ተክለሚካኤል አበበ

 (ክፍል ሁለት)

 

ሌላው እንደጠላቶቻችን ወይም እንደባላንጣዎቻችን የምንመለከታቸው ሰዎች ወደኛ ጎራ ሲያቀኑ ለመቀበልና በአባልነት ልንደባልቃቸው መዘጋጀት አለብን። ለምሳሌ ተስፋዬ ገብረአብን እንውሰድ (ስለዚህ ሰው ጉዳይ ከዚህ በፊትም ጭሬያለሁ)። አንዳንድ ሰዎች፡ በተለይ የድሮ የሻእቢያ ቂም ላይ ሙጭጭ የሚሉ ሰዎች፡ የተስፋዬ መጽሀፍ ምንም ሊዋጥላቸው አልቻለም።
 

 

 

ውይይት ለሰላምና ለጋራ ዓላማ በኢትዮጵያ” ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የቀረበ ጽሁፍ

 

ሐ- ጠላትን ሲመጣ አለመቀበልና ከኛ ጋር ለመደባለቅ ሲጠይቅ መስፈርታችንን ማጠንከር

 

ሰው እሱ ነኝ ያለውን ላይሆን ይችላል። ሰው ግን እኛ ያልነውንም ነው ማለት አይደለም። ተስፋየ ገብረአብ፡ እሱ ነኝ ያለውን ወይንም እኛ ነው ያልነውን ባይሆን፡ አንድ ነገር ግን ርግጥ ነው፤ ተስፋዬን መቀበል ሌሎችም እንዲናገሩና እንዲመጡ ይጋብዛል። ያበረታታል። ብዙ ሰዎች ኢህአዴግን ከድተው ወጥተዋል። ነገር ግን የተስፋዬን ያህል የጻፈና የተናዘዘ የለም። ይሄ ልጅ፡ በወንጀል ሊያስጠይቀው የሚችል ሀጢያቱን እንዲናዘዝ መጠበቅ የለብንም። ከዚያ መለስ ግን፡ በቢሾፍቱ/ደብረዘይት የተወለደ፡ አንድ ስራ ፍለጋ ከእናቱ ተለይቶ የዘመተ የ23 ዓመት ልጅ፡ በወጣትነቱ በምርኮ ኢህአዴግን ተቀላቀለ። ሁለት ጸጉር ያበቀሉቱ ስንት በስተርጅና የሚያቀል ስራ እየሰሩ ሽቅብ ቁልቁል ሲሉ በምንመለከትበት መንደር፡ ይሄ የ23 ዓመት ልጅ ግን፡ ከአስራምናምን ዓመት አገልግሎት በኋላ እነሆ ንስሀ ገባ። ይሄንን ሰራሁ፤ ይሄንንም አደረግሁ አለ። ሌሎችም ያደረጉትን ነገረን። ጌታ ይባርክህ ብለን ወደማህበራችን መደባለቅ፡ አንድም ይሄ ልጅ ያስቀረው ነገር ካለ እንዲናገር መገፋፋት ነው። ሁለተኛ እሾህን በእሾህ ከሆነ፡ ይሄ ሰው በየት መንገድ ብንሄድ እንደሚያዋጣን ትንሽ ሀሳብ ሊሰጠንም ይችላል። ሶስተኛ ሌሎችን ያበረታታል። ያለበለዚያ ግን፡ ባላንጣዎቻችን ወደኛ ጎራ መጥተው የማንቀበላቸው ከሆነ፡ እዚያው እባላንጣችን ጋር ወግነው፡ እኛን መውጋቱን ይመርጣሉ።

 

መ- ዳቦም ያለው ፖለቲካ ያስፈልገናል

 

