የምርጫ ሌባ (ፕ/ር ዓለማየሁ ገ/ማርያም)
ሌባ! ሌባ! ያዘው የምርጫ ሌባ!
ፕሮፌሠር ዓለማየሁ ገ/ማርያም
የታይላንድ ሕገ መንግሥታዊ ፍ/ቤት ባለፈው ሣምንት በምርጫ ያጭበረበሩ ሌቦችን ጉዳይ ተመልክቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሶምቻይ ዎንግስዋትና የስድስት ጥምር ፓርቲው አመራሮች በታኅሳስ 2007 ዓ.ም. በሀገሪቱ የተካሄደውን ምርጫ አጭበርብራችኋል በሚል ጥፋተኛ ብሏቸዋል። ግለሰቦቹ ጥፋተኛ የተባሉት የመራጮችን ድምፅ በመግዛት፣ ድምፅ በማጭበርበር፣ መራጮች የሚሰጡትን ድምፅ በማሳሳትና ሌሎች የምርጫ የማጭበርበር ተግባራት በመፈፀም ነው።
የታይላንድ ሕገመንግሥታዊ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቻት ቾን ላዎርን እንደገለጹት የህዝብ ኃይል ወይም (Peoples Power) የተሰኘው ፓርቲ እንዲፈርስ የተወሰነ ሲሆን፣ የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚዎቹ ለአምስት ዓምታት ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ታግደዋል። ችሎቱም ይህን ውሳኔ ከማሳለፍ ውጪ አማራጭ እንዳልነበረው ገልጿል። ይህም የታይላንድ ሕገመንግሥታዊ ፍርድ ቤት ኃላፊነት ነው ብለዋል። የችሎቱ ፕሬዝዳንት እንዳሉት የሶምቻይን ጥምር መንግሥት ማፍረስ አስፈላጊ ኾኖ የተገኘው ፖለቲካዊ ወጥነትን ለማምጣትና አርኣያ የኾነ ሥራ ለመሥራት ነው። ታማኝ ያልሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የታይላንድን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ያራክሳሉ ብለዋል። በውሳኔው ሶምቻይን ጨምሮ 60 የፓርቲ አመራሮችና የፓርላማ አባላት ለአምስት ዓመታት ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ሕገመንግሥታዊ ችሎቱ ውሳኔ አሳልፏል።
ከሌቦች መካከል ለሕግ የሚገዙ አሉ!
ሶምቻይ ከውሳኔው በኋላ ”ጥፋቱ የኔ አይደለም፣ እኔ ይህን ያደረግኩት ለኔ አይደለም ቢሆንም ግዴታዬ እዚህ ላይ ተጠናቋል፤ እኔም የሙሉ ሰዓት ዜጋ ሆኛለው” ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕገመንግሥታዊ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን እስከሚያሳልፍ ድረስ ለወራት ድርጊቱን ክደው ነበር። ተቃዋሚዎች ግን የታይላንድ ፓርላማ ግፊት እንዲያደርግ በመገፋፋት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ሶምቻይ መንግሥት ሥልጣን እንዲለቅ ተፅዕኖ ለማሳደር የባን አየር ማረፊያን እስከመዝጋት የደረሰ እርምጃ ወስደው ነበር።
