አሥራት አንለይ ትዝታዬና መጽሐፉ
ወለላዬ (ከስዊድን) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
... እራሱን የሚገል እራሱን የሚያድን
እራሱን የሚያስጠላ፤ እራሱን የሚሆን።
እኮ በሉ ጎበዝ! ይኸን ሰው እወቁት፤
ሲፈልግ የሚኖር፤ ሲፈልግ የሚሞት፤ ...
አሥራት ለአሥራት
ትምህርት ቤት ለሁለት ወራት ሲዘጋ ለደብተር መግዣ የሚሆነኝ ገንዘብ የማገኝበት ስራ የሚያስቀጥሩኝ ዘመዶች ነበሩኝ። ሁለት ወይም ሦስት ክረምቶች ሰርቻለሁ። በኋላ እንደተረዳሁት ስራው በክረምቱ ወራት እንዳልወሰልት መቆጣጠሪያ ጭምር እንደነበር ልረዳ ችያለሁ።
የመጨረሻው የስራ ቀጠራዬ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት በወር ስልሳ ብር ጥራዝ ክፍል ሆነ። ክፍሉ ሰፊ አዳራሽ ሆኖ ልዩ ልዩ የስራ ማሽኖች የተከማቹበት ቋሚና ጊዚያዊ ሰራተኞች የሚተራመሱበት ቦታ ነው።
ከኔ ጋር በክረምት ወራት የተቀጠርን ስድስት ልጆች ነበርን። ከነዚህ መሃል አንዱ አሥራት አንለይ ነው። ቢጫ ጃኬት፣ ሙሉ ቀለም ያለው ሸሚዝና ሱሪ ለብሶ ጥራዝ ክፍል አንድ ቀን ታየ። ቀይ ፊትና የሞሉ ጉንጮች ያሉት፣ ”ድንቡሽ ያለ ልጅ” የሚሉት አይነት ነው።
ከዬት እንደመጣና ስሙን ነገረኝ። በቀላሉ ተግባባን ብዙ ፈገግታ የለውም፤ አንደበተ ቁጥብ ነው። ኮራ ያለ ተፈጥሮው ከዝምታውና ከጠቅላላ ሁኔታው ጋር ሲታይ እሰው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀርም፤ ምን ይጀንነዋል? የሚሉ በግልጽ ሊቃወሙት የፈለጉም ነበሩ።
ለኔ ግን ዝምታውም፤ ኩራቱም፤ ተስማምቶኛል። እንዳደንቀውና እንዳከብረው የሚያደርገኝ ተጨማሪ ነገር ደግሞ ተገኘ። ”አረ ወተቴ ማሬ” የሚለውን የሙሉቀን መለሰን ተወዳጅ ዘፈን ግጥም እሱ እንደጻፈው ነገረኝ። ጊዜ አላጠፋሁም ከስራ እንደተለቀቅን ካሴቱ ላይ የተጻፈውን ስም ላረጋግጥ ሙዚቃ ቤት በረርኩ። ትክክል ነበር፤ ”ኧረ ወተቴ ማሬ” ግጥም አሥራት አንለይ ይላል።
የዛን ጊዜ ሰው አድናቆት እንዳሁኑ እንዳይመስላችሁ። ያንን የሚያውቅ ያውቀዋል። እንኳን ግጥም ጽፎ ለታዋቂ ዘፋኝ የሰጠ ይቅርና፤ ዘፋኙን በአካል ያየ፣ የጨበጠ፣ ያነጋገረ አመቱን ሙሉ አለሱ ወሬ የለውም።
ከአስሥራት ጋር ብርሃንና ሰላም ጥራዝ ክፍል እየሰራን ነው። ተፈላልገን ጎን ለጎን እንሆናለን። ምሳም የምንበላው አብረን ነው። በዳንቴል የሚቋጠሩ የምሳ ሳህኖች ነበሩን። አንዳችን ያልያዝን ቀን የሌላኛችንን ምሳ ይዘን ግሩም ድንቅ ሻይ ቤት ጎራ ማለታችን የማይቀር ነው። ሁለት ሁለት ፓስቲ ጨምረንበት በሻይ ካወራረድን በኋላ ወደስራችን እንመለሳለን።
አሥራት በየቀኑ ብዙ የማላውቃቸውን ነገሮች እየመዘዘ ይነግረኛል። ሁሉም ነገር ከዛን ጊዜ ግንዛቤዬ የራቀ በመሆኑ ለዚህ ሰው አድናቆቴ እየናረ ሄዷል። ደስ ሲለው ግሩም የሆነ በሬድዮም ሆነ የትም ቦታ ሰምቼው የማላውቀው ግጥም በቃሉ ያነበንብልኛል። ማንጎራጎርም ይችላል። እንደውም የራሴ ግጥምና ዜማ ናቸው የሚላቸውም የተሟሉ ዘፈኖች በድምፁ አሰምቶኝ ያውቃል። በተለይ ”ሰላም ባህረ ጣና” የሚለውም ዘፈኑን የማዳምጠው በከፍተኛ ተመስጥዖ ነበር።
ይሄ ሰው ማን ይሆን? ማንነቱን እንዴት ይገልጻል? ወደፊት የሚሆነው ምንድነው? አንዱንም ማወቅ አልችልም። አሁን አንድ ላይ የምንሰራ የጥራዝ ክፍል የክረምት ሰራተኞች ነን። ይሄን ብቻ ነው በርግጠኝነት መናገር የምችለው። ሆኖም ተዝቆ በማያልቅ ጥበብ የተሞላ ነፍስ እንዳለው መገመት አላዳገተኝም።
የሊቀ ካህናት ወይም የሊቀ ሊቃውንት አንለይ ተገኝ ልጅ መሆኑን ነገረኝ። እንደእውነቱ ከሆነ ስለ ቤተ ክህነት ሹመት አንዱም አይገባኝም ነበር። እሱ ግን በወግና በስነሥርዓት ነው ያጫወተኝ። ለምን ጓደኛው ነኛ። ነዋሪነታቸው ባህር ዳር እንደሆነና ከዛም እንደመጣ አልደበቀኝም።
ከሁሉ የማይረሳኝ እስካሁንም የሚገርመኝ ነገር ቢኖር እስከዛን ጊዜ ድረስ በዓይኑ አይቷቸው የማያውቃቸውን ሰዎች እየጠቀሰ ከእነርሱ ጋር ወደፊት እንደሚሰራ በርግጠኝነት መናገሩ ነበር።
እንዲህ አለኝ፤ ”ፀጋዬ ገ/መድህንን ታውቃቸዋለህ?”
