ያሬድ ክንፈ ከስዊድን (ሀገር ቤት ላለ ወዳጅ የተጣፈ) ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

Teddi on stage in Stockholmጌትዬ! ከነመላው ቤተሰብህ መልካም የገና በዓል ይሆንልህ ዘንድ ከልቤ እመኛለሁ!

 

እዚህ ስዊድን ውስጥ የኢትዮጵያን ገና ምክንያት በማድረግ ቅዳሜ ታህሳስ 19 ቀን 2000 ዓ.ም. (ዲሴምበር 29 ቀን 2007 ዓ.ም.) ፌሽታ ተደርጎ ነበር። ዋና ከተማዋ ስቶክሆልም ውስጥ ሊልሆልመን እተባለው ክፍለከተማ በኢድሮትስሐለን አዳራሽ ውስጥ ከምሽቱ አራት ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ (ለእሁድ አጥቢያ) 10 ሰዓት ድረስ ነበር ዝግጅቱ። መድረኩን ተቆጣጥሮት የነበረው ተወዳጁ ቴዲ አፍሮ (ቴድሮስ ካሣሁን) ነበር።

 

ጌትዬ! እኔና ጓደኞቼ ከስፍራው ስንደርስ ከምሽቱ 5 ሰዓት አካባቢ ነበር። ያረፈድነው የሐበሻ ፌሽት ሲኖር ሁሌም ቢያንስ 2 ሰዓት ዘግይቶ እንደሚጀመር ሳይታለም የተፈታ በመሆኑ ነበር። ዘፋኝ ስዊድን በመጣ ቁጥር ባልገባም ባለፉት አምስት ዓመታት ከገባኋቸው ፌሽቶች ጋር ሲወዳደር ይኸኛው የተለየ ነበር። ከስፍራው ስንደርስ ወደ አዳራሹ ለመግባት የነበረውን ሰልፍ ልነግርህ አልችልም። ቢያንስ ከ200 ሰው በላይ ነበር። በአንዳንድ ፌሽቶች ላይ 200 ሰው ብቻ ሊገኝ ይችላል።

 

ጌትዬ! እዚህ ሀገር ዲስኮ ቤት ስትወጣ ብዙ ጊዜ ሰልፍ አለ። በተለይ ሞቅ ደመቅ ያለበት ቦታ። ሁሌም እንዳመጣጥህ የመጨረሻው መስመር ላይ ስርዓትህን ይዘህ ትሰለፋለህ። አልያ የስነስርዓት አስከባሪው ልትሸውድና ልታጨናብር ከሞከርክ አሽቀንጥሮ ከሰልፉ ያስወጣሃል። ከእሱ ጋር ግብግብ ከፈጠርህ ጓደኞቹን ይጠራል፤ አሁንም አሻፈረኝ ካልክ ፖሊስ ይጠራና አንከብክበው ይወስዱሃል።

 

ጌትዬ! የሐበሻ ፌስት ላይ የተሰለፍኩበትን ጊዜ አላስታውስም። በዚህኛው ዝግጅት ወደ ፌሽቱ የመጡት ኢትዮጵያውያን ብቻ አልነበሩም። ኤርትራውያን ጭምር እንጂ። ኤርትራውያን ቴዲ አፍሮን ይወዱታልና ‘ባክህ? … ቴዲ “የአዲስ አበባ ልጅ” ሲል ከሚሰማው ጩኸት የበለጠ ይጮህ የነበረው “የአስመራ ልጅ” ሲል ነበር። ቴዲም ይኸው ገብቶት ነው መሰል፤ ወዲያው ሚዛኑን ለመጠበቅ “የኢትዮጵያ ልጅ” ይላል፤ ታዲያ ያኔ ታዳሚው ለአስመራው ከተጮኸው ባላነሰ መልኩ ይጮህለት ነበር።

 

እመግቢያ በር ላይ እጅግ በርካታ ሰዎች ጥቅጥቅ ብለው ነበር። ሰልፍ አልያዙም። እንዳው ምን አለፋህ ከአዲስ መጪዎቹ ግማሹ ካለምንም እፍረት ቀጥ ብለው ወደ መግቢያው ይሄዳሉ። እንግዲህ ይሄንን “ስርዓት አልበኝነት - አንድ” በልልኝ።

 

