ከቃልኪዳን አምባቸው

ለፖለቲካ ንቃተ ኅሊና መፈጠር ገንቢ ሚና ከተጫወቱ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ኢዴአፓ-መድህን በዋናነት ተጠቃሽ ነው፤ ከሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች በአብዛኛው በወጣቶች ተደራጅቷል የሚባለው ኤዴአፓ-መድህን፣ በምርጫ 97 ቅንጅትን ከፈጠሩ አራት ፓርቲዎች አንዱ በመሆን ፖለቲካውን ከማሟሟቁም በላይ፣ በተሣትፎ የሚያምን ፓርቲ ስለመሆኑም ተመስክሮለታል።

 

ኢዴአፓ-መድህን ሌሎችም ሊነሱ የሚችሉ ጠንካራ ጐኖችና በኢትዮጵያ ፓለቲካ ውስጥ ያሳደረው አዎንታዊ ተጽዕኖ ቢኖርም፣ ለጽሑፌ መነሻ ወደ ሆነኝ የፓርቲው የሰሞኑ መግለጫዎች ላይ ማተኮሩን መርጫለሁ። ኢዴአፓ-መድህን በያዝነው አዲስ ዓመት ለሚያካሂደው አራተኛ ድርጅታዊ ጉባዔው እንዲረዳው፣ ለሦስት ወራት የሚቆይ የአባላት ውይይት በየሣምንቱ እያካሄደ የደረሰበትን ግምገማም እንበለው ድምዳሜ፣ በሚያወጣው መግለጫ ይፋ እያደረገ ይገኛል። ኢዴአፓ-መድህን የውይይቱ ቀዳሚ ዓላማ የጠራ ግንዛቤና አቋም ለመያዝ ነው ቢልም የሚያወጣቸው መግለጫዎች ከመስመሩ ውጭ እሽቅድምድም መያዙን ያመለክታሉ።

 

ኢዴአፓ-መድህን በአንድ ሣምንት መግለጫው አንድም “ጠንካራ” የሚሰኝ የተቃዋሚ ፓርቲ እንደሌለ ከድምዳሜ መድረሱን ይፋ ሲያደርግ፣ በሌላው ሣምንት ለፓለቲካው መቀዛቀዝም ሆነ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የመዳከም መንስዔ፣ የህዝቡ አሉታዊነት መሆኑን ደርሼበታለሁ የሚል መግለጫ ያወጣል። (ኢዲአፓ-መድህን "የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጥንካሬዎችና ድክመቶች" የግምገማ ሪፖርት ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!፤ ፓርቲው "የገዥውን ፓርቲ ጥንካሬዎችና ድክመቶች" በሚል ያቀረበውን የግምገማ ሪፖርት ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)

 

አንድም “ጠንካራ” የሆነ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ የለም የሚለው መግለጫም ሆነ የህዝቡ አሉታዊነት ወይንም የተቃዋሚ ፓርቲዎች መዳከም መንስዔ የህዝቡ አሉታዊነት ስለመሆኑ የተደረሰበት ድምዳሜ ምን መሠረት አለው? የሚለውን ኋላ ላይ የምንመለከተው ይሆናል። ከዚያ በፊት ግን ፓርቲው የተወያየባቸው እነዚህ አጀንዳዎች በእርግጥ አባላቱ የጠራ ግንዛቤና ዕይታ እንዳላቸው በአንገብጋቢነት የሚታዩ ናቸውን የሚሉትን ነጥቦች እንፈትሸ።

 

