የኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ዕድሜው አጭር ከመሆኑ ባለፈ የተደራሽነት (Access)፣ የተገቢነት (Relevance) እና የጥራት (Quality) ችግሮች አሉበት። በተለይ የትምህርት ጥራት መጓደል የትምህርት ዘርፉንም ሆነ ከዘርፉ የሚገኙትን ግብዓቶች በስፋት በሚጠቀሙ ተቋማት ውስጥ እየተስተዋለ ነው።

 

የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ጥናት መድረክ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች ላይ የየዘርፉ ምሁራን አስተያየትና ትንተናዎችን በማሰባሰብ ባሳተመው መጽሐፍ ላይ አምዲሳ ተሾመ የተባሉ ምሁር በትምህርት ፖሊሲው ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች ላይ ዳሰሳ አድርገዋል። አቶ አምዲሳ እንደሚሉት በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የሚታየው የጥራት መጓደል የሁሉም መንግሥታት የረጅም ዓመታት ችግር ነው። ለምሳሌ ብንጠቅስ በኃይለሥላሴ ዘመን በ1963 ዓ.ም. የትምህርት ዘርፍ ማሻሻያ መተግበር የጀመረ ሲሆን፤ መሠረታዊ ትምህርት ለሁሉም፣ ትኩረት ለሣይንስ፣ ትምህርትና ልማት፣ የትምህርት ጥራትና የተሟላ ማኅበረሰብ መፍጠር የሚሉ ዓላማዎችን ማሳካት የማሻሻያው ግቦች ነበሩ። ይሁን እንጂ የትምህርት ዘርፍ ማሻሻያው፣ በመሠረታዊ መልኩ የትምህርት ሥርዓቱን ችግሮች አይፈታም የሚል ተቃውሞ ከመምህራኑ ተነስቶ እንደነበር የታሪክ ድርሣናት አስፍረዋል።

 

የደርግ ሥርዓትም ትምህርት የፖለቲካ ዓላማዎቹን እንደሚያሳካለት በመረዳቱ፣ በአሥር ዓመት ውስጥ ቀድሞ የነበሩ የትምህርት ተቋማትን መቶ በመቶ ለማሳደግ ችሏል። የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ በማካሄድ ከዩኔስኮ ”International Reading Association literary prize” የተባለ ሽልማት በ1972 ዓ.ም. ለማግኘት በቅቷል። አዳዲስ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሲገነቡ ለመጀመሪያ ጊዜ የድኅረ-ምረቃ ትምህርት መሰጠት ተጀምሯል። ይሁን እንጂ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ በኮታ መሆኑና በአብዛኛው የስኮላርሺፕ ተጠቃሚ የሚሆኑ ምሁራን የሶሻሊስት ርዕዮተ-ዓለምን ከሚከተሉት ሶቭየት ሕብረት፣ ጀርመን፣ ኩባና መሰል ሀገራት በመሆኑ ምሩቃኑ አመለካከታቸው የሚቃኘው በሶሻሊስት ርዕዮተ-ዓለም ላይ ነው።

 

የደርግ ሥርዓተ ትምህርት በሶሻሊስት ርዕዮተ-ዓለም ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ የተገነቡት የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶችም ደረጃቸውን የጠበቁ እንዳልሆኑና መምህራኑም በቂ ሥልጠና ያላገኙ እንደነበር ይጠቀሳል።

 

