሌላቸው መሪዎች የተለያዩ ሕዝቦች ናቸው። ኢትዮጵያ በእውነት ምንም ዓይነት ስግብግብነት በሌለው፣ ክፍት አእምሮ፣ ወደፊት አሳቢ፣ ደፋር፣ ምክንያታዊ፣ ሀሳባዊ፣ ትጉህ እና ብልህ ወጣት መሪ ታድላለች። በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ አንድ አገር እንደሚሆኑ እተነብያለሁ። ሌላው ሁለቱም ዴሞክራሲያዊ አገሮች ሲሆኑ ነው። ይህ ለወደፊቱ የተተነበየ ነው!

ስለዝሆኖች ጦርነት እና ስለሳር ጉዳይ እንዲህ የሚል የቀድሞ አባባል አለ፣ “ዝሆኖች ሲገጥሙ የሚጎዳው ሳሩ ነው።“ በአሁኑ ጊዜ ሳሩ ማለትም ሕዝቡ በዝሆኖች በሚደረገው ፍልሚያ አሸናፊ ሆኖ ወጥቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከማንዴላ የጨዋታ መጽሐፍ ውስጥ አንድ ገጽ ወስደዋል፣

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ ሲወስኑ ከማንዴላ የጨዋታ መጽሐፍ ውስጥ አንድ ገጽ ወስደዋል። ማንዴላ እንዲህ ብለዋል፣ “ከጠላትህ ጋር ሰላም ለማውረድ ከፈለግህ ከጠላትህ ጋር አብረህ መስራት አለብህ። ከዚያም በኋላ አጋርህ ይሆናል።“

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጠላት የሚለውን ቃል ለመጠቀም እንደማይወዱ አውቃለሁ። ሆኖም ግን እዚህ በተመሳስሎ እጠቀምበታለሁ።

የማንዴላ ትርጉም ያለው ምክር የወጣው ማንዴላ በደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው የጥቂት ነጮች የበላይነት ዘረኛ አገዛዝ ከአፓርታድ ጋር ለረዥም እና ጠንካራ ትግል ካደረጉ በኋላ ነው። ሰላምን እና ፍትህን ለማምጣት እና እርቀ ሰላም ለማውረድ ከአፓርታይድ ጠላቶች ጋር እርቀ ሰላም ማውረድ አስፈላጊ እንደሆነ ግንዛቤ ወስደዋል። አሮጌው ዓይነት የጥላቻ፣ የበቀልተኝነት እና ዓይን ላወጣ ዓይን ማውጣት እያልን ከሄድን ደቡብ አፍሪካ በሙሉ የዓይነ ስውራን አገር ይሆናል ነበር ያሉት። ደቡብ አፍሪካን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ለማሸጋገር እመርታን የሚያሳይ የአስተሳሰብ እና የአመለካከት ለውጥ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ አውቀዋል። ጠላታቸውን ለማሸነፍ ከጦርነት እና ከወታደራዊ ኃይል ይልቅ የስምምነት ስልት መጠቀምን ወስነዋል።

ከጠላት ጋር መስራት በማታለል እና የግል ጥቅምን ለማግኘት ሊሆን አይገባም። በሁለቱም ወገን በእውነት፣ በቅንነት፣ በመፈጸም ብቃት እና በአመለካከት መልካምነት መሰረት ሲሰራ ነው። ያለፈውን ስህተት የማይደግም እና በእራስ መተማመን ስሜት እና እራሳቸውን እርስ በእርሳቸው የሚተጋገዙትን አምላክ ያግዛቸዋል በሚል እምነት የሚመራ እና ካለፈው ስህተት ሊማር የሚችል አመራር ሲኖር ነው።

ከጠላት ጋር መስራት ከሰላም እና ጦርነት ያለመኖር ዝግ ድባብ ውስጥ ነጻ ሊያወጣ የሚችል ብቸኛው መንገድ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጓዳዊነት፣ ሰላም እና እርቅ መንፈስ ጦርነትን ያስወግዳሉ፣

