አቶ በረከት በፕላዝማ ለመምህራን አብዬታዊ ዲሞክራሲን ሰበኩ
መምህራን ፍላጐታቸው የትምህርት ጥራትና ኑሮን ያገናዘበ ደሞዝ ማግኘት መሆኑን አሳወቁ
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ሰኔ 27 ቀን 2001 ዓ.ም. July 4, 2009)፦ ሰኔ 21 ቀን ከጠዋቱ 2 ሰዓት ተኩል በኋላ መምህራን ወደ አጋርፋና ፍቼ እንደዚሁም ሌሎች አካባቢዎች ለፖለቲካዊ ንቃት ከተንቀሳቀሱ ወዲህ ሰኞ ሰኔ 22 ቀን 2001 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማም ጭምር የተጀመረው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ የልማታዊ መንግስት እና የፍትሃዊ ሥርዓት ትምህርት በዛሬውም እለት ቀጥሎ ውሏል።
9 ሺህ የሚሆኑ በአዲስ አበባ ከተማ የመንግሥት ተቀጣሪ መምህራን የውዴታ ግዴታ ተሳትፎ ያደረጉበት ፖለቲካዊ ንቃት አሃዱ ሲል፣ አስተማሪዎቹ በፕላዝማ ቴሌቪዥን አማካይነት ከአንቂው ካድሬ አቶ በረከት ስምኦን ጋር ከሰኞ እስከ ረቡዕ ባለው ቀን ተፋጠዋል። በፕላዝማ የሚሠራጨው የአቶ በረከት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ትንተና እንደመምህራኑ አባባል “አሰልቺና የማይዋጥ” አስተምህሮ ካበቃ በኋላም የንቃቱ ተሳታፊዎች ማብራሪያና ገለፃ ከሚሰጧቸው የበታች የኢሕአዴግ ካድሬዎች ጋር ሙግትና አተካራ ገጥመዋል።
እነዚሁ መምህራን “እኛን ስለመንግሥት ልማት፣ ፍትሐዊነትና ዴሞክራሲያዊ መብት አክባሪነትና አስከባሪነት ማስተማርና ማሳወቅ…. ለምን አስፈለገ?” በማለት የመድረክ መሪዎቹን ጠይቀዋል። ይሄን የመሰለውን ጥያቄ ካቀረቡት መምህራን መካከል አብዛኞቹ ሴቶች መሆናቸው ታውቋል። ወሳኝና ወቅታዊነት ያለው ጥያቄም በአብዛኛው የተሰነዘረው፣ የፖለቲካ ንቃታቸውን በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙት ት/ቤቶች አዳራሽ እንዲቀበሉ ከተደረጉት መምህራን በኩል ነው።
ከመነሻው ለዚህ አይነቱ የቅድመ ምርጫ ቅስቀሳ የሚመስል ፖለቲካዊ ንቃት ልባዊ ፍቃዱ የሌላቸው መምህራን፤ የአቶ በረከት ስምኦን አስተምህሮ በፕላዝማ ሲተላለፍ፤ እነሱ የየራሳቸውን የግል ስልክ ከፍተው ሙዚቃ በመስማትና መንግሥትን የሚተቹ ቀልዶችን በማድመጥ ቅዋሜያቸውን አሳይተዋል።
የበረቱትም ፍላጐታቸው የኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት በተግባር ተሻሽሎ መታየትና ዝቅተኛው የመምህራን ደመወዝ ክፍ ያለና የኑሮውን ውድነት ያገናዘበ እንዲሆን ለመድረኩ የኢሕአዴግ ካድሬዎች በግልጽ አስታውቀዋል። ሰኔ 21 ቀን የተጀመረውና ሳምንቱን የተካሄደው ፖለቲካዊ ንቃትም በሚቀጥለው ሳምንት ጭምር ከቀጠለ በኋላ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።