”አዎን ብሄራዊ ትያትር አይቻቸዋለሁ።”
”ኃይማኖት ዓለሙንስ?”
”አውቃቸዋለሁ።”
”መራዊ ስጦትንስ?”
”እሳቸውንም አውቃለሁ።” … ሌሎች፣ ሌሎችንም ጠየቀኝ። ማወቄን ነገርኩት። ማወቄ ስል ማየቴን ነው፤ በርግጥም ላያቸው ልጨብጣቸውም የቻልኩበት እድል ገጥሞኛል። አጎቴ ብሄራዊ ትያትር ይሰራ ነበር።
”ወደፊት ከነሱ ጋር ነው የምሰራው አለኝ።” ሲለኝ፤ ምንም ብወደውና ባከብረው ይሄንን ማለፍ አልፈለኩም። መጠየቅ ነበረብኝ።
”አንተ በፊት ታውቃቸዋለህ?”
”አላውቃቸውም።”
”ለስራ ጠርተውሃል?”
አስራት ፈገግ አለ፤ ”አልጠሩኝም።”
”ታዲያ እንዴት ከነሱ ጋር እንደምትሰራ ለማወቅ ቻልክ?”
”ሙያው ስላለኝ እቀጠራለሁ። የሚቀጥረኝ ኃይማኖት አለሙ ነው። ጋሽ ፀጋዬ በብዙ ይደግፉኛል። እውጭም እንድማር ይረዳኛል” አለኝ። ይሄ በእውነት ሲፈጸም ተመልክቻለሁ። ብሄራዊ ትያትር ቤት ተቀጥሯል፤ ጋሽ ፀጋዬ ቤትም ቤተኛ ሆኖ ኖሯል፤ ውጪ ለትምህርት መሄዱም አልቀረም።
ጋሽ ፀጋዬም ”ባልወልደውም የመንፈስ ልጄ ነው።” እያለ አድናቆትና ድጋፉን ሳያቋርጥበት እንደኖረ አውቃለሁ።
ሌላ ቀን እኔም ጉራዬን ልነፋ አሰብኩ፤ ”አሰግድ ገ/ብረእግዚአብሄርን ታውቀዋለህ?” በወሬ ማህል ጠየኩት።
”አላውቀውም፤ ምን ይሰራል?”
”ትያትረኛ ነው። ”ግደይ ግደይ አለኝ”ን በቴሌቪዥን አይተሃል?”
”አላየሁም።”
”የኢንሹራንስ ወኪል ሆኖ ከወጋየሁ ንጋቱና ከቱራፋት ገብረእየሱስ ጋር ሰርቷል።” ታሪኩን ነገርኩት ... ”ሁለት ወዶንስ?”
”አላየሁም።”
”አምስት ለዜሮንስ?”
”አላየሁም።”
እነዚህን ሁሉ እንደሰራ ተናዘዝኩ። ”እንዴት ኮሚክ መሰለህ!” የሚልም ጨመርኩ። ”በምን አወከው? ምንህ ነው?” እንዲለኝ ጠበኩ፤ አላለኝም።
በምትኩ ”የት ትያትር ቤት ነው የሚሰራው?” አለኝ።
”ብሄራዊ ትያትር ነዋ ... አጎቴ’ኮ ነው” የሚል መጨመር የግድ ነበር።
”ኦ! ነው እንዴ! ከሱም ጋር አብረን እንሰራለን” ብሎኝ ነገሩን ዘጋው። የሚለው ብዙም ባይገባኝ ዝም አልኩ።
********************
... ይሄ ጎልማሳነት ጠብ ያለሽ በዳቦ
ደም ፍላት መጀነን ጉዳት መች ታስቦ
ና ውጣ ነይ ውጪ ሰንዝሪ ልሰንዝር
ጠባይ ምን አገባው በቦክስ መዘረር ...
አሥራት አንለይ
ከኛ ጋር ሌሎች በክረምት ወራት ተቀጣሪዎች አሉ ብያለሁ። አንዱ ተስፋዬ ኃ/ማርያም ይባላል። ጮሌ የመርካቶ ልጅ ነው። ከሁላችንም ጋር የሚግባባ ጓደኛችን ነው። በተለይ ከኔ ጋር አብረን ያደግን ያህል እንዋደዳለን። መርካቶም ንግድ ቤታችን ነው ብሎ አንድ ቤት ወስዶናል። ፓስቲና ሻይ እንደልቤ አብልቶኛል። ጆተኒም እንጫውታለን፤ በግራ እጁ ጭምር ያሸንፈኝ ነበር። በአካባቢው ”ተስፍሽ”፣ ”ተስፍሽ” የማይለው የለም። የብርሃንና ሰላም ስራችንን ከጨረስን በኋላ ተገናኝተን አናውቅም። ከዛ ቀውጢ ጊዜ ከተረፈ አንዱ ጋ ገብቶ ይሆናል - አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ... እንጃ ...
