ተመስገን ዘነበ

በተናገረበት ተጽፎ በተናገረበት ወይንም በቴሌቭዥንም ሆነ በመድረክ በታየበት ወቅት ነገሬ ተብሎ ትኩረት ያልተሰጠው ድርጊት አንድ ቀን ዐብይ ጉዳይ ሆኖ ብቅ ይልና የመነጋገሪያ አጀንዳ ይሆናል። የቅንጅት አመራሮች “በሀገር ባህልና ወግ መሠረት” በይቅርታ በተፈቱበት ዕለትም ሆነ በሐምሌ 13 ቀን 1999 ዓ.ም. ሰሞን የተሰጡ መግለጫዎችን፣ የተደረጉ ቃለ ምልልሶችን፣ የተነገሩ የተነበቡ ጉዳዩችን ትኩረት ሰጥቶ ከታሳሪዎች መፈታት በላይም አጉልቶ ያጤናቸው አልነበረም።

 

ይህን ጉዳይ ዋንኛዎቹ ባለቤቶች መንግሥት፣ ሽማግሌዎቹና ከእስር ተፈቺዎቹ እንኳን በወቅቱ ትኩረት ሰጥተው የተከታተሉት፣ ማስተንፈስና ለሚሊኒየሙ አከባበር የተሻለ ገጽታ መፍጠር ላይ ያተኮረ ስለነበረ ከዚህ በመለስ የነበሩ ጉዳዩች ላይ ትኩረት ሳይሰጣቸው ማለፉ ብዙ የሚገርም አይሆንም።

 

በወቅቱ የድርጅቱ ዋንኛ ተዋናይ የውጤቱም ባለቤት ሆነው የቀረቡት የሀገር ሽማግሌዎች የሰጡትን መግለጫ ያነበበው ቢኖር እንኳን በደንብ አጢኖ ይዘቱን መርምሮ ለመረዳት የተቸገረ ጥያቄ ለማንሳትም የሞከረ ስለመኖሩ አላስታውስም። በእርግጥም የዛሬን አያድርገውና በታሣሪዎች መፈታት የነበረው ደስታ ሌላ ነገር ለማስታወስ የሚያስችል አልነበረም። ዛሬ ግን ያ በጊዜው ትኩረት ያልተሰጠው የሀገር ሽማግሌዎች መግለጫ የሚነበብ ብቻ አልሆነም። የሚያነጋግርና የሚያጠያይቅ ለታሪክ ማስረጃም የሚቀርብ እንጂ።

 

የሽማግሌዎቹ ነገር ከትናንት ድርጊታቸው በላይ የዛሬ ዝምታቸው ኧረ! እንደውም መጥፋታቸውም ይበልጥ አነጋጋሪ ይሆናል። እውነቱን ለመናገር የማይደፍር የሠራው ሥራ ጥያቄ ባስነሳ ግዜ አደባባይ ወጥቶ የማይመሰክር ሽማግሌ መጀመሪያስ እንዴት አድርጐ እንዲህ አይነት ከባድ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ በአስታራቂነት ለመሠለፍ ይበቃል? የሚል ጥያቄም ያስነሳል።

 

እነርሱ ሽማግሌዎቹ አስታረቅን ብለው ያወጁት፤ ዛሬ ደፍረው ከአደባባይ ወጥተው የነበረ የሆነውን ሊነግሩን ባይደፍሩም በወቅቱ በደስታ ሰሜት ተውጠው በድል አድራጊነት መንፈሥ ተኩራርተው ያወጡትን መግለጫ እየጠቀስን ዛሬ እየሆነ ካለው ጋርም እያጣቀስን አስተያየት ልንሰጥ፣ ምላሽ ባናገኝም ጥያቄ ልናቀርብ ይቻለናል።

 

የሐምሌ 13 ቀን 1999 ዓ.ም. የሀገር ሽማግሌዎች መግለጫ ያኔ ትኩረት ያልተሰጠውና ያልስተዋለው፤ ዛሬ ግን ጥያቄ የሚያስነሳው ይዘቱ ከርዕሱ ይጀምራል። ሽማግሌዎቹ የእስረኞቹን መፈታት ያበሰሩበት፣ የተፈቱበትን ምክንያትና ሂደቱን የገለፁበት፣ የእነርሱንም የ18 ወራት ጥረት የተናገሩበት የሐምሌ 13ቱ (1999 ዓ.ም.) መግለጫ ርዕስ “ከፕሮፌሠር ኤፍሬምና ከሀገር ሽማግሌዎች የተሰጠ መግለጫ” ነው የሚለው።