ደርግን በማስወገድ መንበረ ሥልጣኑን የተቆናጠጠው በኢህአዴግ የሚመራው የሽግግር መንግሥቱ በ1987 ዓ.ም. የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ አዘጋጅቶ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል። ይህ ፖሊሲ ለትምህርት መስፋፋት፣ ለተለያዩ የትምህርት ተቋማት መገንባትና ለግሉ ዘርፍ ተሣትፎ በር ከፍቷል። ኢህአዴግ ሀገሪቱን ሲቆጣጠር ከነበሩት ሁለት የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ውጪ ምንም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለይ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ባይኖሩም፣ በአሁኑ ወቅት 20 የሚሆኑ የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች፣ ከ70 በላይ የግልና መንግሥታዊ ያልሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሉ። የፖሊሲው ግቦች እንደ እኩልነት፣ ነፃነት፣ ፍትሐዊነት፣ እውነት፣ የሰብዓዊ መብት መከበርን የመሳሰሉ ዲሞክራሲን ማስረጽ የሚል ሲሆን፤ ዓላማዎቹ በዝርዝር ሲታዩ ተማሪዎችን በቀለም ትምህርት ከማብቃት ይልቅ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው።

 

በዘርፉ ብቃት ያላቸውና ለሚሰጡት የትምህርት ዓይነቶች የማይመጥኑ መምህራን፣ አንድም ከትምህርት ቤት በቀጥታ የተመረጡ፣ አንድም ከየወረዳው በፖለቲካዊ ብቃታቸው የተመለመሉ መሆናቸው የጥራቱን ጉዳይ ከመግደሉም በላይ ከታሰበው ግብ ለመድረስ የማይቻል ነው ማለት በቂ ምክንያት ሊሆን ይችላል።

 

እርግጥ ነው በርካታ አዳዲስ ዩኒቨርስቲዎች እየተገነቡ ሥራ ጀምረዋል። ይሁን እንጂ እንኳን አዳዲሶቹ፤ ነባሮቹ ዩኒቨርስቲዎችም ውስጣዊ አደረጃጀታቸው የተሟላ አይደለም። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 3ኛ ዓመት የሶሻል ሣይንስ ተማሪ የሆነው ምህረት አበበ ዩኒቨርስቲው ከመማሪያ ሕንፃ በቀር ብዙ ነገሮች እንደሚጐድሉት ያምናል፤ በመምህራኑ ብቃት ላይም ጥርጣሬ አለው፤ እንዴት በዩኒቨርሲቲ ለማስተማር እንደታደሉም ይጠይቃል።

 

የኢንተርናሽናል ሊደርሺፕ ተቋም መሥራችና ፕሬዝዳንት ፕሮፌሠር ባደግ በቀለ፣ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፣ በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት መጓደል እንደሚታይ ገልፀዋል። ለጥራት መጓደሉም ከፍተኛ ነጥብ ያመጡ ተማሪዎች በዩኒቨርስቲው በመምህርነት እንዲያስተምሩ መደረጉ የመምህራን እጥረት መሆኑን ይገልፃሉ። በሌላው ዓለም የቢ.ኤ. ዲግሪ ያለው የማስተርስ ዲግሪን አያስተምርም፤ እንዲሁም የማስተርስ ተማሪ የፒ.ኤች. ዲግሪን አያስተምርም። በኢትዮጵያ ግን ይኼን መመልከቱ የተለመደ ከመሆኑም በላይ ለትምህርት ጥራት መጓደሉ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ነው ያመለከቱት።

 

እንደ ፕሮፌሠር ባደግ ገለፃ ከትምህርት ጥራት መለኪያዎች መካከል የአስተማሪዎች ብቃትና የትምህርት ማስተማሪያ አጋዦች (ቤተ መጻሕፍት፣ ኢንተርኔትና የመሳሰሉት) ይጠቀሳሉ፤ የትምህርት ጥራት መጓደል ከተማሪዎች የተወዳዳሪነት አቅም ማነስ ጋር የሚያያዝ ሲሆን፣ መንግሥት ከመጠን በላይ ተማሪ በመቀበል ላይ ማተኮር ሳይሆን ከተቋማቱ ጋር ተመጣጣኝ ተማሪ በመቀበል ተወዳዳሪ ማድረግ ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ይላሉ።

 

