ወደምዕራብ በሄድን ቁጥር ራዕያችንን እናጣለን

ማስታወሻ ከሰሜን አሜሪካ

ችግርና ምሬት እንደ መነሻ - አንደኛ

“በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሀሳብህ አርፎ ከሆነ ብዙ ሥራ ይጠብቅሀል” ይላል ከሁለት ሣምንት በፊት የደረሰኝና በየቀኑ እንደዳዊት የምደግመው የምስኪኑ ጓደኛዬ ደብዳቤ። በጽሁፍና በድርሰት ታሪክ ውስጥ በዚህች አጭር ሕይወቴ እንደተረዳሁት ምሬትንና ችግርን እንደመጻፍ የሚቀል ዓለማቀፋዊ ነገር የለም። ለመጻፍም ለመናገርም የሚቀል ርዕስ - ችግር ነው። ባለጸጋዎቹም፣ ነዳያኑም አገራት የችግራቸው ዝርዝር ተዝቆ አያልቅም። አሁን ካናዳና አውስትራሊያ ችግር ያለባቸው ይመስላሉ? እንደውም እነዚህ ሰዎች ሥልጣኔን ብቻ ሳይሆን ችግርንም ነው እንዴ የሠሩት? እስክትሉ ድረስ ችግር ቤቱን የሠራበት ምድር እዚህ ነው። እንዲሁም ዜናዎቻቸውን ብትሰሙ፣ የሚጻፉትም የሚነገሩትም ምሬትና ችግር ይበዛባቸዋል።

 

ለምሳሌ ሰሞኑን የአሜሪካንን ወይም የካናዳን መገናኛ ብዙኀን ብትዳስሱ፣ ዋና ዋና ዜናዎቹ ችግሮች ናቸው። ምርጫቸው ራሱ መሰረት ያደረገው ችግርን ነው። ህዝብን የሚያስለቅሰው የጤና አገልግሎት እናሻሽላለን፣ የሕገወጥ ስደተኞችን ጉዳይ ፈር እናስይዛለን፣ ሥራ-አጥነትን እንቀንሳለን፣ ሽብርተኝነትን እንዋጋለን፣ …። የወንጀል መበራከት፣ የሽብረተኞች ስጋት፣ የጤና አገልግሎት መጓደል፣ የቤት ዋጋ መናር፣ የዕፅ ተጠቃሚዎች ቁጥር ማሻቀብ፣ የቤት አልባዎች ቁጥር መበራከት፣ …። ምርጫው ራሱ ስለነዚህ ችግሮች ነው፤ ኦባማ እንዲህ አድርጎ፣ ሂላሪ እንዲህ ሠርታ። ፍቅሩም ችግር ነው። ኃይማኖቱም ችግር ነው። እያማረረኩ አይደለም። በዚህ በምዕራቡ ዓለም በሕይወት ትነቅንቅ ምክንያት ሚስት ለባሏ፣ ባል ለሚስቱ፣ ወላጆች ለልጆቻቸው፣ በስንት መከራ ጊዜ አጥሯቸው፤ ልጅና መኪና የመቀባበል ሕይወት በሚገፉበት የተጣበበ፣ በምቾት የተለወሰ የማይመች ሕይወት ውስጥ፤ እንዲህ እንደ ጓደኛዬ ያለ ደብዳቤ በር ዘግተን እንድናስብ፣ ወይም ገለል ብለን እንድንቆዝምና እንድናሰላስል ይረዳል። እነሆ እኔም ችግር ቀሰቀሰኝና ከዚህ ከተሰቀልኩበት ጥበቃ ስፍራዬ ችግር ልጽፍላችሁ ነው።

 

ከሰባት ዓመት በላይ ሳላየው ሳላወራው የቆየሁት ወዳጄ ነው እንዲያ የሚል ደብዳቤ የጻፈልኝ። “በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሃሳብህ አርፎ ከሆነ ብዙ ሥራ ይጠብቅሀል። ከስር ጀምረህ የምትቆፍረው ጉድጓድ መኖር አለበት። …” እያለ ይቀጥላል ጓደኛዬ። እየጦዘ፣ እያጦዘኝም የሚሄደው ደብዳቤው እንዲህ እያለ የስጋትና የምሬት ጥግ ላይ ይደርሳል። “... ስለተማረው የምታስበውን ያህል ተፈጥሮ ስለምታስተምረው አፈር ገፊ ማሰብ ይኖርብሀል። ስለከብት ጭራ ተከትሎ አዳሪ የምትጨነቀውን ያህል ስለወፍዘራሽ ተቀላቢውም ማሰብ አለብህ። ኢትዮጵያ ቀምለህ የማትጨርሰው ቅማል፣ ፈትገህ የማይጠራ እድፍ፣ ቆፍረህ የማያልቅ ጉድ የበዛባት ሀገር ነች። ወረቀትና ጥናት እንዳያሳስትህ፣ አብረህ ኖረህም የማታውቀው ህዝብ ያጋጥምሀል። …” ምናልባት በቀጣዮቹ ሣምንታት የጓደኛዬን ሙሉ ደብዳቤ አስነብባችኋለሁ።

 