የኢትዮጵያን ችግር በፖለቲካዊ መንገድ ሊፈታ የሚጥር ምሁር፡ ያ ነጻ አወጣሃለሁ የሚለውን አካባቢና ህዝብ በሁሉም መንገድ ለመድረስ መጣር አለበት። ለምሳሌ ሁልግዜም የሚሰማኝ ነገር፡ ከተቃውሞ ፖለቲካችን ባሻገር ተለዋጭና ተጓዳኝ ልማቶችን በተወለድንባቸው አካባቢዎች ስለማድረግ ነው። ቀላል አይደለም። ግን መሞከር። ህይወት ሙከራ ነው። የሰው ልጅ ታሪክ የሙከራና የፍልሚያ ነው ይለናል ሮናልድ ራይት።[1] የሚያዋጣን የሚበጀን መንገድና መፍትሄ እስክናገኝ ድረስ መሞከርና መፈተሽ። ይህ ህዝብ ተርቧል። የተራበ ሰው ደግሞ ተስፋ ብቻ ሳይሆን ዳቦም ይሻል። በምንም መልኩ ተጋፍተን ዳቦም መወርወር አለብን። ከህዝቡ ጋር ያለን ትስስር መጨመር ካለበት፡ ይሄ ትንንሽ ልማቶችን በተወለድንባቸው አካባቢዎች ማድረግ አንዱ መንገድ ነው። በዚህ መሀከል ያለው ተስፋ፡ እንደዚህ እንደ ኦባማም ቢሆን፡ ድንገተኛ ታሪክ አይጠፋምና መሞከር ነው የሚል ነው። አንድ በዚህ በቀድሞ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ውጥ የነበረ በውጭ አገር የሚኖረ ጸሀፊ፡ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ እንቅስቃሴ የጀመረው ከኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅቃሴ ጋር ተያይዞ ነው ይላል። ከዚህ ሰው ፅሁፍ ውስጥ የማረከኝና በተደጋጋሚ የምሰማው ነጥብ ግን፡ እነዚህ የኢትዮጵያ ተማሪዎች አገር ቤት ካለው እንቅስቃሴ ጋር የጠበቅ ግንኙነት እንዲኖራቸው ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው።[2] ይሄ አገርቤት ካለው እንቅስቃሴና ህዝብ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ይዞ መቆየት አሁንም አስፈላጊና ልናስብበት የሚገባ ነው። ነጻ አወጣዋለሁ ወይንም ተበድሏል ከሚለው ህዝብ የራቀ ትግልና ቃል፤ ባዶ ይመስለኛል። ምንም የማይሰማ ጩኸት። በዚህ ረገድ በአገራችን እንድንሰማ፡ የሚሰማ የሚደመጥ፡ የሚስተዋል፡ የሚማርክ፡ የሚያሰልፍ ድምጽ የሚፈጥር ግንኙነት መገንባት አለብን። ያንን ተሰሚነት ደግሞ በደረቅ ተቃውሞ ብቻ አናገኘውም። ከተቃውሞዋችን ባሻገር፡ እንደምንም ተሽሎክሉክን የወለደንና ያስተማረን ሕዝብ ጋር የሚደርስና፡ የዛሬን ረሀብ አብርዶ፡ የነገው ተስፋ ጋር የሚያሻግር መለስተኛና የሚታይ ልማትና ቁሳዊ ስጦታ ማበርከት አለብን። በምሁራን በኩል እየሆነ ያለው ግን ያ አይደለም። 

 

ዘመን የሚዘል ችግርና የምሁራን ሽኩቻ

 

የኢትዮጵያ ችግሮች ድንገት የተወለዱና በዘመነ ኢህአዴግ የተከማቹ አይደሉም። ግን የኢህአዴግ ችግሩ ይሄንን ሁሉ ችግር፡ ባንድ ዙር፡ ባንድ ርእዮተ ዓለም፡ ባንድ ፓርቲ፡ ባንድ ዘመን፡ ባንድ ትንፋሽ፡ ባንድ ፖሊሲ እፈታለሁ ማለቱና ለሌሎች አማራጮች መንገድ አለመክፈቱ ነው። ይሄንን ችግር ግን ያባሰው ከምንም በላይ፡ እኛ በተለይም በዚህ በውጭ የምንኖረው ሰዎች ሕዝቡን ሰርጾ የሚገባና የሚያቸንፍ ስልት አለመንደፋችን ብቻ ሳይሆን፡ ጭራሹንም እርስ በርስ መናደፋችን ነው። የራሳችንን መንገድ ለመገንባት መጣር አንድ ነገር ነው። አንዱ የጀመረውን ለመናድ ሲጭሩ ማደር ግን ሌላ ነገር ነው። በዚህ ሁሉ መሀል ነው፡ የኢትዮጵያ ወጣት ወደቀደሙት ታላላቆቹ አሻግሮ ሲመለከት እነዚያ ትናንት አንተ የጳውሎስ ነህ አንተ የአጵሎስ እያሉ ሲፋለሙ የነበሩት ወገኖች አሁንም በዚያው ቅኝት፡ እንዲያውም በባሰና ወደ ወጣቱ ወደራሱ በሚጋባ መልኩ ሲደባደቡ የሚያመው። ይሄ የክስ መድረክ አይደለም። ግን እንደው በትህትና በየዋህነት ለመጥቀስ ያህል፡ አንዳንድ ምሁራን የራሳቸሁንም የዚህንም ትውልድ ችግር የመመርመር ተልእኮዋችሁን በድል ሳትወጡ፡ እንደውም የቀደመ ቂምና ቁርሾ እያስታወሳችሁን፡ ፖለቲካዊ ደም መቃባታችሁን እንደቀጠላችሁ ነው።[3]

 