ሌላው ለትምህርት ጥራት መጓደል መንስዔ ሊሆኑ ከሚችሉት ጉዳዮች መካከል፣ የትምህርት ፖሊሲው መንግሥት በተለወጠ ቁጥር ለሥርዓቶቹ እንዲመች ተደርጎ መለዋወጡ ነው። በአብዮቱ ዋዜማ የትምህርት ዘርፍ ማሻሻያ (Educational Sector Review) የተደረገ ሲሆን፣ በደርግ ዘመንና አሁን ባለው በኢህአዴግ ዘመን የተለያዩ የፖሊሲ ለውጦች ተደርገዋል። ይህ ሲሆን ታዲያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የተማሪዎች ችሎታና ተፈጥሮዓዊ ክህሎትን ግምት ውስጥ ያስገባ ጥራት ያለው ትምህርት የመስጠቱ ጉዳይ ነው።

 

በቅርቡ እንኳ የ70/30 ፖሊሲ ተቀርጾ ለተፈጥሮ ሣይንስና ቴክኖሎጂ የበለጠ ትኩረት እንደሚሰጥ ከተገለፀ በኋላ፣ መንግሥት ፖሊሲውን ለመተግበር ወደኋላ አፈግፍጓል። በአንድ በኩል መንግሥት የቀረፀው ፖሊሲ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ የሰው ኃይል በብዛት የሚያስፈልግ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ቢያብራራም፣ በሌላ በኩል ፍላጐት ከጥራት ጋር አብሮ ሊሄድ እንዳልቻለ በመረዳት ይመስላል፣ በየጊዜው የሚታዩ ውጤቶችን መሠረት አድርጐ ወደ 70/30 ትግበራ እንደሚገባ ያስታወቀው። ዋናው ጥያቄ ግን “የሀገሪቱን ዕድገት ሊያፋጥን የሚችል የትምህርት ፖሊሲ ለምን አይቀረፅም?” የሚል ነው። የትምህርት ፖሊሲው መንግሥታት የፖለቲካ ጥቅም ማራመጃና የሥርዓታቸው አቀንቃኝ መፍጠሪያ ባደረጉት ቁጥር፣ የትምህርት ጥራት መጓደሉ አይቀሬ ነው። እርግጥ ነው የአንድ ሀገር የትምህርት ፖሊሲ ሀገሪቱ ከምትገኝበት ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት።

 

የትምህርት ፖሊሲውን ለማስፈፀም የተቀረጹ ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች

 

የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲው የተቀረፀበትን ግብ ለመምታት እንዲያስችል በሚል ስትራቴጂዎችና ዝርዝር ፕሮግራሞች ተነድፈዋል። ስትራቴጂው ሁሉንም የትምህርት ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ካሪኩለም መንደፍ፣ አዲስ የትምህርት አሰጣጥ መዋቅር የማስተዋወቅ፣ (የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ከ6-8 ውስጥ እንዲጠናቀቅ፣ የመማሪያ ክፍሎች ከ1-4፣ የመጀመሪያ ሳይክል ከ5-8ኛ፣ ሁለተኛ ሳይክል ሁለተኛ ደረጃ ከ9-10፣ የመሰናዶ ትምህርት ከ11-12፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና (TVET) ያካተተ ሲሆን፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ምርምርን መሠረት ባደረገ ሥልጠና የዲፕሎማ፣ የዲግሪና የድኅረ-ምረቃ ትምህርት እንደሚሰጥ ይጠቅሳል)። ስትራቴጂው ከ1-3ኛ ክፍል ተማሪዎች ያለ ምንም ምዘና በ(automatic promotion) እንዲያልፉ የሚያደርግ ሲሆን፣ መንግሥት የደጋሚና የትምህርት አቋራጭ ተማሪዎችን ቁጥር መቀነስ ላይ ትኩረት ያደረገ ይመስላል።

 

