በቆሎና ጥይት

የአዲስ አበባ ፖሊስ ዛሬ ሚያዝያ 5 ቀን 2013 ዓ.ም. 868 ጥይቶችን በበቆሎ ውስጥ ደብቆ ሊያዘዋውር የነበረ ግለሰብ ተይዟል በማለት አስታውቋል

ጥብቅ ክትትል የሚሻው የሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር

ትዕግሥት መንግሥቴ (ኢዛ) ኢትዮጵያ ውስጥ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር በየጊዜው እየተበራከተ መጥቷል። በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች በተለያዩ መንገዶች የጦር መሣሪያዎችን ሲያዘዋውሩ ተያዙ የሚባሉ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ስለመዋላቸው በተደጋጋሚ እየተዘገበ ይገኛል።

በዚህ አደገኛ ወንጀል ተሳታፊ የኾኑ ግለሰቦች ተያዙ መባልን እንጂ ለሕግ ቀርበው ስለተወሰደባቸው እርምጃ እንብዛም አይሰማም። ነገር ግን በየጊዜው በተለያዩ ቦታዎች የሚያዙት የጦር መሣሪያዎች ቁጥር ሲታይ፤ ዝውውሩ ተራ ንግድ አለመኾኑን ከማመላከቱም በላይ፤ አሁንም ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ ያመላክታል።

ንጹሐን በጠራራ ፀሐይ የሚገደሉበት እና የሚቆስሉበት እንዲህ በሕገወጥ መንገድ በሚዘዋወሩ የጦር መሣሪያዎች መኾኑን ጭምር እንደኾነ ልብ ሊባል ይገባል።

የጦር መሣሪያ ዝውውሩ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ሲፈጸም እንደነበር፤ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ቦታዎች ስለተያዙ የጦር መሣሪያዎች ዝውውሮች የሰማናቸው መረጃዎች ያሳያሉ።

ይህ ደግሞ የጸጥታ ኃይሉ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ቁጥጥሩን በተለያየ መንገድ ማከናወን የሚገባው መኾኑን የሚያመላክት ነው። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚኾነው የአዲስ አበባ ፖሊስ ዛሬ ሚያዝያ 5 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዲስ አበባ መርካቶ አውቶብስ መናኸሪያ በሕገወጥ መንገድ ሊዘዋወሩ የነበሩ ጥይቶችን እስካሁን ባልተለመደ ሁኔታ ለማስተላለፍ የተደረገው ሙከራ ነው።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ዛሬ 868 ጥይቶችን በበቆሎ ውስጥ ደብቆ ሊያዘዋውር የነበረ ግለሰብ ተይዟል በማለት አስታውቋል።

ይህ ግለሰብ በሁለት ከረጢት በያዘው በቆሎ ውስጥ ሸሽጐ ከነበረው ጥይቶች ውስጥ 200ዎቹ የብሬን ጥይቶች ሲሆኑ፤ 668ቱ ደግሞ የክላሽንኮቭ ጥይቶች ናቸው። ግለሰቡ እነዚህን ጥይቶች በቆሎ በማስመሰል በተሽከርካሪ ጭኖ ሊወጣ ሲል የተያዘ ሲሆን፣ የትንሿ መናኸሪያ ሠራተኞች ባደረባቸው ጥርጣሬ በተደረገ ፍተሻ ግለሰቡ መያዙን ነው የፖሊስ መረጃ የሚያመላክተው።

የመናኸሪያው የሥነሥርዓት ተቆጣጣሪዎች ከዚህም ቀደም በተመሳሳይ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ሲያደርጉ የነበሩ ግለሰቦችን እንዲያዙ ማድረጋቸውንም ጠቅሷል።

ጥይትና ሌሎች የጦር መሣሪያዎች ሕገወጥ ዝውውር የአገርን ሰላም ከማናጋት በላይ፤ ዓላማቸው ከወንጀል ጋር የተያያዘ የጥፋት ተልዕኮ ያላቸው ናቸውና ቁጥጥሩ ይጥበቅ። በወንጀሉ ተሳታፊ የኾኑና የተያዙ ግለሰቦችም ኾኑ ቡድኖች ለሕግ ቀርበው የተወሰደባቸው እርምጃም ለሕዝብ ይፋ ይኹን። ፍርድ ቤት ቀርበው ጥፋተኛ ኾነው ሲገኙ፤ የተጣለባቸውን ቅጣት ለሕዝብ ይፋ ማድረግ፤ ሌሎች ከዚህ የሕገወጥ መሣሪያ ዝውውር እንዲታቀቡ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አለውና። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!