Pfro. Mesfin W/Mariamፕ/ር መስፍን ወልደማርያም (ታኅሳስ 2001)

ፕሬዝዳንት ሙጋቤ የብዙዎቹ የአፍሪካ መሪዎች ዓይነተኛ አብነት ናቸው፤ ፕሬዝዳንት ሙጋቤ ሲጀምሩ የነፃነት ታጋይ አርበኛ ሆነው ነበር። በዚያን ጊዜ ሮዲዝያ በሚባለው ሀገር የሚኖሩ ነጮች፣ የደቡብ አፍሪካ ነጮችን አብነት ተከትለው፣ የነጮች የበላይነት የሠፈነበት አገዛዝ የዛሬ ሠላሳ ሦስት ዓመታት ግድም በጉልበት መሠረቱ፤ ሁለት የዚምባብዌ መሪዎች ጫካ ገቡና የትጥቅ ትግል ጀመሩ። የጎረቤት የአፍሪካ ሀገሮችና ሌሎችም እየረዱዋቸው፣ ውጊያቸውን ቀጠሉ፤ እንግሊዞች ባዘጋጁት እርቅ የትጥቅ ትግሉ አብቅቶ ወደ ሠላማዊ የፖለቲካ ትግል ገቡ።

 

የሠላማዊ የፖለቲካ ትግሉን ቀደም ብለው ሲያካሂዱ የነበሩ ሙዜሬዋ የሚባሉ ጳጳስ የፖለቲካ መሪ ነበሩ፤ ሙጋቤና ንኮሞ ከጫካ ከነወታደሮቻቸው ሲገቡ ጠመንጃ የበላይነትን እየያዘ መጣና ሙዜሬዋ ጫካ ባለመግባታቸው፣ የነጮች አቀንቃኝ እየተባሉ ይዘለፉ ጀመረ። እርቁን ተከትሎ በተደረገው ምርጫ፣ ሙጋቤ የበለጠ የህዝብ ድምፅ አገኙና በሥልጣን ወንበሩ ላይ ወጡ። ነጮቹ በጣም ያለሙት ትልቅ ሀገር ለሙጋቤ፣ ለንኮሞና ለሙዜሬዋ አልበቃም አለ። ሙጋቤ ሁሉንም እየጠለፉ ጣሉና ሥልጣን የግሌ ነው ብለው ሙጭጭ አድርገው ያዙ።

 

በአፍሪካ ደረጃ ከፍተኛ የነበረው የልማት ሁኔታ ቀስ በቀስ እየወረደ፣ የዚምባብዌ ህዝብ በችጋር የሚጠቃበት ደረጃ ላይ ደረሰ። የነጮቹን ሠፋፊ እርሻ ለመከፋፈል የተወሰደው እርምጃ፣ የሙጋቤን የማን አለብኝነት የጡንቻ አስተሳሰብ የሚያሳይ ነው። ህዝቡ በነጮቹ እርሻ ላይ እንዲዘምትና እንዲዘርፍ አደረጉት። በመውደቅ ላይ የነበረው የሀገሩ የልማት ሁኔታ መንኮታኮት ጀመረ፣ የዚምባብዌ ገንዘብ ክፉኛ ጥንቡን ጣለ፤ አንድ ዳቦ ለመግዛት ብዙ ብር መሸከም አስፈለገ። በሙጋቤ የጭካኔ አገዛዝ ምክንያት፣ ምዕራባውያን መንግሥታት እየጮሁ በሀገሩ ላይ የተጣለው የኢኮኖሚ ማዕቀብ ህዝቡን በችጋርና በችግር አደማው፤ በዚያ ላይ ትንሽ ተቃውሞ የሚያሳየውን ሁሉ በጥይት እያነደዱ፣ በጉልበት መንዳት ልማድ ሆነ፤ ፀጥ-ለጥ አድርጎ የመግዛት ዘዴና ልማድ ተስፋፋ።

 