ፓርቲው ከድምዳሜ የደረሰበት መግለጫ፣ ከመወያያ አጀንዳው አስፈላጊነት አንስቶ፣ በእርግጥ ፓርቲው ይህንን ግምገማ ለማድረግ ያለውን ተቀባይነት (ተዓማኒነት) እንዲሁም ለራሱ ለፓርቲው የሚኖረውንም ፋይዳ አጠያያቂ ያደርገዋል። ለኢዴአፓ-መድህን አንገብጋቢው ጉዳይ እሱ ራሱ ጠንካራ ተቃዋሚ ሆኖ ያለመገኘቱ ወይንስ ሌሎች ተቃዋሚዎችም ጠንካራ አለመሆናቸው? ሌሎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባለመጠናከራቸው ኢዴአፓ-መድህን ጠንካራ ተቃዋሚ ሆኖ እንዳይወጣ ይታሰባል? ፓርቲው ራሱን የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥራትና ደረጃ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን አድርጎ በመሾም እየሠራ ያለ ይመስላል፤ ኢዴአፓ-መድህንን ለመገምገም የሚያስገድደው ዐብይ ጉዳይ ለምን ጠንካራ የተቀዋሚ ፓርቲ መሆን እንዳልቻለ ነው፤ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ ለመሆን ባለመቻላቸው ኢዴአፓ-መድህን ለምን ተቆጨ ተብሎ ክርክር መግጠም አይቻል ይሆናል። ነገር ግን አጠቃላይ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን ጥንካሬና ድክመት በመለካትም ሆነ በመተንተን የተጠመደው ውይይት፣ የኢዴአፓ-መድህንን ጥንካሬና ድክመት ለይቶ፣ ፓርቲው እንደ ፓርቲ ስላለበት ደረጃ አባላቱ ሊደርሱበት የሚገባው የጠራ ግንዛቤና አቋም ሠርጎ እንዳይቀር ሥጋት ያሳድራል።

 

ኢዴአፓ-መድህን የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መዳከም ብቻ ሣይሆን የገዢውን ፓርቲ መጠናከርም በመግለጫው አሳውቋል። ኢዴአፓ-መድህን ግን እንደ ፓርቲ የት ላይ እንዳለ ግልጥልጥ አድርጎ አላሳየንም፤ “ተቃዋሚዎች የት ደረጃ ላይ እንዳለችሁ ገምግሜ እኔ እነግራችኋለሁ” የሚል የሚመስለው አዴአፓ-መድህን፣ ራሱን በተቃዋሚ ካባ ጀቡኖ ሁላችንም ደካሞች ነን ከሚለው የግምገማ ድምዳሜ ውጭ ራሱን “ጠንካራ” ከተባለው ገዥ ፓርቲ ጋር አነጻጽሮ ምን ደረጃ ላይ እንዳለና የድክመቱን ምክንያት፣ ድክመቱን ወደ ጥንካሬ ለመለወጥ የደረሰበትን ስምምነት ቢገልጽልን አበጀህ ባሰኘን ነበር። ከተቃዋሚ ፓርቲዎች “አንድነት ፓርቲ” ወይም “ቅንጅት” የሚለውን መጠሪያ የተረከበው ፓርቲ ወይም “መኢአድ” አንዳቸው ጠንካራ ሆነው ቢያገኛቸው ኖሮ የሚተላለፍልን የግምገማ መግለጫ ምን ይሆን ነበር? “እገሌ የሚሰኘው ተቃዋሚ ጠንካራ ሲሆን፣ ኢዴአፓ-መድህን ግን አይደለምና ድምፃችሁን ለእገሌ ስጡ” እንባል ይሆን? ኢዴአፓ-መድህን እምን ደረጃ ላይ እንዳለና የድክመቱንም ተጨባጭ ምክንያት አባላቶቼ አጥርተው ያውቁታል የሚለን ከሆነ የሚነግረን ወይም የሚወያየው በሌሎች ፓርቲዎች ድክመት ላይ ስለሚሆን የሚያወጣልን መግለጫ ስለሚኖረው ፋይዳም ጭምር ማብራሪያ ቢያክልበት የሚበጅ ይሆናል።

 

ፓርቲው ባወጣቸው መግለጫዎች ደረስኩበት ያለው ድምዳሜ ሙግት የሚከፍት ነው፤ “አንድም ጠንካራ የሆነ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ የለም” ሲባል፣ የፓርቲ ጥንካሬ መለኪያዎቹ ምን ምን ናቸው? የመሥፈርቶቹ ተቀባይነት ለኢዴአፓ ወይንስ ሌሎች ፓርቲዎችና ህዝቡንም ጨምሮ ስምምነት ተደርሶባቸዋል? የመሥፈርቶቹ ተቀባይነት ለፓርቲው ብቻ ከሆነና ለአባላቱ ግንዛቤ የሚያገለግል ከሆነ ስምምነት ባልደረሰበት መሥፈርት በጋዜጣ እንዲገለጽልን ማድረጉ ለምን አስፈለገ? አንዳንዶቹ መሥፈርት ተደርገው የተወሰዱት ከምርጫ 97 ጋር ተያያዥነት ያላቸውና ጥቅል የሆኑ ጉዳዮች ሲሆኑ፣ አንዳንዶቹ ኢዴአፓ-መድህንን እንድንታዘበው የሚጋብዙንም ናቸው።

