በአንድነት ፓርቲ ላይ የተጀመረውን መሰረተ ቢስ ጥቃትን በተመለከተ

ግርማ ካሣ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.) - ጥቅምት 20 ቀን 2001 ዓ.ም.

ከዚህ በታች የማቀርበው ሃሳብ የግሌን እንጂ ማንን የፖለቲካ ፓርቲ ወይንም ማኅበር ወክዬ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ።

 

በሥራችን እንመዘን - ጭፍን ፖለቲካ ይቁም!

አንድ ስማቸውን መጠቀስ የማልፈልግ በአውሮፖ የሚኖሩ የታወቁ ኢትዮጵያዊ “ነገ ኢህአዴግን ልንደግፍ እንችላለን” በሚል ርዕስ በቀረበው ጽሑፌ ላይ በመመርኮዝ አክብሮት የተሞላበት ግን ጠንካራ የቅሬታ አስተያየት በኢ-ሜይል አድራሻዬ ላኩልኝ። ”ጽሑፎችህ በወያኔ ድረ ገጾች ላይ እየወጡ ነው። የምታቀርባቸው ሃሳቦች የበለጠ ወያኔን እየረዳና ተቃዋሚውን እየጎዳ ነው። ያለህን ተቀባይነት እንዳታጣ ጥንቃቄ እንድታደርግ እመክርሃለሁ” ነበር እኝህ ሰው ያሉኝ።

 

ኢ.ኢ.ዲ.ኤን. (የኢትዮጵያውያን ኢሜል ዲስትሪቡሺን ኔትዎርክ) የሚባለው በዳያስፖራ አሉ የሚባሉ ታዋቂ ኢትዮጵያውያንን ያቀፈ የኢሜል ፎረም ውስጥ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ሃሳቦችን እያቀረብኩኝ በፎረሙ ውስጥ እንቀሳቀስ ነበር። በሀገራችን መፍትሔው ዕርቅና ሠላም እንደሆነ፣ ጥቂቶች ባደረጉት ስህተት መላው የኢህአዴግ አባላት በሙሉ እንደ ጠላት መቆጠር እንደሌለባቸው የሚገልጹ ሃሳቦች አቀረብኩ። ይህ የዕርቅ ጥሪዬ እንደ ድክመትና ፍርሃት ከመቆጠር አልፎ ”ወያኔ ነው” እስክባል ድረስ ትልቅ ተቃውሞ ከአንዳንድ የፎረሙ አባላት ደረሰኝ።

 

ያ ብቻ አይደለም። ኢህአዴግ ውስጥ ጥሩ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉና በጅማላ እነርሱን ከመጨፍጨፍ ተቃውሞዋችንን መረጃ ላይ እና የገዢው ፓርቲ አመራሮች የሚሠሩት ሥራ ላይ ያተኮረ እንዲሆን በመከራከሬ በፎረሙ ቦርድ ጽሑፎቼን እንዳላቀርብ ታገድኩኝ። (ከእስር ቤት እንደተፈቱ ወ/ት ብርቱካን ሚደቀሳ ”ቅንጅት የሰው ጠላት የለውም”፣ ሲሉ ፕሮፌሠር መስፍን ደግሞ ”ወያኔ ጠላት አይደለም” ብለው አረፉላቸው። እንግዲህ ይህ ፎረም እነ ብርቱካን ሚደቅሳንና ፕርፌሠር መስፍንን አባላት ቢሆኑ ኖሮ ያግዷቸው ነበር ማለት ነው?)

 

በቃሊቲ እስር ቤት የታሰሩ የዲሞክራሲ ታጋዮች ከመፈታታቸው በፊት የተግባር ሊግ፣ የተለያዩ የፖለቲካና የሲቪክ ማኅበራትን አሰባስቦ፣ አንድ አይነት የጋራ ሥራ እንዲሠራ ቴሌኮንፈራንሶች ያደርግ ነበር። በዚህ ቴሌኮንፈራንስ ውስጥ በተወሰነ ደረጃ ተገኝችቼ ነበር።

 

