ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ, Journalist Demissie Damteመስፍን ነጋሽ

በእኔ እድሜ የደምሴን ያህል አገራዊ የስፖርት ስሜትን፣ በተለይ እግር ኳስን ወደ ልባችን ያቀረበ ጋዜጠኛ አልነበረም። እንደዛሬው ኢንተርኔት መገልበጥ ማእረግ በማያሰጥበት ዘመን። በሳምንት ሁለትና ሦስት ቀን ስታዲየም በምገባበት፣ ሁለቱን ሙሉጌታዎች፣ እነሚሊዮን በጋሻውን፣ እነቸርኬን (ጊዮርጊስ)፣ እነሙሉዓለም እጅጉን (ጦሩ)፣ እነአብዲን (መድን)፣ እነአፈወርቅን (እርሻ)፣ ያ ደሞ የአየር ኀይሉ አጥቂ ማን ነበር? ... ረሳሁት ማለት ነው? (ይልቅ ተከላካያቸው መሰለ፣ ጆን ቴሪን ቁጭ ነበር)፣ ከዛ ደሞ ... ይህ ሁሉ ሲሆን ብቸኛው የስፖርት መረጃ ምንጫችን ደምሴ ነበር፤ እርግጥ ሌሎችም ጋዜጠኞች ነበሩ በተለይ እነ ... ማነው ... ይንበርበሩ መሰለኝ። ቢሆንም ደምሴ የተለየ መስህብ ነበረው።

 

 

 

 

ከሁሉም የማልረሳው የደምሴ ገጠመኝ በ1980 የምስራቅና መከካለኛው አፍሪካን ዋንጫን ያሸንፍን (የበላን) ጊዜ የሆነው ነው። ብዙ ሰው የሚያስታውሰው ጨዋታው በፍጹም ቅጣት ምት ማለቁንና ዳኛቸው ደምሴ (ደምሴ "ዳኙ" እያለ ያቆላመጠው፣ አመለ ሸጋው ተጫዋች) የመጨረሻውን ምት አስቆጥሮ ማሸነፋችንን ነው። ለፍጹም ቅጣት ምት የደረስነው ግን 1 ለ 0 ስንመራ ቆይተን ባለቀ ሰዓት ባገባነው ጎል ነበር። ታዲያ ብዙ ተመልካች በመበሳጨቱ ጨዋታው ሳይጠናቀቅ መውጣት ጀምሮ ነበር። ለዋንጫ መድረሳችን የፈጠረው ስሜት ከመናሩ የተነሣ፣ በገዛ ሜዳችን ሌላ ሲሸለም አናይም ብለው ነው። ቀኑ ገብርኤል ነበር፤ ብዙ ሰው ተስሎ እንደነበርም አስታውሳለሁ።

 

እኔ መጨረሻውን ሳናይ አንሄድም ካሉት ወገን ሆኜ ቆየሁ፤ ጥቂት ጓደኞቼ ግን ለመውጣት ጉዞ ጀመሩ፤ አንዳንዶቹም ከወጡ ቆዩ። በመጨረሻ (በትክክል አስታውሼው ከሆነ) "ሙሉዓለም ያሻማትን፣ ገ/መድኅን ኀይሌ በጭንቅላት ገጭቶ ከመረብ አዋሃዳት" የምትለዋ ዝነኛዋ የደምሴ የምስራች መጣች። መቼም በዚያ ደቂቃ በስታዲየሙ የተሰማውን ድምጽ መቼም አልረሳውም፤ እስከዛሬም አቻ ወይም መግለጫ አላገኘሁለትም። "ተመልካቹ ጮኸ" ማለት ተርታ ንግግር ነው፤ ቋንቋ ከስሜት ጠቦ የሚገኝበት።

 

ለማንኛውም ጎሉ ገብቶ፣ እኩል ሆነን፣ ለፍጹም ቅጣት ምት በቅተን፣ አሸነፍን። መንጌም ደስ ብሏቸው ዋንጫውን ለአገራቸው ልጆች ሰጡ፤ የተሸናፊዎቹ "አባት"ና አገር በኋላ መጠጊያ እንደሚሰጡዋቸው እንዴት ይጠርጥሩ። (እኛ ሰፍር ስታዲየም ሊሰራ ቃል የተገባውም ያን ጊዜ ነበር መሰለኝ።) ታዲያ ጨዋታው ሳያልቅ የወጣው አንዱ የት/ቤት ጓደኛችን ጎሉን የሰማው ታክሲ ውስጥ እንደገባ ኖሯል። ግን በደንብ አልሰማም። ከዚያ "የውይይቱን" ወያላ ይጠይቀዋል፤ "ማን አገባ በናትህ?" ወያላው መለሰ "ደምሴ ዳምጤ"። እሱ ገ/መድኅንን የት ያውቀዋል፤ ደምሴ ዳምጤን እንጂ።

 

በ60 ዓመት መሞት እኩለ ቀን አለፍ እንዳለ እንደመሞት ነው። እርግጥ ደምሴ አመሻሽ ላይ በ90 ቢሞትም ኖሮ ማዘናችን አይቀርም ነበር። ለማንኛውም፣ ድሃዋ አገር ከሰጠችው ያላነሰ፣ መልሶ ሰጥቷት ስለሞተ ሕይወቱ የባከነ አልነበረም።

 

ደምሴ፣ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን እንደጦር በሚፈሩ ሁለቱ አምባገነኖች ዘመን በስፖርት ጋዜጠኝነት ሰርቷል። ምን አጋጥሞት ይሆን? የጫረው ነገር ይኖር ይሆን? ደምሴ ያቺ የገ/መድኅን ጎል ምንጊዜም ያንተ መዘከሪያ ናት፤ የታክሲ ረዳቱ ያጸደቀልህን ጎል አጽድቄ አስታውሳለሁ፤ ከልጅነት የኳስና የስታዲየም ጓደኞቼ ጋራ።

መስፍን ነጋሽ/ለ - www.adebabay.com

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