የቫንኩቨር ቅድስት ማርያም ቤ/ክ ውዝግብ በፍርድ ቤት መሰማቱን ቀጥሏል (ዘገዬ በቀለ)
በላይ፣ ሰብለና፣ ኤርሚያስ ከተከሳሽ ወገን ምስክርነታቸውን ሰጡ፤ ታሪኩም ጀምሯል
ዘገዬ በቀለ - ከቫንኩቨር
ሲጀምር፤ ሲንደረደር
“ቄሱ ሥራቸውን ባግባቡ አልተወጡም፣ በጎሣና በዘር ይከፋፍሉን ነበር። ስብከቱን ትተው ፖለቲካ ያስተምሩን ነበር” ደግሞ ደጋግሞ ይሄንን ነው ያለው ሦስተኛው የዕለቱ ምስክር። ያም ብቻ አይደለም። “እኔ ፍጹም ሥልጣን አለኝ፣ የቤተክርስቲያኗም መሪ እኔ ነኝ፣ ያለኔም ፈቃድ ስብሰባም ውይይትም ሊደረግ አይገባም አሉን። ...” ዝርዝሩ ብዙ ነው። አቶ በላይ ከበደ ገለቱ ይባላል። መልከ መልካምና ረጅም ቁመናው ያማረ፣ ሆን ብሎ ያሳስታል ተብሎ የማይገመት የቤተሰብ ሰው፣ የልጆች አባት፣ በሙያው አካውንታንት ነው።
ይቅርታ ለስምንት ዓመት አካባቢ እስራኤል ሲኖር ቆየና በ2004 ዓ.ም. (በዚህ ጽሑፍ ላይ የተጠቀሱት ዓመቶች በአውሮፓውያን አቆጣጠር ናቸው) ወደ ቫንኩቨር መጣ። አሁን የጭቅጭቁ መነሻ የሆነችው የቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን አባል ሆኖ ለረጅም ጊዜ ኖረ። አሁንም አባል ነው። ምስክርነቱ እንዲህ ነው። ይሄ የቤተክርስቲያኑ ጭቅጭቅ ሲፈጠር፣ እሱና ሌሎች አምስት ሰዎች የሽማግሌ ኮሚቴ ተብለው ውዝግቡ የተፈጠረባቸውን ወገኖች ሁኔታ እንዲያጠኑና የመፍትሔ ሃሳብ እንዲያመጡ ወይንም እንዲያስታርቁ ተመረጡ። ሽምግልናቸው እንደሱ ምስክርነት ከሆነ ባንደኛው ወገን ማለትም በአባ ዮሐንስ/ገብረኪዳን ችግር ምክንያት አልሠራም። ስለዚህ የሽማግሌው ኮሚቴ ፈረሰ። ከዚያ በፊት ግን እሱን ጨምሮ የሽማግሌው ኮሚቴ ሥራውን እየሠራ ሳለ የተከሳሽ ወገን የቤተክርስቲያኑን አባት አብርሬያለሁ አለ። በእሱ፣ በአቶ በላይ ምስክርነት ውስጥ ባይካተትም የሽማግሌው ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆነው አቶ አስቻለው እንዳካፈለን ከሆነ የሽማግሌው ኮሚቴ የፈረሰውና በፍርሰቱም ላይ ማህተም የመታበት ባንድ በኩል ሽምግልና እየተካሄደ በሌላ በኩል ደግሞ ተከሳሹ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ቄሱን/መነኩሴውን አባርሬያለሁ ማለቱ ነው። ይቀጥላል ...