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ ጦርነቱን ያስቆመውን የሰላም ስምምነት በመቀበል ተግባራዊ ታደርጋለች ብለዋል። ውሳኔውን ለመቀበል ያቀረቧቸው ምክንያቶች እርሳቸው የሰላም ሰው ብቻ ሳይሆኑ ጥልቀት ያለው ልዩ የሆነ የስልታዊ አስተሳሰብ ሰው መሆናቸውንም ያመላክታል። ጎረቤት አገሮች የተሰበሩ ልዩነታቸውን ለመመለስ የሚችሉ ከሆነ ብቻ በሰላም ለመኖር ይችላሉ። የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀብለው ተግባራዊ ለማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንዲህ ብለዋል:

“አሳዛኝ የሆነ አወዛጋቢ ጉዳይ ለብዙ ጊዜ ተሸክመን የቆየነው እና ትላንት እልባት ያገኘው ከኤርትራ ጋር ያለን ግንኙነት ነው። የፖለቲካ ምሁራን በአሁኑ ጊዜ ከኤርትራ ጋር ለ20 ዓመታት ያህል የቆየውን ግንኙነት በሶስት የቢሆን መላምቶች ይገልጹታል። እነርሱም አንደኛ በጠርነት ውስጥ ያለን እና በጦርነት ሆነን የቆየንበት ሁኔታ እንደሆነ። ሁለተኛው አማራጭ ጦርነት የሌለበት፣ ሰላም የሌለበት ሁኔታ እንደሆነ ይቆጥሩታል። ይህም ማለት ቀሪው ዓለም በአሁኑ ጊዜ እኛን ፈርጆ ያለበት ሁኔታ ነው። እኔ በዚህ ትንታኔ አልስማማም። እንደዚህ ያለ ጦርነት የሌለበት ሰላም የሌለበት የሚባል ነገር የለም። ቁስለኛ የሌለበት ጦርነት በማለት እጠራዋለሁ። በርካታ የሞቱ ሰዎች ላይኖሩ ይችላሉ። ሆኖም ግን እውነታው የጦርነት ሸክሙ ሁሉንም የገንዝብ፣ የጭንቀት እና የስልጠና ወጭ የመሳሰሉትን ይዞ በድንበሩ ላይ ይዘልቃል። ወታደሮች ለማሸነፍ ወይም ለመሸነፍ ለአንድ ወይም ደግሞ ለሁለት ሰዓት ያህል ይዋጋሉ። ሆኖም ግን ለጦርነት ዝግጅት፣ ጥቃት የመተንበይ እና የስነ ልቦናው ጭንቀት ለዋናው ጦርነት ከመዘጋጀት እና ጥቃት ከመሰንዘር አያንስም። ላለፉት 20 ዓመታት ወታደሮቻችን በበረሀ እና በጉድጓድ እየተሰቃዩ ወይ የመዋጋት ዕድል አላገኙም ወይም ደግሞ ሰላም አልተቀዳጁም። ቀጣይነት ባለው ጭንቀት ውስጥ ይኖራሉ። አሁን ያለን ሁኔታ ጦርነት የሌለበት እና አልፎ አልፎ ሰው የሚሞትበት ሰላም የሌለበት ሁኔታ ነው።

ይህንን ጦርነት የሌለበት፣ ሰላም የሌለበት ሁኔታ ማስቆም አስፈላጊነቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይይሆን በአጠቃላይ ለአፍሪካ ቀንድ ጭምር ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ትልቅ እና የትልቅ ሕዝብ አገር ናት።

