ከሶማሊያ የመውጫው ጊዜ አሁን ነው (ከፕ/ር ዓለማየሁ ገ/ማርያም)
ከፕሮፌሠር ዓለማየሁ ገብረማርያም
በሶማሊያ ያለው ሁኔታ እየተለወጠ ነው፤ ነገሮች ሁሉ በሶማሊያ ለሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በፍጥነት እየተበላሸበት ነው። አልሸባብ የሚባሉት ጀሃዲስቶች የሶማሊያን አንዳንድ ክፍሎች እየተቆጣጠሩ ሲሆን፣ ወደ ሞቃዲሾም መገስገስ ጀምረዋል። አልሸባብ እንደ ቀድሞ የደፈጣ ውጊያ በማድረግ ተኩሶ የሚሸሽ አልሆነም፤ ይልቁንም ይዞታውን እያጠናከረ ነው። በቅርቡ እንኳ ደቡባዊቷን የወደብ ከተማ ኪስማዩን ሲቆጣጠር ከመካከለኛው ምሥራቅ ደጋፊዎቻቸው የገንዘብ ድጋፍ ጎርፎላቸዋል።
በጀመሩት ግስጋሴ የሞቃዲሾን አየር ማረፊያ የዘጉ ሲሆን፣ የሞቃዲሾን ወደብም ለመቆጣጠር ዝተዋል። ታጣቂዎቹ፣ የአፍሪካ ሕብረት ሠላም አስከባሪ አባላት በሆኑት የዑጋንዳና ቡሩንዲ ወታደሮች ላይ የእጅ ቦንብ እየወረወሩ ግስጋሴያቸውን እያፋጠኑ ሲሆን፤ ግድያ፣ ዝርፊያና አፈና የሶማሊያ የዕለት ተዕለት ውሎ እየሆነ መጥቷል።
በሶማሊያ ምንም ዓይነት ተጨባጭ መፍትሔ አልተገኘም፤ ጦርነቱ በሰውም ኾነ በንብረት ላይ ያሣደረው ጉዳት ኢትዮጵያውያን ሊታገሱት ከሚችሉት በላይ እየሆነ ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ”ስትራቴጂያዊ ሽንፈት” እያጋጠመው ሲሆን፣ ሁለት ዓመት ባስቆጠረው የሶማሊያ ቆይታው ምንም የስኬት ምልክት አይታይም።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሶማሊያ ያገኘው ድል ጮቤ አስረግጦት፣ ባለሥልጣናቱ በጥቂት ሣምንታት ጦሩ ተልዕኮውን አጠናቆ እንደሚለቅ በተደጋጋሚ ፍንጭ ሲሰጡ ነበር። ጠ/ሚ መለስ ዜናዊም በአሸናፊነት መንፈስ ”… ወደ ሶማሊያ የዘመትንበትን የጀሃዲስቶችን እንቅስቃሴ መቆጣጠርና ለኢትዮጵያ ሥጋት እንዳይሆኑ የማድረግ ቀዳሚ ተልዕኳችንን አሳክተናል። የሶማሊያ የሽግግር መንግሥትን የማረጋጋትና ለብሔራዊ እርቅ ሁኔታዎችን አመቻችተናል …” ሲሉ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሙሉ ለሙሉ የተሳካ ባይሆንም ሶማሊያ ዓለም አቀፍ ሠላም አስከባሪዎችን ለማስገባት ዝግጁ ስትሆን ጦሩ እንደሚወጣ ገልፀዋል። ቢሆንም ዋነኛ ጥያቄው የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ መውጣቱ ብቻ አይደለም፤ የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ ቢወጣም ለውጥ ሊፈጠር ይችላል ወይ? የሚለው ነው።
አቶ መለስ የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ሕብረት ወይም የየትኛውም ወገን ሠላም አስከባሪ አካባቢውን ሲረከብ፣ ”አረጋጋኋት” የሚሏትን ሶማሊያ በክብር ለቀው መውጣት ይፈልጋሉ፤ ይህ ግን የሚሆን አይመስለኝም። ምክንያቱም ይህንን ኃላፊነት በመቀበል ዕርዳታ ማድረግ ስህተትና ሞኝነት ብሎም ኃላፊነትን ያለመወጣት ነውና።