ትንሽ ለማስታወስ - የነገሩ አመጣጥ
ኦኬ! ታሪኩን ለመጀመሪያ ጊዜ ለምታነቡ ነገሩ እንዲህ ነው። በ1990ዎቹ አካባቢ የቫንኩቨር ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በካናዳ ስር በሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ ተባባሪነትና በኋላ ላይ በአቡነ ዜናማርቆስ ቡራኬ ተቋቋመች። ሲፈጠርም ጀምሮ ቤተክርስቲያኗ ከአባ ገብረመድህን/ከአባ ጳውሎስ ሕብረት አልነበራትም። እነሆ እንደ ከሳሽ ወገን ክስ ከሆነ ዘመዶቻችን ቀስ በቀስ ገቡበትና ማንም ሳያውቅ ማንም ሳይሰማ፤ እኚያን ተንኮል ያልገባቸው መነኩሴ አጃጅለው የቤተክርስቲያኗን ስምና መተዳደሪያ ደንብ ለውጠው ያቺ ቤተክርስቲያን እያለች ነገር ግን በዛችው ቤተክርስቲያን ንብረት፣ ጽላት እንዲሁም ገንዘብ፣ እንዲሁም ምዕመናን ሌላ አዲስ ቤተክርስቲያን በብሪቲሽ ኮሎምቢያ አቋቋሙ። በ2005። ለህዝቡ አልተነገረም። አልተገለጠም።
በኋላ ላይ ቄሱም ነገሩ ሲገባቸውና እንደተታለሉ ሲያውቁት ዘራፍ አሉ፤ ነገሩም ተጋለጠ። በሽምግልና ቢሞከረም ችግሩ ሊፈታ አልቻለም። ስለዚህ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሄደ። ከሳሽ ቀድሞም የነበረችው አሁንም ያለችው ኆህተ ሰማይ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን፤ ተከሳሽ ደግሞ የአዲሲቷ ማርያም የቀድሞ ሰበካ ጉባዔ አባላት እነተክላይ፣ እነታሪኩ፣ እነኤርሚያስና ሌሎችም። መቼም ይሄንን የነእከሌን መዝገብ ጉዳይ ለምዳችሁታልና የነተክላይ መዝገብ ወይም ጉዳይ እንበለው። ወደ ዛሬው ውሎና ምስክርነት ልመልሳችሁ።
ዳግም ወደበላይ፤ በላይ ዘለቀ አይደለም፤ በላይ ከበደ
እንግዲህ ከዚህ በኋላ ነው አቶ በላይ መጥቶ የዛሬውን ምስክርነት መስጠት የጀመረው። እንደ አቶ በላይ አጀማመሩ ላይ በርግጥም ገለልተኛ ሆኖ ምስክርነት ለመስጠት ሞክሮ ነበር። እያደር ግን አልተሳካለትም። ግማሹ ስህተት፣ ግማሹ ቅጥፈት ነበረበት። ለምሳሌ፤ የፓትርያርክ መኖር አለመኖር “ቢግ ዲል” አልነበረም ብሏል። ባንድ በኩል እንደ ሽማግሌ ለመሆን ጣረ። ነገር ግን ቀስ በቀስ አቋሙ ሲያመልጠውና ወገንተኝነቱ ሲንፀባረቅ ተስተውሏል። ስለረቂቅ የቤተክርስቲያኑ መተዳደሪያ ደንብ ምንም ችግር አልነበረም። በኋላ ላይ አንዳንድ ሰዎች መጥተው ያንን ረቂቅ የቤተክርስቲያን ሕገመንግሥት ሲያሰራጩ ነው ችግርና ቅዥንብር የተፈጠረው አለ። ይህም ብቻ አይደለም። ባንድ በኩል ህዝቡ ረቂቁን መተዳደሪያ ደንብ ያውቁታል ሲል፤ በሌላ በኩል ግን የለም ረቂቅ መተዳደሪያ ደንቡ በምስጢር እንዲያዝ ከሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ተነጋግረናል። ከሽማግሌዎቹ መካከል ጥቂቶቹ መረጃ አሾልከው ሰጥተዋል ብሎ መክሰስም ጀመረ።
“እንዴት አወቅህ?” ለሚለው ጥያቄ ምላሽ አልነበረውም። በነገራችን ላይ አለው የከሳሽ ጠበቃ ቤተክርስቲያን ኢትዮጵያስ ቢሆን አባት የላትም እንዴ? በአባት አይደለም እንዴ የምትተዳደረው? ...
