ደሞዝ፣ መንጃ ፈቃድና ንግግር
አባ ጅፋር
ሰው ይናገራል። ፍሬ ነገር የሆነ፤ ገለባ የሆነ ነገር ይናገራል። ገለባብም ጥቅም አለው። ከብት ይመግባል። ከብቶችም ሆዳቸው ይሞላል።
ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ሴትዮ ተናገሩ። ሰኔ እና ሰኞ ከመገጣጣሙ በፊት "ቀዳሚ" የሚል ቅጽል ከሥማቸው በፊት ይነገርላቸው ነበር። ይኸ ቅጽል እንዴት እንደተሰጣቸው ሳስብ ሳስብ ሳስብ ... ቆየሁና ተገለጠልኝ። መድኃኒዓለምን! ለወሬ፣ ለነገር፣ ለምንትሥ ... ቀደም ... ቀደም ... ቀደም ... ቀልቀል ... ቀልቀል ... ስለሚሉ ነዋ! አሊያማ አንድ ኮስታራ ባል፤ ስምንት ልጆች፤ የኩሽና ሥራ ... ሥንቱን ልጥራ ... ይህንን ሁሉ ችለው እየሰሩ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩ ሴቶች ቀዳሚ ሳይባሉ ... እሺ "እነሱማ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸውና ሚሊዮን ሴቶችን ቀዳሚ ማድረግ አይቻልም" ከተባለ ... ታዲያ እንደማንኛውም ሃገር ለምን የርዕሰ ብሄሩ ሚስት "ቀዳሚ" አልተባሉም? ሚስት የላቸውም? "አይ! አንተ ደግሞ እሳቸውን'ኮ እዚያ ጎለትኳቸው እንጂ ርዕሰ-ርዕሳኑማ እኔ ነኝኮ" ማለቱ ነበር እገሌ? ሰኞና ሰኔ ሳይገጣጠምበት በፊት?
የሆነስ ሆነና ሴትዮዋ ከዕለታት አንድ ቀን ሲናገሩ ሰማሁ።
"እገሌ'ኮ መንጃ ፈቃድ አልነበረውም።" ሲሉ ተናገሩ።
እኔም ሰማሁ ... "እገሌ'ኮ መንጃ ፈቃድ የሚያስፈልገው የመገናኛና የትራንስፖርት መሥሪያ ቤትን ሕግ ተከትሎ መንዳት ሲፈልግ ነው። ሰውየው ሕግ ተከትሎ ሰርቶ ያቃል'ንዴ?" ብዬ ሰማሁ።
ሴትዮዋም ቀጠሉ ...
"እጌሌኮ ደሞዙ ደቃቅ ነበረች። ለዚያውም ለምንወደውና ለሚወደን ድርጅታችን መዋጮ ወጭውጮ፤ የምትቀረው ለሽንኩርት መግዣም አትበቃኝም።" ሲሉ አማረሩ።
እኔም ሰማሁ ... "አቤት! አቤት! አቤት! ... እገሌ ለካ ገብጋባ ነበር?! እንዴ!? ከድፍን ኢትዮጵያ የሚሰበሰበው ግብር አልበቃ ብሎት ደሞዝ ይበላል?" ብዬ ሰማሁ።
እኚ ሴትዮ! እንደገና ተናገሩ! "ምንትሥ የሚባለውን የካድሬ ኢንኩቤተር የፈለሰመው እገሌ'ኮ ነው። ይጻፍልኝ! በማርከር ይሰመርበት! ጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ ይጠራልኝ! ..."
እኔም ሰማሁ ... "የምንትሥን መገበሪያ ሰርቆ የበላ ሳይጠየቅ ይለፈልፋል" ብዬ ሰማሁ። "እውነትም ቀዳሚ ... እውነትም ... " ብዬ ሰማሁ።
ገለባውን ማን በልቶት ይሆን?
አባ ጅፋር



