ሀበሻ በየመን

ሀረድ ካምፕ ውስጥ ያሉ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በተላላፊ በሽታ ተጠቅተዋል … የመን ታይምስ ጋዜጣ

ልጄን ማዳን እፈልጋለሁ እርዱኝ … ልጇ የታመመባት እናት

በየመን 14,000 ኢትዮጵያዊያን ችግር ውስጥ ገብተዋል … የየመን ሬድዮ

ግሩም ተ/ኃይማኖት

ሰሞኑን የታተመ አንድ ”አል-ወሳይቂያ” የተባለ ጋዜጣ በአንዲት ኢትዮጵያዊት ላይ የተደረገ ግድያን ምስጢር አጋልጧል። ”እስከሞት የሚሰቃዩ ኢትዮጵያዊያን በሰነዓ” የሚል ርዕስ ሰጥቶ ምንጩ የየመን ሁማን ራይት ሚኒስቴር እንደሆነ ጠቅሶ ዘገባውን ለንባብ ያበቃውን ጋዜጣ ትርጉም እነሆ፦

 

 

እንደ ሁማን ራይት መግለጫ አንዲት ሌይላ የተባለች ኢትዮጵያዊት በምትሰራባቸው ሰዎች እሰሞት የደረሰ ስቃይ እንደተፈፀመባት ታወቀ። በአሰሪዎቿ ተሰቃይታ ለሞት የተዳረገችው የ25 አመት ወጣት እና የአንድ ልጅ እናት የሆነችው ኢትዮጵያዊት ጉዳይ አሁንም አወዛጋቢ እንደሆነ ነው። ሌላው ቀርቶ ከጁን 21/ 2011 ጀምሮ ሬሳዋ ሆስፒታል ፍሪጅ ውስጥ እንደሚገኝ፣ እንዳልተቀበረ ጭምር ጋዜጣው ዘግቧል።

 

ሶስት ሆነው አሰቃይተው እንደ ገደሉዋት እና ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እንደ ተፈፀመባት ሬሳውን የመረመረው ዶክተር ገልፅዋል። እንደ ዶክተሩ ገለፃ ከሆነ በጣም አሰቃይተው ደብድበዋት መሞቷን ገላዋ ላይ ብዙ ቦታ የዱላው ምልክት መታየቱ እና በተለይ ደግሞ የራስ ቅሏ ተሰብሮ መገኘቱ ከፍተኛ ድብደባ እንደ ደረሰባት ነው የሚያሳየው። ሰውነቷ ላይ ብዙ ቦታ በእሳት አቃጥለዋታል። ብረት አግለው እና በሲጋራ ጭምር እንዳቃጠሉዋት ነው የተጠቀሰው። በሲጋራ እና ብረት አግለው የተቃጠለው ጠባሳ የተገኘው ፊቷ፣ ወገቧ፣ እግሯ፣ ሆዷ፣ እና የተለያየ ቦታ ነው። በጣም ከፍተኛ ስቃይ እንዳሳለፈች ዶክተሩ ቢገልፅም የሰነዓ ሰሜን ቀጠና ፍርድ ቤት ለሶስቱ ተከሳሾች የሰጠው ውሳኔ እጅግ አሳዛኝ ነው። ምንም ሳይባል በዳኛ ውሳኔ በነፃ ተለቀዋል።

 

ከሶስቱ አንዱ በእድሜ ወጣት የሆነው አባቱ ዳኛ በመሆናቸው በሽተኛ ስለሆነ ተብሎ ከእስር ነፃ ወጥቷል። ሁለቱ ላይ ደግሞ የቀረበው መረጃ በቂ ስላልሆነ በሚል በዳኛው ውሳኔ በነፃ ተለቀዋል። በሰብዓዊ መብት የወንድማማቾች /አል-ሸቃይቅ/ ማህበር ሊቀመንበር አመል ባሻ ነች ስለሁኔታው ይፋ ያደረገችው። ክሱን እየተከታተለች ያለችው ፋይዛ ሱሌማን ስትሆን እስከመጨረሻውም እንደምትከታተል እና ወንጀለኞቹ ላይ እንዲፈረድባቸው የምትፈልግ በመሆኑ የተከሳሾች ቤተሰብ እያስፈራሩዋትም እንደሆነ ስለጉዳዩ በፌስ ቡክ አመል ባሻ ገልፃለች። የኢትዮጵያዊቷ ሟች ሌይላ እህት ሰብዓዊ መብት ውስጥ የምትሰራው ፋይዛ ሱሌማን ቤት ሰራተኛ ነች። ፋይዛ ወንጀሉን ካወቀች በኋላ ወንጀሉን ፈፃሚዎች የፍርድ ቅጣት እንዲያገኙ ጉዳዩን ፍርድ ቤት እየተመላለሰች ትከታተላለች።