እነሆ ጓደኛዬ ግን ሀሳቤን ጫረው። ምሬቴን ለኮሰው። ብሶቴን አጋጋለው። በዚህ ክረምት መጽሐፍ እጽፋለሁ እያልኩ፣ ካገር ከወጣሁ እንኩዋን ሰባት ክረምት አሳለፍኩ። ምንም የረባ ነገር ካልሰራሁበት ሰላሳ ዓመቴ ጋር ሲነጻጸር ይሻላል። እንዲህ እንደጓደኛዬ ያለ ሃሳቤን የሚጭር ነገር ሳገኝ ነው ብዕሬን የማነሳው። የምሰማው ሁሉ ምሬት ሆነብኝ። ወንድሜን ስልክ ደወልኩለት። ጠጅ ይወድ ነበርና “ጠጅ ስንት ገባ?” አልኩት። ነገረኝ። የሽሮ ዋጋ። የጤፍ ዋጋ። የበርበሬ። የምትኖሩትንና እንደኔ በስልክና በወሬ ሳይሆን በሕይወት የምታውቁትን የኑሮ ዋጋ እዚህ መጻፌ ጠቀሜታው አይታየኝም። አገሬን ሳውቃት በችግር ነው። ለሺህ ዓመታት በተከመረ ችግር። ስለያትም በችግር ነው። ለሺህ ዓመታት ፈተን ያልጨረስነውን የሺህ ዓመታት ችግር እንደታቀፍን፣ ዕድሜ ለኢህአዴግ ሌላ ችግር ቆለለብንና ጓደኛዬ ችግር ጻፈልኝ። የግሉን አይደለም፤ ያገሪቱን። እና ወደኋላ ሄድኩኝ።

 

ምናለ እንደትናንቱ ቢያደርገኝ - ሁለተኛ

ሁለተኛ መነሻዬ የዛሬ ወር አካባቢ እዚህ ከምኖርበት ከተማ፣ ከምማርበት ዩኒቨርስቲ መጥተው ንግግር ያደረጉልን የቀድሞ የካናዳ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ወ/ሮ ሎርዬ ዱቤ (ዱብ) በወጣትነታችንና በልጅነታችን ወደዩኒቨርሲቲ ስንገባ ይዘናቸው ስለምንመጣው ታላላቅ ሃሳቦችና እነሱን ይዘን ስለመጓዝ የጣሉት ሃሳብ ነው። ቃል በቃል አላስታውሰውም። ግን በጥሬ ትርጉሙ “ልጆች፣ ተማሪዎች፣ ዓለም ፍትሐዊ አይደለችም። ቢሆንም እባካችሁን ወደ ሕግ ትምህርት ቤት ስትመጡ ይዛችኋቸው የመጣችሁትን ወርቃማና ድንቅ የፍትህ ሃሳቦች በምንም መልኩ አትጣሏቸው። ዓለም ፍትሃዊ ለመሆን የናንተን እርዳታ ትሻለች …” አይነት ነገር።

 

ሰባት ዓመት ወደ ኋላ ሄድኩና ከሰባት ዓመት በፊት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ት/ቤት ይዤ ስለገባሁት ራዕይና፣ አሁን ከሰባት ዓመት በኋላ ስለምገኝበት ሁኔታ አሰብኩ። የሰው ልጅ በእውኑ የልጅነት/የወጣትነት ራዕዩን ጠብቆ መቆየት እንደምን ይቻለዋል? ሰዎች ሲያድጉና ከሀገራቸው ሲርቁ የነበራቸውን በነበረው ልክ መያዝ ትተው፣ በትዝታና በናፍቆት ብቻ መወዝወዝን ለምን ይመርጣሉ? ማለቴ ለምን እንመርጣለን? አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በነበርንበት ሰዓት ስለኢትዮጵያና ህዝቦቿ የነበረን ራዕይ እንዳቅምና እንደጊዜውም ልክ ቢሆን ጣሪያ የነካበት ጊዜ ነበር። አሁን የት ገባ? አንዳንድ ግዜ ዘወትር ተማሪ ተማሪ ስባል መኖርን እጸየፍና፣ ቁጭ ብዬ ሳስበው ግን እዚያው ዕድሜ ልኬን ‘ተማሪ’፣ ‘ወጣት’ ሆኜ መቅረትን እመኛለሁ። ማደግ ስሜትንና ሀቀኝነትን፣ ተቆርቋሪነትንና ለወገን አሳቢነትን ይገድላል ልበል? የትግልን ማለቴን ነው። ሩቅ አትሂዱ። እነመለስን ተመልከቱ። ለጥፋትም ቢሆን፣ ብቻ ለቆሙለት ነገር የተሰዉት፣ የሕይወታቸውን እኩሌታ የሰዉት በዚያ በተማሪነት ዘመናቸው በተለኮሰባቸው የትግል ንዳድ ነው።

 

እኔን አንዱን ታናሽ ብላቴና በተመለከተ የተከሰተው ይሄ ነው። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እያለን ራዕያችን ጣሪያ ነካ። ከዚያ ወጥተን ኬንያ ስንሰደድ ይዤ የተሰደድኳቸው ሃሳቦች ከወራት በኋላ መነመኑ። ከዓመታት በኋላ ከሰሙ ብዬ ተስፋ ባላስቆርጣችሁም፤ ኮሰመኑ። እንደውም የሆነ ሰዓት ላይ ከኤደን ገነት የተባረረውን አዳም የሆንኩ ያህል ተሰምቶኝ ነበር። ወደ ካናዳ ስመጣ ጭራሽ የነበረኝንም አጣሁ። እንደውም ኬንያ ይሻል ነበር ልበል? ምቾት በሌለበት ቦታ ሁሉ አገርን መርሳት ይከብዳል። ነገር የሚበላሸው ምቾትና ጥጋብ፣ ምግብና ምግብ ሲበዛ ነው። ህወሓት/ኢህአዴግ ከመነሻው ዓላማው መልካም ነበረ ብዬ ለመናገር ባልደፍርም፤ ጨርሶውኑ የተበላሸው ግን፤ ያ ስሙን የረሳሁት ወዳጄ እንዳለው አዲስ አበባ ገብቶ ምግብና ሴት ሲበዛበት ነው። ምግብም ይሁን ፍትህ ያልራበን ዕለት ፍትህና ምግብ የተራበውን ህዝባችንን ማሰብ ከቶም አይቻለንም። ጥቂቶች ብቻ ናቸው የጠገቡ ዕለት ከሚኖሩበት ክበብ ውጪ ማሰብ የሚቻላቸው። ብዙዎቻችን የምናስበው በኑሯችን፤ ወይም በሕይወታችን የተገደበ ነው።