በአፍሪካ ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ናት። እናም በአስመራ እና በአዲስ አበባ መካከል ሰላምን ለማረጋገጥ ኃላፊነት የሚሰማው የመንግሥት ኃላፊነነት ነው። የአውቶብስ እና የባቡር አገልግሎት ይኖራል፣ እናም የኢኮኖሚ ግንኙነቶቻችን ይጠናከራሉ። የእነዚህን ወንድማማች ሕዝቦች ግንኙነት ለማጠናከር ተነሳሽነቱን በመውሰድ እንሰራለን። ሁሉም ኢትዮጵያውያን ይህንን ማወቅ አለባቸው….. “ ነበር ያሉት።

ማንዴላ ትልቁ ህልማቸው ሠላሟ የተረጋገጠ አፍሪካን ማየት እንደሆነ ተናግረዋል።

እ.ኤ.አ ሀምሌ 2012 “ሰላሟ የጠረጋገጠ ኢትዮጵያን ማለም” በሚል ርዕስ ጽፌ ነበር። ዛሬ በዓይኖቼ ሰላምን አያለሁ፣ በጆሮዎቼ ሰላምን እሰማለሁ፣ በልቤ አስተውላለሁ፣ በአእምሮየ አሰላስላለሁ። እንዲህ በማለት እጸልያለሁ፣ “ሰላም ለኢትዮጵያ ይሁን።“

በእኔ የልጅነት ዘመን ወጣት በነበርኩበት ጊዜ እና ሙሉ ተስፋ በነበረኝ ጊዜ የጆን ሌኖንን የሙዚቃ ቅላጼ “ሁላችንም እያልን ያለነው ለሰላም ዕድል ስጥ“ እያልን እንዘምር ነበር። ከሌኖን ጋር እንዲህ በማለት እናልም ነበር፣

ሰላምን መያዝ ነው ልቦናን አስፍቶ፣

ከጥላቻ ወጥመድ ምንድን ሊገኝ ከቶ፣

ከበቀል መርዝነት ፍቅርን ለይቶ፣

በሰው ልቦች ሁሉ እንዲተኛ ገብቶ፣

አጥብቆ በመያዝ ማስተማር ነው ተግቶ።

 

እኔ አላሚ ሰው ነኝ ልትል ትችላለህ፣

ሌት ቀን በመጸለይ ትፍገመገማለህ፣

ግብህን ለመምታት ትፍጨረጨራለህ፣

የሠላሙ ዳኛ መሆንን ትሻለህ፣

የፍቅር አማልክት መሆን ታስባለህ።

 

ዓላማህ ቆንጆ ነው እጅግ የሚስማማ፣

ለሰው ልጆች መድህን ስራ ሳታቅማማ።

 

እኔ በወጥመዱ በሳቱ ገብቼ፣

ለውጥን ለማሳለጥ ዋትቼ ዋትቼ፣

ለሕዝቤ ፍቅርን ሰላምን ገንብቼ፣

እሰናበታለሁ አሻራ ሰጥቼ፣

ፍትህ እኩልነት ሰላምን አምጥቼ።

 

እኔ ብቻ አይደለሁ የምታገለው፣

ሌላውም ይመጣል ፍትህ የከዳው፣

ባርነት ጸንቶበት ሰላም የሌለው።

 

አንተም እንደዚሁ ባላማ ጸንተህ፣

ለሰው ልጆች ሰላም ቃልኪዳን ገብተህ፣

በህሊናህ ፍቅር ምሰሶ ሰርተህ፣

ትቀላቀላለህ አንድ ቀን መጥተህ።

 

ዓለም በአገሮች ተከፍላ ተከፍላ፣

ወደመንደርነት ሄዳ ወደ ኋላ፣

መኖር እንደማትችል አስቀምጣ መላ፣

አንድ ትሆናለች የኋላ የኋላ ።

በሹመት በዓላቸው ዕለት ኔልሰን ማንዴላ እንዲህ ብለዋል፣ “በፍጹም በፍጹም በፍጹም ይህች ቆንጆ አገር ከእንግዲህ አንዱ በሌላው የምትጨቆንባት አትሆንምለቆንጆዋ ደቡብ አፍሪካ ህልም ካለ ወደ ዓላማቸው የሚወስዱ መንገዶችም አሉ። ከእነዚህ መንገዶች ሁለቱ መልካም ነገር እና ይቅርባይነት በመባል ሊጠሩ ይችላሉ።“