ሶማሊያ ያሳለፈችው ጊዜ
እ.ኤ.አ. በታህሳስ 2006 ዓ.ም. ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ለዋሽንግተን ፖስት የኢትዮጵያ ጦር በሶማሊያ ገብቷል መባሉን አስተባበሉ፤ በቃለ ምልልሱም ”… በሶማሊያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ቢኖሩንም ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የሽግግር መንግሥቱ በጠየቀን መሠረት በባይድዋ ሥልጠና የሚሰጡ ናቸው፤ አሁን ግን የሽግግር መንግሥቱ የሥልጠና እገዛ ስለማይፈልግ በደስታ እንወጣለን …” ነበር ያሉት። በሶማሊያ የሚገኙ ጽንፈኛ ቡድኖች በሀገሪቱ ከኃይማኖት ነፃ የሆነ መንግሥት እንዲመሠረት የማይፈልጉ ሲሆን፣ እንደ ታሊባን ያለ አገዛዝ ለመመስረት እንደሚያልሙ ገልፀዋል። ይህ ሊሆን የሚችለው በንግግር ብቻ ነው። ወታደሮቹ በሶማሊያ የሚቆዩትም ለጥቂት ሣምንታት ሁኔታዎች እስኪረጋጉና ዓለም አቀፍ የሠላም አስከባሪ ጦር በሶማሊያ በመሥፈር ክፍተቱን እስኪሞላ ድረስ ነውም ብለው ነበር።
እ.ኤ.አ. በግንቦት 2007 ዓ.ም. ከአልጀዚራ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ጦር ሥልጠና እየሰጠ ብቻ ሳይሆን፣ ከሽግግር መንግሥቱ ጋር በመሆን አሸባሪዎችን እየተዋጋ መሆኑን ተናግረዋል። ”… ሶማሊያን አልወረርንም፣ ዓለም አቀፍ እውቅና ባለው ለሶማሊያ የሽግግር መንግሥት እገዛ እንድንሰጠው ተጋብዘን ነው ይህንን ያደረግነው …” ብለው በጦርነቱ አሜሪካ የነበራትን ሚና ግን ክደዋል። ”… እኛ አሜሪካን ወክለን አይደለም ከአሸባሪዎች ጋር የተዋጋነው፣ አሜሪካ ራሷ በእኛ መሣተፍ የተቀላቀለ ስሜት ነበራት፤ አንዴ ከገባንበት በኋላ ግን ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ድጋፍ አገኘን …” ማለታቸው ይታወሳል። በኅዳር 2007 ዓ.ም. ደግሞ ለፓርላማው ”የኛ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መውጣት፣ አክራሪዎች ዳግም እንዲደራጁ ያደርጋል፤ የኢትዮጵያ ጦር የከፈለውን መሥዋዕትነት መና ያስቀራል …” ብለው ነበር።
ሶማሊያ አሁን ያለችበት ሁኔታ
በሶማሊያ ነገሮች በፍጥነት ወደከፋ ሁኔታ እየተለወጡ ነው። የሶማሊያ ጀሃዲስቶች ሽንፈትን በፀጋ አልተቀበሉም። የኢራቅ ዓይነት የደፈጣ ውጊያ እያደረጉ ነው። በጦርነቱ የሚቀጠፉ ሠላማዊ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን፣ እስካሁን 20 ሺህ ሶማሊያውያን እንደሞቱ ተገምቷል። የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያን ከወረረ ጊዜ ጀምሮ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሶማሊያውያን ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። አምነስቲ ኢንተርናሸናል እንደገለፀው፣ የኢትዮጵያ ጦር የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየፈፀመ ነው። ከዚህ ውስጥ ያለምክንያት መግደል፣ ማሰቃየት፣ መግረፍ፣ መድፈርና ያለ ሕግ ማሰር እንዲሁም የጅምላ ቅጣቶች የሚጠቀሱበት ሲሆን፣ የአቶ መለስ መንግሥት ግን ድርጊቱን ”የተቀነባባረ ሴራ” ሲል አስተባብሏል።
አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ መንግሥት የጦሩን የሶማሊያ ቆይታ በተመለከተ ኃላፊነት እንደማይሰማው ገልፀዋል። ፖርላማውም ሆነ ህዝቡ ጦሩ በሀብትም ሆነ በሕይወት የደረሰበት ኪሣራ ምን ያህል እንደሆነ ማወቅ ይፈልጋል፣ እኛ ግን ሁሉ ነገር ተደብቆብናል።
የሶማሊያ አሸባሪዎችና ጀሃዲስቶች ጠንካራ ይዞታዎችን ከማበጀት በላይ እየተስፋፉ መጥተዋል። የሶማሊያ ባህር ዳርቻዎች የዝርፊያ ማዕከላት እየሆኑ ሲሆን፣ ዘራፊዎቹ የሳተላይት ሞባይል ስልክ፣ ፈጣን ጀልባና የጦር መሣሪያ በመያዝ፣ በሕንድ ውቅያኖስ ላይ ዝርፊያ እያካሄዱና ለንግድ እንቅስቃሴ አደጋ እየሆኑ ነው። በቅርቡ እንኳ አቶ መለስ የባህር ላይ ዘራፊዎቹ እንቅስቃሴ ከሶማሊያ አለመረጋጋት ጋር የተያያዘ በመሆኑ እንደሚያሳስባቸው በመግለጽ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አንድ እርምጃ ይወስዳል የሚል ግምት እንዳላቸው ተናግረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም መስፍንም በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዜ ላይ በሶማሊያ ያለውን የአፍሪካ ሕብረት ሠላም አስከባሪ የሚያግዝ ጦር የተባበሩት መንግሥታት በአፋጣኝ እንዲያሠፍር ጠይቀዋል።
የሶማሊያ ጦርነት እንደ ኢራቅ ጦርነት ሁሉ በኢትዮጵያውያን አልተደገፈም። የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ሳይቀሩ ጦሩ በፍጥነት ከሶማሊያ እንዲወጣ በፖርላማ ውስጥ የተቀናጀ ዘመቻ እያደረጉ ነው። በቅርቡ የአሜሪካ ድምፅ እንደዘገበው፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሶማሊያ የተከፈለው የሰውና የሀብት መሥዋዕትነት ከሚገመተው በላይ መሆኑን በመጥቀስ ለጠ/ሚኒስትር መለስ ደብዳቤ አስገብተዋል። አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ”… ሶማሊያውያን መልሰው እየወጉን ነው፣ በኔ ግምት እኛ ተሸንፈናል …” ብለው ነበር። የአቶ መለስ ፖሊሲ ግን ”በማንኛውም ቀን ከሶማሊያ ልንወጣ እንችላለን፣ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አይደለም ያለነው፤ የሽግግር መንግሥቱንና የሶማሊያ ህዝብን ጥለን መውጣት ግን አይቻለንም፣ በሶማሊያ የተጀመረውን የእርቅ ሂደት መሻሻል አይተን እንጂ እንዲሁ ጥለናቸው አንወጣም …” የሚል ነው።
የአቶ መለስ ዜናዊ ”ሠላም”
የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሶማሊያ ሲዘምት አቶ መለስ ዜናዊ፣ ”በሣምንታት ውስጥ ተልኳችንን እናጠናቅቃለን …” ያሉት በሶማሊያ ወረራ ኃላፊነት የማይሰማቸው እንደነበሩ ያሳያል። ለጦርነቱ የሚያስፈልገው ወጪ ከገመቱት በላይ መሆኑን አሁን ተገንዝበውታል። በሣምንታት ይጠናቀቃል የተባለው ጦርነት ሁለት ዓመታት ያህል የጦሩን ጥንካሬ ከመፈታተኑም በላይ የሀገሪቱን ውስን ሀብት እየቀነሰው ነው፤ በዲፕሎማሲውም ያሳደረው ጫና የለም።
ጦርነቱ በሚጀመርበት ወቅት ተልዕኮውን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ፣ በአፍሪካ ቀንድ መለስተኛ ኢምፓየር የመመሥረት ሃሳብ ነበራቸው አቶ መለስ። በሶማሊያ ሠላም፣ መረጋጋትና ነፃነት በማምጣት ”ራስን የማኮፈስ” ራዕይ ነበራቸው። በአፍሪካ ቀንድ ሕግን የማስከበር ብቸኛ ኃላፊነት ያለባቸው እሳቸው እንደሆኑ ያስባሉ።
ሶማሊያውያን በኢትዮጵያ በኩል የሚመጣ ሠላም እንደማያስደስታቸው ለማሳየት ሞክረዋል። አቶ መለስ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ወደ ሶማሊያ ጦር የማይልክ ከሆነ ወይም ለኢትዮጵያ ጦር ድጋፍ ካላደረገ ሀገሪቱን ለሥጋት አጋልጦ እንደሚወጣ እያስጠነቀቁ ነው። ይህ ደግሞ ለአልሸባብና ለሌሎች እስላማዊ ፅንፈኞች የልብ ልብ ይሰጣቸውና ሶማሊያን ወደ እርስ በርስ ግጭት ውስጥ ይከታታል፤ የአሸባሪዎች መፈልፈያም ያደርጋታል። ለዘመቻው የመጀመሪያ ጊዜያት የተሰጠው ምክንያትም ይኸው ነበር። ይሁን እንጂ ዓለም ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏል። የአፍሪካ ሕብረት ሀገራት ጦር እንዲያዋጡ ማሳመን ከተጀመረ ሁለት ዓመት ሊሞላው ቢሆንም፣ ከዩጋንዳና ቡሩንዲ በስተቀር ጦር ያዋጣ የለም። ሥልጣን ለማስረከብ የተቃረቡት ፕሬዝዳንት ቡሽም በዚህ የተነሳ አረንቋ ውስጥ መዘፈቅ የፈለጉ አይመስልም። ማንኛውም ወገን በኢትዮጵያ ጦር መውጣት ሊፈጠር የሚችለውን ነገር ለመቀበልም ዝግጁ አይደለም።
አቶ መለስ ከሶማሊያ ለቆ የመውጣቱ ነገር የፈጠረባቸው ጥርጣሬ አለ። አንደኛ፦ ጦሩ ለቆ የሚወጣ ከሆነ በድንገት ሁኔታዎች ተለዋውጠው፣ በሶማሊያ የእርስ በርስ ግጭት ሊፈጠር ይችላል የሚል ነው። ይህ ግን አሳማኝ አይደለም - ሶማሊያ አሁንም የጐሣ ግጭት አለባትና። ዚያድ ባሬ እ.ኤ.አ. በ1991 ዓ.ም. ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ አሁንም ድረስ ሶማሊያ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ነች። ሁለተኛ፦ ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል እየለቀቁ መውጣት ጀሃዲስቶች እንዲጠናከሩ ያደርጋል የሚል ሃሳብ አላቸው። ጀሃዲስቶች አሁንም ቢሆን ደቡባዊ ሶማሊያን የተቆጣጠሩ መሆናቸውና ይዞታቸውን ማስፋታቸው ጥርጣሬውን ውድቅ ያደርገዋል። ሦስተኛ፦ የሽግግር መንግሥቱ ወታደራዊም ኾነ የደኅንነት ኃይል ካልተጠናከረ በእስላማዊ ጽንፈኞቹ በቀላሉ ሊጠቃ መቻሉም አቶ መለስን ያሳስባቸዋል። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ጦር የሽግግር መንግሥቱን ወታደራዊ ተቋማት ለማጠናከር ዓመታት የፈጀ ሥልጠና ሰጥቷል። ከዚህ ይልቅ ለጐሣ የሚኖር ታማኝነትና ወገንተኝነት ችግሩን ሊያወሳስቡት እንደሚችሉ ይገመታል። አራተኛ፦ ያልታቀደ መውጣት የኢትዮጵያን ጦር ተጋድሎ ዋጋ ቢስ ያደርጋል፣ ደጋፊዎቻችንና ሶማሊያን ለአደጋ ያጋልጣል፣ የጦሩንም ሞራል ይጐዳል … የሚል ነው።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያውያን ደጋፊዎቹ እንኳ ከጥቃት መታደግ አልቻለም። ጦርነቱ የህዝብ ድጋፍ አላገኘም። ጦሩ የነበረው አማራጭ በሶማሊያ መቆየት፣ ጦርነቱን ማሸነፍ፣ መሸነፍ ወይም ሞራል መጠበቅ ነው። የሚያሳምመው እውነት የሶማሊያ ወረራ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጋር ያልተያያዘ መሆኑ ነው። ወረራው በዓለም አቀፍ ሕግ ተቀባይነት የሌለው፣ ትልቅ ፖለቲካዊ ስህተት ነው። ሌላን ሀገር ወርሮ ለሠላማዊ ሰዎች ሕልፈትና መፈናቀል ምክንያት መሆን በሞራል ደረጃም ስህተት ነው።
የመውጫ ስትራቴጂ
የአቶ መለስ ህልም የተረጋጋች፣ ዲሞክራሲ የሠፈነባት፣ ጠንካራ የሕገመንግሥት ጥበቃ ያላት አንዲት ሀገር በሶማሊያ በረሃ (የበረሃ-ገነት) መመሥረት ነው። በሁለት ዓመት ውስጥ እንኳ በሶማሊያ በ17 ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ፣ ዲሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ለመመሥረት አልቻሉም። እጃቸውን በማስረዘም በኢትዮጵያ እንዳደረጉት በሶማሊያም የከፋፍለህ ግዛ ስትራቴጂ መመሥረት ይፈልጋሉ። ይህ ግን የሚሆን አይመስልም በመሆኑም በዚህ ጨዋታ አቶ መለስ የሚኖራቸው ምርጫ አንደኛ በፍጥነት ከሶማሊያ መውጣት ሲሆን፣ ምክንያታዊ የሚሆነውም ይኸው ነው። ይህም አሣጥሮ መሮጥ (cut and run) ሲሆን፣ የሚደርስ ኪሳራን በመቀነስ ለቅቆ መውጣትን ያመለክታል። ተንታኞች ግን ቀስ በቀስ መውጣት አማራጭ መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
ሌላው አማራጭ የፀረ-ጀሃድና የፀረ-ሽብር ዘመቻው ደም አፋሳሽ፣ ወጪ ጠያቂ የልማት ችግር መሆኑን አምኖ እዚያው መቆየት ነው። ይሁን እንጂ ጀሃዲስቶቹ ደግሞ ብዙ አካባቢዎች እየተቆጣጠሩና ሞቃዲሾን ለመያዝ እየገሰገሱ መሆናቸው አስቸጋሪ ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና የሽግግር መንግሥቱ ፓለቲካዊ አመራር የሚሰጡበት፣ አስተዳደራዊ ሥራዎች የሚያከናውኑበት፣ ሕግና ሥርዓት የሚያስከብሩበት የተወሰነ አካባቢ አለ፤ ግን ይህ እስከ መቼ ይቀጥላል? የሚለው ስትራቴጂ ይዞታቸውን ለመተው ሊገደዱ እንደሚችሉ ያሳያል።