የስብሰባው መሪ የነበሩት አንዲት የማደንቃቸው ኢትዮጵያዊት ”የኢትዮጵያ መንግሥት” እኔ ደግሞ ”ኢህአዴግ” እያልኩኝ ነበር አገዛዙን የምንጠራው። ድንገት በስብሰባው መሃል ”ለምንድን ነው ወያኔ የማትሉት?” በሚል ጭቅጭቅ ተነሳ። ወያኔንን እንደ መንግሥት መቁጠር ወይንም ደግሞ የኢትዮጵያን ህዝብ እንደወከለ አድርጎ ”ኢህአዴግ” ማለቱ በስብሰባው የነበሩት አንዳንዶቹን እጅግ አበሳጭቶ እንደነበረ አስታውሳለሁ።

 

ታዲያ ”ይሄን ሁሉ መዘርዘሩ አሁን ምን አመጣው?” የሚሉ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ። የኢትዮጵያን ሪቪው ዋና አዘጋጅ አቶ ኤሊያስ ክፍሌ የግንቦት ሰባት መሪ ከሆኑት ከአቶ አንዳርጋቸው ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ ካዳመጥኩኝ በኋላ የጭፍንና ግትር ፖለቲካ የሚያራምዱ በዳያስፖራ ያሉ አንዳንድ አካላት የጀመሩት ፕሮፖጋንዳ እጅግ ስላሳሰበኝ ነው አንዳንድ ያጋጠሙኝንና ከላይ የተዘረዘሩትን የጠቀስኩት።

 

ስለሠላምና ስለእርቅ አሁን ካለው አገዛዝ ጋር ችግሮችን በሰላም መፍታት ስለሚቻልበት መንገድ የሚናገሩ ኢትዮጵያውያን ከጊዜ ወደ ጊዜ ዝም እንዲሰኙ እየተደረጉ ሲሆን፣ ከተናገሩም ደግሞ ”ወያኔ እንባላለን” በሚል ፍርሃት የሚጠነቀቁ ብዙዎች ናቸው። ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ የመናገር መብታቸው እየተገፈፈ ነው ማለት ነው በሌላ አባባል።

 

ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲ እንዲኖር እንፈጋለን። አብዛኞቻችን የምንኖረው ዲሞክራሲ በሰፈነባቸው ሀገራት ነው። ነገር ግን ከኛ የተለየ ሃሳብ አንድ ሰው ካመጣ ”ወያኔ ነው፣ ገንዘብ በልቶ ነው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ቤት እያሠራ ነው፣ …” ይባላል። ይህ አይነቱ ባህል መቆም አለበት ባይ ነኝ።

 

የታሰሩ የሕሊና እስረኞች እንዲፈቱ የሚጠይቅና የተለያዩ የፖለቲካ የሲቪክ ማኅበራትና የመገናኛ ብዙኃንን ያቀፈ የጋራ መግለጫ እንዲወጣ ለማድረግ አንድ ወቅት አንድ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር። በዚህ ወቅት ሁለት የፓልቶክ ክፍሎችም የመግለጫው አካል እንዲሆኑ ጥያቄ ቀረበላቸው። (አቅራቢው እኔ ነበርኩኝ) መግለጫው ከተነበበላቸው በኋላ ”እነማን ናቸው ይሄን ያስተባበሩት?” ብለው ጠየቁ። ”አስተባባሪዎቹን ማወቅ ለምን አስፈለጋችሁ? ይዘቱ ተነቦላችኋል። የምትስማሙ ከሆነ ደግፉት፣ እንዲሻሻል የምትፈልጉ ከሆነ ሃሳብ አቅርቡ። የምትቃወሙም ከሆነ መብታችሁ ነው” ብዬ መለስኩ። ከሃያ አራት በላይ ድርጅቶች በጋራ መሪዎች እንዲፈቱ የሚጠይቀው የጋራ መግለጫ ላይ ስማቸውን ሲያስገቡ የፓልቶክ ክፍሎቹ ግን አስተባባሪዎቹ እነማን እንደሆኑ ካላወቅን አንደግፍም አሉ።

 