ህዝቡ መከራውና ችግሩ እያየለበት ሲኼድ፣ በብዛት የተቀናቃኝ የፖለቲካ ቡድኖችን መደገፍ ጀመረ። የአገዛዙ ቀኝ እጅ ከሆኑትም ውስጥ ወደ ተቀናቃኝ ጎራ ዞሩ። በተቀናቃኝ ቡድኑ ጎራ መሪ እንዳይኖር ለማድረግ ብዙ ተሞከረ፤ መሪውን ይዘው እንዳይሞት እንዳይሽር አድርገው ለቀቁት። ለጥቂት ጊዜ በደቡብ አፍሪካ ተጠልሎ ካገገመ በኋላ ተመለሰ። የምርጫውን ሥርቆት አንድ ፖሊስ በስውር ካሜራ አንስቶ ለቢቢሲ በመስጠት አጋልጦታል። ያም ሆኖ የተቀናቃኝ ቡድኑ መሪ አሸነፈ፤ ሙጋቤ ግን “እንዴት ተብሎ” ብለው አማላጆችንም ሽማግሌዎችንም እያሳፈሩ መለሱ። በምርጫው ቢሸነፉም ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲቀጥሉና የተቀናቃኙ ቡድን መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆን አስታራቂዎች ውለታ አስገብተዋቸው ነበር፤ ስምምነቱንም እስከ ዛሬ አላከበሩም።

 

ሰሞኑን ደግሞ የሙጋቤ የጭካኔ አገዛዝ ክፉኛ የሚጋለጥበት ነገር አጋጠመው። በሀገሩ የውሃ ችግር በመከሰቱ ሰው ሁሉ ያገኘውን የተበከለ ውሃ እየጠጣ የኮሌራ በሽታ ተዛመተና ብዙ ሰዎችን ጨረሰ፤ አሁን ያለው ግምት ከአንድ ሺህ ሰዎች በላይ መሞታቸው ነው፤ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ በሕመሙ እየተሰቃዩ ነው። ፕሬዝዳንት ሙጋቤ ግን በሀገራቸው የኮሌራ በሽታ ችግር እንደሌለ ይናገራሉ፤ እሳቸው ዘንድ መቼም አይደርስምና በምን ይወቁት! በሽታው ግን ድንበር-ዘለል በመሆኑ ወደ ደቡብ አፍሪካ ጠረፍ ስለደረሰ፣ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት አካባቢውን “የአደጋ ክልል” በማለት ዐውጆ የሕክምና ባለሙያዎችን ልኮ እየተከላከለ ይገኛል። በመካድ ችግሩን የሚያስወግዱት የሚመስላቸው የአፍሪካ መሪዎች ብዙ ናቸው።

 

ዓለም በሙሉ የሚጮህበት፣ ብዙ ግፍ በሚሠራበት ሀገር አልፎ አልፎ አንዳንድ አስገራሚ ነገሮች ብቅ ይላሉ። እኔን ያስገረመኝ የአንድ ፖሊስ ታሪክ ነው። ሁኔታውን ሁሉ ከተመለከተ በኋላ የተቀናቃኙ የፖሊቲካ ቡድን አባል ይሆናል፤ ይያዝና ታስሮ ፍዳውን ይበላል፤ ከዚያም ከሥራው ይታገዳል። በፍርድ ቤት ክስ ይመሰርትና ይፈረድለታል። ከነበረበት ዝቅተኛ ሥራ ላይ ተመድቦ፣ ዱሮ ከነበረው ደመወዝ ግማሽ ብቻ እያገኘ እንዲሠራ ይደረጋል። የዚምባብዌ ፍርድ ቤት የፖሊሱን መብት ማስከበሩ ያስገርማል።

 

በነፃነት ታጋይነት ወንበሩ ላይ የወጡት ሙጋቤ ዛሬ የነፃነት ጠላት ሆነው ከነጮቹ አገዛዝ ዘመን በከፋ ሁኔታ ውስጥ ጨምረውታል። ሆኖም ለዚምባብዌ ህዝብ ፍርድ ቤት ካለ፣ አንዱ የዚምባብዌ ስደተኛ “ሰው ሁሉ እየወጣ ድንጋይ ብቻ የሚቀርበት ሀገር ይሆናል” ያለው ትክክል አይመስለኝም።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