ኤርሚያስ ጋሹ (የኢዴአፓ መድህን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል)

(”የኢዴአፓ-መድህን የቀውስ ፖለቲካ” በሚል ርዕስ በቃልኪዳን አምባቸው ለቀረበው ጽሑፍ የተሰጠ ምላሽ)

ቃልኪዳን አምባቸው የተባሉ ፀሐፊ ኢዴአፓ-መድህን ፓርቲን አስመልክተው ለሁለተኛ ጊዜ ጽፈዋል። ”የኢዴአፓ-መድህን የቀውስ ፖለቲካ” በሚል ርዕስ ያቀረቡት ይኸው የአቶ ቃልኪዳን ጽሑፍ፤ ቀደም ሲል ለፃፉት ጽሑፍ እኔ የሰጠሁትን ምላሽ መነሻ ያደረገ ነው።

 

ይሁንና ፀሐፊው እኔ የሰጠሁትን ምላሽ ነጥብ በነጥብ እየጠቀሱ መከራከሪያ አላቀረቡም። እንዲያውም እኔ ያቀረብኳቸውን አንዳንድ ነጥቦችን ሆን ብለው አዛብተው አቅርበዋል። አሁንም የፃፉት በመጀመሪያ ጽሑፋቸው ኢዴአፓን በመተቸት ያቀረቧቸውን ነጥቦችን እንደገና በመድገም ነው። በዚህኛው ጽሑፋቸው የተጨመረው ነገር የኢዴአፓ-መድህን አመራር አባላትን በስም ጠቅሰው መዝለፋቸው ነው።

 

የአቶ ቃልኪዳን አሁንም ዋነኛ ትችታቸው፤ ከምርጫ 97 በኋላ ኢህአዴግ መጠናከሩን፣ ተቃዋሚዎች መዳከማቸውንና የህዝቡ የፖለቲካ ተሳትፎና ግንዛቤ ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ ኢዴአፓ-መድህን ለምን ገመገመ? የግምገማውንስ ውጤት ለምን በመግለጫ አወጣ? ለመሆኑ ኢዴአፓ-መድህን ማን ሆነና ነው ይህንን የሚያደርገው? … ወዘተ የሚሉትን ሃሳቦች አቅርበዋል። ይህንን የኢዴአፓ-መድህንን አካሄድ ባለፈው ጽሑፋቸው ”ውል የሳተ” ሲሉ በዚህኛው ጽሑፋቸው ”የቀውስ ፖለቲካ” ብለውታል። ሃሳባቸው ግን ቀድሞውንም ውል ካልነበረው ከራሳቸው የአስተሳሰብ ቀውስ የመነጨ ስለመሆኑ ጽሑፋቸውን ተርትረን እንየው።

 

ህዝብን ስለመገምገም

 

አቶ ቃልኪዳን ”የኢዴአፓ-መድህን ህዝቡን መገምገም አይችልም፤ ለመሆኑ ጥቂት መቶ ሰዎች ህዝብን ተሳስተሃል ማለት እንዴት ይችላሉ?” ይላሉ። አስቸጋሪ የሚሆነው የእሳቸው ክርክር ከንድፈ ሃሳብም ሆነ ከፖለቲካዊ ዕውቀት ያልመነጨ መሆኑ ነው። በመርኅ ደረጃ ህዝብም ጭምር የሚሳሳት መሆኑን ከተግባባን፣ ይህን ለማለት ጥቂት መቶ ሰዎች ብቻ ሳይሆን አንድም ሰው ቢሆን ግምገማ እንዳያካሂድ የሚል ነገር አይኖርም። የኢዴአፓ-መድህን ዓላማ ህዝብን ተሳስተሃል ማለት እና መውቀስ አይደለም። የፀሐፊው ሃሳብ ከግንቦት 97 ምርጫ አንፃር በህዝቡ ተሳትፎ ሂደትና ከፖለቲካዊ ግንዛቤ አንፃር፣ ”ምንም ችግር አልነበረም” የሚል ከሆነ እዚያ ላይ ተለያይተን ክርክሩን ችግር ”ነበረበት” ወይም ”አልነበረበትም” ብሎ መቀጠል ነው። የኢዴአፓ-መድህንን አስተሳሰብ የሚመጥነው እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ነው።

 

