እኛ እና ወላጆቻችን (ያሬድ ክንፈ)
ያሬድ ክንፈ ከስዊድን
ጌታው! ሀገር አማን ናት ወይ? … ስለሀገር ቤቱ ኑሮ ልጠይቅህ አልደፍርም። ምክንያቱም - በቀደም ዕለት እዚህ ስዊድን ከሚኖር ወዳጄ ጋር በስልክ ስንጠርቅ፣ ሀገር ቤት ደውሎ እናቱን “እንዴት ነሽ? … ኑሮስ እንዴት ነው? …” ብሎ ይጠይቃታል፤ እናቱም “… አዬ ልጄ! እጅግ በጣም ጥሩ ነው! በጣም! … በ-ጣ-ም! …” ብላ ትመልስለታለች። ልጅም የእናቱን ጠባይ ስለሚያውቅ “እንዴት?” ብሎ ይላታል። እናትም “ዛሬ ከነገ እንደሚሻል እርግጠኛ ስለሆንኩ” ብላ ሀገር ቤት ያለው ነገር እየባሰ እንጂ እየተሻለ እንደማይሄድ አስረግጣ ስለነገረችው፤ እኔም ከወዳጄ እናት ተምሬ ሀገር ቤት ያለን ሰው ስለኑሮ መጠየቅ እርም ብያለሁ። አንተንም ባለቤትህንም ጭምር።
የሀገራችን ሁኔታ እየባሰበት እንጂ እየተሻሻለ አልሄድ ያለው ለምንድን ነው? ይሄ መቼም የብዙዎቻችን ጥያቄ እንደሆነ እርግጥ ነው። ብዙ ምክንያት መደርደር ይቻላል። ካለምንም ማጋነን አብዛኞቹ ምክንያቶች ትክክል ይሆናሉ ብዬ አምናለሁ። ባይሆኑም ለትክክለኝነት ቅርብ ናቸው። ከተሰደድሁ ወዲህ የአውሮጳውያኑን በተለይም የስዊድናውያንን ነገር በተቻለኝ መጠን ከእኛ ጋር አወዳድረዋለሁ። በአብዛኛው ጊዜ እኛ በኢትዮጵያችን የለመድነውና የምንከተለውን ነገር ከእነሱ ጋር ሳወዳድረው የእኛ ስህተቶች በጣም ጎልተው ይታዩኛል። ለምሳሌ ወላጆቻችን እና ልጅ አስተዳደጋቸው።
የዛሬው ጦማሬ/ደብዳቤዬ ለአንተና ለባለቤትህ ስለሆነ በጋራ አንብቡት። በዚህ ጦማሬ የማነሳቸው ነገሮች በቀጥታ አንተን/አንቺን የማይመለከቱ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ስጥፍ ግን አንተ/አንቺ ብል ቅር እንዳይላችሁ - አደራ! እናንተን ባይመለከቱ እኔን፣ አክስቶቻችሁን አጎቶቻችሁንና ልጆቻቸውን፣ ዘመዶቻችሁን፣ ጎረቤቶቻችሁንና ልጆቻቸውን፣ … እንደሚመለከቱ እንዳትዘነጉ። ሌላው ነገር ደግሞ የእናንተንም ሆነ የእኔን ወይንም ሌሎች ወላጆችን ለማጣጣልና ለማጥላላት አይደለም ዓላማዬ። ወደ መጨረሻ ላይ እመጣበታለሁና ታገሱኝ።
ከሁሉ በፊት ስዊድን ውስጥ ልጃችሁን መትታችሁ ብትገኙ ፍርድ ቤት ቀርባችሁ ከመቀጣታችሁ ባሻገር ልጃችሁን ትቀማላችሁ። እዚህ ሀገር ከማንኛውም የሰው ልጅ በሙሉ ቅድሚያ የሚሰጠውና ከፍተኛውን ማዕረግ የተጎናፀፈው “ልጅ” ነው። እንደ ሀገር ቤት ልጅ ማሳደግ ቀላል ነገር አይደለም። ምክንያቱም ከባድ ኃላፊነትን የሚጠይቅ ነውና። ስለዚህ ልጅ ዕቅድ ተይዞለት የሚወለድ እንጂ፤ እንደ ሀገር ቤት ጊዜያዊ የወሲብ ስሜትን ለማርካት ሲባል ተፀንሶ ከተወለደ በኋላ “በድሉ” የሚል ስም የሚወጣለት አይደለም። “ምና’ባቱ! በድሉ ያድጋል!” ብሎ ነገር ስዊድን ውስጥ አይሠራም።