 

ኬንያ የዕለት ተዕለት ኑሯችን የግድ ሀገራችንን እንድናስታውስ የሚያስገድድ ነው። ማለቴ በልቶ ለማደር፣ ሳይታሰሩ ለመሰንበት መውተርተሩ ወደድንም ጠላንም ኢትዮጵያን እንድናስታውስና፤ ቢሆንም ባይሆንም ዕለት ዕለት ይሄንን መከራችንን ያበዛ ስርዓት እንድናማርርና፣ የሚወገድበትን መንገድ እንድናሰላስል የሚያስገድድ ሕይወት ነበረን። በርግጥ የኬንያ ሕይወት የዚያኑም ያህል ይሄንን ለአገር የመቆም ህልም ይገድላል። ምክንያቱም ስለሚበላውና ስለዕለት ኑሮው የሚያስብ ሰው ህዝብን ነፃ ስለማውጣት ማሰብ ቅርቡ ወይም የሚጨበጥ አይደለም። መጥገብም መራብም የልጅነትን ሕልም ያስረሳል። ሁለቱም ያኔ አደግ አደግ ስንል ይዘን የምንነሳቸውን ድንቅ ሃሳቦች ካስረሱን፣ ከአገርና ከህዝብ ነፃነት አንጻር በካናዳ ጥጋብ ኢትዮጵያን ከመርሳት ይልቅ በኬንያ ረሃብ ያገርን ጉዳይ ወደ ጎን ማድረግ ይሻላል ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም የኬንያ ረሃብ አቅም ይነሳል እንጂ፤ አቅል አይነሳም። የካናዳ ጥጋብ ግን ዓረቦቹ እንደሚሉት ሆድን አስፍቶ፤ አገር፣ ወገን፣ ምናምን የታጨቀበትን ጭንቅላት ያጠባል። ድሮም ተስፋችን ከምስራቅ እንጂ ከምዕራብ እንደሆነ አልተጻፈም።

 

ወደ ምዕራብ በሄድን ቁጥር ባዳ እንሆናለን - እንደአዝማች

ከኢትዮጵያ በራቅኩ ቁጥርና ከኢትዮጵያ ተለይቼ በቆየሁ ቁጥር ስለኢትዮጵያ መናገር እየፈራሁ መጣሁ። የምሳሳት መሰለኝ። የራሴ ኢትዮጵያዊ ትዝታና መረጃ አለኝ። ወይም ነበረኝ። የራሴ ተሞክሮና መረጃ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በዚህ ሰባት ዓመት ውስጥ ግን ስለ ኢትዮጵያ የምሰማቸው በሁለት ጽንፍ የሚገኙ መረጃዎች ግራ አጋቡኝ። አንድኛው፣ ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት አ.አ.ዩ. ይሄን ስርዓት አምርሮ ሲጠላ ሲፋለም የነበረ አሁን ትምህርቱን ጀርመን አገር እየተከታተተለ የሚገኝ ወዳጄ፣ በዚህ ባለፉት ዓመታት ውስጥ ምን እንዳስተዋለ አላውቅም ስለስርዓቱ ያለው አመለካከት ተለውጦ “ይሄ ስርዓት ከፍተኛ እድገትና ግንባታ እያስመዘገበ ነውና መረዳት አለበት፤ ብዙ ተስፋ ሰጪ ነገሮችም አሉ። ይልቅስ ተቃዋሚዎች ቅንነት የሚጎድላቸው፣ ፍቅርን የማይሰብኩ፣ አገር ሊመሩ የማይገባቸው ናቸው” ይለኛል። እኔም “የግንባታውንና የእድገቱን ነገር እንዳፍህ ያርግልን” ብቻ ነው ያልኩት።

 

በሌላኛው ጽንፍ የሚገኘው እኔ ራሴ እንደምገኝበት የማስበው ጎራ ደግሞ፣ የስርዓቱን እብሪት ማሸቀብ፣ እስራትና እንግልት መብዛት፣ የኑሮ ውድነትና የአፈናውን መበራከት ነው ሹክ የሚለኝ። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሕግ ት/ቤት የተማርነው “የነገሮችን አንድ ጎን ብቻ አትመልከት፤ የተቃራኒውንም እንጂ” የሚለው ብሂል ተከትሎኝ መጣና በራሴ ጸረ-ኢህአዴግ አቋም ብቻ መታወሩን ባለመሻት ዘወትር በተቻለ መጠን ስለኢህአዴግ ያለኝን መረጃ ከራሱ ከኢህአዴግ ምንጮች በመቅዳት ጭምር ራሴን በመረጃ ለማበልጸግ እጥራለሁ። በዚህ ረገድ የዋልታና የኢዜአም ደንበኛ ነኝ። በተቃዋሚዎች አቅጣጫና በራሴ ምንጮች ስለሚነገረው ችግር ሰምቼ ሰምቼ፣ ምርር ሲለኝ፤ ወደ ዋልታ እሄድና ትግራይ ውስጥ የሚገነቡትን ግድቦች፣ የሚታነጹትን ተቋማት፣ የሚሠሩትን እርከኖች፣ … እቆጥርና እጽናናለሁ። ከሁሉም አቅጣጫ መረጃ ስለማግኘት አስፈላጊነትና ስለራሴ በመረጃ ረሃብ የተነሳ ስለኢትዮጵያ ለማውራት ያጋጠመኝን እክል ነው የማወራው፤ እንጂ ስለትግራይ መልማት ወይም ስለሌሎች መደህየት አይደለም። በዚህ የተነሳ አብዛኛውን ግዜ ከኔ እዚያው ተወልጄ እዚያው ካደግኩት ይልቅ፣ አምባሳደር ያማሞቶ ይሻል ይሆን እንዴ ብዬ የአሜሪካንን የመረጃ ጣቢያዎች አፈትሻለሁ።