እንግዲህ ይሄ የሚያሳየው ምን ያህል ነገሮችን የምንመዝንበት ሚዛን እጅግ የጠበበ እንደሆነ ነው። አንድ ነገር መመዘን ያለብት ”ማን ሠራው?” የሚለውን ጥያቄ በመጠየቅ ሳይሆን? ”ምን ተሠራ?” በሚለው መሆን አለበት። ሰው የኢህአዴግ አባል ስለሆነ፣ ወይንም ከአንድ ክልል ስለተወለደ ሊለይ አይገባም። ከኢህአዴግ ዘንድም ሆነ ከአንድነት ፓርቲ ዘንድ ጥሩ ሥራ ካልተሠራ ማውገዝ፣ ጥሩ ሲሠራ ደግሞ ማበረታታት ያስፈልጋል።

 

ኢህአዴግ በሚቆጣጠራቸው ፖሊሶቹ አማካኝነት ጋዜጠኞችን ሲያንገላታ፣ በህዝብ ገንዘብ የሚሠሩ የመገናኛ ብዙኃንን የአንድ ፓርቲ መጠቀሚያ ብቻ ሲያደርግ፣ ህዝባችን እየተራበ የተራበው ወገናችን ምግብ እንዳያገኝ ፖለቲካውን ለመጠበቅ ሲል ቁጥራቸውን ሲያሳንስ፣ ህዝባችን እየተራበ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በሶማሊያ ሲጠፋ፣ ንጹኅ ዜጎች ወንጀል ሳይሠሩ በግፍ ሲገድሉ፣ … ኢትዮጵያውያን ልናወግዘውና ልንታገለው ያስፈልጋል።

 

በአንፃሩም መንገዶችን፣ ድልድዮችን፣ ዩኒቨርሲቲዎችን ለማስፋፋት ገዢው ፓርቲ ሲንቀሳቀስ መተባበርና መደገፍ አለብን። ”ምንድን ነው የሚሠራው?” የሚለውን ጥያቄ በመጠየቅ ነው የምንደግፈውንና የምንቃወመውን መወሰን ያለብን።

 

እንደው በጭፍኑ ዜጎችን መጠራጠር፣ ማጥቃት፣ መሳደብ የኋላ ቀርነት ምልክት ይመስለኛል።

 

አንድነት ላይ ጥቃቱ ለምን?

 

በተለይም ደግሞ በአሁኑ ሰዓት ይህ አይነቱ ጥቃትና የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ እየተደረገ ያለው እራሳቸውን ሰውተውና ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሆነው ሠላማዊና ህዝባዊ በሆነ መንገድ በሀገራችን ለውጥ እንዲመጣ እየታገሉ ያሉ ወገኖቻችን ላይ መሆኑ ደግሞ በሀገራችን ለውጥ እንዲመጣ የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሊቃወመውና ሊታገለው የሚገባ ጉዳይ ነው እላለሁ።

 

ከአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጋር በተደረገ ቃለ መጠይቅ ላይ የኢትዮጵያን ሪቪው ዋና አዘጋጅ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ መራር አባላት ክህደት እንደፈጸሙና ህዝብን እየበደሉ እንደሆነ ሲናገሩ ሰምቻለሁ። ”የአንድነት መሪዎች ወደ ህዝብ ከመሄድ ይልቅ ወደ ያማማቶ መሮጥ ነው ሥራቸው? የቅንጅት ስምንቱን ጥያቄዎች ሳይመለሱ ምርጫ ምርጫ ያላሉ …” እያሉ ነበር አቶ ኤሊያስ ክፍሌ ሲያወግዙ የተሰሙት።

 

