ፀረ ሁሉም አቋም የት ያደርሳል? (አዕምሮ በለጠ)
አዕምሮ በለጠ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ) - የአንድነት አባል ከአዲስ አበባ
በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ብዛት ያላቸው ድረ ገፆችና ብሎጎች ብዙ ያጽፋሉ። የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች የአንድነት አመራር አባላት በአውሮፓ እያደረጉ ያሉትን የሥራ ጉብኝት የተመለከተና ጥሩ፣ ሚዛናዊና የራስን አመለካከት በመግለፅ መብት የተፃፉ፤ ግማሾቹ አንድ ፅንፍ ይዘው የሚጓዙ፤ በምክንያትና በጨዋነት ያልታነፁ ጽሑፎችን አንብበናል። እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ በውጭ ሀገር ያላችሁ ወገኖች የምትጽፉትን ከፍቶ ለማንበብ የተለያዩ ሰርቨሮችን መጠቀም ግድ ይላል። ምክንያቱም መንግሥት ስለሚያግዳቸው በቀላሉ ተከፍተው የሚነበቡ አይደሉምና። እንዲህም ሆኖ አግኝተን የምናነባቸው ብሎጎች ፅንፈኛና ለመፃኢ የሀገራችን ሠላምና ልማት፤ ብሎም አሁን ካለው የመጠላላትና የመወነጃጀል ፖለቲካ ፀድቶ አንድ ሀገርን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያንኳስስ፣ ከገዢው የመከፋፈልና የአንባገነንነት አገዛዝና አስተሳሰብ ያልተሻለ፣ በዚያው የተቃኘ ሆኖ እናገኘዋለን።
በውጪ ያሉ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ያገባኛል የሚሉ፣ እንጀራቸውን በፖለቲካ ፍም የሚያበስሉ እና ተራ የሀገር ተቆርቋሪ ዜጎች ሁሉ ከሀገራቸው በተሻለ ሃሳባቸውን በነፃነት ያራምዳሉ፤ ድረ ገፆችን በመክፈት፣ ፖል ቶክ በማዘጋጀት ይወያያሉ - ያለ አንዳች ስጋት። እነሱ (እናንተ) በዚህ ነፃነት ውስጥ ስትኖሩ እኛ እዚህ ሀገር ውስጥ ያለነው ግን እናንተ የፃፋችሁትን ለማንበብ እንኳ ከቴሌ ጋር የሌባና የፖሊስ ጨዋታ መጫወት ይጠበቅብናል። እንዲህም ሆነን አግኝተን ስናነባችሁ በምዕራቡ ዓለም ለምትኖሩ ዜጎቻችን የምንሰጣችሁን ክብር እንድንነሳችሁ፤ ከስሜታዊነትና ከእውቀት የራቃችሁ (ይቅርታ) መሆናችሁን እንድንታዘብ ታደርጉናላችሁ። በርግጥ ሀገራዊ አጀንዳን አንግበው ከስሜትና ከጥላቻ ርቀው ልባዊ ስሜታቸውን የሚገልፁ አያሌ መኖራቸውን ሳንረሳ ነው።
ሰሞኑም በሊ/መንበሯ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳና በሥራ አስፈፃሚው አቶ አክሉ ግርግሬ የሚመራ የአንድነት ፓርቲ የልዑካን ቡድን የተለያዩ የአውሮፓ ከተሞችን በመጎብኘት አባላትና ደጋፊዎች ፓርቲው የተመሰረተበትን መርኅና ዓላማ ለማስረዳት፤ አጠቃላይ የፖለቲካ ሥራ ለመሥራት ተጉዟል። የልዑካን ቡድኑ አውሮፓን ከመርገጡ በፊት ጀምሮ አንዳንድ ብሎጎች ዲያስፖራው ድጋፍ እንዲነፍገው ጥሪ እስከማስተላለፍ ደርሰዋል። በስብሰባው ላይ የሚገኝ ቢኖርም “እርሱ የኢትዮጵያ ጠላት ነው” ሲሉ አውጀዋል። አንድነትንም የኢህአዲግ ሽፋን ሰጪ፣ የዓለም ኅብረተሰብ ጫና እንዳያሳድርበት መንገድ የሚዘጋ እና ሠላማዊ ትግል ኢትዮጵያ ውስጥ የትም አያደርስም እያሉ ሲጽፉ ሰንብተዋል። አሁንም ስድብና ዛቻ ጨምረው እየፃፉ ነው። የሀገር ውስጥ ፖርቲዎችንም ጥንብ እርኩሳቸው ሲወጡ ሰንብቷል።