የፖሊሲው ማስፈፀሚያ ስትራቴጂዎች ወደ ተግባር የሚሸጋገሩትም፣ በትምህርት ዘርፍ የልማት ፕሮግራሞች ሲሆን፣ በፖሊሲው መሠረት ሦስቱ የትምህርት ዘርፍ ፕሮግራሞች ተቀርፀው ሁለት ተተግብረዋል።

 

ሦስተኛው ዘርፍ ደግሞ በመተግበር ላይ ይገኛል። ይህ ፕሮግራም መንግሥት የትምህርት ተደራሽነት፣ ተገቢነት፣ ጥራትና ፍትሐዊነትን ለማሻሻል እንደሚያስችል መንግሥት በርግጠኝነት የሚናገርለት ፕሮግራም ነው።

 

መንግሥት ከሚሊኒየሙ የልማት ግቦች ጋር ተያያዥነት ያላቸው የሚመስሉትን ስትራቴጂዎችን ለማሳካት፣ በስፋት ይንቀሳቀስ እንጂ በኢትዮጵያ የት/ቤቶች የውስጥ ድርጅት ያለመሟላታቸውና ሥርጭታቸውም ፍትሐዊ ያለመሆኑ፣ በሁሉም ደረጃ የቅበላ መጠኑን ለማሳደግ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት አላስቻለም። ለምሣሌ የመጀመሪያው የትምህርት ልማት ፕሮግራም በተተገበረባቸው ዓመታት የአ/አ የቅበላ መጠን 83% ሲደርስ፣ የአፋር 8% ላይ ተገድቦ መቅረቱ፣ በአርብቶ አደር አካባቢዎች ሴቶች እንደተለመደው ወደ ት/ቤት አለመግባታቸው በዕቅዱ ላይ የታዩ ችግሮች ነበሩ። ከሁሉ በላይ የትምህርት ጥራት የማሽቆልቆሉ ነገር እንዲሁ በዋዛ የሚታይ አልሆነም። መምህራን በቂ ሥልጠና ሳያገኙ፣ የመማሪያ መጽሐፍትና የትምህርት ቁሳቁስ ሳያሟሉ፣ ተገቢ የፈተና (የምዘና) ሥርዓት ሳይዘረጋ ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ ላይ ብቻ ያተኮረ ትምህርት እንዲከታተሉ መደረጉ፣ ለትምህርት ጥራቱ መጓደል በምክንያትነት ሊጠቀስ ይችላል።

 

በሁለተኛው የትምህርት ልማት ፕሮግራም፣ የትምህርት ጥረትን ለማስጠበቅ መንግሥት በተለያዩ የትምህርት ዓይነቶች የሬድዮ ፕሮግራም ማዘጋጀትና ማሠራጨት፣ ቤተመጻሕፍትን ማደራጀት፣ የተማሪ-ክፍል ጥመርታን ወደ 1ለ60 ማሳነስ፣ ICT ማስጀመርና 7 ሺህ የሚሆኑ መምህራን የሥራ ላይ ሥልጠና በመስጠት ዲግሪ እንዲያገኙ ማድረግ የሚሉት ፕሮግራሙ ሲተገበር ታሳቢ ያደርጋቸው ጉዳዮች ነበሩ።

 

አሁን እየተተገበረ ያለው ሦስተኛው የትምህርት ልማት ፕሮግራም፣ ከሁለቱ ፕሮግራሞች ጋር የሚመሳሰል ሲሆን፤ የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂን ለማሳካት በሚያስችል መልኩ የተነደፈ መሆኑን መንግሥት ይጠቅሳል። በዚህም የትምህርትን ጥራት ማሻሻል እንደሚችል ያምናል።

 