 

የዘፈንና የግጥም እንጂ የጽሁፍ አዝማች የለውም። የጽሁፍ ሕግነት ደግነቱ እንደእግዚአብሔር ሕግ ከወረቀት አያልፍም። ተከታትሎ የሚያስፈጽም ፖሊስ የለውም። ያው አንባቢው ነው ጠባቂው። ከጣመው ያነበዋል፤ ካልጣመውም ይተወዋል። ስለዚህ ለጽሁፌም አዝማች ላበጅ ተነሳሁ። እነሆ አዝማች። እዚህ ውጭ አገር ቁጭ ብዬ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን የተመለከተ ነገር ለመጻፍ ስነሳ፣ “ይሄ እንዲህ ቢሆን፣ ይህን እንዲህ ብታደርጉት፣ ህዝቡ አደባባይ ወጥቶ ቢቃወም፣ ነፃነትን ለማግኘት መስዋዕትነት ያስፈልጋል፣ ሆ ብላችሁ ተነስታችሁ ...” የሚሉ የሚመስሉ ጽሁፎችን ለመፃፍ ስነሳ ወይም እንደዚያ የሚሉ ጽሁፎች እዚህ ምዕራቡ ዓለም በምንገኝ ሰዎች ሲጻፍ ሳይ፤ ስቅቅ ይለኛል። ተሻለና የተረጋጋ አገር የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ ካልተጠየቁና ካልተጋበዙ በስተቀር፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አደገኛ በሆነ ሕይወት ውስጥ የሚኖሩትን ሰዎች ወደ አደጋና መስዋዕትነት የሚገፋፋ ጽሁፍ ወይም ምክር መለገስ አለባቸው ብዬ አላምንም። ያንን ስሜት ወይም መልዕክት ያዘለ ጽሁፍ ስጽፍ አፍራለሁ። ስለዚህ አፌንና እጄን መሰብሰብ ባልችልም እንኩዋን፤ ቢያንስ በየጽሁፎቼ ጣልቃ ይሄንን አዝማች ማስገባት መረጥኩ።

 

አካባቢያችሁንና ነባራዊውን ሁኔታ እያያችሁ የምታደርጉትን እናንተ ታውቃላችሁ። ይሄንን ከኢትዮጵያ ብዙ ሺህ ኪ/ሜ በራቀና የኢህአዴግ ዱላ ከማይደርስበት ቦታ ሆኜ የምጽፍላችሁን ማስታወሻ እንደማስታወሻ፣ ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ወዲያ ስለነበረው ወዲህም ስላለው ጥቂት ኢትዮጵያውያን ሕይወትና ሩጫ ማጣቀሻ ብቻ እንጂ፤ ከዚያ ያለፈ የቅስቀሳና ገፋፊነት ፋይዳ የለውም። የሸሸና የፈረጠጠ እሱ፣ ያልሸሹትንና ያልፈረጠጡትን ከዚያው ከመከራቸው ምድጃ ላይ የተጣዱትን ስለ ድፍረትና መጋፈጥ፣ ስለትግልና ተጋድሎ ሊሰብክ አይችልም። ሰው ያልኖረውን ወይም የማይኖረውን ወይም ባጠገቡም የማያልፍበትን ሕይወት ሲሰብክ አያምርበትም። “ይሄ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ሁሉ የሚሰብከው ሰባኪና ወንጌላዊ የኖረውን ነው እንዴ የሚሰብከን?” እንዳትሉኝ። እሱን እናንተ ታውቁታላችሁ። ይልቅስ ስብከቴና አዝማቼ አንድ ነገር አስታወሱኝ። ባልኖርበትም ወይም የሕይወቴ መመሪያ ባላደርገውም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚማርኩኝ፤ የማልረሳቸው ጥቅሶች አሉ። ይቅርታ ይሄኛው ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይደለም፤ ከዚያው አካባቢ እንጂ። የኢየሱስ ክርስቶስን ስቅለት የሚያሳይ ስዕል ላይ ነው ያየሁት። “ክርስቶስን ‘የሰውን ልጅ ምን ያህል ትወደዋለህ?’ ብለው ሲጠይቁት፤ ‘ይሄን ያህል’ አለና እጆቹን ዘርግቶ ሞተ”። መጠኑን በአጋኖ፣ በቁጥር፣ በመስፈሪያ ሳይሆን በሞቱ ገለጸው። ክርስቲያን ነን እስላም፣ ሂንዱ ነን ኤቴይስት፣ … እኔ ምን አገባኝ። ብቻ የትኛውም እምነት ውስጥ ፍቅርና እምነት፣ ተቆርቋሪነትና ስስት አለ። ለሚስት ይሁን ለቤተሰብ፣ ለልጅ ይሁን ለጎረቤት፣ ለጣዖት ይሁን ለምናምን፣ … ብቻ ፍቅር ወይም ሸክም አለ። ስለዚህ ያልዋልኩበትን ከምሰብካችሁ ይልቅ፣ በዚያ በልጅነቴ ለምመኘው፣ ኢትዮጵያን እንዳገሮች አገራ ሆና የማየት፣ ሕልም እስከመጨረሻው ብሰለፍና ዛሬ ዴሞክራሲን በኢትዮጵያ ሁሉ እንዲስፋፋ ካደረጉት ጎን ሆኜ “ጎበዝ እንዲህ እናድርግ፣ በዚህ እንግባ፣ በዚህ መንገድ እንጓዝ፣ …” ብል፤ ምንኛ በታደልኩ። በቦረና ሰነጣጥቀን፣ በኬንያ አቆራርጠን፣ ወደካናዳ ካቀጣጠነው በኋላ፤ “ጎበዝ ዴሞክራሲ እንዲህ ነው፣ ይሄን ደግሞ እንዲህ አድርጉት፣ ቅንጅት እንዲህ መሆን አለበት፣ ይሄንን ማድረግ አለበት፣ …” የሚል አስተያየት መስጠት ይዘገንነኛል። ቢያመልጠኝና ጽሁፌ ውስጥ ይሄንን ብታስተውሉ ግን፤ አዝማቼን አስገቡልኝ። በሞያሌ ካገር የራቀ ሰው እንደዚያ ያደርገዋል። ላገሩ ባዳ።

