ብሩክ ግዛው (ከአዲስ አበባ)

ላለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ ከ10 በመቶ በላይ ዕድገት ማሳየቷን መንግሥት በተለያየ ጊዜ እየገለፀ ይገኛል። እንዲያውም ዕድገቱ በዚሁ ከቀጠለ በቀጣዩ 15 እና 20 ዓመታት ውስጥ ዓመታዊ ገቢያቸው ከ765.00 ዶላር በላይ ወደሆኑት የመካከለኛው ገቢ ሀገሮች ትመደባለች ሲል አስረግጦ ተናግሯል። እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ሀገሬ በ20 ዓመት ውስጥ እንኳን ባይሳካ በ30 ዓመት ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ መሰለፍ በቻለችና ህዝቦቿ ጠግበው ማደር ቢችሉ ምንኛ በተደሰትኩ።

 

እኔን ግራ ያጋባኝ “የኢኮኖሚው ዕድገት አሁን ላለው የዋጋ መናር ምክንያት ነው” መባሉ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትራችን በተለያየ ጊዜ ከሚሰጡን መላ ምቶች አንዱ፤ የኑሮ ዕድገት በመከሰቱ የሥራ ዕድል ተፈጠረ፣ የሥራ ዕድል መፈጠሩ ደግሞ የበላተኛውን ቁጥር ጨመረ፣ የበላተኛው ቁጥር ሲጨምር የአቅርቦት እጥረት ተከሰተ፣ የአቅርቦት እጥረቱ ውድነትን አስከተለ፤ ይሄ ደግሞ ሊቀረፍ የሚችለው በግንባታ ላይ ያሉ ፋብሪካዎች በሙሉ ሥራ ሲጀምሩ እየተቃለለ ይሄዳል የሚል ነበር።

 

እኔ ለራሴ እስከዛ ያለው እንቆቅልሽ አልፈታ ብሎኛል። በማታ ትምህርት ያገኘኋትን አንዲት ድግሪ ይዤ ሥራ የተቀጠርኩ ሠራተኛ ነኝ። በደረጃ ዕድገት በትርፍ ሰዓት ሥራ፤ የሞባይል መደወያ ካርድ ተጨምሮ ወደ 3500 ብር አካባቢ ደምወዝተኛ ነኝ። ክፍለ ሀገር ያለች እናቴ የደምወዜን መጠን ሰምታ “አንተማ ሀብታም ነህ” እያለች በነገር መወጋጋት ጀምራለች።

 

ይሄን ያህል የወር ደምወዝ ማግኘት እስከማስታውሰው ቅርብ ግዜ ድረስ ትልቅ ነገር ነበር። በተለይ እንደኔ 150 ብር የነዳጅ መሙያ ገንዘብ ተሰጥቶት መኪና ያለው ከሆነ ያስከብረዋል። አሁን ይኼ ተረት ሆኗል። አንዳንድ ጊዜ ‘ከእኔ እጅግ በጣም ዝቅተኛ በሆነ ደምወዝ ተቀጥረው የሚሠሩ ምኑን ከምኑ እያደረጉት ይሆን የሚኖሩት?’ ስል እጨነቃለሁ፤ ወይስ የኑሮ ውድነቱ ባለቤት ዕቃ ከምሸምትበት እኛ መንደር ብቻ ነው ያለው? ስል አስባለሁ።

 

የምኖረው ከሁለት ልጆቼ ጋር ባለአንድ መኝታ ክፍል ኮንዲሚኒየም ቤት በ900 ብር ተከራይቼ ነው። ከሁለቱ ልጆቼ አንዷን ቀላል ዋጋ ተብሎ 250 ብር በወር ከፍዬ አስተምራለሁ፤ ለወንዱ ልጄ ደግሞ 150 ብር በመክፈል መዋለ ሕፃናት አስተምረዋለሁ። ትምህርት ቤት እናታቸው ስለምታመላልሳቸው በወር ከ60 ብር በላይ የትራንስፖርት እከፍላለሁ።

