አንገቱን የደፋ ሩቅ ማየት አይችልም (ዳኛቸው ቢያድግልኝ)
ዳኛቸው ቢያድግልኝ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
በአካልም ይሁን በሃሳብ አንገቱን የደፋ ሩቅ ማየት አይቻለውም። አንገታችንን ስንደፋ የዕይታችንን መጠን እናሳንሰዋለን፤ እንደ ቁመታችን ልክና እንደቆምንበት መሬት የምናየውም ይገደባል። በሞራልም በመንፈሥም አንገት ከደፋን ነገን የማየት አቅም ያንሰናል። ኑሮአችን የዛሬን ብቻ ይሆናል። ለዛሬ ብቻ መኖር ማለት ደግሞ ከሆድ እልፍ አይልም።
የዛሬን ብቻ የምንል ከሆነ ስለ ማንነታችንና ስለክብራችን ብዙም ግድ አይለንም። አንገት መድፋት ማለት ሽንፈት ማለት ነው። አንገት መድፋት ማለት የቅስም ስብራት ወይም ተስፋ ማጣት ማለት ነው። የሰው ልጅ አንገቱን ከደፋ በበረት ውስጥ እንዳለ የቤት እንስሳ ነው። ያ ሁሉ መንጋ ጉልበቱ በረቱን በርግዶ ሊያስወጣው እንደሚችል አያውቀውም። አንገቱን የደፋ ሰውም እውቀቱና ብልሀቱ ካለበት ችግር ሊያወጣው ስለመቻሉ ይጠራጠራል። አንገቱን የደፋ ህዝብም ያለውን ታላቅና እምቅ ጉልበት ልብ አይለውምና የለንቋሳና የደካማ መጫወቻ መሆን ግዱ ይሆናል።
ፈውስን የሚሻ ህመምተኛ እድናለሁ የሚል ተስፋ በውስጡ ከሌለ በጣም ቀላል ደዌም ወደ ሞት ይወስደዋል። እድናለሁ የሚልና ለመዳንም የሚቻለውን ሁሉ የሚያደርግና በተጨማሪም ከህመሙ በላይ ጤናው ተሟልቶ ሊያደርግ የሚሻውን የሚያስብ ሰው መዳኛ የለውም ከሚባል በሽታም እንኳ ሲፈወስ ይታያል። የችግር አረንቋ ውስጥ ተዘፍቆ መውጫ መግቢያ ጨልሞበት ያለ ሰው በምትታየው ትንሽ የተስፋ ጭላንጭል ያለበትን ሳይሆን የሚደርስበትን እያሰበ ከታላቅ ደረጃ ይደርሳል። ከትቢያ ተነስተው አንቱ የተባሉ ብዙ ናቸው። በአብዛኞቻችን ሕይወትም ውስጥ ይህ እውነታ አለ።
ለስደት እግራቸውን ያነሱና ከቀዬአቸው የወጡ ሰዎች ያለፉበትን መንገድ መለስ ብለው ሲመለከቱት በእርግጥም እነርሱ ያንን ሁሉ እስከማለፋቸው ድረስ በእርግጠኛነት ለመናገርም ይከብዳቸዋል። ያኖራቸው ተስፋ፣ ያቆያቸው ፍላጎት፣ ያበረታታቸው እምነት መሆኑን የሚገነዘቡ ብዙ ላይሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን በእውቀትም፣ በገንዘብ አቅምም፣ ሆነ በጉልበት የተሻሉ ሆነው የአዕምሮ ዝግጅታቸው በቂ ባለመሆኑ ምክንያት ተስፋ ቆርጠው የቀሩ ስለመኖራቸውም እናውቃለን። ስለዚህም ነው ከአንገት ቀና ማለትና ሩቅ ማየት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቢባን የሚነግሩን።
በጎጥ ደረጃ የሚያስቡ ሰዎች ከጎጥ ወደ መንደር ቁልቁል ሊሄዱ የግድ ነው። ምክንያቱም የዕይታቸውን መጠን በመንደር ገድበውታልና። ለዚህም ነው ዘወትር የጎጥ ንቅናቄዎች እልፍ ያለ ሁሉን አቀፍ የሆነ ጉዳይ የሚከብዳቸው። የጎጣቸውን ወርቅነትና ታላቅነት ሲያስቡ ሌሎችን እንደሚጎዱ ስለማያውቁ ጥላቻና ጠላት ሲያፈሩ ይኖራሉ። የመንደርና የጎሣ ሽኩቻ አሳር ያበላቸዋል። እንደ ሀገር ማሰብ ይጨልምባቸዋል፣ የያዙት እየተበተነባቸው ሸምቀቋቸውን ባጠበቁ መጠን ከየአቅጣጫው እየተተረተረባቸው ነፃ እናወጣሃለን የሚሉትን ህዝባቸውን ከችግር ወደ መከራ ሲጨምሩ ይስተዋላል። አምባገነኖች ሩቅ ማየት የሚችሉ ቢሆን ኖሮ ሽቅብ እየወጡ ሲፈጠፈጡ አዘውትረን ባልተመለከትን ነበር። ነገር ግን አንደኛቸው ከሌላኛው ስለማይማሩ በተመሳሳይ የማበጥና የመተንፈስ አዙሪት ውስጥ ተራ በተራ ሲሽከረከሩ እናያለን።
