አባጅፋር

ፊት ላይ ያሉት ቀዳዶች የተበጁት ለመተንፍሰ፣ ለመብላት፣ ለመናገርና ለመናፈጥ ነው። እንዳስፈላጊነታቸው እንጠቀመባቸዋለን። በዚህም ምክንያት ሰውየው ተናገሩ።

 

 

"የሃገራችን ወጣቶች ሁለተኛ ደረጃን በከፍተኛ ውጤት ጨርሰው ... አሪፍ አሪፎቹ ብቻ ዩኒቨርሲቲ ይገባሉ። ዩኒቨርሲቲ ውስጥም ለበርካታ ዓመታት ታሽተው፤ የአሪፍ "ቅሺሞች" ተባርረው፤ የአሪፍ "አሪፎች" ብቻ በከፍተኛ ሁኔታ፤ በተራቀቀ ሥልት፤ ሥራ መሥራት እንዲችሉ፤ በዕውቀት ታንጸው ይመረቃሉ።" አሉ ሰውየው ከድሃው የኢትዮጵያ ህዝብ ከተሰበሰበ ግብር በሚያገኙት ደሞዝና ጥቅማጥቅሞች የገዙትን ክራቫት እያስተካከሉ።

 

ድሃው የኢትዮጵያ ህዝብም በየደቂቃው የሚወደደው ኑሮ ይቀየርልኛል ብሎ ይመኛል - እነዚህ ወጣቶች በሥራ ላይ ተሰማርተው በሚያመጡት ለውጥ ምክንያት። እነሱን ለማስተማር የገፈገፈው ግብርም ለውጥ ያመጣልኛል፤ የተሻለ ኑሮ ይመጣልኛል፤ ብሎ ያስባል።

 

ሰውየው ቀጠሉ። "እነዚህ በከፍተኛ ሁኔታ የሠለጠኑ ምሩቃን ካዛሬ ጀምሮ ድንጋይ ቆርጠው፣ ፈልጠው፣ ጠርበው ... ድንጋይ ያነጥፋሉ። ህዝባችንም ጭቃ ሳይነካው የሚረማመድበት ጎዳና ያገኛል።" አሉ።

 

ይህንን ሰማሁና ደሳለኝ ደበረኝ።

 

የኢትዮጵያ ገበሬም "ኧረ እኔ በዚያ ሰፈር መቼ አልፍና?! ያ ሰፈር'ኮ ያንተ መኖሪያ ነው።" ሲል አማረረና ... "የባሰ አታምጣ!" ብሎ ጸሎት ጀመረ።

 

ይህንን አየሁና ደግሞ አዘንኩ። የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ ነፃነትና ብልጽግናን በጸሎት አታገኝም። እግዚአብሔር በነፃ እንድትኖርና እንድትበለጽግ ፈቅዶልሃል። ነፃነትና ብልጽግናን ግን ባቋራጭ መንገድ፤ በጸሎት፤ እንድታገኝ የፈቀደ አይመስለኝም። እባክህ ከጸሎት ባሻገር እንዴት እንደምታገኛቸው አስብበት!

 

ሰየው መቼም ይናገራሉ። እና ከዕለታት አንድ ቀን ደግሞ ይህንን አሉ።

 

"ይሄንን ያሁኑን ጉባዔ እጅግ የተለየና የደመቀ የሚያደርገው ነገር ... ከድንቅም ድንቅ ... ከግሩምም ግሩም የሚያደርገው ነገር ቢኖር "እገሌ" ለኛ ሲል መሰዋቱ ነው። አዎን "እገሌ" ተሰውቶ የዘንድሮ ጉባዔውን በጣም የተለየና ግሩም ድንቅ አድርጎታል።" አሉ።

 

ህምምምም ... ይህንን ሰማሁና ደግሞ ደሳለኝ ...

 

የሚቀጥለውን ጉባዔ ደግሞ እጅግ በጣም፣ በጣም፣ በጣም፣ የደመቀ ለማድረግ ሥንት "እገሌ" ቢሰዋ ይሻላል ታዲያ?!


አባጅፋር

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