ማንም ሰው የፈለገውን ሃሳብና ዓላማ የማራመድ፣ ከፈለገም ሌላውን የመተቸት መብት እንዳለው ታፍነን እንኳ የምንስማማበት ሐቅ ነው። እዛ በነፃነት የሚንቀሳቀሱትና የሚጽፉትም ይሄ መብት እንዳላቸው ስላረጋገጡ ነው። ነገር ግን የሌላውን ሃሳብና ዓላማ ለማጣጣል ተገቢውን አመክንዮ (ሎጂክ) በማቅረብና የራስ ሃሳብ ሚዛን እንዲደፋ ከማድረግ ይልቅ፤ ስድብን፣ ስሜታዊ አስተያየቶችን ታስቀድማላችሁ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ያለእናንተ አስተያየትና ድጋፍ የትም የማይራመድ፤ ሀገር ውስጥ ካለው ይልቅ እናንተ ደርሶ የሀገር ወዳድ ትሆናላችሁ። ከነገ ዛሬ ይቅርታቸው ተነስቶ ዘብጥያ ሊወርዱ እንደሚችሉ እያወቁ መንግሥትን የሚሞግቱ እያሉ፤ በተደላደለ ኑሮ የሚኖሩትን ለማሞካሸት ትጥራላችሁ፤ እዚህ ሀገር ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በተግባር ከመፈተን በሩቅ ሆናችሁ የቃላት ጀግና ትሆናላችሁ፤ የምትደርሳችሁ ቁንፅል መረጃ ላይ ተንተርሳችሁ ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ተንታኝና አዋቂ ትሆናላችሁ (በርግጥ የመረጃ ዘመን ላይ ብንሆንም አይተን ከምንዳስሰው አትበልጡም)። ከዚህ ሁሉ አልፎ ጠላትና ወዳጅ በሚል ክፍፍል ውስጥ ገብታችሁ ትጎነታተላላችሁ። በሠለጠነ ዓለም እየኖራችሁ …
ጠላትና ወዳጅ እስከመቼ
… ከዚህ ልዑካን በፊት በፕሮፌሠር መስፍንና በአቶ አስራት ጣሴ (የአንድነት ዋና ፀሐፊ) የሚመራ ቡድን በአሜሪካን ስምንት ስቴቶች ጉብኝት አድርጎ መመለሱ ያታወሳል። በዛ ጉብኝት ወቅት ፕሮፌሠር መስፍን በአንድ መድረክ ላይ “ወያኔ ጠላት አይደለም” በማለታቸው ስፍር ቁጥር የሌለው ነቀፋን አስተናግደዋል። የአሁኑ የነወ/ሪት ብርቱካን ጉብኝት ላይም እነዛው ድረ ገፆችና ብሎጎች ጠላትን ትከላከላላችሁ ሲሉ እየከሰሷቸው ነው።
ከዚህ ቀደም የትግራይ ልማት ማኅበር በአንድ ቀን 146 ሚሊየን ብር የሰበሰበበትን የቴሌ ቶን ዝግጅት ቪዲዮ ያያችሁ የዲያስፖራው አባላት የትግራይን ህዝብ ጠላት አድርጋችሁ ስትፅፉ እንደነበረ የቅርብ ትዝታችሁ ነው። ያሁኑም ከዚህ የተለየ አይደለም። ማንም የፖለቲካ መጠቀሚያ፣ ማንም ተጠቃሚ ሲሆን አብሮ ነገሮችን መግፋት የብስለት፣ የትምህርት፣ በነፃነት የማሰብ ውጤት አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ አቋቁሞ ለሚታገል ፓርቲም (በተለይ ለአንድነት) የህዝብ ጠላት የለውም። የሰው ጠላት የለም የሃሳብ እንጂ።
የአንድ ሀገር ልጆች ሆነን የራሳችንን ቡድን (ብሔር፣ ፓርቲ) ፍላጎት ብቻ አንግበን የምንነሳ፤ አንዱን ጠላት አንዱን ወዳጅ የምናደርግ ከሆን ከኢህአዲግ ከፋፍለህ ግዛ በምን ተሻልን? እናስብላታለን የምንላት ሀገርስ ዘለቄታዊ ሠላምና አንድነትን እንዴት ልታገኝ ትችላለች? ኢትዮጵያዊያን የተባልንስ በዚህ አስተሳሰብ ታስረን እንዴት የሚፈለግብንን በመወጣት ያሰብነው ቦታ ለመድረስ እንችላለን? ጠላት ካለ ፍርሀት አለ። ጠላት ካለ ለማጥፋትና ለመጠፋፋት ማሻጠር የማይቀር ነው። በዚህ ሁኔታ ደግሞ ሀገር ሀገር አትሆንም። እንወዳታለን የምንላትስ ሀገር የቷን ነው? ሀገር ማለት ተራራው፣ መሬቱና ወንዙ ብቻ ነው እንዴ? ህዝቡስ ሀገር የሚያስጠራ፣ ሀገር የሚያስብለው? ደግመን እንላለን የሰው ጠላት የለንም የሃሳብ እንጂ።