ይሁን እንጂ በቅርቡ የተሰማው ዜና አስደንጋጭ ነው። የትምህርት ጥራት መጓደልን ለማሻሻል መንግሥት ትኩረት ሰጥቻለሁ ሲል ለውጡን ለመመልከት ሁሉም የመጓጓቱን ያህል በሀገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ ክልል ወረዳዎች በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ሲያገለግሉ የነበሩ የዲግሪ ምሩቃን፣ የዩኒቨርስቲ መምህራን ሆነው መመደባቸው የትምህርት ጥራቱን ከድጡ ወደማጡ ሊወስደው ይችላል። የተመለመሉት የመንግሥት ሠራተኞች ውጤታቸው ከ2 ነጥብ 75 በላይ እንዲሆን መጠየቁም በትምህርታቸው ከፍተኛ ነጥብ በማምጣት በዩኒቨርስቲዎች ሰቅለው ከሚቀሩት ጋር ሲነፃፀሩ ደከም ያሉ ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዩኒቨርስቲዎች የሚያስተምሩ የመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቃን፣ የመበርከታቸው ጉዳይ የትምህርት ጥራት መጓደል ከመሆን ባለፈ የሥርዓቱን ችግርም ያሳያል።

 

በተቀረፀው የትምህርት ፖሊሲ አማካይነት የትምህርት ተደራሽነት፣ ተገቢነትና ጥራቱ ለማሳደግ መንግሥት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እንዳለው ለማሳየት ሞክሯል። ይሁን እንጂ ፖሊሲው ሲተገበር ክፍተቶች ያሉበት ለመሆኑ በርግጠኛነት መናገር ይቻላል። ለምሣሌ ያህል የትምህርት ይዘቱ ምን ይምሰል? የትምህርት ማጠናቀቂያ ጊዜ እንዴት ይሁን? የትኛው የትምህርት ዘርፍ ትኩረት ይሰጠው የሚሉና መሰል ጉዳዮች ከባለድርሻ አካላት ጋር ያልተመከረባቸውና ከላይ የወረዱ መሆናቸው (Top-down) ለወላጆች፣ ለመምህራንና ለተማሪዎች እንግዳ የመሆኑ ጉዳይ ካለፉት ሥርዓቶች የትምህርት ፖሊሲ የማይለይበትን ሁኔታ ያሳያል።

 

መንግሥት በትምህርት ፖሊሲው አገኘኋቸው የሚላቸው ውጤቶች

 

በመጀመሪያዎቹ ሁለት የትምህርት ልማት ፕሮግራሞች፣ ተደራሽነትን በማሳደግ በኩል ውጤት መገኘቱን መንግሥት ይገልፃል። በገጠር አካባቢዎች ሳይቀር ት/ቤቶች በቅርበት እንዲከፈቱ መንግሥት ከለጋሾችና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ያደረገው ጥረት አጠቃላይ የቅበላ መጠኑን እንዳሳደገለትም መረጃ ያጣቅሳል።

 

በሁለቱም ፕሮግራሞች ጥራትን በማስጠበቅና ተገቢነትን በማረጋገጥ በኩል መንግሥት ስኬት እንዳስመዘገበ ያስታወቀ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ፕሮግራሙ ለተደራሽነት ትኩረት ሲሰጥ በመጠኑም ቢሆን ለጥራት ትኩረት ያለመስጠቱን አምኗል። አቶ አምዲሳ ተሾመ በጥናታቸው የመንግሥት መምህራን ደረጃቸውን እንዲያሳድጉ የሚሰጠው ሥልጠና በመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች የመጀመሪያ ሳይክል ለማስተማር ብቁ የሆኑ መምህራንን ቁጥር ከ85% ወደ 96 በመቶ፣ ለሁለተኛ ሳይክል ደግሞ ከ21% ወደ 54% ከፍ ብሏል። ይሁን እንጂ በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች የታየው ስኬት አመርቂ አይደለም። ምክንያቱ ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ የሚያስተምሩ መምህራን ብቃትን ከ40 በመቶ ወደ 61 በመቶ ከፍ ለማድረግ የታቀደ ቢሆንም፣ በፕሮግራሙ የመጨረሻ ዓመት ላይ ብቁ የነበሩ መምህራን በመቶኛ 36 በመቶ ብቻ ነበር።