በመጨረሻ ግን ከሌቦች መካከል ለሕግ የሚገዙ ታማኞች ተገኙ። የመንግሥት ቃልአቀባይ ናታውት ሳይካአ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩና የስድስት ጥምር ፓርቲ አመራሮች የሕገመንግሥታዊ ችሎቱን ውሳኔ ለመቀበል ተስማሙ። ”ለሕግ እንገዛለን” አሉ። የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮቹ ተገናኝተው በቀጣይ ስለሚኾነው ነገርም ለመምከር ወሰኑ። በታይላንድ የሕግ የበላይነት መከበሩ እንግዳ ነገር አይደለም፤ የሀገሪቱ ሕገመንግሥት በሀገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባትና ለማስፈፀም ጠንካራና የተሟላ ነው። ሙስናን ለመዋጋት የሚያስችል ሕገመንግሥታዊ ሥልትና፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚመሩበት ሙያዊ ሥነምግባርና ምርጫ በሐቀኝነት የሚካሄድበት ሥርዓት ሕገመንግሥቱ አካቷል። ገለልተኛ የኾነው የምርጫ ኮሚሽን ያለውን ሥልጣንና ኃላፊነትም በሕገመንግሥቱ ተደንጓል። ለምሳሌ የምርጫ ኮሚሽኑ አንድን ዕጩ የሚሰርዝበት፣ ዳግም ምርጫ የሚጠራበት፣ ምርጫው በፍትሃዊነትና በሐቀኝነት ላለመካሄዱ መረጃ ሲኖረው ምርጫው ወይም የተወሰነው የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ እንዲደገም የሚወስንበት ሥልጣን አለው።
የታይላንድ መንግሥት ሕግ አስፈፃሚው፣ ሕግ አውጪውና የዳኝነት አካሉ የሚመሩበት ሕገመንግሥታዊ የሥነምግባር መርሆዎች አሉት። ለምሣሌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ካቢኔው፣ ሕግ አውጪዎቹ ወይም ዳኞቹ ከማንኛውም የንግድ ሥራ ጋር የሚያያይዝ የገንዘብ ትስስር ወይም ጥቅም እንዲኖራቸው አይፈቀድም። የጥቅም ግጭት በሚያስነሱ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ እንዲገቡ ወይም ሕግን ባልተከተለ ቅጥር፣ ዝውውር፣ ሹመት ዕድገት ወይም ስንብት ውስጥ እጃቸውን እንዲያስገቡ አይፈቀድም። የታይላንድ ሕገመንግሥት በርካታ የሥነምግባር ክልከላዎችን በባለሥልጣናቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በትዳር ጓደኞቻቸው እና በልጆቻቸው ላይም ያስቀምጣል።
የሕገመንግሥቱ የፀረ-ሙስና ድንጋጌዎችም ቁርጥ ባለ ቋንቋ የተገለፁ ናቸው። ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሚኒስትር ወይም የተወካዮች ም/ቤት አባል የሚሆን ወይም ሌላ የመንግሥት ሥልጣን የሚይዝ ግለሰብ በሥልጣን የሚባልግ ከኾነ ከኃላፊነቱ እንደሚሰናበት በግልፅ ተደንግጓል። የሙስና ወንጀሎች የሚጣሩት ነፃ በኾነ ብሔራዊ የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሲሆን፣ ኮሚሽኑ ጥቆማዎችን የማጣራት፣ መረጃ የመሰብሰብ፣ አስፈላጊ ሲሆን ሴኔቱ እንዲወያይበትና የሥራ ማስወገድ ውሳኔ እንዲወስን ሊያደርግ ይችላል። የፀረ-ሙስና ኮሚሽኑ በቂ ምክንያት (ጥርጣሬ) ሲኖረው ግለሰቡ ከኃላፊነቱ እንዲታገድ በአብላጫ ድምፅ በመወሰን የሴኔቱን ውሳኔ የሚሽርበት ሥልጣንም አለው። የታይላንድ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ታክሲን ሺንዋትራ ከሀገር በመውጣት በብሪታንያ ፖለቲካዊ ጥገኝነት የጠየቁት በሙስና ወንጀል ላለመጠየቅ ነበር። አንድ ባለሥልጣን በሙስና ተከሶ በኃላፊነቱ ከተነሳ (ከታገደ) በኋላ ጥፋተኛ ቢባል ከተመራጭነቱ ወይም ከመንግሥት ኃላፊነቱ አምስት ዓመታት ሊታገድ ይችላል።