የአንድነት መሪዎች ከሰባ በላይ ልዑካንን ልከው በስድስት ክልልሎች ከ10 ሺህ በላይ ፎርም ሲሰበስቡ ወደ ያማማቶ ሄደው ነው እንዴ? ወደ አራት መቶ ዜጎች ከየክልሉ መጥተው የአንድነት መሥራች ጉባዔ ለማድረግ በፖሊስ ተከልክለው በኢምፔሪያል ሆቴል ደጃፍ ላይ ተንሳፈው የነበሩት እነ ያማማቶዎች ናቸው እንዴ? እንጂነር ግዛቸውና ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በደቡብ ኢትዮጵያ በሆሳና፣ በሳውላ፣ በቡታጅራ፣ በወላይታ ሶዳ እንዲሁም በርካታ የደቡብ ኢትዮጵያ ከተሞች ህዝባዊ ስብሰባ ሲያደርጉ፣ የአገዛዙ የደህንነት አባላት ሳይፈሩ በድፍረት ያዘጋጁት ህዝባዊ ስብሰባዎች ያዘጋጁት ኢትዮጵያውያን የያማማቶ ሠራተኞች ነበሩ እንዴ? በቅርብ ጊዜ ወ/ት ብርቱካ ሚደቅሳና አቶ ተመስገን ዘውዴ በሰሜን ኢትዮጵያ በደሴና በወልዳይ ኢትዮጵያውያንን አነጋግረው በዚያም ጽ/ቤትች ተከፍተዋል። የተከፈቱት ጽ/ቤቶች የአሜሪካን ኤምባሲ ቅርንጫፎች ናቸውን?

 

በጣም የሚያሳዝነውና የሚያሳፍረው ደግሞ የኢትዮጵያ ሪቪው ዋና አዘጋጅ መሰረት የሌለውና የማይጨበጥ ክስ ህዝብ በሚወዳቸው መሪዎች ላይ ሲያቀርቡ፣ የተከበሩና በሳል ፖለቲከኞች ከሚባሉ መካከል አንዱ የሆኑትና አንድ ወቅት የቅንጅት ዓለም አቀፍ ኮሚቴ የአመራር አባል የነበሩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ዝም ማለታቸውና እዚያው እርማት እንዲደረግ አለመጠያቃቸው ነው። እንደውም አቶ አንዳርጋችው ከአቶ ኤሊያስ ጋር ዳንኪራ በመምታት ጭራሹኑ እነ ብርቱካን ሚደቅሳ በምርጫ የሚሳተፉ ከሆነ አንድነት ፓርቲ የህዝብ ድጋፍ እንዳያገኝ እንደሚታገሉ ነበር የተናገሩት። (በአንድነት ፓርቲ ላይ ውጭ ሀገር ተቀምጦ የሚደረግ የማስፈራራት ዘመቻ ይሉታል ይሄ ነው)

 

እነ ብርቱካን ሚደቅሳ ዳያስፖራ ባሉ አንድ ወቅት ታዋቂ በሆኑ ድረ ገጾችና ፓልቶክ ክፍሎች የሚወረፉት ለምንድን ነው? ምንድን ነው እነዚህ ሰዎች ማድረግ ያለባቸው? አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ምን እንዲያደርጉ ነው የሚፈልጉት? አቶ ኤሊያስ ክፍሌ የአንድነት መሪዎች ምን ቢያደርጉ ነው የሚደሰቱት?

 

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ተመርቀው ኢትዮጵያ ውስጥ ዳኛ የነበሩ ሴት ናቸው። ከርሳቸው ጋር የተማሩ አንዳንድ ኢትዮጵያን ኑሮዋቸውን በአሜሪካን ሀገር አድርገው የታወቁ ጠበቃ የሆኑ አሉ። ዶ/ር ያዕቆብ ወልደማርያም በተባበሩት መንግሥታት ዓቃቢ ሕግ ሆነው የሠሩ ቨርጂኒያ በሚገኝ የታወቀ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፕሮፌሠር ነበሩ። ኢንጂነር ግዛቸው በአዲአ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢንጂነሪንግ አስተማሪ ናቸው። እንዲሁም ሌሎች በአንድነት አመራር ውስጥ የሚሠሩ ኢትዮጵያውያን በውጭ ሀገር ቢኖሩ በኢኮኖሚ የተሻለ ኑሮ ሊኖሩ የሚችሉ ሰዎች ናቸው።

 