 

አንድ የሽምግልና ቡድን ሆነው የታዩት እኛም እንደ አንድ የቆጠርናቸውና በብዛታቸው ተደንቀን ተግባራቸውን ያደነቀናቸው ሽማግሌዎች አንድነታቸው ቀርቶ አንድም ሁለትም መሆንም ሳይችሉ ሁለት የተለያዩ አባላት መሆናቸውን ነው የመግለጫው ርዕስ የሚያሳየው።

 

በእርግጥ ቤተመንግሥት የመዘለቅ፣ ከአቶ መለስም ጋር መነጋገርና መመሪያ መልዕክት መቀበል የሚችሉት ፕ/ር ኤፍሬም ይስኃቅ ብቻ እንደነበሩ ሰምተናል።

 

በዕለቱ በቴሌቭዥን የታዩት ብዙዎች ሽማግሌዎች ደግሞ በሂደቱ ውስጥ ያልነበሩ፤ እንደውም አንዳንዶቹ ምን ሲሠራ እንደነበረ እንኳን በውኑ የማያውቁ እንደነበሩ ነው የሚነገረው። ይህ ከሆነ ለምን ዓላማ ስለምንስ ተብሎ በቁጥር በርክተውና አድማቂ ሆነው እንደቀረቡ ባይታወቅም፤ ሁሉም ተጠቃለው የሂደቱ አካል ተደርገው እስከታገሉ የውጤቱ ባለድርሻ ተበለው እስከቀረቡ ድረስ መግለጫው “ከሀገር ሽማግሌዎች የተሰጠ” ሊባል ሲገባው ፕ/ር ኤፍሬምንና ሌሎቹን ሽማግሌዎች ሁለት የተለያዩ አባላት አድርጐ ማቅረቡ ምክንያት ቢኖረው ነውና ይህ ያኔ ያስተዋልነው እና ከቁም ነገር ያልቆጠርነው ጉዳይ፤ ዛሬ ግን ምላሽ የሚያስፈልገው ዐብይ ጉዳይ ሆኖ አግኝተነዋል፤ እነሆ ጠየቅን።

 

18 ወራት የፈጀ የታገለውና እስረኖችን ለማስፈታት የበቃው የሽምግልና ሂደት ታሪክ መዝግቦ የሚይዘው ትውልድም የሚቀባበለው የሀገራዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው አጉል ከመሆኑ አንፃር ፕ/ር ኤፍሬምንና ቀሪዎቹን ሽማግሌዎች ለያይቶ ሁለት የተለያዩ አባላት አድርጐ ያቀረበው የመግለጫው ርዕስ ያልታሰበበት የተለየ ትርጉም ይሰጣል ተብሎም ሳይገመት የተፃፈ ነው ብሎ ለመቀበል ይከብዳል። በመሆኑም በመግለጫው ለሁለት ተከፍለው የተገለፁት ወገኖች ፕ/ር ኤፍሬምና ሌሎቹ ሽማግሌዎች ማብራሪያ ሊሰጡበት ይገባል።

 

በወቅቱ ትኩረት ካላገኘውና ዛሬ መነጋገሪያ ሊሆን ከበቃው ከዚህ ከተጠቀሰው መግለጫ ሌላም ጥያቄ ማንሳት ይቻላል። መግለጫው “በዚሁ መሠረት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ደጋፊዎቻቸውና ሌሎችም ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ባለው መንገድ የቀረበውና ወደፊትም በዚሁ ጉዳይ ሊቀርብ የሚችል ክስ የሚቋረጥበትና እስረኖችም ሆኑ ፍርደኞች ከእስር ተፈትተው ለሀገራችን ሠላም መግባባትና መቻቻል የሚፈጠርበት ምቹ ሁኔታ እንዲኖር ማንም ሳይጠይቀን በማንም ሳንወከል እንደ ሀገር ተቆርቋሪ ዜጐች ባለጉዳይ በመሆን ከላይ በጠቀስነው መሠረት ጉዳዩን በአንክሮ ስንከታተል ሰንብተናል።” ይላል። ከዚህ ከመግለጫው አንድ ከፍል የሚመዘዘውና በወቅታዊ ጉዳይ ዋቢ ተደርጐ የሚቀርበው ክስ “የሚቋረጥበት” የሚለው ቃል ይሆናል።

