Happy Ethiopian Newy Year! መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልዎ!

ልዑልሰገድ (ከአቢሲኒያ) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

የዛሬ 18 ዓመት ግንቦት 13 ረቡዕ አዲስ አበባ ውስጥ ዕኩለ ቀን ላይ በውይይት ታክሲ እጓዛለሁ። ከቀበና አቅጣጫ የአራት ኪሎ አደባባይን አቋርጦ ታክሲው ወደ ፒያሣ አቅጣጫ ይገሰግሳል። በታክሲው ስፒከር የዕለቱ የዜና ዕወጃ ይሰማል። ዜናው ከወትሮው የተለየ ነበር። ኮ/ል መንግሥቱ ሀገር ጥለው ኮበለሉ የሚል።

 

ዜናው እንደተሰማ ከተሳፋሪዎቹ መካከል ቆቡን ጉልበቱ ጋር ያስቀመጠው ትራፊክ በከፍተኛ ሁኔታ ተናደደ። አንዲቷ ለቅሶዋን አቀለጠችው። እኔ ደግሞ ከት ብዬ ሳቅሁ። ያሳቀኝ ታክሲው ውስጥ የነበረው ክስተት ነበር። የሰውየው መናደድና የሴቷ ማልቀስ። በኔ መሳቅ የበገነው ትራፊክ ሊገስጠኝ ሞክሮ ያልጠበቀውን አፀፋ ሲያገኝ መልሶ ኩምሽሽ አለ።

 

ለእነዚህና ለሌሎቹ በርካታ ሰዎች ኮ/ል መንግሥቱ ዘላለማዊ ባለሥልጣን ናቸው። በእነሱ ግምት ያለመንጌ ሁሉም ከንቱ ሁሉም ጭለማ ነው። አምባገነኖች የራሳቸውን ተክለ ሰውነት አግነው የሀገር ዋልታ ሆነው መታየትና ሀገር ገደል መክተት ሥራቸው ነው። ያለመታደል ሆኖ ከመንግሥቱ የባሰ አውሬ ገጠመን እንጂ ከመንግሥቱም ወዲያ ሀገር ትኖራለች ወደፊትም ትቀጥላለች።

 

ሰሞኑን አቶ መለስ ሳይፈልጉ በውጭ ጋዜጠኞች በሚጠየቁት “መቼ ሥልጣን ይለቃሉ?” ጥያቄ አፋቸው ያመጣላቸውን መለፍለፍ ይዘዋል። ሥልጣን በቃኝ ፓርቲዬ ከፈቀደ መልቀቄ ነው ብለዋል።

 

አቶ መለስ ለሥልጣን ሲሉ የራቀውን ትተን ከ1997 ምርጫ ውጤት በኋላ በመቶ የሚቆጠሩ ንጹሃንን አስገድለዋል። አሥር ሺህዎችን በግፍ አስግዘው በእስር አንገላተዋል። ሥልጣናቸውን ለማጠናከር የፕሬስ ነፃነትን የሚገድብ አዋጅ አውጥተዋል። በመልካም አስተዳደር ላይ ይሠራሉ የሚሏቸውን መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ለማፈን በሕግ ስም ሕግ አርቅቀዋል። የሀገራቸውን ጉዳይ የሚያነሱ ተቃዋሚዎችን እና አርቲስት ቴዲ አፍሮን ጨምሮ በርካታ ንጹሃንን በፈጠራ ወንጀል አስረዋል። የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት አልበቃ ብሏቸዋል። ስለዚህም በቅርቡ ድግሞ ህዝቡን የሚያሸብር ራሱ ወያኔ የፃፈውን ሕገ-መንግሥት የሚደፈጥጥ “ፀረ-አሸባሪነት” የተሰኘ ሕግ አውጥተዋል።

 

የሀገሪቱን መከላከያ ደህንነትና የፌደራል ፖሊስ ሙሉ ለሙሉ በወያኔ አባላት አመራር ስር አድርገዋል። የክልል አስተዳደሮችም በቀጥታ የወያኔ ሞግዚታዊ አሠራር ስር ናቸው። በመላው ሀገሪቱ የመለስን የአፈና ድርጊት የሚቃወም ሁሉ የጥይት ራት እንደሚሆን ሰሞኑን በደሴ ጭምር አሳይተዋል።

 

የመለስን የአፈና መዋቅር ማጠናከር ለተመለከተና በየቀኑ የሚፈለፍሉትን ሕገ-ወጥ አዋጅ ላስተዋለ ሥልጣን ይለቃሉ ማለት ይከብዳል። ለዚህ ነው አብዛኛው ህዝብ ሥልጣን በፈቃዳቸው ይለቃሉ የሚለውን አይቀበለውም። ለሥልጣን ብለው ሕፃናትንና አዛውንቶችን ሳይቀር በአደባባይ በጥይት ያስቆሉ ነብሰ ገዳይ ምን ታይቷቸው ሥልጣን ይለቃሉ ብሎ ይገምት?