“ዌል ይሄ ኢትዮጵያ አይደለም! ይሄ ካናዳ ነው!”
ምንድነው ልዩነቱ?
እዚህ ገንዘቡን የሚያዋጣው ህዝቡ ነው። ስለዚህ ህዝቡ መወሰን አለበት።
ኢትዮጵያስ?
“ኢትዮጵያ ገንዘቡ የሚመጣው ከላይ ከቤተክህነት ስለሆነ ሰዎችም ከላይ ይሾማሉ … ስለዚህ … ህዝቡ በቤተክርስቲያኖቹ አስተዳደሮች ላይ ድምፅ የለውም።” እዚህ ጋር እንኩዋን የዋህ ሆኖ ነው። ወይም ሆን ብሎ ሲያደናግር። ዛሬ አናውቅም።
ቤተክርስቲያኗ ቀደም ሲል በማን ስር እንደነበረችና በማን ስም እንደሚቀደስ፣ ስለትክክለኛው ሲኖዶስ፣ ስለአቡነ መርቆሪዎስ፣ ስለአቡነ ይስኃቅ፣ ስለምዕመናኑ፣ አባል ስለሆኑና ስላልሆኑትም ሰዎች ተጠየቀ። እሱም መለሰ። እነሆ ህወሓት/ኢህአዲግ በሄደበት ምስክር አያጣም። ስለ ፓትሪያርኮቹ እኔ አላስተዋልኩም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሁለቱንም ሲጠሩ ተመልክቻለሁ። ስለሲኖዶስ ስለውጪው ሲኖዶስ አላውቅም። እዚህ ከመጣሁ በኋላ በተለይ ከ2006 ወዲህ ሰምቻለሁ። እስራኤል ይኖር የነበረ ኢትዮጵያዊ ስለትክክለኛው የስደት ሲኖዶስ አላውቅም አለ። ስለአባላት (ይህቺኛዋ በጣም የምታበሳጭና በየቦታው የምትነሳ ነገር ነች።) በ2004 የመጣው ሰው፣ እነዚያ ቡናና ሻይ ሸጠው ቤተክርስቲያኑን ያቋቋሙትን ምዕመናን አላውቃቸውም አለ። “ጭራሽ አይቻቸው የማላውቀው ቤተክርስቲያን መጥተው የማያውቁ ሰዎች ናቸው” የበጠበጡን። በነገራችን ላይ ከዚህ ውዝግብ የምንማረው ዋናው ነገር በየቤተክርስቲያናቱ የምትማልዱ ሁላ የአባልነት መታወቂያችሁን አግኙት። ያለበለዚያ ምን ብርና ላብ ስታዋጡ ብትኖሩ መደበኛ አባል ካልሆናችሁ ከኋላችሁ የመጡት ብልጦቹ እነብርሃኔ፣ እነመድህኔ፣ ... ይፈነግሏችኋል። ያ ነው በቫንኩቨር የተከሰተው። ወደጠበቃው ልመልሳችሁ።
እሺ ለምን ቄሱ ተባረሩ? ለምን አስፈለገ? ... ሲል ጠበቃው ጠየቀ፤ “ያንን ለያይተን ማየት ነው ያለብን” አለ አቶ በላይ። “እኛ የተቋቋምነው ለእርቅ ነው። ግን ደግሞ ሥራ አስፈጻሚው ሥራውን መሥራት ይችላል። በሌላ በኩል ግን ቄሱን ሥራቸውን መሥራት የለባቸውም። ምክንያቱም እኛ እየሸመገልን ነው።” እርስ በርሱ የሚጋጭና የምስክሩን ወገንተኛነት ያሳየ ምስክርነት ነው። “እኔ ነገሩ ከቁጥጥር ሲወጣ ሳይ ለሽምግልና ኮሚቴው አሳውቄ በገዛ ፈቃዴ ለመውረድ ወስኛለሁ።” አለ። ለማን ለማን እንዳሳወቀ ሲጠየቅ ግን፤ ለሁሉም እንዳላሳወቀና ከኮሚቴው መካካል ሁለቱን ከመነኩሴው ጋር ባላቸው ጉድኝት ምክንያት ቀልቡ እንዳልወደዳቸውና እንዳላማከራቸው ያህል ገልጿል። በተለይ አንዷ የኮሚቴው አባል ቀደም ሲል ሳናግራት ስቃብኝ ስለሄደች እሷን ላናግራት አልፈቀድኩም ብሏል።