የዲያስፖራ ፍራንክ የትግልን ውጤት አይወስንም
ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ በሀገር ቤት ካለው ህዝብ በተሸለ የኢኮኖሚና የትምህርት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የብዙዎቻችን እምነት ነው። በርግጥም በኢኮኖሚ ያደገ ሀገር የተሻለ ይከፍላል፣ የተሻለ ያስተምራል። በዚህም ምክንያት አብዛኛው የፖለቲካ ፓርቲ በውጭ ከሚገኙ ወገኖቹ የገንዘብም የእውቀት ዕርዳታን ይፈልጋል፤ ይጠይቃል። የተወሰኑት ፓርቲዎች ይህን እያገኙ በተሻለ እንቅስቃሴ ውስጥ ይገኛሉ። ነገር ግን ከውጭ በመጣ እውቀትና ገንዘብ ብቻ የኢትዮጵያ ችግር አይፈታም። አንድን ፓርቲ ፓርቲ የሚያደርገው በሀገር ውስጥ የሚኖረው የአባላት ብዛት፣ ጥራትና ቆራጥነት ነው። ትግሉም የነሱ የሥራ ውጤት፣ የነሱ የገንዘብ ውጤት፣ የነሱ የእውቀት ውጤት ነው የሚሆነው።
መንግሥት ፓርቲዎች ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ደጋፊዎቻቸው ገንዘብ እንዳይሰበስቡ የተለያየ እንቅፋት እየፈጠረባቸው እንደሆነ የታወቀ ነው። በሀገር በውስጥ ስሙን ጠቅሶ ገንዘብ ለፓርቲ መርዳት መዘዙ ስለሚከፋ ማንም ያደርገዋል ተብሎ አይጠበቅም። በውጭ ያላችሁ ግን ከየትኛውም ተፅዕኖና ማስፈራሪያ ነፃ ስለምትሆኑ ገንዘባችሁን ለምትደግፉት ፓርቲ ትለግሳላችሁ። ይህም ፓርቲዎቹ ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር እንድትሞክሩ ሊያደርጋችሁ ይችላል። ነገር ግን ፓርቲዎቹ ከዲያስፖራው ተፅዕኖ መላቀቅ ይኖርባቸዋል። ከዲያስፖራው ገንዘብ የህዝብ ተቀባይነት፣ ለአንድነት፣ለዲሞክራሲና ለፍትህ በሚከፍሉት መስዋዕትነት የሚያመጡት ውጤት ይበልጣል። ፍሙ ያለው እዚህ፤ የሚፈጀውም እዚህ ያሉትን ነው።
ሠላማዊ ትግል አያዋጣም?
(በዚህ ጉዳይ ላይ አውደ ብቻ ብዙ ጊዜ ጽፋለች) አንድነትም ሆነ ሌሎች የሀገር ውስጥ ሠላማዊ ታጋይ ፖለቲከኞች በዲያስፖራው የሚተቹት ሠላማዊ ትግል ላይ ሙጭጭ በማለታቸው ነው። ሠላማዊ የሚሉት ትግል እንደሰሞኑ ላሉት ድረ ገፆች የየዋህ ጨዋታ፤ ውጤት የማያስገኝ ነው። ስለዚህ ጠላት የሚሉትን ወገን ደፍጥጦ ማጥፋት ያስፈልጋል። ይህንን ለማድረግም ጫካ መግባት፣ ብረት ማንሳት፣ የደም ግብር መክፈል፣ ያለችውን መሰረተ ልማት ማጥፋት፣ … ከሠላማዊ ትግል ውጪ ያለው አማራጭ ይሄ ነው። ይሄ ደግሞ 3000 ዘመን ቆጠረች ለምንላት ሀገር ሲጠቅም አላየንም። በድህነት፣ በበሽታ፣ በጠላትነት በመፈራረጅ ከመኖር በቀር።