ሰው የመጀመሪያውን ስህተት በተለያየ ምክንያት ሊሰራ ይችላል። የቀድሞ የኢትዮጵያ ተማሪዎች፡ ዴሞክራሲአዊ ባህል እያልን የምንጠራው የምርጫ ስርአትና የብዙሀን ፓርቲ ስርአት ባልሰፈነበት፡ ልምዱም ባልኖረበት ሁኔታ ከምንም ተነስተው ለዚያች አገር ይጠቅማል ያሉትን ሁሉ ለመስራት ባደረጉት ጥረት አንድ ስህተት ቢሰራ፤ ሊከሳቸው የሚችል ማንም ሊኖር አይገባም። የኢትዮጵያ ተማሪዎች፡ ኢፍትሀዊነት በነገሰበትና መሬት በጥቂት ባላባቶች ተይዞ ገበሬዎች በገባርነት በሚሰቃዩበት ወቅት ተነስተው፡ “የለም ይሄማ አይበጅም” ብለው መሬት ላራሹ እንዲሆን ከዚያም ባሻገር፡ ጠቀመም አልጠቀመም፡ ረባም አልረባም፡ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት እስከመገንጠል አራምደው ኤርትራ ብትገነጠል፡ የደረሰው ሁሉም ጥፋት ቢደርስ፡ ያ የመጀመሪያ ተሞክሮ ነበርና፡ ወጣትነትም ስለሆነ በዚያ አክርረን ልንወቅሳቸው ወይንም ልንከሳቸው አይቻለንም። ምክንያቱም የአለም ታሪክ የሙከራ፡ የመጀመሪያው ሙከራ ሁሉ ደግሞ የጥፋት ነውና።[4] ነገር ግን ያ ሁሉ አልፎ፡ ከዓርባ ዓመታት በኋላ፡ ዛሬም ተማሪ ወጣት እንሁን ቢሉ ወይም ብትሉ፡ የሚቀበል የለም። አይሆንም። ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ የዛሬ ምሁራን፡ የትናንትናዎቹ ተማሪዎች በያንዳንዱ እርምጃቸው ጥንቃቄን ሊያደርጉ ይገባል።

 

የተማሪና የወታደር ነገር

 

አንዳንድ ሰዎች የተማሪን ስራና እንቅስቃሴ ያጣጥላሉ። ተማሪ ግን ተማሪ ነው። ልክ ወታደር ወታደር እንደሆነው ሁሉ። ተማሪ ሀላፊነቱ መጫር ነው። በተማሪዎችና ወታደሩ እንቅስቃሴ የሀይለስላሴ መንግስት ተገረሰሰ። ያንን ከግብ ማድረስ ያዋቂው ሀላፊነት ነው። ደርግ መጣ። እንደ ኢህአፓም ይሁን እንደ መኢሶን እንደ ደርግም ይሁን እንደ ሌላ በዚያ ዘመን የተሰራ ስራ ዛሬያችንን ቢያበላሸውም፡ የበለጠ የሚያቃጥለው ያ በዚያ ዘመን የተሰራው ሳይሆን፡ ያ በዚያ ዘመን የተሰራውና ዛሬም ድረስ እየተከተለ እንዳንስማማ አይደለም እንዳንደማመጥ የሚያደርገው ጉዞዋችን ነው። ያኔ ያልተደማመጠ ትውልድ ዛሬም እንዳይደማመጥ የተደገመበት ይመስላል።  ቀደም ሲል እንደተናገርኩት፡ ይሄ የክስ መድረክ አይደለም። ማንንም ለመክሰስም አልቆምኩም። ግን ስላለፈው ሳስብ አንድ ነገር ያበሳጨኛል። አባቴ ወታደር፡ ሰላሳ አራት ዓመት ይህቺን አገር አገልግሎ፡ ከኮንጎ እስከ ኦጋዴን ከቦረና እስከ ባሬንቱ ተንከራቶ የሞተ ሰው ነበርና ለወታደር ታላቅ ክብር አለኝ። ግን ወታደር ወታደር ነው። አባቴ ሰዎች በመረጡት ግዜ፡ ሰዎችም በጫኑበት ግዜ ያገር ሽማግሌ፡ ሚስት አማጭ፡ የተጣሉ አስታራቂ፡ የሰበካ ጉባኤ አባል ሆኖ ቢያገለግልም፡ ሁልግዜም ግን ወታደር ነበር። ድንበር የሚጠብቅ፡ አገር የሚጠብቅ ወታደር። ስለዚህ ወታደር እወዳለሁ። ወታደር አለመውደድም አልችልም። ግን ወታደር ወታደር እስከሆነ ድረስ ነው።

 