በሩ ላይ የነበሩት ስነስርዓት አስጠባቂዎች ስላቃታቸው ሌላ ኃይል አዘዙና ወደ አስር የሚጠጉ የሠለጠኑ ጠባቂዎች መጡ። እነሱም ስነስርዓት ሊያሲዙንና በስርዓት ሊያስገቡን ሞከሩ። ሆሆይ! … እኛ ማን ይችለናል ሐበሾችም አይደለን?! … አቃትናቸው። እነኛ ሁሉ ፍልጥ ፍልጥ የሚያካክሉ ስዊድናውያን ስነስርዓት አስከባሪዎች እኛ ሐበሾችን (ኤርትራውያንንም ይጨምራል) ሊቆጣጠሩን አልቻሉም።

 

ጌትዬ! በዚህ መሃል ጠባቂዎቹ ጎትተው ከሰልፉ ሲያወጡት ወይንም በገዛ ዘሮቹ ሐፍረት ተሰምቶትና ውርደትን ጠልቶ ከሰልፉና ከግርግሩ መሃል ሹልክ ብሎ ወጥቶ የሄደው ሐበሻ በርካታ ነው። … በመጨረሻም ወደ አስር አካባቢ የሚጠጉ ፖሊሶች መጥተው አንዴ ፈሰሱ። የሚገርመው ግን እኛ ሐበሾች እንኳን ለማይታየው፣ ለማይዳሰሰው፣ ለማይጨበጠውና በሃሳብ ደረጃ ለተቀመጠው ለስርዓትና ለስነስርዓት ቀርቶ መሣሪያ ለታጠቁ ፖሊሶችም ላለመገዛት የተማማልን መሆናችንን ልብ ያልኩበት የመጀመሪያ ጊዜ ቢኖር የቴዲ ፌሽት ነው ብል አላጋነንኩም። ይኸኛውን ደግሞ “ስርዓት አልበኝነት - ሁለት” አትልልኝም።

 

መርሳት የሌለብህ ነገር ቢኖር ጌታው! ወደ ፌሽቱ የሚዘልቀው ህዝብ ቁጥር እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልመጣም። ፖሊሶቹ በመጡ ጊዜ ከውጭ የነበርነው ሰዎች ቁጥር ካለማጋነን 350 ደርሷል። ብቻ በዚህም በዚያም ተብሎ ከ22 በላይ የሚሆኑ የስነስርዓት አስከባሪዎችና ፖሊሶች ሆነው ማስገባት ሲጀምሩ እኔና ጓደኞቼ ቶሎ የመግባት ዕድል አጋጠመንና ከምሽቱ ሰባት ሰዓት አካባቢ ገባን። ሁለት ሰዓት ሙሉ ዝናብ እየዘነበብንና እጅግ ቢያንስ ወደ ዜሮ ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሚሆን ቅዝቃዜ ላይ ነበርን። በኋላ ሁሉንም ሰው አስገብተው እስኪጨርሱ ድረስ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት አልፎ ነበር።

 

ጌታው! አሁን ደግሞ ሁሌም የሐበሻ ፌሽቶች ላይ ከማይጠፉትና በዚህኛውም ላይ ከተከሰቱት ችግሮች አንድ ሁለቱን ልጥቀስልህ። ችግር አንድ፦ ብዙ ጊዜ መጠጥ (አልኮልና ለስላሳ) መሸጡ አይቀርም። የፈለገው አይነት ጥማት ቢጠማህ “አለቀ” መባሉ የማይቀር ነገር ነው። ከዚያ የከፋው ደግሞ ተሰልፈህ ትውላታለህ እንጂ ተራ አይደርስህም። አንድ ወዳጄ ለእኔና ለእሱ ቢራ ሊገዛ ከፊቴ ተሰልፏል። ሁለት አዝዞ አንዱን ሰጡትና ለእኔ ወደኋላ አቀበለኝ። እዚያው ሰልፉ ጋር ቆመን ሁለተኛውን የሚሰጠው ጠፋ። በፊት የቆምነውን ተወውና አንዱን ቢራ ካገኘን በኋላ 15 ደቂቃዎች ቆምን። ቢቸግረኝ ወጣ ብዬ ጠበቅሁት። እሱ እስኪመለስ ድረስ የሰጠኝን የቆርቆሮ ቢራ ሳልከፍተው እጄ ላይ ሞቀ።