ባንድ በኩል በህዝቡ የተመረጥን ገለልተኛ ቡድኖች ነን ቢልም፤ መልሶ ግን የሥልጣን ክፍተት እንዳይፈጠር ስለተጨነቅን ለሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴው ነው ሪፖርት ያደረግነው ብሏል። ነገሩ ዝብርቅርቅ ያለ ነው። ኮሚቴው ለምን መነኩሴውን አባረረ? ለሚለው ጥያቄ፣ ባንድ በኩል በኛ ፒቲሽን ነው ሲል፤ መልሶ ደግሞ የለም የፒቲሽኑ መንፈሥ መነኩሴውን ለማባረር ሳይሆን ያው ስብከታቸው ፖለቲካ ስለበዛበትና ያንን ለመቃወም ብቻ ያህል ነው። በመጨረሻም ምስክሩ መሰከረ። ምስክርነቱን እንደሽማግሌ ኮሚቴ አባል ጀምሮ፤ እንደ ተከሳሽ ወገን ደጋፊ ጨረሰ።
እነ ሰብለ፣ እነኤርምያስ የዋህ ምስክሮች
ከዚያ በፊት ግን ሰብለ አስፋውና ኤርሚያስ ኃይለሥላሴ መስክረዋል። ብዙ ተንኮል አልተመለከትኩባቸውም። ሰብለ ምስኪን መልከ መልካም ሴት ነች። ስለቶማስ ተነሳ። ቶማስ ተስፋ። እንዴት ያለ የኢትዮጵያ ነገር የሚያንገበግበው ጥርት ያለ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ነው። አልፎ አልፎ ቤተክርስቲያን ይሄዳል። ገንዘብም ያዋጣል። በመደበኛ አባልነት ግን አልተመዘገበም። መጥፎ ነገር። ሰብለ ግማሽ በራሷ ግማሽ ባስተርጓሚ መሰከረች። ስለቤተክርስቲያኑ ምዝገባ፣ ስለአባ ገብረኪዳን፣ ስለተደረጉ ስብሰባዎች፣ እሷ ስለሰጠችው አስተያየት፣ ስለአባ ዮሐንስ/ገብረኪዳን ፖለቲካና ፖለቲካዊ ስብከት፣ እሷም ይተዉ ብላ እንዳስጠነቀቀቻቸው፣ ከሁለት ወር በፊት እንደደወሉላት፣ ስለአባ ምሣሌ እንግዳ፣ ቤተክርስቲያኑ ቀደም ሲል በሳቸው አመራር ስር ባለው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በካናዳ እንደተመዘገበ፣ የኋለኛው ለውጥ የስም ብቻ እንደሆነ እንጂ፣ የቤተክርስቲያን ወይንም የሕጋዊ ሰውነት ለውጥ እንዳልሆነ፣ ከኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በካናዳ መገንጠላቸውን ወይም መለየታቸውን ለምን መናገር እንዳላስፈለገ ይኸውም ህዝቡ ስለሚያውቀው እንደሆነ፣ አባ ገብረኪዳን ሲቀድሱ የሁለቱንም የአቡነ መርቆሪዎስንም የአቡነ ጳውሎስንም ስም ያነሱ እንደነበር፣ የመሰላትን ተናግራለች።