አብዛኞቹ የአንድነት አመራር አባላት የቅንጅት ላዕላይ ምክር ቤት አባል የነበሩ ሲሆን፣ ወደ ሁለት ዓመት ገደማ በቃሊቲ እስር ቤት የተንገላቱ ናቸው። ያኔ በግፍ እስር ቤት የወረወራቸው አገዛዝ ነው አሁንም እየገዛ ያለው። ነገ አገዛዙ መልሶ ወደ ቃሊቲ ሊያወርዳቸው ይችላል። ነገ የዲሞክራሲን ጥያቄ እነዚህ ሰዎች በማንሳታቸው መከራ ሊደርስባቸው ይችላል። እንደዚያም ሆኖ የመጣው ይምጣ ብለው ነው መስዋዕትነትን ለመክፍለ ተዘጋጅተው የኢትዮጵያ ህዝብ ለመብቱና ለነፃነቱ እንዲቆም የሚታገሉት።

 

ታዲያ ከዚህ የበለጠ በሕይወታችው ላይ እስከመወሰን ድረስ መስዋዕትነት ከከፈሉ ሌላ ምን አድርጉ ነው የምንላችው? የአንድነት መሪዎች ዋሽንግተን ተቀምጠው ወይም አስመራ ተክለው ጠዋታና ማታ ወያኔዎችን እንዲረግሙ ወይም እንዲሁ በባዶ ህዝብን ገና ሳያደራጁ አንዳንድ ንቅናቄዎችን አድርገው ለጥቂት ሣምንታት ትልቅ ዜና ፈጥረው እንደገና እንዲታሰሩ ነው የሚፈለገው? ከሦስት ዓመታት በፊት የተፈጠረውን ታሪክ ረሳንን? እውነት ለመናገር ኢትዮጵያን ሪቪው ከነብርቱካን ሚደቅሳ ምን እንደሚፈልግ አይገባኝም።

 

አንድ ነገር በተመሳሳይ መልኩ ደግመን ደጋግመን ብንሠራው አዲስ ውጤት አናመጣም። አሠራር፣ ዘዴ መቀየር አለበት። ታዲያ አሁን ልክ ያኔ በቅንጅት ላይ ጫና ይደረግ እንደነበረው ነው አሁንም በአንደነት ላይ ጫና ለማድረግ እየተሞከረ ነው ያለው። ያኔ በስሜት ግለት ይሠራ እንደነበረው አሁንም እንደዚያ ነገሮች ግንፍል ብለው የምንዘግበውና የምናወራው ነገር እየፈለግን ይመስለኛል። ይህ ትልቅ ስህተት ነው። የአንድነት ፓርቲ ካለፈው የተማረ ስለሆነ ሥራውን የሚሠራው በጥንቃቄና በማስተዋል ነው። ስለሆነም ከጊዜ ወደ ጊዜ የበለጠ የህዝብ ድጋፍ እያገኘ ነው የሚመጣው።

 

እያየንም ነው። እነበርቱካን ሚደቅሳ ሥራቸውን እያሳዩ ናቸው። አንድም ጊዜ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችን ሲያጥላሉ አልታዩም። በሀገር ቤት ያሉትን የተለያዩ የተቃውሞ ፓርቲዎች በአንድ ላይ መጥተው በጋራ ሥራው እንዲሠራ እየታገሉ ናቸው። ከዲፖሎማቲክ ማኅበረሰቡ ጋር ጥሩ ግንኙነት አላቸው። ”ኢህአዴግ በምርጫ ከተቀየረ በኢትዮጵያ ሊያስተዳድር የሚችል አቅም ያለው ኃይል የለም” የሚለውን የምዕራባውያንን አመለካከት ለማስቀየርና አንዱ የአገዛዙ የድጋፍ መሰረትን ለመበጠስ የሚደረገው ሙከራ አስተዋይነትን ይጠይቃልና።

 

በአሜሪካን ሀገር የተቀመጡት የኢትዮጵያ ሪቪው ዋና አዘጋጅ የአሜሪካ መንግሥት ሥራ አስፈጻሚው አካል (እነ ያማማቶ) ከሕግ አውጭው አካላ የበለጠ ጫና በኢህአዴግ ላይ ሊያደርሱ እንደሚችሉ የሚዘነጉት አይመስለኝም። የአንድነት ፓርቲ ወደ ያማማቶ ነው የሚሮጡት የሚለውም ክሳቸው በዚህ ሚዛን ሲመዘን ጨቅላነት የሞላበት ክስ እንደሆነ እናያለን።

 

ስለ 2007ቱ ምርጫ

 

”እውነትም ኣርነት ያወጣኋል” እንደተባለ እስቲ የውሸት ፖለቲካ ለጊዜው እንተውና እውነትን እንነጋገር። የት ቦታ ነው የአንድነት ፓርቲ ምርጫ እገባለሁ ብሎ መግለጫ ያወጣው? የትኛው የአንድነት አመራር አባል ነው ምርጫ እንገባለን ያለው?