 

የሕፃናቱ ወተት፣ ምግብ (ቤት የሚበሉትና ለት/ቤት የሚቋጥሩት)፣ ደብተር፣ ልብስ፣ ጫማ የሚያስፈልጋቸው ነገር ተዘርዝሮ አያልቅም። ባለቤቴ የወር ደመወዝተኛ መሆኔን ትረሳዋለች መሰለኝ በየቀኑ ካልሆነ በየሁለት ቀኑ ተጠይቀኛለች። ተደጋግሞ የተነገረ ታሪክ እየደጋገምህ ለምን ታሰለቸናለህ የሚለኝ አንባቢ ያለ አይመስለኝም … ለማንኛውም ወደ ተነሳሁበት ልመለስ።

 

የራሴንና ልዩ ልዩ ወጪዎቼን ደማምሬ ከሚተርፈኝ ላይ ለቤት ወጪ የምሰጣት 1500 ብር አይበቃኝም አለችና ከባለቤቴ ጋር ፍልሚያ ገባን። ነገሩ እየተካረረ በመምጣቱና የቤተሰብ ገላጋይነት በማስፈለጉ ሽማግሌ ገባ። እናም አብረን ገበያ እንድንወጣ ተፈረደብን። ሠላምና መረጋጋት ለማምጣት ገንዘቤን በኪሴ አድርጌ ገበያ ወጣን። “አንደኛ ደረጃ የአድኦ ጤፍ 50 ኪሎ ይበቃናል” አልኩ - 650 ብር፤ ይሄኔ “እንዴ በአንድ ዕቃ 950 ብር ቀረ አልኩ”። ምስር ኪሎው 20 ብር፣ ሦስት ኪሎ ታዘዘ፤ ለወር አስፈላጊ ነው የተባለ ሁሉ ተፈለገና ተገዛ ኪሴ ተመናመነ። “ለወር አይበቃንም ገንዘብ ጨርሻለሁ ያለውን አብቃቂና ባይሆን ለሚቀጥለው ወር …” አልኳት፤ ገንዘብ ከጨረስኩ የመግዛት ሃሳቧን እንደምትቀይር ለቤት ውስጥ አስፈላጊ የሚባሉት ዘይትና ጋዝ ግን እንዳልገዛች ነገረችኝ።

 

እሱ ደሞ ስንት ይሆን ስል በሃሳብ ተዋጥኩ። አራት ሊትር ዘይት 100 ብር ‘አበስኩ ገበርኩ!’ አልኩና ከሌላኛው ኪሴ ተበደርኩ። ‘ጋዙ ደግሞ ስንት ይሆን?’ ወደ ነዳጅ ማደያ አመራን። ሰሞኑን በየመካከሉ እየጠፋ የሚመጣው ነዳጅ ማደያዎቹን ከሚገባው በላይ አጨናንቋቸዋል። እንዲያውም እኛ ስንደርስ በተራ ምክንያት የሚደባደቡ ነበሩ።

 

ማለፍ ስለማይቻል የጋዝ ጄሪካኑን ይዛ እንድትሄድና ገዝታ እንድትመጣ ነገርኳት ለወር የሚያስፈልገን 20 ሊትር ነው፣ 160 ብር እንድሰጣት ጠየቀችኝ። በድንጋጤ ተውጬ ቀረሁ። ባለመረታት ‘ይህን ሁሉ ምን ታደርጊዋለሽ? ለምን መሥሪያ እንደሚያገለግል ዘርዝሪልኝ’ ብሎ መጠየቁ እንደማያዋጣኝ ሳውቅ፤ በይ ብዬ ሂሳቡን አውጥቼ ሰጠኋት።

 

የኑሮ ውድነቱ ኪሴን ማራቆቱ በተቀደደ ካልሲና ጫማ ማስኬዱ አንሶት ከባለቤቴ ጋር የነገር ፍልሚያ አስገጠመኝ። ራሴን ከየትኛው የኅብረተሰብ ክፍል እንደምመድበው ግራ ገባኝ። ከዝቅተኛው ነኝ፤ ከመካከለኛው? እንዳልል አያድርስብን እንጂ አንድ የቤተሰብ አካል ቢታመም የሕክምና ገንዘብ እንኳን የለኝም።