የእኛ ወላጆች ምግብ አንበላም ስንላቸው ስለምግብ ጥቅም አስረድተው እኛን ከማሳመን ይልቅ፤ ጥፊያቸውና ኩርኩማቸው ይቀድም ነበር። አሁን ሳስበው ያስቀኛል - የንዴት ሣቅ። እስቲ አሁን በሞቴ! ልጅ እያለን ምግቡ ሳይጥመን ቀርቶ ወይንም በሌላ ምክንያት “በቃኝ! አልበላም” ስንል የሚሞረሙረን እኛን ሆኖ ሳለ፤ ወላጆቻችን ለምንድን ነበር ይቀጠቅጡን የነበረ? “እኔ ለእናንተ ብዬ የሰው ፊት እየገረፈኝ የምሠራው ከርሳችሁን ለመሙላት ብዬ ነው ‘ንጂ …” ብለው የተለመደ ዱላቸውን ያሳርፉብን ነበር። ልክ እኛ ባንወለድ ኖሮ እነሱ ሳይሠሩና ሳይለፉ ይኖሩ ይመስል …
የምግቡ ቀላል ምሳሌ ሊሆን ይችላል ብዬ ነው ያነሳሁት። ወላጆቻችን የሚፈልጉት፤ ነገር ግን እኛ የማንፈልገው አብዛኛውን ነገር ካለፈቃዳችን በልጅነታችን እንድናደርግ ያስገድዱን የነበረው በዱላ ብቻ ነበር ብል ማጋነን አይሆንብኝም። … ለምን? … አያቶቻችን እየገረፉ ስላሳደጓቸው? … የአያቶቻችንን ቂም እኛ ላይ ሊወጡ ስለፈለጉ? … እናንተም የምትገምቷቸውን ጨምሮ ሁሉም መልስ ናቸው።
የቤት ውስጡ ሳያንሰን ትምህርት ቤት ስንሄድ ከጥበቃ ጓዱ ጀምሮ እስከ ርዕሰ መምህሩ (ዳይሬክተሩ) ድረስ ከእጃቸው ዱላ ተለይቷቸው አያውቅም። ባለፍን ባገደምን ቁጥር ሾጥ ሊያደርጉን ሁሌም በተጠንቀቅ ዝግጁ ነበሩ። ለት/ቤት ዩኒት ሊደርነት የሚመረጠው አስተማሪማ በተማቺነቱና በክፋቱ የተጨበጨበለትና ተወዳዳሪ የማይገኝለት ነበር። ከሁሉ የሚገርመኝ ደግሞ ጎረቤት ተብዬዎች ናቸው - ያልወለዱትን ልጅ “ለመቅጣት” ሲጣጣሩ። … እንግዲህ ጎረቤቶች አልወለዱን፣ አያስተዳድሩን፣ አያበሉን፣ አያጠጡን፣ … ምን ልሁን ብለው ኑሯል እንዲያ ክፉዎች የነበሩት? …
አንዳንድ ወላጆችማ ለኑሯቸውና ለሕይወታቸው መዛባት በቀጥታ ተጠያቂ የሚያደርጉት የገዛ ልጆቻቸውን ነው። እናትሽ “አንቺ ባትወለጂ ኖሮ እንዲህ ያለ መከራና ችግር ውስጥ ባልተዘፈቅሁ!” ብላ መወለድሽን እንድታማርሪ አድርጋሽ አታውቅምን? አንተንስ ቢሆን አባትህ ብይ (ጊሮ) ስትጫወት አግኝቶህ በዚያች ስንትና ስንት ዓመታት ከወገቡ ላይ ባላወለቃት ወዛምዋና አንድዬዋ የቆዳ ቀበቶው ነፍስህና ስጋህ የተላቀቁ እስኪመስለህና መተንፈስ እስኪያቅትህ ድረስ ሲገርፍህ … ምርር ብሎህና ግራ ተጋብተህ “ነዝንዣችሁ ነው ወይንስ ማመልከቻ አስገብቼ የወለዳችሁኝ?” የሚል ጥያቄ ተጭሮብህ አያውቅምን? …
ስዊድናውያን ልጃቸው ምግብ አልበላ ሲል መጀመሪያ ለምን እንደማይበላ ይጠይቁታል። የቀረበለትን የምግብ አይነት እንደማይወደው ከነገራቸው ከቻሉ ሌላ ይሠሩለታል፤ ካልቻሉ ይተዉታል። ሌላ ቀርቶ አይጨቃጨቁትም። እዚህ ጋር ሌላው ልብ እንድትልልኝ የምፈልገው “ስዊድናውያን” ብዬ ስልህ ሁሉም ሙሉ ለሙሉ አንድ አይነት ናቸው ልልህ ሳይሆን፣ አብዛኛውን ስዊድናዊ ለማለት ፈልጌ ነው።