ሌሎች ደግሞ የጣልያን ሰፈር ልጆች ነን የሚሉ ነበሩ። አደፍርስ እና ምናሴ ይባላሉ። አደፍርስ ረጅም ደልደል ያለ ሰውነት ያለው፤ ሞኝ በሚመስል ፊት ብልጥነቱን የደበቀ ክፉ ቀበሮ ነበር። እማያመጣው የኩምክና ወሬ የለም። በዚህ ላይ ሌሎችን አሳስቶ ወይም አጣልቶ የሚደሰት አይነት ነው። አንድ እንደካቦ አይነት ወዲያ ወዲህ የሚመድበንን ሰው፤ ”ምን አግብቶት ነው የሚያዘን? ብሎሃል” ብሎ አጣልቶኝ፤ ሰውዬው መከራዬን ሲያሳየኝ ከርሟል።
ምናሴ ደግሞ አጭርና ሳቂታ፣ አጭበርባሪ የሚመስል ብልጥነቱን አይኑም፣ አፍንጫውም የሚመሰክሩለት፤ በዚህ ላይ እሱም ያደረገውንም ያላደረገውንም አጋኖ የሚያወራ ተንከሲስ አይነት ልጅ ነበር። አንድ ቀን የኒያላ ሲጋራ ካርቶን እየቀደድንና እያጠፍን ስንሰራ እሱ እና አደፍርስ ቻይና ግሩፕ መሆናቸውን ነገረኝ። ጥርስ አውልቀው በጨርቅ ቋጥረው መስጠት እንደሚችሉ፤ ከፈለጉ ምላስ ቆርጠው ለውሻ መጣል እሚያዳግታቸው እንዳልሆነ፤ … አውራልኝ። ”ምታስቦካውን አስቦካ። ማስፈራራትህ ነው?” ብዬ አሾፍኩበት። የሁለቱም ጉራቸውና የሚሰሩት ስራ ቢያናድደኝም ተግባብቻቸው ለመኖር ችያለሁ። ምን ዋጋ አለው አሥራትን ጠመዱብኝ።
”እሱ ከማን በልጦ ነው? እያረፈደ የሚገባው?” ይላሉ። ”ሁልቀን ቀላል ስራስ የሚሰጠው ለምንድነው?” እያሉ ይተነኩሱታል። ”ደግሞ እኮ ኩራቱ፣ ከኛ በምን ይበልጣል?”፣ … የማይሉት ነገር የለም። አሥራት ደግሞ አይወዳቸውም። አናግሯቸው አያውቅ። ”እነዚህ አውደልዳይ ዱርዬዎች” ይላል። ለእውነት ለመመስከር ግን ልጆቹ ልክ ነበሩ። አሥራት በፈለገበት ሰዓት ይገባል፤ ተናጋሪ አልነበረውም። ይሄ እኔም የታዘብኩት ጉዳይ ነው።
በዚህ መሀል አንድ ቀን ከጥራዝ ክፍል ያለቀ መጽሐፍ በትልቅ ጋሪ ጭነን እታች ወዳለው መጋዘን እንድንወስድ ታዘዘ። ጣሊያን ሰፈሮቹ፣ እኔና አስራት ነበርን። አሳንሱር ውስጥ ገብተን መውረድ እንደጀመርን፤ አሳንሱሩ አንድ ቦታ ቆመ። የጣሊያን ሰፈሮቹ ልጆች አቁመውት ሊሆን ይችላል።
ቆዳ ሞኙ ለአጭሩ ትዛዝ ሰጠ። ”ምናሴ ጩቤዬን አቀብለኝ” በኃይለኛ ሁኔታ እንደተናደደ ይርገፈገፍ ጀመር። እንደመፎከርም ቃጣው ... እኔ ሳቄን ልቆጣጠር አልቻልኩም።
አጭሩ እንደተደናገጠ መስሎ ”ኧረ ባክህ ተው! ምን ልታደርግ ነው?” እንደመርበትበት አለ።
”ይሄን ጉረኛ መቦጫጨቅ አለብኝ” ... አሥራት ላይ አፈጠጠ።
”ተወው እባክህ፣ ለዛሬ ምህረት አድርግለት” ... ምናሴ የሚለምን መሰለ።
”አልምረውም! አምጣ በቃ! ጩቤዬንንንንን ...” አደፍርስ አንበሳ ሆኖ አስራትን አድራሻውን ጠየቀው።
”ምን ልትሆን ነው? አድራሻዬን የምትጠይቀኝ?” ... የአሥራት ፊት ደም መስሎ ቀላ፤ እንደተቆጣ ነብር ተነፋፋ …
አደፍርስ ቀጠለ፤ ”ደምህን ቀድቼ ለቤተሰቦችህ እልካለሁ። አለቀ በቃ … በቃ!” የአሳንሱሩን ግርግዳ በጡጫ ነረተው።
ድጋሚ ሳቄ አመለጠኝ። አሳንሱሩ ተንቀሳቅሶ ቦታው ደርሷል። በሩ ሲከፈት ከውጪ የሚጠባበቁ ሰዎች ገጠሙን። አሥራት ቀድሞ ወጥቶ ይጮህ ጀመር። ”የማናባትክን ደም ነው የምትቀዳ? እያንዳንድህ ተራ በተራ ና። አርህን ነው የማበላህ፤ ፈሳም ዱርዬ ሁላ ...”
የቆሙት ሰዎች ግራ ገብቷቸው ያዩን ጀመር። የቢሮ ሰራተኞችና ኃላፊዎች ናቸው። እነ አደፍርስ ምንም እንደሌለ እቃውን እየገፉ ወረዱ ደንግጠዋል። ፊት ለፊት ካለው መጋዘን ሦስታችን ገባን። አሥራት ውጪ ቆሞ ይጮሃል። አራግፈን ስንወጣ አሥራት አልነበረም፣ ዝም ልላቸው አልፈለኩም።
”ለምንድነው? ሁል ቀን አሥራትን የምትለክፉት?” ...