ወታደርና ሽፍታ ቤተ መንግስት ገብቶ ከከረመ ነገር ይበላሻል። ጥንትም እንደዚያ ነበር። አሁንም እንደዚያ ነው። ዩኒፎርም መለወጥ ተፈጥሮን አይለውጥም። የሆነው ሆነ። ግን እንደወታደርም ይሁን እንደተማሪ፡ የቀደመውን ስህተት መድገም የለብንም። ምን ያህል ያስኬድ እንደሁ እንጃ እንጂ፡ አቶ ስዬ አብርሀ የዛሬ ዓመት ከምናምን ወደዚህ ወደ ዲሲ ሲመጡና ሲናገሩ ያሉትም ይሄንኑ ነው። የኛ ትልቁ ችግራችን፡ ፖለቲካውንና ወታደራዊውን ተፈጥሮ አደባልቀን የያዝን ወታደሮች ነበርን። ያንኑ ባህርይ ይዘን ከተማ ገባን። ስለዚህ በወታደራዊ ተፈጥሮ ላይ ዴሞክራሲአዊ ተፈጥሮ ሊስማማን አልቻለም።[5] አቶ ስየ ይሄንን የተናገሩት ኢህአዴግ/ህወሀት ለምን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ኢዴሞክራሲያዊ ሆነ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ሳይሆን ኢህአዴግ ለምን በነሱ በነአቶ ስዬ ላይ ጨከነ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ነበር።

 

ደግሞ ደጋግሞ አንድ አይነት ስህተት

 

ተስፋ በሌለበት የተስፋ ምድረበዳ፡ የኢትዮጵያ ወጣት፡ ከምሁራን የሚማረውንና የሚጠብቀውን ነገር መዘርዘር ቀላል ነው። እሱ ላይ ጊዜ አላባክንም። ይልቅስ ይህ ትውልድ ከምሁራን የማይማረው፡ ወይም የማይወስደው አንዱና ዋንኛውን ነገር፡ ልጥቀስ፤ እልህ መጋባትና ስህተትን መድገም። እልህ ከችግሩ እንጂ እልህ ከሰዎች መጋባት አያስፈልግም። ሰው ቦታውን ካጣ ሁሌም ነገር ይበላሻል። እኔ ራሴ ያለቦታዬ ከሆነ ይሄንን ያልኩት በጣም ይቅርታ። ወጣቶች ግን በቅን ልቡና ስህተት ላይ ቢወድቁ ስህተታቸውን ይቅር ለማለት የተዘጋጀን ነን። እነዚያው ትናንት በስህተት ውስጥ ያገኘናቸው ወጣቶች ግን ዛሬ በስህተት ውስጥ፡ ለዚያውም በተመሳሳይ ስህተት ውስጥ ሲዳክሩ ብናገኛቸው፡ ቢያንስ እናዝናለን። ይሄን ፖለቲካዊ የጭቃ ጅራፍ የመወራወር ባህል እጅግ ከመልመዳችን የተነሳ፡ ነገር ካልመረረ የሚጥመን ያለንም አይመስለኝ። ባለፈው ሰሞን ከዚህ ከምርጫ 97 በኋላ የተፈጠረውን ብዙዎቻችንን አንገት ያስደፋ ሽኩቻ ያሰታውሷል። አንድ ጸሀፊ እንዳለው፡ እኛ ኢትዮጵያዊአን ደግና ሩህሩህ፡ ለእንግዳ የሰው አገር ሰው ደግ የመሆናችንን ያህል፡ የዚያኑም ያህል አንዳችን አንዳችን ላይ የምንጨክንና ለማዋረድ የምንተጋ መሆናችንም የተገለጸበት ቅጽበት ነበር።[6] በሁሉም አቅጣጫ የምንጎዳው የምንጠቃውም በተመሳሳይ ጠላት በተመሳሳይ ስልትና በተመሳሳይ ጥይት ነው። በስልጣን የሚቀመጡትም፡ ስልጣን ለመያዝ የሚታገሉትም ሲያጠቁን የሚያጠቁን በተመሳሳይ መልኩ ነው። ደርግ መጣ ሰው ገደለ። ተቃዋሚዎች ተባሉ። አሁንም ተቃዋሚዎች ተባሉ እኛንም አባሉን። የመንግስታቱን እንተወው። ለማስቆምም አቃተን እንበል። በኛ በኩል ያለውን ግን ላለማስቆም ምን ምክንያት፡ ሰበብስ አለን?

 