 

ኢህአዴግ ጠንካራ ፓርቲ ለመሆን ችሏል የሚል ምስክርነት የሚሰጠው የኢዴአፓ-መድህን መግለጫ፣ ለዚህ ጥንካሬ ያበቃው በሚሊኒየሙ አከባበር ስለኢትዮጵያ ታሪክና አንድነት በጎ ነገር መናገር በመቻሉ ነው ይለናል፤ ሌላው ተቃዋሚዎች ራሳቸውን በሐቅ ገምግመው ድክመቶችንና ጠንካራ ጎኖችን ለህዝቡ ቢናገሩ ከድክመት ወደ ጥንካሬ ለማለፍ የሚችሉት በሁለትና በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንጂ በ2002 ዓ.ም. በሚደረገው ምርጫ ተቃዋሚ የፓለቲካ ፓርቲዎች ቦታ ላይኖራቸው እንደሚችል በጊዜ ርዝማኔ ተለክቶ የተቀመጠ ድምዳሜም ጭምር ሠፍሮልናል።

 

ኢዴአፓ-መድህን ለተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መዳከም የህዝቡን አሉታዊነት ወይም ተስፋ መቁረጥ እንደ መንስዔነት ይፋ አድርጓል። ህዝብ የት ቦታና መቼ፣ በምንስ መልኩ ለኢዴአፓ-መድህን ተስፋ መቁረጡን እንዳሳወቀው የሚታወቅ ነገር የለም። “ህዝብ” በሚል የተገለፀው የአዲስ አበባ ህዝብ ወይንስ የኦሮሚያ፣ የደቡብ የሚለው በድፍን የቀረበ ነው። ኢዴአፓ-መድህን የህዝቡን አሉታዊነት እንዴት ብሎ ለካው? ፓርቲው ያለው ህዝቡ ውስጥ ከሆነ ተለይቶ እሱ አዎንታዊ፣ ህዝቡ አሉታዊ የተደረገበት የግምገማ ውጤት ከህዝቡ የተገኘ ወይንስ ከውጭ የመጣ? የሚሉት አጠራጣሪ ወይም ድፍን የሆኑና የማይጨበጡ ጉዳዮች ናቸው።

 

ኢዴአፓ-መድህን መሬት ሊረግጥ ይገባል፤ ህዝብን ተሳስተሃል የሚለው ማን ነው? በምንስ መሥፈርት? እዚህ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ለአዲስ አበባ ህዝብ መንገዱን ሁሉ ወርቅ ብናነጥፍለት፣ ህዝቡ ግን ወርቁን ወርቅ ካላለው ትርጉም አልባ እንደሚሆን ያስረዱትን በመጥቀስ፣ ኢዴአፓ-መድህን ህዝቡን ከመለካት ለምን ህዝቡ ውስጥ ያለውን ተቀባይነት ለመለካት እንዳልደፈረ የጠራ አቋም ማስያዝ አለበት። ፓርቲው ከመስመሩ ውጭ ከመሮጥ ይልቅ የውስጥ ዲሞክራሲው ያቀረበው አማራጭ የፖለቲካ ፕሮግራም ምን ውጤት ሊያመጣ እንደሚችልና ያገኘውን ተቀባይነት የመመዘን፣ የህዝብን አመኔታና ተቀባይነት ለማግኘት ህዝብን ከመወንጀል፣ ፓርቲው የሚጠበቅበትን መወያየቱ ራሱን ለማየት ይረዳዋል፤ ኢዴአፓ-መድህን ሐቁን ለመጋፈጥ ይድፈር።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