ነገሮችን በእርጋታና ወደእውነታው አትኩረን ከተመለከትን ብዙ ኢትዮጵያውያን አንገት ደፍተናል። በብዙዎቻችን የዕድሜ ዘመን አምባገነኖች በፈረቃ ሲያሸማቅቁንና ቁልቁል ሲደፍቁን ቆይተዋል። እኛም አንዴ ከደፋቂው አንዴ ከተደፋቂው ስንወግን፤ ወይም ዳር ቆመን ስንመለከት የዘመን አዙሪት ካለንበት አድርሶናል። ልጆቻችንም በኛው የመቀጣቀጥ ታሪክ ተሸማቅቀዋል። ዘወትር የገደለሽ በላ የሚዘመርባት ሀገራችን ደግሞ የተመቸችው እንደ ጭልፊት ሰማይ ሰማዩን ሲዞሩ ለነበሩ የድል አጥቢያ አርበኞች ነው። እኒህ ራዕይ አልባዎች በተገኘው አጋጣሚ የሚበሉትን በልተው አፍርሰውና አፋርሰው ፈትለክ የሚሉ ናቸው።
በሀገራችን ውስጥ ጥረው ግረው ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱትን ድሮ አቆርቋዥ ቡርዧ እያለ ዛሬ ቆርቁዞ የሚኖረው ትውልድ አባከናቸው። የዛሬዎቹ ባለሀብቶች በርካታዎቹ የአየር በአየር ዘራፊዎችና ሽፍቶቹ ናቸው። የነኚህ መተዳደርያ የማፍያ ሕገ ደንብ ነውና በግድም አንገት ያስደፋል። በዚህ ሁሉ አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ የገዘፈ ራዕይ ይዘው ያለነፃነት የመኖርን አስከፊነት ተገንዝበው ይልቁንም ለመጪው ትውልድ ባርነትንና ባዶነትን ላለማስረከብ የሚተጉ መኖራቸውንም እያየን ነው።
ታሪክም ከአንገታቸው ቀና ያሉ ብዙ ሰዎችን በምሳሌነት ዘግቦልናል። ማርቲን ሉተር ኪንግ ዛሬ የሆነውን ትናንት በማየቱ ነበር እልህ አስጨራሽ ትግል ታግሎ ደሙን በአውራ መንገድ ላይ ያፈሰሰው። ለግድያው እጃቸው ያለበት ሁሉ ይልቁንም እንዲያው የማይሞከረውን ነገር ሞክሮ ቤተሰቡን በትኖ አለፈ ያሉት ወገኖቹም ጭምር ግን በዚያን ዘመን ዛሬን ለማየት ያልቻሉ ነበሩ። የትናንት ባለግዙፍ ራዕይ ሰዎች መስዋዕትነት ዛሬ ኦባማን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አድርጎታል። የኢትዮጵያ ጀግኖች አንገታቸውን የደፉ ቢሆን ኖሮ የዓለማችን ታላላቅ ኃይሎች ያጸደቁትንና የደገፉትን የኢጣልያን ሞግዚትነት ወይም ገዢነት ባልሞገቱ ነበር።
አፍሪካ በጠቅላላው በቅኝ ግዛት ስር ወድቃ መርዝና እሳት ከሰማይ ማዝነብ ከሚችል ታላቅ ኃይል ጋር ለመጋጠም ባልሞከሩ ነበር። ይልቁንም አንገት የደፉ መንገድ ጠቋሚ ባንዶች ከሚሠሩት ደባ ጋር ተደምሮ ተስፋ መቁረጥ የግድ ሊሆን በተገባ ነበር። ነገር ግን አንገታቸውን ያልደፉ ሰፊ ራዕይ የነበራቸው ጀግኖች በጦርና ጋሻ ተፋልመን አሸናፊ እንሆናለን ብለው የቆረጡ በመሆኑ ነበር ፋሺዝምን ያህል ኃይል በአሸናፊነት የተወጡት። ምንም ይባሉ ምን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በኢትዮጵያ ላይ የተጫረው እሳት ዓለምን ይለበልባታል ሲሉ ሁነኛ መልዕክት አስተላልፈው ነበር። በእርግጥም ፋሺዝም አዕላፋትን ፈጀ፣ የብዙዎቹን ጎጆ አቃጥሎት አለፈ። ኢትዮጵያ ፋሺዝምን ድል ስታደርግ የመጀመርያዋ ሀገርም ሆነች። አንገት የደፉ ቀድመው ተሸናፊ የሆኑ ብዙ የአፍሪካ ሀገሮች ግን ያለጦርነት ተፈተው ነበር።