ደግሞ ደጋግሞ ተመሳሳይ ችግር ያጠቃናል። ያ ብቻም አይደለም፡ ዋናው እንቅፋታችን በዋናው ችግር የሚፈጠርብን አይደለም። ከዋናው ችግር መለስ እኛ ራሳችን የምንፈጥረው ፖለቲካዊ አባጣ ጎርባጣ ነው የሚያደነቃቅፈን። ለምሳሌ የፊታውራሪ ተክለሀዋርያት ተክለማሪያምን መጻህፍ ስናነብ፡ ፊታውራሪው ከአስር ዓመት የውጭ አገር ትምህርት በኋላ ከፍተኛ ህልም ሰንቀው ወደሀገራቸው ተመልሰው የቀሰሙትን ትምህርት ወደአገራቸው ለማሸጋገር ሲጥሩ ትልቁ እንቅፋቸታቸወ የቴክኖሎጂው እጥረት፡ ወይንም የመልክአ ምድሩ አለመመቸት ወይንም የሰዉ ስንፍና አልነበረም። ይልቅስ የአጼ ምኒሊክን ሞት ተከትሎ፡ የወራሻቸው ልጅ እያሱ ቧልት ማብዛት፡ ከዚያም አጼ ሀይለስላሴም ስልጣን ቢይዙ፡ በራሳቸው በአጼ ሀይለስላሴ የግል ዝና ወዳድነት እንዲሁም በዙሪያቸው የተኮለኮሉት አማካሪዎች ምቀኝነትና አሉባልታ እንጂ። የፊታውራሪ ዘመናዊ ህገ መንግስት የመገንባት፡ ዘመናዊ ከተማ የማነጽ፡ ዘመናዊ ወታደር የመገንባት ህልም አፈር ድሜ ሲበላ፡እንዲያውም ፊታውራሪ ይባስ ብሎም ለህይወታቸውም በሚያሰጋቸው መልኩ ለእስር ሲዳረጉ፡ ቤተሰባቸው ሲሰቃይ እንመለከታለን።[7] የፊታውራሪ ህልም መልካም ሆነ አልሆነ፡ ህልማቸውን ያመከነው የስራው አስቸጋሪነት አይደለም። ስራው ሳይጀመር ገና፡ አላላውስ ያላቸው በልጅ ኢያሱና በሀይለስላሴ ዙሪያ የነበረው ስብስብ የፈጠረው እንቅፋትና ተንኮል ነው። ይሄ የፊታውራሪ መጻህፍት ሀሰት ሆነ እውነት፡ ከሌሎች መጻህፍትም እንደምንረዳው፡ በኛም እድሜ እንደምናየው ብዙውን ግዜ ዋናው ችግራችን ችግሩ ሳይሆን፡ ችግሩን በመፍታት ወይንማ ባለመፍታት ሂደት የምንፈጥረው መሰናክል ነው።

 

ሌላ ምሳሌ፡ በሀይለስላሴም በደርግም በኢህአዴግም ሰዓት ሀገራችን ከረሃብ አልተላቀቀችም። የሚያሳዝነው ግን፡ ያለፉትን መንግስታት እንደሰማሁት፡ የዚህን ስርአት ደግሞ እንዳየሁት ከረሀቡ ይልቅ የበለጠ የሚጎዳን ወይንም ረሀቡን የሚያብሰው፡ መንግስታቱ የግል ዝናቸውንና ክብራቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ረሀቡን እንደሌለ ወይንም የሚያሳስብ እንዳልሆነ አድርገው የሚያስቀምጡት ነገር ነው። ደርግና አጼ ሀይለስላሴ እንዲሁም ኢህአዴግ በተለያየ ሰዓት የሚነሱትን ድርቆች ሲደብቁ ይታወቃል። ይሄ ዛሬ እኛ ከምሁራን ከምንጠብቀው ነገር ጋር ምን ያገኛኘዋል? ምሁራን ስሀተት ላለመድገም፡ ከዋናው ችግር የሚያስቀይስ ወይንም የሚያስዞረን ነገር ላለማድረግ መጠንቀቅ አለባቸው። ለምሳሌ፡ ዋናው ችግራችን የኢህአዴግ አስተዳደር ከሆነ፡ በምንም መልኩ ምሁራን አውቀውም ይሁን ተራቀው፡ ከዚህ ከዋናው የኢህአዴግ አስተዳደር ፊታችንን እንድንመልስና፡ እንዲያውም የራሳችንን ሌላ ችግር እንድንፈጥር የሚያደርግ ነገር ላለመፍጠር መጠንቀቅ አለባቸው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ማንሳት የምፈልገው ነገር የኛም የሌሎቻችንም የተማርነውም ያልተማርነውም “ከላይ ወዳታች በቃ”ም ያስፈልጋል። ድርጅቶቹ ይንዱን ብቻ ሳይሆን እኛም እንገስጻቸው።

 

ያ ከላይ ወደታች የሚለው ፈሊጥ አልሰራም፡ ሴቶችም ይምሩን

 