ኤርሚያስ ቀጠለ። ኤርሚያስ ኃይለሥላሴ። ይሄም ሰው ብዙ ተንኮለኛ አይመስልም። ለረጅም ጊዜ ቶሮንቶ እንደኖረ፣ በ1998 ወደ ቫንኩቨር እንደመጣ፣ አባ ይስኃቅ በ2000 በድቁና ያገለግሉ የነበሩትን አባቱን ጽላቱን ይጠብቁ ዘንድ ቅስና እንደሰጧቸው፣ አባቱ አሁን እዚህ እንደሌሉና በ2001 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሱ፣ እዚያም ባቅራቢያቸው በሚገኝ ቤተክርስቲያን እንደሚያገለግሉ፣ በፍጹም ግን ወደየትኛውም ፓትርያርክ እንደማይወግኑ ተናግሯል።
ትንሽ ግራ የሚያጋባው ስለሲኖዶሱ ክፍፍልና ስለአባቱ ገለልተኛ መሆን የተናገረው ነው። የሲኖዶሱ መከፋፈል ከ2006 በኋላ እንደመጣና ከዚያ በፊት ሲኖዶስ እንዳልነበር፤ ቢኖርም እንደማያውቅ ተናግሯል። እንደሚመስለኝ፣ ይሄ ሲኖዶሱ የተከፈለውና የውጪው ሲኖዶስ የተቋቋመው ከ2006 በኋላ ነው የሚለው ሃሳብ የፈለሰው በ2006 አቡነ መርቆሪዎስ ለጳጳሳት የሊቀ ጳጳስነት ክህነት መስጠታቸውን ተከትሎ ነው ከሚለው የተፋለሰ ሃሳብ ነው። የሆነ ሆኖ ይሄ የ2006 ክስተት የምርም ይሁን የሐሰት ይሄንን ሃሳብ ሰዎች እንዳሻቸው እንዲጠቀሙበት ተመችቷቸዋል። እስከዛሬ የመሰከሩት ምስክሮች ሁሉ፤ የዛሬዎቹን ጨምሮ የውጭ ሲኖዶስ እንዳለ እንደማያውቁና ከ2006 በኋላ ብቻ እንደመጣ እንደሚያውቁ እንደውም አንዳንዶቹ እንደአቶ በላይ ያሉ ሰዎች የአቡነ መርቆሪዎስ ስደትም ለሕክምና ወይም ለሌላ ጉዳይ የመጡ እንደመሰላቸው ሲናገሩ ተስተውሏል። ወደ ተቀረው ምስክር ልመልሳችሁ።
ታሪኩ፣ ብርቱ ሰው - ዋና ምስክር
ታሪኩ ተስፋ ቀጠለ። ከተከሳሾቹ አንዱ ነው። በነገራችን ላይ ታሪኩ በአካባቢው በመልካም ሥራው የተመሰገነ፣ ሁለገብ፣ ጠንካራና ትጉህ ሰው ነው። ከቤተክርስቲያን እስከ እግር ኳስ ቡድኖች ምስረታ፣ ከማኅበረሰብ አገልግሎት እስከ ሰብዓዊ መብት ጥበቃ፤ ከኢትዮጵያ እስከ አፍሪካ ጉዳዮች በትጋት የሚያገለግል ታላቅ የቫንኩቨር አካባቢ ሰው ነው። የዛሬ አስራ ምናምን ዓመት አካባቢ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያምን ወደቫንኩቨር ከጓደኞቹ ጋር የጋበዘና ያስተናገደ፤ እሱም እንደገለጸው እስከ 2005 ድረስ በንቃትና በመቆርቆር የቆየ የሰብዓዊ መብት ታጋይ ነው። ከ2005 በኋላ ምን እንደተፈጠረ እንጃ። ማለት አልገለጸም። ታሪኩ፤ የቤተክርስቲያኑ መስራች፣ እንደውም በቤተክርስቲያኑ ታሪክ የመጀመሪያው ክርስትና የተነሳው የሱ ወንድ ልጁ እንደሆነ በግል ሥራም እንደሚተዳደር በመተረክ ምስክርነቱን ጀመረ። ታሪኩ ትልቅ ሰው ነው። የሱ ምስክርነትም እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው። ወሳኝ ነው።