 

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተዳፍኖ በጽሑፍ ስለመስፈሩም የሚያስታውሰው ያልነበረው ይህ ክስ መቋረጥ የሚለው ቃል ወ/ት ብርቱካን ለዳግም እስራት ከተደረጉ በኋላ በእነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በተሠራጨ አንድ ጽሑፍ ላይ ተጠቅሷል። “ስምምነታችን ክስ ሊቋረጥ ነበረ፤ ፊርማችንን ከያዙ በኋላ ግን ቃላቸውን አጥፈው አስፈረዱብን” ይላል ጽሑፉ። ይህን አባባል ከሽማግሌዎቹ መግለጫ ላይ ከተጠቀሰው ጋር አነፃፅረን ስናየው ስምምነት የተደረሰበት ግን ያልተተገበረ ክስ መቋረጥ የሚባል ጉዳይ እንደነበረ ይነግረናል።

 

ክስ የሚቋረጥበት እና፣ ክስ በኋላ እስረኖቹም ሆኑ ፍርደኖች በማለት በመግለጫው የሠፈረው ቃል ድርጊቱ ከስምምነቱ ባለማስማማቱ በተፈጠረ የሃሳብ መጣረስ የገባ ይመስላል።

 

የዚህ ምክንያት ደግሞ ግልፅ ነው። ምንም የሕግ እውቀት በማይጠየቅ አረዳድ ክስ ከተቋረጠ ፍርድ የለም፤ ከፍርድ በኋላ ደግሞ ክስ አይቋረጥም። ይቅር ተባዮቹ በሽማግሌዎች በቀረበላቸው ሰነድ ላይ የፈረሙት ደግሞ ፍርድ ከመሰጠቱ 27 ቀናት ቀድሞ ነው። ይህ ደግሞ ሰሞነኛውን ጉዳይ ይቅርታው በሕግ አግባብ የተፈፀመ ነው የሚለውን የሚያስጠይቅ ነው። የይቅርታን ጉዳይ ለብቻው ለይቶ በሚደነግገው አዋጅ 395/96 መሠረት ይቅርታ የሚጠይቀው “ፍርድ ከተሰጠ በኋላ በማናቸውም ግዜ ነው።” ሐምሌ 9 ለተሰጠ ፍርድ ይቅርታው ደብዳቤ ላይ የተፈረመው ሰኔ 15 ነው።

 

ይህን እንቆቅልሽ የማስረዳት ኃላፊነት የሽማግሌዎች ነው። በዚህ ጉዳይ ሰው እስር ቤት ያለ መሆኑ ደግሞ ኃላፊነታቸውን ከባድና ግዜ የማይሰጥ ያደርገዋል።

 

መግለጫው ለወቀታዊው ኩነት መሣሪያ የሚሆን ሌላም ተጠቃሽ ነገር ይነበብበታል፤ እንዲህ ይላል። “እንዲሁም ምርጫ 97ን ተከትሎ በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች በየጣቢያው ታስረው የሚገኙ ዜጐች የዚህ የምህረት ውሳኔ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የጀመርነውን ባህላዊ የዕርቅ መንፈሥ አጠንክረን እንቀጥላለን።” ይህ አገላለፅ የሚነግረን ግልፅ የማያሻማ መልዕክት የምህረት ውሳኔው የተገኘው (ምህረት የሚለው አጠያያቂ መሆኑ እንዳለ ሆኖ) በባህላዊ የዕርቅ መንፈሥ እንጂ፤ አሁን እንደሚባለው “በሕግ በሕግ” ብቻ ያለመሆኑን ነው። ወ/ት ብርቱካን የተናገሩትም ይህንኑ ሽማግሌዎቹ በመግለጫቸው ያሠፈሩትን ነው።

 