ከዚህ ውጭ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ትግል ሂደት፣ አንድ ህዝብ ስለሚገኝበት ፖለቲካዊ ግንዛቤ፣ እንዲሁም ስለትግል ልምድና ስለሌሎችም ከህዝብ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ባሕሪያት ስለሚመነጩ ችግሮች መገምገም፣ መወያየትና ችግሮችን ለይቶ መፍትሔ መፈለግ ስህተት ነው የሚል አስተሳሰብ ምን ያህል ጨቅላ እንደሆነ በቀላሉ ማረጋገጥ ይቻላል። ፀሐፊው ያለፈው ጽሑፌን ”እያንዳንዱ ሰው የሚሳሳት ሆኖ መፈጠሩ የሚያከራክር ካልሆነ፣ ብዙ ሰዎች በአንድነት ሲሆኑ መሳሳት አይችሉም ማለት እንዴት ይቻላል?” ብዬ ላቀረብኩት ጥያቄ ፀሐፊው ምላሽም ሆነ መከራከሪያ አላቀረቡም። ይባስ ብለው ባለፈው ጊዜ ያቀረቡትን ሃሳብ ደግመው በማቅረብ አንባቢን አሰልችተዋል፤ ራሳቸውንም ትዝብት ላይ ጥለዋል።

 

ከላይ ከተነሱ ነጥቦች አንፃር በመርኅ ደረጃ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ቀርቶ የአሜሪካ ህዝብም የራሱ ችግር እንዳለበት ያቀረብኩትን ሃሳብ ለማጣጣል የተከተሉት የክርክር ስልት፣ የአሜሪካ መንግሥትም የኢትዮጵያን ህዝብ ይገመግማል እንዳልኩ አድርገው ማቅረባቸው ነው። ለመሆኑ የአሜሪካ መንግሥት የኢትዮጵያን ህዝብ በዚህ ማዕቀፍ ስር ለመገምገም ማነው? ምን አግብቶት?

 

የሰውን ሃሳብ እንደሚመቻቸው መተርጎም የሚቀናቸው አቶ ቃልኪዳን፣ በዚሁ ጽሑፋቸው ኢዴአፓ-መድህን ተቃዋሚዎችንና ኢህአዴግን ገምግሞ፣ ስለኢህአዴግ መጠናከርና ስለተቃዋሚዎች መዳከም መግለጫ ያወጣው፣ ”የኢህአዴግ መጠናከርና የተቃዋሚዎችን መዳከም ለማብሰር” እንደሆነ አድርገው አቅርበዋል፤ ይህ ፍጹም ስህተት የሆነ ግንዛቤ ነው። የኢዴአፓ ዓላማ አባላቱ ስለሀገራቸው ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ያላቸው አስተሳሰብ ተጨባጭ በሆነ እውነታ ላይ እንዲመሠረት ለማድረግ ነው። ከዚህ ውጭ ኢዴአፓ ስለኢህአዴግ መጠናከር ብቻ ሳይሆን ስለአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፍልስፍና ድክመት፣ ሕገ-መንግሥቱ ከዝግጅት ሂደት ጀምሮ በሀገራችን ህዝብ ውስጥ የአንድነት ሳይሆን የመለያየት ምንጭ ስለመሆኑ፣ የኢህአዴግ የኢኮኖሚ አመራር ኢህአዴግ የሚለውን ያህል ውጤት እያስገኘ አለመሆኑን፣ … ወዘተ ገልጿል። ታዲያ ይህ ሁሉ ስለኢህአዴግ ጥንካሬ ለማብሰር የተደረገ ነውን? ፀሐፊው የኢዴአፓን ግምገማና መግለጫ በቁንጽል እየጠቃቀሱ፣ ሙሉውን የግምገማ ውጤት ያላነበበውን ወገን ለማሳሳት በሚመች መንገድ የሚያጥላሉት ለምንድነው? የኢዴአፓ-መድህን ዓላማ፣ አካሄድ፣ አሠራርም ሆነ መርኅ ለአቶ ቃልኪዳን ላይመቻቸው ይችላል። ያልተመቻቸውን ነገር ለመተቸት ደግሞ በሐቅ ላይ መመሥረት እንጂ በሸርና በሸፍጥ መንፈስ ተነሳስተው፣ ፓርቲውን በጭፍን በመውገዝ አፈር-ድቤ ማስጋጥ ከዚህ ዘመን ትውልድ የማይጠበቅ ያረጀ፣ ያፈጀ የሰገሌ ዘመን ፖለቲካ መሆኑን ልብ ሊሉት ይገባል።

 

ስለተቃዋሚዎች

 