 

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በቅርቡ በውጭ ሀገር ላሉ ጋዜጠኖች መግለጫ ሲሰጡ ስለምርጫው የተናገሩት ግልጽና የማያሻሙ ሦስት ነጥቦች አሉ።

 

አንደኛ፦ የአንድነት ዓላማ በምርጫ ሥልጣን ይዞ በኢትዮጵያ አመጣለሁ ያለውን ለውጥ ለማምጣት ነው። የአንድነት ፓርቲ የሽምቅ ተዋጊ አይደለም። ጠመንጃ ይዞ አይንቀሳቀስም። በሠላም፣ በንግግር የሀገሪቷ ችግር ተፈትቶ፣ በምርጫ የህዝብ የበላይነት እንዲረጋገጥ ነው የአንድነት ፓርቲ የሚታገለው።

 

ሁለተኛ፦ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳሩ የጠበበ እንደሆነና ይህንን የፕለቲካ ምህዳር ለማስፋትና የዲሞክራሲት ተቋማት እንዲጠናከሩ እንዲሁም ህዝቡ መንግሥትን የማስገደድ አቅም እንዲኖረው ማደራጀት እንደሚያስፈልግ የአንድነት ፓርቲ ያማናል።

 

አሁን ያለው አገዛዝ ነፃ ጋዜጦች በሰፊው እንዲታተሙ ፈቅዷል። የአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤቶችን ከፍቶም እየተንቀሳቀሰ ነው። ነገር ግን አሁንም ፖሊስ በተቃዋሚዎች ላይ ችግር እየፈጠረ ነው። ስብሰባዎች እንዳይደረጉ የማስፈራራት ዘመቻው አልተቋረጠም። የህዝብ መገናኛ ብዙኃን ሙሉ ለሙሉ በገዢው ፓርቲ ስር ነው። የሕግ ሥርዓቱ ትልቅ ችግር አለበት።

 

እነዚህ ሁሉ እንዲስተካከሉ የአንድነት ፓርቲ ጥይቄ ያቀርባል። ጥያቄዎችም በኢህአደግ ዘንድ ክብደትና ተቀባይነት እንዲኖራቸው አንድነት ከኋላው የሚያሠልፈው የህዝብ ድጋፍ ይወስነዋል። ስለሆነም ህዝብን ማደራጀቱ ወደፊት የሚደረገውን የምርጫ ፍትሃዊነትና ዲሞራሲያዊነት ይወስነዋል።

 

ሦስተኛ፦ የዲሞክራሲ ተቋማት ካልተገነቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና አባላት ወከባ ከበዛ፣ ምርጫው እንደ ያለፈው ክልላዊ ምርጫ አይነት ፀረ-ዲሞክራሲያዊ ከሆነ የአንድነት ፓርቲ የመሳተፉ ጉዳይ የሚረሳ ነው።

 

ከአንድነት መሪዎች እንደሰማነው አንድነት በህዝብ የሚተማመን ድርጅት ነው። ህዝብ ከተደራጀ ለውጥ ማምጣት ይችላል ብሎ ያምናል። አንድነት በወሬና በዛቻ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ የለውም። ለኢትዮጵያዊያንም እንዲሁ በባዶ ዘራፍ እያለ፣ ባዶ ተስፋን መስጠት አይፈልግም። አንድነት የሽንፈትንና የአይቻልምን ፖለቲካ አያራምድም።

 