 

በ25 አመቷ ኢትዮጵያዊ ነፍስ ግድያ የተከሰሱት ሰዎች ቤተሰብ 5.000 ዶላር ካሳ ሰጥተው ከሳሾች ክሱን እንዲሰርዙ ተማፅነዋል። የሟች እህት እና አሰሪዋ ግን በዚህ ስላልተስማሙ በድርድር 12.000 ዶላር ድረስ ከፍ አድረገውላቸዋል። በዚህም ቢሆን ላለመስማማት የቆረጠችው እና ፍትህ የናፈቀችው ፋይዛ ማስፈራሪያ በቤተሰቦቿ በኩል እየደረሳት እንደሆን አመል ባሻ ገልፃለች ሲል ጋዜጣው ዘገባውን አጠናቋል።

 

በሉብናን ኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት በር አካባቢ ጥቃት የተፈፀመባት ኢትዮጵያዊት በቪዲዮ የተቀረጸ ምስል ስለታየ በየቦታው ያለን ኢትዮጵያዊያን ተቃውሞ አሰምተናል። እዚህ የመን ውስጥ ግን ከዛ የበለጠ ጥቃት እየተፈፀመባቸው ያሉ እህቶቻችን በየቤቱ እየተገደሉ ተከራካሪ እየጠፋ ነው። ተከራካሪ ማጣት ብቻ ሳይሆን ሬሳም በየፍሪጅ ውስጥ እየቀረ ነው። የሌይላም ሞት ቢሆን እህቷ በመኖሯ እና የምትሰራባት ሴት የመን ሰብዓዊ መብት ሚኒስቴር ውስጥ ስለምትሰራ ነው ተከራካሪ ያገኘችው። መቅበር ግን አልተቻለም። የሟችን እህት ለማግኘት ጥረት እያደረኩ ስለሆነ ከተሳካ በቃለ-ምልልስ ለማቅረብ እሞክራለሁ።

 

የመን ውስጥ በIOM የተመሰረተ ካምፕ በተለያየ ቦታ አለ። በእነዚህ ካምፖች ውስጥ ያሉ 14.000 ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው መግቢያ ሁኔታ አጥተው እየተሰቃዩ ነው ሲል የየመን ሬድዮ ገለፀ። ሬድዮው እንዳለው ከሆነ የመን በአሁኑ ወቅት የተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ባለመሆኗ ምንም አይነት እገዛ ልታደርግ አትችልም። የኢትዮጵያ መንግስትም ”ወደ ሀገር እንዲመለሱ ወይም ሀገር መግባት ይችላሉ ከዛ የተረፈ ግን ምንም ማድረግ አልችልም” ብሏል። የሬድዮ ጣቢያው ከአንድ ሰዓት በላይ ባቀረበው የመላ ማፈላለግ ውይይት የሳዑዲያ መንግስትን፣ አይ.ኦ.ኤምን፣ ዩ.ኤን.ኤች. ሲ.አርን፣ የኢትዮጵያ መንግስት ተወካይን አካቶ ቢያነጋግርም ምንም ውጤት እንዳላገኘ ገልፃዋል። እንዲያውም የሳዑዲያ መንግስት ከዚህ በኋላ በሀገሩ መሬት ላይ የሚይዛቸውን ወደ ገቡበት /የመን/ እንደሚመልስ አሳውቋል።

 