ወጣት ዐቢይ አሕመድን እና እኔን በወርቃማው የአዛዉንት ዘመኔ አላሚዎች ናችሁ ልትሉን ትችላላችሁ። ሆኖም ግን ሁላችንም እያልን ያለነው ለኢትዮጵያ ሠላሟን ስጧት እናም መልካም ነገር እና ይቅርባይነት በሚባሉ ሁለት መንገዶች ላይ በመጓዝ በመጨረሻ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ወደምትባለው በተራራው ጫፍ ላይ ወደምትገኘው አንጸባራቂ ከተማ እንደርሳለን።

ሁላችሁም ወደ አዲሲቷ ኢትዮጵያ እንኳን በደህና መጣችሁ። ጠላቶች የሉም፡ ሁላችሁም ልታቀርቡት የምትችሉት ነገር ቢኖር የእናንተን የሰው መሆን ገላጩን የይለፍ ወረቀት ብቻ ነው። ሌላውን ነገር ተውት።

ስለሆነም በምትችሉት በማንኛውም መንገድ በመምጣት ተቀላቀሉን። ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዳሉት “መብረር ካልቻልክ ሩጥ፣ መሮጥ ካልቻልክ ተራመድ፣ መራመድ ካልቻልክ ተንፏቀቅ። ሆኖም ግን በማንኛውም ጊዜ መንቀሳቀስህን እንዳታቆም” ነበር ያሉት።

ይምጡ እና ይምሩን ወይም ደግሞ ከኋላ ይከተሉን። መምራት ወይም ከኋላ መከተል ካልቻሉ መልካም ነገር እና ይቅርባይነት እየተባሉ ከሚጠሩት መንገዶች ይውጡ!

//

ተጨማሪ ጽሁፍ፣

“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እባክዎት እባክዎት ወደ ዩኤስ ይምጡ እና የእኛ እንግዳ ይሁኑ” በሚል ርዕስ ማስታዋሻ ቁጥር 8ን በመጻፍ እንዲመጡ ጥያቄ ካቀረብኩ በኋላ ብዙ ጥያቄዎች ደርሰዉኛል::

የነበረኝን ድምጸቴን ፍጹም በሆነ መልኩ በአንድ ጀንበር እርግፍ አድርጌ በመተው የኢህአዴግ አገዛዝ መሪ የሆኑትን ጠንካራ ደጋፊ ለምን እንደሆንኩ ተጠይቂያለሁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ስልጣን ከመያዛቸው በፊት አውቃቸው ነበር ወይ? ጓደኝነት ነበርኝን? ለበርካታ ዓመታት ለመለስ ዜናዊ አንዲትም ቀን አዎንታዊ አድናቆት ሳልሰጠው ስጽፍ የኖርኩ እና አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገና ስልጣን ከያዙበት ቀን ጀምሬ እየደገፍኩ ያለሁት ለምንድን ነው? ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ዩኤስ የሚመጡት መቸ ነው?