 

ደግሞ እንደካናዳ፣ የሰው ልጅ ለማዳው

እዚህ አገር ከመጣሁ ሦስት ዓመት ሞላኝ። ባላመለክትም ካናዳዊ ሆንኩኝ ማለት ነው። ሰው ካናዳዊ ለመሆን አገሪቱ ተምና ያወጣችው የጊዜ መጠን ሦስት ዓመት ነው። ፈረንጅ ብልህ ነው። በ3 ዓመት ውስጥ ስጋው የሌላ ቢሆንም ነፍሱ የኛ ነች ነው ነገሩ። ብትገለብጡትም ለውጥ የለውም። ማለቴ ስጋው የካናዳ ነፍሱ የኢትዮጵያ ቢሆንም፤ ነፍስ ልክ አየር ላይ የመንሳፈፍ ያህል ነው። እዚህ አገር ቁምነገሩ ሲሆን ሲሆን ጭንቅላቱን፣ ያለበለዚያም ጉልበቱን ነው። ሰው ከአገሩ ወጥቶ ሰባት ዓመት፣ አስራ አራት ዓመት፣ ሃያ አንድ ዓመት፣ ሰላሳ አንድ ዓመት መኖር ከቻለ፤ በቃ ምን ቀረ?። ይሄንን በዚህ በምዕራብ ዓለም በቆየን ቁጥር ለአገራችን የሚኖረን ፋይዳና የልጅነት ሕልማችንን ይዞ የመቆየት ዕድላችንን መመንመን ሃሳብ በናቴ መስዬ ባስረዳ ያቀልልኛል።

 

እነሆ ምሳሌ። ዕድሜዋ እየገፋ የመጣው እናቴ፣ ለዓመታት ሳንተያይ አንድ ቀን ልትሞት ትችላለች። ለኔ ልክ እንደብዙዎቻችሁ እናቴ የአገሬ ግማሽ ነች። አጼ ምኒልክስ ይሄንን አይደለም ያሉት። አገርህ አንድም ሚስትህ ናት፣ አንድም እናትህ። ለጊዜው አላገባሁም። ወይም ፈትቻለሁ። ያው አገር መሬቱ ብቻ ሳይሆን ህዝቡም ጭምር ነውና ቤተሰብ፣ ጓደኞች፣ ፍቅረኞች፣ ጨቋኞችም ጭምር፤ የአገሬን ግማሽ ካጣሁ፤ የአገሬን ሙሉ ይዤ ያልሠራሁትን ነገር ልሠራ አልችልም። ገና የመጀመሪያ ድግሪዬን ከመጨረሴ የተቆለለብኝ የገንዘብ ዕዳ የትየለሌ ነው። ይሄ አገር በመጀመሪያ ድግሪ ምንም የሚሠራበት አገር አይደለምና ሌላ ድግሪ ፍለጋ መኳተን አይቀርም። ድግሪ ፍለጋ ስድስት - ሰባት ዓመት፣ ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ፍለጋ ሌለ አምስት - ስድስት ዓመት። አገርም ሕይወትም፣ እኔንና እኛን ጥበቃ ለአምስት ለስድስት ዓመት መኖር አታቆምም። ወይንም እናቴ እኔ በድልም ይሁን በሽንፈት እስክመለስ ሞቷን አታራዝምም። ድግሪ ፍለጋ ደግሞ አልጋ ባልጋ አይደለም። ይሄን በሰዓት የሚከፈል ደመወዝ ፍለጋ ማሳደድ ይመጣል። ስለዚህ ፍራቻዬ በዚህም በዚያም ምክንያት እንደዋዛ ካገር ወጥቼ ያለብዙ ጉልህ መደናቀፍ አምስት ስድስት ዓመት መኖር ከቻልኩ፣ በዚህ ላንድም ቀን ቢሆን በተሻለ መልኩ ለመኖር በሚደረገው ጥረት ውስጥ አዲሱን ሕይወት መልመድ፣ የደሮውንም ረስቶ መኖር መለማመድ ይመጣል። ምክንያቱም የመጀመሪያው ለማዳ እንሰሳ ሰው ነውና።

 

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መፍትሄ የተቀበረው እዚያው ኢትዮጵያ ነው፤ እዚህ ውጭ አገር የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ከገንዘብ ያለፈ ልናበረክት የምንችለው አስተዋጽኦ የለም ብዬ አንዲት ጽሁፍ ጫጭሬ ነበር። እዚህ ያለን ሰዎች በዚህ በስደት አገር የቤት ሥራ የተጠመድንና ግማሹ ድግሪ ማሳደድ ላይ፣ ከፊሉም ልጅ ማሳደግ ውስጥ፣ የተቀረውም ቢዝነስ ማሯሯጥ ላይ የተወጠረ ነው። ይሄ አገር ልጅ “ውጣና ተጫወት፣ ሜዳ ላይ ተራግጠህ ና” የሚባልበት አገር አይደለም። ወደዚህ ወደ ’ነፃነት’ አገር መምጣት ወደ ፋታ የማይሰጥ የሕይወት እስር ቤት የመግባት ያህል ነው ብዬ ተናግሬያለሁ። ልቤ አልተቀበለውም አንድ ነገር ነው። ባይቀበለውም እየኖርኩ ነው ሌላ ነገር ነው። ስለዚህ ሰው አልተቀበልኩትም አልተቀበልኩትም እያለ ሕይወቱን ቢገፋ፣ የሚወዳቸውንም ቢያጣ፣ ዓመታት እየቆጠረ፣ በናፍቆት እየተንጠራወዘ፤ ነገር ግን ከወገኖቹ ተለያይቶ አምስት ዓመት - አስር ዓመት - ሃያ ዓመት … መኖር ከቻለ፤ እንደማቱሳላ ዕድሜው የበዛና በሺህ የሚቆጠር ቢሆን፤ አገሩን ትቶ ሌላ አገር ሰርቶ መኖር ይችላል ማለት ነው። እያንዳንዱ የካናዳ ቀን ከኢትዮጵያና ከወገኖቼ እያንዳንዱን ቀን የሚያርቀኝ መሰለኝ። ያን ያህል ተስፋ መቁረጥ እየተሰማኝ ነው። ልሰለጥን ይሆን? እንደመጀመሪያው ስልጡን እንሰሳ፤ እንደሰው።