 

አቶ መለስን ትግሬ ስለሆኑ አልጠላቸውም። በንጹሃን ደም የታጠቡ በሀገር ላይ ከፍተኛ ወንጀል የፈጸሙ በመሆናቸው ግን እጠየፋቸዋለሁ። እቃወማቸዋለሁ። ኢትዮጵያውያንን በዘር ከፋፍለው ለማጫረስ ዛሬም ድረስ ኃላፊነት የማይሰማቸው በመሆናቸው እንቃቸዋለሁ። በሰው ልጅ ሰብዓዊነት ላይ በፈጸሙት ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ተጠይቀው ማየትም እንደብዙኀኑ ህዝብ እፈልጋለሁ። የሚያሳዝነው በርካታ የአቶ መለስ ደጋፊዎች በጠራራ ፀሐይ ንጹሃንን ማስጨረሳቸውን ያውቃሉ፣ የሀገሪቱን ጥቅምም የሸጡ ከሃዲ መሆናቸውንም አያጡትም። በሳቸው አመራር ወደ አዘቅት እየነጎድን ለመሆኑም አይጠራጠሩም። ነገር ግን እንደሳቸው ዘረኛ ስለሆኑ በትግሬነታቸው ብቻ ይደግፏቸዋል።

 

የመለስ በፈቃዴ ሥልጣኔን እለቃለሁ የሚለው ቀልድ ለእነዚህ በትግሬነታቸው ለሚደግፏቸው ዘረኞች መርዶ ነው። መለስ እየገደሉም፣ እያሰሩም፣ እየዘረፉም፣ የሀገር ጥቅም እየሸጡም፣ … ሺህ ዓመት ቢነግሱላቸው ደስታቸው ነው። የሰሞኑ ወሬ ለእነዚህ ሰዎች የምር መርዶ ሊሆን ይችላል። የዘረኝነት አስተሳሰብ የሰውን ልጅ መልካም አዕምሮ የሚያዛባ በመሆኑ የተሻለውን አማራጭ ለማየት አይችሉም። ስለዚህም የጥንት ፋሺስቶች እንዳደረጉት “ሙሶሎኒ ዘላለም ይኑር!”፣ “ሙሶሎኒ ሁልጊዜም ትክክል ነው!” ማለት የሚቃጣቸው አሉ። ሙሶሎኒ የተጻፈለት መፈክር ሳይደበዝዝ ተዘቅዝቆ መሰቀሉን ግን ማስታወስ አይፈልጉም።

 

አቶ መለስ በፓርቲው ውስጥም ሆነ ከፓርቲው ውጭ ለመመለክ ብዙ ጥረዋል። ገኖ ለመውጣት የሞከረን ተቃዋሚን ብቻ ሳይሆን የራሳቸውንም የትግል አጋሮች ሲያጣጥሉና ሲደፈጥጡ ኖረዋል። በአደባባይ የአርከበ ዕቁባይን ፎቶ ከፒያሣ ከተሰቀለ ከሰዓታት በኋላ ሌሊት በደህንነት ገንጥለው የጣሉ መሆናቸው አይዘነጋም።

 

ራሳቸው ጽፈው ራሳቸው በሚጠየቁበት የመገናኛ ብዙኀን “ለምንድነው በተደጋጋሚ ከሥልጣን ስለመልቀቅዎ የሚጠየቀው?” ለተባሉት ሲመልሱ፤ “ነገሩን አስር ጊዜ መውቀጥ የሚፈልጉ ካሉ ይውቀጡ!” ብለዋል። ማንም ደግሞ እንዳያነሳብኝ ለማለት ነው። ማስጠንቀቂያው የሚሠራው ለሀገር ውስጥ ብቻ ሆነና የውጭ ጋዜጠኞች ሲጨቀጭቋቸው የሚሉት ቢያጡ ሥልጣን በፈቃዳቸው ለቀው በንጹሃን ደም በቦካ እጃቸው ጽሑፍ የመጻፍ ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል። ሰውዬው እውነት የሥልጣን ጥም ባይኖራቸው ኖሮ የህዝብ ድምፅ ዘርፈው ንጹሃንን ባላስጨፈጨፉ ነበር። ተቃዋሚዎች ሥልጣን ወይም ሞት ያሉትን እኚህን ሰው ሥልጣንዎን ያዙ፤ ነገር ግን ለመጨው የሀገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሰረት ለመጣል ነፃ ተቋማት ይመስረቱ ሲባሉ አሻፈረኝ አሉ። የነዚያ ንጹሃን ደም የፈሰሰው ለሳቸው የሥልጣን ጥም ሲባል ነው።

