እኛ ብንተባበር (ግርም ካሣ)
ይህን ሕግን የሚንቅ ሥርዓት ማስወገድ እንችላለን!
ግርም ካሣ (ቺካጎ) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. (ታህሳስ 24 ቀን 2001 ዓ.ም.)
ፕሮፌሠር መስፍን ወልደማሪያም ዋሽንግተን ዲሲ የአንድነት ፓርቲ ልዑክ ቡድን አባል ሆነው ለኢትዮጵያውያን ንግግራቸውን የጀመሩት በፀሎት ነበር። “አምላክችን ሆይ! ኢትዮጵያ ተቸግራለች። እኛም ተችግረናል። እባክህ ፍቅርን ስጠን!” ብለው እግዚአብሔርን ሲማጸኑ ከዓይኖቼ እንባ ፈሶ ነበር። በኢንተርኔት ብቻዬን እከታተል ስለነበረም ድምጼን ከፍ አድርጌ “አሜን!” ብዬ ጮህኩኝ።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከቃሊቲ እስር ቤት በተፈቱ ጊዜ ከጀርመን ድምፅ ሬዲዮ ጋር ያደረጉት አንድ የማልረሳው ቃለምልልስ ነበር። “ስላሰሯቹህ ሰዎች ምን ትላላችሁ? እንደጠላት ነው ወይ የምታይዋቸው?” ተብለው ሲጠየቁ “ቅንጅት የሰው ጠላት የለውም” በማለት ነበር እርሳቸውና አብረዋቸው የታሰሩ ጓደኞቻቸው በጥላቻና በቂም በቀል ያልተሞሉ፣ ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ በኢትዮጵያ መረጋጋት ሠላምና እርቅ እንዲመጣ የሚፈልጉ መሆናቸውን ያሳዩን።
የቀድሞ ቅንጅት አሁን አንድነት አመራር አባላት በዳያስፖራ ካሉ አንዳንድ አካላት ከፍተኛ ተቃውሞ እየደረሰባቸውም ቢሆን “ወያኔ ጠላት አይደለም። የምናደርገው ትግል ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያን ለመጥቀም ዓላማው ያደረገ ትግል እንጂ ፀረ-ወያኔም ሆነ ፀረ-ማንም ትግል አናደግርም።” እያሉ በድፍረት ህዝቡን አስተምረዋል።
እኛም የነዚህን ሠላማዊ የዲሞክራሲ ጀግኖች ጥሪ ተከትለን አብረናቸው የሠላም፣ የዕርቅ፣ የወንድማማችነትና የፍቅር መልዕክት ስናስተጋባ ቆይተናል። “አሁን በሥልጣን ላይ ካሉት ጋር መነጋገርና መወያየት ያስፈልጋል። እነርሱን መለወጥ እንችላለን” በሚል ነጩን የሠላም ባንዲራ አውለብልበናል። ምላሹ ግን መሪዎቻችንን በሰደፍ መደብደብና በግፍ ቃሊቲ ማወረድ ሆነ።
አዎ! መስሎን ነበር፤ በአራት ኪሎ ያሉ ባለሥልጣናት የሚሰሙን። መስሎን ነበር አዕምሮና ልብ ያላቸው። መስሎን ነበር ከዚህ በፊት ከሚሄዱበት መንገድ ሊመለሱ የሚችሉ።
ከጊዜ ወደ ጊዜ የምናየው ግን ተስፋ የምናደርገውን ሳይሆን አንገታችንን የሚያስደፋውን ነው። ልባችንን በደስታ የሚሞላ ሳይሆን ውስጣችንን የሚያቆስል ነው። ፍቅርና ይቅርታን የሚያወሩ እነ ቴዲ አፍሮ በግፍ ሲታሰሩ፣ የሠላምና የሰብዓዊ መብት መከበር ሐዋርያ የሆኑት እነ ፕሮፌሠርን መስፍን ወልደማሪያም ሲደበደቡ፣ ለፍትህና ለኢትዮጵያ አንድነት የቆሙ እነ ብርቱካን ሚደቅሳ ወህኒ ሲጣሉና የጭካኔ የዛቻ የትዕቢት የውሸትና የሸፍጥ ፖለቲካ እየበዛ ሲሄድ ነው የምናየው።
የአሜሪካን ድምፅ ራዲዮ ባልደረባ አቶ ሠለሞን ክፍሌ ከፕሮፌሠር መስፍን ወልደማሪያም ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ ሳዳምጥ ኀዘን ብቻ አልነበረም የተሰማኝ ሐፍረትም እንጂ። ተሸማቀቅሁ። “ኢትዮጵያዊ ናቸው። የኔ ወንድሞች ናቸው” የምላቸው ወገኖች እንዲህ አይነት ሥራ ሲሠሩ ሳይ “ምን አይነት ትውልድ ሆነናል?!” ብዬ አዘንኩኝ።
እስቲ አስቡት! የሰባ ስምንት ዓመት አዛውንትን በሰደፍ መደብደብ ስብዕና ይባላልን? አውሬነት እንጂ። እስቲ አስቡት! አንዲትን ሴት በአራት መኪናና በአሥር ደህንነቶች እያዋከቡ እያንገላቱና እየገፉ መንዳት ሕግን ማክበር ይባላል? ውንብድና እንጂ።