 

ችግር ሁለት፦ የሙዚቃ መድረኩ በታች ከተሰበሰቡት ታዳሚዎች ውስጥ ዘልሎ ወደ መድረኩ ወጥቶ ከመድረኩ በጠባቂዎች ያልተሽቀነጠረበት የሐበሻ ፌሽት አላስታውስም። በዚህ በቴዲ አፍሮ ላይ አንዱ ዘልሎ ገብቶ ቴዲ እየዘፈነ ሳለ ወደላይ እንደ ህጻን ልጅ አንጠለጠለው። ሌላኛው ደግሞ በሁለት እጆቹ ግጥም አድርጎ አንገቱ ላይ ይዞት እንዳይተነፍስና እንዳይዘፍን ካደረገው በኋላ ጉንጩን ግጥም አድርጎ ሞጨሞጨው። ቴዲ ገፋ ባያደርገው ኖሮ አፉ ላይ ይሞጨሙጨው ነበር። አቤት ያኔ የቴዲን ፊትና ንዴት ያየ በጅልነታችን ሆዱን እስኪያመው ድረስ ይስቃል። ወንዶቹ ብቻ ሳይሆኑ ሴቶች ሐበሾችም ጭምር የዚህ ችግር ባለቤቶች ናቸው። “ፍቅርና ጉርሻ ሲያስጨንቅ ነው” የሚለውን በስዊድንኛ ወይንም በሌላ ቋንቋ ተርጉሞ ለማስረዳት ቢቻል እንኳ፤ በተለይ ምዕራባውያን ትርጉሙ የሚገባቸው አይመስለኝም። እውነት ግን ፍቅር የግድ ማስጨነቅ አለበት ‘ንዴ? …

 

እንደው ስሞትልህ ንገረኝማ?! … ምን ሆነን ነው እንዲህ የምንሆን? ‘ንዴ! ዘፋኙ/ኝዋ ሁላችንንም ለማስደሰት አይደለም ‘ንዴ መድረኩ ላይ የወጡት? ታዲያ እኛ ምን እንሁን ብለን ነው መድረኩ ላይ ወጥተን የምናሰቃያቸውና የምናስጨንቃቸው? … ‘ንዴ! ፍቅራችንን የምንገልፀው በጉልበት ብቻ ነው ማለት ነው? ኧረ! ለመሆኑ መቼ ይሆን እኛ የምንሠለጥነው? … አሁን በሞቴ መድረክ ላይ ወጥቶ ቴዲን አስጨንቆ፣ ሌላውን በሺህ የሚቆጠር ታዳሚ ከቁብ ሳይቆጥሩና “የራሳችሁ ጉዳይ!” ብሎ ከማለት አልፎ በጠባቂዎች ተሽቀንጥሮ እስከመወርወር መድረስ ምን የሚሉት የሙዚቃ ስሜትና ለቴዲ ያለ ፍቅር ነው?

 

ችግር ሦስት፦ እስከዛሬ ከገባኋቸው ፌሽቶች ውስጥ ብጥብጥ ያላየሁበት ቢኖር የኢትዮጵያን ሚሊንየም አስመልክቶ የተዘጋጀ ዝግጅትን ብቻ ነው። ከዚያ በተረፈ የተገኘሁባቸው ጥቂት ፌሽቶች በሙሉ ማለት ይቻላል ጠብ አይጠፋቸውም። አብዛኞቻችን ሐበሾች ስንባል አንበሣነት የሚሰማን ስንጠጣ ነው መሰል፣ የሚችለን ያለ አይመስለንም። ሁሉንም ከጥፍራችን ቆሻሻ ሳንቆጥር እንደነፋለን። ቡራ ከረዩ እናበዛለን። ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ይቀናናል። ይኸኛውም ፌሽት ላይ አማባጓሮ ለመፍጠር የሞከሩ ጥቂት ሰዎችን ታዝቤአለሁ።

 