በጣም የሚገርመው “ሠላማዊ ትግል አያዋጣምን፤ ጠላትን ማጥፋትን” የሚያቀነቅኑት ሰዎች ኦባማ ባሸነፈበት ሀገር ውስጥ ተቀምጠው መሆኑ ነው። ሰውዬው አሜሪካንን ለመምራት ሲመረጥ የነጭ ጠላት በሆኑ ጥቁሮች ድምፅ አልነበረም፤ ባለው ጨዋ የፖለቲካ ቅስቀሳና የፖሊሲ አማራጭ እንጂ። ኦባማ ሲወለድ የጥቁሮች እኩልነት በአግባቡ አልተረጋገጠም ነበር። አሁን ጎልምሶ ግን ጥቁር ፕሬዝዳንት እንዲሆን፤ አሜሪካ እንደቀድሞ የአንድ የተወሰነ ቡድን ሀገር ሳትሆን የተባበረች አሜሪካ እንደሆነች፤ ህዝቦቿም የቀለም ሳይሆን የሀገራቸው ጉዳይ፣ ቀለም ሳይሆን የሃሳብ የበላይነት መሆኑን ያሳዩበት ምርጫ ነበር። የሠለጠነ፣ የሠላማዊ ትግል ውጤት ይሄ ነው።
በማይዋዥቅ አቋም እንገፋለን
አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በሀገር ውስጥ እያገኘ የመጣው ድጋፍ አስገራሚ ሊባል የሚችል ነው። ብዙ ጊዜ ፓርቲው ስለዚህ ተቀባይነቱ ሲገልፅ የቅንጅት ሕጋዊም ሞራላዊም ወራሽ በመሆኑ እንደሆነው። ለኔ ግን ይህ ብቻ የተቀባይነቱ ምስጢር ነው አልልም። ቅንጅት ህዝብ ልብ ውስጥ የገባው በተሻለ ሁኔታ ለህዝብ ቅርብ የሆኑ፣ የተሻለ እውቀት፣ የተሻለ የሀገር ፍቅር በነበራቸው ሰዎች የተመሰረተ ፓርቲ ስለነበር ነው። ነገር ግን ይህንን እውቀትና የሀገር ፍቅር አለአግባብ ስለተጠቀሙበት፣ በራሳቸው ዲሞክራሲያዊና ግልፅ ስላልነበሩ ለመበታተን በቅተዋል። ይሄ የመበታተን ዕጣ የደረሰው ፓርቲ እንደገና ህዝብ ጋር ሲቀርብ ለምን ተቀባይ ሆነ? ሲነኩት የሚበረግግ፣ ሲገፉት የሚንከባለል ፓርቲ አልነበረምን? ለኔ መልሱ “አዎ!” ነው።
አንድነት ግን ከዚህ ልምድ ነፃ ወጥቷል። ከቅንጅትም ይለያል። በርግጥ ለዘብተኛ ዲሞክራሲን በመከተል ከቅንጅት ጋር ይመሳሰላል። መመሳሰል ብቻ ሳይሆን መሪዎቹ አባላቱ፣ ደጋፊዎቹና የሚከተለው መርኅ የቅንጅትን ነው። (አንባቢ ቅንጅት ሲባል የቀድሞ መሆኑን አያጣውም)። ነገር ግን ወረቀት ላይ በሰፈረው፣ በተነገረን፣ በሰዎች ተክለ ስብዕና የተከተልነው ቅንጅት እንደተፈረካከሰው ያይደለ፤ በሕግ፣ በሥርዓት፣ በፓርቲ ዲሲፕሊን መታነፅን እንገመግማለን። ፍፁም የሆነ ሰውም ድርጅትም ባናጠብቅም ነገ ሊንሸራተቱ በሚችሉ ስብዕናዎች ላይ ሳይሆን፤ የፓርቲው የመርኅ መሰረት ላይ ቆመን ከላይ እስከታች ያሉ የፓርቲው መሪዎችን እንጠይቃለን፣ እንከሳለን፣ እንተቻለን። ትግሉ ህዝብን የሥልጣን ባለቤት ማድረግ እንጂ ሰዎች የማግዘፍ አይደለም። በዚህ አቋም ሳንዋዥቅ ድጋፋችንን፣ ትግላችንን እናካሂዳለን።
አንድነት በማይዋዥቅ አቋም የሚያስኬደው የድርጅት ጥንካሬን በመገንባት ላይ ይገኛል። ይህም እንደሚሳካ ምልክቶችን እያየን ነው። ፓርቲው በዓላማ ፅናቱ ለመቀጠል የዲያስፖራው ድጋፍ ግድ የሚያስፈልገው፤ የሚያንገዳግደው የዲያስፖራው ነቀፋ አይደለም። ፓርቲው በህዝብ ውስጥ የመግባቱ፣ የተቀባይነቱ ቋንቋ አንድነት፣ ዲሞክራሲ፣ ማኅበራዊ ፍትህና ሁሉን አሳታፊነቱ ነው። ይህ ደግሞ በፅናት መቆምን፣ መስዋዕትነትን፣ ጠንካራ ድግፍን ይፈልጋል። የቻለ፣ ለሀገሬ ያለ ይደግፋል። የአንድነት ቋንቋ አንድነት፣ ዲሞክራሲና ፍትህ ለኢትዮጵያ ህዝብ ነው። ይህም በሠላማዊና ሠላማዊ ትግል ብቻ የሚገኝ ነው።
አዕምሮ በለጠ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )
የአንድነት አባል
ከአዲስ አበባ