መጀመሪያ በቤተክርስቲያን አባልነት፣ ከዚያም በአመራር አባልነት እንዳገለገለ፣ የአባላትን ዝርዝር ጠንቅቆ የያዘ ሰው ነው። ወዳጃችን ታሪኩን በምንም መልኩ በዚህ ነገር ባናነሳው ደስ ቢለንም፤ ታሪኩ ባንድ በኩል ገና ከጅምሩ የቤተክርስቲያን አባላት ላይ ጥብቅ የሆነ የአባልነት ክትትልና ቁጥጥር እንደሌለ እንዲሁም ሰዉ ያሻውን ያህል ገንዘብ እንደሚያዋጣ፣ ብዙ ሰዎችም የወራት ውዝፍ ሊኖርባቸው እንደሚችል አባላትም መደበኛ አባል ባይሆኑም፣ በሥራቸው ግን አባል ሊሆኑ እንደሚችሉ ቢናገርም፣ በሌላ በኩል ግን የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች እንደሆኑና የቻሉትን ያህል ገንዘብ ሊያዋጡ እንደሚችሉ እያወቀ አባል አይደላችሁም ብሎ አንዳንድ ሰዎችን ከድምፅ ውጪ በማድረጉ ሂደት መሳተፉ አስቀይሞናል ብለዋል አንዳንድ ሰዎች። የሆነ ሆነና ታሪኩ መድረክ ላይ ወጥቷል። ምስክርነቱን ሊሰጥ። ምን ይል ይሆን? ችሎቱ ማክሰኞ ይቀጥላል። ታሪኩና ታሪኩን ይዤ እመለሳለሁ።
በመጨረሻም
ይሄ ጽሑፍ የተፃፈው በገለልተኛ ወገን አይደለም። ዘገባውን ሚዛናዊ ለማድረግ ብሞክርም፡ ሙሉ በሙሉ ሚዛናዊ ነው ብዬ ቃል አልገባም። አንድ ነገር ማለት ግን እወዳለሁ።
ለምዕመናን፤
በየቤተክርስቲያናችሁ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ።
መደበኛ አባል ያልሆናችሁ
በመጪው እሁድ ሂዱና መደበኛ አባል ሁኑ። ያለበለዚያ የለፋችሁባትን ቤተክርስቲያናት ሄዷዋል። ሀገራችንን ቀሙን። ቤተክርስቲያናችንንና አድባራቱን ቀሙን። አሁን ደግሞ በዚህ በስደት የገነባናትን ስደታችንንና ቤተክርስቲያናችንን ሊቀሙን ነው።
ለነ አቡነ መርቆሪዎስ ደግሞ መልዕክቴ፤
አታንቀላፉ። አትሳነፉም። ንቁ ነው። በየቤተክርስቲያናቱ እየዞራችሁ በቀላጤም እየጻፋችሁ ህዝባችሁን አንቁ። እነሆ የናንተን ውጊያ እኛ ብቻችንን አንዋጋም። መኖራችሁን የሚያሳይ ሥራ ሥሩ። ቡራኬ፣ መግለጫ፣ ስጡ። ስብሰባም፣ ጉባዔም ጥሩ። ሰልፍም አሰልፉ አንዳንደዜ። አብዛኛው የኛ ህዝብ የዋህ ነው። ተንኮል አያውቅም። ተንኮል አያስብም። ጥቂቶች ግን መጥተው “ገለልተኛ ነን” በሚል ያምሱታል። ያንን የማመስ ሥራ ደግሞ የሚያስተባብሩላቸው የኛ ሰዎች ናቸው። የኛ ባንድ በኩል ኢህአዴግን አጥብቀን እንጠላለን የሚሉ፤ በሌላ በኩል ግን ከነሱዉ ጋር በሰበብ አስባቡ የሚተሻሹ ሰዎች። ያለበለዚያ መቼም ፊታውራሪ አመዴ ሞተዋል፣ ፕሮፌሠር ኤፍሬም ሳይሞቱ ሽምግልናውን ግፉበትና እዚያው እነሱው ጎራ ተቀላቅላችሁ ገላግሉን። እባካችሁ ምሩን።
ዘገዬ በቀለ - ከቫንኩቨር ካናዳ፣ ሚያዝያ 2009