ከአሁን ለአሁን ምርጫው ዲሞራሲያዊ አይሆንም ተብሎ ቁጭ ለማለት ዓላማ የለውም። በምርጫ ዘጠና ሰባት ኢህአዴግ ስላጭበረበረ ያኔ የነበረው ችግር አሁንም ስለሚፈጠር በሠላማዊ መንገድ መንቀሳቀሱ ዋጋ የለውም የሚለውን አባባል የኢትዮጵያን ህዝብ ጉልበት መናቅ አድርጎ ነው የሚያየው። ለምርጫው ብቻ ሳይሆን ምርጫውን ካሸነፈ ሀገር ለማስተዳደር ይዘጋጃል። ምርጫው ፍታሃዊ እንዲሆን ይታገላል። ህዝብ ከጎኑ እስከሆነ ድረስ ዓላማውን ከግቡ እንደሚያደርስ ያምናል። ከሁለት ዓመት በኋላ በሚደረገው ምርጫ መሳተፉና አለመሳተፉ ያኔ ያለውን ሁኔታ ከተጠና በኋላ የሚወሰን ይሆናል።

 

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1996 ዛጄድኖ (በሰርብ ቋንቋ ቅንጅት ማለት ነው) በሚል ስም ተቃዋሚዎች በሰርቢያ አምባገነን ስሎቦዳን ሚሎሶቪች ላይ የህዝብ ተቃውሞ እንዲነሳ አደረጉ። በመሃል በዛጄድኖ ውስጥ ያሉ ሁለት መሪዎች (ዞራን ጂንጂችና ቩክ ድራትስኮቪች) ባለመስማማታቸው ዛጄድኖው ወይንም ቅንጅቱ ፈረሰ። የተቃዋሚዎች መከፋፈል ለስሎቦዳን ሚሎሶቪች ተመቻቸው። እስከ 2000 ዓ.ም. ድረስ በሥልጣን ቆዩ።

 

በ2000 የህዝብ ጥይቄ ታፍኖ ለሁልጊዜ መቆየት ስለማይችል የሰርቢያ ህዝብ በከተማና በገጠር ህዝባዊና ሠላማዊ ተቃውሞውን በማሰማቱ ስሎቦዳን ሚሎሶቪች ከሥልጣን ለመልቀቅ ተገደዱ። የመጀመሪያው ጊዜ ከሸፈ። አንዴ አልተሳካም ተብሎ ዝም አይበላም። ትግሉ መቀጠል አለበት።

 

በዚምባብዌም ተመሳሳይ ታሪክ አለ። ሮበርት ሙጋቤ በሁለተኛው ምርጫ ነው ለህዝብ ጥያቄ በከፊልም ቢሆን የተንበረከኩት። የተቃዋሚው ፓርቲ መሪ ሞርጋን ቻንጋራይ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑና የአንድነት መንግሥት እንዲቋቋም ተደረገ።

 

በኢትዮጵያም ካለፈው ስህተት ተምረን የህዝባችንን ሞራልና አቅም ገንብተን በሠላም ለውጥ ማምጣት እንችላለን። አማራጭ ሳያመጡ የሌሎችን ሥራ ለሚያጥላሉት እኛ ኢትዮጵያዊያኖች ቦታ ሳንሰጥ ህዝባዊና ሠላማዊ እንቅስቃሴ በሀገራችን ስር እየሰደደ እንዲሄድ ከመቼውም በበለጠ የምንንቀሳቀስበት ጊዜ ነው። ዶ/ር ቡልቻ ደምቅሣ ”ኢትዮጵያ እኮ የኛም ናት” እንዳሉ፤ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ጥቂቶች ብቻ የሚያዙበት ጊዜ እንዳከተመ ማሳየት አለብን። እያንዳንዳችን በተለይ በውጭ የምንኖር ኢትዮጵያውያን፤ በኢትዮጵያ ውስጥ እየታገሉ ካሉ ከነብርቱካን ሚደቅሳ እኩል ለሀገራችን መሥራት ይጠበቅብናል። በሽንፈት ወሬ፣ ባልበሰለ ፖለቲካ፣ በተስፋ መቁረጥ የምንሟሟበት አንዳች ምክንያት የለም። ሊኖረም አይገባም።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