ስዊድናውያን የጎረቤቶቻቸውን ልጆች ለመቅጣት፣ ለመሳደብ፣ ለመማታት፣ … አይቃጡም። የጎረቤት ልጅ ሲያጠፋ ካዩ አላስችል ካላቸው በቀጥታ ለወላጅ ሄደው ይነግራሉ። ጎረቤታቸው የገዛ ልጁን ሲመታ፣ ልጁ ላይ ሲጮህበት፣ ልጁን በአግባቡ እንደማይንከባከብ፣ … ካዩ በቀጥታ ለፖሊስ ወይንም ይህንን ጉዳይ ለሚከታተሉ የመንግሥት አካላት ያመለክታሉ። ሲያመለክቱ ደግሞ ማንነታቸውን አሳውቀውና በግልፅ ነው።
አስተማሪ ዱላ ይዞ የሚውልበት የስዊድን ት/ቤት ከነጭራሹ የለም። ተማሪውን የመታ ብቻ ሳይሆን ለመምታት የተንደረደረና የተጋበዘ አስተማሪ ከመምህርነት ዓለም ዕድሜ ልኩን ይሰናበታታል።
የየትኛው ጓደኛችን እናት ነበረች ‘ስትናደድ’ “የኔ መድኃኒዓለም ክርስቶስ ድፍት ያድርግህ! … አልልህም” ብላ የገዛ ልጇን ትለው የነበረችው? ረግማው ስታበቃ “አልልህም” የምትለዋን ቃል ታክልበታለች። በጣም መናደዷን ለመግለጽ ደግሞ “መጨረሻህን ያሳየኝ! … የመኪና ራት ያድርግህ! … ዕድሜህን ያሳጥረው! … ባጭሩ ይቅጭህ! …” … እባክህን ከእነኛ የሚያማምሩ እርግማኖችዋ የረሳሁት ካለ አስታውሰኝ። እስቲ አሁን መለስ ብላችሁ አስቡት! ያ ጓደኛችን በዚያን በጨቅላ ዕድሜው ያለ አዕምሮው ያንን ሁሉ ዕርግማን ይችላልን? ዕርግማንን በተመለከተ ደግሞ በዕድሜ ገፋ ያሉት ጎረቤቶችም ሆኑ የማኅበረሰቡ አባላት ገንዘብ ስለማያወጡበትና በነፃ ስለሆነ ነው መሰለኝ ለሕፃናት በጆንያ ማስታቀፍ ይወዳሉ። ስዊድን በቆየሁባቸው ዓመታት ልጁን የሚራገም ወላጅና ተራጋሚ የዕድሜ ባለጠጋም ይሁን የዕድሜ ደሃ አይቼም ሰምቼም አላውቅም።
አሁን ደግሞ ከዱላ ወደ ፍቅር እናምራ። … እናትና አባትሽ በሕይወት ዘመንሽ በሙሉ ስንት ጊዜ ነው እቅፍ አድርገው “እወድሻለሁ!” ብለው ያሉሽ? … የልጅነትሽን እኔ ላስታውስሽ … በየቀኑ ሲገርፉሽ ነበር እንጂ አፍ አውጥተው “እወድሻለሁ!” ብለው ያቀፉሽን ጊዜ አላስታውስም - አብሮ አደጌ’ም አይደለሽ። … አንተም ብትሆን ያው ነህ። እኔ ረስቼው ከሆነ አንተ አስታውሰኝ … ነፍሳቸውን ይማርና! አባትህ የመጨረሻ ሰዓታቸው መሆኑን ባወቁበት ጥቂት ቀናት አልጋ ላይ በዋሉ ጊዜ እንኳን “ልጄ እወድሃለሁ!” ብለውሃልን? … አይመስለኝም!
እኔ እዚህ ከመጣሁ ከተማርኳቸውና ከኮረጅኳቸው ነገሮች አንዱ ይሄንን ነው። አሁን እናቴን ስልክ ስደውልላት “እወድሻለሁ!” እላታለሁ። መጀመሪያ ሰሞን ግር ብሏት ነበር መሰል ምላሽዋ ዘግየት ብሎ ነበር የሚደርሰኝ። በኋላ ላይ ግን ፍጥነት እየጨመረች መጥታ፣ አሁን የመጨረሻ ፍጥነቷን ተጠቅማ “እኔም እወድሃለሁ!” ትለኛለች። በልጅነቴ ከጎደሉብኝ ነገሮች አንዱ ይኸው ነበርና አሁን ለማካካስ እየጣርኩ መሆኔን በዚህ አጋጣሚ ሳልነግራችሁ አላልፍም። ለዚህ ነው አንቺንም ባለፈው የደወልኩልሽ ጊዜ፤ አቅፈሽው የምትተኝው ባልሽ በየቀኑ “እወድሻለሁ!” ብሎ እየሳመና እያሻሸ የማይነግርሽ ከሆነ፤ አንቺ ‘ዓይን አውጪና’ አቀፍ - ሳም አድርገሽ “እወድሃለሁ!” በይው ያልኩሽ። … አልነገረችህም እንዴ?