አላስጨረሱኝም ሁለቱም በአንድ ድምፅ ”አንተ ምናገባህ?” ብለው አንገታቸውን ቀሰሩ።
”ለምን አያገባኝም? ብትጠነቀቁ ይሻላል!” ጣቴን አጭሩ አፍንጫ ድረስ አስጠጋሁ።
”ኧረ! አንቺም ትፈልጊያለሽ?” አድፍርስ ነበር።
”ሂድና ምታስቦካውን አስቦካ፣ ያንተን ቻይና ግሩፕ ምናምን የምፈራ አይምሰልህ።”
”ኧረ! ይቺ ቀጫጫ!” እንደማጨብጨብ እጁን ካማታ በኋላ ትንሽ ቆይቶ፤ ”እንደጫት ነው ቀነጣጥሼ የምቅምሽ” አለኝ ጡንቻውን አሳይቶኝ ደረቱን ነፋ።
”ብሽቅ! ማንም የሚፈራህ እንዳይመስልህ። እዚች ሰፈር እንዳትደርስ ነው የማደርግህ።” ዓይኑ ድረስ ፊቴን አስጠግቼ ቀረብኩት፤ ምንም አላለ ጋሪውን መግፋት ጀመረ። በጸጥታ ወደ ጥራዝ ክፍል ገባን።
ሌላ ቀን ከአደፍርስ ጋር አንድ ላይ ስንሰራ ስለ አስራት ጠየቀኝ። ”ጓደኛህ የት ቀረ?”
”እሱ ምን ችግር አለበት! ባይመጣም ደሞዙ ይከፈለዋል።”
”እንዴት?”
”አታውቅም እንዴ? አቶ አባተ’ኮ አጎቱ ናቸው።” የብርሃንና ሰላም ስራ አስኪያጅን ጠቀስኩ።
አፍረት ትሁን ድንጋጤ ፊቱ ላይ ስትንቀዋለል ታየችኝ። ጨመርኩለት፤ ”አባቱንስ አላየሃቸውም? እኔ አንድ ቀን በመኪና ይዘውት ሲሄዱ አይቻቸው ነበር። ኮረኔል ይሁኑ ሻለቃ አላውቅም ደረታቸው ላይ የደረደሩት መአት ነገር ነው” አልኩት።
”አሃ! ለዚህ ነዋ ...” ቃላቱን አልጨረሰውም። ምናሴን በአይኑ ፈለገ። ሊያወራ መሆኑ ገብቶኛል፣ እንዳመነኝ ስላረጋገጥኩ ደስ አለኝ። አስራት ከአቶ አባተ ልመንህ እንኳን ሊዛመድ፣ ከሰው መሃል አውጣቸው ቢሉት ማወቁንም እንጃ፣ ሁለቱም ጎጃሜዎች መሆናቸው ግን ለኔ ውሸት ተጨማሪ ድጋፍ ሆነ። እነ አደፍርስ ካዛን ቀን በኋላ አስራትን በክብር ያዙት። ግልግል!
****************************
አሥራት እንዳለኝ ብሄራዊ ትያትር ቤት ተቀጠረ። ያለኝ ቃል አንዷም ዝንፍ አላለች፤ ከነ ወጋዬሁ ንጋቱ፣ ከነ ዓለምፀሃይ ወዳጆ፣ ከነ ሲራክ ታደሰ፣ ከነ በኃይሉ መንገሻ ... ጋር ስሙ በማስታወቂያ ቦርድ ላይ ተለጥፎ አነበብኩ። ታዋቂ ተዋናይ፣ ተደናቂ ገጣሚ ሆኖ አዲስ አበባ ላይ ብቅ አለ። እነዚሁ አርቲስቶች ትያትር ይዘው በየክፍለ ሃገሩ ይዞሩ ጀመር።
አሥራት ለትያትሩ ብቻ አይደለም የሚሄደው፤ ስለዛ ቦታ ግጥም ጽፎ ይመጣል። ይቀኛል፣ ”አሰላ ጮቄ” የምትለዋ ስለ አሰላ የጻፋት ግጥም አትረሳኝም። ቆይቶ ራሽያ ለትያትር ትምህርት ከነ በኃይሉ መንገሻ ጋር መላኩን ሰማሁ። ራሽያ ብዙ አስደናቂ ገድሎች እንደነበሩትም አብሮት ከተማረ የቅርብ ሰው ሰምቻለሁ።
*******************
... ምን ያበሳጨኛል - ምን ያነጫንጨኛል
ህይወት እንደሁ - ህልሙ - መች በኔ ይፈታል
የፈለገ ይክዳኝ የፈለገን ልክዳው
ምን ያበሳጨኛል እኔ ላልወስነው ...
አሥራት አንለይ
ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ስራ በኋላ ካስራት ጋር ደጋግመን ተገናኝተናል። አስራት ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ሆኗል። አመሉ እንደድሮው ሆኖ አላገኘሁትም። በሆነ ባልሆነው ይናደዳል፣ ይነጫነጫል፣ ይቆጣል። አንድ ቀን እዛው ብሄራዊ ትያትር አካባቢ እንደልማዱ ቱግ ብሎ አገኘሁት። ካንዱ ጋር ይጨቃጨቃል፣ እንደማስረዳትም፣ እንደመቆጣትም ይላል። የእጁ አወነጫጨፍ ተናግሮ ከማስረዳት በላይ ፈጠነብኝ። ትከሻውን ነካ አድርጌ የምጠብቀው መሆኔን አስታወስኩት። ሰውዬውን ባለበት ትቶት ወደኔ መጣ።
”አሥራት ምን ሆነሃል?”
”ምን እባክህ! ያ ነጃሳ በጠዋት ነጅሶኝ ነው የሚያስጮኸኝ።”
”የማነው ነጃሳ?!”