 

ከምርጫ 97 በፊትም በተደጋጋሚ ወያኔ ሀገሪቱን ወደ ባሰ ጥፋት ሳይወስድ ብሔራዊ እርቅ እንዲያደርግ ተጠይቆ አልተቀበለውም። እርቁ ለሀገሪቱ የሚጠቅም ቢሆንም ለእነ አቶ መለስ የማይወጡት ዳገት ሆኗል። ይሄን ሁሉ የወያኔ መሪዎችን የሥልጣን ጥም ለምናውቀው ዛሬ በፈቃድ ሥልጣን ስለመልቀቅ በማውራት ሊያደናግሩን ሲሞክሩ አላፈሩም።

 

በእርግጥ የተለያዩ ሀገራት አምባገነኖች ለፈጸሙት ወንጀል ላለመጠየቅ ዋስትና እየጠየቁ ከሥልጣን ለቀዋል። የኬንያው መሪ ዳንኤል አራፕ ሞይ ይጠቀሳሉ። ሞይ ኬንያን ዘርፈው፣ ህዝቡን ረግጠው ሲበቃቸው እና ተቃውሞ እየበረታባቸው ሲሄድ በዝርፊያ ያግበሰበሱትን ሀብት ለመብላት ሥልጣን ለቀዋል። በምትካቸው የተኩት ኪባኪ በምርጫው ላለመውረድ የፈጸሙትን ወንጀል ተመልክተናል።

 

አንዳንዶች መለስን ከሞይ ጋር ያመሳስሏቸዋል። ሰውዬው የዘረፉትን የሀገር ሀብት የሚበሉበት የፋታ ጊዜ ሳይፈልጉ አልቀረም የሚል ጥርጣሬ አላቸው። ለዚህ የገፋፋቸው ነገር ያልጠበቁት በዘር ማጥፋት ወንጀል ይጠየቁ መባልና በሀገር ውስጥ ያለው የታፈነ የተቃውሞ ውጥረት ነው የሚሉ አሉ። በእርግጥ አቶ መለስ ድንገት ተነስተው “አሥራ ስምንት ዓመት የዘረፍኩትን ሀብት አከማችቼ ማን ሊበላው ነው?” የሚል ሃሳብ መጥቶባቸው ይሆን?

 

በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እምነት አቶ መለስ በፍላጎታቸው ከሥልጣን ይለቃሉ ማለት አጠራጣሪ ነው። አጠራጣሪ የሆነበትንም ምክንያቶች ቀደም ብዬ ጠቅሻለሁ። ሌላው ቀርቶ በመጭው ምርጫ ወያኔ ብቻውን ሮጦ፣ ብቻውን ዳኝቶ፣ ብቻውን ለማሸነፍ ዛሬም ሳይታክቱ ሜዳውን ሙሉ ለሙሉ እያጠሩ ነው። የሰውዬውን ለሥልጣን ሲሉ ሕጻናትን እስከመግደል መሄድ ላየ፤ ይሔን ሁሉ የሚያደርጉት ለትግል አጋሮቻቸው ለአገዛዝ እንዲመቻቸው አይመስልም። ይልቅ በለመደ ስልታቸው ለውጭው ጫና፤ ‘እኔ ለመልቀቅ ጠየቅሁ፤ ፓርቲው አንተ ከለቀቅህ ሀገሪቱ አደጋ ላይ ነች አለኝ’ ብለው ቆዳቸውን ለማዋደድ ይሆናል።

 