 

ኢትዮጵያ በድሀ ትከሻ ዓለምን አሳየችኝ። እነሆ ካናዳ እኔንና እኛን ከኢትዮጵያ ማረከች። ቀማቻት። ፍራቻዬ እንዲህ ነው። ይሄ ኢህአዴግ የሚሉት ሰይጣን ሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ፣ ይሄ ከአገር ተለያይቶ መኖር ከቀጸለና ማንም የሚኖርበትን አካባቢ ተለማምዶ በመኖር ሕይወቱን ለማሳመን ይሮጣልና፣ ሕይወት ደግሞ የምንለው ይሄንን ሁሉ ቆጥረን ነውና፤ እንዲህ እንዲህ እያልን እዚሁ ከቀረን፤ አገር ምን ሊቀራት ነው? የወለደንን ህዝብ፣ ያሳደገንን አገር፣ ዓለምን ያሳየንን ወገን ጀርባችንን ሰጥተነው፤ ሁላችንም እንደዋዛ በየራሳችን የኑሮ ሩጫ ውስጥ ስንቀበር፤ እንኩዋንስ አገር ዕቃም እንዳልረሳ ሰው ሁሉም ሠላም ብለን መኖር ስንቀጽል፤ ያቺ ምስኪን ኢትዮጵያ ከልጆቿ ጋር በመከራ ትቀቀላለች። አገርን፣ ህዝብን፣ ወገንን ረስቶ መኖር ይለመዳል። ያቺን የኖርንባትን ዓመታት ያህል ለምደናል። መኖር ተስፋ ይቀጥላል። መኖር ተስፋም ያስቆርጣል።

 

ስልጣኔና ነፃነት - የተስፋ መቁረጥ ውጤቶች

ዕድገትና ስልጣኔ ከተስፋ መቁረጥ ውስጥ ነው የሚወለዱት ልበል ይሆን? ሰው ተስፋ ሲቆርጥ ይጨክናል። ማለቴ አንዱን መስመር ለመከተል ይጨክናል። ለምሳሌ እነ አቶ መለስ ተስፋ ባይቆርጡ ኖሮ፣ ጫካ አይገቡም ነበር። ጫካ ባይገቡ ኖሮ ደግሞ፣ አያሸንፉም ነበር። ሰው ተስፋ ሲቆርጥ ያለ የሌለውን ሕይወቱንም ጭምር ያባክናል። ይሰዋል። ልክ ያኔ እኔ ኢትዮጵያ ሆኜ ወደዚህ ወደውጭ መሲኅአችንን ፍለጋ አንጋጥጬ እመለከት እንደነበረው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ወደውጭ ባለነው ኢትዮጵያውያን እንዳይተማመን ተስፋ ላስቆርጥ ነው ልጽፍ የተነሳሁት። እዚህ እውጭ የተሰበሰብን ሰዎች፣ እነዚያን የልጅነት ድንቅ ራዕያቸውን አጥተው፣ የራሳቸውን ኑሮ ለማሸነፍ ከሚሯሯጡ ወገኖች ነው የምንመደበው። በቤተሰብ ወይም በግለሰብ ደረጃ አውሮፓና አሜሪካ፣ አውስትራሊያና ኤሽያ ባሉ ዘመዶቹ የሚኮራ መብቱ ነው። በቡድን ደረጃ ግን መቼም ቢሆን ተሟልቶለት አንድ ላይ ላንድ ቀንም የማይሰለፍ የሕይወት ባሪያ ነው የተሰበሰበው። ማለቴ የተሰበሰብነው።

 

ስላለንበት አገራዊና ዓለማቀፋዊ ተስፋ አስቆራጭ ዘመን ልጽፍላችሁ ነው የተነሳሁት። ተስፋ ላስቆርጣችሁ፣ ላስጨክናችሁ። ምክንያቱም ስልጣኔና ነፃነት የሚወለዱት ከተስፋ መቁረጥ ስለሆነ ነው። ቁርጥን ከማወቅ። ባለውና በሚያየው ተስፋ ያልቆረጠ አይጨክንም። ይሄንን ጽሁፍ ስጽፍላችሁ ጥበቃ ሥራ ላይ ሆኜ ነው። ለአገራችን ዘብ እንቆማለን ብለን የወጣን ልጆች፣ እዚህ ሰው ህንጻ ላይ ዘብ ቆመናል። የትናንቱና የዛሬውን ሕይወት ልዩነት የትየለሌነት ለማጉላት እንጂ ሌላ ምንም ለማለት አይደለም።

 