ሼክስፒር በጁልየስ ቄሳር ተውኔቱ እንደገለፀው ”ተወዳጁ ብሩተስ ስህተቱ የተፈጠረው በአለቆቻችን ሳይሆን በኛ ምክንያት ነው” ብሎ ነበር። የሀገራት እና የህዝቦች ዕጣ ፈንታ የተቀረፀው በዕድል ወይም በሀብት መዘውር ላይ አይደለም። ሀገራት የሚገነቡት ወይም የሚፈርሱት ዜጐቻቸው ማድረግ ያለባቸውን ሲሠሩ ወይም ማድረግ የሌለባቸውን ሳያደርጉ ሲቀሩ ነው።
የታይላንድና የኢትዮጵያ ዕድል ፈንታም የተመሠረተው በመሪዎቻቸው ላይ አይደለም፤ በህዝቦቻቸው ላይ እንጂ። ታይላንድም አስቀድሞ ዕድሏ የተወሰነው በመተግበር ላይ ባለው ዲሞክራሲ አይደለም። ኢትዮጵያ ከአምባገነኖች በሚሰነዘርባት ፍላፃ ስትወጋ ቆይታለች። በእርግጥ ታይላንድ፣ የሚጠቀሱ ወታደራዊ አምባገነን መሪዎችና መፈንቅለ መንግሥት ከ1930ዎቹ ጀምሮ ተካሂደውባታል። ይሁን እንጂ ጥቂት አምባገነኖች በቅርቡ የተወገዱትን ታክሲ ሺንዋትራን ጨምሮ ለተወሰኑ ጊዜያት በሥልጣን ላይ ቆይተዋል። አምባገነኖቹ የተወገዱት በታይላንድ ህዝብ፣ በነፃና በማያወላውል የፍትህ ሥርዓቱ፣ በነፃ የምርጫና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ነው። በዚህም ከወታደራዊ አምባገነኖች ጋር የተሰለፉ ሳይቀሩ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት እንዲመሠረት ፍላጐታቸውን አሳይተዋል።
ወታደራዊ አምባገነኖችም ለህዝብ ድምፅ (ውሳኔ) መገዛት ጀምረዋል። በባንኮክ አየር ማረፊያ በተካሄደው ተቃውሞ ከተሳተፉት መሃል ቶንክላ ማክሱክ የተባለች ነርስ እንደገለፀችው ሕገመንግሥታዊ ችሎቱ ጠ/ሚ ሶምቻይ እና የምርጫ ዘራፊዎቹን በማገዱ ተደስታለች። ”ሀገሪቱ ሕግ የሚከበርባት መሆኗ ይሰማኛል” ብላለች።
ማንም ሰው የ1997ቱን የኢትዮጵያ ምርጫ ከታይላንድ የሕገመንግሥት ችሎት ውሳኔ ጋር እንዲሁም የምርጫና የፀረ-ሙስና ኮሚሽኑን በታይላንድ ካለው ጋር አያይዞ ሊያስበው ይችላል። 67 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ታይላንድ ዲሞክራሲ እያደገና እያበበባት ለመሆኑ ሕያው ምሳሌ ሆናለች። ከታይላንድ ልምድ በእርግጠኛነት ልንማር የምንችለው ዲሞክራሲ የተጠማዘዘ የምሁራን የፖለቲካ ጨዋታ አለመሆኑን ነው። ዲሞክራሲ የህዝብ ሉዓላዊነት የነገሠበትና ሕግ የበላይ የሆነበት ሥርዓት ነው። ቶማስ ጄፈርሰን እንደጠቀሰው ”ህዝብ የሚራራ ከኾነ ሥርዓቱ የአፈና ነው፤ መንግሥት ህዝቡን የሚፈራ ከኾነ ሥርዓቱ ነፃነት ወይም ዲሞክራሲ ነው።” የሕግ የበላይነት ከሰፈነ፣ ነፃና ገለልተኛ የዳኝነት አካል፣ የምርጫና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ካለ የህዝብ መብት ተከብሯል፤ መንግሥትም ህዝቡን ይፈራል።
ፕሮፌሠር አለማየሁ ገብረማርያም ሳን በርናርዲኖ በሚገኘው የካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የፖለቲካ ሣይንስ መምህር ናቸው።
ማስታወሻ፦ ፕ/ር አለማየሁ ገ/ማርያም “To catch an election thief” በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ያቀረቡትን ጽሑፍ ለአማርኛ አንባቢዎች ይደርስ ዘንድ ወደ አማርኛ በመተርጎም የቀረበ ነው።
- ኢትዮጵያ ዛሬ