ይሄ ከላይ ወደታች የሚለው ስልት የሚሰራ አይመስለኝም። ከታች ወደላይም እንጂ። በምኖርበት ቫንኩቨር አካባቢ በዚያ ከታች ወደላይ በሚለው መርህ መሰረት እየተንቀሳቀስን፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጠብ የሚል ውጤት ለማምጣት ጊዜ ቢፈጅም፡ ለራሳችን ያህል ግን ውጤታማ እየሆንን ነው። ለምሳሌ በቅርቡ ባደረግነው ዘመቻ፡ አንድ የካናዳ ህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል፡ የወ/ት ብርቱካንን ጉዳይ የራሱ ጉዳይ አድርጎ እንዲይዝና እንዲንቀሳቀስ ማድረግ ችለናል። እንዲሁ ከአካባቢያችን ሴቶች ጋር በመተባበር በመስራት ለፖለቲካ እስረኛ ብዙ ገንዘብ ማሰባሰብ ችለናል። እንዲሁም ወደዚህ ስብሰባ ከመምጣቴ በፊት ከሁሉም ድርጅቶች የተወጣጣን ሰዎችና ኢትዮጵያዊያን ባደረግነው ስብሰባ መሪ ድርጅቶቻችን እኛን ማድመጥም እንዳለባቸው የሚገልጽ ጠንካራ ውሳኔ አስተላልፈናል። በነገራችን ላይ አንድ በዚህ አስር አመት ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር፡ ፖለቲካችን ጾታ ያለው ወይንም ጾታ የሚያውቅ ሁሉ መሰለኝ። እኛ ወንዶቹ ስንገናኝ ጭቅጭቅ፡ ክርክር፡ argument፡ ፍልስፍና፡ እውቀት እናበዛለን። ሴቶቹ ቀጥታ ስራ ነው። ለምሳሌ፡ ያኔ አቶ ደበበ እሸቱ ወደኛ አካባቢ ሲመጣ፡ ምንም ሴት የሌለበት የቅንጅት ድጋፍ ሰጪ ኮሚቴ 40 40 ብር መግቢያ አስከፍሎ፡ በስንት መከራና ጨረታ አራት ሺህ ብር ስናሰባስብ፡ በጥቂት ቀናት ውስጥ የተሰባሰቡት ሴቶች ግን ያለምንም ጣጣ አንድ እሁድ ተሰባስበው ያንኑ ያህል ብር ለብርቱካን ሚደቅሳ ሰብስበዋል። ሴቶችን ማሳተፍ ለሴቶች ስንል ሳይሆን ለራሳችን ስኬት ልንቀበለው የሚገባ ነገር ነው።

 

እንደ መደምደሚያ

 

አንድ ጸሀፊ እንዳለው፡ በታሪካችን በቤተሰብና በአካባቢያችን ተሸብበን የምንኖርና ዘመናዊ ባህል ሰርጾ ያልገባብን የዴሞክራሲ ባህል የሌለን ኢትዮጵያዊያን፡ ይሄ ዘመናዊ ባህል በሌለበት ሁኔታ፡ ዴሞክራሲንና የዴሞክራሲን ምሰሶዎች መትከልና እንዲያብቡ ማድረግ እንችላለን ወይ የሚለው ጥያቄ ይኸው አርባ ዓመት ሙሉ መልስ አላገኘም። በኔ እድሜ እንዳየሁት ግን ከመንግስታት ቀጥሎ ትልቁ የዴሞክራሲ እንቅፋት የሚመጣው  ዴሞክራሲ ከማያውቀው ያልሰለጠነ ወይንም ዘመናዊ ያልሆነ (ስልጣኔና ዘመናዊነት አከራካሪ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ) ባላገር ሳይሆን፡ እንዲያውም ዴሞክራሲ ያውቃል ሰልጥኗል፡ የምእራባዊያን ባህል ገብቶታል ከሚባለው ክፍልና ትውልድ ነው። በዚህ አስር አስራ አምስት አመታት የተደረጉትን የፖለቲካ ፍልሚያዎች ሁሉ ብትመለከቱ፡ ምናልባት በቲፎዞነትና በተከታይነት ተራው ህዝብ ተሳትፎ እንደሆነ እንጂ፡ እንደመንግስትም ይሁን እንደተቃዋሚ፡ አብዛኛው ዴሞክራሲን እንዳያብብ የሚያደርጉት ሽኩቻዎች የመነጩት ከተማረውና ከነቃው ይባስ ብሎም በውጭ አገር ከተማረው ክፍል ነው።

 