”ስንቱን ልንገርህ ሁሉም ነጃሳ ነው። እማይሉት፣ እማያመጡት ነገር የለም!” አንገቱን ደፍቶ ትንሽ ቆየና ”አንተ አትናደድም ማለት ነው?” ሲል ጠየቀኝ።
”ለምን እናደዳለሁ? አልናደድም አሥራት”
”ዕድለኛ ነህ። ቢሆንም አንዳዴ ተናደድ” አለኝ።
እሺም እንቢም ለማለት የቸገረ ነገር ነው፤ ሳቅ ብየ ዝም አልኩ። ’ይቺ ሰውዬ ፍልስፍናም ጀመረች እንዴ?’ በሆዴ አማሁት።
”ይገርምሃል እኮ! አለስራ ጎልተውኝ እውላለሁ፤ የልጅ ጡረተኛ አድርገውኛል። ያ ሳያንስ በየዕለቱ ይለክፉኛል ...” እስከነቁጣው መምሩ ቤት ገባን። እኔ ጠጅ፣ እሱ ቢራ ያዝን። አሥራት ቢራውን ጨርሶ ሌላ ቢራ ደገመ። የንዴት ጉሙን በቢራ ሊያተነው እንደፈለገ ገባኝ። እኔም ጠጄን እየኮመኮምኩ አሥራትን በጨዋታ ላዝናናው አቆብቁቤአለሁ።
አዝማሪ እፊታችን ቆሟል። ”የኔማ ጋሽዬ ሰፊ ነው ደረቱ፣ ዋስ ሆኖ ያስፈታል ሸሚዝ ከረባቱ።” ሲል ተሰማ። የተባለለት ሰው ፈንድቋል፣ አፉን ሙሉ እየሳቀ ነው። የመጨረሻ ጥርሶቹ ሳይቀሩ ይታያሉ፣ ከሱ ገንዘብ ልጦ አዝማሪው ወደሌላ ተሸጋገረ።
”አረጀ ሸበተ የሚለው ሰው ማነው፣ ዶሮ እንኳን እሚወደድ ገብስማ ሲሆን ነው።” ሽበታሙ ፈገግ አሉ። አዝማሪው ሌላ ግጥም ጨመረላቸው፤ ”አቶ ሞገስ ደጉ የደጋጎቹ ዘር፣ ለገንዘብ አይሳሳም ይወዳል መመንዘር።” ሞገስ ብዙ አላንገላቱትም አንድ ብር አስጨበጡት።
ወደሌላ እጭር ጠይም ሰውዬ ዞረ። ሰውዬው አንድ ግጥም ከተወረወረለት በኋላ እራሱም ግጥም መስጠት ጀመረ። ”ተቀበል!” አለ ሰውዬው፣ አዝማሬ መነሻ ዜማውን ካለ በኋላ ግጥም መቀበል ጀመረ።
”ገበሩ እረጅም ነው በል” - ”ገበሩ እረጅም ነው”፣ ”የፈረንሳይ ሱሪ” - ”የፈረንሳይ ሱሪ”፣ ”እረረው ድበነው” - ”እረረው ድበነው”፣ ”አልሰጥም ላዝማሪ።”
አዝማሪው መድፊያውን ግጥም አድበስብሶ አልፎት ወደኛ ተወረወረ። ስሜን በምን እንዳወቀም እንጃ ”የኔማ እከሌ ከሌለ ባገሩ - ጥፉ ጥፉ ይላል ብረሩ ብረሩ።” አስራት ሳቅ ጨዋታ ጀምሯል። እጉኑ ያለውን ሰውዬ ወሬ ገታ አድርጎ ”ድገመው! ድገመው!” አለ። ስሜ ሲጠራ ደስ አለው። ጥሎበት ይወደኛል።
የመጀመሪያው ያዲስ አበባ ጓደኛው ባልሆን እንኳን ሁለተኛነትን አላጣም። በምን ይጥላኝ ይወደኛል። የኔ ሙገሳ ካለቀ በኋላ ድምጼን ጎርነን አድርጌ ግጥም ወረወርኩ። ”ለሊት በጨረቃ” – ”ለሊት በጨረቃ”፣ ”ቀንም በፀሐይ” - ቀንም በፀሐይ”፣ … ”ድገመው! ደገመው!” … ”እባክህ አትጥፋ አስራት አንልይ። በልልኝ” አልኩ። ደግሞ ደጋግሞ አለልኝ። አስራት በሳቅ በታጀበ ንግግር ”አንለይ ይሙት! ይሄ ያሸልማል” ብሎ ከደረት ኪሱ አስር ብር መዘዘ። ይሄ ሰውዬ መጠጫ ሊያሳጣን ነው ብዬ ደንገጥ አልኩ፣ ምነው አፌን በዘጋው ... አስራት ብሯን በመዳፉ ይዞ ወደ አዝማሪው ካመላከተ በኋላ እኔ ግንባር ላይ አሳረፋት። ሰዉ ሳቅ በሳቅ ሆነ።
አዝማሪው ቀጠለ ”አስሬ ብጠራው ደስ ይለኛል ስሙን - እከሌ አይነሳኝም የተቀበለውን።” እኔን ነበር፤ አስር ብሯ ላይ ትንቅንቅ ይዟል። የሱን ግጥም ሲጨርስ፤ እኔ ቀጠልኩ። ”ልክ ነህ አንተ ሰው አልፈልግም ሙግት - ወደኋላ አልልም ድርሻህን ለመስጠት።” ከዝች ግጥም ጋር አንድ ብር አስጨበጥኩት።
ማሲንቆውን ሁለት ሰዎች ላይ ደቀነ። አይሰሙትም እርስ በእርስ ይጨቃጨቃሉ። እንደመያያዝ ይቃጣቸውና ሊደባደቡ ነው ስንል መለስ ብለው እንደገና ይጯጯሃሉ። አዝማሪው አልታከተም። ቆይቶ ቆይቶ ያንደኛውን ቀልብ ሳበ። ሰውዬው ጭቅጭቁን ትቶ ግጥም መስጠት ጀመረ። አፉ እንደመያያዝ ብሏል። ”በድሉ ተሰማ በል” አለው ጓደኛውን እያመላከተ። ”በድሉ ተሰማ ቁምነገር ገለባ” - ”ቁም ነገር ገለባ”፣ ”እጅ እግሩ ተቆርጦ አፉ ውሎ ይግባ።” የቤቱ ሰው ጣሪያ ድረስ አስካካ ...