ሀረድ የሚባለው ካምፕ ውስጥ ያሉ በርካታ ኢትዮያዊያን ስደተኞች በተላላፊ በሽታ ሲጠቁ ሁለት በዚሁ በሽታ መሞታቸውን የመን ታይምስ ጋዜጣ ዘገበ። ሙሉ ዘገባውን ለማስነበብ ስለፈለኩ ከታች ጋዜጣውን አያይዤዋለሁ ይመልከቱ። በአሁኑ ሰዓት የየመን መገናኛ ብዙሀን ትኩረት ከሰጡት አንዱ የኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች ጉዳይ ሆኗል። በጦርነቱ ወቅት ቤት ንብረታችን የወደመብን፣ መጠለያ ያልነበረን ሰዎች ተሰባስበን ከዚህ አደጋ አድኑን፣ መፍትሄ ስጡን ብለን UNHCR በር ላይ ለ11 ወራት ተቀመጥን። በ3/7/2011 ቢሮው የየመን አድማ በታኝ ወታደር ጠርቶ አስደበደበን። የሞተው እና የቆሰለው ቁጥር በርካታ ነው። የተጠቀሙበት አስለቃሽ እና ራስን እንዲስቱ የሚያደርገው ጋዝ ግን እስካሁንም ብዙዎች ላይ የማይሽር ጠባሳ ጥሎ አለፈ። ገና ከጅምሩ ዱላን እና ማሳሰርን አማራጭ አድርጎ የተያያዘው የUNHCR ቢሮ በማይሆን ተስፋ ደልሎ አል-ቀረስ የተባለው ካምፕ ግማሾችን አስገባ። በርካታዎችን ግን አሁንም በሚያሳዝን ሁኔታ እስር ቤት ከቶ ነው ያለው። እዚህ አል-ቀረስ የተባለ ካምፕ ውስጥ ሌሎች ስደተኞች ከ14 አመት በላይ ተቀምጠው አስታዋሽ ያጡበት ቦታ መሆኑ ይታወቃል። ሚግሬሽን እስር ቤት ያሉት ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን ስደተኞች ግን ያለ ምንም መፍትሄ ታስረው ከከረሙ በኋላ ውጡ በመባላቸው ”የታሰርንበት ምክንያት ምንድን ነው? ካምፕ እናስገባችኋለን ተብለን ከፈረምን በኋላ እስር ቤት አስገብታችሁ ያቆያችሁን ምን ወንጀል ሰርተን ነው? መፍትሄ የጠየቅነው UNHCR ቢሮው ለታሰርንበት ምክንያት ይስጠን፣ የተየቅነውን የመፍትሄ ጥያቄ ይመልስልን ...” ሲሉ ጠይቀዋል። የእስር ሁኔታቸው በጣም ሰቅጣጭ እና በተፋፈገ ሁኔታ ላይ ነው። ፎቶው ላይ ይመልከቱት…

 

እስረ ቤት ውስጥ ሄጄ ያናገርኳቸውን ሁለት ልጆች ቃለ-ምልልስ እነሆ፦በእስር ላይ ያሉ ስለሆነ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ስል ስማቸውን ከመጥቀስ ተቆጥቤያለሁ።

 

ጥያቄ፦ እንደማያችሁ በጣም ተፋፍጋችኋል በምን አይነት ሁኔታ ላይ ነው ያላችሁት? ከUNHCR ቢሮስ መጥተው ያናግሯችኋል?

 

ወንድ እስረኛ፦ ውሀ የለም፣ ምግብ የለም፣ ውሃ ካለመኖሩ የተነሳ መታጠብ የሚለውን አታስበው። የምንጠጣው የሽንት ቤቱን ውሀ ነው። ሽንት ቤት ተጠቅመህ የምትደፋው ውሀ ባለመኖሩ ይሄው ሽታው አፍኖናል። ያልታመመ የለም። ምግብን በተመለከተ ውጭ ያለው ሰው ነው ተረባርቦ የሚያቀምሰን። እነሱ ሰልችቶን ጥያቄያችንን ትተን እንድንወጣ ነው የሚፈልጉት። ጠዋት አንድ ዳቦ ማታ አንድ ዳቦ ነው የሚሰጡን። እናንተም ወገን ናችሁ በትግላችን እንድንቀጥል ለምን አትረዱንም? አንተ ሁሉን ታውቃለህ ወጥተን መግቢያ ቤት የለንም። ስራ እስክናገኝ የምንበላው የለንም። UNHCR አታሎናል ካምፕ ትገባላችሁ ብለው መኪና ላይ ከጫኑን በኋላ ግማሹን ካምፕ ግማሻችንን ይሄው እስር ቤት ከተውን ቀረን። አይመጡም ወይ ላልከው አንዴ መጥተው ነበር ካምፕ ውሰዱን ብለናቸው ነበር በዛው ጠፉ። አሳስረውን አንድ ቀን እንኳን ቀለብ አላሉንም።

