ርዕዮት ዓለሙ

ማንኛውም ግለሰብ፣ ተቋም፣ ድርጅት ወይም መንግሥት በተለይ ከደረሱበት ችግሮች በመነሳት እንደስህተት የሚያስቀምጣቸው ድርጊቶችና አመለካከቶች ይኖሩታል። ግለሰቡ ወይም ድርጅቱ ስህተቶቹን በትክክል መፈተሽ ካልቻለ በእውነተኛ ስህተቶቹ ፋንታ ስህተት ያልሆኑትን እንደ ስህተት ሊወስዳቸው ይችላል። ይህም እውነተኛውን ስህተት በማረም ፋንታ ሌሎች ስህተቶች የሆኑ “የስህተት ማረሚያ እርምጃዎችን” እንዲወስድ በማድረግ ለተደጋጋሚ ስህተት ይዳርገዋል።

 

ከዚህ በመነሳት ኢህአዲግ እየወሰዳቸው ያሉትን እርምጃዎች ብንመለከት “ስህተቶች” ያላቸውና ስህተቶቹ ያልነበሩ ጉዳዮች የትኞቹ እንደሆኑ በቀላሉ ለመገንዘብ እንችላለን። በቅርብ ጊዜ ከወጡ አዋጆች ውስጥ እንደየሲቪል ማኅበራትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን አዋጅ ብንወስድ የኢህአዲግ “የስህተት ማረሚያ እርምጃ” መሆኑ አያጠያይቅም።

 

ይህ አፋኝ አዋጅ ኢህአዲግ በምርጫ ዘጠና ሰባት ለደረሰበት ኪሳራ እንደምክንያት ካስቀመጣቸው “ስህተቶቹ” ውስጥ “ለሲቪል ማኅበራትና ለመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ነፃነት መስጠት” የሚል እንደሚገኝበት ያሳብቃል። ከአስር በመቶ በላይ ገቢያቸውን ከውጪ የሚያገኙ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በውጪ ድርጅትነት መመዝገባቸውና የመብት ጉዳዮች ላይ እንዳይሠሩ መከልከላቸው፤ ኢህአዲግ ካለፈው ስህተቱ ለመማሩ አስረጂዎች ናቸው።

 

ከላይ የተጠቀሱት ድርጅቶች ዛሬ በአዋጅ ሽባ እንዲሆኑ የተፈረደባቸው በምርጫ ዘጠና ሰባት ወቅት በፈፀሙት “ጥፋት” መሆኑ ግልፅ ነው። ኅብረተሰቡን እየሰበሰቡ በመብቱ ላይ እንዲወያይ፣ እንዲመካከር እና ስለመብት ያለው ግንዛቤ እንዲዳብር ማድረጋቸው ከጥፋታቸው ውስጥ የሚጠቀሱት ናቸው። በእነዚህ ጥፋቶቻቸው ምክንያትም ህዝቡ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በምርጫ እንዲሳተፍና ይጠቅመኛል ያለውን እንዲመርጥ የድርሻቸውን በመወጣታቸው ኢህአዲግ ጥርስ ውስጥ ሊገቡ ችለዋል። እናም ማለት ያለባቸውን እንዳይሉና ማድረግ ያለባቸውን እንዳያደርጉ አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ገብተዋል።

 

አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ያለበት የኑሮ ሁኔታ እንኳን የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን በገንዘብ ለመደገፍ ይቅርና መሰረታዊ ፍላጎቶቹን ለማሟላት እንኳ የማይችልበት መሆኑ እየታወቀ፤ የእነዚህ ድርጅቶች አብዛኛው (90%) የገቢ ምንጭ ከሀገር ውስጥ እንዲሆን መደንገግ ምን ይሉታል? ’ሂድ አትበለው፤ እንዲሄድ አድርገው’ እንዲሉ ኢህአዲግ በቀጥታ ድርጅቶቹ “ይፍረሱ!” ባይልም በአዋጁ አማካኝነት እንዲፈርሱ እያስገደዳቸው ነው።

 