ፀሐፊው በሁለቱም ጽሑፎቻቸው ኢዴአፓ ስለተቃዋሚዎች ያለውን አስተሳሰብ አብጠልጥለዋል። ለመሆኑ የተቃዋሚዎች ፖለቲካ ጉዳይ የሀገር ዕጣ ፈንታ ጉዳይ አይደለም እንዴ? ባለፉት ዓመታት ውድ ዋጋ የከፈልንለት የተቃውሞ ትግል፣ ለኢትዮጵያ ችግሮች መፍትሔ መሆን እየተሳነው በችግር ላይ ችግር እየደረተ፣ በሀገሪቱ ላለው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት ያቃተው ብቻ ሳይሆን ራሱም ሌላ ችግር እየሆነ ሲሄድ፣ ይህንን ተረድቶ ”ለመሆኑ ለተቀዋሚዎች ትግል መዳክም ምክንያቱ ምንድነው? ምንጩስ ምንድነው? መፍትሔውስ?” ከማለት ይልቅ ባለፉት አርባና ሃምሳ ዓመታት በመጣንበት መንገድ ተሸፋፍነንና ተደባብቀን እንጓዝ ማለት ማንን የሚጠቅም ሃሳብ ነው? ከኢዴአፓ ችግሩን አብጠርጥሮ ከማጋለጥ አካሄድ ይልቅ፣ ይህ ኢህአዴግን የበለጠ የሚጠቅም ስለመሆኑ ብዙ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል። ሌላው ቢቀር ችግሩን በተለየ መንገድ አይቶ አዲስ አቅጣጫ የሚፈጥር የኅብረተሰብ ክፍል መነሳት የለበትም? አቶ ቃልኪዳን ለኢዴአፓ-መድህን ቀና አመለካከት ባይኖርዎትም እንኳ፣ አንድን ጉዳይ በአንድ ገጽታው ብቻ አይተው ብያኔ መስጠትም ሆነ ሳያመዛዝኑ መተቸት ቢያንስ ከትዝብት ላይ የሚጥል መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል።

 

ስለኢዴአፓ-መድህን አመራር

 

ፀሐፊው የኢዴአፓ-መድህን አመራር አባላትን በስም በመጥቀስ፣ እሳቸው ”ቀውስ” ያሉት የፓርቲው ፖለቲካ፣ በአመራሩ ውስጥ የተወሰኑ ሰዎች ”በህዝብ ውስጥ ተቀባይነት አጥተናል” ከሚል ሥጋት የመነጨ እንደሆነ ይተነትኑና፣ ተመልሰው ”ይህ የፓርቲው አካሄድ የፓርቲውን ተቀባይነት የሚጐዳ” ስለመሆኑ ያብራራሉ። እሳቸው እንዳሉት አሁን ኢዴአፓ የሚሄድበት የፖለቲካ መንገድ በእነኝህ ሰዎች ተፅዕኖ ምክንያት፣ ፓርቲው በህዝብ ውስጥ ያለውን ተቀባይነት የሚያሳጣ ከሆነ፣ እነኝህ የአመራሩ አባላት ፓርቲውን በህዝብ ውስጥ ሊያስወድድ ሳይሆን ሊያስጠላ የሚችል መግለጫ እንዲያወጣ በማድረግ የራሳቸውን ተቀባይነት ሊያተርፉ የሚችሉት እንዴት ነው? አቶ ቃልኪዳን እርስ በርሱ የሚዋቃ ሃሳብ ለመጻፍ ለምን እንደቸኮሉ ባይገባኝም፤ ‘የረጋ ወተት’ እንዲሉ ለወደፊቱ ስክነት እንዲሰፍንባቸው አደራ እላለሁ።

 

ኢዴአፓ-መድህንን ማዋረድ እንጂ ፍፁም ማመዛዘን የሚባል ነገር ያልፈጠረባቸው አቶ ቃልኪዳን፤ የአቶ ልደቱን ስም በመጥቀስ ”ልደቱ ሥልጣን ይልቀቁ ማለት እንጂ ሥልጣን ልልቀቅ የማይሉ፣ አሮጌ ሥርዓት አራማጅ እንጂ የለውጥ ሐዋርያ አለመሆናቸውን መገንዘብ አያስቸግርም” የሚል ሃሳብ አስፍረዋል። ፀሐፊው አቶ ልደቱን የለውጥ ሐዋርያ አድርገው ላለመቀበል ካላቸው ከራሳቸው ምክንያት ጋር መከራከር ለኔ ምንም ጥቅም የለውም። የሆነ ሆኖ አቶ ልደቱ የለውጥ ሐዋርያ ስለመሆናቸው ለማረጋገጥ ማድረግ ያለባቸው የመጀመሪያው እርምጃ ከፓርቲው አመራርነት ራሳቸውን ማግለል ነው ወይ? በምን ሂሳብ? ለፀሐፊው ለውጥም ሆነ የለውጥ ሐዋርያነት ትርጉም ምንድነው?