ሳቁ ጋብ ሲል በድሉ ቀጠለ፤ ”ሰደበኝ ይሄ ሰው ወሬኛ ነህ ብሎ” - ”ወሬኛ ነህ ብሎ”፣ ”መምሰሉን ንገሩት ያረረ በቆሎ።” ሌላ ሳቅ። ያሁኑ ሳቅ ሳይሆን ቤቱ በንብ የተወረረ መሰለ ሃ ሃ ሃ ሃ ሃ ... እውነትም የሰውዬው የከሳ ጥቁር ፊት ከትላልቅ ቡግሩ ጋር ሲታይ ካረረ በቆሎ ለውጥ የለውም። አሥራት ሳቁን ማቋረጥ አልቻለም። ደግነቱ ሰውዬው የተባለውን የሰማም አይመስል አብሮ ይስቅ ነበር።
እኔ ጎን የተቀመጠው ሰው ጨዋታ ጀመረ። ”ይቅርታ አድርግልኝና ወንድ ልጅ ብዙ ማሽካካት የለበትም” አለኝ። እኔ ዝም። ቀጠለ ”ምንድነው? ይሄ ሁሉ ሳቅ ተገቢ አይደለም። እስቲ ምኑ ነው የሚያስቅ?” አሁንም ዝም። ”እኔ እንደውም ይቅርታ አድርግልኝና ...” ሰውዬው ይቅርታ አድርግልኝ ማለት እንደልምድ የያዘው ፈሊጥ መሆኑ ስለገባኝ ዝምታዬን አጠነከርኩ። በዚህ ላይ ሞቅ ብሎታል። አስራት ጣልቃ ገባ። ”ምናለ ይቅርታ ብታደርግለት?” አለኝ እየሳቀ።
”አላደርግም! ስንቴ ነው ይቅርታ የሚጠይቀኝ?” የተናደድኩ መሰልኩ።
”ሃምሳስ ጊዜስ ቢሆን ይቅርታ ምን ይጎዳሃል?”
የአሥራት በነገር ማያያዝ እነ አደፍርስን አስታወሰኝ። ወደ ጆሮው ጠጋ ብዬ ”እንደነ አደፍርስ ጥርስህን በመሃረብ ቋጥሬ ኪስህ እንዳልከትልህ” አልኩት። አስራት ጊዜ አልወሰደበትም ነገሩ ትዝ ብሎት ሳቁን ለቀቀው። ”ልጬ እንዳልጎርስህ”፣ ካካካ ... ቆልቼ ”እንዳልቅምህ”፣ ሃሃሃ ... ”ምናሴ ጩቤዬን አቀብለኝ ... ጩቤዬንንንንን ...” አሥራት በሳቅ ሞተ።
ስቆ ስቆ ሲያበቃ ”ስማ ለመሆኑ ጩቤውን ሰው ጋ እሚያስቀምጠው ለምን ነበር?” አለኝ እኔም በሳቅ ፍርስ አልኩ። ”ይገርማል እነሱ እኮ ያልሰሩኝ ስራ የለም።” ፊት ለፊት ላሉት የትያትር ቤት ሰራተኞች ታሪኩን ያወራ ጀመር። ... ”አንድ ቀን ደግሞ ምን አሉኝ መሰላችሁ?! ’ኑዛዜ ምናምን የምትጽፈው ነገር ካለ አሁኑኑ ጨርስ’ አሉኝ። ’ምን ልትሆን?’ ብዬ አንዱን ላንቀው ደረስኩ። ፍራቻ ሳይሆን የሚናገሩት ነገርና ድፍረታቸው ያናድደኝ ነበር። ’በቃ! አልቋል ያንተ ነገር’ አለኝ። ደግሞ እኮ እንደ ወዳጅ በጆሮዬ ነበር የሚነግረኝ።” ሁላችንንም በጅምላ ሳቅን። ያቺ ቀን በእንዲህ አይነት ሁኔታ አለፈች።
ከአስራት ጋር እንደዚህ አንዳንዴ እየተገናኘን እንጫወት ነበር። በዛው ዓመት አጎቴ አሰግድ ትንሽ ጊዜ ታሞ አረፈ። ኀዘኑ ለኔ ብቻ አልነበርም፤ ለአሥራትም ጭምር ነበር። የረጅም ጊዜ የስራ ባልደረቦችና ወዳጆች ሆነው ከርመዋል። ከዛን ጊዜ በኋላ ብሄራዊ ትያትር እርም ብዬ ቀረሁ። አሥራትንም እንደቀልድ ተለየሁት። በዚሁ አይነት ሁኔታ ተጨማሪ አመታት ተቆጠሩ።
****************
... ከእንግዲህ ተውኔቱ አቁሟል
ጨዋታዬ እንደሁ አክትሟል
ታርጓል በቅቶትል ተዳፍኗል
የውሂብ ገበያ ቆሟል
ግዞት ወርዷል ፍፃሜውን ተፈጣጥሟል
በመጋረጃው ተዘግቷል።
አሥራት አንለይ
የክፍ ለሀገር ስራዬ አዲስ አበባን የሚያዘወትረኝ አልነበረም። ብመጣም ጉዳይም ጊዜም ስለሌለኝ ብዙ አልቆይም። ያሁኑ አመጣጤ ግን በዓልን ያስከተለ ነበር። ኧረ! እንደውም ከበዓል በኋላም ዕረፍት አለኝ። በዚህ ሰዓት ከምሄድባቸው አንዱ ብሄራዊ ትያትር ይሆናል ብዬ ወስኛለሁ።
አምጨ አምጨ አካባቢው ላይ ተገኘሁ። የመምሩን ቤት በጎን አየት አድርጌ በማለፍ ላይ ነኝ። ምአፉድ ውጪው ላይ ቆሞ ጫማ ያስጠርጋል። ለማ ፒንሳ ፊት ለፊቱ ሆኖ እንደንጉስ አጫዋች እጁን እያወናጨፈ፣ እየቀረበ፣ እየራቀ፣ እየተቀመጠ፣ እየተነሳ ያወራል - አለፍኳቸው። ሰይፈ አርኣያ እና ጀምበሬ በላይ ከባድ ጨዋታ ይዘው በጎኔ አለፉ። አላዩኝም። መልካሙ ተበጀ በሃንኮክ በኩል ወደምታስገባው መንገድ ሲያቋርጥ አየሁት። መቼም እርጅናና እሱ አይተዋወቁም ቁልጭ እንዳለ ነው። ዘፋኝኛ አስተማሪ ለምን እንደማያረጅ አይገባኝም።
አሁን ደስ ደስ ያለኝ መሰለኝ። ወዲያው ደግሞ ኃይለኛ ፍራቻና መረበሽ ወረረኝ። ዓይኔን ጨፈን አድርጌ ከፈትኩ። በዛች ቅጽበት አሰግድ ፊቴ መጥቶ ድቅን አለ። እስከ ሳቁ፣ እስከ ጨዋታው፣ እስከ ሽበቱ፣ በአካል የመጣ መሰለኝ። ወይ ጣጣ! ከቤት ስሸሸው ቀድሞኝ መጥቶ ኖሯል፣ ምነው ባልመጣሁ፣ ቡቡ ልቤ ይበልጥ ተላወሰ። ልመለስ አሰብኩ፤ እግሬ ግን መራመዱን አላቆመም። በደመነፍስ ሳዘግም ከአንጋፋዎቹ የብሄራዊ ትያትር ሰራተኞች መካከል ከአንደኛው ጋር ፊት ለፊት ተገናኘን። መቸም የጥበብ ሰው አንቱ አይባል ጋሼን ጨምሬ ሰላምታ አቀረብኩ። የት ጠፍቼ እንደከርምኩ ጠየቀኝ። እየተነጋገርን ካካባቢው ሳንርቅ እስር ያለችው ቡና ቤት ምናምን ይዘን ቁጭ አልን።
”እንዴ ነህ ጋሼ?”