 

በሁለተኛው የትምህርት ልማት ፕሮግራም፣ የመጀመሪያ ደረጃ ብቁ መምህራን ቁጥር 97.1 በመቶ ሲያድግ፣ የሁለተኛ ደረጃ ግን የጐላ ለውጥ ሳያሳይ የሥራ ላይ ሥልጠና እየተሰጠ ጭምር ከ54.8 በመቶ ከፍ ሊል አልቻለም። በመሆኑም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይሰጡ የነበሩት ትምህርቶች በጥራት ተሰጥተዋል ለማለት የሚከብድበት ጊዜ ነበር። የተማሪ መጽሐፍ 1 ለ1 /ለማዳረስ/ የታለመ ቢሆንም እዚህም ላይ ለመድረስ ቀላል አልሆነም።

 

በቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት (TVET) የሚሰጠው ትምህርትም ጥራቱን ያልጠበቀ መሆኑ ከየተቋማቱ ከወጡ ተማሪዎች እና ከመምህራኖቻቸው መረዳት ይቻላል። ታደሰ ገብረወልድ የተባሉ ፀሐፊ (ፀሐፊው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንደሆኑ ይገመታል።) በአዲስ ራዕይ መጽሔት ሰኔ 1999 ዓ.ም. ላይ ”የሙያና ቴክኒክ ሥልጠና ፕሮግራማችን” በሚል ርዕስ ባሠፈሩት ጽሑፍ ”በሀገራችን የነበረውን እስካሁንም በዋናነት የሚታየው የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና የምስክር ወረቀት ተኮር ሥልጠና ነው ማለት ይቻላል” ብለዋል። ይህ ማለት ደግሞ በቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት የሚሰጠው ሥልጠና በአብዛኛው በንድፈሃሳብ ላይ ያተኮረ፣ ሠልጣኙን ተገቢውን ክሂል የማያስጨብጥ፣ ውጤታማነቱም አነስተኛ የሆነ ሠልጣኝ በማፍራት ላይ ያተኰረ መሆኑን ያሳያል።

 

በሌላ አገላለጽ የትምህርት ፖሊሲው የወለዳቸው ችግሮች ተማሪዎችን ችግር ፈቺ ሳይሆኑ ክፍልና ዓመት በመቁጠር፣ ጥራቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ ሠርቲፊኬት፣ ዲፕሎማ ወይም ዲግሪ እንዲሁም ማስተርስ ዲግሪ እንዲይዙ የሚያደርጋቸው ነው። እንደ ታደሰ ገ/ወልድ ገለፃ የሙያና ቴክኒክ ሥልጠና ሥርዓቱ የሚፈለገውን ውጤት ሊያመጣ የሚችለው ምስክር ወረቀት ተኮር ከሆነ የአሠለጣጠን ዘይቤ ሲወጣ ነው።

 

በትምህርት ልማት ፕሮግራሙ ላይ የተደቀኑ ፈተናዎች

 

የትምህርት ልማት ፕሮግራሙ የትምህርት ፖሊሲውን ለመተግበር የተቀረፀ ከመሆኑ አንፃር መንግሥት የትምህርት ፖሊሲውንም ሆነ የፕሮግራሙን ስኬት በገለልተኛ ገምጋሚዎች ለማረጋገጥ አልሞከረም። ይህ ደግሞ የራሱን ፖሊሲ ስኬት ብቻ እየነገረን ያለው መንግሥት ተዓማኒነቱን ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል። ቢሆንም በሽፋን፣ በተደራሽነት፣ የፆታ አለመመጣጠንን ለማጥበብ የተደረጉት ጥረቶች ለውጥ እያመጡ የመሆናቸውን ያህል በክልሎች መሃከል ፍትሃዊነትን ለማስፈን መንግሥት ትልቅ ፈተና ይጠብቀዋል። በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች እያስተማሩ ያሉት መምህራን ለሚያስተምሩበት ክፍል የሚመጥን የትምህርት ደረጃ የሌላቸው ከመሆኑም ባሻገር ችግሩ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥም እየተስተዋለ መጥቷል። በዚህም የተነሳ የትምህርት ጥራት ከመጀመያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ እየወረደ፤ በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች እንዲያሽቆለቁል፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደግሞ እንዲሞት ምክንያት ሆኗል።