 

ጥያቄ፦ እታለሜ እንደማያችሁ በጣም ተፋፍጋችኋል። በተለይ እናንተ ጋር ደግሞ ህፃናት አሉ። ህፃናቱም እስረኛ ናቸው?

 

ሴት ታሳሪ፦ ጥያቄህ የሚገርም ነው … መቼም ይሄ መዋዕለ ህፃናት አይደለ ምን ሊሆኑ መጡ ብለህ አሰብክ?

 

ጥያቄ፦ እኔ ግማሹ መታሰሩን ግማሹ ካምፕ መግባቱን ስሰማ ልጆች ያላቸውን የወሰዷቸው እንጂ ያሰራቸው አልመሰለኝም። ደግሞ እዚህ እያየኋቸው ቢሆን እንኳን ለአንባቢዎቼ ማስረዳት ያለብሽን እንድታስረጂልኝ ስለምፈልግ …

 

ሴት ታሳሪ፦ ወደ ሀያ ህፃናት አሉ አብረውን። ከአራት ልጆቿ ጋር የታሰረች አለች። ከሁለት ልጆቿ ጋር የታሰረች አለች። እንዲያውም በዚህ መተፋፈግ የተነሳ የሳዓዳ ልጅ ትንሹ ታሞባት ጁሜሪ ሙስተሸፋ /ሆስፒታል/ ተኝቶአል አልሰማህም? /ሰምቼ ጁሜሪ የሚባለው ሆስፒታል ሄጄ ለማየት ሞክሪያለሁ። መድሀኒት መግዣ አጥታ ስታለቅስ መየት ብችልም አይኔ ውስጥም ኪስ ውስጥም ያለው እንባ ብቻ በመሆኑ እሱኑ ጠብ አድርጌ ተመልሻለሁ።/ ያውልህ እዛ ዳር ያለውን እየው /ዞር በሉለት ብላ አጮልቄ በማናግራት መስኮት እንዳይ አደረገችኝ። የሽንት ቤቱ ግማት ደጋግሞ አስነጠሰኝ። እናት ታሞ የተኛውን ልጇን በጥጥ ውሀ ከንፈሩ ላይ ታደርግለታለች። ቆሞ ማየትም ሆነ ማውራት ስላልቻልኩ ማናገሬን ጥዬ ዞሬ የእስር ቤቱን ጊቢ ለቅቄ ውጣሁ።/ እስር ቤቱን ለቅቄ ብወጣም በማግስቱ የሁለት ልጆች እናት ወደ ሆነችው እና ልጇ ታሞባት ሆስፒታል በማስታመም ላይ ያለችው ሳዓዳ ጋር ሄድኩ። መኝታው ላይ መኖሩን እስክጥራጠር ክስት ብሎ ይታያል። ብርድ፣ እና ከምግብ እጥረት የመጣ በሽታ እንደሆነ ነገረችኝ። መተነፍስ አቅቶት ኦክስጂን እና ጉሉኮስ ተድረጎልታል።

 

ጥያቄ፦ አሁን እንዴት ነው ልጅሽ? ህክምናውስ እንዴት ነው?