የምር የምር የሚሰማኝ ያው የሰው ልጅ ፈጠራና ጥበብ አያልቅም እንዲባል፡ የሰው ልጅ ፈጠራ ካላተቤዠን በቀር፡ ነገሮች ከቁጥጥራችን ውጪ እንደሆኑና የኢትዮጵያ ነገር ብቻ ሳይሆን የአለምም ነገር ባብዛኛው እንዳበቃለትና መፍትሄ ለማበጀት እንደዘገየን ነው። ምክንያቱም አብዛኛው ጉዳያችን በኛ እጅ ብቻ አይደለም። ጉዳያችን በሌሎችም እጅ ነው። የኢትዮጵያን ነገር የምንወስነው እኛ ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳንሆን፡ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ያልሆኑም ጭምር ናቸው።[8] ይሄንን ማለቴ ችግራችንን በሙሉና በሀቅ ነው መጋፈጥ ያለብን፡ ማድበስበስ የለብንም፡ባስቀመጥነውና “ዲፋይን” ባደረግነው ችግር ልክ ነው መፍትሄ ፍለጋ የምንሰናዳው፡ ከሚል እምነት በመነሳት እንጂ፡ የለም ችግራችን መፍትሄ የለውም መፍትሄውም በሰው እጅ ነውና እጃችንን አጣጥፈን እንጎለት ለማለት አይደለም። ተስፋን ሊሰጥ የሚችል ሁሉም ግብአት ያለን መሰለኝ። እውቀት፡ ገንዘብ፡ የሰው ሀይል፡ ፍላጎት፡ በቂ ትምህርትና ልምድ፡ ምሬት። የሌሉን ጥቂት ነገሮች፡ ትእግስታና መቻቻል፡ ከተቃርኖ ይልቅ አዎንታዊ ተሰጥኦ ላይ ማተኮር ናቸው። እነዚህ ከተሟሉ መጽህፍ ቅዱስና ሶሻሊዝም/ካፒታሊዝም ያልሰጡንን፡ ታሪካችን ውስጥና ከእይታችን የጠፋብንን ተስፋ ማግኘት እንችላለን። ያለበለዚያ ግን የሞተውን ተስፋችንን እየገደልን፡ የሞት ኑሮ እንኖራል።

 

ተስፋችንን ያመከኗቸው፡ አንዳንዶቹን እኛ ወጣቶቹ የፈጠርናቸው ወይም እኛ የምንቆጣጠራቸው ነገሮች ሲሆኑ፤ አንዳንዶቹ ግን ሌላ ሀይል የፈጠራቸው ናቸው። ለምሳሌ ወጣቶች ይገዳላሉ ይታሰራሉ ይንም ወጣቶች ከትምህርት ፖሊሲው ውጪ መሄድ አይችሉም። አንዳንዶቹ ግን እኛ የፈጠርናቸውና እኛው ልንፈታቸው የምንችላቸው ናቸው። ለምሳሌ ርስ በርስ በጨዋ ቋንቋ መነጋገር አለመቻል በማንም ልናሳብብ የማንችላቸው ጉዳዮች ናቸው። መጽሀፍ ያለማንበብ ባህል በብዛት የባለቤቱ ሀላፊነት ነው። አንድ ነገር ያንድ ነገር ውጤት ብቻ ነው ማለት አይቻለም። የሌሎች የብዙ ነገር ጥርቅም ሊሆን ይችላልና። ተስፋችንን የቀበረው ሌላው ነገር፡ ክስ ነው። መካሰስ አያስፈልግም። መካሰስ ካስፈለገ ግን የቀደመው ነው የሚከሰሰው። በኢትዮጵያ የቅርብ ግዜ ታሪክ ውስጥ፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች የሰሯቸው መልካም ተጋድሎዎች ቢኖሩም፡ መጨረሻው ግን አላማረም። ጎልቶ የሚወጣው ደግሞ አጨራረሱ፡ ደም መፋሰሱ የተፈለገው ግብ አለመምጣቱ ርስ በርስ መባላቱና መናከሱ ነው። ይሄንን እያየና እየሰማ ያደገን ትውልድ “የማይረባ” ብለን ልንወቅሰው አይገባም።፡ለምሳሌ፡ ዶ/ር ብርሀኑ አጠፋ አቶ ሀይሉ ሻውል፡ ሻለቃ ዮሴፍ ልጅ አንዳርጋቸው ወደሚለው ፍርድ ሳንገባ፡ ባንድ አጠቃላይ ነገር ላይ መስማማት እንችላለን። ባለፉት አራት አመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች፡ ከልክ ያለፈ፡ ጤናማ ያልሆነ ርስ በርስ መናከስና መካሰስ፡ ይሄንንም ይሁንን ያንን ትውልድ የሚያኮራ እንዳልሆነና፡ እንደጎዳንም፡ ጥፋተኛው ማንም ይሁን የተሰራው ስራ ግን ትክክል ባለመሆኑ እንስማማለን።

 