ኢትዮጵያውያን ወደውጭ እንደገፍ መሰደድ ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ያሉትን ጊዜያት ተመልከቱ። ብዙ ኢትዮጵያን ነፃ እናወጣለን ብለው የተነሱ ጀግኖች፣ ሱዳንንና ኬንያን ያለፉ ዕለት፤ ለኑሮ ባሪያ ተሆኑ ከሚኖሩበትና ራሳችን ነጻ አውጪ ከምንፈልግበት ዓለም የገቡ ዕለት ነገር ተበላሸ። ጨክነው እዚያው የቀሩትና ጫካ የገቡት ናቸው ያሸነፉት። ከወገኖቼና ከቤተሰቦቼ ተለያይቼ ከዚህ ዓለም ላልፍ እንደምችል ባሰብኩ ቁጥር ተስፋ እቆርጣለሁ። በአሜሪካ ሰፋፊ አውራጎዳናዎች ላይ የሚርመሰመሱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ መኪኖችን ባሰብኩ ቁጥር የሰው ልጅ የመጥፊያውን ነዳጅ መስጫ የሚረግጥ ያህል ይሰማኛል። ዓባይ ከግብጽ እንጂ ከኢትዮጵያ እንደሚነሳ የማያውቁ ሰዎች ባየሁ ቁጥር ለካንስ መበደላችንን፣ መጨቆናችንን፣ መኖራችንንም ከማያውቁ ሰዎች ጋር ነው የምንኖረው የሚለው ኀዘን ይሰማኛል።

 

የደናችንን መመናመን ሳስበው ተስፋ ያስቆረጥኛል። የኛ ጉዳይ (የኢትዮጵያ) በኛ እጅ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም እጅ መሆኑን ሳስብ ተስፋ ያስቆርጠኛል። የችግራችንን ፈርጀ ብዙነት ባሰብኩት ቁጥርና አሁንም እንኩዋን ያንን ችግር ለመቀነስ ሁላችንንም የሚያስተባብር ሳይሆን፤ ሁላችንንም በተቻለ መጠን አራርቆ የሚይዝ መንግሥት እንዳለን ሳስብ ተስፋ እቆርጣለሁ። ከዚያ በቡሃ ላይ ቆረቆር እንዲሉ፣ መወለድ አይቆምምና የቁጥራችንን ማሻቀብ በአገር ደረጃ ሳይሆን በቤተሰብም ደረጃ የምንወልደው ችግር ይታሰበኛልና ተስፋ እቆርጣለሁ። ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮችን መቁጠር ተስፋዬን ያለመልመዋል።

 

ወደምዕራብ ስንሄድ ደግሞ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ይበዛል። ራሳቸው ምዕራባውያን ያለባቸው የችግር መዓት፣ የስልጣኔ ራሱ ጣጣ አያሌ መሆኑንና ከአገር ቤት የምናየው ብቻ ሳይሆን የማናየውም እልፍ አአላፍ ችግር አዝለን እንደምንጓዝ ሳስበው ተስፋ እቆርጣለሁ። ተስፋ መቁረጥን ደግሞ እዝናናበታለሁ። ማለቴ እንከባከበዋለሁ። ምክንያቱም ስልጣኔና ትግል የሚወለደው ከተስፋ መቁረጥ ውስጥ ናውና። የሁለት ሺህ ዓመተ ምህረቱን የአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት ተወዳዳሪ አል ጎርን አትመለከቱም። በዓለም ተስፋ ስለቆረጠ ነው ብድግ ብሎ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ የሚያደርገውና ጎበዝ ልንጠፋ ነው ብሎ የሚያሰብከው። ከኬንያ እስከ ዩጋንዳ፣ ከኬንያም እስከ ካናዳ ያለፍኩበት ሕይወት የሚናገረው ይሄንን ነው።

 

ከኬንያ እስከዩጋንዳ፣ ከኬንያ እስከካናዳ

ብቻ ወደ ምዕራብ በሄድን ቁጥር ስላገራችን ያለን ተጨባጭ ራዕይ እየቀጨጨ፣ እየኮሰመነ ይሄዳል። ራዕይ ስል አገራችን እንድትደርስ የምንፈልግበት ቦታ ደርሳ ማየት መመኘት ማለቴ ሳይሆን፤ አገራችን እዚያ እንድትደርስ መታገል ማለቴ ነው። እንጂ መመኘትማ አናቆምም። ያም ሆነ ይህ አካባቢዬ ስላሸነፈኝ የልጅነት ራዕዬ ከዳኝ። ያኔ ልጅ ሆነን ተፈጥሮን በቁጥጥራችን ስለማዋል የሚነገረው መፈክር ትዝ አለኝ። ሰው ተፈጥሮን በተቆጣጠረ ቁጥር እሱም በተፈጥሮ ቁጥጥር ስር ይውላል። ነዳጁን ቀዳነው፣ እንሰሳውን በላነው፣ ደኑንም ጨፈጨፍነው። በመጨረሻ ግን፤ ይሄ እንደጉድ እንደማያልቅ የምንመነዝረው የአካባቢያችን ሀብት እየተመናመነ እየተመናመነ እየተቆጣጠረን መጣ። ዓለም ጠበበችን። ነገሩን ትንሽ ላቅለው። ሰው አካባቢውን ያሸንፍ ይሆናል። ሰው ባካባቢውም ይሸነፋል። ባካባቢዬ ተሸነፍኩኝ። ለዚያውም በዝረራ።

 

ማንም ኢትዮጵያዊ ወደ ምዕራብ ሲመጣ በሕይወት ሩጫ በዝረራ ይሸነፋል። የዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢ ወደ ካናዳ እንደመጣሁ ሰሞን በጣም አሁንም ድረስ ትንሽ ትንሽ ደስተኛ አልነበርኩም። እዚህ መኖር መቻሌን አምኜ መቀበል አልፈለግኩም። ከአሜሪካን ዋሽንግተን ክልል አልፎ አልፎ እየመጣ የሚጎበኘን ወጣት ኢትዮጵያዊ ጠበቃ፣ እዚህ አገር ደስተኛ አለመሆኔና ማማረሬ አይዋጥለትም ነበርና እንከራከራለን። “ኖ! እዚህ አገር እኮ ማንም እንዳሻው አያስቆምህም፣ ያለሕግ አትታሰርም። ተምረህና ሠርተህ ትኖራለህ። መንገዶቹ፣ ህንጻዎቹ፣ እንደው ራስህን ለመሸወድ እንደሆነ እንጂ፤ ይሄንን ዓለም ትወደዋለህ ... እንዴት አትወደውም? ብዙ ሺዎች ካንተ በፊት መጥተው ወደውት ሰምጠው ቀርተዋል። ይኖራሉ!” ከኚያ ወደ ኬንያ ከሸኙኝ የኢመማ ሰው ጋር የተመካከረ መሰለኝ። እሳቸውም እንደዚሁ ነው ያሉኝ። በመሰደድና በስደት ትግል አያምኑም። ሺዎች ተሰደው ምንም ፈይደው ስለላዩ፤ ለትግል ነው የምሰደደው የሚል ነገር አይዋጥላቸውም።