የኢህአዲግ ሌላው “የስህተት ማረሚያ እርምጃ” የፕሬስ አዋጁ እና በነፃው ፕሬስ አባላት ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ነው። በረባ ባልረባ ጉዳይ ምክንያት እየተፈለገ የነፃው ፕሬስ አባላትን ከማሰር አንስቶ ዳግመኛ እንዳያንሰራሩ ከፍተኛ የገንዘብ መቀጮ እስከ መጣል የሚያስችለውን አዋጅ ማውጣት፤ ጋዜጠኞቹን ለማሳቀቅ የታቀደ መሆኑ ግልፅ ነው። ይህም እንግዲህ ኢህአዲግ ከምርጫ ዘጠና ሰባት ተመክሮ የቀሰመው “ትምህርት” መሆኑ ነው። አዎን! በዛን ወቅት የእነዚህ ጋዜጠኞች ብዕር ያለውን እውነታ በመረጃ መልክ ለኅብረተሰቡ ከማቅረብ አልፎ ለመረጃ በራቸው ክፍት የነበረውን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ቃለ-ምልልሶችና ሃሳቦች ለህዝቡ ያስነብቡ ነበር። ስለዚህም ዛሬ “የእጁን እንዲያገኝ” ተፈርዶበታል።

 

ምንም እንኳን ኢህአዲግ እውነተኛ ስህተቶቹን ወደኋላ አድርጎ ብዙ እንደ ስህተት የሚያያቸው “ስህተቶች” እና ”የስህተት ማረሚያ እርምጃዎች” ቢኖሩትም ለዚህ ጽሑፍ የመጨረሻ ወደሚሆነው እንለፍ።

 

በምርጫ ዘጠና ሰባት ኢህአዲግ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የነበረው አመለካከት ንቀት የተሞላበት እንደነበር የሚታወቅ ነው። ከማስረጃዎቻችን አንዱ የጠቅላይ ሚንስትሩ ጠንካራ ተቃሚ ፓርቲ ቢኖር ደስታቸው እንደሆነ በተደጋጋሚ መግለፃቸውና ማዕበል ላሉት ሰልፈኞች ኢህአዲግ ምርጫውን ያለምንም ማጭበርበር ማሸነፍ እንደሚችል በመግለፅ ሚያዝያ ሀያ ዘጠኝ ያደረጉት ንግግር ነው። ይህ እርግጠኝነት ግን ከአንድ ቀን ሊዘል አልቻለም ሚያዝያ ሰላሳ ተቃዋሚዎች ብቸኛ የምርጫ ጉልበት የሆነው ህዝብ ከእነሱ ጋር በመሆኑ በጠሩት ሰልፍ አረጋገጡ። ከዛች ቀን በኋላ ኢህአዲግ “ስህተቱን” ተገነዘበ።

 

ስህተቱ ለተቃዋሚዎች የነበረው ዝቅተኛ ግምት ቢሆንም እንደ ስህተት የወሰደው ግን “ተቃዋሚ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸውን አለመቆጣጠሩን” ነበር። ይህንንም “ስህተቱን” እንደለመደው ለማስተካከል ከምርጫው በኋላ “የስህተት ማረሚያ እርምጃዎችን” መውሰዱን የቅንጅት ፓርቲ መሪዎችን፣ አባላትና ደጋፊዎች ጭምር በማሰር አሳየ። በዚህም ለጊዜውም ቢሆን የተነሳበት የተቃውሞ ወጀብ ፀጥ ያለ መሰለው። ከተፈቱ በኋላ የነበረውም ሁኔታ የእፎይታ ጊዜውን የሚያራዝምለት መስሎ ታየው።

 

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በሊቀመንበርነት የምትመራው አንድነት ፓርቲ በተመሰረተ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢህአዲግን አላስተኛ ያለ እንቅስቃሴ የጀመረው በዚህ ጊዜ ነበር። ጋዜጦች ስለፓርቲው እንቅስቃዎች መዘገባቸው፣ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አካላት በየክልሉ እየተዘዋወሩ ቅርንጫፍ ቢሮዎች መክፈታቸው፣ የህዝቡ መልካም አቀባበል፣ በሊቀመንበሩ መሪነት በውጪ ሀገር የተደረጉ ጉዞዎች ስኬታማነትና በተለይ ደግሞ ኅዳር ሀያ ሰባት በመብራት ኃይል አዳራሽ የተደረገው ህዝባዊ ስብሰባ የፈጠረው መነቃቃት ገዥው ፓርቲን ሠላም ነሳው። ”እባብን መቅጨት በእንጭጩ” ያለው ገዥው ፓርቲም ሠላም የነሳውን አካል ለማፈራረስ ቆርጦ ተነሳ።