 

እ.ኤ.አ በ2004 የተደረገ አንድ አገራዊ ጥናት እንዳመለከተው ከመካከለኛ ውጤት በታች የሚያመጡ ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም በጅምላ የማለፍ ነገር እየተዘወተረ ነው። በመጀመሪያ ሳይክል እየተተገበረ ያለው የሁሉም ይለፍ መርህ (automatic promotion) በጥቅሉ ሲታይ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት አነስተኛ ነው። ይህ መርህ የሚደግሙና የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ቁጥር የቀነሰ ቢሆንም ትምህርት በጥራት የማዳረስ ፈተና እንዲጋረጥ አድርጓል።

 

የቴክኒክ ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት (TVET) ከመሰናዶ ትምህርት የሚወድቁ ተማሪዎች የሚገቡበት የመሆኑ ጉዳይም በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው እንድምታ የተዛባ እንዲሆን አድርጐታል። ተማሪዎችና ወላጆች ልጆቹ የመሰናዶ ትምህርት ባለመግባታቸው እንደመጨረሻ ዕድል አድርገው ስለሚቆጥሩት አብዛኞዎቹ በሚፈልጉት የትምህርት አድርገው መቁጠራቸውና አብዛኞዎቹ በሚፈለጉት የትምህርት መሥክ አለመመደባቸው ከዚሁ ከትምህርት ጥራት መጓደል ጋር ሊያያዝ ይችላል።

 

በየደረጃው እንደሚተገበር የሚጠበቀው የ70/30 ፖሊሲ እንዲሁ የትምህርት ፖሊሲውና የትምህርት ልማት ፕሮግራሙ ፈተናዎች መሆናቸው አይቀሬ ነው። በአንድ በኩል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ከማኅበራዊ ሳይንስ የትምህርት መስኮች ወደ ተፈጥሮ ሳይንስና ኢንጂነሪንግ የትምህርት መስኮት እንዲያመዝኑ የሚገደዱ ሲሆን ይህም ቀድሞውኑ የብቃት ችግር ባለባቸው መምህራን እየተሰጠ ሲፈጠር የነበረውን የትምህርት ጥራት መጓደል ችግር ወደባሰ ደረጃ እንዳያደርሰው ያሰጋል። በሌላ በኩል የ70/30 መተግበር መንግሥትን ለትግበራው (ለማሽነሪ፣ ለኮምፒዩተር...) ከፍተኛ ገንዘብ እንዲመድብ የሚያስገድደው ሲሆን፣ ይህን ማሟላት ሊከብደው እንደሚችል ስለሚታሰብ ይህም ለትምህርት ጥራት መጓደል የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

 

እ.ኤ.አ. በ2000 ተ.መ.ድ. በሴኔጋል በትምህርት ላይ ባካሄደው ጉባዔ እ.ኤ.አ. በ1990 በተነደፈው የዳካር የድርጊት ማዕቀፍን ላይ ሲመክር የትምህርት ለሁሉም ግብን ማሳካት ትምህርትን በጥራት ከማዳረስ ተነጥሎ መታየት እንደሌለበት አሳስቦ ነበር። ሀገራትም በሁሉም ረገድ የትምህርት ጥራትን ለማሳካት የሚያስችሉ ሥራዎችን እንዲሠሩ፣ ከትምህርት የሚገኘው ግብም ሕይወትን በሚለውጥ መልኩ በችግር ፈቺነቱ መገለጽ እንደሚኖርበት ጠቅሷል። የትምህርት ጥራትን መለካት አስቸጋሪ ቢሆንም በግብዓቱ፣ በውጤቱና በሂደቱ የሚታወቅ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት መጓደል ችግር በስፋት ለመኖሩ ሁሉም ወገን ያረጋገጠው ጉዳይ ነው።