አሁን ግን አንገት የደፋን በርካታ ኢትዮጵያውያን አለን። በተለይ በውጭ የምንኖር። በስደት ብዙ የተንከራተትንና ቀን ሲወጣልን የነበርንበትን እንኳ የማናስብ ዘወር ብለን የማናይ በርካቶች ነን። ምንም ነገር ማድረግ ባንችል ቢያንስ እኒያን ወገኖቻችንን ተስፋ መመገብ የምንችል ሰዎች እንኳ መሆን አልቻልንም። እኔ ወንዙን ከተሻገርኩ ወዲያ ማዶ ላሉት ወንድም እህቶቼ እኔ ምንተዳዬ የምንል ብዙ ነን። ሀገር መውደድ ማለት ወገን መውደድ ማለት ነው። ሀገር ማለት ተራራና ሸንተረሩ ብቻ ሳይሆን ህዝቡ ነው።
ስለፖለቲካ ከማሰባችን በፊት ስለ ሰው ልጅ ፍቅር ሊኖረን ይገባል። ይህ ጎድሎን ግን ስለ ሀገር ፍቅር የምናወራ ከሆነ አንድም ውሸት አልያም ሥልጣን ፈላጊዎች ነን ማለት ነው። ታላቅ የፖለቲካ አስተዋጽዖ ማድረግ ቢሳነን፤ ከማኪያቶ ወጪ ሸርፈን የሚንቀሳቀሱትን እንኳ ብናበረታታ መልካም ሆኖ ሳለ፤ ከቶ ምንም ባልተሳተፍንበትና ግዴታችንን ባልተወጣንበት፤ ሊያውም ሌሎች በሚያደርጉት ትግል ቶሎ ተስፋ እንቆርጣለን። ሌሎቹን ቀጥረን የምናሠራቸው ይመስል ነፃነታችንን በወኪል ለማግኘት እንሻለን።
ወ/ት ብርቱካን የፖለቲካ ሰው ስለሆነች ብቻ ሳይሆን እንደሰብዓዊ ፍጡር እንኳ እየደረሰባት ያለው ግፍ ሊያሳዝነን በተገባ ነበር። ሠላማዊ ሰልፉ እንኳ ቀርቶ ‘ፒቲሽን’ ለመፈረም በወራት ጊዜ ውስጥ 1926 ፊርማ ብቻ ነው የሰፈረው። ስለዚህ ከቁጥር እንኳ የሚገባ ድጋፍ የላትም ለሚል የጠላት የመከራከርያ ነጥብ ያግዝ እንደሁ እንጂ ለታቀደው ዓላማ ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው አላውቅም። የቴዲ አፍሮም እንዲሁ ፊርማው 5091 ላይ ቆሟል። ከእስር ተፈትቶ ኮንሰርት ያዘጋጃል ቢባል ስንት ህዝብ ሊገኝ እንደሚችል ስንገምተው ለወገኖቻችን በችግራቸው ጊዜ ፈጥኖ ደራሾች ነን ለማለት አያስፈራም ይሆን?
በመጨረሻም እርስ በእርስ መጠባበቁን ቀነስ አድርገን እንደ ኦባንግ መፈክር የድርሻችንን ታህል ብቻ ብንሠራ መልካም ነው። ሰዎችን ሰማይ ጥግ ቆልለን ያልሆኑትን ሆኑ ብለን ክበን ትንሽ ሳይሆን ሲቀር አውርደን የምንፈጠፍጥ መሆን የለብንም። ከሁሉ በላይ ግን በሕይወታችን አቅጣጫዎች ሁሉ ከአንገታችን ቀና እንበል በዛሬ ላይ ቆመን ነገን እንመልከት። ይህ እንደ ሰብዓዊ ፍጡር ከወገኖቻችን፣ ከቤተሰቦቻችን፣ እንዲሁም ከሥራ ባልደረቦቻችን ጋር በሠላም የሚያኖረን መንገድ ነው። እልፍ ሲል ደግሞ ነፃነታችንን የመቀዳጃ መንደርደሪያው ነው።
አንገቱን የደፋ መለመን እንጂ መጠየቅ አይችልም። ይገባናል የምንለው ነገር ካለ፤ “መብታችን ነው!” ብለን የምናምን ከሆነ ለማስፈጸም የሞራል ወይም የስነልቡና ዝግጅትና የእውቀት ስንቅ ይዘን መነሳት አለብን። ያኔ ከአንገታችን ቀና እንላለን። ወደፊት ለመሄድ ደግሞ በጥንካሬአችን ላይ መረባረብ ያሻል። ያልመጡትን ለመሳብ ወደኋላ ከመመለስ ከጀገኑት ባለ ራዕዮች ጋር ፈጥነን እንገስግስ። የአሸናፊ አጀቡ ብዙ ነውና ለምነን ያላመጣናቸው ጊዜው ሲደርስ ሮጠው ይደርሱብናል። ስለዚህ አብሮ ለመሄድ ሲባል ተጓትቶ ከመውደቅ ይልቅ የአስተሳሰብና የዓላማ አንድነት ያላቸው ፈጥነው ቢገሰግሱ የድል ባንዲራውን ከተራራው አናት ላይ ለመትከል ያስችለናል። ሩቅ ማየት ከቻልን ያለጥርጥር ካሰብንበት እንደርሳለን!!
ዳኛቸው ቢያድግልኝ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