አንዳንድ ነገሮችን ለተሻሉት መተው መልመድም አለብን። ዴፈረንስ ይሉታል የካናዳ ፍርድቤቶች። በቅርቡ በካናዳ የተወሰነ አንድ ፍርድ የሰጠው ትንታኔ እጅግ ይማርካል።[9] አንዲት ካናዳዊ ዜግነት ያላት፡ ነገር ግን ከሌላ አገር የመጣች መጤ ሴት፡ አብሯት የሚኖረውንና ካናዳ ውስጥ ለመኖር ሕጋዊ ፈቃድ የሌለውን የልጇን አባት “ስፖንሰር” ለማድረግ ስታመለክት፡ እሷም እሱም ከካናዳ መንግስት ማህበራዊ እርዳታ/ድጎማ/ዳረጎት የሚቀበሉ ነበሩና፡ የካናዳ መንግስት የኢሚግሬሽን ህግም በመንግስት የገንዘብ እርዳታ የሚኖሩ ሰዎች ሌላ ሰው ሰፖንሰር ማድረግ አይችሉም ይል ነበርና፡ ይህቺ ሴት ሰፖነሰር ማድረጉን በተከለከለች ግዜ፡ የመንግስት ድጎማ መቀበል አለመቀበልን መሰረት አድርጎ መድልዎ ማደረግ የካናዳን የሰብአዊ መብት ድንጋጌ/ሕገ መንግስት የሚጥስ ልዩነት/ዲስክሪሚኔሽን ነው ብላ ከሰሰች። ፍርድ ቤቱ፡ “የለም የካናዳ ህግ አውጪዎች፡ የመንግስት እርዳታ የሚቀበሉ ሰዎች ሰውነት የጎደላቸው ዜጎች ናቸው ከሚል እምነት ተነስተው ሳይሆን፡ አንድ የመንግስት እርዳታ የሚቀበል ሰፖንሰር፡ ሌላ ፈላሽ/ስደተኛን ለመቀበል የሚያስችል አቅም ሊኖረው አይችልም ከሚል ተጨባጭ ግምት የመነጨ ስለሆነ፡ ህጉ መድልኦ አያደርግም፡ መድልዎ ቢያደርግም እንኩዋን ያደረጉበትን ምክንያትና ሰበብ ለመመርመር እነሱ ሕግ አውጪዎቹ ከኛ የተሻላ ቦታ ላይ ናቸውና ለነሱ እንተወዋለን ብሎ ወስኗል። አንዳንድ ግዜ አንዳንድ ነገሮችን ላንዳንድ ሰዎች መተው መልካም ነው። የኢትዮጵያ ምሁራን አንዳንድ መፍትሄዎችንና ውሳኔዎችን ለምሳሌ በሚቀጥለው ምርጫ እንሳተፍ አንሳተፍን፡ ችግሮችን ለመመርመር ከናንተ የተሻለ ቦታ ላይ ላሉ ምሁራን፡ ካስፈለገም መሀይማን፡ ወይም የድርጊቱ ዋና ተዋናዮች መተው ሊኖርባችሁም ይችላል። እኛ የኢትዮጵያ ወጣቶች፡ አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ፡ እስኪ መልካም እንዳልክ እንዳልሽ፡ አንዱ ከአዋቂዎቻችን የምንጠብቀውና የናፈቀን ነገር ነው። ለጊዜው የማያልቀውን ጨረስኩ። አመሰግናለሁ።

 

 እሁድ፡ 29 March 2009 ዓ.ም. ዋሽንግተን ዲሲ፡

 

 



[1] Ronald Wright, A Short History of Progress, Toronto፣ 2004

[2] ማሩ ጎበና፡ The Search for Alternative Mechanisms: Part II, March 2009 accessed online at http://ethioforum.org/wp/archives/868

[3] ከዚህ ቀደም በማለዳ ቁጥር ስድስት 2007፡ ላይ በጻፍኩት “የምስኪኖች እሮሮና የግብዞች ፌዝ” ላይ ይሄንን የሚመለከት አስፍሬያለሁ።

[4] ሮናልድ ራይት፡ ከላይ ማስታወሻ 19 ላይ

[5] ተስፋሚካኤል ሰአህለስላሴ፡ “ስዬ አብርሀ፡ አዲስ ወይን ጠጅ ባዲስ አቁማዳ ወይንስ አሮጌ ወይን ጠጅ ባዲስ አቁማዳ?” ጥር፡ 2008

[6] ማሩ ጎበና (ዶ/ር)፡ Reviewing the damaging effects of the Ethiopian diaspora politics፡ ክፍል 2፡  February 28, 2009 http://ethiomedia.com/aurora/9954.html

[7] ተክለሀዋርያት ተክለማሪያም፡ ኦቶባዮገራፊ (የህይወቴ ታሪክ)፡ 1953 ተጻፈ እና በአ.አ.ዩ.ፕ. አዲስ አበባ፡ በ1999 ታተመ። ይሄንን መጽሀፍ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ማንበብ አለበት።

[8] ፍቅረስላሴ ወግደረስ ከአባይና ቀይባህር ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ የገባችበትን ፈተና አስመልክተው ያቀረቡት ወረቀት። ጦቢያ መጽሄት (እ.ኤ.አ. 2000 ዓ.ም. አካባቢ)።

[9] የካናዳ ፌደራል ፍርድ ቤት ውሳኔ፡ Guzman v. Canada (Minister of Citizenship and Immigration) 2006 FC 1134; [2006] F.C.J. No. 1443 (QL).

 

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