ችግር አራት፦ “ያስተሰርያል” የሚለውን የቴዲ ሲዲ ቢያንስ በሣምንት አንድ ጊዜ አዳምጠዋለሁ። እናም ዘፈኖቹን ጠንቅቄ ከነግጥማቸውና ከነዜማቸው አውቃቸዋለሁ። በዚህ ምሽት ፌሽት ላይ ግን በሚገርምህ ሁኔታ ቴዲ መዝፈን እስከሚጀምር ድረስ የትኛው ዘፈን እንደሆነ ግራ ሲገባኝ ቆየሁ። ቢቸግረኝ አብረውኝ ከነበሩት ጓደኞቼ ውስጥ ያሉትን ስጠይቃቸውም ከእኔ ተሽለው አልተገኙም። ቴዲ ግጥሙን መደርደር እስኪጀምር ድረስ የትኛው ዘፈን እንደሆነ ማወቅ እጅግ አስቸጋሪ ነበር። እውነት ለመናገር የመሣሪያ ተጫዋቾቹ ሲዲው ላይ እንዳለው አድርገው መጫወት አልቻሉም። መቼም ይሄንን በተመለከተ ቴዲ ከኔ የተሻለ ያውቃልና እስቲ ሀገር ቤት ስታገኘው ጠይቀው። ቴዲ ግን ድምጡ ሲዲው ላይ እንዳለው ነው ብል አላጋነንኩም።

 

ጌትዬ! ታዲያ ቴዲን ስታገኘው የመሣሪያ ተጫዋቾቹ ችሎታ ማነስ ነው ወይንስ ሲዲውን ስትሠራ ተጨንቀህና ተጠብበህ በኮምፒዩተር በመታገዝ ስለሠራኸው ነው? ብለህ ጠይቅልኝ። ከሺህ በላይ ሐበሾች የገቡት ሙዚቃውን ለማጣጣምና ለመደሰት ሆኖ ሳለ፤ እንዲህ ያለ ደረጃውን ያልጠበቀ የመድረክ ዝግጅት የቴዲንም የመድረክ ችሎታ በበኩሌ ጥያቄ ውስጥ እንዳስገባው አስገድዶኛል። እኔን ብቻ ሳይሆን ብዙዎችንም ጭምር። ካልሆነ ካልሆነ’ኮ የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሙዚቃውን ብቻ አቀናብሮ በሲዲ ይዞ አንድ ሰው መድረክ ላይ እየረዳውና የዘፈኖቹን ቅደም ተከተል አስተካክሎለት እሱ መዝፈን ይችላል። የመድረክ ችሎታውንም ያስመሰክራል።

 

እውነት ለመናገር እስከዛሬ በመድረክ ካየኋቸው የኛዎቹ ድምጣውያን አስቴርን አወቀን አደንቃለሁ። መድረክ ላይ ይዛቸው የምትቀርባቸው መሣሪያ ተጫዋቾች የተጨበጨበላቸው ናቸው። እሷም የመድረክ ችሎታዋ እንከን የሚወጣለት አይደለም። እንደሚገባኝ ከሆነ ከምንም በላይ ለሙዚቃዋ እና ለመድረክ ዝግጅቷ ከልቧ ትጨነቃለች። ለዚህም ነው መሰል አዘውትራ በየመድረኩ የማትገኘው። ከተገኘችም … አንተው ጨርሰው፤ መቼም ላንተ አልነግርህምና …

 

ጌትዬ! እንግዲህ በጥቂቱ እኛንና ፌሽቶቻችንን በስደት ካስቃኘሁህ ይበቃሃል። ከዚህ ጦማሬ (ደብዳቤዬ) መቼም 1) ስነስርዓት እንደሌለን፣ 2) ለስርዓት ብቻ ሳይሆን ለሕግ እና ለሕግ አስከባሪም ተገዥ አለመሆናችንን፣ 3) ሁለት ሺህ ላይ ቆመንም የተቀናጀና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ አለመሆናችንን፣ 4) ፍቅርና ጉርሻ ካላስጨነቀ ምን ዋጋ አለው በሚል ፈሊጥ ጉልበተኝነት የተጠናወተን በመሆኑ የመድረክ ክብር የማናውቅ መኃይሞች መሆናችንን፣ 5) ጠብ ያለሽ በዳቦ አይነት ጠብ አጫሪ መሆናችንን፣ … እንደተገነዘብህ ተስፋ አለኝ።

 

ለማንኛውም መልካም ገና ይሁንልህ! ሄይዶ! (በስዊድን አፍ ‘ሠላም ሁንልኝ!’ ማለት ነው።)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!