አንደኛ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በማንኛውም ጊዜ ወይም ቦታ ተገናኝቼ ወይም ተነጋግሬ አላውቅም። ሆኖም ግን ለበርከታ ዓመታት እንደማውቃቸው ያህል ይሰማኛል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዩቱቢ ንግግር ሲያደርጉ በምንመለከትበት ጊዜ የእኔ ሐሳብ በስፋት ሲተላለፍ እየተመለከትኩ ስለነበር በግለሰብ ደረጃ እኔን እና እርሳቸውን አያይዞናል የሚል እምነት አለኝ። ምናልባትም ላለፉት 13 ዓመታት ገደማ ያህል ሁልጊዜ ሰኞ በቋሚነት ትችት ሳቀርብ የቆየሁ በመሆኔ ስለእኔ ሊያውቁ ይችሉ ይሆናል።

በእርግጥ ቶሎ ይሆናል ብየ ስለማስበው እና ወደ ዩናይትድ ሴትስ ሲመጡ ከእርሳቸው ጋር ለመገናኘት በጣም ጉጉ ነኝ ምክንያቱም በርካታዎቹ የእርሳቸው ደጋፊዎች የእርሳቸውን ጉብኝት እርግጠኛ ቀን መቸ እንደሆነ ይጠይቁኛል። እንዲያውም ጥቂቶች ለማወቅ ይፈልጋሉ ስለሆነም የአየር ቲኬት በማዘጋጀት እርሳቸውን ለማየት እና ዩኤስ ከደረሱ በኋላ የሚያደርጉትን ንግግር ለማዳመጥ ስለሚፈልጉ ነው።

እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዩኤስ አሜሪካንን መቸ እንደሚጎበኙ ምንም ዓይነት መረጃ የለኝም። የመጨረሻ ዝግጅት ከተደረገ በኋላ ይፋ የሆነ መግለጫ ይሰጣል ብየ አምናለሁ።

አንድ የቆየ አባባል እንዲህ ይላል፣ “መቅረት ልብ የበለጠ እንዲናፍቅ ያደርጋል፡፡“ በአጠቃላይ ስለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማለት የምፈልገው ነገር በአሜሪካ ውስጥ የሚገኙት በርካታ የእርሳቸው ደጋፊዎች በየዕለቱ ናፍቆታቸው እየጨመረ ሄዷል!

ሁለተኛ ስለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የእኔ ደጋፊነት እና ተከራካሪነት ቀደም በማለት በትዕግስት በመጠበቅ ላለፉት 13 ዓመታት እንደ ዐቢይ አሕመድ ያለ ወጣት መሪ ከጨለማው የጨቋኝ አገዛዝ እንዲወጣ እና 13 ወራት የጸሐይ ብርሀን ባላት ምድር ላይ እውን እንዲሆን እፈልግ ስለነበረ ነው።

ማቋረጫ በሌለው መልኩ የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው (ወጣቱ) ትውልድ ኢትዮጵያን ያድናታል ስል በፊቴ ይስቁብኝ ነበር። እኔ የዋህ እና ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የተነጠልኩ እንደሆንኩ ይናገሩ ነበር። ምክንያቱም ለበርካታ ዓመታት እዚያ ስላልነበርኩ ነው። የኢትዮጵያን ወጣት እንደማላውቀው ይናገሩ ነበር። የኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ ገንዘብ በማሳደድ እና ቶሎ ወደ ሌላ አቅጣጫ ዘወር በማለት ባህል ውስጥ ተጠምዶ ይገኛል። ስለጠፋ ትውልድ ጊዜዬን እያባከንኩ እንደሆነ አድርገው ያስቡ ነበር።

ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ወጣት ላይ እምነት አላጣም ወይም ደግሞ ኢትዮጵያን ነጸ እንደሚያወጧት እምነቴን አላጣሁም። በፍጹም። እ.ኤ.አ መስከረም 2016 ዓ.ም አድርጌው በነበረው ቃለመጠይቅ ስለኢትዮጵያ ወጣት የማስበው የነበረውን በትክክል ገልጫለሁ። ከዚያም ባለፈ እንዲህ የሚል መፈክር አውጥቻለሁ፣ “የኢትዮጵያ ወጣቶች ከተባበራችሁ በምንም አነት አትሸነፉም።“

