መክብብ ማሞ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

ሰሞኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን የተፈጠረው ግርግር የብዙዎቻችንን ቀልብ የሳበ መሆኑ ዕሙን ነው። ወደ ግርግሩ በመግባት ዝርዝር ማብራሪያ ለመስጠት አልፈልግም - የሙያው ብቃትም ሆነ ዕውቀት የለኝም። ሆኖም ግን በዚህ ጽሑፍ ለማተኮር የፈለኩት ፍትህንና የሰብዓዊ መብትን በተመለከተ የኃይማኖት መሪዎች እስከምን ድረስ መሄድ ይጠበቅባቸዋል የሚለውን ነው።

 

እንኳንስ ገና የዲሞክራሲ ምንነት በሥርዓት ባልተለመደባት ሀገራችን ኢትዮጵያ ይቅርና፤ በሠለጡትና የዲሞክራሲ ፋና ወጊ ነን በሚሉት ምዕራባውያን ሀገሮችም ውስጥ ኃይማኖት እና የኃይማኖት መሪዎች በፖለቲካና መንግሥት አስተዳደር ውስጥ ቁልፍ ሚና አላቸው። ይህ ልምድም ከጥንት ዘመን ጀምሮ ሲሠራበት የቆየ ሲሆን፣ በተለይም በመካከለኛው ዘመን የካቶሊክ ቤ/ክ በአውሮፓ የነበሩትን መንግሥታት በቀጥታ የማዘዝ ሥልጣን ነበራት። ይህንን ሥልጣን ጳጳሱ በመጠቀም ነገሥታትን ይሾምና ይሽር እንደነበር ከታሪክ እንረዳለን።

 

በ11ኛው ክፍለ ዘመን መጠናቀቂያ አካባቢ በጀርመኑ ንጉሥ ሔንሪ እና በሮማው ጳጳስ ግሬጎሪ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት “ንጉሡ የጳጳሱን ሥልጣን ተጋፍቷል” በሚል ከቤ/ክ በተወገደ ጊዜ፤ እዚያው ሮም ድረስ ሄዶ ይቅርታ እንዲጠይቅ በተደረገበት ተጽዕኖ ምክንያት ወደዚያው ያቀናል። ሮም ከደረሰም በኋላ ሦስት ቀን ሙሉ በአውሮፓ ብርድና በረዶ እየተንገላታ የጳጳሱን ደጅ ከጠና በኋላ ነበር ይቅርታን ያገኘው። (አንዳንዶችም ባዶ እግሩን በረዶ ላይ ቆሞ ይቅርታን እንደጠየቀ ይናገራሉ።) በዘመናችንም በአውሮፓም (ራሺያን ጨምሮ) ሆነ ሰሜን አሜሪካ እንዲሁም ሌሎች ሀገሮች የኃይማኖት መሪዎች በመንግሥት አሠራር ላይ ተጽዕኖ የማድረግ ኃይል እንዳላቸው በተደጋጋሚ የሚስተዋል ተግባር ነው። ይህም ከግብረሰዶማውያን “ጋብቻ” ጀምሮ እስከ ውርጃ፣ የሞት ቅጣት፣ ወዘተ ድረስ የሕግ አወጣጥንም ሆነ ፖሊሲ ቀረጻን ወደሚፈልጉት አቅጣጫ ሲዘውሩት የሚስተዋል ነው።

 

ወደሀገራችንም ስንመጣ ቤተክህነትና ቤተመንግሥት ለዘመናት የተሳሰረ ግንኙነት እንዳላቸው እንረዳለን። ነገሥታት ወደዙፋናቸው ሲወጡ በቤተክህነት አንጋሽነት ነበር ሥልጣናቸውን የሚረከቡት። የቤተክህነት መልካም ፈቃድና ድጋፍ የሌለው ዐፄ አልጋው አይረጋም፣ የግዛት ዘመኑም አይረዝምም። ይህም በዐፄ ቴዎድሮስ ዘመን የታየ ሲሆን፣ ንጉሡ ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩትን አዲስ የመንግሥት መዋቅርና የቤ/ክ አስተዳደር በመቃወም የቤተክህነት መሪዎች ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል። ይኸው የቤተክህነት የበላይነት እስከ ዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የዘለቀ መሆኑ የብዙዎቻችን የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

 

ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ከዐፄ ሥርዓት ተላቅቃ ወታደራዊው ደርግ ሥልጣኑን በተረከበ ጊዜ በቤተመንግሥትና በቤተክህነት መካከል የነበረው ግንኙነት መልኩን በመቀየር ቤተክህነት ቀጥታ የሥርዓቱ ተገዢ እና አስፈጻሚ መሆን ጀመረች። በዚህም ምክንያት ደርግ ቤተክህነትን በእጁ በማስገባቱ ለዓመታት ያሻውን ሲያደርግ፣ ሲያስር፣ ሲገድል፣ … ወዘተ ከቤተክህነት በኩል የተሰነዘረበት ምንም ዓይነት ጠንካራ ተቃውሞ አልነበረም። እንደ ሰማዕቱና ጀግናው አቡነ ጴጥሮስ “ውጉዝ ከመአርዮስ …” በማለት በድፍረት ያወገዘው የኃይማኖት አባት ባለመኖሩ በወዲ ዜናዊ ዘመንም ይኸው ወኔ ቢስነት ሊቀጥል ችሏል።

 

ለአብነት ለመጥቀስ ያህልም ከምርጫ 97 በኋላ የአግዓዚ ሠራዊት አልሞ ተኳሾች ንጹኀንን ግንባራቸውንና ደረታቸውን በጥይት እየበሱ ሲገድሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት ዋና ዋና ኃይማኖቶች - የክርስትናና (የኦርቶዶክስ ተዋኅዶና ሁሉንም ፕሮቴስታንቶችን ጨምሮ) የእስልምና ኃይማኖት መሪዎች መካከል በድፍረት ወጥቶ ይህንን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የተቃወመ አልነበረም። አሁንም እየተደረገ ስላለው አፈና፣ ግድያና የሰብዓዊ መብት ረገጣ ከየትኛውም የኃይማኖት አባቶች በኩል የሚሰማ ምንም ነገር አለመኖሩ የኃይማኖት መሪዎች የሞራል ዝቅጠት ጉልህ ማስረጃ ነው።

 

የሮማው ሊቀጳጳስ ቤኔዲክት ከሦስት ሣምንት በፊት ያወጡት ባለ 50 ገጽ ሰርኩላር (Papal Encyclical) ነበር። ይህ ሰርኩላር “በጎነት በእውነት” (CARITAS IN VERITATE) ተብሎ የተሰየመ ሲሆን፤ በጽሑፉም ላይ ስለ ፍቅር (በጎነት) ሲናገሩ “ፍቅር ሰዎችን ስለፍትህና ሠላም በድፍረትና በጽናት እንዲቆሙ የሚያደርጋቸው ልዩ ኃይል ነው” ይላሉ። ሲቀጥሉም ይህ ፍቅር ሰዎችን ከፈጣሪቸው ጋር በማስተሳሰር ከቤተሰቦቻቸው፣ ከወዳጆቻቸው እና ከሚጎዳኙት ቡድን ጋር በደቂቅ (micro) ደረጃ የሚያስተሳስራቸው ብቻ ሳይሆን በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በልሂቅ (macro) ደረጃም የሚያስተሳስራቸው እንደሆነ ይጠቅሳሉ። “እውነት የሌለበት ፍቅር ወደ ስሜታዊነት አዘቅት የወረደ ከመሆን ያለፈ ብቻ ሳይሆን ባዶም ነው። እውነት በሌለበት ባህል ውስጥ ፍቅር ለሞት የሚያደርስ አደጋን ይጋፈጣል” በማለት የፍቅርንና የእውነትን (ሐቅ) ግንኙነት ጽሑፉ ካስረዳ በኋላ በማስከተልም ሲቀጥል ዓለማችን አንድ እየሆነች ባለችበት ባሁኑ ጊዜ ለሰዎች ዕድገት “ልዩ አትኩሮት ሊሰጣቸው ከሚገባቸው ነገሮች መካከል አንዱ ፍትህ” እንደሆነ የሚገልጽ ሲሆን፤ “ፍትህ ደግሞ ፍትህን እንደሚሻ” ያስረዳል። ይህም በፍትህ ውስጥ ያለ ፍቅር “የሰዎችን ሕጋዊ መብት ማወቅና ማክበርን እንደሚጠቀልል እና በዚህች ምድር ላይ የሚገኝ ማንኛውንም ሀገር በሕግና በፍትህ ለመገንባት ጥረት እንደሚያደርግ” ጽሑፉ ያብራራል።

 