አቶ መለስ በአዲሱ “ሥልጣን እለቃለሁ” ቴአትራዊ ቃለ-ምልልሳቸው ከዚህ ቀደም የሠሩትን ድራማ ማጣጣላቸው ገርሞኛል። የሽግግር መንግሥቱን በኢፌዲሪ መንግሥት ቀየርኩ ሲሉ “ሥልጣን ለመጀመሪያ ጊዜ በሠላማዊ መንገድ ተሸጋገረ” የተሰኘ ድራማ በፓርላማ ተብዬው ሠርተዋል። በዚያ ቴአትር መዶሻውን ለነጋሶ ሰጡ። ፎቶ ተነሱ። ስላልነበረው ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር ንግግር አደረጉ። ደጋፊዎቻቸውን አስጨበጨቡ። ህዝቡ ግን ቴአትሩን ያውቅ ስለነበር ዶ/ር ነጋሶን የመለስ ፈረስ እስከማለት ደርሶ ነበር። አቶ መለስ ሰሞኑን ሥልጣን ለመጀመሪያ ጊዜ እለቃለሁ በማለት አዲስ ድራማ ሰርተው፤ ሌላ ነጋሶ ፈልገው መዶሻ ለመስጠትና በዋናው መዶሻ ሲቀጠቅጡን ለመኖር አስበው ይሆናል።

 

በንጹሃን ደም የታጠቡት አቶ መለስና ጥቂት ጓደኞቻቸው ቀልዳቸውን ይቀጥላሉ። አቶ መለስ ሺህ ዓመት ይንገሡ የሚሉ ተጨማሪ ልመናዎችን በቅርቡ ማየታችን አይቀርም። እነሱ ድራማቸውን ይከውኑ። እኛም ራሳችንን ነፃ ለማውጣት ተበታትነን ሳይሆን በአንድነት ቆመን የነዚህን ሰው በላዎች መጨረሻ ማፋጠን ጊዜው ግድ ይለናል።

 

የብዙኀኑ ህዝብ ራስ ምታት አቶ መለስ ሀገሪቱን ገለው፣ ዘርፈውና፣ በንጹሃን ደም ተለቃልቀው የት ሊሄዱብን ነው የሚል ጭንቀት አይደለም። በእሳቸው ይሁንታ የሚሰጠውን ሌላ ገዢ ለመቀበል በጭሰኝነት እጁን አጣጥፎ የሚቀመጥም አይኖርም። ዛሬ ሁሉም በየአቅጣጫው ለመብቱ በጋራ የሚቆምበትን የተበታተኑ ትግሎች መልክ ይዘው በአንድነት ራሱን ነፃ ማውጣት ይፈልጋል። በዚህ የሚዘናጋ የለም። ባይሆንም ቢሆንም ግን በወያኔ ሰፈር “መለስ ይለቃል” መባሉ የተወሰነ ጭንቀት ይፈጥራል። አቶ መለስን በዘሩ ብቻ ከነወንጀሉ ለሚደግፉ ዘረኞች ሺህ ዓመት ይንገሡ ማለታቸውን ሊቀጥሉ ይችላሉ። የሰውዬውን ወንጀል ለምንጠየፍ ግን አቶ መለስ ሥልጣን ቢለቁም በደም የቦካ እጃቸውን ፍትሕ ፊት ለማቅረብ እንጂ ሀገሪቱ ለሌላ ነብሰ ገዳይ እንድትሰጥ እጃችንን አጣጥፈን የማንቀመጥ መሆናችንን ጮክ ብለን ልንነግራቸው ይገባናል።

 

አቶ መለስ ወደዱም ጠሉ ከሥልጣን መውረዳቸው አይቀርም። እንደመንግሥቱም ሽው ብለው የሚሔዱበት ዓለም ጠቧል። በንጹሃን ደም በቦካ እጃቸው ለመሆኑ ምን ሊጽፉበት ነው? እንዴት ባለ አብዮታዊ አመራር ዘረኛ ሥርዓት መርቶ አንድን ሀገር ጉድጉዋድ መክተት እንደሚቻል? ወይስ እስከዛሬ የምፈልገውን ያህል ንጹሃንን ሙሉ ለሙሉ ባለመግደሌ ይፀጽተኛል ሊሉን? እንደሳቸው ኅሊና የሌላቸው ነብሰ ገዳዮች ከዚህስ የተሻለ ምን ሊሉን ይችላሉ? ለመሆኑ በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በዘር ማጥፋት ወንጀል የሚጠየቅ አቶ መለስን የመሰለ ዘር አጥፊ ምን እንዲጽፍ ይፈቀድለታል? አቶ መለስ ሊወርድብን ነው ብለው የሚያለቅሱ ምን አለበት ለሰውዬው አስቀድመው ቢጠይቁላቸው? እስከዚያው ግን አቶ መለስን ሌላ ድራማ አያስቡ በደም በቦካ እጅዎም ስለመጻፍ አይቃዡ እላለሁ።


 

ልዑልሰገድ (ከአቢሲኒያ) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!