ብዙ ጊዜ ወላጆቻችን ፍቅራቸውን ይገልፁልን የነበረው ለእኛ በልጅ አዕምሮ በማይገባ መንገድ ነበር። ወላጅነታቸውንና ወላጅ ለአብራኩ ክፋይ የሚኖረውን ፍቅር ለመካድ ከነጭራሹ አልዳዳም። እንኳን የሰው ልጅ እንስሳትን መመልከቱ በቂ ነውና። ቢሆንም ግን ወላጆቻችን እየገረፉን፣ እየረገሙን፣ እያስፈራሩን፣ በነፃነት የምንፈልገውን እንዳንጫወት፣ የምንፈልገውን እንዳናደርግ፣ የምንፈልገውን ጓደኛ እንዳንይዝ፣ የምንፈልገውን ጫማና ልብስ ሳይገዙልን፣ የምንፈልገውን የትምህርት መስክ እንዳንመርጥ ሲጫኑን፣ … እነሱን በተስማማቸው እንጂ የእኛን ፍላጎት፣ አቅምና አዕምሮ ባላገናዘበ መልኩ ማሳደጋቸው ተገቢ ነበር ብዬ አላምንም። ይህ አስተሳሰቤ ከስደት የተገኘ ሳይሆን፣ አብሮኝ የተፈጠረ መሆኑን ለአንተም ሆነ ለአንቺ ማስረዳት አያስፈልገኝም፤ ታውቁታላችሁና።
ይሄን ያህል ወደኋላ ተመልሼ ልጅነታችንን፣ አስተዳደጋችንንና ወላጆቻችንን ያነሳሁት ከሁሉም በላይ ወላጆቻችን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ምን ያህል ነፃነታችንን ገፍፈው እንዳሳደጉን ለማሳየት እና ይህንን የሠሩትን ስህተት እኛም እንዳንደግመው እንማማር ዘንዳ ነው። የእኔና የእናንተ ትውልድ እንደናንተ ልጅ በመውለድ አዲስ ወላጆች የሆኑና፣ እንደኔ ያልወለዱም አሉ። የእኛም ትውልድ ወግ ደርሶት “ወላጅ” ለመሰኘት በቅቷልና፣ … መጭውን ትውልድ በዱላ ሳይሆን፤ በመግባባት፣ በመነጋገርና በውይይት የሚያምን ለማድረግ እኛ መሠረቱን መጣል አለብን ለማለት ነው ከላይ ማስታወስ የማትፈልጉትን ሁሉ ያነሳሁባችሁ።
እኛ በገዛ ወላጆቻችንና ማኅበረሰባችን ተበድለን አድገናል። “የልጆች ተበድሎ ማደግ በኛ ይብቃ!” ልንል ይገባል። እኛ ልጆቻችንን በነፃነት አሳድገን መጭውን ትውልድ ካላስተካከልነው፤ ያ ያልተስተካከለ ትውልድ ሥልጣን ላይ ወጥቶ ሀገር ማስተዳደር ሲጀምር እሱም እንደዘመኑ ባለሥልጣናት ቂመኛ እንደማይሆን ምን ማረጋገጫ አለን? … ሌላም መፈክር አለኝ። እኔን ተከትላችሁ በሉ “ቂመኛነት በወላጆቻችን ይብቃ!” … አንድ ላይ! ... “ቂመኛነት በዘመኑ ባለሥልጣናት ይብቃ!” ... አንድ ላይ በሉ ‘ንጂ! … “ቂመኛነት በእኛ ይብቃ!” … አሁንም አንድ ላይ! … “ቂመኛነት …!”
ጌታውና እመቤቲቱ! አደራችሁን ለእናቴም ይህቺን ጦማሬን አስነብቧት፤ “ቂመኛነት እንኳን ሰው፤ ሀገርም ያጠፋል” ብላ ያስተማረችኝ እሷ ናትና። ሄይዶ! (በስዊድን አፍ “ቻዎ!”)