ኢህአዲግ ውስጥ ጥሩ ልብ ያላቸው ፓርቲውን ወደ ቀናው መንገድ ሊመሩት የሚችሉ ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ተስፋ ነበረኝ። አሁንም እነዚህ ሰዎች አሉ ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን በዚህ ሣምንት ከታየው አሳዛኝ ሁኔታ አንድ በግልጽ የደረስኩበት ድምዳሜ አለ። እርሱም ኢሕአዲግን ወደ ጥሩ አቅጣጫ ሊወስዱ የሚችሉ ኃይላት በፓርቲው ውስጥ ምንም ለውጥ ሊያመጡ እንዳልቻሉና በነርሱ ተስፋ ማድረግ ከአሁን በኋላ የሚያዋጣ እንዳልሆነ እየታየኝ ነው።
“ታዲያ ምንድን ነው የሚያዋጣው?” ብላችሁ ብትጠይቁኝ በቀዳሚነት አንድ ነገር አጉልቼ እናገራለሁ። መፍትሔው የሚያዋጣው በአንዲት ኢትዮጵያ የምናምን በሀገራችን ዲሞክራሲ እንዲሰፍን የምንሻ ሁሉ በቅንነት እርስ በርስ ከመጠቃቃት ተቆጥበን በሚያስማሙን ነገሮች ላይ መተባበሩ ብቻ ነው።
ለዚህም እንዲረዳ የሚከተሉትን ነጥቦች ለፖለቲካ እና ሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ለመገናኛ ብዙኃን በአክብሮት አቀርባለሁ።
1. እያንዳንዱ ድርጅት ሌላውን ከመንቀፍ ተቆጥቦ በሚሠራው ሥራ ላይ ያተኩር። በሥራው ውጤት የሚያመጣ ድርጅት ምንም በሌሎች ቢተችም በህዝብ መደገፉ አይቀሬ ነው። ኢትዮጵያውያን ወሬ ሳይሆን ውጤት ነው የሚፈልጉትና።
2. በሌሎች ድርጅቶች የድጋፍ ካልሆነ የጥቃት መግለጫ ማውጣት፣ የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎችን መሳደብ ይብቃ!
3. በመግለጫዎቻችን በመገናኛ ብዙኃኖቻችን የምናወጣቸው በእውነት ላይ የተመሰረቱ ያልተለጠጡና ያልተጋነኑ ይሁኑ! የሠለጠነ ስብዕና ያለን ጨዋ ኢትዮጵያውያን መሆናችንን በዚህ እናሳያለን።
4. “የሠላማዊ ትግል አይሠራም፤ የትጥቅ ትግል አይሠራም” እያልን መከራከራችንን እናቁም። እኔ ሠላማዊው ትግል የሚበጅ አማራጭ ነው እላለሁ። ይህ አቋሜ ይከበርልኝ። “አይ ወያኔ በጠመንጃ ካልሆነ አይቻለም” የሚሉ ደግሞ እነርሱ ይዘናል ባሉት መንገድ ይቀጥሉበት። አቋማቸው ይከበርላቸው። “ይሄ ይበጃል ያ ይበጃል” የሚለውን ክርክር ሂደት የሚወስነው ይሆናል።
5. ሕብረት መፍጠሩ ጠቃሚ ቢሆንም በችኮላ ሕብረት መፍጠሩ ጉዳት ሊያመጣ ይችላል። ሕብረት መፍጠሩ ላይ አሁን ከማተኮር ቢያንስ ቢያንስ በጋራ የሚሠሩ ሥራዎች ላይ አብሮ የመሥራትን ባህል ማዳበር ይጠቅማል። የጋራ ህዝባዊ ሠላማዊ ሰልፎችን ለማድረግ፣ የጋራ መግለጫዎችን ለማውጣት ያስችል ዘንድ ከሁሉም ወገን የተውጣጣ አንድ ግብረ ኃይል፣ የዲፖሎማሲውን ሥራ በቅንጅት የሚሠራ ሌላ ግብረ-ኃይል በአስቸኳይ እንዲቋቋም ያስፈልጋል። ሥራው አንድ አይነት ሆኖ በአሥር ገመድ በተለያዩ ድርጅቶች መጎተት የለብንም። አሜሪካኖችና አውሮፓዊያኖችም ቢሆኑ ከሃያ ድርጅቶች መስማት አይፈልጉም። በአንድ ድምፅ ካልተናገርን ይንቁናል።
ውድ ኢትዮጵያውያን እነብርቱካን ሚደቅሳ በቃሊቲ እየተሰቃዩ ነው። እነፕሮፌሠር መስፍን ሰደፍ አርፎባቸዋል። ያለፉትን ልዩነቶቻችንን አቻችለን ከዚህ በፊት ለተነጋገርነውና ለተቀያየምነው ይቅር ተባብለን ለአንዲት ኢትዮጵያ በጋራ ለመሥራት ክብራችን መዋጥ ያቅተናልን? አያቅተንም። እንችላለን።
ትንሹ ዳዊት ግዙፉን ጎሊያድ ጥሏል። እኛ ከተባበርን፣ እኛ ከተደጋገፍን የማንወጣው ተራራ የለም። እኛ እንተባበር፤ በርግጥ ይህ ሕግን የሚረግጥ ሥርዓት ሲወገድ እናያለን። ጥያቄው “እንችላለን ወይ?” አይደለም፤ ጥያቄው “ፍላጎቱ አለን ወይ?” የሚል ነው።
ግርም ካሳ (ቺካጎ) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ታህሳስ 24 ቀን 2001 ዓ.ም.