 

ሰዓዳ፦ እነሱ ህይወት ከማትረፍ ይልቅ ገንዘብ ላይ ነው ቅድሚያቸው። ወረቀት እየፃፉ መድሀኒት ግዢ ይሉኛል። 50 እና መቶ ዶላር ይባላል ዋጋው እንድታውቅ የምፈልገው እንኳን ይሄን ያህል ላገኝ እና ልገዛለት ቀርቶ አሁን ወተት የምገዛበት የለኝም..ካለህ ስጠኝ ባዶ ሆዱን ከሚሞት ወተት እንኳን አቅምሼው ይሙት … /ምን ማድረግ አለብኝ የሚለውን ባስብ ምንም ላደርግላት አልቻልኩም። ለዛን ሰዓት ወተት ገዛሁለት በማለት በቂ እንዳልሆነ እረዳለሁ ግዴታ የሚችሉ ሰዎች ተረባርበው እንዲረዷት አሰብኩ። አስቤ …

 

ጥያቄ፦የሚረዱ ሰዎች ቢገኙ ምን እንዲረዱሽ ትፈልጊያለሽ?

 

ሰዓዳ፦ ለህክምና የማወጣው የለኝም፣ መድኃኒት መግዣ የለኝም፣ የማበላው የለኝም፣ ውሀ ገዝቼ የማጠጣበት የለኝም….ምንም የለኝም። አባቱም የለም። ለ11 ወር UNHCR በር ላይ ተኝተን ነበር የምንበላው የምንጠጋበት በማጣታችን ነው እዛ የወደቅነው። ልጄ የስደት ጌጤ ነው ላጣው አልፈልግም። ምን ላብላው፣ በምን መድሀኒት ልግዛለት? እባካችሁ ልጄን ማዳን እፈልጋለሁ እርዱኝ በልልኝ ...

 

የምትችሉ ሰዎች እባካችሁ ስልክ ቁጥሯ ከታች አለላችሁ እና እርዱዋት …

 

የመን ውስጥ ሁማን ራይት ሚኒስትር በር ላይ ተቀምጠን በUNHCR ቢሮ የሚደረግብን በደል ልክ አይደለም መፍትሄ ይሰጠን ብለን ጠየቅን። በአስለቃሽ ጭስ እና በጥይት ስንደበደብ በድብቅ የቀዳነውን ሲዲ ለሚኒስትሯ አቀረብን። ህገ-ወጥ ስራ እንደተሰራብን እና የጠየቅነው ጥያቄ አግባብነት ያለው መሆኑን በደብዳቤ አስደግፈው ሰጡን። የሚገርመው ግን ከጥቂት ቀናት በኋላ ሚኒስትሯ ፖሊስ አምጥተው አሳሰሩን። አንድ ቀን እስር ቤት አድረን በማግስቱ ያዙ ተብለው የምንያዝበትን ምክንያት ሳያውቁ የያዙን ፖሊሶች ”… ወደ ሀገራቸው መልሷቸው …” ብለው ደብዳቤ ፅፈው ለሚግሬሽን እስር ቤት አስረከቡን። እኛ ስንታሰር ውጭ ቀርተው የነበሩት ሚኒስትሯን እንዴት እንዲህ ታደርጊያለሽ ብለው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው መፈክር እያሰሙ ሲጮሁ ”አላረኩም” በሚል ክህደት ተደውሎ ተለቀቅን። ይህ የሆነው ከ15 ቀን በፊት ሲሆን አሁንም ማክሰኞ በ15/5/2012 ቀን ላይ ሚኒስትሯ ”ስደተኛ የሚባል ነገር እዚህ ጋር ማየት አልፈልግም እንድታስነሱልኝ፣ ካልሆነ ከስራ ነው የማባርራችሁ” ብለው ዝተው ገቡ። ማታ ላይ የተጠናከረ የፖሊስ ሀይል መጥቶ 10 ልጆችን ለቅመው ፖሊስ ጣቢያ ወሰዷቸው። እስከ አሁንም በእስር ላይ ናቸው። በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊ ስደተኛው ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ህገ-ወጥ መሆኑን የየመን ሬድዮ ራሱ አፕሪል 8 ባቀረበው ፕሮግራም አሳውቋል።

 

የሰዓዳን ልጅ ለማዳን እጃችሁን መዘርጋት ለምትፈልጉ ስልክ ቁጥሯ 00967737757698 ነው።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