ሦስተኛው አማራጭ አካባቢያዊና ዓለማቀፋዊ ጫና ለማሳደር መሞከር ነው። ጥያቄው ግን በዚህ በኩል ማን ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል የሚለው ነው። የአፍሪካ ሕብረት እንኳ ቃል የገባውን ሠላም አስከባሪ ለማቅረብ አልቻለም። የተባበሩት መንግሥታትም የሞራል ድጋፍ ከመስጠት ውጪ ምንም ማድረግ አልቻለም። ጽ/ቤት ተቀምጦ ጀሃዲስቶቹን ከማውገዝ ውጪ ምንም አላከናወነም። በአራተኛ ደረጃ የሽግግር መንግሥቱ ከጀሃዲስቶቹ ጋር እንዲሠራ መተው ሲሆን፣ የመንግሥትን ሥራ የሚያከናውን መንግሥት አለመሆኑ በራሱ ችግር ነው።
በአንድ በኩል ራሱን የሚከላከል የተደራጀ ሠራዊት የሌለው ሲሆን፣ በሌላ በኩል የጎሣና የኃይማኖት መሪዎች እንዲሁም ተቃዋሚዎች፣ ለሽግግር መንግሥቱ ድጋፍ አለመስጠታቸው በስም ብቻ ላለው መንግሥት አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጥራል። አምስተኛው አማራጭ ከጀሃዲስቶች ጋር የማይግባቡበትን ስትራቴጂ ይዞ መቀጠል ነው። ይህ ደግሞ አደገኛው ስትራቴጂ ሲሆን፣ በሶማሊያ የውጭ ኃይል መቆየቱ ተቃውሞ ሊቀሰቅስ፣ የሠላማዊ ዜጎች ሕይወት ሊቀጥፍና ወታደራዊ ኪሣራ ሊያስከትል ይችላል። ቢሆንም የተመረጡ ዘመቻዎችን በማካሄድ ታጣቂዎች ላይ ጫና ማሳደር ይቻላል።
የፍፃሜው ጨዋታ ከሶማሊያ መውጣት
ኢትዮጵያም ሆነች ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከሽብር ሥጋት ነፃ መሆን ይፈልጋል። የአቶ መለስ ጥያቄም ሶማሊያን ለቆ በመውጣት ቀድሞ ወደነበረችበት የጎሣ ጦርነት እንድትመለስ ማድረግ ይገባል ወይ? የሚል ነው። አቶ መለስ የሽብርተኝነት ነበልባልን በማሳየት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለዘመቻቸው ድጋፍ ማግኘትና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊጣል የሚችልባቸውን ማዕቀብ ማስወገድ የሚፈልጉ ቢሆንም፤ በሶማሊያ ጦርነት ሠላም የማግኘት ስትራቴጂያቸው ሙሉ በሙሉ አልተሳካም። ይህም ”ጦርነትን በፈለግኸው ጊዜ መጀመር ትችላለህ፣ በፈለግኸው ጊዜ ግን መቋጨት አትችልም” የሚለውን የቆየ ብኂል ያስታውሰናል።
የአቶ መለስ ችግርም የሶማሊያን ጦርነት እንዴት ማጠናቀቅና መውጣት ይቻላል የሚል ነው። ዋነኛ ግቡ ግን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለኢትዮጵያውያንም ሆነ ሶማሊያውያን ሞትና መፈናቀል ምክንያት ሳይሆን ከሶማሊያ ያለ ችግር እንዲወጣ ማድረግ ነው።
ፕሮፌሠር አለማየሁ ገብረማርያም ሳን በርናርዲኖ በሚገኘው የካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የፖለቲካ ሣይንስ መምህር ናቸው።
ማስታወሻ፦ ፕ/ር አለማየሁ ገ/ማርያም “The End of Pax Zenawi in Somalia” በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ያቀረቡትን ጽሑፍ ለአማርኛ አንባቢዎች ይደርስ ዘንድ ወደ አማርኛ በመተርጎም የቀረበ ነው።
- ኢትዮጵያ ዛሬ