”አለሁ! ይሄው እንደምታየኝ ነኝ።” የሸበተ ጎፈሬ ፀጉሩን በአራት ጣቱ ወደኋላ አረሰው።
”እርጅና መጣ መሰለኝ”
”የት ይቀራል፤ ይሄው እዚሁ እየሰራሁ፣ እዚሁ እየዋልኩ፣ እዚሁ እየተነሳሁ፣ እዚሁ እየተቀመጥኩ፣ እንደተደገመበት በግ ዙርያውን ስንቀዋለል ዕድሜዬን ገፋሁት” አለኝ። አነጋገሩ እንደቀልድ ቢሆንም የሚያሳብቅበትን ተስፋ መቁረጥ ሊደብቀው አልቻለም። እንደማዛጋት አለና ”እሬሳዬም ከዚሁ ሳይወጣ አይቀርም” የምትል አከለ።
”መሞቻውን ማን ያውቃል ብለህ ነው ጋሼ?! አንተ እንደውም ዕድለኛ ነህ። ከሙያህ ሳትረቅ፣ ከምትወደው ሳትለያይ ኖርክ። እግዚአብሔርን ማመስገን ይገባሃል። ጤነኛ ነህ፣ የዕድሜ ባለጸጋም ነህ፣ …” ላበረታታው ፈለኩ።
”እሱስ ልክ ነህ ይመስገነው! ኧረ ይመስገነው!” አለ እንደ እግዚዎታ ሁለት እጁን ወደላይ ቀስሮ፣ አይኑን ሰቀለ። ትያትር የሚሰራ መሰለኝ። የመጣብኝን ሳቅ እንደመሳል ብዬ አጠፋሁት። በመሃል ጨዋታ ቀይረን ስናወራ ከቆየን በኋላ አሰግድ ተነሳ፣ መቼም ብሸሸውም አይሸሸኝ።
”ወንድምህ ሞገደኛ ነበር” አለኝ።
ሞገደኝነቱን አውቃለሁ። ከሱ አፍ የሚወጣው አጓጓኝ ”እንዴት?” አልኩት።
”አንድ ጊዜ አንድ አዲስ ሹም መጡ። ወፍራም ናቸው። ይሄ እኛ የምናውቀው ውፍረት እንዳይመስልህ፣ አህያ እስከጭነቱ የዋጡ ነው የሚመስሉት።” ከዚህ በኋላ ምንም ሳይለኝ ብቻውን ይስቅ ጀመር። ሳቁን እስኪያቆም በፈገግታ ቆየሁ። ቀጠለ …
”ሹሙ የሁላችንንም የግል ፋይል እያስቀረቡ ሲመረምሩ ቆዩ። በመጨረሻ ስብሰባ ጠሩን።” አሁንም ትንሽ ብቻውን ሳቀ። ”ከየት መስሪያ ቤት እንደመጡ፣ ለረጅም ጊዜ በዚህ ስራ ላይ መቆየታቸውን፣ ያደረጉትን የስራ ክንዋኔ፣ አሁንም በዚህ መስሪያ ቤት እንዲደረግ የሚፈልጉትን፣ አንስተው አወሩ። በስተመጨረሻም ጭቅጭቅና ንትርክ እንደማይወዱ ተናገሩ። ሁላችንንም በቀና መንፈስ መስራት እንደሚገባን አክለውበት አሰናበቱን። አሰግድ ፋይሉን ወስደው እንዳደሩበት ስለሚያውቅ ተናዶባቸዋል። መቸም ሲፈጥረው አለቃ አይወድም። እነሱም አይተኙለት።”
”ይሄ በሆነ ሦስተኛ ቀን፤ አሰግድ የደሞዝ ብድር ማመልከቻ ጽፎ አቀረበ። ሹሙ ማመልከቻውን ያነበቡት በፈገግታ ነበር። ’ሙክት መግዣ ምናምን ያልከው እኔ ምንስ ብትገዛበት ምንቸገረኝ ብለህ ነው?’ ኪኪኪኪ … አይ! አቶ አሰግድ ማመልከቻውን አልመሩትም እንደሚፈቀድለት ነግረው አሰናበቱት።”
”ሹሙ ከትንሽ ቆይታ በኋላ አይናቸው ማመልከቻው ላይ አረፈ። ”ለአቶ” በሚለው ምትክ ”ላቶ” ነበር ብሎ የጻፈው።” ሁለታችንንም ለረጅም ጊዜ ስንስቅ ቆየን። ሳቃችን ጋብ ሲል ጨዋታውን ቀጠለ፤ ”ሹሙ እንደሰደባቸው ገብቶአቸው እርር ድብን እንዳሉ ዋሉ። እንደ ውሽማ መርዶ ነገሯን ቢያፍኗትም አፈትልካ ወጥታ ተሰማች።” እንደገና ሳቅን።
ከሱ ጋር እየሳቅሁ አስራትን ማሰብ ጀምሬአለሁ። የመቀማመሻ ሰአትም እየተቃረበ ነው፤ ላገኘው ቸኮልኩ። ጨዋታው ናፍቆኛል፣ አቤት ስንት ጊዜው ካየሁት። አሁንም እየተናደደ ይሆን? የሰይጣን ልጆች ... ጥፍራም ጭራቆች ... እንደው እንደው እንደው መቼ ይሆን እውነትን ምናገኛት? ማማረሩም፣ ንጭንጩም ናፈቀኝ። ”አስራት ደህና ነው? አሁን አገኘው ይሆን?” ጠየኩ።
ሰዬው ጸጥ ብሎ ቀረ። አየሁት። አጎነበሰ፣ ፊቱ አመድ መሰለ። ”ምነው? ጋሼ ምነው?”