 

መልስ ለመመለስ ተውተረተርኩ። ትዝ እንደሚለኝ ከሆነ “እንዴት መሰለህ … የሰው ልጅ በሕይወቱ ውስጥ የሚኖርለት፣ ቢያደርገውና ቢሳካለት ደስ የሚለው ሕልም አለው። ለኔ በዚህ ድሎት ውስጥ መኖር ሠላም አይሰጠኝም። ስለዚህ እዚህ አገር መኖር ያ በልጅነት የምመኘውን ደስታ አይሰጠኝም። ያ የተሰደድኩለት ዓላማ ...” ብዬ መለስኩለት። ያለፉትን ሦስት ዓመታት ሕይወቴን ሳየው፣ የመጪውን ሦስት ዓመት ስተነብየው በቀጥታ ለራሴ ብቻ እድገት ከመኳተን ውጪ ለሀገሬና ለህዝቤ ልሠራ የምችለው ፋይዳ ያለው ነገር አልታይህ አለኝ። ያ የልጅነቴ ሕልም የት ገባ? ምን በላው? ይሄ የምዕራቡ ዓለም እንኩዋንስ ሕልሜን እኔንም ሳይበላኝ አይተወኝም። ነገሩ እንዲህ ነው።

 

ወደ ኬንያ በሸሸን ማግስት በነበሩ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ስደቴን ወደምዕራብ፣ ወደካናዳ እስካሰፋ ድረስ ውስጤን የሚያኝከውና ግራ የሚያጋባኝ እስከ ምርጫ 97 ድረስ ያልተመለሰልኝ አንድ ጥያቄ ነበር። ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ ግዜ ጀምሮ የመጀመሪያውን ሁለት ሦስት ዓመታት ግድየለም ብለን እንደችሮታ ግዜ ብንወስድለት እንኩዋን፣ ከዚያ በኋላ የነበሩትን ዓመታት ስናያቸው በኢትዮጵያ ውስጥ ስለነበረውና ስላለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጭቆና፣ አፈናና ፍዳ ምንም የምንከራከር አይመስለኝም። ነገር ግን ሰዉ ታሰረ፣ በገፍ ተገደለ፣ አገር ተገነጠለ፣ ሰው ከነቤተሰቡ ከሥራ ተባረረ፣ ብሔርን ከብሔር አጋጨ፣ … እያልን እየተናገርን አስር - አስራ አምስት ዓመት ይሄ ህዝብ ይሄን ሁሉ በደል ተቋቁሞ እንዴት መኖር ቻለ? ይሄ ህዝብ እውነት ተበድሏል ወይንስ እኛ ነን ተበድለሀል የምንለው? (ልክ ኢህአዴግ ተበድለህ ነበር ነፃ አወጣሁህ እንደሚለው ማለት ነው) ይሄ ህዝብስ ከተበደለ ልክ ደርግና ከዚያ በፊት የነበሩት ስርዓቶች ይበድሉት እንደነበረው ነው የተበደለው ወይንስ የኢህአዴግ የተለየ ነው? ታዲያ ይሄን የምናወራውን ሁሉ በደል ተሸክሞ እንዴት መኖር ተቻለው? የሚሉ ጥያቄዎች ይፈታተኑኝ ነበር።

 

መቼም ያለፈ ግዜ ነው ጥያቄየ የመነጨው ከንዴትና ከተስፋ መቁረጥም ጭምር ነበር። በሰዓቱ አብረውን ተሰደው ነበሩት ተማሪዎች የስደት ሕይወት ሲያስደነግጣቸውና ያልጠበቁት ነገር ሲያጋጥማቸው በኛ በወቅቱ አመራር ላይ በነበርነው እንደተበሳጩብን ሁሉ፣ እኔም በወቅቱ ኬንያ ያላለፍኩበትን የማላውቀውን ፈተና ስትደቅንብኝና ግራ ስጋባ፣ እውነት ይሄ ህዝብ እኛ በምንለው ልክ ተበድሎ ከሆነ፣ አደባባይ ወጥቶ ይሄንን ስርዓት የማይፋለምበት ምክንያት ምንድነው የሚሉ ጥያቄዎች ተጋረጡብኝ። በደልን የሚተረጉመው ማነው? ተበዳዩ ራሱ ወይንስ ሌላ ሦስተኛ ሰው? ወይስ ይሄ ህዝብ እኛ የምንለውን ያህል አልተበደለም? ... ምርጫ 97 መልስ ሰጠኝ። ይሄ ህዝብ በመበደሉ ድምፁን ለፈቀደው ሰጠ። ከዚያ በኋላ የሆነውን ታውቁታላችሁ። ሌላም ጥያቄ ተወልዶብኝ ነበር። ስለኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎችና ልክ በሌላው ዓለም እንደምናየው ለምን ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በብዛትና በእልህ እንደማይገቡ። እነሱም መልስ ሰጡኝ። እነሆ ሌላ ጥያቄ ተወለደብኝ። ሌላውን ጥያቄ ይዤ እመለሳለሁ።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!