 

የትምህርት ግብዓቱ በቀጥታ ግንኙነት ያለው ከመማሪያና ማስተማሪያ ቁሶችና ከሰው ኃይሉ ጋር ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ሁኔታውን እያባባሱት የመጡት በዘርፉ የሚመደቡና እየተመደቡ ያሉ መምህራን ናቸው። በቅርቡ እንኳ ከዩኒቨርስቲ ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ”ሰቃዩች” በዩኒቨርስቲዎች እንዲቀሩ ሲወሰን ምንም ዓይነት የማስተማር ችሎታ የሌላቸው ከመሆኑና በተመሳሳይ የትምህርት ደረጃ ለሚገኙ ተማሪዎች ትምህርት መስጠታቸው በጉዳዩ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉን ተማሪዎች ገልፀዋል። የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው የመንግሥት ሠራተኞች ከየወረዳው ሳይቀሩ ተመልምለው በየዩኒቨርስቲዎቹ እንዲያስተምሩ መመደባቸውም የጥራት መጓደሉን ሊያባብሰው እንደሚችል ይገመታል። ጥራቱን የሚያጓድለው መምህራኑ ከየወረዳው ተመልምለው መምጣታቸው ብቻ ሳይሆን በሥነ ትምህርት (Pedagogy) ላይ ሥልጠና የሌላቸው፣ ከትምህርት ዓለም የራቁ፣ የሚሰጣቸውን ትምህርት በበቂ ሁኔታ ለማስተማር አዲስ የሆኑና ከነርሱ ጋር በተመሳሳይ የትምህርት ደረጃ የሚገኙ ተማሪዎችን የሚያስተምሩ መሆናቸው ጭምር ነው። ከዚህ ባልተናነሰ ሁኔታ አንድ መምህር በዩኒቨርስቲ ደረጃ የሚያስተምራቸው ተማሪዎች ቁጥር መብዛት የትምህርት ጥራት ዋነኛ ችግር ከሆነ ሰነባብቷል። መምህራንም የትምህርት (የመማር-ማስተማር) ሂደቱ ዋንኛ ግብዓት ከመሆናቸው አንፃር በምልመላና በሥራ ሂደት ክትትል ሊደረግባቸው ይገባል። አንዳንድ መምህራን አላቸው ከሚባለው የትምህርት ደረጃ የማይመጥን ዕውቀት እንዳላቸው በተማሪዎቻቸው መገለጹ መምህራኑን በከፍተኛ ደረጃ የሚስገምታቸው ሲሆን፣ ትምህርት የእግር ኳስ ጨዋታ ቢሆን ኖሮ ከደረጃ በታች ተጫወቱ ተብሎ በተቀጡ ነበር።

 

የትምህርት ጥራት በዝቅተኛ ደረጃ ከሚገኝባቸው ሀገራት መሃከል አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን፤ መምህሮቹ በቂ ሥልጠና ያላገኙ፣ በደምወዛቸው የማይረኩና ባለው ተቋማዊ የውስጥ ድርጅት አለመሟላት የሚያማርሩ ናቸው።

 

በመሆኑም መንግሥት የመምህራኑን ችግር ቢቀርፍ፣ ለግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እውቅና የሚሰጥበትን መንገድ አዳዲስ የመንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲቋቋሙም ቢተገብር፣ የውስጥ ድርጅቶችን ቢያሟላ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እገዛ ከማድረጉ በተጓዳኝ ተወዳዳሪና ችግር ፈቺ የሆኑ ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን ለማፍራት ያስችላል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