 

የደምወዜን መጠን ሰምታ ቱጃር ያደረገችኝ እናቴ እንደዛ ብትገምት አልፈርድባትም፤ በአፄ ኃይለሥላሴ የሥልጣን ዘመን በመኖሯ እሱን እያወዳደረች ነው ልበል፤ ግን እኔ እራሴ የኖርኩበትን የደርግ ዘመን አሰብኩ፤ የኑሮ ውድነት እየተባባሰ በመምጣቱና በዝቅተኛና በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለው ህዝብ ክፉኛ በመቸገሩ ምክንያት ቢያንስ መሠረታዊ የሆኑትን የምግብ ሰብሎችና ሌሎች የፍጆታ ሸቀጣ ሸቀጦችን እንደ ስኳር፣ ዘይት፣ ሣሙና፣ ክብሪት፣ ፓስታ፣ ማኮረኒ፣ ዱቄት፣ … በየቀበሌው በተቋቋሙ ሕብረት ሱቆች ውስጥ በጣም በቅናሽ ዋጋ ያከፋፍል እንደነበር አስታውሳለሁ።

 

የኑሮ ውድነቱ እጅግ ቢጫነኝም በቅርቡ ከባለቤቴ ጋር በተፈጠረው አለመግባባት ደግሞ የተሰማራሁበትን የገበያ ሁኔታ ስቃኝ ደምወዜ ከ3 ሺህ ብር በላይ በመሆኑ መንግሥት ከዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል ባይመድበኝም ራሴን እዛ አግኝቼዋለሁ። ከኔ በላይ በጣም ያሳሰበኝ ግን መንግሥት ዝቅተኛ ናቸው የሚላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የኑሮ ሁኔታ ነው።

 

በሙያዬ ኢኮኖሚስት ባልሆንም በገዛ ራሴ ላይ እየደረሰ ያለው የኑሮ ውድነት በመላ ምትና በልድ ጨዋታ ለኑሮ ውድነቱ ምክንያት ዕድገቱ መሆኑን ፈፅሞ እንዳምነው አያደርገኝም።

 

ይልቅኑ የኢኮኖሚ ዕድገቱ አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ሊያቅፍ ባለመቻሉ፤ ብዙኀኑ በኑሮ ውድነትና በዋጋ ንረት እየደቀቀ የሚሄድ በመሆኑ በተለያየ መንገድ ሀብት ወደ ካዝናቸው አስገብተው ከደለበ ኪሳቸው እየመዠረጡ “ያጠናነው ጥናት የኢኮኖሚ ዕድገት እንዳለ ያሳያል …” በሚል የተሳሳተ መረጃ ከሚያቀብሉ ኢኮኖምስቶች በጊዜው ዞር ብሎ ለዋጋ ንረቱ መሠረታዊ መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል።

 

መንግሥት በተለያየ ጊዜ የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር የወሰዳቸው እርምጃዎች ምናልባት በረጅም ጊዜ የትኛውን የኢኮኖሚ ሴክተር እያጠናከረ መሄድ እንዳለበት የሚያሳይና ሌሎች ፖሊሲዎቹንም እንዲመረምር የሚያስገድዱት ናቸው።

 

የዋጋ ንረቱ የበለጠ ማሻቀብ እንጂ መቀነስ ባልቻለበት ሁኔታ መንግሥት ከወሰዳቸው ስንዴን በአነስተኛ ዋጋ የማቅረብ፣ የደምወዝ ጭማሪና ሌሎች ርምጃዎች በተጨማሪ የኢኮኖሚ ፖሊሲውን እንዲሁም ዕድገቱን የማጣጣምና የመፈተሸ ሥራ መሥራት መቻል ይኖርበታል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