 

ኢዴአፓ-መድህን ከተመሠረተ ከስምንት ዓመታት በላይ ሆኖታል። በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ከአምስት ዓመታት በላይ የቆየው በዶ/ር አድማሱ ገበየሁ ሊቀመንበርነት ነው። ዶ/ር አድማሱ ሁለት ጊዜ በጉባዔ የተመረጡ ሲሆን፤ አቶ ልደቱ ደግሞ ከሁለት ዓመታት በፊት በተደረገ ጉባዔ ከፓርቲው ዋና ፀሐፊነት ወደ ሊቀመንበርነት እንዲመጡ ተደርገዋል። እውነታው ይኼ በሆነበት ሁኔታ እንዴት ተደርጐ ነው የአቶ ልደቱ ሥልጣን መልቀቅ ጉዳይ አጀንዳ የሚሆነው? ለመሆኑ የፓርቲያችን መሪነት አቶ ልደቱ ሲፈልጉ የሚለቁትና ሲፈልጉ የሚይዙት ነው ወይ?

 

ፀሐፊው ”የፓርቲው አባላት ፓርቲያቸውን የማጠናከር ፈጣን እርምጃ መውሰድ ይገባቸዋል” በማለት መክረዋል። ምክሩ ጥሩ ነው። ነገር ግን የፓርቲው አባላት ፓርቲውን ለማጠናከር ፈጣን እርምጃ እየወሰዱ መጥተዋል። የፓርቲው ተቀናቃኝ የሆኑ ወገኖች ኢዴአፓን ያለ ልደቱ፣ ሙሼና አብዱራህማን ማየት የሚፈልጉበትን ምክንያት በማረጋገጥ፣ ማን መሪያቸው መሆን እንደሚገባ ጠንቅቀው እያወቁ መጥተዋል። በተለይም በአቶ ልደቱ ላይ የሚደረገው የአሉባልታ ዘመቻ ለምን እንደሆነ በማረጋገጥ፣ ይህ በሀገሪቱ የፖለቲካ ሕዋ ላይ ለዘመናት የነገሠ የአሉባልታ ዘመቻ እየበረታ በሄደ ቁጥር፣ አባላቱ በአቶ ልደቱ ላይ ያላቸው እምነት እየጠነከረ የሚሄድ ሆኗል። የኢዴአፓ አባላት የፀሐፊው ምክር ከቀናነት ሳይሆን ከክፋት የሚመነጭ ከፋፋይነት እንደሆነ ለማወቅ፣ ከሚያስፈልገው በላይ የላቀ ችሎታ ያላቸው መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለአቶ ቃልኪዳን ብቻ ሳይሆን፣ በዚህ ከንቱ አስተሳሰብ ዙሪያ ለተኮለኮሉ ሁሉ መልዕክቱ ቢደርሳቸው መልካም ነው።

 

ስለጋዜጠኞች

 

ፀሐፊው ”የኢዴአፓ መድህን አመራሮች በፓርቲው ላይ አስተያየት የሚጽፍን ጋዜጠኛ፣ የፓርቲው ተቀናቃኝ አድርጐ መፈረጃቸው” የተለመደ ነው ይላሉ። በመጀመሪያ በየጋዜጣው ላይ የሚቀርቡ እንዲህ ዓይነት ጽሑፎች፣ ከጋዜጠኝነት ሙያና ሥነምግባር አንፃር ተቃኝተው የሚቀርቡ ናቸው ወይ? ከጋዜጠኝነት ሙያ፣ ሥነምግባርና መርኅ አንፃር የሚመነጩ ቢሆኑ ኖሮ ”ኢዴአፓ-መድህን እንዲህ ዓይነት አሠራር የሚከተለው ለምንድነው?” የሚል ጥያቄ በማንሳት ሙያዊ ትንታኔ በመስጠት፣ በተቃራኒው ከሚገኙ ሃሳቦች ጋር ይመሳከሩ ነበር። ባለፉት ዓመታት ስለኢዴአፓ እና መሪዎቹ ላይ የተባለውን ሁሉ እናንሳና፣ ለኢዴአፓ ብለን ሳይሆን እስቲ ለፍትህና እውነት ብለን አንድ ባንድ እንፈትሽ። ከተባለው ሁሉ አንዱም እውነት አለመሆኑን በቀላሉ ማረጋገጥ ይቻላል።