”የሰማህ መስሎኝ ነበር እኮ።”
”ምኑን?”
”የአሥራትን ማረፍ”
ከዛ በኋላ የሚለውን አልሰማሁትም። የሆነ ነገር ያወራልኝ እንደነበር አስታውሳለሁ። ማጀራቴን አንድ ነገር ጨምድዶ ያዘኝ፣ ጉሮሮዬ ላይ ቆሮቆንዳ የተወተፈብኝ መስሎ ተሰማኝ፣ መላ አከላቴ ወደ ድንጋይነት የተቀየረ ያህል ከበደኝ። እንባ አልፈሰሰኝም። በምትኩ ላብ ነበር ድፍቅ ያደረገኝ። እንዳቀረቀርኩ ብዙ ቆየሁ። ”ለመሆኑ ምን ሆኖ ሞተ? ታሞ ነበር?”
”የለም እራሱን አጠፋ።”
”ምነው? ምነው? ጋሼ እናንተ እያላችሁ ...”
”እንዴ! ሞት’ኮ በሽምግልና አይመጣም። ደሞም እኮ የኛ ሞት እነሱን አያድንም” እንደመወራጨት አለ። ሃሳቤን ያየው በሌላ መልኩ መሆኑ ገባኝ።
”እንደሱ ማለቴ አይደለም! ብትመክሩት ... ብታጽናኑት ...”
”አዬዬ ... ሰው ሞቱን መች አማክሮ ይሞታል። ተውኝ እባክህ አሥራት በከንቱ ቀረ ...”
እንባዬ በዓይኖቼ ሞሉ፣ መርዶ አርጂዬ አላናጠፈኝም። እንዲወጣልኝ ፈልጎ ዝም አለኝ። አልቅሼ አልቅሼ ሲበቃኝ ቀና ብዬ አየሁት። አያለቅስም። አልቅሶ አልቅሶ እንደበቃው ገባኝ። ለስንቱ አልቅሶ ይቻለው። ፊቱ ግን የኀዘን ጥላ እንደለበሰ ነው። ኀዘን ብቻ አይደለም ቁጭት ጭምር እንዳለው ያስታውቃል። ሁሉም የግዜሩን ሞት በተገቢው ሁኔታ መሞታቸውን ልቡ ሊቀበል አልቻለም። እንዴት ይቀበል?! የመጨረሻ ዘመናቸውን ችግር አይቷል። እባዶ ቤት አብሮ ተኮማትሮ አድሯል። እርሃባቸውን ተርቧል። ህመማቸውን ታሟል። መታከሚያ አጥተው ሲሰቃዩ ተመልክቷል። ... እናም ሞታቸውን መቀበል አልቻለም።
ሁሉንም በስም መጠየቅ ድፍረት አጣሁ። ”ሌሎቹስ ደህና ናቸው?” ማለት ግን ነበረብኝ።
ትንሽ ካማጠ በኋላ ”አሉ። በጡረታም፣ በሞትም፣ በህመምም ተመናምነን ጥቂቶች ተርፈናል” አለኝ። አቤት! ይሄ እንኳን ከሆነ ስንት ዘመኑ ...
ይሄ ሰው ዛሬም በህይወት አለ። ይሄን ጥያቄ የጠየኩት አሁን ቢሆን ኖሮ፤ ”ከኔና መናፈሻ ካለው የአንበሳ ሃውልት በስተቀር ማንም የለም!” ብሎ እጁን አራግፎ እንደሚነግረኝ እርግጠኛ ነኝ። አዎን! ከዛ ውጪ ምንም ሊለኝ አይችል፤ ማን አለና ይዋሸኝ።
*********************
... ያችን ፎቶ ብቻ አምጣልኝ
በቅርስነት የማኖር ነኝ
በውርስነት የምትሸኘኝ
የሞት ሸኝ!!
እሷን ብቻ እንድትሰጠኝ
ሌላማ ምን ቢኖረኝ ...
አሥራት አንለይ
ዛሬ የአሥራት አንለይ የግጥም መድብል በእጄ ገባ። ዕድሜ ይስጣት ባለቤቱ እቴነሽ አበበ ናት ያሳተመችው። አንዱም አልቀራት፤ ትካዜ ይዞት የሚስላቸው ሥዕሎች ሁሉ አብረው ተካተዋል። አርዕስቱ ”የመጀመሪያይቱ” ይላል። በጀርባው ”አሥራት ለአሥራት” የሚለው ግጥሙ ተቆርጦ ሰፍሯል፤ ከስሩ ”ሀ ሁ በስድስት ወር” ላይ እንደ አያያ ቃሌ ሆኖ ትያትር የሰራበት ፎቶ አርፏል። መጽሐፉን ገና አላነበብኩትም፤ ከዛ በፊት ይሄን ትዝታ መጻፍ ነበረብኝ።
********************