የወ/ት ብርቱካን አሳሪዎች ይህን መግለጫ አያውቁትም ወይንስ እንደኛው በወቅቱ ትኩረት አልሰጡትም ነበር ማለት ነው?። በወቅቱ ትኩረት ባይሰጡት አይፈረድባቸውም፤ የወቅቱ ትኩረት ሌላ ነበርና። ዛሬ ግን ሰው ለማሰር ሲነሱ ሂደቱን በደንብ መቃኘት፣ የሆነ የነበረውን ግራና ቀኝ ፊትና ኋላ ማየት ይገባቸው ነበር።

 

“በቃል ያለ ይረሣል፤ በጽሑፍ ያለ ይወረሣል” እንዲሉ፤ ይህ ከላይ የተገለፀው የሽማግሌዎቹ ቃል በጽሑፍ ሠፍሮ መግለጫ ተብሎ በመንግሥት መገናኛ ብዙኀን ሳይቀር የተነበበ ነው። በታሪክ ሰነድነትም ይገኛል። ታዲያ ይህን በቃል ብቻ የተነገረን ሳይሆን በጽሑፍ የሠፈረን ነገር ይቅር ተባዩቹ ቢናገሩት ወንጀሉ ምንድን ነው? መንግሥት ይህ ሀሐት ነው፣ እስረኞቹን ለመፍታት ያበቃው ሂደት የተከናወነው በሽማግሌ ሳይሆን በህዝቡ ባህል ብቻ ነው ካለ፤ መጠየቅ ያለበት ወ/ት ብርቱካንን ሳይሆን “በ18 ወራት ጥረት ያስፈታናችሁ እኛ ነን” ያሉትን ሽማግሌዎች መሆን በተገባው ነበር።

 

“ሽማግሌ ዋሽቶ ያስታርቃል” በሚለው ሀገራዊ ብሂል መሠረት ሽማግሌዎቹ ለዕርቅ ሲሉ ዋሽተው ከሆነስ? ብለን ትንሽ እንኳን ጥርጣሬ እንዳንፈጥር መንግሥት በወቅቱ የሽማግለዎቹን መግለጫ አላስተባበለም።

 

“ከፕ/ር ኤፍሬምና ከሀገር ሽማግሌዎች የተሰጠ” የሚለው የሐምሌ 13/1999 ዓ.ም. መግለጫ ከያዛቸው ማብራሪያ የሚጠየቁ ጉዳዩች ሌላኛው ክስ መቋረጥ፣ ይቅርታ፣ ምህረት፣ እያለ በተለያየ ቦታ የገለፀው ነው። እነዚህ ሦስት ጉዳዮች በአንድ ጉዳይ ላይ በአንድ ጊዜ ተፈፃሚ ሊሆኑ አይችሉም። ስለዚህ የ18 ወራቱ የሽምግልና ጥረት ያስገኘው ውጤት በትክክል የትኛውን ነው? ሂደቱን ከድርጊቱ አፈፃፀሙን ከውጤቱ እያነፃፀሩ ሽማግሌዎቹ ሊናገሩ ግድ ይላቸዋል።

 

የሠሩት ተክዶ ያስፈፀሙት ተሽሮ ጭራሽ ሽምግልና የሚባል ነገር አልነበረም ተብሎ እየተነገረ እና በዚሁ ጉዳይ ወ/ት ብርቱካን በእስር ባለችበት ወቅት የሽማግሌዎቹ ዝምታ የዕድሜ ሽምግልናቸውን የኃይማኖት ክህነታቸውን የተዋቂነት ስብዕናቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ይሆናል።

 

ሽማግሌነትም፣ ክህነትም (የቤተክርስቲያን ሰውነት) ታዋቂ ግለሰብነትም እነዚህ ሦስቱም ለእውነት መቆምን፣ የሠሩትን ደፍሮ መናገርን፣ አጥፊውን አጥፊ ማለትን፣ ያለ አግባብ እየተጠቃ ያለ ሰውን መታደግ ይጠይቃሉ። ይህን ማድረግ ካልተቻለ ስሙ እንጂ ግብሩ ከሌለ ሽማግሌነትም ክህነትም ታዋቂነትም ሁሉም ሊያስከብሩ አይችሉም።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