 

በሌላ በኩል፣ ”የኢዴአፓ መድህን አመራሮች፣ በፓርቲው ላይ አስተያየት የሚጽፍን ጋዜጠኛ የፓርቲው ተቀናቃኝ አድርጐ መፈረጃቸው የተለመደ ነው” እያሉ ”እኔ ልጻፍ እናንተ መልስ አትስጡኝ” ማለት ግን ከዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ውጭ መሆኑንም ሊረዱት ይገባል። የኢዴአፓ-መድህን አመራር አባላት በሐሰት እየተወነጀሉ ምላሽ አይስጡ ማለት ተገቢ አይደለም። አቶ ቃልኪዳን ወደዱትም፣ ጠሉትም ወደፊትም ለሚጻፍብን ውሸት ሁሉ፣ መልስ መስጠት አግባብ ሆኖ ካገኘነው ”ውሸት ነው” ነው ብለን መመለሳችን የማይቀር መሆኑን ቢረዱት መልካም ነው።

 

በቅንጅት ውስጥ ኢዴአፓ በአንድ በኩል ለቅንጅቱ ዓላማ መሳካት ውድ ዋጋ እየከፈለ፣ በሌላ በኩል ቅንጅቱ ቅንጅት መሆን እያቃተው ሲሄድ ብቻ ሳይሆን፤ ኋላ ግልጽ እንደሆነው ፈጽሞ የፖለቲካ ዓላማችንን ለማሳካት የማይችል ስብስብ መሆኑን ሲያረጋግጥ፣ ስለወሰደው እርምጃ በአንዳንድ ጋዜጦችና ጋዜጠኞች ምን ተብሎ ነበር የተፃፈው? የውሳኔው ምንጭ የፖለቲካ ዓላማን ከመሳትና ህዝብን ከመክዳት የመነጨ እንደሆነ ተደርጎ ማለቂያ የሌላቸው ውሸቶች ተጽፈዋል። አቶ ቃልኪዳን ”ጋዜጠኞች” ያሏቸው ፀሐፊዎች የኢዴአፓ-መድህንን አስተሳሰብ ለማጥፋት ባይፈልጉ ኖሮ ይህንን የተቀነባበረ ውሸት እንዳለ ከማስተጋባት ይልቅ በመረጃ ላይ በመመሥረት አጣርቶ ለማቅረብ ይሞክሩ ነበር። ይህ ዓይነቱ አሠራር ከጋዜጠኝነት ሙያ አንፃር የተሠራ፣ ሚዛኑን የጠበቀ ትችት ነው ወይስ ኢዴአፓ-መድህንን የማጥፋት ዘመቻ? የትናንቱ ትናንት አልፏል። ዛሬም ኅሊናን ዘግቶ በጥፋት ዘመቻው መገፋቱ ምን ይባላል? ለመሆኑ በዚህ ሀገርና ህዝብ ውስጥ የእውነት ጠርዝና የኅሊና ደርዝ የት ድረስ ነው? የኢዴአፓ-መድህን አመራር አባላት ይህንን ሁሉ ጥቃት ለመቀበል የመረጡት፣ ለፖለቲካ ዓላማቸው ግብ መድረስ ካላቸው ሐቀኝነትና ፅናት ባይሆን ኖሮ፣ ይህ አሉባልታና የጋዜጣ ዘመቻ ያስከተለባቸውን የአካልና የኅሊና ጉዳት የሚያካክስ ሌላ ምንም ዓይነት ጥቅም በዚህ ምድር ላይ አይገኝም።

 

በመጨረሻ፤ ፀሐፊው የኢዴአፓ-መድህን አቋሞች ለምርጫ ኮረጆ ፋይዳ የማይኖራቸው መሆኑን ለመግለጽ ሞክረዋል። አቶ ቃልኪዳን እውነተኝነት እና ትክክለኝነት አያስመርጥም ነው የሚሉን? እውነተኛና ትክክለኛ መሆናችን ካላስመረጠን ይህ እኮ የኛ ችግር አይሆንም። ነገር ግን አሁን የኛ ጭንቀት የምርጫ ኮረጆ አይደለም። የእኛ የመጀመሪያ ትኩረት የኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ዋነኛ መገለጫው ከሆነው ድክመት ማላቀቅና፣ ለሀገርና ለህዝብ የሚጠቅም ራዕይ መቅረጽና ከተለመደው መሳሳትና መዝረክረክ ራሳችንን ማጽዳት ነው። ይህንንም ነው እኛ የራዕይ ፖለቲካ የምንለው። ተግባባን?

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