በመጨረሻም ትክክለኛ መሆኔን አረጋገጥኩ። የኢትዮጵያ ወጣት ድል አድራጊ እና አሸናፊ እየሆነ መጥቷል። እናም የእነርሱን መሪ ዐቢይ አሕመድን በማየቴ ታድያለሁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቅን አስተሳሰብ፣ መልካም እምነት፣ ጥሩ ልብ እና ልዩ ምሁራዊነት ያላቸው መሆናቸውን አምናለሁ። ከመልካም መሰረት የመጡ የሕዝብ ልጅ ናቸው። በአገሪቱ ውስጥ ትልቁን የስልጣን ቦታ የያዙ መልካም ስብዕና ያላቸው ሰው ናቸው። ለሚያምኑበት የፖለቲካ እና የሞራል እምነት ወሳኝ፣ ደፋር፣ እና እውነተኛ ሰው ናቸው። አአምሯቸው ክፍት ነው። እናም በማንኛውም ጊዜ ጓደኞቻቸውን እና ጠላቶቻቸውን በሰለጠነ ውይይት እንዲሳተፉ ፈቃደኛ ናቸው። ከመናገራቸው በፊት ያዳምጣሉ፣ እናም በምንም ዓይነት መንገድ በመንታ ምላስ አይናገሩም። የሚያደርጉትን ይናገራሉ፣ የሚናገሩትን ያደርጋሉ። ሁሉንም ልዩነቶች ለመፍታት የእርሳቸውን ቅንነት የተሞላበት የሰላም፣ የእርቅ እና የውይይት መልዕክት እወዳቸዋለሁ። በሕግ የበላይነት፣ በሰብአዊ መብት መከበር፣ በመልካም አስተዳደር እና በተጠያቂነት ላይ ያሏትን የእርሳቸውን አዲሲቷን ኢትዮጵያ ርዕይ እጋራለሁ።

ከሁሉም የበለጠ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንደኔ በአንድ ዋና ነገር በኢትዮጵያዊነት ላይ እንደሚያምኑ አምናለሁ!

ከ10 ሳምንታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለ27 ዓመታት በተለያዩ ጎራዎች ተበታትነው የነበሩትን ኢትዮጵያውያን ወደ አንድ በማምጣት ወንድማማቾች እና እህትማማቾች እንዲሆኑ አድርገዋል።

ስለቅድመ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አገዛዝ ቀደም ሲል በተደጋጋሚ ለበርካታ ጊዜ ስናገረው እንደቆየሁት ከመለስ ዜናዊ ወይም ከህወሀት አመራር ጋር የሆነ ግላዊ ግንኙነት የለኝም። በእርግጥ እነርሱ በሕግ የበላይነት፣ ሰብአዊ መብትን በማክበር የመከፋፈል እና የጥላቻ ፖለቲካ ስራቸውን በመተው ቢሰሩ ቁጥር አንድ ደጋፊያቸው እንደምሆን በተለያዩ አጋጣሚዎች ተናግሪያለሁ።

እ.ኤ.አ ጥር 2014 አቅርቤው በነበረው ትችቴ እንዲህ በሚለው የጋንዲ አስተሳሰብ እንደምኖር ግልጽ አድርጊያለሁ፡ “ኃጢያትን ጥላ እንጅ ኃጢያተኛውን አትጥላ።“ ጠይዎችን የምንጠላቸው ከሆነ የእነርሱ የመስታወት ግልባጭ እንደምንሆን አምናለሁ። የምንጠላውን ነው የምንሆነው። እንደ ሰብአዊ ፍጡር መለስን እና የእራሱን ጓደኞች የምንጠላቸው ከሆነ እነርሱን ሆንን ማለት ነው። መጥላት ካለብን መጥላት ያለብን ድርጊታውን እንጅ የእነርሱን ሰውነት አይደለም።

እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ በአሜሪካ የሲቪል መብቶች ንቅናቄ ይታገሉ ለነበሩት የነጻነት ታጋይ ሕዝቦች የማርቲን ሉተር ኪንግ አስተምህሮ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ላለው ሁኔታ ተስማሚ ነው። ለሰብአዊ መብት እና ለፍትህ በሚደረገው ትግል ጥቁሮች ጨካኞች እና የጥላቻ ዘመቻ አራጋቢዎች ከሆኑ ይሳሳታሉ። በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉት ጥቁሮች የተወደደውን ማህበረሰብ ለመመስረት ይፈልጋሉ። ሰላማዊ ትግሉ በግለሰቦች ላይ ሳይሆን በጭራቃዊነት ኃይሎች ላይ እንዲደረግ መራው። ውጥረቶች የነበሩት በጎሳዎች መካከል አልነበረም። ሆኖም ግን ውጥረቶች የነበሩት በፍትህ እና በኢፍትሀዊነት ኃይሎች እና በብርሀን እና በጨለማ ኃይሎች መካከል ነው። እኛም ማድረግ ያለብን ልክ እንደዚያ ነው። በመጨረሻም በጎሳ፣ በኃይማኖት፣ በቋንቋ እና በክልል ልየኑት ቢኖርም ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን። ሁላችንም የሰላምን እና የእርቅን ቋንቋ መማር እንችላለን። እኔ በሰላም እና በእርቅ ትምህርት ቤት ገና ጀማሪ 1ኛ ክፍል ነኝ። ረዥም ጉዞ መጓዝ አለብኝ። ሆኖም ግን የዐቢይ አሕመድን እና የ75 ሚሊዮን ወጣቶችን እርምጃ በመከተል ምርኩዜን ይዤ እያነከስኩም ቢሆን ከዚያ እደርሳለሁ።

ሁልጊዜ የሰው ልጆች ለውጫዊ ተንኳሽ/stimuli ቅጽበታዊ ምላሽ ይሰጣሉ። ጥቂት ሰዎች ከእኛ አውሬ/beast የሚለውን ቃል ሲያወጡ ሌሎች ደግሞ ደግ/best የሚለውን ቃል ይይዛሉ። በሁለቱ ቃላት ማካከል ያለው ልዩነት ‘a’ የተባለችዋ አንዷ ፊደል ብቻ ናት።

ዐቢይ አሕመድን እደግፋለሁ፣ እከላከልላቸዋለሁ። ምክንያቱም ደግ/best ነቴንና መልካምነቴን አንድያበራ አርገዉልኛል ። በቅድመ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አገዛዝ ጊዜ የምጽፋቸውን ትችቶች የሚያነብ ሰው “ኃይለኛ”፣ “ይቅርታ የማያደርግ” እና ከዚያም በማለፍ “ጨካኝ” የሚሉ ሰዎች ነበሩ። አሁን የእኔን ሌላውን ጎን ሲመለከቱ በደስታ እየተገረሙ ነው። ለዐቢይ አሕመድ የማደርገውን በጎ ነገር እና የአሁኑን የእኔን ሁኔታ እንደወደዱት አስባለሁ።

እንዲያው ግላዊ በሆነ ምልከታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለህዝብ አደባባይ በሚቀርቡበት ጊዜ ሁልጊዜ ፈገግ ይላሉ። “ሳቅ ዓለም ከአንተ ጋር አብሮ ይስቃል” የሚለው አባባል እንዴት ያለ እውነተኛ ነገር ነው!

ከአክብሮት ጋርና ታላቅ ምስጋና– ከኤርትራ ጋር የተደረገውን የሰላም እና የእርቅ የመጀመሪያውን እርምጃ ለወሰዱት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ! እግዚአብሄር ይባርክዎ!

ሰላም! ሰላም!

ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ የሰላም እና የእርቅ ዕድል ይሰጥ።

ኢትዮጵያዊነት ዛሬ!

ኢትዮጵያዊነት ነገ!

ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ሰኔ 5 ቀን 2010 ዓ.ም

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