ይህንን ሃሳብ ይዘን አሁን ሀገራችን ወዳለችበት ሁኔታ ስንመጣ የሀገራችን ህዝብ በአሁኑ ጊዜ ይህ ነው በማይባል የሰብዓዊ መብት ረገጣ እና ፍትህ አልባነት ውስጥ እንዳለ በየቀኑ የምንሰማው እውነታ ነው። ከእነዚህ ሰለባዎች መካከል አንዷ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ለአብነት የምትጠቀስ ናት። ይህች የሠላማዊ ትግል መሪና የሕግ ተገዢ ሌላ አሳዳጊ ወላጅ ከሌላት ልጇና ጧሪ ከሌላቸው እናቷ ተለይታ ለወራት በእስር ስትማቅቅ፤ “እየተፈጸመ ያለው ነገር ተገቢ አይደለም” ብሎ የተቃውሞ ድምፁን ያሰማ የየትኛውም ኃይማኖት አባት (መሪ) አለመኖሩ የኃይማኖት መሪዎቻችንን ምን ያህል በፍርሃት የተተበተቡና ሞራላቸው ምን ያህል የላሸቀ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው።

 

ይህንን ኢ-ሰብዓዊ ተግባር መቃወም አንዳንዶቹ “በመንግሥት (በፖለቲካ) ሥራ ውስጥ እኛ መግባት አንችልም” በማለት ከንቱ ምክንያት በመስጠት ለማሳመን እንደሚሞክሩት ሳይሆን ፈሪና ለሥርዓቱ ሰጥ ለጥ ብለው መገዛታቸውን የሚያሳዩበት ጉልህ ማስረጃ ነው። ይህንንም በማድረጋቸው ምዕመኖቻቸውንና ተከታዮቻቸውንም እንዲሁ በፍርሃት አፋቸውን ለጉመው እንዲገዙ እያደረጉ መሆናቸውን ሳይረዱት የሚቀሩ አይመስለኝም።

 

ኅብረተሰብ የሚመራበት የሞራል (ግብረገብ) እና የፍትህ መመሪያ በአብዛኛው ምንጩ ኃይማኖት ነው። ሆኖም ግን አሁን በሀገራችን ባሉት ዋና ዋና ኃይማኖቶች ውስጥ ያሉ መሪዎች ለጥቅም የተገዙና እርስ በርሳቸው በዘር፣ በጎሣ፣ … ወዘተ ተከፋፍለው እየተፋለሙ ባሉበት ወቅት በእነዚሁ የኃይማኖት መሪዎች መካከል የታጣውን እውነትን፣ መከባበርን፣ ሐቀኝነትን፣ ወኔ ሙሉነትንና የዓላማ ፅናትን ከፖለቲካ መሪዎቻችን መጠበቅ ከንቱነት ነው። የሁለቱንም አካሄድ በአሁኑ ወቅት በግልጽ እያየነው ያለ ነው።

 

የኃይማኖት መሪዎች ለእውነት፣ ለሐቅ እና ለፍትህ ሲቆሙ በማይታዩበት ሁኔታ ላይ ህዝብ ከከንፈር ያላለፈ “ፍቅር” ማሳየቱ ለምን ይገርመናል? ይህ ፍቅር አልባነት ባዶነትን እና ወኔቢስነትን ከማስፋፋቱ ባሻገር የራስን ጥቅም የማሳደድ ጭፍን አመለካከት ውስጥ የሚጥል ሲሆን፤ ለሐቅና ለፍትህ የሚቆሙ ሰዎችን እንደ ሞኝና አላስተዋይ ወደመቁጠር እንደሚዘቅጥ እሙን ነው።

 

ህዝብ ከኃይማኖት መሪዎቹ ግብረገብ እና ለሕቅ መቆምን ካልተማረና ይህንንም ደግሞ በፋና ወጊነት የሚያሳየው መሪ ካላየ ቀስ በቀስ የአንድ ሀገር ህልውና ወደማክተሙ መሄዱ አይቀሬ ነው። በእንደዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ህዝብም “ፍትህ ይገባኛል፤ የሰብዓዊ መብቴ ሊከበር ይገባል!” ብሎ ለመብቱ ለመቆም ገና ረጅም ጉዞ ይቀረዋል። ስለዚህም ታላቁ መጽሐፍ እንደሚለው (ሚክ. 7፡4 እና 6፡8) ከመካከላችን ያለው “እጅግ ጨዋና ታማኝ የተባለው ሰው ከአሜኬላና ከኩርንችት በማይሻልበት” ዘመን የኃይማኖት መሪዎቻችን “ፍርድን ያደርጉ ዘንድ እና ምሕረትን ያወዱ ዘንድ” እንዲሁም ስለ እውነትና ስለ ፍትህ እንደ አቡነ ጴጥሮስ በድፍረት ይቆሙ ዘንድ ህዝብ ይጠብቅባቸዋል።


 

መክብብ ማሞ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