 

በተደጋጋሚ ሲወስዳቸው ከነበሩ እርምጃዎቹ እንደሚታወቀው የአንድን እንቅስቃሴ መሪ በማሰር እንቅስቃሴውን ማዳከም ብሎም ማጥፋት እንደሚችል የሚያምነው ኢህአዲግ፤ በአንድነት ፓርቲ መሪ ወ/ት ብርቱካን ላይ ዓይኖቹን አሳረፈ። ዓላማውን ለማሳካት ይረዳው ዘንድም ወ/ት ብርቱካን ስዊድን በተካሄደው ህዝባዊ ስብሰባ ላይ የቅንጅቱን መሪዎች የእስር አፈታት በተመለከተ ከህዝብ ለተጠየቀችው ጥያቄ የሰጠችውን ምላሽ እንድታስተባብል፤ ይህ ካልሆነ ግን ከዚህ በፊት የተፈረደባት የዕድሜ ልክ እስራት ተግባራዊ እንደሚሆን አስጠነቀቀ። ለማስተባበያ የተሰጣት ቀነ ገደብ ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት ሀያ ቀን መሆኑ ቀርቶ ኢህአዲግ ባዘዘው መሰረት ሦስት ቀን እንዲሆን ተደረገ።

 

ሕገመንግሥቱ በአንቀጽ ሀያ ዘጠኝ በሚፈቅደው መረጃ የመስጠት መብት ተጠቅማ የይቅርታውን ሂደት ለህዝብ የገለፀችው ወ/ት ብርቱካንም እውነትን ማስተባበል ከቆመችለት ዓላማ ጋር የማይሄድና የማታደርገው መሆኑን “ቃሌ” በሚል ርዕስ ጽፋ ለመገናኛ ብዙኀን በላከችው ጽሑፍ አረጋገጠች። እውነትን ተናግራ በመሸበት በማደር የምታምነው የወ/ት ብርቱካን ማደሪያም እስር ቤት ሆነ። የኢህአዲግ “ጥፋት የማረሚያ እርምጃ” ግን ግቡን በመምታት ፋንታ ሌላ ስህተት ወለደ።

 

ይዳከማል ተብሎ የታሰበው አንድነት ፓርቲም የመሪው ጀግንነት ይበልጡኑ አጀግኖት በተጠናከረ መልኩ ትግሉን ቀጠለ ብዙዎችም አብረውት መሆናቸውን በተለያየ መልኩ ገለፁለት። በውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያን በሠላማዊ ሰልፎች፣ በግጥሞችና በዘፈን ጭምር አብሮነታቸውን ሲያረጋግጡ በሀገር ውስጥ ያሉት ደግሞ ብርቱካንን ለመዘከር በተደረጉ እንደሻማ ማብራትና የስነጽሑፍ ምሽት ባሉት ዝግጅቶች ላይ ተገኝተው በቻሉት ሁሉ ድጋፋቸውን ሰጡ። ከፓርቲው በተጨማሪ ሌሎች በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መሪዎች፣ የአሜሪካ ሴናተሮች የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችና ሌሎችም መታሰሯን አወገዙ።

 

በእነዚህና መሰል እንቅስቃሴዎች “የማረሚያው እርምጃ” ራሱ ስህተት እንደነበር የተረዳው ኢህአዲግ አሁንም ሌሎች ስህተት የሆኑ “የስህተት ማረሚያዎቹ የሚያስተካክልባቸውን እንቅስቃሴዎች” ጀመረ። የቴሌቪዥኑ የህትመት ዳሰሳ ፕሮግራምና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሚል ሰበብ በቅርቡ የጀመረው የማደናገሪያ ዘመቻ ተጠቃሾች ናቸው። ሆኖም እነዚህ እንቅስቃሴዎች የነቃን ህዝብ ለማታለል የሚደረጉ ትዝብት ማትረፊያዎች ከመሆን ባለፈ ፋይዳ እንደማይኖራቸው ከወዲሁ ለመገመት አያዳግትም። ስለዚህም ከዚህ የስህተት አዙሪት ለመውጣት ኢህአዲግ ቆም ብሎ ራሱን መፈተሽ፣ እውነተኛ ስህተቶችን መገንዘብና ትክክለኛ የእርምት እርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅበታል።

 

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